የተቀጠቀጠ ሸምበቆ
ክርስቶስ የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም

ምዕራፍ 3 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ

ክርስቶስ የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም

ሁለተኛው ነጥብ፦ ክርስቶስ የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም የሚለው ነው። ሐኪሞች በሽተኞቻቸውን ብዙ ሕመም ቢያሳድሩባቸውም ተፈጥሮአቸውን አያጠፉም፤ ይልቁንም ቀስ በቀስ ያበረቱታል። የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ይበጣሉ ይቈርጣሉም፤ የአካል ክፍልን ግን አይቈርጡም። የታመመና ነጭናጫ ልጅ ያላት እናት ስለዚያ አትጥለውም፤ ታዲያ ከምንጩ ይልቅ በወራጁ ውኃ የበለጠ ምሕረት ይኖራልን? የምሕረትን ስሜት በውስጣችን ከሚተክለው ከእግዚአብሔር ይልቅ በራሳችን የበለጠ ምሕረት አለ ብለን እናስባለንን? ነገር ግን ክርስቶስ ለተቀጠቀጡ ሸምበቆዎች ሁሉ ያለውን ምሕረት ይበልጥ ለመግለጥ፣ በራሱ ላይ የወሰዳቸውን የሚያጽናኑ ግንኙነቶች ተመልከት፤ ባል፣ እረኛ፣ ወንድምና የመሳሰሉት ናቸው፤ እነዚህንም እስከ መጨረሻው ይፈጽማቸዋል፤ ሌሎች እርሱ የጠራቸውን በጸጋው ይፈጽሙ ዘንድ፣ እርሱ ግን ከፍቅሩ የተነሣ በራሱ ላይ የወሰዳቸውን፣ በአባቱ ምደባና በራሱ በፈቃድ መቀበል እንዲህ ጽኑ በሆነ መሠረት ላይ የቆሙትን እነዚህን ግንኙነቶች አይፈጽምምን? ርኅሩኅ እንክብካቤውን ለማሳየት ከየዋሆቹ ፍጥረታት የተዋሳቸውን ስሞች ተመልከት፤ በግ፣ ዶሮና የመሳሰሉት ናቸው። እግዚአብሔር ራሱ የሰጠውን ስሙን ተመልከት፤ ኢየሱስ ማለትም አዳኝ ነው። ለስሙ የሚስማማውን አገልግሎቱን ተመልከት፤ ይኸውም ልባቸው የተሰበረውን ይፈውስ ዘንድ ነው (ኢሳይያስ 61:1)። በጥምቀቱ ጊዜ እንደ ርግብ የዋህ መካከለኛ እንደሚሆን ለማሳየት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በእርሱ ላይ ወረደ። አገልግሎቶቹን የፈጸመበትን የጸጋ አኳኋን ተመልከት፤ እንደ ነቢይ በአፉ በረከት ይዞ መጣ፦ «በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው…» (ማቴዎስ 5)፤ በራሳቸው ላይ ብዙ ተቃውሞ የሚያነሣባቸው ልብ ያላቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጋበዛቸው፦ «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።» (ማቴዎስ 11:28)። ሕዝቡን «እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች» ሆነው ባየ ጊዜ አንጀቱ እንዴት ተላወሰ! (ማቴዎስ 9:36)። ወደ እርሱ የመጣውን ማንንም ከቶ ወደ ኋላ አልመለሰም፤ አንዳንዶች ግን በራሳቸው ሄዱ። ስለ ጠላቶቹ እንደ ካህን ሊሞት መጣ፤ በሥጋው ወራት ለደቀ መዛሙርቱ የጸሎትን ሥርዓት ሰጣቸው፤ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡትን ልመና በአፋቸው አኖረ፤ በልባቸውም ይማልድ ዘንድ መንፈሱን አኖረ፤ አሁንም በእግዚአብሔር ቍጣና በእነርሱ መካከል ቆሞ ስለ ደካሞች ክርስቲያኖች በሰማይ ይማልዳል፤ ደሙን ላፈሰሱትም እንባውን አፈሰሰ። እንዲሁም የዋህ ንጉሥ ነው፤ የሚያለቅሱትን ወደ ፊቱ ያስገባል፤ የድሆችና የተጨነቁ ሰዎች ንጉሥ ነው፤ የግርማ ጨረሮች እንዳሉት ሁሉ የምሕረትና የርኅራኄ አንጀትም አለው፤ የሰላም አለቃ ነው (ኢሳይያስ 9:6)። የተፈተነው «የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላል» ዘንድ ካልሆነ ስለ ምን ነው? (ዕብራውያን 2:18)። ቸር ይሆን ዘንድ ባሕርያችንን በራሱ ላይ ከወሰደው ከእንዲህ ያለ ቸር መካከለኛ ምን ዓይነት ምሕረትን አንጠብቅም? (1ኛ ጢሞቴዎስ 2:5)። በሽታን ሁሉ የሚፈውስ ጥሩ ሐኪም ነው፤ በተለይም የተሰበረን ልብ በመጠገን ረገድ፤ ነፍሳችንን በገዛ ደሙ መለጠፊያ ይፈውስ ዘንድ፣ እኛ ራሳችን በኃጢአታችን ባመጣነው በዚያ ሞትም ያድነን ዘንድ ሞተ፤ ታዲያ በሰማይም ያው አንጀት የለውምን? እግር በምድር ሲረገጥ በሰማይ ያለው ራስ፦ «ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ?» ብሎ ጮኸ (የሐዋርያት ሥራ 9:4)። ከፍ ከፍ ማለቱ የገዛ ሥጋውን እንዲረሳ አላደረገውም፤ ከመከራ ነጻ ቢያወጣውም ለእኛ ካለው ርኅራኄ ግን ነጻ አላደረገውም። «ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ» የሚቦጭቀው በላያቸው ሊነግሥ ያልወደዱትን ብቻ ነው (ሉቃስ 19:17)። በፊቱ ራሳቸውን በሚደፉት ላይ ኃይሉን አያሳይም።

ከዚህ በቀር በችግራችን ሁሉ ወደ ጸጋው ዙፋን በድፍረት መቅረብን ካልሆነ ምን እንማራለን? እርሱ በዚያ የሚገለጠው ለኃጢአተኞች ብቻ ሆኖ ሳለ ኃጢአታችን ተስፋ ያስቈርጠናልን? ተቀጥቅጠሃልን? አይዞህ፤ ይጠራሃል፤ ቍስልህን አትሰውር፤ ሁሉን በፊቱ ግለጥ፤ የሰይጣንን ምስጢር አትጠብቅ። እየተንቀጠቀጥህም ቢሆን ወደ ክርስቶስ ሂድ፤ እንደዚያች ምስኪን ሴት «የልብሱን ጫፍ» ብቻ እንኳ ብንዳስስ (ማቴዎስ 9:20)፣ እንፈወሳለን፤ የጸጋ መልስም እናገኛለን። በሥጋችን ወዳለው ወደ እግዚአብሔር በድፍረት ሂድ፤ በድፍረት ወደ እርሱ እንድንሄድ ለዚህ ዓላማ ከሥጋችን ሥጋ ከአጥንታችንም አጥንት ሆኗልና። ወዳጃችን ብቻ ሳይሆን ወንድማችንና ባላችን የሆነ እንዲህ ያለ መካከለኛ በእርሱ ዘንድ ስላለን ወደ እግዚአብሔር ለመሄድ ከቶ አትፍራ። መላእክት ከሰማይ፦ «እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ» ብለው ማወጃቸው ተገቢ ነበር (ሉቃስ 2:10)፤ ሐዋርያውም በጌታ ደግመን ደጋግመን ደስ እንዲለን ቢያነሣሣን ተገቢ ነበር (ፊልጵስዩስ 4:4)፤ ይህን ያደረገበትን ምክንያት በሚገባ ያውቅ ነበር፤ ሰላምና ደስታ የመንግሥቱ ሁለት ዋና ፍሬዎች ናቸው። ዓለም እንደ ፈለገ ይሁን፤ በዓለም ደስ ሊለን ባይቻለን እንኳ በጌታ ደስ ሊለን ይቻለናል። የእርሱ መገኘት ማናቸውንም ሁኔታ የሚያጽናና ያደርገዋል። ደቀ መዛሙርቱ ምትሀት ያዩ መስሏቸው በፈሩ ጊዜ፦ «አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ» አላቸው (ማቴዎስ 14:27)፤ እርሱ ባለበት ለፍርሃት ምንም ምክንያት እንደሌለ ያህል ነው።

ራሳችንን እንደ ተቀጠቀጥን ሲሰማን ይህ ያጽናን፤ የክርስቶስ አካሄድ በመጀመሪያ ማቍሰል፣ ከዚያም መፈወስ ነው፤ ጤናማና ሙሉ የሆነች ነፍስ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገባም። በፈተና ጊዜ እንዲህ ብለህ አስብ፦ ክርስቶስ ስለ እኔ ተፈተነ፤ እንደ ፈተናዬ መጠን ጸጋዎቼና መጽናናቶቼ ይሆናሉ። ክርስቶስ እኔን እስከማይሰብር ድረስ መሐሪ ከሆነ፣ እኔም ተስፋ በመቍረጥ ራሴን አልሰብርም፤ ቈራርጦ እንዲሰብረኝም ለሚያገሣው አንበሳ ለሰይጣን ራሴን አሳልፌ አልሰጥም።

ሦስተኛ፣ የክርስቶስንና የሰይጣንን፣ የመሣሪያዎቹንም ተቃራኒ ጠባይ ተመልከት። ስምዖንና ሌዊ የሴኬም ሰዎች ታመው ሳሉ እንደ ተነሡባቸው (ዘፍጥረት 34:25)፣ ሰይጣን በጣም ደካሞች በሆንንበት ጊዜ ይነሣብናል፤ ክርስቶስ ግን ኃጢአትና ሰይጣን በእኛ ውስጥ ያበጁትን ስብራት ሁሉ ይጠግናል፤ ልባቸው የተሰበረውን ይጠግናል። እናትም ከልጆቿ እጅግ የታመመውንና እጅግ ደካማውን አብልጣ እንደምትንከባከብ፣ እንዲሁ ክርስቶስ በምሕረት ወደ ደካሞቹ አብልጦ ያዘነብላል፤ ደግሞም እጅግ ደካሞቹ ነገሮች ድጋፍ ለማግኘት ከራሳቸው በሚበረታ ነገር ላይ እንዲደገፉ በውስጣቸው ተፈጥሮአዊ ዝንባሌን ያኖራል። የወይን ተክል በብርቱ ዛፍ ላይ ይደገፋል፤ እጅግ ደካሞቹ ፍጥረታትም ብዙ ጊዜ እጅግ ብርቱ መጠለያ አላቸው። ቤተ ክርስቲያን ደካማነቷን ማወቋ በውዷ ላይ እንድትደገፍና ከክንፉ በታች እንድትሸሸግ ፈቃደኛ ያደርጋታል።

ገጽ 1 / 1 · 4 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ