የተቀጠቀጠ ሸምበቆ
የክርስቶስ አገዛዝ በግልጥ ድል አድራጊ ይሆናል

ምዕራፍ 25 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ

የክርስቶስ አገዛዝ በግልጥ ድል አድራጊ ይሆናል

ፍርድ ድል አድራጊ ይሆናል የተባለው ብቻ ሳይሆን፣ ክርስቶስ በግልጥ ወደ ድል እንደሚያወጣው ደግሞ ተነግሮአል። ከዚህም ጸጋ ክብር እንደሚሆንና የሁሉንም ዓይን እንደሚስብ እናስተውላለን። አሁን ክርስቶስ ድል ያደርጋል፤ ዓላማዎቹንም ይፈጽማል፤ ነገር ግን በተወሰነ መልኩ በማይታይ ሁኔታ ነው፤ በውስጣችንና በውጭ ያሉ ጠላቶቹ የበላይነት ያላቸው ይመስላሉ። ነገር ግን ፍርድን ድል ለመንሣት በሁሉ ፊት ያወጣዋል። አሁን ዓይናቸውን የሚጨፍኑ ክፉዎች ለሥቃያቸው ያዩታል። ብልጣ ብልጥ ሰዎች የፈለጉትን ማየት ወይም አለማየት በሥልጣናቸው አይሆንም፤ ክርስቶስ በልባቸው ላይ ሥልጣን ይኖረዋል፤ ቍጣውም ያለ ፈቃዳቸው ወዲያውኑ ነፍሳቸውን እንደሚይዝ፣ እንዲሁ መከራቸውን የሚያበዛውን እንዲያዩና እንዲያውቁ በነፍሳቸው ዓይኖች ላይ ሥልጣን ይኖረዋል፤ ኀዘን ከሕዋሳቶቻቸው ሁሉ ጋር፣ ሕዋሳቶቻቸውም ከኀዘን ጋር ይጣበቃሉ።

ያን ጊዜ በነገሮች ላይ የሚቀቡአቸው የሐሰት ማሳመሪያዎች ሁሉ ይጠረጋሉ። ሰዎች የመልካምነትን ስም፣ የክፋትንም ጣፋጭነት በአንድነት ሊያገኙ ይመኛሉ፤ ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ዓይን የሚገልጣቸውን ያን እውነት ያህል ከልባቸው የሚቃወሙት ምንም ነገር የለም፤ ዋናው ጭንቀታቸው ከዓለምና ከገዛ ሕሊናቸው ጋር እንዴት ተለሳልሰው እንደሚኖሩ ነውና። ነገር ግን ከዚህ ከሞኞች ገነት የሚባረሩበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገሮችን ያስተላለፉበት መንገድ ይበልጥ ብልጠት የተሞላበት በሆነ መጠን ኀፍረታቸው ይበልጣል። እግዚአብሔር የባሕርያቱን ዋና ክብር ይገልጥ ዘንድ የመረጠው ክርስቶስ አሁን ከአካሉ ከቤተ ክርስቲያን አንጻር ተከድኖአል፤ ነገር ግን በቅዱሳኑ ሊከበር ብዙም ሳይቆይ ይመጣል (2ኛ ተሰሎንቄ 1:10)፤ ከባሕርያቱም የአንዱንም ግልጥ መገለጥ አያጣም፤ ከክርስቶስና ከሙሽራይቱ ክብር በቀር ሌላ ክብር በማይኖርበት ጊዜ እርሱ ማን እንደ ሆነ ለዓለም ሁሉ ያሳውቃል። አሁን እንደሚጤስ የጥዋፍ ክር ያሉት በዚያን ጊዜ በሰማይ ጠፈር ላይ እንደ ፀሐይ ይበራሉ (ማቴዎስ 13:43)፤ ጽድቃቸውም እንደ ቀትር ይወጣል (መዝሙር 37:6)። በአዳም ውስጥ የነበረው የእግዚአብሔር መልክ ፍጥረታት ሁሉ እስኪያከብሩት ድረስ የሚያዝዝ ግርማ ነበረው፤ በፍጹምነቱ ያለው የእግዚአብሔር መልክማ በሁሉ ዘንድ አክብሮትን እንዴት አብልጦ ያዝዝ ይሆን! አሁንም እንኳ ታላላቆቹ ጸጋ ሲያበራባቸው በሚያዩአቸው ሰዎች ፊት በልባቸው ውስጥ ስውር ፍርሃት ይኖራል፤ ሄሮድስ መጥምቁን ዮሐንስን የፈራው ከዚህ የተነሣ ነበር፤ ታዲያ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ቀን ተብሎ በሚጠራው በመገለጣቸው ቀን ይህ እንዴት ይሆን? (ሮሜ 8:19)። የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ የሚሆንበትና ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል የሚባልበት ይበልጥ የከበረ ዘመን ይመጣል (ራእይ 11:15)፤ ያን ጊዜ ፍርድና እውነት ድላቸውን ያገኛሉ፤ ያን ጊዜ ክርስቶስ የገዛ ጉዳዩን ይሟገታል፤ እውነት ከዚያ በኋላ ኑፋቄና መከፋፈል ተብላ አትጠራም፤ ኑፋቄም ኵላዊ ትምህርት ተብሎ አይጠራም፤ ክፋት ከዚያ በኋላ ጭምብል ለብሶና ተሸሽጎ አይመላለስም፤ መልካምነት በራሱ ድምቀት ይገለጣል፤ በራሱም ጨረሮች ያበራል፤ ነገሮች እንደ ማንነታቸው ይሆናሉ፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለም (ማቴዎስ 10:26)፤ ዓመፅ ከዚያ በኋላ በምሥጢር አይመላለስም፤ ምክራቸውን ከጌታ ለመሰወር የሚያስቡ ጥልቅ አስመሳዮች ከዚያ በኋላ በደመና ውስጥ እንዳሉ ሳይታዩ አይመላለሱም። ክርስቶስ በራሱ የተለኰሰችውን እጅግ ታናሿን ፍንጣሪ እንደማያጠፋ፣ እንዲሁ ከላይ ያልሆኑትን የሚያማምሩ ውጫዊ መልኮች እጅግ ያማረውን ነበልባል እንኳ ያዳፍናል።

ይህ ቢታመን ኖሮ፣ ሰዎች ድፍረትን ብቻውን ለሚሰጠን ለቅንነት ይበልጥ ዋጋ በሰጡ ነበር፤ የኀፍረት መሸፈኛዎችንም ባልፈለጉ ነበር፤ በእነርሱ መታመን አሁን ሰዎችን ይበልጥ ትምክህተኞች እንደሚያደርግ፣ እንዲሁ ከዚህ በኋላ ለታላቅ ኀፍረት ያጋልጣቸዋል።

ፍርድ ወደ ድል የሚወጣ ከሆነ፣ በገዛ አታላይ ልባቸውና በስሕተት መንፈስ የተገዙ ሰዎች ወደ ውርደት ይወጣሉ፤ ጸጋንና እውነትን ከክብር ጋር ያጣመረ ያ እግዚአብሔር፣ በመጨረሻ ኃጢአትንና ኀፍረትን አጣምሮአቸዋል፤ የሰው ብልሃትና ኃይል ሁሉ እግዚአብሔር ያጣመረውን ከቶ ሊለየው አይችልም። እውነትና እግዚአብሔርን መምሰል ለጊዜው ሊረገጡ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሁለቱ ምስክሮች ከተገደሉ በኋላ ዳግመኛ ተነሥተው በእግሮቻቸውም ቆሙ (ራእይ 11:11) እንደ ተባለ፣ እንዲሁ ከእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ በመጨረሻ በገዛ መሠረቱ ላይ ይቆማል። የሥጋ ብቻ ሳይሆን የመልካም ስምም ትንሣኤ ይኖራል። መላእክትን ከሰማይ የጣለው እርሱ፣ ትቢያና የትል መብል ተቃራኒ መንገድ እንዲሄዱና ሁልጊዜ እንዲህ አሸንፈው እንዲቀጥሉ ይፈቅዳል ብለን ልናስብ እንችላለን? አይደለም፤ ክርስቶስ በእውነት የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ እንደ ሆነ (ራእይ 19:16)፣ እንዲሁ በእርሱ ላይ የሚነሡትን እነዚያን የአፈር ቍርጥራጮች ሁሉ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃ ያደቅቃቸዋል (መዝሙር 2:9)። በእግዚአብሔር ላይ ጨክኖ የተነሣና የተከናወነለት ማን አለ? (ኢዮብ 9:4)። አንድም የለም፤ ያለ ጥርጥር የሰው ቍጣ ለክርስቶስ ምስጋና ይሆናል (መዝሙር 76:10)። ስለ ፈርዖን የተነገረው ከፈቃዳቸው ይልቅ ነፍሳቸውን ማጣት ስለሚመርጡ እልኸኞች ጠላቶች ሁሉ ይነገራል፤ ይኸውም ክርስቶስ በውርደታቸው ለራሱ ክብርን ያገኝ ዘንድ ብቻ እንደ ተነሡ ነው።

እንግዲህ ፍጻሜያቸውን አይተን የምንንቀጠቀጥባቸውን የእነዚያን ሰዎች መንገዶች እንዳንከተል እንጠንቀቅ፤ በሰዎችና በነገሮች ላይ ለማይረባ ፍርድ ተላልፎ ከመሰጠት የበለጠ በሰው ባሕርይ ላይ ሊደርስ የሚችል የሚያስፈራ ፍርድ የለም፤ ክፉውን መልካም መልካሙንም ክፉ ማለት ከወዮታ በታች ነውና (ኢሳይያስ 5:20)።

በአሳሳች ክርክርና በሽንገላ የሌሎችን ፍርድ የሚያጣምሙ፣ እያሳቱና እየሳቱ የሚኖሩ ሰዎች በሌላ ቀን እንዴት በእርግማን ይጫኑ ይሆን? ያን ጊዜ የቀዳሚቱ እናታችን የሔዋን ማማረር ይነሣል፤ ግን ፍሬ ቢስ ሆኖ ነው (ዘፍጥረት 3:13)፦ እባብ አሳተኝ፤ ሰይጣን በእገሌና በእገሌ በኩል አሳተኝ፤ ኃጢአት አሳተኝ፤ ሰነፍ ልብ አሳተኝ። ነፍሳችንን በምን መሠረት ላይ አደጋ ላይ እንደምንጥል ማሰብ ከጥበብ ከፍተኛ ነጥቦች አንዱ ነው። በክርስቶስ ብርሃን ስለ ነገሮች ትክክለኛ ፍርድ ያላቸውና ያ ፍርድ በልባቸው ላይ እንዲሰለጥን የሚፈቅዱ ሰዎች ብፁዓን ይሆናሉ።

የብዙ ሰዎች ነፍስ በሕዋሳታቸው ውስጥ ሰጥማለች፤ ከተራ ሰዎች ስሕተትና ከነገሮች ጥላ በተነሡ ደካማ አስተያየቶችም ትወሰዳለች። ሰይጣንም የውጭውን መልካምና የውጭውን ክፉ ምናብ ሊያሰፋና ካለው በላይ ሊያገዝፍ፣ መንፈሳዊ ነገሮችን ግን ሊያሳንስ፣ በሐሰተኛ መነጽሮች እያሳየ ዝግጁ ነው። በዚህም ሰዎች በከንቱነት እየታመኑ በገዛ ግምታቸው ራሳቸውን ያሸንፋሉ። እኛም አብልጠን የምናከብረውም ነገር አብረን የምንጠፋበት ሁኔታ እንዴት ያለ ወዮታ ነው! ይህም የክርስቶስ ፍርድ ወደ ድል እንደሚመጣ ያህል በእርግጥ ይሆናል፤ የሰው ከንቱ ልብ በዚህ ዓለም ነገሮች ውስጥ ካለው የበለጠ መልካም ነገር ለመገመት በሰፋበት መጠን፣ ነፍስ ስሕተቷን ባየች ጊዜ መከራዋ ይበልጥ እንዲሰማት በዚያው መጠን ትሰፋለች። እግዚአብሔርን በሚፈራ ጥበበኛ ሰውና በተታለለ ዓለማዊ ሰው መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው፤ አንዱ አሁን ከንቱ ነው ብሎ የሚፈርድበትን ሌላው ከዚህ በኋላ፣ ጊዜው ካለፈ በኋላ፣ ከንቱ መሆኑ ይሰማዋል። ነገር ግን የባሕርያችን ከንቱነት ይህ ነው፤ በአሁኑ ነገሮች ከመታለልና ከመሳሳት ከሁሉ አብልጠን ብንሸሽም፣ ከሁሉ በሚበልጡት ጉዳዮች ግን ወደን አላዋቂዎችና የተሳሳትን እንሆናለን።

ገጽ 1 / 1 · 4 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ