ምዕራፍ 22 · 4 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ የሠራው ሥራ
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በሰው ውስጥ የሚሠራው የመንፈስ ቅዱስ ሙሉ ሥራ በታሪክ ውስጥ የተገለጠበት ብቸኛው ፍጹም መገለጥ ነው።
1. ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስ ቅዱስ ተወለደ። በሉቃስ 1:35 እንዲህ እናነባለን፦ «መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።» ቀደም ብለን እንዳየነው አማኙ ዳግመኛ በመወለድ ከእግዚአብሔር ይወለዳል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በመጀመሪያ ልደቱ ከእግዚአብሔር ተወለደ። እርሱ አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ነው (ዮሐንስ 3:16)። የእግዚአብሔር ልጅ በማርያም ማኅፀን የተፀነሰው በማርያም ውስጥ በሠራው በመንፈስ ኃይል ብቻ ነበር። ዳግመኛ የተወለደ ሰው ከምድራዊ አባቱ የተቀበለው ሥጋዊ ባሕርይና በእግዚአብሔር የተሰጠው አዲስ ባሕርይ አለው። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አንድ ቅዱስ ባሕርይ ብቻ ነበረው፤ ይኸውም በሰው ውስጥ አዲስ ባሕርይ የሚባለው ነው። ቢሆንም ሰው የሆነች እናት ስለ ነበረችው እውነተኛ ሰው ነበር።
2. ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ቅዱስና ነውር የሌለበት ሕይወት ኖረ፤ ራሱንም ያለ ነውር ለእግዚአብሔር አቀረበ። በዕብራውያን 9:14 እንዲህ እናነባለን፦ «ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?» ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎች ሰዎች ሊገጥሙአቸውና ሊያሸንፉአቸው በሚችሉበት መንገድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ ፈተናዎችን ገጠመ፤ አሸነፋቸውም። ተፈትኖ በፈተና መከራን ተቀበለ (ዕብራውያን 3:18)፤ በነገር ሁሉ እንደ እኛ ተፈተነ (ዕብራውያን 4:15)፤ ነገር ግን አንድ ጊዜ እንኳ በምንም መንገድ ለፈተና እጅ አልሰጠም። የተፈተነው ከኃጢአት ፈጽሞ ተለይቶ ነበር፤ ነገር ግን ድሎቹን ያገኘው ለሁላችንም ክፍት በሆነው መንገድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር።
3. ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ለአገልግሎት ተዘጋጀ። በሐዋርያት ሥራ 10:38 እንዲህ እናነባለን፦ «እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና።» በብሉይ ኪዳን ስለሚመጣው መሲሕ በተሰጠው ትንቢታዊ ራእይ በኢሳይያስ 61:1 እንዲህ እናነባለን፦ «የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል» ሉቃስ ስለ ጌታችን ምድራዊ ሕይወት በጻፈው ዘገባ በሉቃስ 4:14 «ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ» እናነባለን።
እንዲሁም ኢየሱስ በናዝሬት ምኵራብ ሲናገር ስለ ራሱ እንዲህ አለ፦ «የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ፥ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል።» (ሉቃስ 4:18-19)። እነዚህ ክፍሎች ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ለጠራው አገልግሎት ብቁ የሆነው በመንፈስ ቅዱስ በተሰጠው ልዩ ቅባት እንደ ሆነ አንድ ትምህርት ይዘዋል። ከተጠመቀ በኋላ በዮርዳኖስ በቆመ ጊዜ «መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ»፤ በዚያን ጊዜና በዚያ ስፍራ በመንፈስ ቅዱስ ተቀባ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተጠመቀ፣ በፊቱ ላለውም አገልግሎት ታጠቀ። ኢየሱስ ክርስቶስ ለአገልግሎት የሚያስፈልገውን ኃይል የተቀበለው እኛ በምንቀበልበት በዚያው መንገድ፣ በተወሰነ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነበር።
4. ኢየሱስ ክርስቶስ እዚህ በምድር ሳለ በእንቅስቃሴዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ይመራ ነበር። በሉቃስ 4:1 እንዲህ እናነባለን፦ «ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ።» እዚህ በምድር ላይ እንደ ሰው ሲኖርና ለእኛ ምሳሌ ሲሆን፣ የሕይወቱ እያንዳንዱ እርምጃ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሥር ነበር።
5. ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ላይ ባረፈው መንፈስ ተማረ። በሥጋው ወራት የጥበቡ ምንጭ የእግዚአብሔር መንፈስ ነበር። በብሉይ ኪዳን ስለሚመጣው መሲሕ በተነገረው ትንቢት በኢሳይያስ 11:2-3 እንዲህ እናነባለን፦ «የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርንም በመፍራት ደስ ይለዋል፤ ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፥ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም።» ቀጥሎም በኢሳይያስ 42:1 «እነሆ፥ የምደግፈው ባሪያዬ፥ ነፍሴ ደስ የምትሰኝበት ምርጤ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አድርጌአለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል፤ ወዘተ.» እናነባለን። ይህ ትንቢት በናዝሬቱ ኢየሱስ እንደ ተፈጸመ ማቴዎስ በማቴዎስ 12:17-18 ይነግረናል።
6. መንፈስ ቅዱስ በሙላቱ ሁሉ በኢየሱስ ላይ ኖረ፤ በዚህም ምክንያት የተናገራቸው ቃላት የእግዚአብሔር ቃላት ራሳቸው ነበሩ። በዮሐንስ 3:34 እንዲህ እናነባለን፦ «እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና።»
7. ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ለመረጣቸው ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝን ሰጠ። በሐዋርያት ሥራ 1:2 እንዲህ እናነባለን፦ «በመንፈስ ቅዱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን ካዘዘ በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ።» ይህ ከትንሣኤው በኋላ ያለውን ጊዜ የሚመለከት ነው፤ ስለዚህም ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ እንኳ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሥራቱን እንደ ቀጠለ እናያለን።
8. ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ተአምራቱን ያደረገው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር። በማቴዎስ 12:28 «እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ…» እናነባለን። ጌታችን ከዚህ ምድር ከሄደ በኋላ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለአንዳንዶች ተአምራትን የማድረግ ኃይል የተሰጠው በመንፈስ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 12:9-10)፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ተአምራቱን ያደረገው በዚያው መንፈስ ኃይል ነበር።
9. ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን የተነሣው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር። በሮሜ 8:11 እንዲህ እናነባለን፦ «ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።» የሚሞተውን ሰውነታችንን ሕያው የሚያደርገውና አንድ ቀን የሚያስነሣን ያው መንፈስ ኢየሱስን አስነሣው። በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ስለ ሠራው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ካደረግነው ከዚህ ጥናት በርካታ ነገሮች ግልጽ ናቸው፤ በመጀመሪያ የሰውነቱን ፍጹምነት እናያለን። እኛም ልንቀበለው መብት ባለን በዚያው መንፈስ ኃይል ኖረ፣ አሰበ፣ ሠራ፣ አስተማረ፣ ኃጢአትን አሸነፈ፣ ለእግዚአብሔርም ድልን ተቀዳጀ።
በሁለተኛ ደረጃ፣ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ፈጽመን የተመካን መሆናችንን እናያለን። አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የኖረውና የሠራው፣ ያከናወነውና ድል የነሣው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከሆነ፣ እኛማ በሕይወት እያንዳንዱ መታጠፊያ፣ በአገልግሎት እያንዳንዱ ገጽታና ከሰይጣንና ከኃጢአት ጋር በምናደርገው በእያንዳንዱ ትግል ምን ያህል አብልጠን በእርሱ ላይ የተመካን እንሆናለን?
ግልጽ የሆነው ሦስተኛው ነገር ለእኛ የተከፈተልን አስደናቂው የመብት፣ የበረከትና የድል ዓለም ነው።
ኢየሱስ በመጀመሪያ የተወለደበት ያው መንፈስ እኛም ከእርሱ ዳግመኛ እንድንወለድ ለእኛ ተሰጥቶአል። ኢየሱስ ራሱን ያለ ነውር ለእግዚአብሔር ያቀረበበት ያው መንፈስ እኛም ራሳችንን ያለ ነውር ለእርሱ እንድናቀርብ ለእኛ ተሰጥቶአል። ኢየሱስ ለአገልግሎት የተቀባበት ያው መንፈስ እኛም ለአገልግሎት እንድንቀባ ለእኛ ተሰጥቶአል። ኢየሱስ ክርስቶስን በምድር ላይ በእንቅስቃሴዎቹ የመራው ያው መንፈስ ዛሬ እኛን ሊመራን ዝግጁ ነው። ኢየሱስን ያስተማረውና ጥበብንና ማስተዋልን፣ ምክርንና ኃይልን፣ እውቀትንና እግዚአብሔርን መፍራትን የሰጠው ያው መንፈስ እኛን ሊያስተምረን እዚህ አለ።
ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌያችን ነው (1ኛ ዮሐንስ 2:6)፤ እርሱ «በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር» ነው (ሮሜ 8:29)። እርሱ በመንፈስ ቅዱስ ያገኘው ሁሉ እኛም ዛሬ እንድናገኘው የተሰጠ ነው።
ተፈጸመ
ምዕራፍ 22 ተጠናቋል
መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ የሠራው ሥራ