ምዕራፍ 21 · 9 ደቂቃ ንባብ · 11 ደቂቃ ማዳመጥ
መንፈስ ቅዱስ በነቢያትና በሐዋርያት ውስጥ የሚሠራው ሥራ
መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያትና በነቢያት ውስጥ የሚሠራው ሥራ ፈጽሞ ልዩ ነው። ለሐዋርያትና ለነቢያት ለልዩ ዓላማ ልዩ ስጦታን ይሰጣቸዋል።
በ1ኛ ቆሮንቶስ 12:4-11፣ 28-29 እንዲህ እናነባለን፦ «የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው…
ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። … እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል። ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን?» በሐዋርያትና በነቢያት ውስጥ የሚሠራው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ልዩ እንደ ሆነ ከእነዚህ ቍጥሮች ግልጽ ነው።
መንፈስ ቅዱስ በሰባኪዎች፣ በአስተማሪዎችና በተራ አማኞች ውስጥ ወደ እውነት እየመራቸውና የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን እየከፈተ የሚሠራው ሥራ በነቢያትና በሐዋርያት ውስጥ ከሚሠራው ሥራው ጋር አንድ ነው፤ ልዩነቱም በመጠን ብቻ ነው የሚለው ትምህርት በዘመናችን እጅግ እየተለመደ መጥቶአል። ይህ ትምህርት ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነና ሐሰት እንደ ሆነ አሁን ከጠቀስነው ክፍል ግልጽ ነው። «መንፈስ ግን አንድ ነው» ቢባልም «የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው»፣ «አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው»፣ «አሠራርም ልዩ ልዩ ነው» (1ኛ ቆሮንቶስ 12:4-6) ተብሎ በግልጽ የተነገረውን፣ እንዲሁም «ሁሉስ ነቢያት ናቸውን?»፣ «ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን?» (1ኛ ቆሮንቶስ 12:29) ተብሎ ሁሉ ነቢያት፣ ሁሉም ሐዋርያት እንዳልሆኑ የተገለጠውን እውነት ቸል ይላል።
የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በሐዋርያትና በነቢያት ውስጥ ባለውና በሌሎች ሰዎች ውስጥ ባለው ሥራው መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳነስ የሚሞክር አንድ ስመ ጥር ሰባኪ፣ ባስልኤል የቤተ መቅደሱን ሥራ ይቀይስ ዘንድ «በእግዚአብሔር መንፈስ» እንደሚሞላ መጽሐፍ ቅዱስ መናገሩን ያነሣል (ዘጸአት 31:1-11)።
ይህንንም የነቢዩ በመንፈስ አነሣሽነት መናገር ከሠዓሊው ወይም ከመሐንዲሱ መነሣሣት እንደማይለይ ማስረጃ አድርጎ ያቀርበዋል፤ ይህን ሲያደርግ ግን ቤተ መቅደሱ «በተራራው ለሙሴ እንደ ተገለጠለት ምሳሌ» (ዘጸአት 25:9፣ 40) ሊሠራ እንደ ነበረና ስለዚህም ራሱ ትንቢትና የእግዚአብሔርን እውነት የሚገልጥ ትምህርት እንደ ነበረ ይዘነጋል። ተራ የሕንጻ ጥበብ አልነበረም። በእንጨት፣ በወርቅ፣ በብር፣ በናስ፣ በጨርቅ፣ በቁርበትና በሌሎችም ነገሮች የተገለጠ የእግዚአብሔር ቃል ነበር። ሐዋርያው ወይም ነቢዩ የእግዚአብሔርን ቃል በብራና ላይ በብዕርና በቀለም ለመግለጥ ልዩ የመንፈስ አነሣሽነት እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ባስልኤልም እውነትን በእንጨት፣ በወርቅ፣ በብር፣ በናስና በሌሎችም ለመግለጥ ያንኑ ያህል ልዩ የመንፈስ አነሣሽነት ያስፈልገው ነበር። በዘመናችን ስለ መንፈስ አነሣሽነት በመጀመሪያ ሲታይ እጅግ የተማረ የሚመስል ብዙ ክርክር አለ፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛ አባባሎች ጋር በጥብቅ ሲመዘን አይቆምም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመገናኛው ድንኳን የበለጠ በመንፈስ አነሣሽነት የተሰጠ ነገር የለም፤ አፍራሽ ተቺዎችም ይህን ድንኳን ይበልጥ ቢያጠኑ፣ አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ከልዩ ልዩ ምንጮች ተቀናብረዋል ስለሚለው ብልሃት የተሞላበት ነገር ግን ደካማ ስለ ሆነው ንድፈ ሐሳባቸው ተስፋ በቈረጡ ነበር።
2. ለዘመናት ከሰው የተሰወረና ሰዎች ያለ ረዳት በሰው አእምሮ ምርምር ያላገኙትና ሊያገኙትም ያልቻሉት እውነት ለሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ ተገልጦአል። በኤፌሶን 3:3-5 እንዲህ እናነባለን፦ «አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤ ይህም ምሥጢር አሁን ለቅዱሳን ሐዋርያቱና ለነቢያቱ በመንፈስ እንደ ተገለጠ፥ በሌሎች ትውልዶች ለሰው ልጆች አልታወቀም ነበር።» መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ከመናገሩ በፊት ሰዎች ፈጽሞ ያላገኙትን እውነት ይዞአል። ሰዎች ለራሳቸው ቢተዉ ኖሮ ፈጽሞ ሊያገኙት የማይችሉትን እውነት ይዞአል።
የሰማዩ አባታችን በታላቅ ጸጋው ይህን እውነት በአገልጋዮቹ በሐዋርያትና በነቢያት በኩል ለእኛ ለልጆቹ ገልጦልናል። የዚህ መገለጥ አድራጊ መንፈስ ቅዱስ ነው። ዛሬ ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን አባባሎች በሰው አእምሮ ምርምር መደምደሚያዎች ወይም «በክርስቲያናዊ ንቃተ ህሊና» ልንፈትናቸው ይገባናል ይሉናል። የእግዚአብሔር መገለጥ ከሰው አእምሮ ምርምር እንደሚልቅ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማጥናትና በውስጥ በመዋሐድ ያልተገኘ ንቃተ ህሊናም ሁሉ ክርስቲያናዊ ንቃተ ህሊና እንዳልሆነ ስናስብ የዚህ ሁሉ ሞኝነት ግልጽ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ፈጽሞ ያላገኘውን እውነት እንደ ያዘ መጻሕፍት ራሳቸው ይናገራሉ፤ እኛም ይህን በተግባር የተረጋገጠ እውነት አድርገን እናውቀዋለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምራቸው እጅግ ልዩና ውድ ትምህርቶች ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ያገኙት አንድም የለም። ንቃተ ህሊናችን የእግዚአብሔር መጽሐፍ መሆኑ ከቶ ግልጽ ከሆነው ከዚህ መጽሐፍ አባባሎች የሚለይ ከሆነ፣ ገና ፍጹም ክርስቲያናዊ አልሆነም፤ ልናደርገው የሚገባንም የእግዚአብሔርን መገለጥ ወደ ንቃተ ህሊናችን ደረጃ ዝቅ ለማድረግ መሞከር ሳይሆን ንቃተ ህሊናችንን ወደ እግዚአብሔር ቃል ደረጃ ከፍ ማድረግ ነው።
3. ለነቢያት የተሰጠው መገለጥ ከራሳቸው አሳብ የተለየ ነበር። በእነርሱ ውስጥ በነበረው በክርስቶስ መንፈስ ተሰጣቸው። ትርጉሙም ምን እንደ ሆነ አእምሮአቸው ይመረምረው ነበር። አሳቡ የእርሱ እንጂ የእነርሱ አልነበረም። በ1ኛ ጴጥሮስ 1:10-12 እንዲህ እናነባለን፦ «ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር። ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን ባወሩላችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፤ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።» እነዚህ ቃላት በነቢያት ውስጥ ያለ፣ ከነቢያትም የተለየ አንድ አካል፣ ያም አካል መንፈስ ቅዱስ፣ ከአሳባቸው የተለየውን፣ እነርሱ ራሳቸው ፈጽመው ያላስተዋሉትንና በትጋት ሊፈልጉትና ሊያጠኑት ያስፈለጋቸውን እውነት እንደ ገለጠ ግልጽ ያደርጋሉ። የሚያስበውና የሚናገረው ከእነርሱ የተለየ ሌላ አካል ነበር፤ እነርሱም እርሱ የተናገረውን ለማስተዋል ይፈልጉ ነበር።
4. ከነቢያት ንግግር አንዱም በነቢዩ በራሱ ፈቃድ አልመጣም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ተናገረ፤ ነቢዩም በንግግሩ በመንፈስ ቅዱስ ይነዳ ነበር። በ2ኛ ጴጥሮስ 1:21 እንዲህ እናነባለን፦ «ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።»
እንግዲህ ነቢዩ በሌላው እጅ ያለ መሣሪያ ብቻ ነበር፤ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ነዳው እንዲሁ ተናገረ።
5. በትንቢታዊ ንግግሮች ውስጥ የተናገረው መንፈስ ቅዱስ ነበር። በነቢዩ አንደበት ላይ የነበረው የእርሱ ቃል ነበር። በዕብራውያን 3:7 «ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል። ‹ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት…›» እናነባለን። ደግሞም በዕብራውያን 10:15-16 «መንፈስ ቅዱስም ደግሞ ይመሰክርልናል፤ ‹ከዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ በአሳባቸውም እጽፈዋለሁ›» እናነባለን።
ደግሞም በሐዋርያት ሥራ 28:25 «እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ። ‹መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን … መልካም ተናገረ፤› ወዘተ.» እናነባለን። ደግሞም በ2ኛ ሳሙኤል 23:2 «የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፥ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነው» እናነባለን። በእነዚህ ክፍሎች በትንቢታዊ ንግግሮች ውስጥ ተናጋሪው መንፈስ ቅዱስ እንደ ነበረ፣ በነቢዩም አንደበት ላይ የነበረው የእነርሱ ሳይሆን የእርሱ ቃል እንደ ነበረ ተነግሮናል። ነቢዩ መንፈስ ቅዱስ የተናገረበት አፍ ብቻ ነበር። እንደ ሰው፣ ማለትም መንፈስ ካስተማረውና ከተጠቀመበት ውጭ ሲሆን፣ ነቢዩ እንደ ሌሎች ሰዎች ደካማ ሊሆን ይችል ነበር፤ መንፈስ በእርሱ ላይ በነበረ ጊዜና በመንፈስ ቅዱስ ተነሥቶ በተነዳ ጊዜ ግን በትምህርቱ ፍጹም ነበር፤ በዚያን ጊዜ ትምህርቱ የራሱ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ትምህርት ነበርና።
እንዲህ በመንፈስ ቅዱስ በተነዳ ጊዜ የሚናገረው ነቢዩ ሳይሆን እግዚአብሔር ነበር። ለምሳሌ ጳውሎስ ስለ ብዙ ነገሮች ብዙ የተሳሳቱ እምነቶች እንደ ነበሩት ብዙም አያጠራጥርም፤ ነገር ግን በመንፈስ ኃይል እንደ ሐዋርያ ባስተማረ ጊዜ ፍጹም ነበር፤ ይልቁንም በእርሱ በኩል ያስተማረው መንፈስ ስሕተት የሌለበት ነበር፤ የዚህም ውጤት የሆነው ትምህርት እንደ እግዚአብሔር ራሱ ፍጹም ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ እንደ ሰው ያሰበውን ሊሆን የሚችለውንና እንደ ሐዋርያ በእርግጥ ያስተማረውን በጥንቃቄ መለየታችን መልካም ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለን እንደ ሐዋርያ ያስተማረው መዝገብ ነው። አንዳንዶች በ1ኛ ቆሮንቶስ 7:6፣ 25 «ዳሩ ግን ይህን እንደ ፈቃድ እላለሁ እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም … ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ» ሲል ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ የጌታ ቃል እንዳለው እርግጠኛ እንዳልነበረ አምኖ ይቀበላል ብለው ያስባሉ። ይህ የክፍሉ እውነተኛ ትርጉም ከሆነ (ይህም ከመጠራጠር በላይ አጠያያቂ ነው)፣ ጳውሎስ እርግጠኛ ባልሆነ ጊዜ ይህን ለማመልከት ምን ያህል ጥንቁቅ እንደ ነበረ እናያለን፤ ይህም በሌሎቹ ክፍሎች ሁሉ ተጨማሪ እርግጠኛነት ይሰጠናል።
አንዳንድ ጊዜ ጳውሎስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ጌታ በእርሱ የሕይወት ዘመን እንደሚመለስ አስተምሮ ነበር፤ በዚህም ተሳስቶአል ይባላል። ጳውሎስ ግን ጌታ በእርሱ የሕይወት ዘመን እንደሚመለስ በየትም ስፍራ ፈጽሞ አላስተማረም።
እርግጥ በ1ኛ ተሰሎንቄ 4:17 «ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን» ይላል። ቃላቱን በጻፈ ጊዜ ገና በሕይወት ስለ ነበረ፣ ስለ ጌታ መመለስ ሲናገር ራሱን አስቀድመው ካንቀላፉት ጋር አልቈጠረም። ይህ ግን ጌታ እስኪመጣ ድረስ በሕይወት እንደሚቆይ ማረጋገጡ አይደለም።
በዚያ የአገልግሎቱ ዘመን በሕይወት ሊቆይ ይችላል የሚል ተስፋ ነበረው፤ ስለዚህም በመጠባበቅ ዝንባሌ ይኖር ነበር፤ የመጠባበቅ ዝንባሌ ግን በዘመናት ሁሉ ለእያንዳንዱ አማኝ እውነተኛው ዝንባሌ ነው። ጳውሎስ እስከ ጌታ መምጣት ድረስ በሕይወት እንደሚኖር ጠብቆ ሊሆን ይችላል፤ ያን ቢጠብቅም እንኳ አላስተማረውም። መንፈስ ቅዱስ በትምህርቱ ከሌሎቹ ስሕተቶች ሁሉ እንደ ጠበቀው ከዚህም ጠበቀው።
6. በሐዋርያው ውስጥ የነበረው መንፈስ ቅዱስ ያስተማረው አሳቡን (ወይም «ጽንሰ ሐሳቡን») ብቻ ሳይሆን አሳቡ የሚገለጥባቸውን ቃላትም ጭምር ነው። በ1ኛ ቆሮንቶስ 2:13 እንዲህ እናነባለን፦ «መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።» ይህ ክፍል አሳቡ ብቻ ሳይሆን ቃላቱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርጠውና ተምረው እንደ ተሰጡ ያስተምራል። ይህም አሳብ ከአእምሮ ወደ አእምሮ የሚተላለፈው በቃላት ስለ ሆነ፣ አሳቡንም የሚገልጡት ቃላቱ ስለ ሆኑ፣ ቃላቱ ፍጹማን ባይሆኑ በእነዚህ ቃላት የተገለጠው አሳብ የግድ ፍጹም ያልሆነና በዚያው መጠን እውነት ያልሆነ ይሆን ስለ ነበር፣ የማይቀር መደምደሚያ ነው።
ጳውሎስ «መንፈስ በሚያስተምረን ቃል» ብሎ ከተናገረው የበለጠ ግልጽ ሊሆን የሚችል ነገር የለም። መንፈስ ቅዱስ ራሱ በሐዋርያት ውስጥ ስለ ሠራው ሥራው የሚነሡትን ዘመናዊ፣ ብልሃት የተሞላባቸውን፣ ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑትንና ሐሰተኛ ንድፈ ሐሳቦችን ሁሉ አስቀድሞ አውቆ መልስ ሰጥቶባቸዋል። የዚህን ድንቅ መጽሐፍ አባባሎች አገላለጽ ይበልጥ በጥንቃቄና በትክክል ባጠናን መጠን፣ አሳቡን ለመግለጥ የተመረጡት ቃላት እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ትክክለኛ መሆናቸውን ይበልጥ እንረዳለን። ብዙ ጊዜ የአንድ አስቸጋሪ የሚመስል ነገር መፍትሔ የሚገኘው የተጠቀሙትን ቃላት በትክክል በማጥናት ነው። የተጠቀሙት ቃላት ትክክለኛነት፣ ጥራትና ፍጹምነት የሚያስደንቅ ነው።
ላይ ላዩን ለሚያጠና ተማሪ ቃላቱ ራሳቸው በመንፈስ አነሣሽነት ተሰጥተዋል የሚለው ትምህርት አጠያያቂ፣ እንዲያውም የማይመስል ሊመስለው ይችላል፤ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስን ቃላት ዘወትር የሚያሰላስል ማንኛውም ዳግመኛ የተወለደና በመንፈስ የተማረ ሰው የእግዚአብሔር ጥበብ ቃላቱ ሊገልጡት በሚሞክሩት አሳብ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቃላቱ ራሳቸው ውስጥ እንዳለ ይረዳል። የአንድ ቃል፣ የአንድ ፊደል፣ የአንድ ጊዜ አመልካች፣ የአንድ የሰዋስው ሁኔታ ወይም የቍጥር ለውጥ በብዙ ስፍራዎች ወደ ተቃርኖ ወይም ወደ ሐሰት በጣለን ነበር፤ ቃላቱን ግን ልክ እንደ ተጻፉ ስንወስዳቸው አስቸጋሪ ነገሮች ይጠፋሉ፤ እውነትም ደምቆ ይበራል። ከቍስ አካል እጅግ ጥቃቅን ቅንጣቶች የቅርጽን ፍጹምነትና ለዓላማቸው የሚስማሙበትን ብልሃት በአጕሊ መነጽር ስናይ፣ የተፈጥሮ መለኮታዊ መገኛ ይበልጥ በግልጽ ይበራል።
እንዲሁም የአንድ ቃል አገላለጽ የእግዚአብሔርን ፍጹም አሳብ የሚገልጥበትን ፍጹምነት ስናስተውል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ መገኛ በአጕሊ መነጽር ሥር ይበልጥ በግልጽ ይበራል።
ነገር ግን አንድ ሰው፦ «መንፈስ ቅዱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ደራሲ ከሆነ፣ የአጻጻፍ ስልትና የአገላለጽ ልዩነቶችን እንዴት እናብራራቸዋለን? ለምሳሌ ጳውሎስ ሁልጊዜ የጳውሎስን ዓይነት አነጋገር፣ ዮሐንስም የዮሐንስን ዓይነት አነጋገር ወዘተ. የተጠቀመው ለምን እንደ ሆነ እንዴት እናብራራለን?» ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። የዚህ መልስ እጅግ ቀላል ነው። ይህን ነገር ማብራራት ባንችል እንኳ፣ ብዙ ነገሮችን ማብራራት እንደማይችልና ይበልጥ ቢያውቅ ኖሮ በቀላሉ ሊያብራራቸው እንደሚችል ለማወቅ በቂ ትሕትናና ጥበብ ላለው ሰው ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር ቃል ግልጽ አባባል አንጻር ብዙም ክብደት አይኖረውም ነበር። እነዚህ ልዩነቶች ግን በቀላሉ ይብራራሉ።
መንፈስ ቅዱስ ለማንኛውም ግለሰብና በእርሱም በኩል እውነትን ሲገልጥ፣ በዚያ ሰው የቃላት ሀብትና የአስተሳሰብ መንገድ ውስጥ ያሉትን ቃላት፣ ሐረጎች፣ አገላለጾችንና ፈሊጦችን ለመጠቀም፣ የዚያንም ሰው ልዩ ባሕርይ ለመጠቀም የሚበቃ ጥበብና በቋንቋ አጠቃቀምም የሚበቃ ችሎታ አለው። በእርግጥም አንዱ እውነት እጅግ በተለያዩ አገላለጾች ፍጹም በሆነ ትክክለኛነት መገለጡ የዚህ መጽሐፍ መለኮታዊ ጥበብ ምልክት ነው።
7. የሐዋርያትና የነቢያት ንግግሮች የእግዚአብሔር ቃል ነበሩ። እነዚህን ቃላት ስናነብ የምንሰማው የሰውን ድምፅ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ድምፅ ነው። በማርቆስ 7:13 «ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ» እናነባለን። ኢየሱስ በሙሴ በኩል የተሰጠውን ሕግ ከሕግ አጥባቂዎች ወግ ጋር እያነጻጸረ ነበር፤ ይህንንም ሲያደርግ በዚህ ክፍል በሙሴ በኩል የተሰጠው ሕግ «የእግዚአብሔር ቃል» እንደ ሆነ ይናገራል። በ2ኛ ሳሙኤል 23:2 «የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፥ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነው» እናነባለን። እዚህም እንደ ገና የእግዚአብሔር ነቢይ ንግግር የእግዚአብሔር ቃል እንደ ነበረ ተነግሮናል። እንዲሁም እግዚአብሔር በ1ኛ ተሰሎንቄ 2:13 «ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን» ይላል። እዚህ ጳውሎስ በእግዚአብሔር መንፈስ ተምሮ የተናገረው ቃል የእግዚአብሔር ቃል ራሱ እንደ ነበረ ያውጃል።
ምዕራፍ 21 ተጠናቋል
መንፈስ ቅዱስ በነቢያትና በሐዋርያት ውስጥ የሚሠራው ሥራ