ምዕራፍ 31 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ
ስለ ራሳችን
ጸጋና ማስተዋል ብዙ ጊዜ ስለሚጐድሉን በራሳችን ከመጠን በላይ ልንታመን አይገባንም። በተፈጥሮ ያለን ብርሃን ጥቂት ነው፤ እርሱንም በቸልተኝነት ቶሎ እናጣዋለን። በልባችን እንዲህ ዕውሮች መሆናችንን ብዙ ጊዜ አናስተውልም። ይህም ሳለ ክፉ እናደርጋለን፤ ከዚያም ስለ ክፋቱ ምክንያት በማቅረብ የባሰ እናደርጋለን። አንዳንድ ጊዜ በስሜት እንነዳለን፤ ቅንዓት እንደ ሆነም እናስባለን። ሌሎችን ስለ ትንሽ ስሕተት እንገሥጻለን፤ በራሳችን ያለውን የሚበልጠውን ግን ቸል እንላለን። ከሌሎች የምንቀበለውን መከራ ፈጥነን እንሰማዋለን፤ በልባችንም እናብሰለስለዋለን፤ ሌሎች ከእኛ የተነሣ ምን ያህል መከራ እንደሚቀበሉ ግን ምንም አናስብም። ሰው የራሱን ሥራ በሙላትና በትክክል ቢመዝን፣ በሌሎች ላይ ከባድ ፍርድ የሚፈርድበት ብዙ ምክንያት አያገኝም።
የውስጥ ሰው ስለ ራሱ መጠንቀቅን ከሌላው ጉዳይ ሁሉ ያስቀድማል፤ ራሱን በጥንቃቄ የሚጠብቅም ስለ ሌሎች አንደበቱን መግታት አይከብደውም። እንዲህ ስለ ሌሎች ጉዳይ ዝም ካላልህና ራስህን በተለየ ጥንቃቄ ካልተመለከትህ፣ ከቶ ልበ ትጉ ለእግዚአብሔርም ያደርህ አትሆንም። ፈጽመህ ለእግዚአብሔርና ለራስህ ብትጠነቀቅ፣ በዙሪያህ በምታየው ነገር ብዙም አትታወክም።
አሳብህ በራስህ ላይ ካልሆነ የት ነው ያለው? በልዩ ልዩ ነገሮች ከተጠመድህ በኋላስ ራስህን ቸል ካልህ ምን አተረፍህ? እውነተኛ የአእምሮ ሰላምና የዓላማ አንድነት እንዲኖርህ ብትወድ፣ ሌላውን ሁሉ ወደ ጐን ጥለህ ራስህን ብቻ በዓይንህ ፊት ልታኖር ይገባሃል።
ከጊዜያዊ ጭንቀት ሁሉ ራስህን ነጻ ብታደርግ ታላቅ እድገት ታደርጋለህ፤ ጊዜያዊ የሆነውን ማናቸውንም ነገር ከፍ አድርጎ መቍጠር ታላቅ ስሕተት ነውና። ከእግዚአብሔር ራሱ ወይም ከእግዚአብሔር ከሆነው በቀር፣ ምንም ነገር ታላቅ፣ ምንም ከፍ ያለ፣ ምንም ደስ የሚያሰኝ፣ ምንም ተወዳጅ አድርገህ አትቍጠር። የፍጥረታትን መጽናናት እንደ ከንቱ ቍጠረው፤ እግዚአብሔርን የምትወድ ነፍስ ከእርሱ በታች ያሉትን ነገሮች ሁሉ ትንቃለችና። ዘላለማዊና ወሰን የሌለው እግዚአብሔር ብቻ ሁሉን ያረካል፤ ለነፍስ መጽናናትን፣ ለሥጋም እውነተኛ ደስታን ያመጣል።
ምዕራፍ 31 ተጠናቋል
ስለ ራሳችን