የመንፈስ ቅዱስ ማንነትና ሥራ
መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተለየ መሆኑ

ምዕራፍ 3 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተለየ መሆኑ

እስካሁን መንፈስ ቅዱስ አካል፣ ያውም መለኮታዊ አካል እንደ ሆነ አይተናል። አሁን ደግሞ ሌላ ጥያቄ ይነሣል፦ እርሱ እንደ አካል ከአብና ከወልድ ተለይቶ የሚታወቅ የተለየ አካል ነውን? የአዲስ ኪዳንን ቃሎች በጥንቃቄ የሚያጠና ሰው ያለ አንዳች ጥርጥር እንደዚያ መሆኑን ከማግኘት ሊያመልጥ አይችልም። በሉቃስ 3:21-22 እንዲህ እናነባለን፦ «ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ»።

እዚህ በሦስቱ መካከል የሚቻለውን ያህል ግልጽ ልዩነት ተደርጎአል፦ በምድር በነበረው በኢየሱስ ክርስቶስ፣ አንድ አካል ሌላውን አካል እንደሚያናግር ከሰማይ ሆኖ በተናገረው በአብ፣ እንዲሁም በአካል መልክ እንደ ርግብ ከሚናገረው ከአብ ዘንድ ወደሚናገረው ወደ ወልድ በወረደውና ከወልድ የተለየ አካል ሆኖ በእርሱ ላይ ባረፈው በመንፈስ ቅዱስ መካከል። በማቴዎስ 28:19 የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስሞች በግልጽ ተለይተው እናያለን፤ በዚያ «እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ … ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው» እናነባለን። መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የተለየ መሆኑ በዮሐንስ 14:16 እንደ ገና እጅግ በግልጽ ይታያል፤ በዚያ «እኔም አብን እለምናለሁ፥ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል» እናነባለን። እዚህ አንዱ አካል ወልድ ወደ ሌላው አካል ወደ አብ ሲጸልይ፣ የሚጸለይለት አብም ለሁለተኛው አካል ለወልድ ጸሎት መልስ ሌላ አካልን፣ ሌላ አጽናኝን ሲሰጥ እናያለን።

ቃላት አንዳች ትርጉም ካላቸው — በመጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በእርግጥ የሚሉትን ማለታቸው ነው — አብ፣ ወልድና መንፈስ ሦስት የተለያዩና የተለዩ አካላት መሆናቸውን መሳት አይቻልም። ደግሞም በዮሐንስ 16:7 ወደ አብ በሚሄደው በኢየሱስና በእርሱ ፋንታ ሊተካ ከአብ ዘንድ በሚመጣው በመንፈስ ቅዱስ መካከል ግልጽ ልዩነት ተደርጎአል። ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦ «እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ»።

ተመሳሳይ ልዩነት በሐዋርያት ሥራ 2:33 ተደርጎአል፤ በዚያ «ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው» እናነባለን። በዚህ ክፍል ወደ አብ ቀኝ ከፍ ከፍ ባለው በወልድ፣ እርሱ ወደ ቀኙ ከፍ ከፍ ባለበት በአብ፣ እንዲሁም ወልድ ከአብ ተቀብሎ በቤተ ክርስቲያን ላይ ባፈሰሰው በመንፈስ ቅዱስ መካከል የሚቻለውን ያህል ግልጽ ልዩነት ተደርጎአል።

ይህን ሁሉ ስናጠቃልል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሦስቱ አካላት — በመንፈስ ቅዱስ፣ በአብና በወልድ — መካከል የሚቻለውን ያህል ግልጽ ልዩነት ያደርጋል። እነርሱ እርስ በርሳቸው ግንኙነት ያላቸው፣ አንዱ በሌላው ላይ የሚሠሩ፣ አንዱ ስለ ሌላው ወይም ለሌላው የሚናገሩ፣ እርስ በርሳቸውም የሁለተኛና የሦስተኛ መደብ ተውላጠ ስሞችን የሚጠቀሙ ሦስት የተለያዩ አካላት ናቸው።

ምዕራፍ 3 ተጠናቋል

መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተለየ መሆኑ

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ