ምዕራፍ 4 · 7 ደቂቃ ንባብ · 9 ደቂቃ ማዳመጥ
የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው
ሮሜ 8:33
ይህ መጽደቅ፣ ማለትም ጻድቅ መደረግ፣ እንዴት ያለ ድንቅ ነገር ነው! የእግዚአብሔርን ሕግጋት ፈጽሞ ባንተላለፍ ኖሮ ባላስፈለገን ነበር፤ በራሳችን ጻድቃን እንሆን ነበርና። በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሊያደርገው የሚገባውን ያደረገ፣ ሊያደርገው የማይገባውንም ከቶ ያላደረገ ሰው በሕግ ይጸድቃል። ነገር ግን አንተ ውድ አንባቢ ሆይ፣ እንደዚያ ያለህ ሰው እንዳልሆንህ እርግጠኛ ነኝ። ኃጢአት የሌለብህ መስለህ ለመታየት የማትሞክር ሐቀኛ ሰው ነህ፤ ስለዚህ መጽደቅ ያስፈልግሃል።
እንግዲህ ራስህን ብታጸድቅ ራስህን የምታታልል ብቻ ትሆናለህ። ስለዚህ ይህን አትሞክር። ፈጽሞ ዋጋ የለውም።
እንደ አንተ ሟቾች የሆኑ ባልንጀሮችህ እንዲያጸድቁህ ብትጠይቃቸው ምን ሊያደርጉልህ ይችላሉ? ከእነርሱ አንዳንዶቹ በጥቂት ውለታ ስለ አንተ መልካም እንዲናገሩ ልታደርጋቸው ትችላለህ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከዚያ ባነሰ ነገር ከጀርባህ ያሙሃል። ፍርዳቸው ብዙም ዋጋ የለውም።
ጥቅሳችን ግን፦ «የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው» ይላል፤ ይህ ደግሞ እጅግ ወደ ነጥቡ የሚያደርስ ነው። በጥንቃቄ ልናስብበት የሚገባ አስደናቂ እውነታ ነው። ና፣ ተመልከት።
በመጀመሪያ ደረጃ፣ በደለኞችን ለማጽደቅ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ባላሰበ ነበር። በግልጥ ዓመፅ ኖረዋል፤ በሁለት እጃቸው ክፋትን ሠርተዋል፤ ከክፉ ወደ ባሰ ሄደዋል፤ ስለ ኃጢአታቸው ተቀጥተው ለጊዜው እንዲተዉት ከተገደዱ በኋላ እንኳ ወደ ኃጢአት ተመልሰዋል። ሕግን ተላልፈዋል፤ ወንጌልንም ረግጠዋል። የምሕረትን አዋጅ እንቢ ብለዋል፤ በኃጢአተኝነታቸውም ጸንተዋል። ታዲያ እንዴት ይቅር ሊባሉና ሊጸድቁ ይችላሉ? ሰዎች ባልንጀሮቻቸው ተስፋ ቈርጠውባቸው፦ «እነዚህ ተስፋ የሌላቸው ናቸው» ይላሉ። ክርስቲያኖች እንኳ በተስፋ ሳይሆን በኀዘን ይመለከቷቸዋል። አምላካቸው ግን እንዲህ አይደለም። እርሱ በሚመርጥበት ጸጋው ግርማ ከእነርሱ አንዳንዶቹን ዓለም ሳይፈጠር መርጦአቸዋልና፣ እስኪያጸድቃቸውና በውድ ልጁ ተቀባይነት እንዲያገኙ እስኪያደርጋቸው ድረስ አያርፍም። «አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው» ተብሎ ተጽፎ የለምን? እንግዲህ ጌታ ሊያጸድቃቸው የወሰነባቸው አንዳንዶች እንዳሉ ታያለህ፤ ታዲያ አንተና እኔ ከእነዚያ ቍጥር ለምን አንሆንም?
ከእግዚአብሔር በቀር እኔን ለማጽደቅ ማንም ባላሰበ ነበር። ለራሴ እንኳ ድንቅ ነኝ። ጸጋ በሌሎችም ዘንድ እንዲሁ እንደሚታይ አልጠራጠርም። በእግዚአብሔር አገልጋዮች ላይ በቍጣ አረፋ ይደፍቅ የነበረውን የጠርሴሱን ሳውልን ተመልከት። እንደ ተራበ ተኵላ ጠቦቶቹንና በጎቹን ወዲህና ወዲያ ያስጨንቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በደማስቆ መንገድ ላይ መታው፤ ልቡንም ለወጠው፤ ፈጽሞም አጸደቀው፤ ስለዚህም ይህ ሰው ብዙም ሳይቆይ በእምነት ስለ መጽደቅ ከሰበኩት ሁሉ የሚበልጥ ሰባኪ ሆነ። በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን በመጽደቁ ብዙ ጊዜ ተደንቆ መሆን አለበት፤ በአንድ ወቅት በሕግ ሥራ ለሚገኝ መዳን አጥብቆ የሚሟገት ቈራጥ ሰው ነበረና። እንደ አሳዳጁ ሳውል ያለውን ሰው ለማጽደቅ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ባላሰበ ነበር፤ ጌታ እግዚአብሔር ግን በጸጋው የከበረ ነው።
ነገር ግን ማንም ሰው ኃጢአተኛውን ለማጽደቅ ቢያስብ እንኳ፣ ይህን ሊያደርግ የሚችል ከእግዚአብሔር በቀር ማንም የለም። ማንም ሰው በራሱ ላይ ያልተፈጸመን በደል ይቅር ማለት ፈጽሞ አይቻለውም። አንድ ሰው ክፉኛ በድሎህ ቢሆን አንተ ይቅር ልትለው ትችላለህ፤ ይቅር እንደምትለውም ተስፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን ሦስተኛ ሰው ያለ አንተ ይቅር ሊለው አይችልም። በደሉ የተፈጸመው በአንተ ላይ ከሆነ ይቅርታው ከአንተ መምጣት አለበት። በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርተን ከሆነ ይቅር የማለቱ ሥልጣን የእግዚአብሔር ነው፤ ኃጢአቱ በእርሱ በራሱ ላይ ነውና። ዳዊት በአምሳ አንደኛው መዝሙር፦ «አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ» የሚለው ስለዚህ ነው፤ በደሉ የተፈጸመበት እግዚአብሔር በደሉን ሊያስወግድ ይችላልና። ለእግዚአብሔር ያለብንን ዕዳ ታላቁ ፈጣሪያችን ደስ ቢያሰኘው ሊተውልን ይችላል፤ እርሱ ከተወው ደግሞ በእርግጥ ተትቶአል። ኃጢአትን የሠራንበት ታላቁ እግዚአብሔር ብቻ ያን ኃጢአት ሊደመስስ ይችላል፤ ስለዚህ ወደ እርሱ ሄደን ከእጁ ምሕረትን መፈለጋችንን እናረጋግጥ። ለእነርሱ እንድንናዘዝ በሚፈልጉ ሰዎች ከመንገዳችን አንሳሳት፤ ለሚሉት ነገር በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ምንም ሥልጣን የላቸውም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም የኃጢአትን ስርየት እንዲያውጁ የተሾሙ ቢሆኑ እንኳ፣ እኛ ራሳችን በመካከለኛው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ ታላቁ ጌታ ሄደን ከእጁ ይቅርታን ብንፈልግና ብናገኝ አሁንም ይሻላል፤ ይህ ትክክለኛው መንገድ እንደ ሆነ እርግጠኞች ነንና። በሌላ ሰው እጅ የሚፈጸም ሃይማኖት እጅግ ብዙ አደጋ አለበት፤ የነፍስህን ጉዳይ ራስህ ብትከታተለው፣ በማንም ሰው እጅ ባትተወው ይሻልሃል።
ኃጢአተኛውን ሊያጸድቅ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እርሱ ግን ይህን ፍጹም አድርጎ ሊፈጽመው ይችላል። ኃጢአታችንን ወደ ኋላው ይጥላል፤ ይደመስሰዋል፤ ቢፈለግ እንኳ እንደማይገኝ ይናገራል። ከራሱ ወሰን የሌለው ቸርነት በቀር ሌላ ምንም ምክንያት ሳይኖረው፣ እንደ ደም የቀላውን ኃጢአት እንደ በረዶ ነጭ የሚያደርግበትን፣ መተላለፋችንንም ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ ከእኛ የሚያርቅበትን የከበረ መንገድ አዘጋጅቶአል። «ኃጢአታችሁንም አላስብም» ይላል። ኃጢአትን እስከ መጨረስ ድረስ ይሄዳል። ከጥንት ሰዎች አንዱ በመደነቅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦ «ኃጢአትን ይቅር የሚል፥ የርስቱንም ቅሬታ መተላለፍ የሚያልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቍጣውን ለዘላለም አይጠብቅም» (ሚክያስ 7:18)።
አሁን የምንናገረው ስለ ፍትሕ አይደለም፤ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር እንደ ሥራቸው ስለሚያደርገውም አይደለም። ከጻድቁ ጌታ ጋር በሕግ ውል ልትዋዋል ብትል የዘላለም ቍጣ ይጠብቅሃል፤ የሚገባህ ያ ነውና። ስሙ የተባረከ ይሁን፤ እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፤ ይልቁንም አሁን በነጻ ጸጋና ወሰን በሌለው ርኅራኄ ውል ከእኛ ጋር ይነጋገራል፤ «በቸርነት እቀበላችኋለሁ፤ በፈቃዴም እወድዳችኋለሁ» ይላል። እመነው፤ ታላቁ እግዚአብሔር በደለኞችን በብዙ ምሕረት ሊይዛቸው እንደሚችል በእርግጥ እውነት ነውና፤ አዎን፣ ኃጢአተኞችን ሁልጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እንደ ነበሩ አድርጎ ሊይዛቸው ይችላል። የአባካኙን ልጅ ምሳሌ በጥንቃቄ አንብብ፤ ይቅር ባዩ አባት የተመለሰውን ተቅበዝባዥ ልጅ ከቶ እንዳልሄደ፣ ከጋለሞቶችም ጋር ራሱን ከቶ እንዳላረከሰ ያህል በፍቅር እንዴት እንደ ተቀበለው ተመልከት። ይህንንም እስከዚህ ድረስ ስላደረገው ታላቁ ወንድም ያጒረመርም ጀመር፤ አባቱ ግን ፍቅሩን ከቶ አልመለሰም። ወንድሜ ሆይ፣ ምንም ያህል በደለኛ ብትሆን ወደ አምላክህና ወደ አባትህ ብቻ ብትመለስ፣ ከቶ ክፉ እንዳላደረግህ አድርጎ ይይዝሃል! እንደ ጻድቅ ይቈጥርሃል፤ እንደዚያም ያደርግልሃል። ለዚህ ምን ትላለህ?
ይህ ምንኛ ድንቅ ነገር እንደ ሆነ ግልጥ አድርጌ ላሳይ እወዳለሁና—ኃጢአተኛውን ለማጽደቅ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ባያስብ፣ ከእግዚአብሔርም በቀር ማንም ሊያደርገው ባይችል፣ ጌታ ግን ሊያደርገው እንደሚችል አታይምን? ሐዋርያው ተግዳሮቱን እንዴት እንደሚያቀርብ ተመልከት፦ «እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው።» እግዚአብሔር አንድን ሰው ካጸደቀው መልካም ሆኖ ተደርጎአል፤ በትክክል ተደርጎአል፤ በጽድቅ ተደርጎአል፤ ለዘላለም ተደርጎአል። በወንጌልና በሚሰብኩት ሰዎች ላይ መርዝ በተሞላ አንድ መጽሔት ውስጥ፣ ኃጢአት ከሰዎች ሊወገድ ይችላል ብለን የምናስብበት አንድ ዓይነት ንድፈ ሐሳብ እንደምንይዝ የሚገልጥ ጽሑፍ አነበብሁ። እኛ ንድፈ ሐሳብ አንይዝም፤ እውነታን እናውጃለን። ከሰማይ በታች ካሉት እውነታዎች ሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ክርስቶስ በክቡር ደሙ ኃጢአትን በእርግጥ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔርም ስለ ክርስቶስ ብሎ በመለኮታዊ ምሕረት ውል ከሰዎች ጋር እየተነጋገረ በደለኞችን ይቅር ይላቸዋል፤ ያጸድቃቸዋልም—በእነርሱ ውስጥ በሚያየው ወይም ወደ ፊት በእነርሱ ውስጥ ይገኛል ብሎ አስቀድሞ በሚያየው ነገር ሳይሆን በገዛ ልቡ ውስጥ ባለው በምሕረቱ ባለ ጠግነት መጠን። ይህን ሰብከናል፤ እንሰብካለን፤ በሕይወት እስካለንም ድረስ እንሰብከዋለን። «የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው»—ኃጢአተኛውን የሚያጸድቅ እርሱ ነው፤ እርሱ ይህን በማድረጉ አያፍርም፤ እኛም ይህን በመስበካችን አናፍርም።
ከእግዚአብሔር ራሱ የሚመጣው መጽደቅ ከጥያቄ በላይ መሆን አለበት። ፈራጁ ነጻ ካወጣኝ ማን ሊኰንነኝ ይችላል? በዓለማት ሁሉ ላይ ያለው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጻድቅ ነህ ብሎ ካወጀልኝ ማን ይከሰኛል? ከእግዚአብሔር የሆነ መጽደቅ ለነቃ ሕሊና በቂ መልስ ነው። መንፈስ ቅዱስ በእርሱ አማካይነት በመላው ማንነታችን ላይ ሰላምን ይተነፍሳል፤ ከእንግዲህም አንፈራም። በዚህ መጽደቅ የሰይጣንንና እግዚአብሔርን የማይፈሩ ሰዎችን ጩኸትና ስድብ ሁሉ ልንመልስ እንችላለን። በዚህ ልንሞት እንችላለን፤ በዚህ በድፍረት ከሙታን እንነሣለን፤ የመጨረሻውን ታላቅ ችሎትም እንጋፈጣለን።
በዚያ ታላቅ ቀን በድፍረት እቆማለሁ፤
ማንስ ምንም ሊከሰኝ ይችላል?
በጌታዬ ነጻ ተደርጌአለሁና
ከኃጢአት አስፈሪ እርግማንና ነቀፋ።
ወዳጄ ሆይ፣ ጌታ ኃጢአትህን ሁሉ ሊደመስስ ይችላል። ይህን ስናገር በጨለማ ውስጥ በግምት አልተኩስም። «ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል።» እስከ ጕሮሮህ ድረስ በወንጀል ብትዘፈቅ እንኳ በአንድ ቃል ርኵሰቱን ሊያስወግድልህና፦ «እወዳለሁ፥ ንጻ» ሊልህ ይችላል። ጌታ ታላቅ ይቅር ባይ ነው።
«በኃጢአት ስርየት አምናለሁ።» አንተስ?
እርሱ በዚህች ሰዓት እንኳ፦ «ኃጢአትህ ተሰረየችልህ፤ በሰላም ሂድ» የሚለውን ፍርድ ሊያውጅ ይችላል፤ ይህን ካደረገ ደግሞ በሰማይ ወይም በምድር ወይም ከምድር በታች ያለ ምንም ኃይል በጥርጣሬ ሥር፣ ይልቁንም በቍጣ ሥር ሊያስገባህ አይችልም። ሁሉን የሚችለውን የፍቅር ኃይል አትጠራጠር። አንተ እግዚአብሔርን እንደ በደልኸው ባልንጀራህ በድሎህ ቢሆን ይቅር ልትለው ባልቻልህ ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን እህል በአንተ ቍና አትስፈር፤ ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ አሳቡና መንገዱ ከአንተ አሳብና መንገድ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው።
«እንግዲህማ» ትላለህ፤ «ጌታ ይቅር ቢለኝ ታላቅ ተአምር ይሆን ነበር።» ልክ ነው። ከሁሉ የላቀ ተአምር ይሆናል፤ ስለዚህም ያደርገዋል ብሎ መጠበቅ ይቻላል፤ እርሱ ያልጠበቅነውን «የማይመረመረውን ታላቅ ነገር» ያደርጋልና።
እኔ ራሴ ሕይወቴን መከራ ባደረገብኝ በአስፈሪ የበደለኛነት ስሜት ተመትቼ ነበር፤ ነገር ግን፦ «እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፣ ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ትድኑማላችሁ፤ እኔ አምላክ ነኝ፥ ሌላም የለም» የሚለውን ትእዛዝ በሰማሁ ጊዜ—ተመለከትሁ፤ በቅጽበትም ጌታ አጸደቀኝ። ያየሁት ስለ እኔ ኃጢአት የተደረገውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነበር፤ ያም እይታ ዕረፍት ሰጠኝ። በምድረ በዳ በእሳታማዎቹ እባቦች የተነደፉት ወደ ናሱ እባብ በተመለከቱ ጊዜ ወዲያው እንደ ተፈወሱ፣ እኔም ወደ ተሰቀለው አዳኝ በተመለከትሁ ጊዜ እንዲሁ ሆንሁ። እንዳምን ያስቻለኝ መንፈስ ቅዱስ በማመን ሰላምን ሰጠኝ። ቀደም ሲል መኰነኔን እርግጠኛ እንደ ነበርሁ፣ ይቅር እንደ ተባልሁ እንዲሁ እርግጠኛ ሆንሁ። የእግዚአብሔር ቃል ስላወጀውና ሕሊናዬም ስለ መሰከረለት በመኰነኔ እርግጠኛ ነበርሁ፤ ጌታ ባጸደቀኝ ጊዜ ግን በእነዚያው ምስክሮች እንዲሁ እርግጠኛ ሆንሁ። በመጽሐፍ ያለው የጌታ ቃል፦ «በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም» ይላል፤ ሕሊናዬም እንዳመንሁ፣ እግዚአብሔርም ይቅር በማለቱ ጻድቅ እንደ ሆነ ይመሰክራል። ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስና የራሴ ሕሊና ምስክርነት አለኝ፤ እነዚህ ሁለቱም በአንድ ይስማማሉ። ኦ፣ አንባቢዬ በዚህ ጉዳይ የእግዚአብሔርን ምስክርነት ቢቀበል ምንኛ በወደድሁ! ያን ጊዜ እርሱም ደግሞ ብዙም ሳይቆይ ምስክሩን በነፍሱ ይይዝ ነበር!
በእግዚአብሔር የጸደቀ ኃጢአተኛ፣ በሥራው የጸደቀ ጻድቅ ሰው—እንዲህ ያለ ቢገኝ—ከሚቆምበት ይልቅ በጸና መሠረት ላይ ይቆማል ብዬ ለመናገር እደፍራለሁ። በቂ ሥራ እንደ ሠራን ከቶ እርግጠኞች ልንሆን አንችልም ነበር፤ ከሁሉ በኋላ እንዳንጐድል ሕሊና ሁልጊዜ ይታወክ ነበር፤ የምንደገፈውም ሊሳሳት በሚችል ፍርድ በሚሰጥ በሚንቀጠቀጥ ብይን ላይ ብቻ ይሆን ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ራሱ ሲያጸድቅ፣ መንፈስ ቅዱስም ከእግዚአብሔር ጋር ሰላምን በመስጠት ለዚህ ሲመሰክር፣ ያን ጊዜ ጉዳዩ የተረጋገጠና የጸና እንደ ሆነ ይሰማናል፤ ወደ ዕረፍትም እንገባለን። አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም የተቀበለችውን ነፍስ የሚወርሰውን የዚያን ጸጥታ ጥልቀት ምንም አንደበት ሊናገረው አይችልም።
ምዕራፍ 4 ተጠናቋል
የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው