የመንገደኛው ጉዞ በቀላል ቃላት
ወንዙና ወርቃማዪቱ ከተማ

ምዕራፍ 10 · 7 ደቂቃ ንባብ · 9 ደቂቃ ማዳመጥ

ወንዙና ወርቃማዪቱ ከተማ

ከዚያም ተኛሁ፤ እንደ ገናም ሕልም አለምሁ። ክርስቲያንና ተስፈኛ ወደ እነዚያ ኮረብቶች ግርጌ ሲወርዱ አየሁ። በዚያ የትምክሕት አገር አለ። ይህም አገር በአንዲት ትንሽ የጎን መንገድ ወደ ጽዮን ተራራ ከሚወስደው መንገድ ጋር ይገናኛል። በዚያም አላዋቂ የተባለ አንድ ፍልቅልቅ ወጣት አገኙ። ክርስቲያንም «ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሄዳለህ?» አለው።

አላዋቂ፦ ጌታዬ ሆይ፣ የተወለድሁት ወደዚያ በግራ በኩል ባለው አገር ነው። ወደ ሰማያዊቱ ከተማ መሄድ እፈልጋለሁ።

ክርስቲያን፦ በበሩ እንዴት ለመግባት ታስባለህ?

አላዋቂ፦ ሌሎቹ የዓለም ሰዎች ሁሉ በሚገቡበት መንገድ።

ክርስቲያን፦ ታዲያ በዚያ በር እንድታልፍ የምታሳየው ምን አለህ?

አላዋቂ፦ የጌታዬን ፈቃድ አውቃለሁ፤ መልካም ኑሮም ኖሬአለሁ። ለያዝሁት ነገር ሁሉ ዋጋውን እከፍላለሁ። አሥራት አወጣለሁ፤ ለድሆችም ምጽዋት እሰጣለሁ። ወደምሄድበት አገር ለመሄድም የገዛ አገሬን ትቻለሁ።

ክርስቲያን፦ ነገር ግን በዚህ መንገድ መጀመሪያ ባለው በር አልገባህም፤ የገባኸው በትንሽ የጎን መንገድ ነው። ስለዚህ ስለ ሠራኸው ሁሉ መልካም ብታስብም፣ ጊዜው በደረሰ ጊዜ «ሌባ ነህ» ተብለህ እንዳትከሰስ እፈራለሁ። ስለዚህም አትገባም።

አላዋቂ፦ እንግዲህ እኔ አላውቃችሁም። እናንተ በራሳችሁ እምነት ጽኑ፤ እኔም በራሴ እምነት እጸናለሁ። ሁሉ መልካም እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ስለምታወሩት በር ደግሞ፣ ከአገራችን እጅግ የራቀ መሆኑን ዓለም ሁሉ ያውቃል። በአካባቢያችን ሁሉ ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ የሚያውቅ አንድ ሰው እንኳ ያለ አይመስለኝም። ማወቅም ለምን እንደሚያስፈልገው አይገባኝም። እንደምታዩት ከአገራችን የሚወርድ ያማረ ለምለም የጎን መንገድ በሚቀጥለው መታጠፊያ ላይ አለንና።

ክርስቲያን ተስፈኛን በለሆሳስ እንዲህ አለው፦ «ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው።»

ተስፈኛ፦ ከፈለግህ እንለፈው። ምናልባት በኋላ መስማት ሲችል እናነጋግረዋለን።

ስለዚህ ጉዞአቸውን ቀጠሉ። አላዋቂም ጥቂት ርቆ በኋላቸው ይከተል ነበር። ከዚያም ከሚሄዱበት መንገድ ሌላ መንገድ ተገንጥሎ ሲወጣ አዩ። ከሁለቱ መንገዶች የትኛውን እንደሚይዙ አላወቁም።

ቆመው ሲያስቡ፣ ቆዳው ጥቁር የሆነ ነገር ግን ነጭ ልብስ የለበሰ አንድ ሰው ወደ እነርሱ መጥቶ «ለምን እዚህ ቆማችኋል?» አላቸው። እነርሱም ወደ ሰማያዊቱ ከተማ እየሄዱ እንደ ሆኑ ነገሩት፤ ነገር ግን ከሁለቱ መንገዶች የትኛውን እንደሚይዙ እንዳላወቁ ነገሩት።

ሰውየውም «እንግዲያስ ተከተሉኝ፤ እኔም ወደዚያ መሄዴ ነውና» አለ።

ስለዚህ ከእርሱ ጋር ሄዱ። ነገር ግን መንገዱ መታጠፉ ግልጽ ነበር። ብዙም ሳይቆዩ ጀርባቸውን ወደ ሰማያዊቱ ከተማ እያዞሩ እንደ ሆነ አወቁ።

ብዙም ሳይቆይ ክርስቲያንና ተስፈኛ ሁለቱም በመረብ ተያዙ፤ ምን እንደሚያደርጉም አላወቁም። በዚያን ጊዜ ነጩ ልብስ ከጥቁሩ ሰው ጀርባ ላይ ወደቀ።

ያን ጊዜ የት እንዳሉ አዩ። ስለዚህ በዚያው ተቀምጠው አለቀሱ።

ክርስቲያን፦ በጎቻቸውን ከሚጠብቁት ከአራቱ እረኞች አንዱ ሸንጋዩ ለእግሮቻችን መረብ እንዳይዘረጋብን እንድንጠነቀቅ አልነገረንምን?

ተስፈኛ፦ እነዚያ እረኞች የመንገዱን መግለጫ ጽሑፍም ሰጥተውን ነበር። እኛ ግን አላነበብነውም፤ ስለዚህ በትክክለኛው መንገድ አልሄድንም። እንዲህም እያለቀሱና እያቃሰቱ በመረቡ ውስጥ ተኙ።

በመጨረሻም አንድ የሚያበራ ሰው በእጁ ከቀጭን ገመድ የተሠራ ጅራፍ ይዞ ወደ እነርሱ ሲመጣ አዩ። እርሱም «እዚህ ምን ታደርጋላችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ?» አላቸው።

እነርሱም ወደ ጽዮን ለመሄድ እንደሚፈልጉ ነገሩት። ነገር ግን ነጭ ካባ የለበሰ አንድ ጥቁር ሰው ከመንገድ እንዳሳታቸው ነገሩት። ያ ሰው ወደዚያው ስፍራ እንደሚሄድ ተናግሮ መንገዱን እንደሚያሳያቸው ነግሯቸው ነበር።

እርሱም «ይህ ሸንጋይ ነው። ለጊዜው የሚያበራ ሰው ልብስ የለበሰ ሐሰተኛ ሰው ነው» አለ።

ስለዚህ መረቡን ቀደደና ሰዎቹን አወጣቸው። ከዚያም እንደ ገና በትክክለኛው መንገድ ላይ ያቆማቸው ዘንድ እንዲከተሉት ነገራቸው። «ትናንት ሌሊት የት ነበራችሁ?» ብሎ ጠየቃቸው።

እነርሱም «ደስ በሚያሰኙ ተራሮች ላይ በጎቻቸውን ከሚጠብቁ እረኞች ጋር ነበርን» አሉ።

እርሱም «ታዲያ ግራ በገባችሁ ጊዜ ጽሑፋችሁን ለምን አላነበባችሁም?» አላቸው።

እነርሱም ይህን እንዳላሰቡት ነገሩት።

ከዚያም በሕልሜ እንዲህ አየሁ፦ እንዲጋደሙ አዘዛቸው። የሚሄዱበትን መልካም መንገድ ሊያስተምራቸውም አጥብቆ ገረፋቸው። «የምወዳቸውን እንዲህ አደርጋቸዋለሁ» አለ።

ስላስተማራቸውም ነገር አመሰገኑት። በትክክለኛውም መንገድ የደስታ መዝሙር እየዘመሩ ኮረብታውን ወጡ።

በመጨረሻም አየሩ ሰዎችን የሚያስተኛ ወደሆነ ምድር ደረሱ። በዚያም የተስፈኛ ዓይኖች ከበዱ። እርሱም «እዚህ ተጋድመን ትንሽ እንተኛ» አለ።

ክርስቲያን፦ ፈጽሞ አይሆንም፤ ተኝተን ዳግመኛ እንዳንነቃ።

ተስፈኛ፦ ወዳጄ ክርስቲያን ሆይ፣ ቀኑን ሙሉ ለደከመ ሰው እንቅልፍ ጣፋጭ ነው።

ክርስቲያን፦ በጎቹን ከሚጠብቁት እረኞች አንዱ ከተደገመበት ምድር እንድንጠነቀቅ እንደ ነገረን አታስታውስምን? ይህን ያለው እንዳንተኛ እንድንጠነቀቅ ነው። ስለዚህ አናንቀላፋ፤ ነገር ግን እንንቃ።

ተስፈኛ፦ ጥፋተኛ መሆኔን አያለሁ።

ክርስቲያን፦ እንግዲያውስ እንቅልፍ ከዓይናችን እንዲርቅ፣ እየሄድን ሳለ አንድ ነገር ልጠይቅህ። አሁን የምታደርገውን ማድረግ መጀመሪያ እንዴት ጀመርህ?

ተስፈኛ፦ መጀመሪያ ስለ ነፍሴ መልካም ማሰብ እንዴት እንደ ጀመርሁ ማለትህ ነውን?

ክርስቲያን፦ አዎን።

ተስፈኛ፦ ለረጅም ጊዜ በከንቱነት ገበያ የሚታዩትና የሚሸጡት ነገሮች ታላቅ ደስታ ይሰጡኝ ነበር።

ክርስቲያን፦ የምትለው ምን ዓይነት ነገሮችን ነው?

ተስፈኛ፦ በዚህ ሕይወት ደስ የሚያሰኙ ነገሮችን ሁሉ ነው፤ እንደ ውሸት፣ መሐላና ስካር። በአጭሩ ራስን መውደድንና ነፍስን የሚገድሉ ነገሮችን ሁሉ። ነገር ግን የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ሞት እንደ ሆነ ከአንተና ከታማኝ ሰማሁ።

እንዲህም እያወሩ መንገዳቸውን ቀጠሉ።

ነገር ግን በሕልሜ አየሁ፤ በዚህ ጊዜ ክርስቲያንና ተስፈኛ የተደገመበትን ምድር አልፈው ወደ ቤዩላ ምድር ደርሰው ነበር። በዚያ አየሩ ጣፋጭ ነው። መንገዳቸው በዚህ ምድር በኩል ስለ ነበረ ለመውጣት አልቸኮሉም። በዚህ ቀኑን ሙሉ የወፎችን ዝማሬ ይሰሙ ነበር፤ ፀሐይም ቀንና ሌሊት ታበራ ነበር። የሞት ሸለቆ በግራ በኩል ነበረ። ይህ ምድር ግዙፉ ተስፋ ቆራጭ ሊደርስበት አይችልም ነበር። ከዚህ ስፍራ የጥርጣሬ ምሽግን እንኳ ማየት አይችሉም ነበር።

አሁን ጽዮንን ማየት ይችሉ ነበር። በዚህም አንዳንድ የሚያበሩ ሰዎች ሊቀበሏቸው መጡ። ደግሞም በጽዮን የሚኖሩትን ሰዎች ድምፅ ሰሙ፤ ይህንም የደስታ ምድር በደንብ አዩ። ከተማይቱ ልዩ ልዩ ቀለም ካላቸው ውድ ዕንቁዎች የተሠራች ነበረች፤ መንገዶቿም በወርቅ የተነጠፉ ነበሩ። በክርስቲያን ላይ ያበራው ብርሃን እጅግ ደማቅ ስለ ነበረ ሊቋቋመው አልቻለም፤ ታመመም። ተስፈኛም እንዲሁ ታመመ። ስለዚህ ለጥቂት ጊዜ ተኝተው አለቀሱ፤ ደስታቸው ከአቅማቸው በላይ ነበረና።

በመጨረሻም ቀስ በቀስ ወደ ጽዮን ቀረቡ፤ በሮቹም ወለል ብለው ተከፍተው አዩ።

በመንገዱ ላይ አንድ ሰው ቆሞ ነበር። ክርስቲያንና ተስፈኛ «እነዚህ የወይን ተክሎችና አዝመራዎች የማን ናቸው?» ብለው ጠየቁት።

እርሱም የንጉሡ እንደ ሆኑ ነገራቸው። በመንገዱ ለሚሄዱት ደስታ እንዲሰጡ በዚያ እንደ ተተከሉም ነገራቸው። የወደዱትን ፍሬ እንዲበሉ ፈቀደላቸው፤ የንጉሡን የአትክልት መንገዶች ሊያሳያቸውም ወሰዳቸው። በዚያም ተኙ።

ከዚያም በሕልሜ አየሁ፤ በመንገዳቸው ሁሉ ከተናገሩት ይልቅ በእንቅልፋቸው ብዙ ተናገሩ። በዚህም ተደነቅሁ። ሰውየው ግን «ለምን በዚህ ትደነቃለህ? የዚህ ወይን ፍሬ ጭማቂ እጅግ ጣፋጭ ስለሆነ የተኙትን ሰዎች ከንፈሮች ያናግራል» አለኝ።

ከዚያም ሲነቁ ወደ ጽዮን ለመውጣት እጅግ እንደ ፈለጉ አየሁ። ነገር ግን ቀደም ብዬ እንዳልሁት፣ ከንጹሕ ወርቅ ከተሠራችው ከሰማያዊቱ ከተማ እጅግ ደማቅ ብርሃን ያበራ ነበር። ስለዚህ ለዚህ ተብሎ በተሠራ መነጽር ካልሆነ በቀር ገና ሊመለከቷት አልቻሉም።

ሲሄዱም ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎችን አገኙ። የሁለቱም ፊት እንደ ብርሃን ያበራ ነበር።

እነዚህ ሰዎች «ከወዴት መጣችሁ?» ብለው ጠየቁ። በተነገራቸውም ጊዜ «አንድ የቀራችሁ ነገር ብቻ ነው፤ እርሱም ከባድ ነው። ከዚያም በኋላ ጽዮን ትገባላችሁ» አሉአቸው።

ክርስቲያንና ተስፈኛም ሁለቱ ሰዎች አብረዋቸው እንዲሄዱ ለመኑአቸው፤ እነርሱም አብረዋቸው ሄዱ። ነገር ግን «የምትደርሱት በገዛ እምነታችሁ ነው» አሉአቸው።

በእነርሱና በበሩ መካከል ሰፊና ጥልቅ የሆነ ኃይለኛ ወንዝ ነበረ። ድልድይም አልነበረውም። ክርስቲያንና ተስፈኛ ወንዙን በማየት ብቻ ደንግጠው መንቀሳቀስ አቃታቸው።

አብረዋቸው የሄዱት ሰዎች ግን «በዚህ ወንዝ ውስጥ ካላለፋችሁ በቀር ወደ በሩ መድረስ አትችሉም» አሉአቸው።

ምስኪኑ ክርስቲያንም «ወደ በሩ የሚወስድ ከዚህ ሌላ መንገድ የለምን?» አለ።

እነርሱም «አለ፤ ነገር ግን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በዚያ መንገድ የሄዱት ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው፤ እነርሱም ሄኖክና ኤልያስ ናቸው» አሉ።

ክርስቲያንና ተስፈኛ እንደ ገና ወንዙን ሲመለከቱ ልባቸው በፍርሃት ቀለጠ። ማዕበሉን እጅግ ፈርተው ወዲያና ወዲህ ተመለከቱ። ቢሆንም ወደ ጽዮን የሚወስደው መንገድ በዚህ ወንዝ ውስጥ ነበረ። ክርስቲያንም «የወንዙ ጥልቀት በሁሉ ስፍራ አንድ ነውን?» ብሎ ጠየቀ። አንድ እንዳልሆነ ተነገረው፤ ነገር ግን ይህ ምንም እንደማይረዳው ተነገረው። በስፍራው ንጉሥ ባለው እምነት መጠን ወንዙ ጥልቅ ወይም ጥልቀት የሌለው ሆኖ ያገኘዋልና። ስለዚህ ወደ ወንዙ ገቡ። ክርስቲያን ግን ወደ መልካሙ ወዳጁ ወደ ተስፈኛ ጮኾ «ማዕበሎቹ ራሴን ከበቡኝ፤ እየሰመጥሁ ነው» አለ። ተስፈኛም «አይዞህ፤ እግሮቼ የወንዙን ታች ይሰማቸዋል፤ መልካምም ነው» አለ።

ክርስቲያን ግን «ወይ ተስፈኛ ሆይ፣ የሞት ጣር ያዘኝ፤ ወደምናፍቀው ምድር አልደርስም» አለ። ይህንንም ሲል ደመና ዓይኖቹን ሸፈነ፤ ማየትም አልቻለም።

ተስፈኛ የክርስቲያንን ራስ ከውኃው በላይ ለማቆየት እጅግ ደከመ። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያን ፈጽሞ ይሰምጥ ነበር፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ግማሽ ሞቶ እንደ ገና ብቅ ይል ነበር።

ከዚያም ተስፈኛ «ወዳጄ ሆይ፣ ይህ ሁሉ የመጣብህ እግዚአብሔር ያደረገልህን ሁሉ ታስታውስ እንደ ሆነ፣ በልብህም በእርሱ ተደግፈህ ትኖር እንደ ሆነ ሊፈትንህ ነው» አለ።

ተስፈኛም በእነዚህ ቃላት ክርስቲያን በጥልቅ ሐሳብ ውስጥ እንደ ገባ አየ። ስለዚህ «አይዞህ፤ ክርስቶስ ይፈውስሃል» አለው።

ከዚያም ክርስቲያን በታላቅ ድምፅ ጮኾ «ኦ፣ አየዋለሁ! ይናገረኛልም፤ ‹በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ› ይለኛል» አለ።

በዚያን ጊዜ ሁለቱም ብርታት አገኙ። ወንዙም እንደ ድንጋይ ጸጥ አለ። ክርስቲያንም የወንዙን ታች በእግሩ ተሰማው፤ ተሻግሮም መሄድ ቻለ። እንዲህም ወደ ማዶው ዳር ደረሱ። በዚያም የሚያበራ ልብስ የለበሱት ሁለቱ ሰዎች ይጠብቋቸው ነበር። ልብሳቸውም በወንዙ ውስጥ ቀረ።

ጽዮን በገደላማ ኮረብታ ላይ እንደ ነበረች ልብ በል። ቢሆንም ክርስቲያንና ተስፈኛ በቀላሉና በፍጥነት ወጡ፤ ሁለቱ ሰዎች እጆቻቸውን ይዘው ይመሩአቸው ነበርና።

ኮረብታው በሰማይ ውስጥ ቆሞ ነበር፤ መሠረቱ በዚያ ነበረና። ስለዚህ ደስ የሚያሰኝ ንግግር እየተነጋገሩ በአየር ውስጥ ወጡ። የሚያበሩት ሰዎች ስለ ስፍራው ደስታ ነገሩአቸው። ደስታው በምንም አንደበት ሊነገር የማይችል እንደ ሆነ አሉ። በዚያም የሕይወትን ዛፍ እንደሚያዩ፣ ከፍሬውም እንደሚበሉ ነገሩአቸው።

እነርሱም እንዲህ አሉ፦ «ወደዚያ በደረሳችሁ ጊዜ ነጭ ልብስ ትለብሳላችሁ፤ ከቀን ወደ ቀንም ለዘላለም ከንጉሡ ጋር ትነጋገራላችሁ። በምድር ላይ ያያችኋቸውን ነገሮች፣ ማለትም ጭንቀትንና ችግርን፣ ኀዘንንና ሞትን በዚያ አታዩም። አሁን ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ለመሆን ትሄዳላችሁ።»

ክርስቲያንና ተስፈኛ፦ በዚያ ምን እናደርጋለን?

እነርሱም እንዲህ አሉ፦ «ስለ ድካማችሁ ሁሉ ዕረፍት፣ ስለ ኀዘናችሁም ሁሉ ደስታ ታገኛላችሁ። የዘራችሁትን ታጭዳላችሁ — በመንገድ ላይ ስለ ንጉሡ ያፈሰሳችሁትን እንባ ሁሉ ፍሬ። በዚያ ስፍራ የወርቅ አክሊል ትደፋላችሁ፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውንም ሁልጊዜ ታያላችሁ። በዚያም በፍቅር፣ በደስታ እልልታና በምስጋና መዝሙር ታገለግሉታላችሁ።»

ወደ በሩ እየቀረቡ ሳሉ፣ እነሆ፣ ብዙ ቅዱሳን ሊቀበሏቸው መጡ። ሁለቱ የሚያበሩ ሰዎችም እንዲህ አሏቸው፦ «እነዚህ በዓለም ሳሉ ጌታችንን የወደዱና ስለ ስሙ ሁሉን የተዉ ሰዎች ናቸው። ገብተው ጌታቸውን በደስታ እንዲያዩ በመንገዳቸው እንድናመጣቸው ጌታ ላከን።»

ከዚያም ሠራዊቱ ሁሉ በታላቅ እልልታ ከየአቅጣጫው ከበቧቸው (የሚጠብቋቸው ይመስል)። ስለዚህ ለክርስቲያንና ለተስፈኛ ጽዮን ሁሉ ልትቀበላቸው የወረደች መሰለ።

ክርስቲያንና ተስፈኛ በበሩ በገቡ ጊዜ ታላቅ ለውጥ ሆነባቸው፤ እንደ ወርቅ የሚያበራ ልብስ ለበሱ። በገናዎችንና አክሊሎችን ይዘው የመጡ የሚያበሩ ሠራዊት ነበሩ፤ እነርሱም «ወደ ጌታችሁ ደስታ ግቡ» አሏቸው። ከዚያም በጽዮን ያሉ ደወሎች ሁሉ ሲደወሉ ሰማሁ።

በሮቹ ሰዎቹ እንዲገቡ ወለል ብለው በተከፈቱ ጊዜ ጽዮንን አየኋት። እንደ ፀሐይ ታበራ ነበር። መሬቷ ወርቅ ነበረ። በዚያ የሚኖሩት ሰዎች ፊታቸው በፍቅር የተሞላ ነበረ፤ በራሳቸው አክሊል፣ በእጆቻቸውም የዘንባባ ዝንጣፊ ነበረ። በአንድ ድምፅም የምስጋና እልልታ ያሰሙ ነበር።

ከዚያም በሮቹ እንደ ገና ተዘጉ። እኔም ደግሞ ይህን ደስታ ለመካፈል ገብቼ ቢሆን ብዬ ተመኘሁ። ከዚያም ነቃሁ፤ እነሆ ሕልም ነበረ።

ገጽ 1 / 1 · 7 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ