ምዕራፍ 20 · 12 ደቂቃ ንባብ · 16 ደቂቃ ማዳመጥ
የእግዚአብሔር ሰረገሎች
«የእግዚአብሔር ሰረገሎች እልፍ አእላፋት፥ ሺህ ጊዜ ሺህ ናቸው፤ ጌታ በመካከላቸው ነው፤ ሲና በመቅደሱ ውስጥ ነው።» (መዝሙር 68:17)።
ሰረገሎች ለመጓጓዣና ወደ ፊት ለመገስገስ የሚያገለግሉ ናቸው። የምድር ሰረገሎች እንቅፋቶችን ሁሉ አልፈው ተሳፋሪዎቻቸውን ወደ መድረሻቸው ያደርሳሉ። የእግዚአብሔር ሰረገሎች ደግሞ ነፍሳትን ይሸከማሉ። በእግዚአብሔር ሰረገሎች የምትጓዝ ነፍስ የምትደርስባቸውን የክብር ስፍራዎች ምንም ቃል ሊገልጻቸው አይችልም። ጥቅሳችንም እነዚህ ሰረገሎች «እጅግ ብዙ» እንደ ሆኑ ይነግረናል። በዙሪያችን በየአቅጣጫው ይጠብቁናል፤ እኛ ግን፣ የሚያሳዝነው፣ ሁልጊዜ አናያቸውም። የምድር ሰረገሎች ሁልጊዜ ይታያሉ፤ የእግዚአብሔር ሰረገሎች ግን የማይታዩ ናቸው።
«ፈረሶችንና ሰረገሎችን ብዙ ሠራዊትም ወደዚያ ሰደደ፤ በሌሊትም መጥተው ከተማይቱን ከበቡ።
የእግዚአብሔርም ሰው ሎሌ ማልዶ ተነሥቶ በወጣ ጊዜ፥ እነሆ፥ ፈረሶችና ሰረገሎች ያሉት ሠራዊት ከተማይቱን ከብቦ ነበር። ሎሌውም፦ ‹ወዮ ጌታዬ! ምን እናደርጋለን?› አለው።
እርሱም፦ ‹ከእነርሱ ጋር ካሉት ይልቅ ከእኛ ጋር ያሉት ይበዛሉና አትፍራ› አለ። ኤልሳዕም፦ ‹አቤቱ፥ እንዲያይ ዓይኖቹን ክፈት› ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ከፈተ፤ እርሱም አየ፤ እነሆም፥ በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራው በእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተሞልቶ ነበር።» (2ኛ ነገሥት 6:14-17)። ለራሳችንና አንዳችን ለሌላው ልንጸልየው የሚያስፈልገን ጸሎት ይህ ነው፦ «ጌታ ሆይ፥ እንድናይ ዓይኖቻችንን ክፈት።» በዙሪያችን ያለው ዓለም ወደ ክብራማ የድል ስፍራዎች ሊወስዱን በሚጠባበቁ የእግዚአብሔር ፈረሶችና ሰረገሎች የተሞላ ነውና። ነገር ግን ሰረገሎች አይመስሉም። ይልቁንም ጠላቶች፣ መከራዎች፣ ፈተናዎች፣ ሽንፈቶች፣ አለመግባባቶች፣ ተስፋ መቍረጦችና ክፉ ድርጊቶች ይመስላሉ። ሊጨፈልቁን የሚጠባበቁ ግዙፍ የመከራ ጋሪዎች ይመስላሉ። ነገር ግን የድል ሰረገሎች ናቸው። ነፍሳችን ወደምትናፍቀው የድል ከፍታ ሊወስዱን ይችላሉ።
«በምድር ከፍታዎች ላይ» ልንጋልብ ብንወድ፣ ወደዚያ ሊያደርሱን ወደሚችሉት ሰረገሎች መግባት ይገባናል፤ እንዲህ ላለው ከፍ ያለ ግልቢያ የሚበቁት ደግሞ «የእግዚአብሔር ሰረገሎች» ብቻ ናቸው። (ዘዳግም 32:12-13) «እግዚአብሔር ብቻውን መራው፥ ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም። በምድር ከፍታ ላይ አስጋለበው፥ የእርሻውንም ፍሬ በላ፤ ከዓለትም ማርን፥ ከጭንጫ ድንጋይም ዘይትን አጠባው።»
«በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በምድርም ከፍታዎች ላይ አስጋልብሃለሁ፤ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ፤ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሮአልና።» (ኢሳይያስ 58:14)።
በሕይወታችን ከሚደርስብን እያንዳንዱ ነገር የሚጨፈልቀንን የጃገርኖት ሰረገላ ወይም ወደ ድል ከፍታ የምንወጣበትን ሰረገላ ልናደርገው እንችላለን። ሁሉም የተመካው ነገሮቹን እንዴት እንደምንቀበላቸው ላይ ነው፤ ከፈተናዎቻችን በታች ተጋድመን በላያችን እንዲያልፉና እንዲጨፈልቁን እንፈቅድላቸዋለን? ወይስ ወደ ሰረገላ እንደምንወጣ ወደ እነርሱ ወጥተን በድል ወደ ፊትና ወደ ላይ እንዲሸከሙን እናደርጋቸዋለን?
«ሲሄዱም እየተነጋገሩም ሳሉ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በሁለቱ መካከል ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ። ኤልሳዕም አይቶ፦ ‹አባቴ፥ አባቴ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞቹ!› ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ለሁለት ቀደደው።» (2ኛ ነገሥት 2:11-12)። ወደ እግዚአብሔር ሰረገሎች በወጣን ቁጥር በኤልያስ ላይ የሆነው ነገር በእኛም ላይ በመንፈስ ይሆናል። እኛም እንነጠቃለን። እንደ ኤልያስ በላያችን ወዳሉት ሰማያት ሳይሆን በውስጣችን ወዳለው ሰማይ እንነጠቃለን፤ ይህም ሲታሰብ ከእርሱ መነጠቅ የሚበልጥ ታላቅ መነጠቅ ነው ማለት ይቻላል። ሁሉ ነገር ከሚያቆስልበትና ሁሉ ነገር ደስታ ከሚነሣበት ከዝቅተኛው ምድራዊ የሕይወት ደረጃ ተነሥተን «በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ» እንወሰዳለን፤ በዚያም ከበታች ባለው ሁሉ ላይ በድል እንጋልባለን።
«ከእርሱ ጋር አስነሣን፥ በክርስቶስ ኢየሱስም ከእርሱ ጋር በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን» (ኤፌሶን 2:6)። እነዚህ «ሰማያዊ ስፍራዎች» ውስጣዊ እንጂ ውጫዊ አይደሉም፤ ወደ እነርሱ የሚያደርሰውም መንገድ ውስጣዊ ነው።
ነገር ግን ነፍስን በዚህ መንገድ ላይ የሚሸከማት ሰረገላ አብዛኛውን ጊዜ አንድ ውጫዊ ጕዳት፣ ወይም ፈተና፣ ወይም ተስፋ መቍረጥ ነው፤ ለጊዜው ደስ የሚያሰኝ ሳይሆን የሚያሳዝን የሚመስል ቅጣት ነው፤ ዳሩ ግን በኋላ «ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን» የሚያፈራ ነው።
«ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በአንተም ሲገሥጽህ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፋልና ብሎ እንደ ልጆች የሚነግራችሁን ምክር ረስታችኋል። ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን? እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።» (ዕብራውያን 12:5-11)።
እነዚህን ተግሣጾች፣ ለጊዜው ምንም ያህል የሚያሳዝኑ ቢሆኑ፣ ነፍሳችሁን ወደ መንፈሳዊ ስኬትና ከፍ ከፍ ወደ ማለት «ከፍታዎች» ሊወስዱ የተላኩ የእግዚአብሔር ሰረገሎች አድርጋችሁ ተመልከቷቸው፤ ከሁሉ በኋላም «በፍቅር የተለበጡ» መሆናቸውን ታገኛላችሁ።
«ንጉሡ ሰሎሞን ከሊባኖስ እንጨት ለራሱ ሰረገላ ሠራ። ምሰሶዎቹን ከብር፥ መደገፊያውን ከወርቅ፥ መቀመጫውን ከሐምራዊ ግምጃ አደረገ፤ ውስጡም በኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ፍቅር የተለበጠ ነበረ።» (መኃልየ መኃልይ 3:9-10)። የአንተ የግል ሰረገላ እጅግ የማያምር ሊመስል ይችላል። ጠባዩ የሚቈረቍር ዘመድ ወይም ወዳጅ ሊሆን ይችላል፤ የሰው ክፋት፣ ወይም ጭካኔ፣ ወይም ቸልተኝነት ውጤት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚልከው ሰረገላ ሁሉ የግድ በፍቅር የተለበጠ ነው፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና፤ የእግዚአብሔርም ፍቅር ማንኛዪቱም ነፍስ በየትም ስፍራ ልታርፍበት ካገኘችው ነገር ሁሉ እጅግ ጣፋጭ፣ እጅግ ለስላሳና እጅግ ርኅሩኅ ነው። ሰረገላውን የሚልከው በእርግጥ ፍቅሩ ነው።
«አቤቱ፥ በወንዞች ላይ ተቈጥተሃልን? ቍጣህ በወንዞች ላይ ነበረን? ወይስ በፈረሶችህና በማዳንህ ሰረገላ ላይ በተቀመጥህ ጊዜ መዓትህ በባሕር ላይ ነበረን? ቀስትህን ፈጽሞ ገለጥህ፤ ብዙ ፍላጾችን ጠራህ። ሴላ። ምድርን በወንዞች ሰነጠቅህ። ተራሮች አዩህ ተጨነቁም፤ የውኃ ጐርፍ አለፈ፤ ቀላዩ ድምፁን ሰጠ፥ እጁንም ወደ ላይ አነሣ። በሚወረወሩት ፍላጾችህ ብርሃን፥ በሚያብረቀርቀውም ጦርህ ብልጭታ ፀሐይና ጨረቃ በስፍራቸው ቆሙ። በመዓት በምድር ላይ ተራመድህ፥ በቍጣም አሕዛብን አኬድሃቸው። ሕዝብህን ለማዳን፥ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ።» (ዕንባቆም 3:8-13)። በዚህ ስፍራ ነቢዩ የሚነግረን፣ እግዚአብሔር በ«ማዳኑ ሰረገሎች» እየጋለበ ሕዝቡን ለመታደግ እንዲመጣ ያደረገው በሕዝቡ መንገድ ላይ በተደቀኑት እንቅፋቶች ላይ የነበረው ቍጣው እንደ ሆነ ነው። እግዚአብሔር በላዩ ሲቀመጥበት ሁሉ ነገር «የማዳን ሰረገላ» ይሆናል። ሰማያችንን የሚያጨልሙና የጽድቅን ፀሐይ ብርሃን የሚጋርዱ የሚመስሉት «ደመናት» እንኳ፣ ብናውቀው፣ የእርሱ ሰረገሎች ናቸው፤ ከእርሱም ጋር ወደ እነርሱ ልንወጣና በጨለማው ሁሉ ላይ «እየተከናወነልን ልንጋልብ» እንችላለን።
«አንተ ኃያል፥ በክብርህና በግርማህ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ! በግርማህም ስለ እውነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም በድል ተቀምጠህ ውጣ፤ ቀኝህም ድንቅ ነገርን ታስተምርሃለች!» (መዝሙር 45:3-4)። «በኪሩብ ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስ ክንፍ ላይ ፈጥኖ መጣ።» (መዝሙር 18:10)። «ይሹሩን ሆይ፥ ሊረዳህ በሰማያት ላይ፥ በግርማውም በደመናት ላይ እንደሚጋልበው እንደ እግዚአብሔር ያለ የለም።» (ዘዳግም 33:26)። በቅርቡ ያረፈ አንድ ጸሐፊ እንደ ተናገረው፣ እጅግ በበረታና በሚያደክም ጥረት እንኳ ደመናትን ጠራርገን ልናስወግድ አንችልም፤ ነገር ግን ከበላይ ወዳለው ጥሩ አየር እስክንደርስ ድረስ ከእነርሱ በላይ ከፍ ብለን ልንወጣ እንችላለን፤ ከእግዚአብሔርም ጋር የሚጋልብ ሰው ከምድር ከተወለዱ ደመናት ሁሉ እጅግ ከፍ ብሎ በሰማያት ላይ ይጋልባል።
«የምድር መንግሥታት ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ለጌታ ዘምሩ። ሴላ። ከጥንት ጀምሮ ባሉት በሰማያት ሰማያት ላይ ለሚጋልበው ዘምሩ፤ እነሆ፥ ድምፁን፥ የኃይሉን ድምፅ ያሰማል። ለእግዚአብሔር ኃይልን ስጡ፤ ግርማው በእስራኤል ላይ፥ ኃይሉም በደመናት ውስጥ ነው።» (መዝሙር 68:32-34)። ይህ ምናባዊ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ልንተገብረው ስንጀምር እጅግ ተግባራዊ ነው።
እጅግ ዝግተኛ የሆነች አንዲት ሠራተኛ የነበረቻትን አንዲት እመቤት አውቃለሁ። ሠራተኛዪቱ በሁሉ ነገር እጅግ መልካምና ጠቃሚ ነበረች። ነገር ግን ዝግተኛነቷ በተፈጥሮዋ ፈጣን የሆነችውን እመቤቷን ያበሳጫት ነበር።
እመቤቲቱ በቀን ሀያ ጊዜ በልጅቱ ላይ ትቈጣ ነበር። ሀያ ጊዜም ትጸጸትና ቍጣዋን ለመግታት ትሞክር ነበር። ግን በከንቱ ነበር። በዚህ ትግል ምክንያት ሕይወቷ መራራ ሆነባት። አንድ ቀን ለረጅም ጊዜ ትዕግሥትን ለማግኘት ስትጸልይ እንደ ነበረች ትዝ አላት። ምናልባት ይህች ዝግተኛ ሠራተኛ ነፍሷን ወደ ትዕግሥት ለመውሰድ ጌታ የላከው ሰረገላ ትሆን ይሆናል ብላ አሰበች። ወዲያውኑ እንደዚያው አድርጋ ተቀበለቻት፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም የሠራተኛዋን ዝግተኛነት ለነፍሷ ሰረገላ አድርጋ ተጠቀመችበት። ውጤቱም የማንም ዝግተኛነት ፈጽሞ ሊያናውጠው ያልቻለ የትዕግሥት ድል ሆነ።
በአንድ ጉባኤያችን ላይ፣ ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ከሌሎች ሁለት ሴቶች ጋር በአንድ ክፍል ለማደር የተገደደች አንዲት እኅት አውቃለሁ። እርሷ መተኛት ፈለገች፤ እነርሱ ግን ማውራት ፈለጉ። በመጀመሪያው ሌሊት ተረበሸች። ሌሎቹ ጸጥ ካሉ በኋላም ለረጅም ጊዜ ተበሳጭታና ተቈጥታ ተጋድማ ቈየች። ባትበሳጭ ኖሮ መተኛት በቻለች ነበር። በማግሥቱ ግን ስለ እግዚአብሔር ሰረገሎች ሰማች። በዚያች ሌሊት የሚያወሩትን እኅቶች እንደ ሰረገሎቿ ልትቈጥራቸው ወሰነች።
ጣፋጭ ጠባይንና ትዕግሥትን እንድትማር ይረዱአታል። ሰላምና ጸጥታ ተሰምቷት ተጋደመች። ነገር ግን ሌሊቱ እጅግ ገፋ፤ ሁሉም ተኝተው መሆን ይገባቸው ነበር። ስለዚህ በለሆሳስ «እኅቶቼ፣ እኔ እዚህ ተጋድሜ በሰረገላ እየጋለብሁ ነው» አለች። ይህም ፍጹም ጸጥታ አመጣ። ሰረገላዋ በውስጥም በውጭም ወደ ድል አደረሳት።
የራሳችንን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ሰረገሎች ለመሳፈር ብንመርጥ፣ እኛም ያንኑ እናገኛለን።
«ለርዳታ ወደ ግብፅ ለሚወርዱ፥ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ሰረገሎች ብዙ ስለ ሆኑ፥ ፈረሰኞችም እጅግ ብርቱዎች ስለ ሆኑ በእነርሱ ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤል ቅዱስ ግን ለማይመለከቱ፥ እግዚአብሔርንም ለማይሹ ወዮላቸው! እርሱ ደግሞ ጠቢብ ነው፥ ክፉንም ያመጣል፤ ቃሉንም አይመልስም፤ ነገር ግን በክፉ አድራጊዎች ቤትና ዓመፃን በሚሠሩ ሰዎች ረዳቶች ላይ ይነሣል። ግብፃውያን ሰዎች ናቸው እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ ናቸው እንጂ መንፈስ አይደሉም። እግዚአብሔር እጁን በዘረጋ ጊዜ ረዳቱ ይሰናከላል፥ የተረዳውም ይወድቃል፥ ሁሉም በአንድነት ይጠፋሉ።» (ኢሳይያስ 31:1-3)። «እነዚያ በሰረገሎች፥ እነዚያም በፈረሶች ይታመናሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም እንታመናለን። እነርሱ ተሰነካከሉ ወደቁም፤ እኛ ግን ተነሣን ቀጥ ብለንም ቆምን።» (መዝሙር 20:7-8)። ዘወትር የሚገጥመን ፈተና በ«ግብፅ ሰረገሎች» መታመን ነው። እናያቸዋለን። እውነተኛና ጠንካራ ይመስላሉ። የእግዚአብሔር ሰረገሎች ግን የማይታዩና የማይዳሰሱ ናቸው። በዚያ መኖራቸውን ማመን ያስቸግራል። ዓይኖቻችን እነርሱን ለማየት አልተከፈቱም።
«በመልእክተኞችህ ጌታን ሰድበሃል፤ እንዲህም ብለሃል፦ ‹በሰረገሎቼ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሊባኖስ ጥግ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹን ዝግባዎች፥ የተመረጡትንም ጥዶች ቈርጫለሁ፤ እስከ ዳርቻው ማደሪያ፥ እስከ ፍሬያማውም ዱር ገብቻለሁ።›» እኛም ከፍታዎቹን «በሰረገሎቻችን ብዛት» ልንደርስ እንሞክራለን። መጀመሪያ በአንድ ነገር፣ ከዚያም በሌላ እንደገፋለን። ይህንም የምናደርገው መንፈሳችንን ለማሻሻልና መንፈሳዊ ድሎችን ለማግኘት ነው። «ለርዳታ ወደ ግብፅ እንወርዳለን።» (2ኛ ነገሥት 19:23)።
እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ሰረገላ እንድንወጣ ከማድረሱ በፊት ብዙ ጊዜ የራሳችንን ሰረገሎች ሁሉ ለማጥፋት ይገደዳል።
«በዚያም ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ፈረሶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ሰረገሎችህንም አፈርሳለሁ፤» (ሚክያስ 5:10)። «የመንግሥታትንም ዙፋን እገለብጣለሁ፤ የአሕዛብንም መንግሥታት ኃይል አጠፋለሁ፤ ሰረገሎችንና በእነርሱ ላይ የሚቀመጡትን እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ፈረሰኞቻቸውም እያንዳንዱ በወንድሙ ሰይፍ ይወድቃሉ።» (ሐጌ 2:22)። መንፈሳዊ ዕድገታችንን እንዲረዳን በአንድ ውድ ወዳጃችን ላይ እጅግ እንደገፋለን። ስለዚህ ጌታ ከዚያ ወዳጅ ሊለየን ይገባዋል። መንፈሳዊ ዕድገታችን በምንወደው አንድ ሰባኪ አገልግሎት ላይ የተመካ እንደ ሆነ እናምናለን። አሁን ደግሞ በማይገባን ሁኔታ ከእርሱ እንለያለን። የጸሎት ስብሰባችንን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍላችንን የመንፈሳዊ ብርታታችን ዋና ምንጭ አድርገን እንመለከታለን። አሁን ደግሞ ልንገኝበት አንችልም። ስንደገፍባቸው በነበሩት መሣሪያዎች እንወሰድባቸዋለን ብለን ተስፋ ወደ አደረግናቸው ስፍራዎች ብቻውን ሊያደርሰን የሚችለው «የእግዚአብሔር ሰረገላ» እጅግ ባዘንባቸው በእነዚያው ማጣቶች ውስጥ ይገኛል። እግዚአብሔር ወደ እርሱ ሰረገላ እንዳንወጣ መንገድ የሚዘጋውን የራሳችንን ሰረገላ ሁሉ በፍቅሩ እሳት ሊያቃጥለው ይገባዋል።
«እነሆ፥ እግዚአብሔር ቍጣውን በመዓት፥ ተግሣጹንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ በእሳት ይመጣል፤ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው።» (ኢሳይያስ 66:15)። እንግዲያስ ሰረገሎቻችንን ለማጥፋት ለሚረዳን፣ ተዘጋጅቶ በአጠገባችን ወደሚጠብቀን ወደ እግዚአብሔር ሰረገላ እንድንጠጋ ለሚያስገድደን ፈተና ሁሉ እናመስግን።
«ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ፤ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ነውና። እርሱ ብቻ ዓለቴና መድኃኒቴ ነው፥ መጠጊያዬም ነው፤ አልታወክም። መድኃኒቴና ክብሬ በእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ የኃይሌ ዓለት፥ መታመኛዬም እግዚአብሔር ነው። ሕዝብ ሁሉ ሆይ፥ ሁልጊዜ በእርሱ ታመኑ፤ ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር መጠጊያችን ነውና። ሴላ።» (መዝሙር 62:5-8)። «እርሱ ብቻ» ለማለት ከመቻላችን በፊት ሌሎች መጠጊያዎች ሁሉ ወደሚከዱን ስፍራ መምጣት ይገባናል። እኛ «እርሱ እና ሌላ ነገር» እንላለን።
«እርሱ እና የእኔ ተሞክሮ»፣ ወይም «እርሱ እና በቤተ ክርስቲያን ያለኝ ግንኙነት»፣ ወይም «እርሱ እና የክርስቲያን አገልግሎቴ» እንላለን፤ ወደ «እርሱ ብቻ» ከመድረሳችን በፊት ከ«እና» በኋላ የሚመጣው ሁሉ ሊወሰድብን ወይም ከንቱ መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባዋል። የሚታዩ ሰረገሎች በእጅ እስካሉ ድረስ ነፍስ ወደማይታዩት አትወጣም።
«ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ ለስሙም ዘምሩ፤ በምድረ በዳ ለሚጋልበው ዝማሬን አንሡ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው፤ በፊቱም ደስ ይበላችሁ!» (መዝሙር 68:4)። ከእግዚአብሔር ጋር «በሰማያት ላይ» ልንጋልብ ብንወድ፣ በምድር ላይ የምናደርገው ግልቢያ ሁሉ ወደ ፍጻሜ መምጣት ይገባዋል።
«አቤቱ፥ አካሄድህን አዩ፤ የአምላኬንና የንጉሤን አካሄድ በመቅደስ ውስጥ አዩ።» (መዝሙር
68:24)። የእግዚአብሔርን አካሄድ ለማየት ወደ ሀልዎቱ መቅደስ መግባት ይገባናል፤ በአካሄዱም ተካፋዮች ሆነን ከእርሱ ጋር ለመሄድ ምድራዊ አካሄዶችን ሁሉ መተው ይገባናል።
«የሰው አካሄድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ ሰውስ መንገዱን እንዴት ያስተውላል?» (ምሳሌ 20:24)። «አረማመዴ በመንገድህ ጸና፤ እግሮቼም አልተንሸራተቱም።» (መዝሙር 17:5)።
«እግዚአብሔርን ታግሼ ጠበቅሁት፤ ወደ እኔም ዘንበል አለ፥ ጩኸቴንም ሰማ።» (መዝሙር 40:1)። ወደ እግዚአብሔር ሰረገላ ስንወጣ አካሄዳችን «ይጸናል»፤ የድል ጕዞውን ምንም እንቅፋት ሊገታው አይችልምና። ስለዚህ ወደዚህ የሚያደርሱን ጕዳቶች ሁሉ ትርፍ ናቸው።
«ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጠው ስለ ጌታዬ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ እውቀት ሁሉን እንደ ጉዳት እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጎዳሁ፤ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ በእርሱም እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ ይህም ከሕግ የሆነ የራሴ ጽድቅ ሳይኖረኝ፥ በክርስቶስ በማመን የሆነው ጽድቅ፥ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር የሆነው ጽድቅ እንዲሆንልኝ ነው።» (ፊልጵስዩስ 3:7-9)። ጳውሎስ ይህን አስተውሎ ነበር፤ እንዲህ ያለ ሊነገር የማይችል ትርፍ ባመጡለት ጕዳቶችም ተመካ።
«ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። እርሱም። ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።» (2ኛ ቆሮንቶስ 12:7-10)። ሊያስጨንቀው የተላከው የሰይጣን መልእክተኛ፣ ያ «የሥጋ መውጊያ» እንኳ፣ ለፈቃደኛ ልቡ በሌላ መንገድ ሊደርስባቸው ወደማይችል ድሎች የሚወስደው ሰረገላ ብቻ ሆነለት። በትግሎቹ «ደስ ይለኛል» ማለት — ይህ እነርሱን ከሰረገሎች ሁሉ ወደሚበልጥ ሰረገላ መለወጥ ካልሆነ ምንድር ነው?
ዮሴፍ ስለሚመጣው ድሉና ስለ ንግሥናው ሕልም አለመ። ለሥጋ ዓይን ግን ወደዚያ የወሰዱት ሰረገሎች መራራ ውድቀቶች ይመስሉ ነበር። ወደ መንግሥት የሚወስድ እንግዳ መንገድ ነበር፤ በባርነትና በወኅኒ በኩል ያልፍ ነበር። ሆኖም ዮሴፍ ወደ ድሉ የሚደርስበት ሌላ መንገድ አልነበረም። ሕልሙ፣ ዘፍጥረት 37:5-10፦ «ዮሴፍም ሕልም አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እነርሱም ደግሞ አብዝተው ጠሉት። እንዲህም አላቸው፦ ‹ያለምሁትን ይህን ሕልም ስሙ፤ እነሆ፥ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበር፤ እነሆም፥ የእኔ ነዶ ተነሥታ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶዎች በዙሪያዋ ከብበው ለእኔ ነዶ ሰገዱ።› ወንድሞቹም፦ ‹በእውነት በእኛ ላይ ልትነግሥ ነውን? ወይስ በእውነት ልትገዛን ነውን?› አሉት። ስለ ሕልሙና ስለ ቃሉም አብዝተው ጠሉት። ደግሞ ሌላ ሕልም አለመ፥ ለወንድሞቹም እንዲህ ብሎ ነገራቸው፦ ‹እነሆ፥ ደግሞ ሌላ ሕልም አለምሁ፤ እነሆ፥ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ።› ለአባቱና ለወንድሞቹም በነገራቸው ጊዜ አባቱ ገሠጸውና፦ ‹ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በእውነት እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልሃለንን?› አለው።»
ሰረገሎቹ፣ ዘፍጥረት 37:19-20፦ «እርስ በርሳቸውም፦ ‹እነሆ፥ ያ ባለ ሕልም መጣ፤ አሁንም ኑ፥ እንግደለው፥ ከጕድጓዶቹም በአንዱ እንጣለው፤ ክፉ አውሬ በላው እንላለን፤ ሕልሞቹም ምን እንደሚሆኑ እናያለን› ተባባሉ።» ዘፍጥረት 27:28፦ «እግዚአብሔር ከሰማይ ጠል፥ ከምድርም ስብ፥ የእህልንና የወይንን ብዛት ይስጥህ።» ዘፍጥረት 39:19-20፦ «ጌታውም ሚስቱ፦ ‹ባሪያህ እንዲህ አደረገብኝ› ብላ የነገረችውን ቃል በሰማ ጊዜ ቍጣው ነደደ። የዮሴፍም ጌታ ወሰደው፤ የንጉሡ እስረኞች ወደሚታሰሩበት ወደ ወኅኒ ቤት አገባው፤ በዚያም በወኅኒ ቤት ነበረ።» በሰረገሎቹ እንዴት እንደ ተጓዘ፣ ዘፍጥረት 39:1-6፦ «ዮሴፍም ወደ ግብፅ ወረደ፤ የፈርዖንም ሹም የዘበኞቹ አለቃ ግብፃዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ካወረዱት ከእስማኤላውያን እጅ ገዛው። እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ፤ የተከናወነለትም ሰው ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታው ቤትም ነበረ። ጌታውም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ ሆነ፥ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዳከናወነለት አየ። ዮሴፍም በፊቱ ሞገስ አገኘ፥ አገለገለውም፤ በቤቱም ላይ ሾመው፥ ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው። በቤቱና ባለው ሁሉ ላይ ከሾመው ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር ስለ ዮሴፍ የግብፃዊውን ቤት ባረከ፤ የእግዚአብሔርም በረከት በቤትና በእርሻ ባለው ሁሉ ላይ ነበረ። ያለውንም ሁሉ በዮሴፍ እጅ ተወው፤ ከሚበላውም እንጀራ በቀር ስለ ምንም አያስብም ነበር።»
ዘፍጥረት 39:21-23፦ «እግዚአብሔር ግን ከዮሴፍ ጋር ነበረ፤ ምሕረቱንም አበዛለት፤ በወኅኒ ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሰጠው። የወኅኒ ቤቱም አለቃ በወኅኒ ቤት ያሉትን እስረኞች ሁሉ በዮሴፍ እጅ ሰጠ፤ በዚያም የሚደረገውን ሁሉ የሚያደርገው እርሱ ነበረ። የወኅኒ ቤቱ አለቃ በዮሴፍ እጅ ያለውን ምንም አይመለከትም ነበር፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና።
የሚያደርገውንም ሁሉ እግዚአብሔር ያከናውንለት ነበር።» ድሉ።
እንግዲህ ወደ እነዚህ ሰረገሎች እንዴት መውጣት እንደሚቻል አንድ ቃል ልናገር። መልሴ በቀላሉ ይህ ነው፦ በእያንዳንዳቸው ውስጥ እግዚአብሔር የት እንዳለ ፈልገህ አግኝ፤ በእርሱም ውስጥ ተሸሸግ። በሌላ አነጋገር፣ መከራ ሲመጣበት እናቱን ፈልጎ አግኝቶ በእቅፏ እንደሚሸሸግ ትንሽ ልጅ አድርግ። ከሁሉ በኋላ በድል የሚያሻግረን እውነተኛው ሰረገላ እግዚአብሔር ራሱ የሚሸከመን መሸከም ነው።
ኢሳይያስ 46:4፦ «እስከ ሽምግልናችሁ ድረስ እኔ ነኝ፥ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ፥ እኔም እሸከማለሁ፤ እኔ እሸከማለሁ፥ አድናችሁማለሁ።» በእናቱ እቅፍ ሰረገላ ውስጥ የተሸከመ ሕፃን እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ስፍራዎች በድል ያልፋል፤ አስቸጋሪ መሆናቸውንም እንኳ አያውቅም።
ኢሳይያስ 63:9፦ «በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፤ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄው ተቤዣቸው፤ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አነሣቸው፥ ተሸከማቸውም።» «በእግዚአብሔር ክንዶች» ሰረገላ የምንሸከም እኛማ እንዴት ይልቅ! እንግዲያስ ወደ ሰረገላህ ግባ። በሕይወትህ ያለውን የተበላሸ ነገር ሁሉ ለአንተ የተሰጠ የእግዚአብሔር ሰረገላ አድርገህ ተቀበል። ስሕተቱን የሠራው ማንም ይሁን፣ አሁን ለአንተ የእግዚአብሔር ሰረገላ ነው። ወደ ሰማያዊ የድል ስፍራ ሊያደርስህ ይገባዋል። ሁለተኛ ምክንያቶችን ሁሉ ከአእምሮህ አውጣ፤ በዚያ ነገር ውስጥም ጌታን ፈልገህ አግኝ። «ጌታ ሆይ፥ የሚታየውን ጠላት ሳይሆን የማይታዩትን የመዳን ሰረገሎችህን እንዳይ ዓይኖቼን ክፈት» በል።
በመከራው ውስጥ፣ ምንም ዓይነት ቢሆን፣ ፈቃዱን ተቀበል፤ በፍቅሩም እቅፍ ውስጥ ተሸሸግ። «ፈቃድህ ትሁን፤ ፈቃድህ ትሁን!» እያልህ ደጋግመህ ተናገር።
ለፈቃዱ ከመገዛትና በፍቅሩ ከመታመን ከዚህ አንድ ሐሳብ በቀር ሌላውን ሐሳብ ሁሉ ከልብህ አውጣ።
መከራህን ሰረገላህ አድርገው። ያን ጊዜ ነፍስህ ፈጽሞ ሊሆን ይችላል ብለህ ባላሰብኸው መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር «በሰማያት ላይ ትጋልባለች»።
ምንም አልጠራጠርም፤ ዓይኖቻችን ቢከፈቱ ቤቶቻችንን፣ የሥራ ቦታዎቻችንንና መንገዶቻችንን «በእግዚአብሔር ሰረገሎች» ተሞልተው እናያቸው ነበር። ከእኛ ማንም ሰረገላ በማጣት በእግሩ የሚሄድበት ምክንያት የለም።
ሕይወትህን ሸክም ያደረገብህ ያ በቤትህ የሚኖር ቍጡ ሰው ከአሁን ጀምሮ ክብራማ ሰረገላ ሊሆንልህ ይችላል።
ወደ ሰማያዊ ትዕግሥትና ቻይነት ከፍታ ያደርስሃል። አለመግባባቶችህ፣ ውርደትህ፣ የደረሰብህ ክፉ ድርጊት፣ ተስፋ መቍረጥህ፣ ጕዳትህና ሽንፈትህ ሁሉ ሰረገሎች ናቸው። ወደ ናፈቅኸው የድል ከፍታ ሊወስዱህ ይጠብቃሉ።
እንግዲያስ በምስጋና ልብ ወደ እነርሱ ውጣ። በፍቅሩ ብርሃን ውስጥ ሁለተኛ ምክንያቶችን ሁሉ ከዓይንህ አጥፋ።
በክንዶቹ ይሸከምሃል፤ ደኅንነትህን ይጠብቃል፤ በሁሉም ላይ ድልን ያቀዳጅሃል።
ምዕራፍ 20 ተጠናቋል
የእግዚአብሔር ሰረገሎች