ምዕራፍ 3 · 10 ደቂቃ ንባብ · 13 ደቂቃ ማዳመጥ
እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ያጸድቃል
ይህ መልእክት ለአንተ ነው። ጥቅሱን በሮሜ መልእክት በአራተኛው ምዕራፍ በአምስተኛው ቍጥር ታገኘዋለህ፦
ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል።
ትኩረትህን ወደ እነዚህ ቃላት እንድትመልስ እጠይቅሃለሁ፦ «ኃጢአተኛውን የሚያጸድቅ።» እነዚህ ቃላት እጅግ አስደናቂ ቃላት ይመስሉኛል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ኃጢአተኛውን የሚያጸድቅ» የሚል እንዲህ ያለ አነጋገር መገኘቱ አያስደንቅህምን? የመስቀልን ትምህርቶች የሚጠሉ ሰዎች እግዚአብሔር ክፉ ሰዎችን እንደሚያድንና ከርኩሳን እጅግ የከፉትን ወደ ራሱ እንደሚቀበል በእርሱ ላይ እንደ ክስ እንደሚያቀርቡት ሰምቻለሁ። ይህ የመጽሐፍ ቃል ክሱን እንዴት እንደሚቀበለውና በግልጥ እንደሚናገረው ተመልከት! በአገልጋዩ በጳውሎስ አፍ፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት፣ «ኃጢአተኛውን የሚያጸድቅ» የሚለውን ስም ለራሱ ይወስዳል። ዓመፀኞችን ጻድቃን ያደርጋቸዋል፤ ቅጣት የሚገባቸውን ይቅር ይላቸዋል፤ ምንም ሞገስ የማይገባቸውንም ሞገስ ያደርግላቸዋል። መዳን ለመልካሞች፣ የእግዚአብሔርም ጸጋ ከኃጢአት ነጻ ለሆኑት ለንጹሓንና ለቅዱሳን እንደ ሆነ አስበህ ነበር፤ አይደለምን? ብትበልጥ እግዚአብሔር ዋጋህን እንደሚሰጥህ በአእምሮህ ገብቶአል፤ የተገባህ ስላልሆንህም ሞገሱን የምታገኝበት መንገድ ሊኖር እንደማይችል አስበሃል። እንግዲህ «ኃጢአተኛውን የሚያጸድቅ» እንደሚለው ያለ ጥቅስ ስታነብ በመጠኑ መደነቅህ አይቀርም። መደነቅህ አያስገርመኝም፤ እኔ ከእግዚአብሔር ታላቅ ጸጋ ጋር ይህን ያህል ብተዋወቅም ከመደነቅ ፈጽሞ አላቋርጥምና። ቅዱስ አምላክ ቅዱስ ያልሆነን ሰው ማጽደቅ መቻሉ በእርግጥ አስደናቂ ይመስላል፤ አይደለምን? እኛ በልባችን በተፈጥሮ ባለው ሕግ አጥባቂነት ዘወትር ስለ ራሳችን በጎነትና ስለ ራሳችን ብቃት እንናገራለን፤ የእግዚአብሔርን ትኩረት ለማግኘት በእኛ ውስጥ አንዳች ነገር ሊኖር ይገባል ብለን በግትርነት እንይዛለን። እንግዲህ ማታለያን ሁሉ አልፎ የሚያይ እግዚአብሔር በእኛ ዘንድ ምንም ዓይነት በጎነት እንደሌለ ያውቃል። «ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥» ይላል። «ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ» እንደ ሆነ ያውቃል፤ ስለዚህም ጌታ ኢየሱስ ወደ ዓለም የመጣው በእኛ ዘንድ በጎነትንና ጽድቅን ሊፈልግ አይደለም፤ ነገር ግን እነርሱን ፈጽሞ ለሌላቸው ሰዎች ሊሰጣቸው ነው። የሚመጣው ጻድቃን ስለ ሆንን ሳይሆን ጻድቃን ሊያደርገን ነው፤ ኃጢአተኛውን ያጸድቃል።
ጠበቃ ወደ ፍርድ ቤት ሲመጣ፣ ሐቀኛ ሰው ከሆነ፣ የንጹሕን ሰው ጉዳይ ሊከራከርለትና በሐሰት ከተከሰሰበት ነገር በፍርድ ቤቱ ፊት ሊያጸድቀው ይመኛል። የጠበቃው ዓላማ ንጹሑን ሰው ማጽደቅ ሊሆን ይገባዋል፤ በደለኛውን ወገን ሊሸፍን መሞከር የለበትም። በደለኛውን በእውነት ማጽደቅ በሰው መብትም ሆነ በሰው ኃይል ውስጥ አይደለም። ይህ ለጌታ ብቻ የተጠበቀ ተአምር ነው። ወሰን የሌለው ጻድቅ ገዢ የሆነው እግዚአብሔር መልካምን የሚያደርግ ኃጢአትንም የማይሠራ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ እንደሌለ ያውቃል፤ ስለዚህም በመለኮታዊ ባሕርዩ ወሰን በሌለው ሉዓላዊነትና ሊነገር በማይችለው ፍቅሩ ክብር ጻድቃንን ከማጽደቅ ይልቅ ኃጢአተኞችን የማጽደቁን ሥራ በራሱ ላይ ይወስዳል። እግዚአብሔር ኃጢአተኛው ሰው በፊቱ በፍትሕ ተቀባይነት አግኝቶ የሚቆምበትን መንገድና ዘዴ አዘጋጅቶአል፤ በደለኛውን ሰው ዕድሜውን ሙሉ ከበደል ነጻ እንደ ነበረ አድርጎ፣ እንዲያውም ከኃጢአት ፈጽሞ ነጻ እንደ ሆነ አድርጎ በፍጹም ፍትሕ የሚያስተናግድበትን ሥርዓት መሥርቶአል። ኃጢአተኛውን ያጸድቃል።
ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ። ይህ እጅግ አስደናቂ ነገር ነው — ከሁሉ ይበልጥ በሚያገኙት ሰዎች ዘንድ ሊደነቅበት የሚገባ ነገር ነው። እግዚአብሔር እኔን ማጽደቁ እስከ ዛሬ ድረስ ለእኔ ከሰማሁት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ድንቅ እንደ ሆነ አውቃለሁ። ከሁሉን ቻይ ፍቅሩ ተለይቼ ስመለከት ራሴን የብቃት ማጣት ጓዝ፣ የርኩሰት ክምችት፣ የኃጢአትም ክምር እንደ ሆንሁ ይሰማኛል። በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት እንደ ጸደቅሁ፣ ፍጹም ጻድቅ እንደ ነበርሁ ተደርጌ እንደምስተናገድ፣ የእግዚአብሔር ወራሽና ከክርስቶስ ጋር አብሬ ወራሽ እንደ ተደረግሁ በሙሉ እርግጠኛነት አውቃለሁ፤ ሆኖም በተፈጥሮዬ ቦታዬን ከሁሉ እጅግ ኃጢአተኞች ከሆኑት መካከል ልወስድ ይገባኛል። ምንም የማይገባኝ እኔ የሚገባኝ እንደ ነበርሁ ተደርጌ እስተናገዳለሁ። ቀድሞ እግዚአብሔርን የማልፈራ ሆኜ ሳለሁ፣ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን የምፈራ እንደ ነበርሁ ያህል በታላቅ ፍቅር እወደዳለሁ። በዚህ የማይደነቅ ማን ነው? ለእንዲህ ያለ ሞገስ የሚቀርብ ምስጋና የመደነቅን ልብስ ተጎናጽፎ ይቆማል።
እንግዲህ ይህ እጅግ አስደናቂ ቢሆንም፣ ወንጌልን ለአንተና ለእኔ ምን ያህል የቀረበ እንደሚያደርገው እንድታስተውል እወዳለሁ። እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን የሚያጸድቅ ከሆነ፣ ውድ ወዳጄ ሆይ፣ አንተንም ሊያጸድቅህ ይችላል። አንተስ እንዲህ ያለው ሰው አይደለህምን? በዚህ ሰዓት ያልተለወጥህ ከሆንህ ይህ ለአንተ እጅግ ትክክለኛ መግለጫ ነው፤ ያለ እግዚአብሔር ኖረሃል፤ እግዚአብሔርን ከሚፈራ ሰው ተቃራኒ ሆነሃል፤ በአንድ ቃል፣ እግዚአብሔርን የማይፈራ ኃጢአተኛ ነበርህ፤ አሁንም ነህ። ምናልባት በእሁድ ቀን ወደ አምልኮ ስፍራ እንኳ ሄደህ አታውቅም ይሆናል፤ የእግዚአብሔርን ቀን፣ ቤቱንና ቃሉን ንቀህ ኖረሃል — ይህም እግዚአብሔርን የማትፈራ እንደ ነበርህ ያረጋግጣል። ከዚህም የከፋው፣ የእግዚአብሔርን መኖር እንኳ ለመጠራጠር ሞክረህ፣ እንዲህ ማድረግህንም እስከ መናገር ደርሰህ ይሆናል። የእግዚአብሔር መገኘት ምልክቶች በሞሉባት በዚህች ውብ ምድር ላይ ኖረሃል፤ በዚያ ሁሉ ጊዜ ግን የኃይሉንና የአምላክነቱን ግልጥ ማስረጃዎች እንዳታይ ዓይንህን ጨፍነሃል። እግዚአብሔር እንደሌለ ሆነህ ኖረሃል። በእርግጥም ምንም ዓይነት አምላክ እንደሌለ ለራስህ በእርግጠኛነት ማረጋገጥ ብትችል ኖሮ እጅግ ደስ ባለህ ነበር። ምናልባት እንዲህ ሆነህ ብዙ ዓመታት ኖረህ ይሆናል፤ ስለዚህም አሁን በመንገዶችህ ላይ እጅግ ጸንተሃል፤ ሆኖም ከመንገዶችህ በአንዱም ውስጥ እግዚአብሔር የለም። በአንተ ላይ እንዲህ የሚል ስያሜ ቢለጠፍብህ፦
እግዚአብሔርን የማይፈራ
ባሕር የጨው ውኃ ተብሎ ቢሰየም እንደሚገልጠው ያህል አንተንም በትክክል ይገልጥህ ነበር። አይደለምን?
ምናልባት አንተ ሌላ ዓይነት ሰው ትሆናለህ፤ የሃይማኖትን ውጫዊ ሥርዓቶች ሁሉ በመደበኛነት ፈጽመሃል፤ ሆኖም ልብህ በእነርሱ ውስጥ ፈጽሞ አልነበረም፤ በእውነትም እግዚአብሔርን የማትፈራ ሆነሃል። ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ብትገናኝም ለራስህ ከእግዚአብሔር ጋር ፈጽሞ አልተገናኘህም፤ በመዘምራን ቡድን ውስጥ ነበርህ፤ ሆኖም ጌታን በልብህ አላመሰገንኸውም። በልብህ ለእግዚአብሔር አንዳች ፍቅር፣ በሕይወትህም ለትእዛዛቱ አንዳች ግምት ሳይኖርህ ኖረሃል። እንግዲህ ይህ ወንጌል የተላከለት ሰው አንተ ነህ — እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ያጸድቃል የሚለው ይህ ወንጌል። እጅግ አስደናቂ ነው፤ ደስ የሚያሰኘው ግን ለአንተ የቀረበ መሆኑ ነው። ልክ ለአንተ የሚስማማ ነው። አይደለምን? ምነው ብትቀበለው! ልባም ሰው ከሆንህ እንደ አንተ ላሉት በማዘጋጀቱ የእግዚአብሔርን አስደናቂ ጸጋ ታያለህ፤ ለራስህም እንዲህ ትላለህ፦ «ኃጢአተኛውን ያጸድቃል! እንግዲያስ እኔ ለምን አልጸድቅም? ደግሞስ አሁኑኑ ለምን አልጸድቅም?»
አሁንም ደግሞ ልብ በል፤ እንዲህ መሆኑ ግድ ነው — የእግዚአብሔር መዳን ለማይገባቸውና ምንም ዝግጅት ለሌላቸው ነው። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መቀመጡ ምክንያታዊ ነው፤ ውድ ወዳጄ ሆይ፣ የራሳቸው የሆነ ጽድቅ ከሌላቸው በቀር መጽደቅ የሚያስፈልገው ማንም የለምና። ከአንባቢዎቼ አንዳንዶቹ ፍጹም ጻድቃን ከሆኑ መጽደቅ አያስፈልጋቸውም። ግዴታህን በሚገባ እየፈጸምህ፣ ሰማይንም ባለ ዕዳህ ልታደርገው የቀረብህ ያህል ይሰማሃል። ታዲያ አዳኝ ወይም ምሕረት ምን ያደርግልሃል? መጽደቅስ ምን ያደርግልሃል? እስከ አሁን በመጽሐፌ ሳትሰለች አትቀርም፤ ምንም የሚስብህ ነገር አይኖረውምና።
ከእናንተ አንዳችሁ እንዲህ ያለ የትዕቢት ኩራት የምታሳይ ከሆንህ ለጥቂት ጊዜ አድምጠኝ። በሕይወት መኖርህ እርግጥ እንደ ሆነ መጥፋትህም እንዲሁ እርግጥ ነው። ጽድቃችሁ ሁሉ የገዛ ሥራችሁ ውጤት የሆነ እናንተ ጻድቃን ሰዎች፣ ወይ አታላዮች ወይ የተታለላችሁ ናችሁ፤ መጽሐፍ ሊዋሽ አይችልምና፤ እርሱም «ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥» ብሎ በግልጥ ይናገራል። ያም ሆነ ይህ በራሳቸው ጽድቅ ለሚመኩ የምሰብከው ወንጌል የለኝም፤ አንዲት ቃል እንኳ የለኝም። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ጻድቃንን ሊጠራ አልመጣም፤ እኔም እርሱ ያላደረገውን ላደርግ አልሄድም። ብጠራህ አትመጣም ነበር፤ ስለዚህ በዚያ ማንነትህ አልጠራህም። አይደለም፤ ይልቁንም ያ ጽድቅህ ምን ያህል ሽንገላ እንደ ሆነ እስክታይ ድረስ ተመልከተው እልሃለሁ። ከሸረሪት ድር ግማሽ ያህል እንኳ ጠንካራ አይደለም። ተወው! ሽሽው! ኦ፣ መጽደቅ ሊያስፈልጋቸው የሚችሉት በራሳቸው ጻድቃን ያልሆኑት ብቻ እንደ ሆኑ እመን! በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት ጻድቃን እንዲሆኑ አንዳች ነገር ሊደረግላቸው ያስፈልጋቸዋል። እርግጠኛ ሁን፤ ጌታ የሚያደርገው የሚያስፈልገውን ብቻ ነው። ወሰን የሌለው ጥበብ የማያስፈልገውን ነገር ፈጽሞ አይሞክርም። ኢየሱስ ትርፍ የሆነውን ሥራ ፈጽሞ አይጀምርም። ጻድቅ የሆነውን ጻድቅ ማድረግ ለእግዚአብሔር የሚገባ ሥራ አይደለም — ያ የሞኝ ድካም ይሆን ነበር፤ ዓመፀኛውን ጻድቅ ማድረግ ግን — ያ ወሰን ለሌለው ፍቅርና ምሕረት የሚገባ ሥራ ነው። ኃጢአተኛውን ማጽደቅ — ይህ ለአምላክ የሚገባ ተአምር ነው። በእርግጥም እንዲሁ ነው።
እንግዲህ ተመልከት። በዓለም ላይ በየትም ስፍራ እርግጠኛና ውድ መድኃኒቶችን ያገኘ ሐኪም ቢኖር፣ ያ ሐኪም የሚላከው ወደ ማን ነው? ፍጹም ጤነኞች ወደ ሆኑት ነውን? አይመስለኝም። በሽተኛ ሰው በሌለበት አውራጃ ብታስቀምጠው በቦታው እንዳልሆነ ይሰማዋል። የሚሠራው ምንም ነገር የለም። «ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም።» እንዲሁም የጸጋና የቤዛነት ታላላቅ መድኃኒቶች በነፍሳቸው ለታመሙ እንደ ሆኑ ግልጥ አይደለምን? ለጤነኞች ሊሆኑ አይችሉም፤ ለእነርሱ ምንም ጥቅም ሊሰጡ አይችሉምና። ውድ ወዳጄ ሆይ፣ በመንፈስ እንደ ታመምህ ከተሰማህ ሐኪሙ ለአንተ ወደ ዓለም መጥቶአል። በኃጢአትህ ምክንያት ፈጽመህ የጠፋህ ከሆንህ በመዳን ዕቅድ ውስጥ የታለምኸው አንተው ራስህ ነህ። የፍቅር ጌታ የጸጋን ሥርዓት ባዘጋጀ ጊዜ እንደ አንተ ያሉትን በዓይኑ ፊት ይዞ ነበር እላለሁ። ለጋስ መንፈስ ያለው አንድ ሰው ዕዳ ያለባቸውን ሁሉ ይቅር ለማለት ቢወስን፣ ይህ በእርግጥ ዕዳ ላለባቸው ብቻ እንደሚሠራ ግልጥ ነው። አንዱ አንድ ሺህ ፓውንድ ዕዳ አለበት፤ ሌላው ኀምሳ ፓውንድ ዕዳ አለበት፤ እያንዳንዳቸው ሒሳባቸው ተከፍሎአል ተብሎ እንዲፈረምበት ብቻ ይበቃል፤ ዕዳውም ይደመሰሳል። ነገር ግን እጅግ ለጋስ የሆነው ሰው እንኳ ምንም ዕዳ የሌለባቸውን ሰዎች ዕዳ ይቅር ሊል አይችልም። ኃጢአት በሌለበት ይቅር ማለት ሁሉን ለሚችለው እንኳ አይቻልም። ስለዚህ ይቅርታ ኃጢአት ለሌለብህ ለአንተ ሊሆን አይችልም። ይቅርታ ለበደለኞች መሆን አለበት። ምሕረት ለኃጢአተኞች መሆን አለበት። ይቅርታ የማያስፈልጋቸውን ይቅር ስለ ማለት — ፈጽሞ ያልበደሉትን ምሕረት ስለ ማድረግ — መናገር ሞኝነት ይሆን ነበር።
ኃጢአተኛ ስለ ሆንህ መጥፋት ግድ ይሆንብሃል ብለህ ታስባለህን? ልትድን የምትችልበት ምክንያቱ ይኸው ነው። ራስህን ኃጢአተኛ እንደ ሆንህ ስለምታምን፣ ጸጋ እንደ አንተ ላሉት የተዘጋጀ እንደ ሆነ እንድታምን አበረታታሃለሁ። ከመዝሙር ደራሲዎቻችን አንዱ እንዲህ ለማለት እንኳ ደፍሮአል፦
ኃጢአተኛ የተቀደሰ ነገር ነው፤
መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አድርጎታልና።
ኢየሱስ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን የመጣ መሆኑ በእርግጥ እውነት ነው። ለእውነተኛ ኃጢአተኞች ሞቶ እውነተኛ ስርየት አደረገ። ሰዎች በቃላት ሳይጫወቱ ወይም ለይስሙላ ብቻ ራሳቸውን «ምስኪን ኃጢአተኞች» ብለው ሳይጠሩ ሲቀሩ፣ ከእነርሱ ጋር ስገናኝ እጅግ ደስ ይለኛል። ከእውነተኛ ኃጢአተኞች ጋር ሌሊቱን ሙሉ ብነጋገር ደስ ባለኝ ነበር። የምሕረት እንግዳ ማረፊያ በሩን በእንደነዚህ ላይ ፈጽሞ አይዘጋም — በሳምንቱ ቀናትም ሆነ በእሁድ። ጌታችን ኢየሱስ የሞተው ለምናባዊ ኃጢአቶች አይደለም፤ ነገር ግን የልቡ ደም የፈሰሰው ሌላ ምንም ነገር ሊያስወግደው የማይችለውን ጥልቅ እንደ ደም ቀይ እድፍ ለማጠብ ነው።
ጥቁር ኃጢአተኛ የሆነ — ኢየሱስ ክርስቶስ ነጭ ሊያደርገው የመጣው እንዲህ ያለውን ሰው ነው። አንድ የወንጌል ሰባኪ በአንድ ወቅት «አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል» ከሚለው ጥቅስ ሰበከ፤ ስብከቱም እንዲህ ያለ ስለ ነበረ ከአድማጮቹ አንዱ እንዲህ አለው፦ «ለወንጀለኞች የምትሰብክ ትመስል ነበር። ስብከትህ በአውራጃው ወህኒ ቤት ሊሰበክ ይገባው ነበር።» «ኦ፣ አይደለም» አለ ደጉ ሰው፤ «በአውራጃው ወህኒ ቤት ብሰብክ ኖሮ ከዚያ ጥቅስ አልሰብክም ነበር፤ በዚያ የምሰብከው ‹ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው› ከሚለው ነበር።» ልክ ነው። ሕጉ በራሳቸው ጽድቅ ለሚመኩ ትዕቢታቸውን ሊያዋርድ ነው፤ ወንጌል ደግሞ ለጠፉት ተስፋ መቁረጣቸውን ሊያስወግድ ነው።
ካልጠፋህ አዳኝ ምን ያደርግልሃል? እረኛ ፈጽመው ያልባዘኑትን ሊፈልግ ይሄዳልን? ሴቲቱስ ከቦርሳዋ ፈጽሞ ያልወጡትን የገንዘብ ቍራጮች ለመፈለግ ቤቷን ለምን ትጠርጋለች? አይደለም፤ መድኃኒቱ ለታመሙ ነው፤ ሕያው ማድረግ ለሙታን ነው፤ ይቅርታ ለበደለኞች ነው፤ ነጻ መውጣት ለታሰሩት ነው፤ ዓይን መክፈት ለዕውሮች ነው። ሰዎች በደለኞችና ለፍርድ የተገባቸው ናቸው ከሚለው መነሻ ውጭ አዳኙ፣ በመስቀል ላይ የሞተው ሞቱና የይቅርታው ወንጌል እንዴት ሊብራሩ ይችላሉ? ለወንጌል መኖር ምክንያቱ ኃጢአተኛው ነው። ወዳጄ ሆይ፣ ይህ ቃል አሁን የደረሰህ አንተ፣ የማይገባህ፣ ክፉ የሚገባህ፣ ሲኦልም የሚገባህ ከሆንህ፣ ወንጌሉ የተወሰነለት፣ የተዘጋጀለትና የታወጀለት ዓይነት ሰው አንተ ነህ። እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ያጸድቃል።
ይህን እጅግ ግልጥ ላደርገው እወዳለሁ። አስቀድሜ እንዲህ እንዳደረግሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን ይህን ያህል ግልጥ ቢሆንም ሰውን እንዲያየው ሊያደርገው የሚችል ጌታ ብቻ ነው። ለነቃ ሰው መጀመሪያ ላይ መዳን የጠፋና በደለኛ ለሆነው ለእርሱ በእውነት መሆኑ እጅግ አስገራሚ ይመስለዋል። ንስሐ የገባ ሰው በመሆኑ ለእርሱ መሆን እንዳለበት ያስባል፤ ንስሐው ራሱ የመዳኑ አንድ ክፍል እንደ ሆነ ይዘነጋል። «ኦ፣» ይላል፣ «ነገር ግን እንዲህና እንዲያ መሆን አለብኝ» — ይህ ሁሉ እውነት ነው፤ የመዳን ውጤት ሆኖ እንዲህና እንዲያ ይሆናልና፤ ነገር ግን መዳን የሚመጣለት ከመዳን ውጤቶች አንዳች ከማግኘቱ በፊት ነው። በእርግጥም የሚመጣለት ይህ ባዶ፣ የለማኝ፣ ወራዳና አስጸያፊ መግለጫ — «እግዚአብሔርን የማይፈራ» የሚለው — ብቻ በሚገባው ጊዜ ነው። የእግዚአብሔር ወንጌል ሊያጸድቀው ሲመጣ እርሱ ያ ብቻ ነው።
ስለዚህ በእነርሱ ዘንድ አንዳች መልካም ነገር የሌላቸውን — መልካም ስሜት እንኳ፣ ወይም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስመሰግናቸው አንዳች ነገር እንደሌላቸው የሚፈሩትን — ቸሩ አምላካችን የሚያስመሰግናቸው ምንም ነገር ሳይኖራቸው ሊቀበላቸው፣ እነርሱ መልካም ስለ ሆኑ ሳይሆን እርሱ መልካም ስለ ሆነ ከራሱ ፈቃድ ተነሣሥቶ ይቅር ሊላቸው እንደሚችልና እንደሚፈቅድ አጥብቀው እንዲያምኑ ልለምናቸውን? ፀሐዩን በመልካሞች ላይ እንደሚያወጣ በክፉዎችም ላይ አያወጣምን? ፍሬ የሚሰጡ ወራትን አይሰጥምን? ዝናብንና የፀሐይ ብርሃንን በወቅታቸው እጅግ እግዚአብሔርን በማይፈሩ ሕዝቦች ላይ አይልክምን? አዎን፣ ሰዶም እንኳ ፀሐይዋ ነበራት፤ ገሞራም ጠልዋ ነበራት። ኦ ወዳጄ ሆይ፣ የእግዚአብሔር ታላቅ ጸጋ ከእኔም ከአንተም አስተሳሰብ በላይ ነው፤ ለእርሱ የሚገባውን ታላቅ አሳብ እንድታስብበት እወዳለሁ! ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ የእግዚአብሔርም አሳብ ከአሳባችን እንዲሁ ከፍ ያለ ነው። በብዙ ምሕረት ይቅር ማለት ይችላል። ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ፤ ይቅርታ ለበደለኞች ነው።
ራስህን አስጊጠህ በእውነት ካለህበት የተለየ ሰው ለመምሰል አትሞክር፤ ነገር ግን ኃጢአተኛውን ወደሚያጸድቀው ወደ እርሱ እንዳለህ ና። ከጥቂት ጊዜ በፊት አንድ ታላቅ ሠዓሊ ይኖርባት የነበረችውን ከተማ የአስተዳደር ጉባኤ በከፊል ሥሎ ነበር፤ ለታሪክም ሲል በከተማው በደንብ የታወቁ አንዳንድ ሰዎችን በሥዕሉ ውስጥ ሊያካትት ፈለገ። ጠጕሩ ያልተበጠረ፣ ቡትቶ የለበሰና የቆሸሸ አንድ መንገድ ጠራጊ ነበረ፤ እርሱን ሁሉም ያውቀው ነበር፤ በሥዕሉም ውስጥ ለእርሱ የሚስማማ ቦታ ነበረ። ሠዓሊው ለዚህ ቡትቶ ለባሽና ሻካራ ሰው፦ «ወደ ሥዕል ክፍሌ መጥተህ ምስልህን እንድሥል ብትፈቅድልኝ በደንብ እከፍልሃለሁ» አለው። ሰውዬው በማለዳ መጣ፤ ነገር ግን ወዲያው ተሰናብቶ ተመለሰ፤ ፊቱን ታጥቦ፣ ጠጕሩን አበጥሮ፣ የተከበረ ልብስም ለብሶ ነበርና። የተፈለገው እንደ ለማኝ ሆኖ ነበር፤ በሌላ በማንኛውም ሁኔታ አልተጋበዘም ነበር። እንዲሁም ወንጌል እንደ ኃጢአተኛ ብትመጣ እንጂ በሌላ ሁኔታ ብትመጣ ወደ አዳራሾቹ አይቀበልህም። መታረምን አትጠብቅ፤ ነገር ግን መዳንን ለማግኘት አሁኑኑ ና። እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ያጸድቃል፤ ይህም አሁን ካለህበት ስፍራ ያነሣሃል፤ በከፋው ሁኔታህ ውስጥ ያገኝሃል።
ልብስህን ሳታስተካክል ና። ማለቴ በኃጢአትህና በኃጢአተኝነትህ ሁሉ ወደ ሰማያዊ አባትህ ና። ለምጻም፣ ቆሻሻ፣ ዕራቁት፣ ለመኖርም ሆነ ለመሞት የማትበቃ ሆነህ እንዳለህ ወደ ኢየሱስ ና። አንተ የፍጥረት ጥራጊ የሆንህ፣ ና፤ ከሞት በቀር አንዳች ተስፋ ለማድረግ ባትደፍርም ና። ተስፋ መቁረጥ በአንተ ላይ ቢያንዣብብ፣ እንደ አስፈሪ ቅዠት ደረትህን ቢጫንህም ና። መጥተህ ጌታ ሌላ አንድ ኃጢአተኛ እንዲያጸድቅ ለምነው። ለምን አያደርገውም? ና፤ ይህ ታላቅ የእግዚአብሔር ምሕረት እንደ አንተ ላሉት የታሰበ ነውና። በጥቅሱ ቋንቋ እናገረዋለሁ፤ ከዚህ የበለጠ አጥብቄ ልናገረው አልችልም፦ ጌታ እግዚአብሔር ራሱ «ኃጢአተኛውን የሚያጸድቅ» የሚለውን ይህን የጸጋ ስም ለራሱ ይወስዳል። በተፈጥሮ እግዚአብሔርን የማይፈሩትን ጻድቃን ያደርጋቸዋል፤ እንደ ጻድቃንም እንዲቈጠሩ ያደርጋል። ይህ ለአንተ አስደናቂ ቃል አይደለምን? አንባቢ ሆይ፣ ይህን ጉዳይ በሚገባ እስክታስብበት ድረስ አትዘግይ።
ምዕራፍ 3 ተጠናቋል
እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ያጸድቃል