ምዕራፍ 32 · 8 ደቂቃ ንባብ · 10 ደቂቃ ማዳመጥ
የማይናወጡት ነገሮች
«ዳሩ ግን። አንድ ጊዜ ደግሜ የሚል ቃል፥ የማይናወጡት ጸንተው እንዲኖሩ፥ የሚናወጡት የተፈጠሩ እንደሚሆኑ ይለወጡ ዘንድ ያሳያል።» (ዕብራውያን 12:27)።
በእነዚህ ቃላት ውስጥ እንዴት ያለ ግርማ አለ! የመለኮትን ማኅተም አሻራ ይዘዋል። ማንም ሰው እነዚህን ቃላት ሊናገር አይደፍርም፤ ለታላቁ ተናጋሪ ግን የተገቡ ናቸው። በሐጌ መጽሐፍ ውስጥ እንደምናገኛቸው፣ የመጀመሪያው ዐውዳቸው ደግሞ ከዚህ ይልቅ እጅግ ድንቅ ነው፦ «የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ገና አንድ ጊዜ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰማያትንና ምድርን ባሕሩንና የብሱን አናውጣለሁ፤ አሕዛብንም ሁሉ አናውጣለሁ፥ የአሕዛብም ሁሉ ምኞት ይመጣል።»
እነዚህ ቃላት በመጀመሪያ የተነገሩት ከባቢሎን ወደ ፈረሰው ቤተ መቅደሳቸውና ከተማቸው የተመለሱትን አይሁድ ምርኮኞች ለማበረታታት ነበር። ሽማግሌዎቹ የቀደሙትን ዘመናት ያለፈ ክብር ባሰቡ ጊዜ አለቀሱ፤ እግዚአብሔርም የተዋረዱትን ማጽናናት ደስ እንደሚያሰኘው አጽናናቸው። በአሳብ ደረጃ እንዲህ አላቸው፦ «ተጽናኑ፤ ቍሳዊ ሕንጻዎችን ሁሉ የሚፈትንና የሚገለብጥ ወሳኝ ጊዜ እየመጣ ነው፤ በዚያም መናወጥ ውስጥ ውጫዊው መልክ ምንም ያህል ያማረና ውድ ቢሆን ያልፋል፤ ውስጣዊውና የተሰወረው ክብር ግን ከቀድሞው ሁሉ ይበልጥ ይገለጣል፤ እንዲያውም በመፍረስና በለውጥ ድምፆች ሁሉ መካከል የአሕዛብ ሁሉ ምኞት ይመጣል፤ እነዚህ ቍሳዊ ነገሮች የሚደበዝዝና ያልተሟላ ቅድመ ጥላ ብቻ የሆኑለት እውነተኛው አካል እርሱ ነው።»
እነዚህ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ይኖሩ የነበሩት በታላቅ መናወጥ መካከል ነበር። ዘመኑ ከሞላ ጎደል ሁሉን ያዳረሰ የፈተና ጊዜ ነበር። እግዚአብሔር ምድርን ብቻ ሳይሆን ሰማይንም ደግሞ ያናውጥ ነበር። አይሁድ በፍልስጤም ላይ የነበራቸው ይዞታ ምድሪቱን በጦር እንዳሸነፉአት የራሳቸው አድርገው በሚቈጥሩአት በሮማውያን እየተናወጠ ነበር። ረቢዎች ለእግዚአብሔር ቃል የሰጡት ትርጓሜ በኢየሱስ ቃላት፣ ሕይወትና ሞት በመጣው አዲስ ብርሃን እየተናወጠ ነበር። የቤተ መቅደሱና የሥርዓተ አምልኮው የበላይነት፣ እውነተኛው ቤተ መቅደስ የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን እንደ ሆነችና የሌዋውያን መሥዋዕቶች ሁሉ በክርስቶስ እንደ ተፈጸሙ ባስተማሩ ሰዎች እየተናወጠ ነበር። የሰንበት አከባበርም በእርሱ ፋንታ የሳምንቱን የመጀመሪያ ቀን ሊተኩ በፈለጉ ሰዎች እየተናወጠ ነበር።
የዚህ መናወጥ የመጀመሪያ ምልክቶች የታዩት ኢየሱስ ሕዝብ በተጨናነቀባቸው በፍልስጤም ከተሞች ማስተማርና መስበክ በጀመረና ሕዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ በጐረፈ ጊዜ ነበር። የአይሁድ መሪዎች ሐዋርያትን ዝም ለማሰኘትና የቤተ ክርስቲያንን ወደ ፊት መገስገስ ለማስቆም በፈለጉ ጊዜ ተከታትለው የመጡት የምጥ መናወጦች ይበልጥ ግልጽ ሆኑ። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍና መልእክቶቹ የዚያን አብዮት ብርታት በሚያሳዩ ማስረጃዎች የተሞሉ ናቸው፤ ያ አብዮት እግዚአብሔርን የሚፈሩ ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔር ታቦት እንዲንቀጠቀጡ ሳያደርግ አልቀረም። የሁሉም ጫፍ የመጣው በአስፈሪው የኢየሩሳሌም ከበባ ነበር፤ ያን ጊዜ የአይሁድ ሥርዓት አንድ ጊዜ ለዘለቄታው ተሰባበረ፤ ቤተ መቅደሱ ተቃጠለ፤ የቀሩት የመቅደሱ ዕቃዎች በቲቤር ወንዝ ውስጥ ሰመጡ፤ አይሁድም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻቸውን ለመፈጸም ፈጽሞ አስፈላጊ ከነበረችው ከተማ ተባረሩ። አዲስ ኪዳን በሙሉ እስከ ዛሬ ከተፈጸሙት እጅግ ኃያላን መንፈሳዊ አብዮቶች የአንዱን ምጥ ይመሰክራል፤ ያም አብዮት የፈረንሳይ አብዮት በምድራዊው ዘርፍ ታላቅ እንደ ነበረ በመንፈሳዊው ዘርፍ ታላቅ ነበር።
ይህ መልእክት የተጻፈው በእነዚህ እሳቶች መካከል ነበር። በመንፈስ የተነሣሣው ጸሐፊ «አይዟችሁ» ይላል፤ «እነዚህ መናወጦች የሚመጡት ከእግዚአብሔር እጅ ነው።» የራሱን ቃል ስማ፦ አናውጣለሁ። ለዘላለምም አይቀጥሉም፤ ይህ አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ ዘላለማዊ ዋጋና እውነት ያለውንም ማንኛውንም ነገር አይጎዱም። ቍሳዊው፣ በስሜት ሕዋሳት የሚዳሰሰውና ጊዜያዊው እንዲያልፍ፣ መሠረታዊውና ዘላለማዊው ግን ከቀድሞው በላቀ ውበት ጎልቶ እንዲቆም እርሱ ሁሉን ያናውጣል። ነገር ግን ከንጹሑ ብረት አንዲት ቅንጣት እንኳ በእሳቱ ውስጥ አትጠፋም፤ ከሰማይ ግንብ አንዲት ቍራጭ እንኳ በድንጋጤው አትፈርስም።
እኛም አሁን የምንኖረው በእንዲህ ያለ ዘመን ውስጥ ነው። ሁሉ ነገር እየተናወጠና እየተፈተነ ነው። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ መለኮታዊ ዓላማ አለ፤ ይኸውም የሰው ወጎችና በእውነቱ ላይ የተከመሩ ተጨማሪዎች ሁሉ የድንጋጤውን ኃይል መቋቋም አቅቷቸው ሲወድቁ፣ ዘላለማዊ እውነቱ ይበልጥ ግልጽና የማያሻማ ሆኖ ጎልቶ እንዲታይ ነው። ታዲያ ስለዚህ አብዝቶ በምሬት የሚያለቅስ ማን ነው? አዲሱ የፀደይ ልምላሜ ራሱን መግለጥ ከቻለ፣ ነፋሳት የዛፎቹን አሮጌና የደረቁ ቅጠሎች ስለሚያረግፉ የሚያለቅስ ማን ነው? ፍጹሙ ምስል በሙሉ ተመጣጣኝነቱ ጎልቶ መቆም ከቻለ፣ ከባዱ ምት ቅርጽ ማውጫውን ስለሚሰባብረው የሚያዝን ማን ነው? ሰማይና ምድር ሲፈርሱ ከበታቻቸው ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በማይጠፋ ውበቷ የሚገልጡ ከሆነ፣ ስለ ማለፋቸው የሚተክዝ ማን ነው?
የሥነ መለኮት ሥርዓቶች እየተናወጡ ናቸው። ሰዎች የሥነ መለኮት እምነታቸውን ከመምህሮቻቸው፣ ከወላጆቻቸው ወይም ከቤተ ክርስቲያናቸው አንዲት ጥያቄ ወይም ክርክር ሳያነሡ ይቀበሉ የነበረበት ዘመን ነበር። ክንፉን ያራገበ ወይም አፉን የከፈተ ወይም የጮኸ አልነበረም። አሁን ግን እንዲህ አይደለም፤ አየሩ በጥያቄዎች ተሞልቷል። ሰዎች አባቶቻችን ይወዱት የነበረውን ትምህርት ሁሉ ወደ ማቅለጫው ገል እያስገቡ ናቸው። በዘመናት ለተከበሩ የእምነት መግለጫዎች፣ ለሥነ መለኮት ልዩነቶች ወይም ለትምህርተ ሃይማኖት ቀመሮች ምንም አክብሮት አይታይም። እንደ ማስተስረያ ምንነት፣ እንደ ዳግም ልደት አስፈላጊነት፣ እንደ ወደፊቱ ቅጣት ዘመን ርዝመት ያሉት እጅግ ከፍ ያሉ ርእሰ ጉዳዮች በሕዝብ ጋዜጦች ላይ እየተተቹ ናቸው።
ብዙ የእግዚአብሔር ልጆች በዚህ እጅግ ተጨንቀዋል፤ ስለ ወንጌል እውነትም ይፈራሉ። በዚህ ትግል ውስጥ ከሟች ሰዎች በቀር ሌሎች ተሳታፊዎች እንደሌሉ አድርገው ይናገራሉ። በትግሉ ውስጥ ያሉትን ዘላለማዊ ጉዳዮችና በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉትን የማይታዩ ኃይሎች ይዘነጋሉ። እግዚአብሔር ክቡር ወንጌሉ እንዲጋረድ ወይም መሠረታዊ ክፍሎቹን ሁሉ እንዲነጠቅ ይፈቅዳልን? ይህን ሁሉ ዘመን ወንጌሉን ሳይጓደል ጠብቆት ከኖረ በኋላ አሁን ድንገት ማዳን እንደማይችል ኃያል ሆኗልን? በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን የወንጌል ትምህርት በጥቂት ያልታወቁና ትሑታን ቅዱሳን መካከል ብቻ ስለ ቀረ ከዓለም የጠፋ በመሰለ ጊዜ፣ እርሱ አንድ ሰው አስነሣ፤ ያም ሰው የስሕተትን ማዕበል ወደ ኋላ መለሰ፤ የወንጌልን እውነት ዓርማ እንደ ገና ከፍ አድርጎ አቆመ፤ ታዲያ ይህንኑ እንደ ገና ሊያደርግ አይችልምን?
በእነዚህ አስፈሪ መናወጦች ውስጥ ከእግዚአብሔር ቃል አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ አትጠፋም፤ ከእውነት አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም፤ ከምሽጉም አንድ ድንጋይ ከስፍራው አይነቀልም። ነገር ግን እንዲመጡ የተፈቀደላቸው በከፊል እንደ መንሽ ገለባውንና ስንዴውን ለመፈተን ነው፤ በዋነኛነት ግን ጊዜያዊውና አላፊው ሁሉ እንዲያልፍ፣ ቀላሉ የእግዚአብሔር እውነት ደግሞ ይበልጥ እንዲገለጥና ግንበኞቹ ተመጣጣኝነቱንና ውበቱን በሸፈኑበት የግንባታ ርብራብና ፍርስራሽ ሳይሰወር እንዲያበራ ነው። «የማይናወጡት ጸንተው ይኖራሉ።»
የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች እየተናወጡ ናቸው። አንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት መኖሩ ብቻ በቂ አይደለም፤ መኖሩን ለምን መቀጠል እንዳለበት ምክንያቱን እንዲያሳይ በመጠኑ በድፍረት ይጠየቃል። የዘመኑ መንፈስ ጥቅምን ብቻ የሚመለከት ነው፤ ለአስቸኳይ ፍላጎቶቹ ስለ ተሰጠ አገልግሎት ግልጽ ማስረጃ ላይ ያልተመሠረተን የምሕረት ልመና ሁሉ ለማጤን አይፈቅድም።
የዚህ ምልክቶች እጅግ ግልጽ ናቸው። አሁን የሚቀርበው ሐሳብ ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት እንድትለይ ነው፤ ይህም ሐሳብ ከመንግሥት ጋር ያላት ትስስር ክርስትናን በመካከላችን ለማቆየት አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑትን በድንጋጤ ይሞላቸዋል። የሃይማኖት መምህራን ሹመታቸውን የያዙበትን ወይም ልዩ መብቶችን የሚጠይቁበትን ምክንያት እንዲያሳዩ ይገዳደራሉ። የሥራ ዘዴዎች በሚዛን እየተመዘኑ ናቸው፤ የሚስዮን ዕቅዶች በጥብቅ ይተቻሉ፤ የአምልኮ ሥርዓቶች መልካቸው ይለወጣል። ለውጥ እጅግ በዘመናት የተከበሩትን ልማዶች ያሰጋል፤ ይህ ሁሉ ደግሞ ዋናውን ነገር ከውጫዊው መልክ፣ ዕንቍውን ከሣጥኑ፣ መንፈሱን ከሚያድርበት መቅደስ ጋር ላደባለቁ ሰዎች እጅግ የሚያስጨንቅ ነው። ነገር ግን አንፍራ። ይህ ሁሉ እየተፈቀደ ያለው እጅግ ጥበብ ለሞላባቸው ዓላማዎች ነው። በሕንጻዎቻችን ሁሉ ውስጥ መቃጠል የሚያስፈልገው ብዙ እንጨት፣ ሣርና አገዳ አለ፤ ነገር ግን ከወርቅ ወይም ከብር አንዲት ቅንጣት እንኳ ከቶ አትጠፋም። ማዕበሎቹ በወደቡ ግንብ ላይ የተጣበቀውን የባሕር አረም ሊያጥቡት ይችላሉ፤ ነገር ግን ግንቡን ከሠሩት ድንጋዮች አንዱን እንኳ ከስፍራው ማናጋት አይችሉም። የጥንቲቱ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ቀላልነት የቤተ ክርስቲያንን እድገት በሚያደናቅፉና ሥራዋን በሚያሰናክሉ ብዙ ተጨማሪ ክምችቶች መሸፈኑ አያጠራጥርም፤ ምንም ያህል ብርቱ ቢሆን ነጻ የሚያወጣትን ማንኛውንም መለኮታዊ ጕብኝት በደስታ ልንቀበለው እንችላለን። ቤተ ክርስቲያን ራሷ ግን በዓለት ላይ ተመሥርታለች፤ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።
የስደት ዘመናት በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በጸኑባት ጊዜ መልካም ሆኖላት ነበር። እንደዚያን ጊዜ ንጹሕና በመንፈስ ብርቱ ሆና አታውቅም። እንደዚህ ያሉ ዘመናት እንደ ገና እንዲመለሱ ቢፈቀድና እግዚአብሔር ሕንጻዋን በብርቱ የሰማዕትነት ዐውሎ ነፋሳት ቢያናውጥ፣ ምንም መጨነቅ አያስፈልግም ነበር። ለጊዜው የሚያጎበድዱት፣ በአፍ ብቻ የሚያምኑትና የወቅቱን ልማድ ብቻ የሚከተሉት ይገለጡ ነበር፤ በነፍሳቸው የእግዚአብሔርን ሥራ የተለማመዱት ግን እስከ መጨረሻ ይጸኑ ነበር፤ እውነተኛ ማንነታቸውም ይገለጥ ነበር። «የማይናወጡት ጸንተው ይኖራሉ።»
ጠባያችንና ሕይወታችን ዘወትር እየተናወጡ ናቸው። በፍቅር የተመካንበት ጽድቃችን ሁሉ የደረቁ ቅጠሎች ብቻ እንደ ሆነ ያሳየን ያ ስብከት እንዴት ያለ መናወጥ ሰጠን! ልብን ይዘው የነበሩትን የዓመታት ቍጠባና የንግድ ተአማኒነት በአንድ ምት ጠራርጎ የወሰደውና መንፈሳዊ ዋጋ ያለውን ብቻ የተወልን ያ የንግድ ኪሳራ እንዴት ያለ መናወጥ ነበር! ኃጢአት የለሽ ነን ብለን የገመትነው ከንቱ ሕልም እንደ ሆነ፣ እኛም እንመካባቸው እንደ ነበሩት ሰዎች ለፈተና ተጋላጮች እንደ ሆንን ያሳየን ያ ፈተና እንዴት ያለ መናወጥ ነበር።
የእነዚህ ሁሉ መናወጦች የመጨረሻ ውጤት ምን ሆነ? ከራሳችን አንዲት ጠጉር ስንኳ ጠፍታለችን? አሮጌው ሰዋችን ጠፍቷል፤ የውስጡ ሰውነታችን ግን ዕለት ዕለት ታድሷል። እብነ በረዱ ይበልጥ በተቀረፈ ቍጥር ሐውልቱ ይበልጥ አድጓል። የእንጨት ደጋፊዎቹ ሲፈርሱ ጠንካራው የድንጋይ ግንብ በበለጠ ምሉዕነት ጎልቶ ቆሟል። «የማይናወጡት ጸንተው ኖረዋል።»
«ታላቅ የእግዚአብሔር መንፈስ ሆይ፣ ቀጥል፤ ከአንተ ያልሆነው፣ ይልቁንም ከእኛ የሆነውና ስለዚህም ሐሰተኛና ራስ ወዳድ የሆነው ሁሉ ተገልጦ እንዲገለበጥ፣ እኛም እውነተኛ ሀብታችንን እንድናውቅ፣ እነዚህን ጠባዮቻችንን በምድር መናወጦችህ ከዚህ ይልቅ አብዝተህ አናውጣቸው። ከአጠቃላዩ ጥፋት ተርፈው ለእኛ ሲጠበቁም ስናይ፣ በአንተ ራስህ የተሰጡን ስለ ሆኑ ከራስህ ጽናትና ዘላለማዊነት ተካፋዮች መሆን እንዳለባቸው እናውቃለን። ያንተን መልካሙን ማክበር እንድንማር የራሳችንን ክፉውን እንወቅ።» ቢበዛ እነዚህ መናወጦች ጊዜያዊ ናቸው። የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፣ «ይህ አንድ ጊዜ ብቻ ነው!» ከዚያ በኋላ ከቶ አይደገምም!
ፈጽሞ ሊናወጡ የማይችሉ ጥቂት ነገሮች አሉ። የእግዚአብሔር ቃል። ሰማይና ምድር ያልፉ ይሆናል፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን — ከቶ አያልፍም! ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ የሰው ክብር ሁሉ — አሳቡ፣ ይገባኛል የሚለው፣ ታይታውና ትዕቢቱ — እንደ ሣር አበባ ያማረ ግን ቶሎ የሚረግፍ ነው፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል፤ በወንጌልም የሚሰበከው ቃል ይህ ነው። ዘመናዊውን ትችት አንፍራ፤ ከእግዚአብሔር እውነት አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ሊነጥቀን አይችልም። ሐዋርያው በእጁ ላይ የተጣበቀችውን እፉኝት አራግፎ አንዳች እንዳልጐዳው፣ መጽሐፍ ቅዱስም ያንን ትችት ያራግፈዋል።
የእግዚአብሔር ፍቅር። የወዳጆቻችን ፍቅር በአንድ ወሬ፣ በአንድ አፍታ ቸልታ ወይም በኑሮአችን ሁኔታ መለወጥ ሊናወጥ ይችላል፤ የእግዚአብሔር ፍቅር ግን እንደ ራሱ የማይለወጥ ነው። የፍቅሩን ከፍተኛ ሰማይ ለመንካት ያህል ከፍ ብሎ የሚደርስ ዐውሎ ነፋስ የለም። በእኛ ውስጥ ስላለ አንዳች ነገር ብሎ ሊወደን አልጀመረም፤ እኛ ምን እንደ ሆንን ስላወቀም መውደዱን አያቆምም። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለው የእግዚአብሔር ፍቅር በለውጥም ሆነ በድንጋጤ ሊደፈር አይችልም።
የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት። «… የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል …» በአብዮቶቻችንና በፖለቲካ ለውጦቻችን ሁሉ መካከል ያ መንግሥት እየመጣ ነው። አካልንና ቅርጽን ኃይልንም እየያዘ ነው። አሁን በምሥጢር ውስጥ ነው፤ ነገር ግን በቅርቡ ይገለጣል። በሰው ስሜት ድንገተኛ ጥቃት ወይም ዓመፅም ሊነካ አይችልም። «የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል።»
ሊወሰድ የማይችለውንና የማይጠፋውን ሀብታችንን እንቍጠር፤ በዙሪያችን የጨለማ ፍርሃት ወይም የቀትር ቸነፈር ቢኖርም በፍጹም ሰላም እንጠበቃለን፤ ይህም አንድ ትንሽ ገዥ ቤተ መንግሥቱን ለመዝረፍ የተነሣውን ሁከተኛ ሕዝብ በእርጋታ እንደሚመለከት ነው፤ ምክንያቱም ሀብቱን ሁሉ በእንግሊዝ ባንክ ጠንካራ ምድር ቤቶች ውስጥ እንዲጠበቅ ከብዙ ጊዜ በፊት ልኮታልና።
ይህ የለውጥና የምድር መናወጥ ዓለም ዕረፍታችንም ቤታችንም አይደለም። እነዚህ እግዚአብሔር በሚኖርበት ስፍራ፣ መሠረት ባላት ከተማ፣ ዐውሎ ነፋስ በማይነሣበትና የብርጭቆው ባሕር በእግዚአብሔር ዙፋን ግርጌ በሰላም በተዘረጋበት አገር ይጠብቁናል። ስለዚህ ራሳችንን ለጽናትና ለትዕግሥት፣ ለአክብሮትና እግዚአብሔርን ለመፍራት ብናበረታ ይገባናል፤ በውስጣችንም በዚያም ስፍራ ከእግዚአብሔር ባሕርይ የሚካፈል፣ ሌባው ጊዜ ሊሰርቀው፣ ብልም ሊያጠፋው፣ ለውጥም ሊነካው የማይችል ነገር አለንና።
እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አገልግሎት ልናቀርብ የምንችለው ከእንዲህ ያለ መንፈስ ተነሥተን ነው። ብዙ ጊዜ ለቅዱሱና አፍቃሪው ዓይኑ እጅግ በጣም የሚያስጠላ መሆን ያለበት ራስን ከፍ ማድረግ፣ ከንቱ ውዳሴን መሻትና የሥጋ ብርታት ይታያል። ያም በዙሪያችን ካለው ዓለም ሁከትና መቅበጥበጥ እጅግ ይካፈላል። ነገር ግን አንድ ጊዜ የዘላለማዊውንና ወሰን የሌለውን መንፈስ ስንተነፍስ፣ እጃችን ይበልጥ ይረጋጋል፤ ልባችንም ይበልጥ ጸጥ ይላል፤ ጸጋውንም መቀበል እንማራለን። ስለ እርሱ በጭንቀት አንታገልም፤ የእኛ እንደ ሆነ ይዘን እንጠቀምበታለን፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቃትም እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን እናመልካለን።
ምዕራፍ 32 ተጠናቋል
የማይናወጡት ነገሮች