ምዕራፍ 13 · 16 ደቂቃ ንባብ · 20 ደቂቃ ማዳመጥ
ሰው ያስባል፣ እግዚአብሔር ይፈጽማል
በእግዚአብሔር መግቦት ወደ ስዋቶ እንዳልመለስ በአንድነት የከለከሉኝንና በመጨረሻም በኒንግፖ እንድቀመጥና ለወደፊቱ ሥራ መስፋፋት ማዕከል እንዳደርጋት የመሩኝን የተለያዩ ሁኔታዎች ማስተዋል የሚያስደስት ነው።
ሻንጋይ በደረስሁ ጊዜ መድኃኒቶቼና መሣሪያዎቼ ተቀምጠውበት የነበረው ሕንፃ በእሳት ተቃጥሎ፣ መድኃኒቶቹ ሁሉና ከመሣሪያዎቹም ብዙዎቹ ፈጽመው መጥፋታቸውን ሳገኝ እጅግ ደነገጥሁ። ይህ ለእኔ ታላቅ መቅሠፍት መሰለኝ፤ «ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ» ከማስተዋል ይልቅ እንደ እምነት የለሹ ያዕቆብ «ይህ ሁሉ በእኔ ላይ ሆኖአል» ለማለት ይበልጥ ያዘነበልሁ ይመስለኛል። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን አንዱ ታላቅ ሁኔታ — «በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን» የተባለለት እርሱ — አድርጌ ማሰብን፣ ሌሎቹንም ያነሱ ውጫዊ ሁኔታዎች ሁሉ በእርሱ የታዘዙ ወይም የተፈቀዱ በመሆናቸው የግድ እጅግ ቸሮች፣ እጅግ ጥበበኞችና እጅግ መልካሞች እንደ ሆኑ ማሰብን ገና አልተማርሁም ነበር። ስለዚህ ቅሬታዬና ፈተናዬ እጅግ ታላቅ ነበር።
በሻንጋይ መድኃኒቶች ውድ ነበሩ፤ አቅሜም ውሱን ነበር። ስለዚህ እንደ እኔ የአንድ ሚስዮን አባል ከሆነው ከዶክተር ዊልያም ፓርከር መድኃኒት ለማግኘት ተስፋ አድርጌ በውስጥ አገር በኩል ወደ ኒንግፖ ጉዞ ጀመርሁ። የቀሩኝን ጥቂት ንብረቶቼን ይዤ ሄድሁ፤ ዋናዎቹም ሰዓቴ፣ ጥቂት የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎች፣ ኮንሰርቲና የተባለ የሙዚቃ መሣሪያና በዚያን ዘመን እጅግ ውድ የነበሩ የቻይንኛ መማሪያ መጻሕፍት ነበሩ፤ ከገንዘቤ ግን ከፊሉን በሻንጋይ ትቼ ሄድሁ።
የማልፍበት አገር በድርቅ እጅግ ይሠቃይ ነበር፤ የበጋው ሙቀት የጠነከረበት ወቅት ነበር፤ በታላቁ ቦይ ውስጥ ያለው ውኃም በአጠገቡ ላሉት የሩዝ እርሻዎች በብዛት ስለ ተቀዳና በኃይለኛው ሙቀትም ስለ ተነነ እጅግ ዝቅ ብሎ ነበር። ጉዞውን በተቻለ መጠን የሚስዮን ጉብኝት ለማድረግ ወስኜ ስለ ነበር፣ ክርስቲያናዊ በራሪ ጽሑፎችንና መጻሕፍትን በብዛት ይዤ ተነሣሁ። ሕዝብ በበዛበት አገር በዝግታ እየተጓዝን፣ እየሰበክንና መጻሕፍትን እያደልን አሥራ አራት ቀናት ካሳለፍን በኋላ ሺህ-ሙን-ዋን ወደ ተባለች አንዲት ትልቅ ከተማ ደረስን፤ በዚያም የያዝሁት ጽሑፍ ማለቁን ስላገኘሁ በቀረው ጉዞ ሳልዘገይ የሃይኒንግን ከተማ አቋርጬ በተቻለ ፍጥነት ኒንግፖ ለመድረስ ወሰንሁ።
ኦገስት 4 ቀን 1856።
ከሺህ-ሙን-ዋን ወዲያ ውኃ አልነበረም፤ ስለዚህ የጀልባዬን ሒሳብ ከፍዬ አሰናበትሁ፤ ዕቃዎቼን እስከ ቻንግ-ጋን ድረስ የሚሸከሙ ኩሊዎችን (ሸክም ተሸካሚዎችን) ቀጠርሁ፤ ፀሐይም ሳትወጣ በመንገድ ላይ ነበርን። ለማረፍ ደጋግመው ከሚቆሙት ሰዎች ጋር አገልጋዬ እንዲከተለኝ ትቼ ብቻዬን ቀድሜ ሄድሁ፤ ልናልፍባት ወደሚገባን አንዲት ከተማ በደረስሁ ጊዜም ከሰሜኑ በር ውጭ ባለ አንድ ሻይ ቤት ውስጥ ጠበቅኋቸው። ኩሊዎቹ እጅግ በዝግታ መጡ፤ በደረሱም ጊዜ የደከሙ ይመስሉ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሁለቱም ኦፒየም አጫሾች መሆናቸውን ተረዳሁ፤ ስለዚህ የተሸከሙት አንድ ብርቱ ሰው ሦስት እጥፍ ርቀት ቢሸከመው ከምንም የማይቈጥረው ሸክም ቢሆንም፣ በእርግጥ የዛሉ ይመስሉ ነበር።
ጥቂት ሩዝና ሻይ ከበሉና ለአንድ ሰዓት ካረፉ በኋላ — ይህም እንደማልጠራጠረው የኦፒየም ፒፓ ማጨስን ይጨምራል — ትንሽ ተነቃቁ፤ እኔም ፀሐይ እጅግ ሳትበረታ ቻንግ-ጋን እንድንደርስ ጉዞአችንን እንድንቀጥል አሳብ አቀረብሁ። ነገር ግን አገልጋዬ በከተማዪቱ ውስጥ ወዳጅ ነበረው፤ ቀኑንም በዚያ አሳልፎ በማግሥቱ ጠዋት መሄድ ፈለገ። እኔ ግን ከተቻለ በዚያች ሌሊት ሃይኒንግ ለመድረስ ስለ ፈለግሁ ይህን ተቃወምሁ። . . . ስለዚህ ተነሣን፤ በሰሜኑ በር ገባን፤ የከተማዪቱንም አንድ ሦስተኛ ያህል እንዳለፍን ኩሊዎቹ ለማረፍ ቆሙ፤ ሸክሙንም እስከ ቻንግ-ጋን መሸከም እንደማይችሉ ተናገሩ። በመጨረሻ እስከ ደቡቡ በር ሊሸከሙት ተስማሙ፤ በዚያም በተሸከሙት ርቀት መጠን ይከፈላቸዋል፤ አገልጋዩም ሌሎች ኩሊዎችን ጠርቶ ከእነርሱ ጋር ሊመጣ ኃላፊነት ወሰደ።
እኔም እንደ መጀመሪያው ቀድሜ ሄድሁ፤ ርቀቱም አራት ማይል ያህል ብቻ ስለ ነበር ብዙም ሳይቆይ ቻንግ-ጋን ደረስሁ፤ እስኪመጡም ጠበቅሁ፤ በዚያው ጊዜ እስከ ሃይኒንግ ድረስ ለቀረው ጉዞ ኩሊዎችን ቀጠርሁ። ረጅም ጊዜ ከጠበቅሁ በኋላ በመዘግየታቸው መደነቅ ጀመርሁ፤ በመጨረሻም በዚያች ሌሊት እስከ ሃይኒንግ ያለውን ጉዞ ለመጨረስ እጅግ ዘገየ። ትንሽ ተበሳጨሁ፤ እግሮቼ ባይቈሳሰሉና ከሰዓት በኋላው እጅግ ሞቃታማ ባይሆን ኖሮ ልቀበላቸውና ላፋጥናቸው ወደ ኋላ በተመለስሁ ነበር። በመጨረሻ አገልጋዬ ወደ ወዳጁ ቤት ሄዶ መሆን አለበት፤ እስከ ምሽትም አይመጣም ብዬ ደመደምሁ። ነገር ግን ምሽቱ መጣ፤ አሁንም የእነርሱ ምልክት አልታየም።
እጅግ ተጨንቄ ታይተው እንደ ሆነ በትጋት መጠየቅ ጀመርሁ። በመጨረሻ አንድ ሰው፦ «ከሺህ-ሙን-ዋን የመጣህ እንግዳ ነህን?» ብሎ መለሰልኝ። አዎን አልሁት። «ወደ ሃይኒንግ ትሄዳለህን?» «መድረሻዬ እርሷ ናት።» «እንግዲያውስ ዕቃዎችህ ቀድመውህ ሄደዋል፤ እኔ በአንድ ሻይ ቤት ተቀምጬ ሳለሁ አንድ ኩሊ ገባ፤ አንድ ሲኒ ሻይ ጠጣና የተሸከመው የቀርከሀ ሣጥንና አልጋ — አንተ የአንተ ናቸው ብለህ የገለጽሃቸውን የሚመስሉ — ከሺህ-ሙን-ዋን የመጡ እንደ ሆኑ፣ በዚችም ሌሊት ወደ ሃይኒንግ ሊያደርሳቸው እንደሚገባ፣ በዚያም በአንድ ፓውንድ ዐሥር ካሽ ሒሳብ እንደሚከፈለው እየተናገረ እጅግ ተጣድፎ ወደ ሃይኒንግ ሄደ።» ከዚህም የተነሣ ዕቃዎቼ ቀድመውኝ እንደ ሄዱ ደመደምሁ፤ ነገር ግን ለመራመድ እጅግ ስለ ደከምሁና አሁን ጨልሞ ስለ ነበር ወዲያውኑ ልከተላቸው አልቻልሁም።
በዚህ ሁኔታ ማድረግ የቻልሁት ሁሉ የማድርበት ስፍራ መፈለግ ነበር፤ ይህም ቀላል ሥራ ሆኖ አላገኘሁትም። ልቤን ወደ እግዚአብሔር አንሥቼ ርዳታውን ከለመንሁ በኋላ፣ አንድ የውጭ አገር ሰው በስፍራው መኖሩ ወሬ ገና ያልደረሰበት ይሆናል ብዬ ወዳሰብሁት ወደ ከተማዪቱ ሩቅ ጫፍ አቋርጬ ሄድሁ፤ የእንግዳ ማረፊያም ፈለግሁ። ብዙም ሳይቆይ አንዱን አገኘሁና ገባሁ፤ አሁን ጨልሞ ስለ ነበር ማንም ሳይጠይቀኝ አልፋለሁ ብዬ ተስፋ አደረግሁ። የምግቡን ዝርዝር ስጠይቅ፣ የሚገኘው ቀዝቃዛ ሩዝ — እርሱም ከ«ትንሽ ማረር» እጅግ ያለፈ ሆኖ ተገኘ — እና በመብራት ዘይት የተጠበሱ እባቦች ብቻ እንደ ሆኑ ተነገረኝ። ስለ ዜግነቴ ምንም ጥያቄ እንዲነሣ ስላልፈለግሁ ጥቂት ለማዘዝ ተገደድሁ፤ ለመብላትም ሞከርሁ፤ ብዙም ግን አልተሳካልኝም።
እንዲህ በማድረግ ላይ ሳለሁ የቤቱን ባለቤት፦ «እዚህ ማደር የምችል ይመስለኛል፤ ይቻላል?» አልሁት።
እርሱም ይቻላል ብሎ መለሰ፤ ነገር ግን መዝገቡን አውጥቶ እንዲህ ሲል ጨመረ—
«በዚህ ሰላም በሌለበት ዘመን ባለ ሥልጣናቱ የእንግዶቻችንን መዝገብ እንድንይዝ ያዝዙናል፤ የተከበረ የቤተሰብ ስምዎን ልጠይቅዎ?»
«የማይገባው የቤተሰብ ስሜ ታይ ነው» ብዬ መለስሁ።
«የተከበረው ሁለተኛ ስምዎስ?»
«ትሑቱ ስሜ ያ-ኮ ነው» (ጄምስ)።
«እንዴት ያለ እንግዳ ስም ነው! ከዚህ በፊት ሰምቼው አላውቅም። እንዴት ነው የሚጻፈው?»
ነገርሁት፤ ደግሞም፦ «እኔ በመጣሁበት አካባቢ የተለመደ ስም ነው» ብዬ ጨመርሁ።
«ከወዴት እንደ መጡና ወዴት እንደሚሄዱ ልጠይቅዎ?»
«ከሻንጋይ ተነሥቼ በሃንግቻው በኩል ወደ ኒንግፖ እየተጓዝሁ ነው።»
«የተከበረ ሙያዎ ምንድር ነው?»
«በሽተኞችን እፈውሳለሁ።»
«ኦ! ሐኪም ነዎት ማለት ነው» አለ የቤቱ ባለቤት፤ እኔንም እጅግ በሚያስደስተኝ ሁኔታ መዝገቡን ዘጋ። ሚስቱ ግን ንግግሩን ቀጠለች።
«ሐኪም ነዎት?» አለች፤ «ይህ ደስ ያሰኘኛል፤ በለምጽ የተያዘች ልጅ አለችኝና። እርሷን ከፈወሱልኝ እራትዎንና አልጋዎን በነጻ ያገኛሉ።»
ቢከፈልባቸው እራቴና አልጋዬ ምን ያህል እንደሚያስከፍሉ ለመጠየቅ ጉጉት አደረብኝ፤ እኔንም ፈገግ እያሰኘኝ ዋጋቸው ከእኛ ገንዘብ ከአንድ ፔኒ ተኩል እንደሚያንስ አገኘሁ!
ልጅቷን ልጠቅማት ስላልቻልሁ፣ ለምጽ እጅግ የማይበገር በሽታ እንደ ሆነና ምንም መድኃኒት እንዳልያዝሁ ተናግሬ መድኃኒት ላዝላት እንቢ አልሁ።
እናቲቱ ግን ብዕርና ወረቀት አምጥታ፦ «ቢያንስ የመድኃኒት ማዘዣ መጻፍ ይችላሉ፤ ባይጠቅምም አይጎዳም» ብላ አጥብቃ ለመነችኝ።
ይህንንም ግን ለማድረግ እንቢ አልሁ፤ አልጋዬንም እንዲያሳዩኝ ጠየቅሁ። በምድር ቤቱ ወዳለ እጅግ የተጎሳቈለ ክፍል ተወሰድሁ፤ በዚያም በሁለት በርጩማዎች ላይ በተዘረጉ ሳንቃዎች ላይ፣ ከጥላዬና ከጫማዬ በቀር አልጋም ትራስም ሳይኖረኝ፣ የትንኝ መከላከያ አጎበርም ሳይኖር ሌሊቱን አሳለፍሁ። ሌሎች ዐሥር ወይም ዐሥራ አንድ እንግዶች በዚያው ክፍል ይተኙ ስለ ነበር፣ እንዳይሰረቅ በመፍራት ምንም ነገር ማውለቅ አልቻልሁም፤ ይሁን እንጂ እኩለ ሌሊት ሲቃረብ ፈጽሞ እንዳልሞቀኝ አስተዋልሁ።
ኦገስት 5 ቀን።
እንደሚገመተው፣ በጣም ጥቂት አርፌና ታድሼ ተነሣሁ፤ ደኅንነትም ፈጽሞ አልተሰማኝም። ቁርስ እስኪገኝ ድረስ ረጅም ጊዜ መጠበቅ ነበረብኝ፤ ከዚያም ይዤው የነበረው ብቸኛው ዶላር በአንድ ወይም በሁለት ስፍራ ስለ ተሸረፈ ለመመንዘር ሌላ መዘግየት ገጠመኝ። በዚህም ምክንያት ከዋጋው ከሦስት መቶ ካሽ በላይ ተቀነሰ፤ ይህም በነበርሁበት አስቸጋሪ ሁኔታ ከባድ ኪሳራ ነበር።
ከዚያም አገልጋዬና ኩሊዎቹ ዘግይተው ደርሰው ወይም በማለዳ መጥተው ሊሆን ይችላል ብዬ ስላሰብሁ ስለ እነርሱ ወሬ በከተማዪቱ ሁሉ ፈለግሁ። ከተማዪቱ ትልቅ፣ ረጅምና የተንዛዛች ናት፤ ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላው ሁለት ማይል ያህል ትሆናለች፤ ስለዚህ ይህ ጥቂት ጊዜ ወሰደብኝ። ይሁን እንጂ ምንም መረጃ አላገኘሁም፤ እግሬ ቈስሎና ደክሞም በቀኑ ሙሉ ሙቀት ወደ ሃይኒንግ ተነሣሁ። ጉዞው — ስምንት ማይል ያህል — ረጅም ጊዜ ወሰደብኝ፤ በግማሽ መንገድ ላይ ያለች አንዲት መንደር ግን የማረፊያ ስፍራና አንድ ሲኒ ሻይ ሰጠችኝ፤ ሁለቱንም በደስታ ተጠቀምሁባቸው። እንደገና ልነሣ ስል ብርቱ ዝናብ ጣለ፤ በዚህ ምክንያት የተፈጠረው መዘግየትም ስለ ወንጌል እውነቶች ለሕዝቡ ጥቂት እንድናገር አስቻለኝ።
ወደ ሃይኒንግ ሰሜናዊ ዳር ሰፈር ስቃረብ ከሰዓት በኋላው እጅግ ገፍቶ ነበር፤ በዚያም መጠየቅ ጀመርሁ፤ ስለ አገልጋዬ ወይም ስለ ዕቃዎቼ ግን ምንም ወሬ ልሰማ አልቻልሁም። የባሕር ጀንኮች የሚቆሙት በዚያ ስለ ሆነ ከምሥራቁ በር ውጭ ስለ እነርሱ የመስማት ዕድሌ ይበልጥ እንደሚሆን ተነገረኝ። ስለዚህ ወደዚያ ሄድሁ፤ ከትንሹ የምሥራቅ በር ውጭም ፈለግኋቸው፤ ነገር ግን በከንቱ ነበር። እጅግ ደክሜ ለማረፍ በአንድ ሻይ ቤት ውስጥ ተቀመጥሁ፤ በዚያም ሳለሁ ከማንዳሪኑ ቢሮዎች ከአንዱ የመጡ ብዙ ሰዎች ገብተው ማን እንደ ሆንሁ፣ ከወዴት እንደ መጣሁና የመሳሰሉትን ጠየቁ። የምፈልገው ምን እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ በሻይ ቤቱ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች አንዱ፦ «አንተ የገለጽኸውን የመሰለ የቀርከሀ ሣጥንና አልጋ ከግማሽ ሰዓት ገደማ በፊት በዚህ በኩል ተሸክመው አልፈዋል። ተሸካሚው ወደ ታላቁ የምሥራቅ በር ወይም ወደ ደቡቡ በር የሚሄድ ይመስል ነበር፤ በዚያ ወዳሉት ሆንጎች (የንግድ ቤቶች) ሄደህ ብትጠይቅ ይሻላል» አለኝ። በፍለጋው አብሮኝ እንዲሄድ ለመንሁት፤ ስለ ድካሙም ዋጋ እንደምከፍለው ቃል ገባሁለት፤ እርሱ ግን አልፈቀደም። ሌላ ሰው ከእኔ ጋር ለመሄድ ፈቃደኛ ሆነ፤ ስለዚህ አብረን ተነሣን፤ በሁለቱም በሮች ውስጥና ውጭ በትጋት ጠየቅን፤ ነገር ግን ሁሉም በከንቱ ነበር። ከዚያም ቢሳካለት ብዙ ዋጋ እንደምሰጠው ቃል ገብቼለት በደንብ እንዲፈልግ አንድ ሰው ቀጠርሁ። በዚያው ጊዜ ጥቂት ምሳ በላሁ፤ ተሰብስበው ለነበሩት ብዙ ሕዝብም ተናገርሁ።
ምንም ሳይሳካለት በተመለሰ ጊዜ፦ «አሁን ፈጽሞ ደክሜአለሁ፤ የማድርበት ስፍራ እንዳገኝ ትረዳኛለህን? ከዚያም ስለ ድካምህ እከፍልሃለሁ» አልሁት። እርሱም ሊረዳኝ ፈቃደኛ ሆነ፤ ማረፊያ ፍለጋም ተነሣን። በመጀመሪያው ወይም በሁለተኛው ስፍራ ሰዎቹ ሊቀበሉኝ አልፈለጉም፤ መጀመሪያ ስንገባ ፈቃደኞች ቢመስሉም፣ ይከተለን የነበረና ከመንግሥት ቢሮዎች በአንዱ የሚሠራ መሆኑን ያወቅሁት አንድ ሰው መኖሩ ያስፈራቸው ይመስል ነበር፤ እኔም ተከለከልሁ። ከዚያም ወደ ሦስተኛ ስፍራ ሄድን፤ የማንዳሪኑ መልእክተኛ ከእንግዲህ ስለማይከተለን ማረፊያ ቃል ተገባልን፤ ሻይም ቀረበ፤ አብሮኝ ለሄደው ሰውም ስለ ድካሙ ከፈልሁት።
እርሱ ከሄደ ብዙም ሳይቆይ አንዳንድ የመንግሥት ሰዎች ገቡ፤ ብዙም ሳይቆዩ ወጡ፤ ነገር ግን የጉብኝታቸው ውጤት በዚያች ሌሊት በዚያ ልስተናገድ እንደማልችል መነገሩ ነበር። በዚያ የነበረ አንድ ወጣት ስለ ጨካኝ ድርጊታቸው ወቀሳቸው፤ «ግድ የለም፣ ከእኔ ጋር ና፤ የተሻለ ማረፊያ ልናገኝልህ ካልቻልን በቤታችን ታድራለህ» አለኝ። አብሬው ሄድሁ፤ ነገር ግን የቤቱ ሰዎች ሊቀበሉኝ ፈቃደኞች አልሆኑም። ደክሜ፣ እግሬም ቈስሎ ለመቆም እንኳ እስኪያቅተኝ ድረስ፣ እንደገና ማረፊያ መፈለግ ነበረብኝ፤ በመጨረሻም ቃል ተገባልኝ፤ ነገር ግን ጥቂት ሕዝብ በበሩ አካባቢ ስለ ተሰበሰበ ሕዝቡ እስኪበተን ድረስ ወደ አንድ ሻይ ቤት ሄጄ እንድጠብቅ፣ ያለዚያ ሊያስተናግዱኝ እንደማይችሉ ነገሩኝ። ሌላ ምርጫ ስላልነበረ፣ አሁንም ወጣቱ አብሮኝ እያለ ሄድሁ፤ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ድረስም ጠበቅሁ። ከዚያም ቃል ወደ ተገባልኝ ማረፊያ ተነሣን፤ መሪዬ ግን ሊያገኘው አልወደደም፤ ወደ ሌላ የከተማዪቱ ክፍል እያዞረ ወሰደኝ፤ በመጨረሻም ከሌሊቱ በሰባትና በስምንት ሰዓት መካከል የቀረውን ሌሊት እንደ ቻልሁ እንዳሳልፍ ጥሎኝ ሄደ።
ከአንድ ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ነበርሁ፤ ቤተ መቅደሱ ግን ተዘግቶ ነበር፤ ስለዚህ በፊቱ ባሉት የድንጋይ ደረጃዎች ላይ ተጋደምሁ፤ ገንዘቤንም እንደ ትራስ ከራሴ በታች አደረግሁ፤ አንድ ሰው በስውር ወደ እኔ ሲመጣ ባላይ ኖሮ ብርዱ ቢኖርም ብዙም ሳይቆይ እንቅልፍ ይወስደኝ ነበር። እየቀረበ ሲመጣ በቻይና እጅግ ከተለመዱት ለማኞች አንዱ መሆኑን አየሁ፤ ዓላማውም ገንዘቤን ሊዘርፈኝ እንደ ሆነ አልተጠራጠርሁም። አልተንቀሳቀስሁም፤ ነገር ግን እንቅስቃሴውን እየተመለከትሁ በዚህ የፈተና ሰዓት እንዳይተወኝ ወደ አባቴ ተመለከትሁ። ሰውየው ቀረበ፤ እንደ ተኛሁ ለማረጋገጥ ለጥቂት ጊዜ ተመለከተኝ (ዓይኖቼ በእርሱ ላይ ተተክለው እንዳሉ ማየት እስከማይችል ድረስ እጅግ ጨለማ ነበር)፤ ከዚያም ቀስ ብሎ ይዳብሰኝ ጀመር። እጅግ በረጋ ድምፅ፣ ነገር ግን እንዳልተኛሁና ተኝቼም እንዳልነበር እንዲያምን በሚያደርግ ሁኔታ፦ «ምን ትፈልጋለህ?» አልሁት። ምንም መልስ አልሰጠም፤ ግን ሄደ።
በመሄዱ እጅግ አመሰገንሁ፤ ከዓይኔም በተሰወረ ጊዜ ከካሼ በኪሴ የማይገባውን ያህል በእጅጌዬ ውስጥ በጥንቃቄ ከተትሁ፤ ትራሴንም ከግድግዳው ወጣ ብሎ ያለ አንድ ድንጋይ አደረግሁ። ብዙም ሳይቆይ እንቅልፍ ያንጐላጀኝ ጀመር፤ ነገር ግን የሚቀርቡ የሁለት ሰዎች ድምፅ የሌለው የሚመስል የእግር ኮቴ ቀሰቀሰኝ፤ የነርቭ ሥርዓቴ ከድካም የተነሣ እጅግ ስሱ ሆኖ ስለ ነበር ትንሹ ድምፅ እንኳ ያስደነግጠኝ ነበር። እንደገና ብቸኛ መደገፊያዬ ከሆነው ከእርሱ ጥበቃን ለመንሁ፤ እንደ ቀድሞውም ጸጥ ብዬ ተጋደምሁ፤ እስከዚያም ከእነርሱ አንዱ መጥቶ ካሹን ለማግኘት ከራሴ በታች ይዳብስ ጀመረ። እንደገና ተናገርሁ፤ እነርሱም በእግሬ አጠገብ ተቀመጡ። ምን እያደረጉ እንደ ሆነ ጠየቅኋቸው፤ እነርሱም እንደ እኔ ሌሊቱን በዚያ ሊያሳልፉ እንደ ሆነ መለሱ። ከዚያም ብዙ ስፍራ ስለ ነበረ ወደ ሌላው ጎን እንዲሄዱና ይህን ጎን ለእኔ እንዲተዉልኝ ለመንኋቸው፤ እነርሱ ግን ከእግሬ አጠገብ አንነሣም አሉ፤ ስለዚህ ቀና ብዬ ጀርባዬን በግድግዳው ላይ አስደገፍሁ።
እነርሱም፦ «ብትተኛና ብታንቀላፋ ይሻልሃል፤ ካልተኛህ ነገ መራመድ አትችልም። አትፍራ፤ አንተውህም፤ ማንም እንዳይጎዳህም እንጠብቅሃለን» አሉኝ።
እኔም፦ «ስሙኝ» ብዬ መለስሁላቸው። «ጥበቃችሁን አልፈልግም፤ አያስፈልገኝም፤ እኔ ቻይናዊ አይደለሁም፤ የማያስተውሉትንና ምንም ማድረግ የማይችሉትን ጣዖቶቻችሁን አላመልክም። እግዚአብሔርን አመልካለሁ፤ እርሱ አባቴ ነው፤ በእርሱም እታመናለሁ። ማን እንደ ሆናችሁና ዓላማችሁ ምን እንደ ሆነ በሚገባ አውቃለሁ፤ ዓይኔንም ከእናንተ ላይ አላነሣም፤ አልተኛምም።»
በዚህ ጊዜ ከእነርሱ አንዱ ሄደ፤ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ሦስተኛ ጓደኛ ይዞ ተመለሰ። እጅግ ተጨነቅሁ፤ ነገር ግን ርዳታ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ተመለከትሁ። አንድ ሁለት ጊዜ ከእነርሱ አንዱ ተኝቼ እንደ ሆነ ለማየት ተነሣ። እኔም፦ «አትሳሳት፤ አልተኛሁም» ብቻ አልሁ። አልፎ አልፎ ራሴ ያሸልብ ነበር፤ ይህም ከእነርሱ አንዱ እንዲነሣ ምልክት ነበር፤ እኔ ግን ወዲያውኑ ነቅቼ አንድ ነገር እናገር ነበር። ሌሊቱ በዝግታ እያለፈ ሲሄድ እጅግ ደከመኝ፤ ነቅቼ ለመቆየትና አእምሮዬንም ለማጽናናት ብዙ መዝሙሮችን ዘመርሁ፤ ከቅዱሳት መጻሕፍት አንዳንድ ክፍሎችን ጮክ ብዬ በቃሌ ተናገርሁ፤ በእንግሊዝኛም ጸለይሁ፤ ይህም ጓደኞቼን እጅግ አበሳጫቸው፤ እንዳቆም ለማድረግ ማንኛውንም ነገር የሚሰጡ ይመስሉ ነበር። ከዚያ በኋላ ከእንግዲህ አላስቸገሩኝም፤ ጎሕ ሊቀድ ጥቂት ሲቀረውም ትተውኝ ሄዱ፤ እኔም ጥቂት ተኛሁ።
ኦገስት 6 ቀን።
ባለፈው ምሽት እንዲያ ያሳሳተኝ ወጣት ቀሰቀሰኝ። እጅግ ባለጌ ነበር፤ እንድነሣና ስለ ድካሙ እንድከፍለው አጥብቆ ጠየቀ፤ የሚፈልገውንም በኃይል ለማስፈጸም እስከ መሞከር ደረሰ። ይህ አስቈጣኝ፤ ባልተጠነቀቅሁበትም ቅጽበት፣ እጅግ ተገቢ ባልሆነ ስሜት፣ እችላለሁ ብሎ ባልጠበቀው ብርታት ክንዱን ጨምድጄ ያዝሁት፤ እስቲ ዳግመኛ ጣትህን አሳርፍብኝ ወይም ከዚህ በላይ አስቸግረኝ ብዬም ተገዳደርሁት። ይህ ጠባዩን ፈጽሞ ለወጠው፤ የከተማዪቱ በሮች መከፈታቸውን መድፎቹ እስኪያበስሩ ድረስ በጸጥታ እንድቆይ ተወኝ፤ ከዚያም ኦፒየም የሚገዛበት ገንዘብ እንድሰጠው ለመነኝ። ይህ እንደ ተከለከለ መናገር አያስፈልግም። ትናንት ሌሊት ከእኔ ጋር ሳለ አቃጥያለሁ ያላቸውን የሁለት ሻማዎች ዋጋ ሰጠሁት፤ ከዚያ በላይ አልሰጠሁትም። ከማንዳሪኑ ቢሮዎች ከአንዱ ጋር ግንኙነት እንዳለው ተረዳሁ።
በተቻለ ፍጥነት ለቁርስ የሩዝ ገንፎና ሻይ ገዛሁ፤ ከዚያም ዕቃዎቼን እንደገና ራሴ ፈለግሁ። በዚህ ያሳለፍኋቸው ጥቂት ሰዓታት ፍሬ ቢስ ስለ ሆኑ የመመለሻ ጉዞዬን ጀመርሁ፤ ረጅም፣ አድካሚና አሳማሚ የእግር ጉዞ ካደረግሁ በኋላም ቀትር ላይ (በስድስት ሰዓት ገደማ) ቻንግ-ጋን ደረስሁ። በዚህም ጥያቄዎቼ የጠፉትን ዕቃዎች ምንም ፍንጭ ሊያስገኙልኝ አልቻሉም፤ ስለዚህ በአንድ ሻይ ቤት ምግብ አሠርቼ በላሁ፤ በሚገባ ታጠብሁ፤ ያበጡ እግሮቼንም አጠብሁ፤ ከምሳ በኋላም እስከ ቀኑ አሥር ሰዓት ድረስ አርፌ ተኛሁ።
እጅግ ታድሼ፣ ከሁለት ቀን በፊት አገልጋዬንና ኩሊዎቹን በደቡቡ በር ወደ ተለየኋቸው ከተማ ለመመለስ ተነሣሁ። በመንገድ ላይም ስለ እግዚአብሔር ቸርነት እንዳሰላስል ተመራሁ፤ ትናንት ሌሊት ማረፊያ እንዲሰጠኝ በጸሎት እንዳልጠየቅሁም ትዝ አለኝ። በዙሪያዬ ያሉት ብዙ ክቡራን ነፍሳት እምብዛም ስሜት ሳይፈጥሩብኝ ለጥቂት ዕቃዎቼ እንዲያ መጨነቄም ወቀሰኝ። እንደ ኃጢአተኛ ቀርቤ የኢየሱስን ደም ተማጸንሁ፤ በእርሱ ተቀባይነት እንዳገኘሁ — ይቅር እንደ ተባልሁ፣ እንደ ነጻሁ፣ እንደ ተቀደስሁ — ተረዳሁ፤ ኦ፣ የኢየሱስ ፍቅር ምንኛ ታላቅ ሆኖ ተሰማኝ! መናቅና መጠላት፣ ራስን የሚያስጠጉበት ስፍራ ማጣትም ምን እንደ ሆነ ከዚያ በፊት ካወቅሁት በላይ ጥቂት አወቅሁ፤ በክብር ያለውን ቤቱን ትቶ ስለ እኔ እንዲህ መከራ እንዲቀበል፣ እንዲያውም ሕይወቱን በመስቀል ላይ አሳልፎ እንዲሰጥ ያደረገውን የዚያን ፍቅር ታላቅነት ከዚያ በፊት ከተሰማኝ ሁሉ ይበልጥ ተሰማኝ። «የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው፥ ደዌንም የሚያውቅ» እንደ ሆነ አሰብሁት፤ በያዕቆብ ጕድጓድ አጠገብ ደክሞ፣ ተርቦና ተጠምቶ፣ ነገር ግን የአባቱን ፈቃድ ማድረግ መብሉና መጠጡ ሆኖለት እንደ ነበረ አሰብሁት፤ ይህንንም ከፍቅሬ ማነስ ጋር አነጻጸርሁ። ስላለፈው ይቅርታን፣ ለወደፊቱም ፈቃዱን ለማድረግ፣ ፍለጋውን ይበልጥ በቅርብ ለመከተልና ከቀድሞው ይልቅ ፈጽሞ የእርሱ ለመሆን ጸጋንና ብርታትን ለማግኘት ወደ እርሱ ተመለከትሁ። ስለ ራሴ፣ በእንግሊዝ ስላሉ ወዳጆቼና በሥራው ስላሉ ወንድሞቼ ጸለይሁ። የደስታና የኀዘን ቅልቅል የሆኑ ጣፋጭ እንባዎች በነጻ ፈሰሱ፤ መንገዱም ሊረሳኝ ምንም አልቀረውም፤ ሳላውቀውም መድረሻዬ ደረስሁ። ከደቡቡ በር ውጭ አንድ ሲኒ ሻይ ጠጣሁ፤ ስለ ጠፋው ጓዜ ጠየቅሁ፤ ስለ ኢየሱስ ፍቅርም ተናገርሁ። ከዚያም ወደ ከተማዪቱ ገባሁ፤ ብዙ ከንቱ ጥያቄዎች ካቀረብሁ በኋላም በሰሜኑ በር ወጣሁ።
ወደ ከተማዪቱ ስሄድ በመንገድ ላይ ባገኘሁት ኅብረት በአእምሮም በአካልም እጅግ ስለ ታደስሁ፣ ወደ ሺህ-ሙን-ዋን የሚመልሰኝን የቀረውን ስድስት ማይል በዚያው ምሽት መጨረስ እንደምችል አሰብሁ። መጀመሪያ የአገሬውን ኬኮች ለመግዛት ወደ ሌላ ሻይ ቤት ገባሁ፤ እየበላኋቸውም ሳለሁ ማን ቢገባ ጥሩ ነው? በመጀመሪያው መንገድ ዕቃዎቼን ከተሸከሙት ኩሊዎች አንዱ ራሱ! ከእርሱም እንደ ተረዳሁት፣ እኔ ከተለየኋቸው በኋላ ጓዜን ወደ ደቡቡ በር ወስደው ነበር፤ በዚያም አገልጋዬ ሄደ፤ ተመልሶም እኔ ቀድሜ እንደ ሄድሁ፣ እርሱ ግን ወዲያውኑ ለመነሣት እንዳላሰበ፣ ይልቁንም ቀኑን ከወዳጁ ጋር አሳልፎ ከዚያ በኋላ እንደሚደርስብኝ ተናገረ፤ ዕቃዎቹንም ወደዚህ ወዳጁ ቤት ተሸክመው በዚያ ተዉአቸው። ከእኔ ጋር ወደ ቤቱ እንዲሄድ አደረግሁት፤ በዚያም ሰውየው ቀኑንና ሌሊቱን ከእነርሱ ጋር እንዳሳለፈ፣ በማግሥቱም ጠዋት ሌሎች ኩሊዎችን ጠርቶ ወደ ሃንግቻው እንደ ሄደ ተረዳሁ። ማወቅ የቻልሁት ይህን ብቻ ነበር፤ ስለዚህ በተቻለ ፍጥነት ወደ ሻንጋይ የመመለሻ ጉዞዬን ከመቀጠል በቀር ምንም ማድረግ ስላልቻልሁ ከተማዪቱን እንደገና ለቅቄ ወጣሁ። አሁን ወደ ሺህ-ሙን-ዋን ለመሄድ እጅግ መሽቶ ነበር። የሚያስፈልገኝን ሁሉ ሊሞላልኝ ወደሚችለው ወደ አባቴ ተመለከትሁ፤ አሁን በወንዙ ወለል ላይ ደርቆ በተቀመጠ አንድ ሆንግ ጀልባ (የመንገደኞች ጀልባ) ላይ እንዳድር ስጋበዝም የማያቋርጥ ፍቅሩንና እንክብካቤውን የሚያሳይ ሌላ ምልክት ተቀበልሁ። ሌሊቱ እንደገና እጅግ ቀዝቃዛ ነበር፤ ትንኞቹም አስቸጋሪዎች ነበሩ። ቢሆንም ጥቂት አረፍሁ፤ ፀሐይ ስትወጣም ተነሥቼ ጉዞዬን ቀጠልሁ።
ኦገስት 7 ቀን።
መጀመሪያ እጅግ ታምሜ ነበር፤ ጕሮሮዬም ይቈስለኝ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ያህል ጊዜ የቀኑን ሙቀትና የሌሊቱን ብርድ እንድችል ስላስቻለኝ ስለ እግዚአብሔር አስደናቂ ቸርነት አሰላሰልሁ። አሁን ከአእምሮዬ ላይ ትልቅ ሸክም እንደ ተነሣልኝም ተሰማኝ። ራሴንና ጉዳዮቼን ለጌታ አደራ ሰጥቼ ነበር፤ ለእኔ መልካምነትና ለእርሱ ክብር ከሆነ ዕቃዎቼ እንደሚመለሱልኝ፣ ካልሆነ ደግሞ ሁሉ ለበጎ እንደሚሆን አውቅ ነበር። የጉዞዬ እጅግ አስቸጋሪው ክፍል አሁን ወደ መጨረሻው እየተቃረበ እንደ ሆነ ተስፋ አደረግሁ፤ ይህም ደክሜና እግሬ ቈስሎ ሳለ በመንገዴ ረዳኝ። ሺህ-ሙን-ዋን ደርሼ ቁርስ ከበላሁ በኋላ አሁንም በእጄ ስምንት መቶ ዐሥር ካሽ እንዳለኝ አገኘሁ፤ እስከ ኪያ-ሂንግ ፉ ያለው የሆንግ ጀልባ ዋጋ አንድ መቶ ሃያ ካሽ፣ ከዚያም እስከ ሻንጋይ ሦስት መቶ ስድሳ ካሽ እንደ ሆነ አውቅ ነበር፤ ይህም ለሦስት ወይም ለአራት ቀን ስንቅ ልክ ሦስት መቶ ሠላሳ ካሽ — ወይም ዐሥራ ሁለት ፔኒና ጥቂት ስባሪ — ያስቀርልኝ ነበር። ወዲያውኑ ወደ ጀልባ ቢሮው ሄድሁ፤ ነገር ግን ወንዙ ደርቆ ስለ ነበር ዕቃዎች እንዳልወረዱ፣ ስለዚህም ዛሬ ምንም ጀልባ እንደማይነሣ፣ ምናልባትም ነገ እንደማይነሣ ሳገኝ ደነገጥሁ። ወደ ኪያ-ሂንግ ፉ የሚሄዱ የደብዳቤ ጀልባዎች አይኖሩም ወይ ብዬ ጠየቅሁ፤ ቀድመው እንደ ሄዱም ተነገረኝ። የቀረው ብቸኛ አማራጭ የምሳፈርባቸው የግል ጀልባዎች የሚሄዱ እንደ ሆነ ማጣራት ነበር። ፍለጋዬ ግን በከንቱ ቀረ፤ እስከ ሻንጋይ ድረስ ሊወስደኝ የሚስማማ አንድም ጀልባ ላገኝ አልቻልሁም፤ ባገኝ ኖሮ ችግሬ ባበቃ ነበር።
ልክ በዚህ ጊዜ በቦዩ መታጠፊያ ላይ ወደ ኪያ-ሂንግ ፉ አቅጣጫ የሚሄድ አንድ የደብዳቤ ጀልባ በፊቴ አየሁ። ይህ ሳይታሰብ ከዘገዩት ከኪያ-ሂንግ ጀልባዎች አንዱ መሆን አለበት ብዬ ደመደምሁ፤ ተስፋና የሁኔታው ግድ የቻሉትን ያህል ፈጥኜ ተከተልሁት። ለጊዜው ድካምም የእግር ቍስልም ተረሱ። አንድ ማይል ያህል ካሳደድሁት በኋላ ደረስሁበት።
«ወደ ኪያ-ሂንግ ፉ ትሄዳላችሁን?» ብዬ ጮኽሁ።
«አይ» የሚል ብቻ ነበር መልሱ።
«ወደዚያ አቅጣጫ ትሄዳላችሁን?»
«አይ።»
«በዚያ አቅጣጫ እስከምትሄዱበት ድረስ ታሳፍሩኛላችሁን?»
አሁንም «አይ»፤ ከዚያ በላይ ምንም የለም።
ፈጽሞ ተስፋ ቈርጬና ዝዬ በሣሩ ላይ ወደቅሁ፤ ራሴንም ሳትሁ።
ራሴን እያወቅሁ ስመጣ አንዳንድ ድምፆች ወደ ጆሮዬ ደረሱ፤ ስለ እኔ እየተነጋገሩ እንደ ሆኑም አወቅሁ። አንዱ፦ «ንጹሕ የሻንጋይ ዘዬ ይናገራል» አለ፤ እኔም ከራሳቸው አነጋገር የሻንጋይ ሰዎች እንደ ሆኑ አወቅሁ። ቀና ብዬ ስመለከት ከቦዩ ማዶ በአንድ ትልቅ ሆንግ ጀልባ ላይ እንዳሉ አየሁ፤ ጥቂት ከተነጋገርንም በኋላ ትንሿን ጀልባቸውን ልከው አስመጡኝ፤ እኔም ወደ ጀንኩ ተሳፈርሁ። እጅግ ደጎች ነበሩ፤ ሻይም ሰጡኝ፤ ታድሼም መመገብ በቻልሁ ጊዜ ምግብም ሰጡኝ። ከዚያም እግሮቼን ለማሳረፍ ጫማዬንና ካልሲዬን አወለቅሁ፤ ጀልባ ነጂውም እግሮቼን የምታጠብበትን ሙቅ ውኃ በደግነት አቀረበልኝ። ታሪኬን ሰምተው በእግሮቼ ላይ ያሉትን ቍስሎች ባዩ ጊዜ በግልጽ አዘኑልኝ፤ የሚያልፈውንም ጀልባ ሁሉ በእኔ አቅጣጫ ይሄድ እንደ ሆነ ለማየት ይጠሩ ነበር። አንድም ስላላገኙ፣ ከጥቂት ሰዓታት እንቅልፍ በኋላ በክዋን-ቲ ቤተ መቅደስ ልሰብክ አስቤ ከካፒቴኑ ጋር ወደ የብስ ወረድሁ።
ከጀንኩ ከመውረዴ በፊት ለካፒቴኑና በጀልባው ላይ ለነበሩት ሰዎች አሁን ራሴን መርዳት እንደማልችል፣ እስከ ኪያ-ሂንግ ፉ በእግሬ ለመሄድ ኃይል እንደሌለኝ፣ ዛሬ የምሳፈርበት ጀልባ ባለማግኘቴም ውድ የጉዞ መንገድ በሆነው በደብዳቤ ጀልባ ወደዚያ የሚያደርሰኝ በቂ ገንዘብ ከእንግዲህ እንደሌለኝ ነገርኋቸው፤ የማገለግለው አምላክ እንዴት እንደሚረዳኝ ባላውቅም እንደሚረዳኝ ግን ምንም ጥርጥር እንደሌለኝ፣ የአሁኑ ሥራዬም ባለሁበት ስፍራ እርሱን ማገልገል እንደ ሆነ ነገርኋቸው። ደግሞም እንደሚመጣ የማውቀው ርዳታ እኔና በሻንጋይ ያሉት ሌሎች ሚስዮናውያን የምንሰብከው ሃይማኖት እውነት ለመሆኑ ማስረጃ ሊሆናቸው እንደሚገባ ነገርኋቸው።
ወደ ከተማዪቱ እየሄድን ከካፒቴኑ ጋር እየተነጋገርን ሳለ አንድ የደብዳቤ ጀልባ ሲመጣ አየን። ካፒቴኑ እንዳየው ጠቈመኝ፤ እኔ ግን በእርሱ ለመሳፈር የምከፍለው ከእንግዲህ እንደሌለኝ አስታወስሁት። እርሱ ግን ቢሆንም ጠራው፤ ከሻንጋይ ዘጠኝ የእንግሊዝ ማይል ያህል ወደሚርቅ ስፍራ እንደሚሄድ፣ ከዚያም ከጀልባ ነጂዎቹ አንዱ ደብዳቤዎቹን በየብስ ወደ ከተማዪቱ እንደሚወስድ አወቀ። ከዚያም እንዲህ አለ፦ «ይህ ሰው ከሻንጋይ የመጣ የውጭ አገር ሰው ነው፤ ተዘርፎአል፤ ለመመለስም ከእንግዲህ አቅም የለውም። እስከምትሄዱበት ድረስ ይዛችሁት ብትሄዱና ከዚያም ቀሪውን መንገድ የሚወስደው በሰዎች ትከሻ የሚሸከም ወንበር ብትቀጥሩለት በሻንጋይ ይከፍላችኋል። ጀልባዬ ውኃ በማጣት እዚያ መሬት ላይ ተቀርቅራ እንዳለችና መሄድ እንደማትችል ታያላችሁ። እንግዲህ እኔ ዋስ እሆናለሁ፤ ይህ ሰው ሻንጋይ ስትደርሱ ካልከፈለ፣ ስትመለሱ እኔ እከፍላለሁ።» ፍጹም እንግዳ የሆነ አንድ ቻይናዊ ይህን ያልተጠየቀውን ደግነት ማድረጉ በአጠቃላይ ገንዘባቸውን አደጋ ላይ ለመጣል እጅግ የማይፈልጉትን የቻይናውያንን ጠባይ ለሚያውቅ ሰው ሁሉ ይበልጥ አስደናቂ ሆኖ ይታያል። በደብዳቤ ጀልባው ላይ ያሉት በስምምነቱ ስለ ተስማሙ እንደ መንገደኛ ተሳፈርሁ። ኦ፣ ለዚህ የእግዚአብሔር መግቦት ጣልቃ ገብነትና እንደገና ወደ ሻንጋይ በመንገዴ ላይ በመሆኔ ምንኛ አመሰገንሁ!
አሁን የምጓዝበትን የመሰሉት የደብዳቤ ጀልባዎች ረጃጅምና ጠባቦች ናቸው፤ ውስጣቸውም እጅግ ጠባብ ነው። ትንሽ እንቅስቃሴ በቀላሉ ስለሚገለብጣቸው በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ሁሉ ሰው ተጋድሞ መቆየት አለበት። ይህ ግን ለእኔ የሚያሰለች ሁኔታ አልነበረም፤ በተቃራኒው ጸጥ ብዬ በመቆየቴ እጅግ ደስ አለኝ። በቻይና ካየኋቸው ጀልባዎች ሁሉ እጅግ ፈጣኖቹ ናቸው። እያንዳንዳቸውን ቀንና ሌሊት ያለማቋረጥ እየተፈራረቁ የሚሠሩ ሁለት ሰዎች ያንቀሳቅሷቸዋል። በእግራቸው ትልቁን መቅዘፊያ ይቀዝፋሉ፤ በእጃቸውም በትንሽ መቅዘፊያ ይቀዝፋሉ፤ ወይም ነፋሱ ፍጹም ተስማሚ ከሆነ በእግራቸው እየቀዘፉ በአንድ እጃቸው ትንሽ ሸራ ይቆጣጠራሉ፤ በሌላው እጃቸውም ጀልባዋን ይመራሉ።
አስደሳችና ፈጣን ጉዞ ካደረግሁ በኋላ፣ «አልለቅህም ከቶም አልተውህም» ባለው፣ «እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ» ባለውም በእርሱ ርዳታ ኦገስት 9 ቀን በሰላም ሻንጋይ ደረስሁ።
ምዕራፍ 13 ተጠናቋል
ሰው ያስባል፣ እግዚአብሔር ይፈጽማል