የተቀጠቀጠ ሸምበቆ
ይህን አገዛዝ የሚያስፋፋው ክርስቶስ ብቻ ነው

ምዕራፍ 26 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ

ይህን አገዛዝ የሚያስፋፋው ክርስቶስ ብቻ ነው

አምስተኛው ድምዳሜ ይህ ነው፦ ይህ አገዛዝ የሚቆመውና የሚስፋፋው በክርስቶስ ብቻ ነው፤ ፍርድን ድል ለመንሣት የሚያወጣ እርሱ ነው። የምንዋጋውም የምናሸንፈውም በኃይሉ ችሎት ነው (ኤፌሶን 6:10)፤ ከበጉ ደም የተነሣ በተገኘው መንፈስ ድል እንነሣለን (ራእይ 12:11)።

እጆቻችንን ሰልፍ፣ ጣቶቻችንንም ጦርነት የሚያስተምር እርሱ ብቻ ነው (መዝሙር 144:1)። ተፈጥሮ በመበላሸቷ ለራሷ ህልውና ታደላለች፤ በክርስቶስም አገዛዝ ላይ ራሷን ለማጽናት ትታገላለች። ተፈጥሮን በራሷ ብቻ ብንመለከታት ደግሞ ከራሷ በላይ ከፍ ብላ ወደ ላቀ ደረጃና ባሕርይ ወዳላቸው መንፈሳዊ ሥራዎች ራሷን ልታነሣ አትችልም፤ ስለዚህ ከብርታታችን ሁሉ በላይ ይሸከመን ዘንድ የክርስቶስ መለኮታዊ ኃይል አስፈላጊ ነው፤ በተለይም ብርቱ ተቃውሞ በሚገጥመን መንፈሳዊ ተግባራት ውስጥ፤ በዚያ ተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን፣ ይበልጥ የበረታና አዲስ ብርታት ካልተጨመረ በቀር፣ የተለመደው ጸጋ እንኳ ይከዳናልና። ከተለመደው የከበደ ሸክም የሚያነሣ ሰው ከክብደቱ የሚበልጥ የብርታት መጠን ከሌለው ከሸክሙ በታች ይወድቃል፤ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ብርቱ ግጥሚያ አዲስ ብርታት ያስፈልጋል፤ ጴጥሮስን ተመልከት (ማቴዎስ 26:69)፤ በበረታ ፈተና በተጠቃ ጊዜ በበረታች እጅ ስላልተደገፈና ስላልተያዘ፣ የቀድሞ ብርታቱ ቢኖርም፣ በአሳፋሪ ሁኔታ ወደቀ። ከወደቅንም በኋላ እንደ ገና ስንነሣ ሥራውን ሊሠራ የሚገባው ክርስቶስ ነው፤ ይኸውም፦ 1. የሚቃወሙንን እንቅፋቶች በማስወገድ፣ ወይም 2. በማዳከም፣ ወይም 3. ለጊዜው በማቆም፤ 4. ደግሞም ከመውደቃችን በፊት ከነበረን ወደሚበልጥ ደረጃ የጸጋውን ኃይል በውስጣችን በማሳደግ ነው፤ ስለዚህ በወደቅን ጊዜ፣ በመውደቃችንም ተቀጥቅጠን ስንገኝ፣ እንደ ገና ይጠግነን ዘንድ ወዲያውኑ ወደ ክርስቶስ እንሂድ።

እንግዲህ ከክርስቶስ ልናገኘው የሚገባንን ከራሳችን መጠበቅ አደገኛ መሆኑን እንወቅ። የሶምሶን ብርታት በጠጕሩ እንደ ነበረ (መሳፍንት 16:17)፣ ከውድቀት ወዲህ ብርታታችን ሁሉ በእርሱ ነው፤ እኛ የበታች ሠራተኞች ብቻ ነን፤ እርሱ ሲያንቀሳቅሰን የምንንቀሳቀስ፣ አስቀድሞ በእኛ ላይ ሲሠራ የምንሠራ፣ አርነት በወጣንበት መጠን ብቻ ነጻ የሆንን፣ በምናደርገው በማንኛውም ነገር እርሱ ለጊዜው ከሚያደርገን የማንበልጥ ጠቢባንም ብርቱዎችም ያልሆንን ነን። ያለንን እውቀትና ብርታት የሚያንቀሳቅሰው፣ ሕያው የሚያደርገውና ሥራ ላይ የሚያውለው መንፈሱ ነው፤ ያለዚያ ይከዳናል፤ በውስጣችንም እንደማይጠቅም ነገር ተጥሎ ይቀራል፤ የምንሠራውም አሁን በሚሰጠን ብርታት ስንሠራ ብቻ ነው፤ ስለዚህ በእርሱ የሚደገፉ መንፈሶች ከሁሉ ይልቅ ጠቢባንና ችሎታ ያላቸው ናቸው። ከራሱ ወጥቶ ከሚሄድ ትሕትና የሚበረታ ነገር የለም፤ በራሱ መሠረት ላይ ከሚያርፍ ትዕቢትም የሚደክም ነገር የለም፤ ይህንም ይበልጥ ልናስተውለው ይገባል፤ በተፈጥሮአችን በገዛ ችሎታችን ብርታት ሥራዎችን በመጀመር አንድ ዓይነት አምላክነትን እንመኛለንና፤ ክርስቶስ ግን፦ «ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና» ይላል (ዮሐንስ 15:5)፤ ይህን የሚላቸው በጸጋ ሁኔታ ውስጥ ላሉት ለሐዋርያት ነው። «ጥቂት ማድረግ ትችላላችሁ» አላለም፤ «ምንም» አለ እንጂ። በራሳችን ብንሆን እንዴት በቀላሉ እንሸነፋለን! ለመቃወምስ እንዴት ደካሞች ነን! እኛ ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆ እንመስላለን፤ ስለ ድህነት፣ ስለ ውርደት፣ ስለ ኪሳራና ስለ ሌሎችም ነገሮች በሚወራው ወሬና በሚታሰበው አሳብ እንኳ እንንቀጠቀጣለን፤ ወዲያውኑ እጅ እንሰጣለን፤ በዓይኖቻችን፣ በአንደበታችን፣ በአሳባችንና በልብ ዝንባሌዎቻችን ላይ ሥልጣን የለንም፤ ኃጢአትን እንዲገባና እንዲወጣ እንተወዋለን እንጂ። ክፉውን በመልካም ልናሸንፍ ሲገባን፣ በክፉ እንዴት ቶሎ እንሸነፋለን! ስንቱ መልካም አሳብ ገና ሲወለድ ተይዞ ይቀራል፤ ወደ ውጭ ለመውጣትም ብርታት ያጣል! ይህ ሁሉ ያለ ክርስቶስ መንፈስ ምን ያህል ከንቱዎች እንደ ሆንን ያሳያል። ሐዋርያት ራሳቸው ከላይ ኃይል እስኪለብሱ ድረስ ምን ያህል ደካሞች እንደ ነበሩ እናያለን (ማቴዎስ 26:69)፤ ጴጥሮስ በአንዲት ገረድ ንግግር ደረቀ፤ የክርስቶስ መንፈስ በእነርሱ ላይ ከወረደ በኋላ ግን፣ መከራ በተቀበሉ መጠን መከራን ለመቀበል ይበልጥ ይበረታቱ ነበር፤ መጽናናታቸው ከመከራቸው ጋር አብሮ አደገ፤ ስለዚህ በሁሉም ነገር፣ በተለይም በአስቸጋሪ ግጥሚያዎች፣ በችግሮቻችን ሁሉ ለሁላችን የሚበቃ መንፈስ ወዳለው ወደ ክርስቶስ ልባችንን እናንሣ፤ ከመልካሙ ኢዮሣፍጥም ጋር፦ «አቤቱ፥ የምናደርገውን አናውቅም፤ ዓይኖቻችን ግን ወደ አንተ ናቸው» እንበል (2ኛ ዜና መዋዕል 20:12)፤ የምንዋጋው ሰልፍ የአንተ ነው፤ የምንዋጋበትም ብርታት የአንተ ሊሆን ይገባል። ከእኛ ጋር ባትወጣ በእርግጥ እንሸነፋለን። ሰይጣን በክርስቶስ ላይ ወይም በኃይሉ በሚታመኑት ላይ ምንም ሊያሸንፍ እንደማይችል ያውቃል፤ ስለዚህ ትጋቱ ሁሉ እኛን በራሳችንና በፍጥረት ላይ እንዴት እንደሚያስቀረን ነው፤ እኛ ግን በራስ መተማመን የተጀመረ ነገር በኀፍረት እንደሚያልቅ ይህን ሁልጊዜ በአእምሮአችን ልንይዝ ይገባናል።

ክርስቶስ ፍርድን ድል ለመንሣት የሚያወጣበት መንገድ በእርሱ ላይ የመደገፍን አስፈላጊነት እንድናይ በማድረግ ነው፤ ከዚህም የተነሣ ያ መንፈሳዊ መተው ይመጣል፤ በእርሱም የጸጋንና የመጽናናትን ምንጭ ከራሳችን ውጭ መሆኑን እናውቅ ዘንድ በጸጋም በመጽናናትም በኩል ብዙ ጊዜ ለራሳችን ይተወናል። በተራራው ላይ፣ ይኸውም በጭንቅ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ይበልጥ የሚታየው ስለዚህ ነው (ዘፍጥረት 22:13)። ከራሳችን አውጥቶ በሌላው ላይ እንድንደገፍ በሚያደርገን በእምነት ጸጋ የምንድነውም፣ እምነትም የውጭ ድጋፍ ባነሰው ጊዜ ብቻውን ሆኖ የተሻለ የሚሠራውም ስለዚህ ነው። በትናንሽ ግጭቶች ብዙ ጊዜ የምንወድቀውና በታላላቆቹ የምንጸናውም ስለዚህ ነው፤ በትናንሾቹ በራሳችን ይበልጥ እናርፋለን፤ በታላላቆቹ ግን ከእኛ ወደሚረዝመው ወደ መዳናችን ዓለት እንሸሻለንና። እንዲሁም ከውድቀት በኋላ ይበልጥ የምንበረታው ስለዚህ ነው፤ ቀድሞ ያልታወቀው የተሰወረ ርኵሰት አሁን ይገለጣል፤ ከዚያም ይቅር ወደሚለው ምሕረትና ወደሚደግፈው ኃይል እንድንጠጋ እንመራለን። የዚህ አሠራር አንዱ ዋና ምክንያት መፈለግንም ማድረግንም በእኛ የሚሠራ፣ ይህንም እንደ በጎ ፈቃዱ በገዛ ፈቃዱ የሚያደርግ ክርስቶስ መሆኑን እናውቅ ዘንድ ነው። ስለዚህ ያለ አክብሮትና በድፍረት በመመላለስ የቸርነቱን ኃይል እንዲያቋርጥና ለገዛ ልባችን ጨለማ እንዲተወን ምክንያት እንዳንሰጠው፣ በቅንዓት በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መዳናችንን ልንፈጽም ይገባናል (ፊልጵስዩስ 2:12)።

በክርስቶስ አገዛዝ ሥር ያሉት የመገለጥ መንፈስ አላቸው፤ በእርሱም መለኮታዊ ኃይል በጣፋጭነትና በብርታት ሲያስችላቸው ያያሉ፤ ይሰማቸዋልም፤ ይኸውም ተቃራኒው ሲሰማቸው እምነትን፣ ተስፋ በሌለበት ሁኔታ ተስፋን፣ የእግዚአብሔር አለመደሰት ምልክቶች ባሉበትም ለእግዚአብሔር ፍቅርን፣ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ በሚስቡ ዓለማዊ ጉዳዮችና መደለያዎች መካከልም ሰማያዊ አሳብን ጠብቀው እንዲኖሩ ነው፤ ትዕግሥትን፣ እንዲያውም የሚያስለቅሱ ምክንያቶች በከበቡአቸው መካከል ደስታን፣ በጥቃቶችም መካከል ውስጣዊ ሰላምን የሚጠብቅ ኃይል ይሰማቸዋል። በፈተና በተጠቃን ጊዜ፣ በመከራዎችም በተከበብን ጊዜ የጸናነው ከሚደግፈን ከስውር ብርታት ካልሆነ ከወዴት ነው? ይህን ያህል ጥቂት ጸጋ ይህን በሚያህል ታላቅ የርኵሰት ክምር ላይ ድል አድራጊ ማድረግ ከሰው በላይ የሆነ መንፈስ ይጠይቃል፤ ይህ በባሕር ውስጥ እሳትን፣ በሲኦል ውስጥ እንኳ የሰማይን ቍራጭ እንደ መጠበቅ ነው። ይህን ኃይል ከወዴት እንደምናገኘው፣ ምስጋናውንም ለማን እንደምንመልስ በዚህ እናውቃለን። ለእግዚአብሔርም ለእኛም እጅግ ቅርብ በሆነው በክርስቶስ ውስጥ ለእኛ ተብሎ እንዲህ በደኅንነት መሰወሩ ደስታችን ነው። ከውድቀት ወዲህ እግዚአብሔር የገዛ መዳናችንን በእጃችን አያደርግም፤ ነገር ግን መዳን በክርስቶስ ለእኛ የተገዛና የተጠበቀ ነው፤ እኛም በእግዚአብሔር ኃይል በተሠራውና ያንኑ ኃይል በሚይዘው በእምነት ለእርሱ ተጠብቀናል፤ ይህንንም ኃይል ቅዱስ ጳውሎስ በክብር ይገልጠዋል፤ ይኸውም፦ 1. ታላቅ ኃይል፣ 2. እጅግ የበዛ ኃይል፣ 3. የሚሠራና ብርቱ ኃይል፣ 4. ክርስቶስን ከሙታን ባስነሣበት የተሠራ ዓይነት ኃይል ነው (ኤፌሶን 1:19)። በማባበል ብቻ የሚቀርብ፣ መቀበሉ ወይም እምቢ ማለቱም በእኛ ፈቃድ የሆነ ጸጋ ወደ ሰማይ የሚያደርሰን ጸጋ አይደለም፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ ግን ኃያል የሆነ የመንፈስ ሥራ ይሰማቸዋል፤ ይህም ጐስቋላነታችንንና በክርስቶስ በኩል ያለውን መዳናችንን የሚገልጥልን ብቻ ሳይሆን፣ ከራሳችን እንደ ተዋጀን ከራሳችን ባዶ የሚያደርገን፣ አዲስ ሕይወትንም በውስጣችን የሚያፈስስ፣ ከዚያም በኋላ የሚያበረታን፣ ስንዝልና ክንፋችንን ስናወርድ የሚያነቃቃን፣ ፍጹም ድል እስክናገኝ ድረስም ፈጽሞ የማይተወን ሥራ ነው።

ገጽ 1 / 1 · 5 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ