ምዕራፍ 8 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
የጥርጣሬ ምሽግና ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ
በመንገዱ ግራ በኩል የአቋራጭ መንገድ መስክ ነበረ። በውስጡ መንገድ ያለበት፣ የአጥር መሻገሪያም ያለው ያማረ ለምለም መስክ ነበር። ክርስቲያንም «መልካሙ ተስፈኛ ሆይ፣ ና፤ በሣሩ ላይ እንሂድ» አለ።
ተስፈኛ፦ ይህ መንገድ ቢያስተን ግን ምን ይሆናል?
ክርስቲያን፦ እንዴት ያስተናል? ተመልከት፤ ከመንገዱ ጎን ለጎን አይሄድምን?
ስለዚህ መስኩን አቋርጠው ሄዱ። ነገር ግን ብዙም ሳይሄዱ ከፊታቸው አንድ ሰው አዩ። ስሙ ከንቱ መተማመን ነበር። እርሱም መንገዱ ወደ ሰማያዊቱ ከተማ በር እንደሚወስድ ነገራቸው። ስለዚህ ሰውየው ቀድሞ ሄደ። ነገር ግን እነሆ፣ ሌሊት ገባ። እጅግም ጨለመ። መሪያቸውንም ማየት አቃታቸው። እርሱም ከፊቱ ያለውን መንገድ ስላላየ ወደ ጥልቅ ጕድጓድ ወደቀ። ከዚያ በኋላ ስለ እርሱ ምንም አልተሰማም።
ተስፈኛም «አሁን የት ነን?» አለ።
ክርስቲያንም ዝም አለ፤ ወዳጁን ከመንገድ እንዳሳተው አስቦ ነበርና። አሁንም መብረቅ ከሰማይ ብልጭ አለ፤ ዝናብም እንደ ጐርፍ ወረደ።
ተስፈኛ (እያቃሰተ)፦ ወይ፣ በመንገዴ ብጸና ኖሮ!
ክርስቲያን፦ ይህ መንገድ ያስተናል ብሎ ማን ያስብ ነበር?
ተስፈኛ፦ እኔ ከመጀመሪያው ፈርቼ ነበር፤ ስለዚህም ፍንጭ ሰጠሁህ።
ክርስቲያን፦ መልካም ወዳጄ ሆይ፣ ከትክክለኛው መንገድ ስላወጣሁህ አዝናለሁ።
ተስፈኛ፦ ከዚህ በላይ አትናገር፤ ይህ ለበጎአችን እንደ ሆነ አልጠራጠርም።
ክርስቲያን፦ እንዲህ ቆመን መቅረት የለብንም፤ ለመመለስ እንሞክር።
ተስፈኛ፦ ነገር ግን መልካሙ ክርስቲያን ሆይ፣ እኔ ልቅደም።
ከዚያም እንዲህ የሚል ድምፅ ሰሙ፦ «ልብህን ወደ አውራ ጎዳናው፣ ወደ ሄድህበትም መንገድ አቅና፤ እንደ ገና ተመለስ።» በዚህ ጊዜ ግን ከዘነበው ዝናብ የተነሣ ውኃው ጥልቅ ሆኖ ነበር። ስለዚህ መመለስ አስተማማኝ አልመሰለም። ቢሆንም ተመለሱ። ነገር ግን ጨለማው ብርቱ ነበር፤ ውኃውም እጅግ ሞልቶ ነበር። ስለዚህ አንድ ሁለት ጊዜ ሊያሰጥማቸው ተቃርቦ ነበር። በችሎታቸው ሁሉ ቢሞክሩም በዚያ ሌሊት ሊመለሱ አልቻሉም። ስለዚህ ከዝናቡ የሚከልላቸው ስፍራ አገኙ፤ እስኪነጋም ድረስ በዚያ ተኙ።
በተኙበት ስፍራ አጠገብ የጥርጣሬ ምሽግ ነበረ። ጌታውም ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ ነበር። አሁን የተኙትም በእርሱ መሬት ላይ ነበር። ግዙፉ ተስፋ ቆራጭም በዚያ አገኛቸው። በሻካራ ድምፅም እንዲነቁ አዘዛቸው። «ከወዴት ናችሁ?» አለ፤ «ወደዚህስ ምን አመጣችሁ?» እነርሱም መንገዱን እንደ ሳቱ ነገሩት። ግዙፉ ተስፋ ቆራጭም «ወደዚህ በግድ ለመግባት መብት የላችሁም፤ የተኛችሁበት መሬት የእኔ ነው» አለ።
ጥፋተኞች መሆናቸውን ያውቁ ስለ ነበር ብዙ የሚሉት አልነበራቸውም። ስለዚህ ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ እየነዳ ወሰዳቸው። በጠንካራ ምሽጉ ውስጥ ባለ ጨለማና የሚገማ ክፍል ውስጥ ጣላቸው። በዚያም ለሦስት ቀን ተቀመጡ። በዚያ ጊዜ ሁሉ ብርሃንም ምግብም አንዲት ጠብታ ውኃም አልነበራቸውም። እንዴት እንደ ሆኑ የሚጠይቃቸውም ማንም አልነበረም። ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ ሚስት ነበረችው፤ ስሟም ጥርጣሬ ነበር። ያደረገውንም ነገራት። ከዚያም «ምን ባደርጋቸው ይሻላል?» አላት። ጥርጣሬም «በደንብ ደብድባቸው» አለች። ስለዚህ ሲነሣ ከዱር ዛፍ የተቈረጠ ወፍራም በትር ይዞ ምስኪኖቹ ክርስቲያንና ተስፈኛ ወደ ተኙበት ክፍል ወረደ። እንደ ውሾችም ደበደባቸው፤ በወለሉ ላይ መገላበጥ እንኳ አልቻሉም። ያንንም ቀን ሙሉ በልቅሶና በእንባ አሳለፉ።
በማግሥቱ እንደ ገና መጣ። ከግርፋቱ የተነሣ ታመው አገኛቸው። ከክፍሉ የሚለቀቁበት ምንም ዕድል ስለሌለ ከሁሉ የሚሻላቸው ራሳቸውን መግደል እንደ ሆነ ነገራቸው። እንዲህም አለ፦ «በዚህ ሁሉ መከራ ለምን መኖር ትፈልጋላችሁ?» እነርሱ ግን እንዲለቃቸው ተስፋ እንደሚያደርጉ ነገሩት። በዚህ ጊዜ በቍጣ ፊት ዘሎ ተነሣ። ሊጨርሳቸውም በእርግጥ ነበር፤ ነገር ግን ለጥቂት ጊዜ የሚጥል በሽታ ያዘው፤ እጁም አልታዘዝ አለው። ስለዚህ ወደ ኋላ ተመለሰ፤ በተናገረውም ነገር እንዲያስቡ ትቶአቸው ሄደ።
ክርስቲያን፦ ወዳጄ ሆይ፣ ምን እናድርግ? አሁን የምንኖረው ኑሮ ከሞት የከፋ ነው። እኔ እንደዚህ መኖር ወይም በገዛ እጃችን መሞት የቱ እንደሚሻል አላውቅም። መቃብር ከዚህ ክፍል ይልቅ ያነሰ ሐዘን ያለበት ይመስለኛል። ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ ይግዛን እንዴ?
ተስፈኛ፦ በእውነት ሁኔታችን አሳዛኝ ነው። እዚህ ከመኖር መሞት ይሻለኛል። ነገር ግን ወደምንሄድበት አገር ጌታ «አትግደል» እንዳለ እናስታውስ። በዚህ ሥራ ነፍሳችንንም እንገድላለን። ወዳጄ ክርስቲያን ሆይ፣ በመቃብር ውስጥ ስላለ ዕረፍት ትናገራለህ። ነገር ግን የራሱን ሕይወት የሚያጠፋ ሰው ወደ ደስታ ሊሄድ ይችላልን? ሕግ ሁሉ በግዙፉ ተስፋ ቆራጭ እጅ አይደለም። ዓለምን የፈጠረ እግዚአብሔር እርሱን እንዲሞት፣ ወይም እንደ መጀመሪያው እጅና እግሩ እንዳይሠራ ያደርግ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? እኔ እንደ ሰው ልቤን አጠንክሬ ከዚህ ጭንቀት ለመውጣት ልሞክር ቈርጫለሁ። መጀመሪያ ወደ ክፍሉ በመጣ ጊዜ ይህን ያላደረግሁ ሞኝ ነበርሁ! ነገር ግን ራሳችንን አንግደል፤ መልካም ጊዜ ገና ሊመጣ ይችላልና።
በእነዚህ ቃላት ተስፈኛ የክርስቲያንን ሐሳብ ለወጠው።
ማታም ግዙፉ ገና በሕይወት መኖራቸውን ለማየት ወደ ክፍሉ ወረደ። በእውነትም ስለ እነርሱ ሊባል የሚቻለው በሕይወት መኖራቸው ብቻ ነበር። ከቍስላቸውና ከምግብ እጦት የተነሣ ከመተንፈስ በቀር ምንም አያደርጉም ነበርና። ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ እንዳልሞቱ ባየ ጊዜ እጅግ ተቈጣ። ባልተወለዱ ኖሮ የሚያሰኝ የከፋ ነገር እንደሚደርስባቸውም ተናገረ። በዚህ ጊዜ በፍርሃት ተንቀጠቀጡ። ክርስቲያንም ራሱን ስቶ ወደቀ። ሲነቃ ግን ተስፈኛ እንዲህ አለው፦ «ወዳጄ ሆይ፣ እስከ አሁን ድረስ በእምነት ምን ያህል ብርቱ እንደ ነበርህ አስታውስ። እስቲ ንገረኝ፤ አጶልዮን ሊጎዳህ ቻለን? ወይስ በሞት ጥላ ሸለቆ የሰማኸው፣ ያየኸውና የተሰማህ ነገር ሁሉ ሊጎዳህ ቻለን? ያለፍህባቸውን ፍርሃቶች፣ ሐዘኖችና መከራዎች ተመልከት። አሁን ደግሞ ልብህ ይውደቅን? እኔም ከአንተ ይልቅ እጅግ ደካማ ሰው ሆኜ በዚህ ክፍል ውስጥ ነኝ። ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ እንደ አንተ እኔንም ደብድቦኛል፤ ምግብና ብርሃንም ከልክሎኛል። ስለዚህ ሁለታችንም (ኀፍረትን ለማምለጥ ብቻ እንኳ ቢሆን) የቻልነውን ያህል እንታገሥ።»
ሌሊትም በገባ ጊዜ የግዙፉ ተስፋ ቆራጭ ሚስት «እሺ፣ ሁለቱ ሰዎች እጅ ይሰጣሉን?» አለችው።
እርሱም «አይ፤ ጸንተው መቆምን መርጠዋል፤ ራሳቸውንም አይገድሉም» አላት።
ከዚያም ወይዘሮ ጥርጣሬ «ሲነጋ ወደ ግቢው ውሰዳቸው። የገደልሃቸው ሁሉ የተጣሉባቸውን መቃብሮች አሳያቸው። በዚህ ጊዜም አስፈራራቸው» አለች።
ስለዚህ ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ ወደዚያ ስፍራ ወሰዳቸው። እንዲህም አለ፦ «እጅ ካልሰጣችሁ በአሥር ቀን ውስጥ እዚህ ትጣላላችሁ። ሂዱ፤ እንደ ገና ወደ ጕድጓዳችሁ ውረዱ።» ይህንንም ብሎ እስኪመለሱ ድረስ መንገዱን ሁሉ ደበደባቸው። እዚያም ቀኑን ሙሉ በአሳዛኝ ሁኔታ ተኙ።
ሌሊትም በሆነ ጊዜ ወይዘሮ ጥርጣሬ ግዙፉን ተስፋ ቆራጭ «እነዚህ ሰዎች የክፍሉን መዝጊያ ከፍተው ነጻ እንወጣለን በሚል ተስፋ እንዳይኖሩ እጅግ እፈራለሁ» አለችው።
ግዙፉ ተስፋ ቆራጭም ሚስቱን «ውዴ ሆይ፣ እንዲህ ትያለሽን? እንግዲያስ ፀሐይ ስትወጣ እፈትሻቸዋለሁ» አላት።
በዚያች ሌሊት ክርስቲያንና ተስፈኛ በጕድጓዱ ውስጥ ተኝተው ሳሉ ለመጸለይ ተንበረከኩ። እስኪነጋም ድረስ ተንበርክከው ጸለዩ። ከዚያም ክርስቲያን ድንገት ደንግጦ እንዲህ አለ፦ «በነጻነት መሄድ እየቻልሁ በዚህ ጨለማ ጕድጓድ ውስጥ የምተኛ እንዴት ያለሁ ሞኝ ነኝ! በኪሴ ውስጥ ተስፋ ቃል የተባለ ቁልፍ አለኝ። በጥርጣሬ ምሽግ ያሉትን የበሮች መዝጊያ ሁሉ እንደሚከፍት እርግጠኛ ነኝ።»
ተስፈኛም «ይህ የምሥራች ነው፤ ከጉያህ አውጣውና እንሞክረው» አለ።
ስለዚህ ክርስቲያን ቁልፉን በመዝጊያው ውስጥ አገባው። ወዲያውም መቀርቀሪያው ወደ ኋላ ተመለሰ፤ በሩም ወለል ብሎ ተከፈተ። ክርስቲያንና ተስፈኛም ሁለቱም ወጡ። ወደ ግቢው በር በደረሱ ጊዜ ቁልፉ እንደዚያው ከፈተው። የጥርጣሬ ምሽግ የመጨረሻው ጠንካራ በር መዝጊያ ግን ከበደ። ቢሆንም በመጨረሻ ተከፈተ። ነገር ግን የበሩ ማጠፊያ ብርቱ ሲጢጥታ አሰማ። ይህም ግዙፉን ተስፋ ቆራጭ ቀሰቀሰው። እርሱም ሁለቱን ሰዎች ለመፈለግ ተነሣ። በዚያን ጊዜ ግን በሽታው ስለ ያዘው እጅና እግሩ ዛለ። ስለዚህ ወደ ክፍላቸው በምንም መንገድ ሊደርስ አልቻለም። ክርስቲያንና ተስፈኛ ወደ አውራ ጎዳናው ሸሽተው ተመለሱ፤ ከእርሱም መሬት በሰላም ወጡ። በአጥር መሻገሪያው ላይ ለማረፍ በተቀመጡ ጊዜ በዚህ መንገድ ሊመጡ የሚችሉትን ሰዎች ለማስጠንቀቅ ተስማሙ። ስለዚህ በአንድ ምሰሶ ላይ እነዚህን ቃላት ቀረጹ፦ «ይህ ወደ ጥርጣሬ ምሽግ የሚወስድ መንገድ ነው። ምሽጉን የሚጠብቀው ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ ነው። እርሱ የሰማያዊቱን አገር ንጉሥ አይወድም፤ ወደዚያ መሄድ የሚፈልጉትንም ሁሉ ሊገድል ይፈልጋል።»
ምዕራፍ 8 ተጠናቋል
የጥርጣሬ ምሽግና ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ