የመንፈስ ቅዱስ ማንነትና ሥራ
መንፈስ ለአብና ለወልድ መገዛቱ

ምዕራፍ 4 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

መንፈስ ለአብና ለወልድ መገዛቱ

መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ አካል በመሆኑ ብቻ በሁሉም ረገድ ከአብ ጋር እኩል ነው ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ እንደሚኖር (ቆላስይስ 2:9)፣ እርሱም በእውነትና በፍጹም መለኮታዊ ከመሆኑ የተነሣ «እኔና አብ አንድ ነን» (ዮሐንስ 10:30)፣ እንዲሁም «እኔን ያየ አብን አይቶአል»

(ዮሐንስ 14:9) ሊል እንደሚችል ቢያስተምርም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሁሉም ረገድ ከአብ ጋር እኩል እንዳልነበረ፣ ይልቁንም በብዙ መንገድ ለአብ የሚገዛ እንደ ነበረ በዚያው ልክ በግልጽ ያስተምራል። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ አካል ቢሆንም ለአብና ለወልድ የሚገዛ መሆኑን ያስተምረናል።

በዮሐንስ 14:26 መንፈስ ቅዱስ በአብ፣ ደግሞም በወልድ ስም እንደሚላክ ተምረናል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል በግልጽ ያውጃል፦ «አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል» በዮሐንስ 15:26 ደግሞ መንፈስን ከአብ ዘንድ የሚልከው ኢየሱስ ነው። ቃሉ እንዲህ ይላል፦ «ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል» በሌላ ስፍራ ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ እንደ ተላከ እንደ ተማርን (ዮሐንስ 6:29፤ 8:29፣ 42)፣ እዚህ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በተራው በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚላክ ተምረናል።

መንፈስ ቅዱስ ለአብና ለወልድ የሚገዛ መሆኑ አንዳንድ ስሞቹን ከአብና ከወልድ በማግኘቱም ይታያል። በሮሜ 8:9 «እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም» እናነባለን። እዚህ ሁለት የመንፈስ ስሞች አሉን፤ አንዱ ከአብ ጋር ካለው ግንኙነት የተገኘ «የእግዚአብሔር መንፈስ»፣ ሌላው ደግሞ ከወልድ ጋር ካለው ግንኙነት የተገኘ «የክርስቶስ መንፈስ» ነው።

በሐዋርያት ሥራ 16:7 «የኢየሱስ መንፈስ» ተብሎ ተጠርቶአል። መንፈስ ለወልድ የሚገዛ መሆኑ መንፈስ ቅዱስ «የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርም» በመባሉም ይታያል። በዮሐንስ 16:13 «ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል» እናነባለን። መንፈስ ለወልድ የሚገዛ መሆኑ ራሱን ሳይሆን ክርስቶስን ማክበር የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንደ ሆነ በተገለጠው ሐቅም እንደ ገና ይታያል። ኢየሱስ በዮሐንስ 16:14 እንዲህ ይላል፦ «እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና» በተመሳሳይም ኢየሱስ ራሱን ታላቅ ለማስመሰል አልሞከረም፤ የላከውን አባቱን ሊያከብር ፈለገ።

ከእነዚህ ክፍሎች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በአሁኑ ሥራው የመለኮት ባሕርያት ሁሉ ያሉት ሆኖ ሳለ ለአብና ለወልድ እንደሚገዛ ግልጽ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደ ኖረ፣ እንዳስተማረና እንደ ሠራ ወደ ኋላ እናያለን።

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ