ምዕራፍ 2 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
ዓላማችን ምንድር ነው?
አንድ ታሪክ ሰማሁ፤ ከሰሜን አገር የመጣ ይመስለኛል። አንድ የወንጌል አገልጋይ እጅግ ድሃ እንደ ሆነች ያውቅ ስለ ነበር ሊረዳት አስቦ አንዲትን ድሃ ሴት ሊጠይቅ ሄደ። ገንዘቡን በእጁ ይዞ በሩን አንኳኳ፤ እርሷ ግን አልመለሰችም። ቤት እንደሌለች ደምድሞ መንገዱን ቀጠለ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቤተ ክርስቲያን አገኛትና ችግሯን እንዳስታወሰ ነገራት፦ «ቤትሽ መጥቼ ብዙ ጊዜ አንኳኳሁ፤ መልስ ስላላገኘሁ ቤት አልነበርሽም መሰለኝ።» «ጌታዬ፣ በስንት ሰዓት ነበር የመጡት?» «እኩለ ቀን ገደማ ነበር።» «ወይ ጉዴ!» አለች፤ «ጌታዬ፣ ሰምቼዎት ነበር፤ ባለመመለሴም እጅግ አዝናለሁ፤ ነገር ግን የቤት ኪራይ ሊቀበል የመጣው ሰው መስሎኝ ነበር።» ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ ብዙ ድሃ ሴት ታውቃለች። እንግዲህ እኔ እንድሰማ እመኛለሁ፤ ስለዚህም ኪራይ ልቀበል እንዳልመጣሁ ልናገር እወዳለሁ፤ በእርግጥም የዚህ መጽሐፍ ዓላማ ከአንተ አንዳች ነገር መጠየቅ ሳይሆን መዳን ሁሉም በጸጋ እንደ ሆነ ልነግርህ ነው፤ ይህም በነጻ፣ እንዲያው፣ ያለ ምንም ዋጋ ማለት ነው።
ብዙ ጊዜ ትኩረትን ለመሳብ ስንጓጓ አድማጫችን እንዲህ ያስባል፦ «አሃ! አሁን ግዴታዬ ሊነገረኝ ነው። ይህ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ሊቀበል የመጣ ሰው ነው፤ እኔ ደግሞ የምከፍለው አንዳች እንደሌለኝ እርግጠኛ ነኝ። ቤት እንደሌለሁ አደርጋለሁ።» አይደለም፤ ይህ መጽሐፍ የመጣው ከአንተ አንዳች ነገር ሊጠይቅ ሳይሆን አንዳች ነገር ሊያመጣልህ ነው። የምንነጋገረው ስለ ሕግ፣ ስለ ግዴታና ስለ ቅጣት ሳይሆን ስለ ፍቅር፣ ስለ ቸርነት፣ ስለ ይቅርታ፣ ስለ ምሕረትና ስለ ዘላለም ሕይወት ነው። ስለዚህ ቤት እንደሌለህ አታድርግ፤ ጆሮህን አትድፈን፤ ልብህንም ግድ የለሽ አታድርግ። በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ስም ከአንተ ምንም አልጠይቅም። ከእጅህ አንዳች ነገር የመሻት ዓላማ የለኝም፤ ነገር ግን መቀበሉ ለአሁኑና ለዘላለማዊው ደስታህ የሚሆንልህን ነጻ ስጦታ ላመጣልህ በእግዚአብሔር ስም መጥቻለሁ። በሩን ክፈት፤ ልመናዬም ይግባ። «ኑና እንዋቀስ።» ጌታ ራሱ ስለ አሁኑና ስለማያልቀው ደስታህ እንድትመካከር ይጋብዝሃል፤ ለአንተም መልካም ባያስብ ኖሮ ይህን ባላደረገ ነበር። በርህን የሚያንኳኳውን ጌታ ኢየሱስን እምቢ አትበለው፤ እንደ አንተ ላሉት ሲል በእንጨት ላይ በተቸነከረ እጅ ያንኳኳልና። ብቸኛውና አንዱ ዓላማው የአንተ መልካም ነገር ስለ ሆነ ጆሮህን አዘንብል፤ ወደ እርሱም ና። በትጋት አድምጥ፤ መልካሙም ቃል ወደ ነፍስህ ይስረጽ። የሰማይ መጀመሪያ ወደ ሆነው ወደዚያ አዲስ ሕይወት የምትገባበት ሰዓት ደርሶ ሊሆን ይችላል። እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።፤ ማንበብም አንድ ዓይነት መስማት ነው፤ ይህን መጽሐፍ በምታነብበት ጊዜ እምነት ወደ አንተ ሊመጣ ይችላል። ለምን አይሆንም? ኦ የጸጋ ሁሉ ብፁዕ መንፈስ ሆይ፣ እንዲህ አድርገው!
ምዕራፍ 2 ተጠናቋል
ዓላማችን ምንድር ነው?