ምዕራፍ 14 · 14 ደቂቃ ንባብ · 18 ደቂቃ ማዳመጥ
የመከር ደስታ
«በመከር ጊዜ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል» — ኢሳይያስ 9:3 በቅርቡ «የመከር መግቢያ!» እያሉ እልል ከሚሉ ሰዎች ጋር በዓሉን አከበርሁ። ሀብታሙና ድሀው በአንድነት ሲደሰቱ በማየቴ ደስ አለኝ፤ አስደሳቹ ማዕድ ካበቃም በኋላ ከጠረጴዛዎቹ አንዱን የስብከት መድረክ አድርጌ፣ በዚያ ሰፊ ጎተራ ውስጥ ለትጉህ ጉባኤ ለዘላለም የተባረከውን የእግዚአብሔርን ወንጌል በመስበኬ ደስ አለኝ። ልቤ ከበዓሉ ጋር ተስማምቶ ሐሤት አደረገ፤ አሁንም በዚያው ዜማ እቀጥልና ስለ መከር ደስታ ጥቂት እነግራችኋለሁ። የለንደን ሰዎች የመከር ጊዜ መሆኑን ይረሳሉ፤ በዚህ ታላቅ የጠቈረ ጡብ ምድረ በዳ ውስጥ ስለምንኖር፣ በእህል ነጋዴ ሱቅ መስኮት ላይ ደርቆና ነጥቶ ከምናየው በቀር የስንዴ ዛላ ምን እንደሚመስል አናውቅም ማለት ይቻላል፤ ቢሆንም በእግዚአብሔር ቸርነት የምድር ፍሬ የሚሰበሰብበት የመከር ወቅት እንዳለ ሁላችንም እናስታውስ።
የቅዱሳን በእግዚአብሔር ፊት ያላቸው ደስታ የሚመሰልበት ይህ የመከር ደስታ ምንድር ነው? ራሳቸውን ብቻ ለሚወዱ መንፈሶች የመከር ደስታ ሀብት በመጨመሩ የሚገኝ የግል እርካታ ብቻ ይመስለኛል። አንዳንድ ጊዜ ገበሬው ደስ የሚለው የድካሙን ዋጋ በማየቱና በዚያው መጠን ሀብታም በመሆኑ ብቻ ነው። በብዙዎች ዘንድ ግን ሁለተኛው የደስታ ምክንያት እንደሚቀላቀል ተስፋ አደርጋለሁ፤ ይኸውም የተትረፈረፈ መከር ለድሆች እንጀራ እንደሚሰጥና ከመንገዶቻችንም ማጕረምረምን እንደሚያስወግድ በማወቅ እግዚአብሔርን ማመስገን ነው። መከሩ ባለ ጠጋ ላደረገው ሰው በመከር ደስ መሰኘቱ ተገቢ ደስታ እንደ ሆነ አያጠራጥርም፤ ተግቶ የሚሠራ ሰው ሁሉ በመጨረሻ የተመኘውን ሲያገኝ ደስ ሊለው መብት አለውና።
ሰዎች የመጨረሻውና ከሁሉ የሚበልጠው መከራቸው እንደ ድካማቸው እንደሚሆንላቸው ሁልጊዜ ቢያስታውሱ መልካም ነበር። በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።
አንድ ወጣት ሕይወቱን የሚጀምረው የዱር አጃ የሚለውን በመዝራት ነው፤ ይህን ባይዘራው ይሻለው ነበር፤ አስፈሪ መከር ያመጣበታልና። ከዚህ የዱር አጃ የእውነተኛ ተድላ መከር እንደሚሰበስብ ይጠብቃል፤ ይህ ግን ሊሆን አይችልም፤ የሕይወት እውነተኛ ተድላዎች የሚበቅሉት ከጽድቅ መልካም ዘር ነው እንጂ ከኃጢአት መርዛማ አረም አይደለም። በትልሙ ውስጥ አሜኬላን የሚዘራ ሰው ወርቃማውን የስንዴ ነዶ እንደማያጭድ ሁሉ፣ የክፋትን መንገድ የሚከተልም ደስታን ሊጠብቅ አይገባውም።
ይልቁንም ነፋስን ይዘራሉ፤ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ። ኃጢአተኛ የሕሊና ውጋት ሲሰማው «ይህ የዘራሁት ነው» ማለቱ ተገቢ ነው። በመጨረሻም ስለ ክፉ ሥራው ቅጣቱን በሚቀበልበት ጊዜ ከራሱ በቀር ማንንም አይወቅስም፤ እንክርዳድን ዘራ፤ እንክርዳድንም ማጨድ አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያን ሰው መዳኑ ከጸጋ እንጂ ከሥራ ባይሆንም ከጌታው ዘንድ የጸጋ ብድራት ይሰጠዋል። ዘሩን ተሸክሞ እያለቀሰ የሚሄድ፣ ነዶውን ተሸክሞ እልል እያለ ይመለሳል። የመከር ደስታ በከፊል የድካም ብድራት ነው፤ ጌታን በማገልገላችን ያገኘነው ደስታም እንዲሁ ይሁን።
የመከር ደስታ ሌላም ክፍል አለው፤ ይኸውም ስለ ተደረገልን ውለታ እግዚአብሔርን ማመስገን ነው።
እኛ ከብዙዎቻችን ግምት እጅግ በሚበልጥ መጠን በሚያስደንቅ ሁኔታ በእግዚአብሔር ላይ የተደገፍን ነን። የእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ በነበሩ ጊዜ በየማለዳው እየወጡ መናውን ይለቅሙ ነበር። የእኛ መና በየማለዳው አይመጣልንም፤ በዓመት አንድ ጊዜ ግን ይመጣል። በሰፈሩ ዙሪያ እንደ አመዳይ ተዘርግቶ እንደ ነበረው ሁሉ ይህም ከሰማይ የሚመጣ ስንቅ ነው። ወደ ሜዳ ወጥተን ከደመና የወረደ ምግብ ብንለቅም ታላቅ ተአምር ነው ብለን እናስብ ነበር፤ እንጀራችን ከሰማይ ቢወርድ እንደሚያስደንቀው ሁሉ ከመሬት ወጥቶ መብቀሉስ እንዲያው ታላቅ ድንቅ አይደለምን? ሰማያት የመላእክትን መብል እንዲያዘንቡ ያዘዘ ያው አምላክ ደንቆሮዋ ምድር በጊዜዋ ለሰው ልጆች እህልን እንድታበቅል ያዝዛታል። ስለዚህ መከር በመጣ ቍጥር እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ወቅቱም ያለ ምስጋና መዝሙር እንዲያልፍ አንፍቀድ። በዓለም ላይ በአብዛኛው ከአሥራ ስድስት ወር ስንቅ በላይ ፈጽሞ የለም ብል ትክክል እንደምሆን አምናለሁ፤ ማለትም መከሩ ሲሰበሰብ የአሥራ ስድስት ወር ስንቅ ሊኖር ይችላል፤ በመከር ጊዜ ግን በመላው ዓለም ያለው ስንዴ በአብዛኛው ሕዝቡን ከአራት ወይም ከአምስት ወር በላይ ለማቆየት አይበቃም፤ ስለዚህ መከሩ ባይመጣ በራብ አፋፍ ላይ በሆንን ነበር። ዛሬም ከእጅ ወደ አፍ እንኖራለን። እንግዲህ ቆም ብለን እግዚአብሔርን እንባርክ፤ የመከር ደስታም የምስጋና ደስታ ይሁን።
ለክርስቲያን በመከር አማካይነት የእግዚአብሔርን ታማኝነት ማረጋገጫ መቀበል ታላቅ ደስታ ሊሆንለት ይገባል። ጌታ ምድር በምትኖርበት ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፣ ብርድና ሙቀት፣ በጋና ክረምት እንደማያቋርጡ ቃል ገብቶአል። ሰብል የጫነውም ሠረገላ እህሉን ወደ ቤት ሲያስገባ ስታይ ለራስህ እንዲህ ልትል ትችላለህ፦ «እግዚአብሔር ለተስፋ ቃሉ የታመነ ነው።
የሚያስጨንቅ ክረምትና እርጥብ ጸደይ ቢያልፍም፣ መጸው ወርቃማ እህሉን ይዞ መጥቶአል።» ጌታ ይህን የተስፋ ቃል እንደሚጠብቅ የቀሩትንም ሁሉ እንደሚጠብቅ እርግጠኛ ሁን። የተስፋ ቃሎቹ ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ አዎንና አሜን ናቸው፤ ለምድር የገባውን ቃል ኪዳን የሚጠብቅ ከሆነ፣ በዘላለም ፍቅር ከወደዳቸው ከገዛ ሕዝቡ ጋር የገባውን ቃል ኪዳንማ እንዴት አብልጦ አይጠብቅ! ክርስቲያን ሆይ፣ የተስፋውን ቃል በከንፈርህ ይዘህ ወደ ምሕረት ዙፋን ሂድና ተማጠንበት። የሞተ ፊደል አለመሆኑን እርግጠኛ ሁን። የተስፋውን ቃል በዙፋኑ ፊት ስታነሣ አለማመን እንድትንተባተብ አያድርግህ፤ ይልቁንም በድፍረት እንዲህ በል፦ «ተስፋ ያስደረግኸኝን ቃልህን ለባሪያህ ፈጽም።» አምላካችንን ይህን ያህል ጥቂት ማመናችን ያሳፍረናል። ዓለም በቸርነቱ ማስረጃዎች ተሞልታለች። የሚወጣው ፀሐይ ሁሉ፣ የሚወርደው ዝናብ ሁሉ፣ የሚፈራረቀው ወቅት ሁሉ ታማኝነቱን ያረጋግጣል። ታዲያ ለምን እንጠራጠረዋለን? ምክንያት እስኪኖረን ድረስ ካልተጠራጠርነው ዳግመኛ አለመታመንን ፈጽሞ አናውቅም። በመከሩ መመለስ ተበረታተን፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ብርታት እንዳንወላውል፣ ይልቁንም በመለኮታዊው ቃል እንድናምንና በእርሱ ደስ እንዲለን እንወስን።
ደግሞም፦ ለክርስቲያን በመከር ደስታ ውስጥ ሁልጊዜ የተስፋ ጥበቃ ደስታ ይኖራል። ገበሬው እየታገሠ የሚጠብቀው መከር እንዳለው ሁሉ፣ የጌታችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣትና መገለጥ ለሚጠባበቁ ታማኝ ጠባቂዎች ሁሉ መከር አለ። የበሰለ ክርስቲያን እንደ በሰለ የእህል ዛላ በቅዱስ ትሕትና ራሱን ያጎነብሳል።
በእግዚአብሔር ነገር ገና ለጋ በነበረ ጊዜ ቀጥ ብሎ ቆሞ ነበር፤ በመጠኑም ይመካ ነበር፤ አሁን ግን በጌታ በረከት ስለ ተሞላ በዚያው ተዋርዶአል፤ ራሱንም ያጎነብሳል፤ ማጭዱን ይጠብቃል፤ አይፈራውምም፤ የክርስቶስን ሕዝብ ሊሰበስብ የሚመጣ ተራ አጫጅ አይደለምና — የዓለምን መከር የሚያጭደው ራሱ ነው።
ጌታ የወይኑን ፍሬ እንዲያጭድና በበቀል እንዲረገጥ ወደ መጥመቂያው እንዲጥለው አጥፊውን መልአክ ይተዋል፤ እርሱ ራሱ የዘራውን እህል ግን በገዛ ወርቃማ ማጭዱ ራሱ ይሰበስበዋል። ይህን ነው የምንጠባበቀው። በእንክርዳድ መካከል እያደግን ነው፤ አንዳንድ ጊዜም እንክርዳዱ ከእኛ በርትቶ ስንዴውን እንዳያንቀው በግማሽ እንፈራለን፤ ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንለያለን፤ እህሉም በሚገባ ተበጥሮ በጎተራ በተከተተ ጊዜ እኛም በዚያ እንገኛለን። አሁን እንኳ ልባችንን በደስታ የሚያስፈነድቀው ይህ ተስፋ ነው። የጌታችን የሆኑትን ውድ ነዶዎች ይዘን ወደ መቃብር ሄደናል፤ በዚያም ሳለን «ጌታ ሆይ፥ ተኝተውስ እንደ ሆነ ይድናሉ። ከእነርሱ ጋር እንሙት» ልንል የቀረን ጥቂት እንደ ሆነ አሰብን። የመከር ደስታችን ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ዕረፍት የማግኘትና ሁልጊዜ ከጌታ ጋር የመሆን ተስፋ ነው።
በምድር ላይ ያሉትን እነዚህን የጥላ መከሮች ማየት እጅግ ደስ ሊያሰኘን ይገባል፤ በላይ ያለው የዘላለም መከር ምስልና አስቀድሞ ጥላ ናቸውና።
ስለ መከር ደስታ ይህ ይበቃል፤ ነገር ግን ወደ ፊት እቸኩላለሁ። ለአማኝ እንደ መከር ደስታ የሆኑለት ደስታዎች የትኞቹ ናቸው? ክርስቲያኖች ደስታ የሌላቸው ሕዝብ ናቸው የሚል የተለመደ አስተሳሰብ አለ። እንደምንፈተን እውነት ነው፤ ጐስቋሎች ነን ማለት ግን ሐሰት ነው። አማኞች በመከራቸው ሁሉ በክርስቶስ ፍቅር እንዲህ ያለ ካሣ ስላላቸው አሁንም የተባረከ ትውልድ ናቸው፤ ስለ እነርሱም «እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ» ሊባል ይችላል።
ከመከር ደስታ ጋር የሚተካከል ደስታ ካወቅንባቸው የመጀመሪያዎቹ ወቅቶች አንዱ — ከጀመረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ከእኛ ጋር የቀጠለ ወቅት — አዳኙን አግኝተን መዳንን የተቀበልንበት ጊዜ ነበር። ወንድሞችና እኅቶች ሆይ፣ ነፍሳችሁ የታረሰችበትን ጊዜ እናንተው ታስታውሳላችሁ። ልቤ ያልታረሰ ጦም አዳሪ መሬት ነበር፤ በአረምም ተሸፍኖ ነበር፤ በአንድ ቀን ግን ታላቁ ገበሬ መጥቶ ነፍሴን ማረስ ጀመረ። አሥር ጥቁር ፈረሶች ጥምዶቹ ነበሩ፤ የተጠቀመበትም ማረሻ ስለታም ነበር፤ አራሾቹም ጥልቅ ትልም አወጡ። እነዚያ ጥቁር ፈረሶች አሥሩ ትእዛዛት ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ፍትሕ እንደ ማረሻ መንፈሴን ቀደደው። ተፈርዶብኝ፣ ፈርሼ፣ ተደምስሼ፣ ጠፍቼ፣ ረዳት አጥቼ፣ ተስፋ ቈርጬ ነበር — ሲኦል በፊቴ ያለ መሰለኝ። ከዚያም ደግሞ መስቀለኛ ማረስ መጣ፤ ወንጌልን ልሰማ በሄድሁ ጊዜ አላጽናናኝም፤ በእርሱ ዕድል ፈንታ እንዲኖረኝ እንድመኝ አደረገኝ እንጂ፣ እንዲህ ያለ ስጦታ የማይታሰብ እንደ ሆነ ፈራሁ።
የእግዚአብሔር እጅግ የተመረጡ የተስፋ ቃሎች ፊታቸውን አጨፈገጉብኝ፤ ማስፈራሪያዎቹም በላዬ አንጐደጐዱ። ጸለይሁ፤ ነገር ግን የሰላም መልስ አላገኘሁም። እንዲህ ሆኜ ብዙ ጊዜ ቈየሁ። ከማረሱ በኋላ መዝራቱ መጣ። ልብን ያረሰው እግዚአብሔር ወንጌል እንደሚያስፈልገው እንዲገነዘብ አደረገው፤ የወንጌልም ዘር በደስታ ተቀበለ። በመጨረሻ ጥቂት ተስፋ ማግኘት የጀመርህበትን ያን የተባረከ ቀን ታስታውሳለህን? በጣም ትንሽ ነበረች — ከአፈሩ ብቅ እንደምትል ለጋ ቡቃያ፤ ሣር ወይም እህል፣ ድፍረት ወይም እውነተኛ እምነት መሆንዋን ለይተህ አታውቅም ነበር። ትንሽ ተስፋ ነበረች፤ ነገር ግን እጅግ ደስ በሚያሰኝ ሁኔታ አደገች። ወዮ፣ የጥርጣሬ ውርጭ መጣ፤ የፍርሃት በረዶ ወረደ፤ የተስፋ መቍረጥ ቀዝቃዛ ነፋሳት ነፈሱብህ፤ አንተም «ለእኔ ምንም ተስፋ ሊኖር አይችልም» አልህ። ነገር ግን እግዚአብሔር የዘራው ስንዴ በመጨረሻ በስሎ «ወደ እርሱ ተመለከትሁ፥ ብርሃንም አገኘሁ፤ እግዚአብሔር ጥንት ኃጢአቶቼን ባኖረበት በኢየሱስ ላይ ኃጢአቶቼን አኖርሁ፤ ተወስደዋልም፤ እኔም ድኛለሁ» ማለት በቻልህበት ጊዜ ያ ቀን እንዴት ያለ የከበረ ቀን ነበር! ያን ቀን በሚገባ አስታውሰዋለሁ፤ ከእናንተም ብዙዎቻችሁ እንዲሁ እንደምታስታውሱት አያጠራጥርም። ወገኖቼ ሆይ! ውድ ክርስቶስ የእኛ በሆነ ጊዜ፣ በእርሱም ስላለው መዳን በሙሉ እርግጠኝነት ልንይዘው በቻልን ጊዜ ልባችን እልል እንዳለው ያህል እልል ያለ ገበሬ ከቶ የለም።
ከዚያ ወዲህ ብዙ ቀኖች አልፈዋል፤ የዚያ ደስታ ግን አሁንም በውስጣችን አዲስ ነው። እግዚአብሔርም ይባረክ፤ ወደ ኋላ የምንመለከተው የመጀመሪያውን ቀን ደስታ ብቻ አይደለም፤ ከዚያ ወዲህ ያለውን የየዕለቱን ደስታ ነው — አንዳንዴ ይበዛል፣ አንዳንዴ ያንሳል፤ ደስታችንን የሚወስድብን የለምና፤ እንደ ተቀበልነው አሁንም በክርስቶስ እንመላለሳለን።
አሁንም ተስፋችን ሁሉ በእርሱ ላይ ተደግፎአል፤ ርዳታችንን ሁሉ ከእርሱ እናመጣለን፤ ደስታችንና ሰላማችንም ከቶ በማይናወጥ መሠረት ላይ ስለ ተመሠረቱ ከእኛ ጋር ጸንተው ይኖራሉ። በጌታ ደስ ይለናል፤ አዎን፣ ደግሞም ደስ ይለናል።
የመከር ደስታ በአብዛኛው የሚገለጠው ገበሬው ለወዳጆቹና ለጎረቤቶቹ ግብዣ በማድረጉ ነው፤ እንዲሁም ብዙውን ጊዜ ክርስቶስን የሚያገኙ ሰዎች ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገላቸው ለወዳጆቻቸውና ለጎረቤቶቻቸው በመንገር ደስታቸውን ይገልጣሉ። የእግዚአብሔር ጸጋ ራሱን የሚያካፍል ነው። አንድ ሰው ድኖ ሁልጊዜ ስለዚያ ዝም ሊል አይችልም፤ በምድር ላይ ዝምተኛ ቤተ ክርስቲያን መፈለግ በሰማይ ዲዳ መዘምራንን እንደ መፈለግ ነው። አንድ ሰው ተጠምቶ ወደ ሕያው ምንጭ ከደረሰ፣ የመጀመሪያው ግፊቱ «ሆ፥ እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ!» ብሎ መጮኽ ይሆናል። ሌሎችም ከአንተ ጋር እንዲካፈሉ የሚያስመኝህ የመከር ደስታ ይሰማሃልን? እንደዚያ ከሆነ ደስታህን ለማወጅ የሚገፋፋህን ስሜት አትጨቍነው። ለወንድሞችና ለእኅቶች፣ ለወዳጆችና ለዘመዶች ስለ ክርስቶስ ተናገር፤ ንግግርህ የሚንተባተብ ቢሆንም እንኳ፣ መልእክቱ በራሱ እጅግ አስፈላጊ ስለ ሆነ የምትገልጥበት ቃል ሁለተኛ ደረጃ ጉዳይ ይሆናል። ንገረው፣ በሩቅም በቅርብም አውጀው — አዳኝ እንዳለ፣ አንተም እንዳገኘኸው፣ ደሙም መተላለፍን ሊያጥብ እንደሚችል። በየስፍራው ንገረው፤ እንዲሁም የመከር ደስታ በየብሱና በባሕሩ ላይ ይስፋፋል፤ እግዚአብሔርም ይከብራል።
የመከር ደስታን የሚመስል ሌላም ደስታ አለን፤ ደግሞም ብዙ ጊዜ እናገኘዋለን። እርሱም የተመለሰ ጸሎት ደስታ ነው። በእምነት መጸለይ ምን እንደ ሆነ እንደምታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ። አንዳንድ ጸሎት እምነት ስላልተቀላቀለበት በእርሱ የሚቀርቡትን ቃላት እንኳ አያህልም። «ከቍርባንህ ሁሉ ጋር ጨው ታቀርባለህ»፤ መሥዋዕታችን ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግን የእምነት ጨው ያስፈልጋል። ከምሕረት ዙፋን ጋር የተላመዱ ሰዎች ጸሎት እውነት እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔር ለጸሎት ይመልሳል የሚለውም ትምህርት ተረት እንዳልሆነ ያውቃሉ። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በጥበብ ምክንያት መልሱን ያዘገያል፤ ያን ጊዜ ልጆቹ መጮኽ፣ መጮኽ፣ ደግሞም መጮኽ አለባቸው። የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል እንደ ተባለለት ገበሬ ናቸው፤ በመጨረሻም የጸሎቱ መልስ ሲመጣ መከሩን እንደሚቀበል ገበሬ ይሆናሉ። የሐናን ዋይታና የሐናን ቃል አስታውሱ። በነፍሷ ምሬት ወደ እግዚአብሔር ጮኸች፤ ልጅዋም በተሰጣት ጊዜ «ከእግዚአብሔር የለመንሁት» ማለት የሆነውን «ሳሙኤል» ብላ ጠራችው፤ «ስለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ልመናዬን ሰጠኝ።» 1ኛ ሳሙኤል 1:27።
የጸሎት ልጅ ስለ ነበረ ለእርሷ ውድ ልጅ ነበረ። በጸሎት መልስ ወደ አንተ የሚመጣ ማንኛውም ምሕረት የሳሙኤል ምሕረትህ፣ የምትወደው ምሕረትህ ይሆናል። ስለ እርሱ «ስለዚህ ምሕረት ጸለይሁ» ትላለህ፤ ለመንፈስህም የመከርን ደስታ ያመጣልሃል።
ፈተናን ስናሸንፍ ደግሞ በውስጣችን ሌላ የመከር ደስታ ይኖረናል። አንዳንድ ጊዜ ከደመና በታች መሆን ምን እንደ ሆነ እናውቃለን፤ በውስጣችን ያለው ኃጢአት በሚያጨልም ኃይል ይነሣል፤ ወይም ከውጭ የሚመጣ መከራ ደመና ሆኖ ይሸፍነናል፤ እንመላለስበት የነበረውንም ቀና መንገድ እንስታለን። የእግዚአብሔር ልጅ በእንዲህ ያለ ጊዜ ራሱንም ዙሪያውንም ስለሚፈራ ርዳታ ለማግኘት በብርቱ ይጮኻል። ከእግዚአብሔር ሕዝብ አንዳንዶቹ ለሳምንታትና ለወራት በአንድነት ለድርብ ፈተና — ከውጭም ከውስጥም — ተጋልጠው በመራራ ጭንቀት ወደ እግዚአብሔር ጮኸዋል። እጅግ ከባድ ትግል ነው፤ የኃጢአቱ ድርጊት እጅግ በሚማርክ ቀለም ተስሎአል፤ የፈተናው አሳሳች ድምፅም አስማት ያደረገባቸው እስኪመስል ድረስ ማርኮአቸዋል። ነገር ግን በመጨረሻ እግራቸው ሳይንሸራተት በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ አልፈው ሲወጡ፣ በአጶልዮን ሳይጠፉ እንደ ገና ወደ ቀኑ ብርሃን ሲወጡ፣ ሊነገር የማይችል ደስታ ይሰማቸዋል፤ ከዚህም ጋር ሲነጻጸር የመከር ደስታ የልጅ ጨዋታ ብቻ ነው። ጥልቅ ደስታን የሚያውቁት መራራ ኀዘን የቀመሱ ናቸው። ሰውዬው በትግሉ እንደ በረታ፣ በፈተናውም ውስጥ በማለፉ ልምድንና የጸና እምነትን እንደ ሰበሰበ ሲሰማው፣ ልቡን ከፍ ያደርጋል፤ በራሱ ሳይሆን በአምላኩ ፊት በመከር ደስታ ደስ ይለዋል። የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፣ ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።
ደግሞም ጠቃሚዎች እንድንሆን በተደረግን ጊዜ የሚገኝ የመከር ደስታ አለ። የክርስቲያን ሁሉ ዋነኛ ምኞት ጠቃሚ መሆን ነው። በውስጣችን ለእግዚአብሔር ክብር የሚነድድ ቅናት ሊኖር ይገባል። ጠቃሚ ለመሆን የሚሻ ሰው ዕቅዱን አውጥቶ ሥራውን በጀመረ ጊዜ ውጤቱን መጠባበቅ ይጀምራል፤ ነገር ግን ውጤቱ እስኪመጣ ሳምንታት ወይም ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ሠራተኛው እስካሁን ፍሬ ባለመኖሩ አይወቀስም፤ ያለ ፍሬ መኖር ቢያረካው ግን ይወቀሳል።
አንድ ሰባኪ የሚለወጥ ሰው ሳያገኝ ሊሰብክ ይችላል፤ ማንስ ይወቅሰዋል? ነገር ግን በዚያ ደስተኛ ሆኖ ቢኖር ማን ያመካኝለታል? በእግዚአብሔር ጸጋ የሌሎችን ሰዎች ልብ መስበር ካልቻልን የገዛ ልባችንን መስበር ድርሻችን ነው፤ ሌሎች ስለ ኃጢአታቸው ካላለቀሱ ስለ እነርሱ ማልቀስ የዘወትር ልማዳችን ሊሆን ይገባል። ልብ ትጉህ፣ ሞቃትና ቀናተኛ በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ በመጠኑ ስኬትን ይሰጣል — አንዱ አምሳ፣ አንዱም መቶ። ስኬቱ ሲመጣ በእውነት የመከር ደስታ ነው። በወጣትነቴ አገልግሎት አንዲት ነፍስ ሰላምን እንዳገኘች መጀመሪያ በሰማሁ ጊዜ የተሰማኝን ደስታ ለመጥቀስ ራሴን ማውሳቴ የማይቀር ነው።
በአንዲት መንደር ለጥቂት ሰንበቶች ሰብኬ ነበር፤ ጉባኤውም እየጨመረ ነበር፤ ነገር ግን አንድም ሰው እንደ ተለወጠ አልሰማሁም ነበር፤ እኔም «ምናልባት በእግዚአብሔር አልተጠራሁም ይሆናል። እንድሰብክ አይፈልግም፤ ቢፈልግ ኖሮ መንፈሳዊ ልጆችን በሰጠኝ ነበር» ብዬ አሰብሁ። በአንድ ሰንበት ደጉ ዲያቆኔ «አትዘን። ባለፈው ሰንበት አንዲት ድሀ ሴት ለመዳን በሚያደርስ ሁኔታ ልቧ ተነክቶአል» አለኝ። ያቺን ሴት ለማየት ምን ያህል ጊዜ የቈየሁ ይመስላችኋል? ወደ ጎጆዋ ለመድረስ የወሰደብኝን ጊዜ ያህል ብቻ ነበር። የእግዚአብሔር ጸጋ ሥራ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ከገዛ አፏ ለመስማት ጓጕቼ ነበር። የአንድ ድሀ የቀን ሠራተኛ ሚስት ብቻ ብትሆንም፣ ቅዱስ ሕይወት ኖራ ወደ ሰማይ እስክትወሰድ ድረስ ሁልጊዜ በልዩ ፍቅር እመለከታት ነበር።
ከዚያ ወዲህ በብዙዎች ምክንያት በጌታ ደስ ብሎኛል፤ ነገር ግን ያ በአገልግሎቴ ላይ የታተመው የመጀመሪያው ማኅተም በተለየ ሁኔታ ውድ ሆኖልኝ ነበር። የመከርን ደስታ ጥቂት እንድቀምስ አደረገኝ። አንድ ሰው ሀብት ቢያወርሰኝ ኖሮ አንዲት ነፍስ ወደ አዳኙ መመራቷን በማወቄ ካገኘሁት ደስታ መቶኛውን እጅ እንኳ ባልሰጠኝ ነበር። ይህ ደስታ የሌላቸው ክርስቲያኖች አንድ አማኝ ከሰማይ በዚህ ወገን ሊያውቃቸው ከሚችላቸው እጅግ የተመረጡ ደስታዎች አንዱን እንዳጡ እርግጠኛ ነኝ። እንዲያውም ነፍሳት ሲድኑ ሳይ ገብርኤልን ስለ ዙፋኑ፣ መላእክትንም ስለ በገናቸው አልቀናባቸውም። ሌሎችን አዳኙን ወደ ማወቅ አምጥተን በቤዛው አክሊል ላይ አዲስ ዕንቍዎችን መጨመር ከቻልን፣ ለጊዜው ከሰማይ ውጭ መሆናችን ራሱ ሰማያችን ይሆናል።
የመከርን ደስታ የሚመስል ሌላም ደስታ እጠቅሳለሁ፤ ይኸውም ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለ ኅብረት ነው። ይህ የሚነገርለት ነገር ከመሆን ይልቅ የሚለማመዱትና የሚደሰቱበት ነገር ነው። ከክርስቶስ ጋር ያለ ኅብረት ምን እንደ ሆነ ልንገልጥ ብንሞክር አንችልም። ከሰዎች ሁሉ ጠቢብ የነበረው ሰሎሞን ቤተ ክርስቲያን ከጌታዋ ጋር ስላላት ኅብረት እንዲጽፍ በመንፈስ በተነሣሣ ጊዜ ምሳሌዎችንና ምሳሌያዊ ቋንቋን መጠቀም ግድ ሆነበት፤ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞንም ለመንፈሳዊ አእምሮ ሁልጊዜ ደስ የሚያሰኝ ቢሆንም፣ ለዓለማዊ አእምሮ ግን የፍቅር ግጥም ብቻ ይመስላል። ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። 1ኛ ቆሮንቶስ 2:14 ነገር ግን ኦ፣ ክርስቶስ የአንተ መሆኑን ማወቅና ወደ እርሱ መቅረብ እንዴት ያለ ደስታ ነው! ጐኑን መንካትና ጣትህን በችንካሮቹ ምልክት ውስጥ ማግባት — እነዚህ የየዕለቱ ደስታዎች አይደሉም። ነገር ግን እንዲህ ያለ የቀረበና የግል ኅብረት በልዩ ቀኖቻችን ወደ እኛ ሲመጣ ነፍሳችንን እንደ አሚናዳብ ሰረገሎች ከፍ ያደርጋታል፤ ወይም ከፈለጋችሁ፣ በዓለምና ዓለም ታላቅ ወይም ውድ ብሎ በሚጠራው ሁሉ ላይ እንድንራመድ ያስችለናል።
ክርስቶስ ከእኛ ጋር ከሆነ ሁኔታዎቻችን ምንም አይደሉም — እርሱ አምላካችን፣ መጽናናታችንና ሁሉ ነገራችን ነው፤ በመከርም ደስ እንደሚለን በፊቱ ደስ ይለናል።
በአንድ ተግባራዊ ቃል ልደመድም ስለምፈልግ በዝርዝር ለመግባት ጊዜ የለኝም። ከእኛ ብዙዎቻችን ጥልቅ ደስታ የሚያመጣልንን መከር አጥብቀን እንናፍቃለን። በቅርቡ ብዙ ሰዎች ለሰዎች ነፍስ ምን ያህል ጥልቅ ርኅራኄ እንደሚሰማቸው አካፍለውኛል። ሌሎቻችን ደግሞ ከቶ ጸልየን ከምናውቀው በላይ እንድንጸልይ፣ ክርስቶስ የሚጠፉትን እንዲያድን ከቶ ተጨንቀን ከምናውቀው በላይ እንድንጨነቅ ምሥጢራዊ ግፊት ተሰምቶናል። በዚህች ምድር ላይ ጥልቅ መንፈሳዊ መነቃቃት እስኪሆን ድረስ አንረካም። ይህን ስሜት እኛ ራሳችን አልፈጠርነውም፤ ልናፍነውም አንፈልግም። ሊታፈን ይችላል ብለንም አናምንም፤ ሌሎችም ያንኑ ሰማያዊ ሸክም ይሰማቸዋል፤ በረከቱ እስኪመጣም ድረስ ቀንና ሌሊት ወደ እግዚአብሔር ያለቅሳሉ፤ ይጮኻሉም። ይህ መዝራቱ ነው፤ ይህ ማረሱ ነው፤ ይህ መከስከሱ ነው — እስከ መከሩ ድረስ ይቀጥል። በየስፍራው ያሉ ወንድሞቼና እኅቶቼ «በጭንቀት ተሞልተናል፤ ነፍሳት እስኪድኑ ድረስ በምጥ ውስጥ ነን» ሲሉ ለመስማት እናፍቃለሁ። «ልጆችን ስጠኝ፥ አለዚያ እሞታለሁ» የሚለው የራሔል ጩኸት ዛሬ የአገልጋያችሁ ጩኸት፣ የሌሎችም የሺዎች ናፍቆት ነው። ያ ምኞት እየበረታ ሲሄድ መነቃቃት ይቀርባል። ለክርስቶስ መንፈሳዊ ልጆች ሊኖሩን ይገባል፤ አለዚያ ለመዳናቸው ካለን ናፍቆት የተነሣ ልባችን ይሰበራል። ኦ፣ ምነው እነዚህ ናፍቆቶች፣ ጕጕቶች፣ ምኞቶችና ጥረቶች በበዙ! የመነቃቃት መከር እስኪመጣ ድረስ ብንጸልይ በደስታው እንካፈላለን።
ከሁሉ የሚበልጥ ደስታ የሚኖራቸው እነማን ናቸው? ስለ እርሱ ከሁሉ ይበልጥ የተጨነቁት ናቸው። ከእናንተ በስውር የማትጸልዩ፣ ወደ ጸሎት ስብሰባም የማትመጡ በረከቱ ሲመጣና ቤተ ክርስቲያን ስታድግ ደስታ አይኖራችሁም። በመዝራቱ ድርሻ አልነበራችሁም፤ ስለዚህ በመከሩ የሚኖራችሁ ድርሻ ጥቂት ነው። ስለ ነፍሳቸው ለሌሎች ፈጽሞ የማይናገሩ፣ በሰንበት ትምህርት ቤት ወይም በሚስዮን ሥራ የማይካፈሉ፣ ነገር ግን በበረከቱ ብቻ የሚደሰቱ — እነዚህ ለጌታ ስለማይሠሩ ከመከሩ ደስታ ምንም አይኖራቸውም። ደግሞስ ሰነፎች ደስተኞች እንዲሆኑ ማን ይፈልጋል? ይልቁንም በቅናታችንና በጭንቀታችን እንዲህ ለማለት ይቃጣናል፦ «ሜሮዝን ርገሙ፤ እግዚአብሔርን ለመርዳት፥ በኃያላን ላይ እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምና በእርስዋ የሚኖሩትን ፈጽማችሁ ርገሙ።» — መሳፍንት 5:23 በመንፈሱ ጌታን ለመርዳት ብትመጡ የመከሩን ደስታ ትካፈላላችሁ። የሚወዷቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ሲመጡ ከሚያዩት የበለጠ ደስታ የሚኖረው ማንም አይኖር ይሆናል። ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ ባሰባችኋቸው ቍጥር የሚያስጨንቋችሁ ልጆች አሏችሁ፤ ስለ እነርሱ ዘወትር ወደ ጸሎት የሚገፋችሁ ጭንቀት ይሁኑላችሁ፤ በረከቱ ቢመጣስ ወደ እነርሱ የማይመጣው ለምንድር ነው? መነቃቃት ቢሆን ልጃችሁ የማትለወጠው፣ ዱርዬው ልጃችሁ የማይድነው ለምንድር ነው? ወይም ተጠራጣሪና የማያምን ሆኖ የኖረው ሽበታም አባታችሁ እንኳ — የእግዚአብሔር ጸጋ የማይደርስለት ለምንድር ነው? ኦ፣ ያን ጊዜ እንዴት ያለ ደስታ ይኖራችኋል!
የቅርብ ዘመዶቻችሁ ከጌታችሁ ከክርስቶስ ጋር ሲተባበሩ ስታዩ መንፈሳችሁን እንዴት ያለ ደስታ ይሞላዋል!
ስለ እነርሱ አጥብቃችሁ ጸልዩ፤ በገዛ ቤታችሁም ገና የመከርን ደስታ፣ በገዛ ቤተሰባችሁም የመከር መግቢያን እልልታ ታገኛላችሁ።
አድማጬ ሆይ፣ ምናልባት ስላልዳንህ ከዚህ ደስታ ጋር የሚያገናኝህ ብዙ ነገር የለህ ይሆናል። ቢሆንም ያልተለወጠ ሰው እግዚአብሔር በባረከው አገልግሎት ሥር፣ ሰዎች እንዲለወጡ በሚጸልዩ ሰዎች መካከል መሆኑ ድንቅ ነገር ነው። አንተ ወጣት ሆይ፣ ክርስቲያን እናት ማግኘትህ በረከት ነው።
አንቺ ያልተለወጥሽ ሴት ሆይ፣ እግዚአብሔርን የምትፈራ እኅት ማግኘትሽ ታላቅ በረከት ነው። እነዚህ ስለ እናንተ ተስፋ ይሰጡናል። ዘመዶቻችሁ እየጸለዩ ሳሉ ስለ እናንተ ተስፋ አለን። ጌታ ኢየሱስ ገና የእናንተ ይሁን።
ነገር ግን ኦ፣ ሳታምኑ ብትቀሩ፣ ወደ ሌሎች የሚመጣው በረከት ምንም ያህል የበለጸገ ቢሆን አይጠቅማችሁም። «እሺ ብትሉ ብትሰሙኝም የምድርን በረከት ትበላላችሁ።» — ኢሳይያስ 1:19 ነገር ግን አንዳንዶች በኀዘን «መከሩ አለፈ፥ በጋውም ተፈጸመ፥ እኛም አልዳንንም» ብለው ይጮኹ ይሆናል። — ኤርምያስ 8:20 በመነቃቃት ውስጥ አልፈው ሳይለወጡ የሚቀሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከቀድሞው ይበልጥ እንደሚደነድኑ ተስተውሎአል። ይህን አምናለሁ፤ ስለዚህ ከተጽዕኖው አንድም እንዳያመልጥ የእግዚአብሔር መንፈስ በእንዲህ ያለ ኃይል እንዲመጣ እጸልያለሁ።
እንዲህ ብለህ ጸልይ፦ «ኃያል መንፈስ ሆይ፣ አትለፈኝ!
ዕውርን የምታበራ አንተ ነህ፤ የኢየሱስ ጽድቅ ምስክር ሆይ፣ የኃይልን ቃል ንገረኝ፤ እኔንም፣ እኔንም።»
«በኃጢአት ለረጅም ጊዜ ተኝቼ ነበርሁን? ለረጅም ጊዜ ቸል ብዬህ አሳዝኜህ ነበርሁን?
ዓለም ልቤን ይዞት ነበርን?
ኦ፣ ይቅር በለኝ፣ አድነኝም፤ እኔንም፣ እኔንም።»
ኦ፣ ምነው በመላው ዓለም ያሉ አማኞች ሁሉ ትጉህና የማያቋርጥ ጸሎት በጸለዩ! አብያተ ክርስቲያናቶቻችን ጽዮንን በምድር ላይ ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ ለእግዚአብሔር ዕረፍት ሳይሰጡ ወደ ማያቋርጥና ብርቱ ጸሎት ቢነቃቁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ስትመጣና የሰይጣን ኃይል ሲሰበር እናይ ይሆናል።
ከእናንተ ክርስቶስን የምትወዱ ሁሉ፣ በስሙ አጥብቃችሁ እንድትጸልዩ እለምናችኋለሁ፤ ከእናንተ ቤተ ክርስቲያንን የምትወዱና እድገቷን የምትመኙ ሁሉ፣ በዚህ የጸሎት ወቅት ወደ ኋላ እንዳትሉ እማልዳችኋለሁ። የመከሩ ደስታ እስኪሰጥ ድረስ እንድትጸልዩ ጌታ ይምራችሁ። በአንድ ሰንበት «በሚቀጥለው ወር ሥራውን እንደምትይዙት ጌታ እናንተን ይይዛችኋል» እንዳልሁ ታስታውሳላችሁን? ለብዙዎች እውነት እንደሚሆን ይሰማኛል — ቤተ ክርስቲያኑን እንደምትይዙት ጌታ እናንተን ይይዛችኋል። ጥቂት ብትዘሩ ጥቂት ታጭዳላችሁ፤ ጥቂት ብትጸልዩ ጥቂት ሞገስ ትቀበላላችሁ። ነገር ግን በቅናትና በእምነት ብትሠሩ፣ ለጌታም ብዙ ብትጸልዩና ብትሠሩ፣ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ ተመልሶ ይሰጣችኋል። ሌሎችን በጠብታ ብታጠጡ ጠብታ ትቀበላላችሁ፤ መንፈስ ግን የሕይወትን ውኃ ወንዞች ከነፍሳችሁ እንድታፈስሱ ቢረዳችሁ፣ የሰማያዊ ጸጋ ጎርፍ ወደ መንፈሳችሁ ይጐርፋል። እግዚአብሔር ያልተለወጡትን ያስገባ፤ በኢየሱስ ወደ ቀላል መታመንም ይምራቸው፤ ያን ጊዜ እነርሱም የመከርን ደስታ ያውቃሉ። ይህን በስሙ እንለምናለን። አሜን።
ምዕራፍ 14 ተጠናቋል
የመከር ደስታ