ምዕራፍ 12 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
የተርጓሚው ቤት
በዚህ ጊዜ ክርስቲያና፣ ምሕረትና አራቱ ልጆች ወደ ተርጓሚው ቤት ደረሱ። ወደ በሩ ሲቀርቡ በቤቱ ውስጥ የክርስቲያናን ስም ሲጠሩ ሰሙ። እርሷ ከከተማዋ መሸሿ ብዙ ወሬ አስነሥቶ ነበርና። ነገር ግን እርሷ በበሩ ላይ ቆማ እንደ ነበረች አላወቁም። በመጨረሻ በጠባቧ በር እንዳደረገችው በሩን አንኳኳች። ንጽሕት የምትባል አንዲት ወጣት ልጃገረድም ወደ በሩ መጣች።
ንጽሕት፦ በዚህ ስፍራ ማንን ማነጋገር ትፈልጋላችሁ?
ክርስቲያና፦ ይህ ቤት በመንገዱ ለሚያልፉ ሰዎች ማረፊያ እንደ ሆነ ሰምተናል። ስለዚህ እንድታስገቡን እንለምናለን። እንደምታዪው ቀኑ መሽቷል፤ በሌሊት መጓዝም አንፈልግም።
ንጽሕት፦ እባክሽ ስምሽ ማን ነው? ለጌታዬ ልንገረው።
ክርስቲያና፦ ስሜ ክርስቲያና ነው። ከጥቂት ጊዜ በፊት በዚህ መንገድ ያለፈው የክርስቲያን ሚስት ነበርሁ። እነዚህም አራቱ ልጆቹ ናቸው።
ንጽሕትም ወደ ውስጥ ሮጣ ገባች። በዚያ ላሉትም «በበሩ ላይ ማን እንደ ቆመ ልትገምቱ ትችላላችሁ? ክርስቲያና፣ ልጆቿና ወዳጇ ናቸው!» አለቻቸው።
እነርሱም በደስታ ዘለሉ፤ ለጌታቸውም ሊነግሩት ሄዱ። እርሱም ወደ በሩ መጥቶ «ክርስቲያን ወደ ሰማያዊቱ ከተማ ሲነሣ በጥፋት ከተማ የተዋት ክርስቲያና አንቺ ነሽን?» አለ።
ክርስቲያና፦ አዎ፣ እኔ ነኝ። ልቤ እጅግ ደንዳና ነበር። ስለ ጭንቀቱ ግድ አልሰጠኝም፤ እንደ ቻለ ብቻውን እንዲሄድም ተውሁት። እነዚህ አራቱ ልጆቹ ናቸው። አሁን ግን እኔም መጥቻለሁ። ከዚህ መንገድ በቀር ትክክል የሆነ መንገድ እንደሌለ በእርግጥ አውቃለሁና።
ተርጓሚው፦ ታዲያ ለምን በበሩ ላይ ቆማችኋል? ግቡ። አሁን ገና ስለ እናንተ እያወራን ነበር፤ በመንገድ ላይ እንዳላችሁ ሰምተን ነበርና። ኑ፣ ውድ ልጆቼ፣ ግቡ። ነዪ፣ ውዲቱ ልጃገረድ፣ ግቢ። ከዚያም ወደ ቤቱ አስገባቸው፤ ተቀምጠውም እንዲያርፉ ነገራቸው። በቤቱ ያሉት ሁሉ በደስታ ፈገግ አሉ። ክርስቲያና ወደ ሰማያዊቱ ከተማ እየሄደች ስለ ሆነ ደስ አላቸው። ልጆቹም በእግዚአብሔር መንገድ ሲሄዱ በማየታቸው ተደሰቱ። በጎ ፈቃዳቸውንም ለማሳየት እጃቸውን ጨበጡአቸው። ምሕረትንም በለስላሳ ቃል አነጋገሯት። ሁሉም እንዲዝናኑ ነገሯቸው። እራት እስኪደርስ ድረስ ተርጓሚው ለክርስቲያን ያሳያቸውን ነገሮች ሁሉ አሳያቸው። ከዚያ በኋላ ወደ አንድ ክፍል ወሰዳቸው። በዚያ ክፍል በእጁ መሰቅሰቂያ የያዘ አንድ ሰው ቆሞ ነበር። ይህ ሰው ወደ መሬት እንጂ ወደ ሌላ ቦታ ማየት አይችልም ነበር። ሌላ ሰው ደግሞ በእጁ አክሊል ይዞ በዚያ ቆሞ ነበር። መሰቅሰቂያውን ቢሰጠው አክሊሉን እንደሚሰጠው ይነግረው ነበር። የመጀመሪያው ሰው ግን ቀና ብሎ አላየም። በወለሉ ላይ የወደቀውን ገለባ፣ አቧራና እንጨት መሰብሰቡን ቀጠለ።
ክርስቲያናም እንዲህ አለች፦ «ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ የማውቅ ይመስለኛል። ይህ የዚህ ዓለም ሰው ሥዕል ነው፤ አይደለም እንዴ፣ ደጉ ጌታዬ?»
ተርጓሚው፦ ልክ ብለሻል። መሰቅሰቂያው የሚያሳየው አሳቡ በምድር ነገር ላይ ብቻ እንደ ሆነ ነው። በሚመጣው ዓለም ያለውን ሕይወት እንደ ተራ ዘፈን ይቆጥረዋል። ቀና ብሎ እንኳ እንደማያይ ልብ በሉ። ለብዙ ሰዎች ገለባ፣ እንጨትና አቧራ ለመኖር ዋና ነገሮች ሆነውባቸዋል።
በዚህ ጊዜ ክርስቲያናና ምሕረት አለቀሱ። «ወይኔ፣ አዎ፣ ይህ በጣም እውነት ነው!» አሉ።
ከዚያም ተርጓሚው ዶሮና ጫጩቶቿ ወዳሉበት ክፍል ወሰዳቸው። ለጥቂት ጊዜ በደንብ እንዲመለከቷቸውም ነገራቸው። ከጫጩቶቹ አንዷ ውኃ ልትጠጣ ወደ ገንዳው ሄደች። በጠጣች ቁጥርም ራሷንና ዓይኖቿን ወደ ሰማይ ታነሣ ነበር።
እርሱም እንዲህ አለ፦ «ይህች ወፍ የምታደርገውን እዩ። መልካም ነገር ሁሉ ከየት እንደሚመጣ ከእርሷ ተማሩ። በላይ ለሚኖረው ጌታም ስለ እርሱ ክብርና ምስጋና ስጡ። እንደ ገናም ተመልከቱ። ዶሮዋ ከጫጩቶቿ ጋር ያላትን ልማድ ሁሉ እዩ። ቀኑን ሙሉ የምትጠራበት ጥሪ አላት። አልፎ አልፎ ብቻ የምትጠራበት ጥሪም አላት። በክንፎቿ ልትሸፍናቸው የምትጠራበት ሦስተኛ ጥሪ አላት። አራተኛውም ጠላት ስታይ የምትጮኸው ታላቅ ጩኸት ነው።» ደግሞም እንዲህ አለ፦ «አሁን የእርሷን ልማድ ከንጉሣችሁ መንገድ ጋር አወዳድሩ። የእነዚህንም ጫጩቶች ጠባይ ፈቃዱን ማድረግ ከሚወዱ ሰዎች ጋር አወዳድሩ። ያን ጊዜ ምን ማለቴ እንደ ሆነ ትረዳላችሁ። እርሱ ከቅዱሳኑ ጋር የሚሄድበት መንገድ አለውና። ቀኑን ሙሉ በሚጠራበት ጥሪ ምንም አይሰጥም። አልፎ አልፎ በሚጠራበት ጥሪ ግን የሚሰጠው መልካም ነገር በእርግጥ አለው። ወደ ክንፎቹ ሊመጡ ለሚወዱም ጥሪ አለው፤ ሊጠብቃቸውም ክንፎቹን ይዘረጋል። ነፍሳቸውን ሊጎዱ ከሚችሉ ሰዎች ሰዎችን የሚያስጠነቅቅበት ጩኸትም አለው። እኔ ምሳሌዎችን የምመርጠው ከዕለት ኑሮ ነው። ከራሳችሁ ሕይወት ጋር ሳገጥማቸው ለመረዳት አይከብዷችሁምና። ይህን ሁሉ እንዳሳያችሁ የሚገፋፋኝ ለነፍሳችሁ ያለኝ ፍቅር ነው።»
ክርስቲያና፦ እባክህ ሌላም አሳየን።
ከዚያም ተርጓሚው ስንዴና እህል ወደ ተዘራበት እርሻው ወሰዳቸው። ሲመለከቱ ግን ዛላዎቹ ተቈርጠው ነበር፤ ከገለባው በቀር ምንም አልቀረም።
ተርጓሚው፦ በዚህ አዝመራ ምን እናድርግ?
ክርስቲያና፦ ከፊሉን አቃጥለው፤ የቀረውን ደግሞ መሬቱን ለማዳበር ተጠቀምበት።
ተርጓሚው፦ አያችሁ፣ የምትፈልጉት ፍሬ ነው። ፍሬ ስለሌለው አዝመራውን ሁሉ ትጥላላችሁ። በዚህ ነገር በራሳችሁ ላይ ፍርድ እንዳታመጡ ተጠንቀቁ። በፍሬ ማለቴ ሥራ ማለቴ ነውና።
ወደ ቤት ሲመለሱ ማዕዱ ገና አልቀረበም ነበር። ስለዚህ ክርስቲያና ተርጓሚውን ሌሎች ነገሮችን እንዲያሳያቸው ወይም እንዲነግራቸው ለመነችው።
ተርጓሚው፦ ሰው ጤናው በጠነከረ መጠን ለኃጢአት ይበልጥ ያዘነብላል። ዐሣማ በወፈረች መጠን ጭቃን ይበልጥ ትወዳለች። ለአንድ ዓመት ሙሉ ከመትጋት ይልቅ አንድ ወይም ሁለት ሌሊት ነቅቶ ማደር ይቀላል። እንዲሁም እስከ መጨረሻ ከመጽናት ይልቅ በመልካም መጀመር ይቀላል። አንድ ቀዳዳ መርከብን ያሰጥማል፤ አንድ ኃጢአትም የሰውን ነፍስ ይገድላል። ሰው በመልካም ሊኖር ቢወድድ የመጨረሻ ቀኑን ያስብ።
ክርስቲያና፣ ምሕረትና ልጆቹ ሌሊቱን በደንብ ካረፉ በኋላ ከፀሐይ ጋር ተነሡ፤ ሊሄዱም ተዘጋጁ። ተርጓሚው ግን ትንሽ እንዲቆዩ ነገራቸው። «ከዚህ የምትሄዱት በሥርዓቱ መሠረት መሆን አለበት፤ የዚህ ቤት ሕግ እንዲህ ነውና» አላቸው።
ከዚያም ንጽሕትን ወደ መታጠቢያው እንድትወስዳቸውና በዚያ አቧራውን እንድታጥብላቸው ነገራት። ይህ ከሆነ በኋላ ታድሰውና በርትተው ወጡ። ተርጓሚውም እንዳለው «እንደ ጨረቃ የተዋቡ» ሆኑ።
ቀጥሎም በአጠገቡ ያሉትን ማኅተሙን እንዲያመጡ አዘዛቸው። ባመጡትም ጊዜ በሄዱበት ስፍራ ሁሉ እንዲታወቁ ምልክቱን በእነርሱ ላይ አደረገ።
ከዚያም ተርጓሚው «ልብስ አምጡላቸው» አለ። እነርሱም እንደ በረዶ ነጭ የሆነ ልብስ ለበሱ። እያንዳንዳቸው ሌሎቹ በዚያ ደማቅ ብርሃን ሲያበሩ ባዩ ጊዜ ተደነቁ።
ከዚያም ተርጓሚው ታላቅ ልብ የተባለውን ከአገልጋዮቹ አንዱን አስጠራ። የብረት ጥሩር እንዲለብስ፣ ሰይፍና ጋሻም እንዲይዝ አዘዘው። ሊያርፉበት ወደሚችሉበት ውቡ ቤት ወደሚባለው ስፍራ እንዲወስዳቸውም ነገረው።
ተርጓሚውም ለእያንዳንዳቸው መልካም ምኞቱን ገልጾ ተሰናበታቸው። እነርሱም መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ እንዲህም እያሉ ዘመሩ፦
«ጌታ ሆይ፣ እንድተጋና እንድጸልይ አንቃኝ፤ ልቤንም ከኃጢአት አንጻ፤ መስቀሌን ዕለት ዕለት እንድሸከም፣ ጌታንም በፍርሃት እንዳገለግል አድርገኝ።»
ቀጥሎም የክርስቲያን ሸክም በመቃብሩ ውስጥ ወደ ጠፋበት ስፍራ ደረሱ። በዚያም ቆም አሉ። ሕይወታቸውን ለማዳን ሕይወቱን የሰጠውንም አመሰገኑ። ከዚያም ኮረብታውን መውጣት ጀመሩ። ኮረብታው እጅግ ዳገታማ ነበር፤ ድካሙም ክርስቲያናን አስለከለካት።
እርሷም «ከነፍሳቸው ይልቅ ዕረፍትን የሚወዱ ሰዎች ከዚህ ይልቅ የሚቀል መንገድ እንደሚመርጡ እንዴት እንጠራጠራለን?» አለች።
ከዚያም ምሕረት «ምንም ይምጣ፣ ትንሽ ማረፍ አለብኝ» አለች።
ከልጆቹ ሁሉ ታናሹ ያዕቆብም አለቀሰ።
ታላቅ ልብም «ኑ፣ ኑ! እዚህ አትቀመጡ። ልዑሉ ያስቀመጠው መቀመጫ በአጠገባችን አለና» አለ። ይህንም ብሎ ትንሹን ልጅ በእጁ ይዞ ወደዚያ ወሰደው። ሁሉም በመቀመጣቸውና ከፀሐዩ ሙቀት በመዳናቸው ደስ አላቸው።
ከዚያም ምሕረት እንዲህ አለች፦ «ለሚሠሩ ሰዎች ዕረፍት እንዴት ጣፋጭ ነው! እንደ እኛ ያሉ ሰዎች እንዲያርፉ ይህን መቀመጫ በዚህ ያስቀመጠው ልዑሉ እንዴት ቸር ነው! ስለዚህ ስፍራ ብዙ ሰምቻለሁ። ነገር ግን እንዳንተኛ እንጠንቀቅ፤ ይህ ቀድሞ ምስኪኑን ክርስቲያንን ብዙ አስከፍሎታልና።»
ምዕራፍ 12 ተጠናቋል
የተርጓሚው ቤት