እንደ ንስር ተምዘግዘግ
ቅባት

ምዕራፍ 9 · 12 ደቂቃ ንባብ · 15 ደቂቃ ማዳመጥ

ቅባት

በምዕራፍ ሁለት ውስጥ ቅባትን ስተረጉም እግዚአብሔር በአንድ ሰው ወይም በአንድ አገልግሎት ላይ ማኅተሙን፣ ይሁንታውንም ማኖሩ ነው ብዬ ነበር፤ ይህም በሚገለገሉት ሰዎች ሕይወት ላይ ዘላለማዊ ተጽዕኖ እንዲኖር ነው።

እርሱ አንዳንድ አገልግሎቶችን እንደሚቀባና ማንም ሰው ሊያቀናብረው የማይችል አስደናቂ ውጤት እንደሚታይ ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ በዚህ ጊዜ (በ1999) «የዕርቅ ጉዞ» እየተካሄደ ነው፤ በዚህ ጉዞ ጥቂት አማኞች የመስቀል ጦረኞች ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት የሄዱበትን መንገድ ዳግመኛ እየተከተሉ ነው። እነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች ቅድስቲቱን ከተማ ከሙስሊሞች እጅ ነጻ ለማውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ አውሮፓን አቋርጠው ባደረጉት ጉዞ በፈጸሙት ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና ዝርፊያ ይታወሳሉ።

ሊይዙት የቻሉት ሙስሊምም ሆነ አይሁዳዊ ሁሉ ማለት ይቻላል ተገድሏል። የዛሬው ሙስሊም በክርስቲያኑ ላይ ላለው ጥላቻና አለመግባባት ዘሩን የዘሩት እነርሱ ናቸው። የዛሬዎቹ ተጓዦች ግን ፍጹም የተለየ ዓላማ አላቸው። በሄዱበት ሁሉ ወደ ሙስሊም መሪዎች ቀርበው በዐረብኛ፣ በእንግሊዝኛና በአካባቢው ቋንቋ የሚነበብ የጽሑፍ ይቅርታ ያቀርባሉ። ምንም ቅድመ ሁኔታ የለበትም፤ ከብዙ ዘመን በፊት በመስቀል ዓርማ ሥር የተፈጸሙትን በደሎች በትሕትና የራስ አድርጎ መቀበልና ማመን ብቻ ነው። በ1999 መጨረሻ የንስሐና የዕርቅ መልእክታቸውን ይዘው ኢየሩሳሌም እንደሚደርሱ ይጠብቃሉ።

የኢማሞችና የመስጊድ መሪዎች ምላሽ መደነቅና መቀበል ሆኗል፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም የእነዚህን ክርስቲያኖች መምጣት ከአስተርእዮ — እግዚአብሔር በአደባባይ ሕዝቡን ከመጎብኘቱ — ጋር አመሳስለውታል። ብሔራዊ ጋዜጦች፣ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ለአገሮቻቸው ሕዝብ ሁሉ ብዙ በጎ ዘገባዎችን አስተላልፈዋል።

ከዚህ አስደናቂ ክንውን ጋር ስማቸው የተያያዘ ወንዶችና ሴቶች አሉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በአውሮፓ ሙስሊም ሕዝቦች ልብ ላይ ሲሠራ ሁሉም ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆነው ለመቆየት ይጓጓሉ። በእውነት ቅባቱ በዚህ አገልግሎት ላይ ነው።

አንተም የእግዚአብሔር ደስታ ግልጽ ሆኖ የሚታይባቸውንና ታላቅ ዘላለማዊ ተጽዕኖ እየተደረገባቸው ያሉ አገልግሎቶችን ልታስብ እንደምትችል እርግጠኛ ነኝ። ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ልብ ሳይሆን በሰው አእምሮ የተወለዱ ሌሎች እጅግ ብዙ ፕሮግራሞች አሉ። ያስጀመረው ሰው ለዚህ ሥራ ባለው ቁርጠኝነት ቅንና ትጉ ሊሆን ይችላል — እግዚአብሔርም ታማኝነቱን ለማክበር በተወሰነ መጠን ስኬት ሊሰጠው ይችላል — ነገር ግን ቅባቱ ጥቂት ነው ወይም ፈጽሞ የለም። እኔ ራሴ እንኳ ወንጌልን በማስፋፋት ስም ብዙ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ድርጊቶችንና ሰብአዊነትን ብቻ ያማከለ አስተሳሰብን ያየሁባቸው ትልልቅ አገልግሎቶች አካል ሆኜ ነበር።

ፕሮግራማችንን ያለ ብዙ እንቅፋት እንድንቀጥል ብቻ በሰዎች ላይ የፖለቲካ ጫና ተደረገ፤ ሥራቸውን እንደሚያጡ ተዛተባቸው፤ ሁኔታዎች በተንኮል ተቀነባበሩ፤ ግማሽ እውነቶች ተነገሩ (ከውሸት በምንም አይለዩም!)። ነፍሳት ዳኑ — የእግዚአብሔር ጸጋ ድንቅ አይደለምን? — ከዚያ በኋላ ግን ሰዎች ግቡ መንገዱን ትክክል ያደርገዋል ብለው አመኑ፤ ቀጣዩን ፕሮግራማቸውንም በዚያው በሚናወጥ መሠረት ላይ ማቀዳቸውን ቀጠሉ። በፊቱ ታማኝነታችንንና ትሕትናችንን ጠብቀን ቢሆን ኖሮ የእግዚአብሔርን ጸጋ ምን ያህል አብልጠን ባየን ነበር?

ዛሬ ዓለማዊ የንግድ ሥራ ቢጀምሩ ኖሮ በዚያው ልክ ስኬታማ ይሆኑ የነበሩ ትልልቅ «አገልግሎቶች» ያሏቸው ብዙ ሰዎች አሉ። አገልግሎቱ የተገነባው በእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታዎች (ካሪስማታ) እና ቅባት ላይ ሳይሆን በግል ማራኪነታቸው (ካሪዝማ) ወይም በንግድ ብልሃታቸው ላይ ነው። በአብያተ ክርስቲያናቶቻችን ያሉ ብዙዎች በእምነታቸው ላይ ላዩን ብቻ የሆኑበትና ኢየሱስ እንድንሆን የሚጠራንና የሚጠብቅብንን ድል ነሺዎች መሆን የተሳናቸው ዋነኛ ምክንያት ይህ እንደ ሆነ ጥርጥር የለውም፤ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትና ፓስተሮች የሚታገሉበት፣ ቤተ ክርስቲያን ብለን በምንጠራው ብዙ ነገር ላይ የገሃነም ደጆች የሚበረቱበት፣ በመንግሥቶቻችን ዓለማዊና ሰብአዊነትን ብቻ ያማከለ አስተሳሰብ ላይ ይህን ያህል ጥቂት ተጽዕኖ የሚደረግበትም ምክንያት ይኸው ነው።

የእግዚአብሔር ቅባት ያለባቸው ወንዶች፣ ሴቶችና ፕሮግራሞች እጅግ ያስፈልጉናል። እርሱ ያላስጀመራቸውን ፕሮግራሞች፣ ላላስታጠቃቸውና በሚሳተፉበት አገልግሎት ውስጥ ላልለቀቃቸው ሰዎችስ ለምን ቅባቱን ይሰጣል? እርሱ በሰዎች ላይ ሸክምን አኑሯል፤ አስታጥቋቸዋልም፤ በእነርሱም አማካይነት ክብሩን በታላቅ ቅባት ይገልጥ ዘንድ ወደ አገልግሎቱ እስኪለቀቁ ድረስ ይጠብቃል።

አንዳንድ ጊዜ መለቀቅ የሚያስፈልጋቸው ምእመናን ሳይሆኑ አገልጋዮቹ ናቸው!

በአውስትራሊያ፣ በኩዊንስላንድ የሚኖሩትን ጂምና ካቲ የተባሉ ወጣት ባልና ሚስት ቤት ጎበኘሁ። ጂም ሥራቸውን ለማስፋፋት ለሚያስቡና እንዲህ ያለው እርምጃ ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ የባለሙያ ማስተዋል ለሚያስፈልጋቸው አነስተኛ የንግድ ድርጅቶች አማካሪ ነበር። ለጥቂት ዓመታት በገንዘብ ረገድ እንዴት እንደ ተቸገሩ ነገረኝ፤ ምክንያቱም ለኩባንያ ዳይሬክተሮች «እጅ መንሻ» (ጉቦ) በመስጠት ለመሳተፍ እምቢ በማለቱ አንዳንድ ድርጅቶች ሊቀጥሩት አልፈለጉም ነበር። ጂምና ካቲ የሚካፈሉባት ቤተ ክርስቲያን የተሰብሳቢዎቿ ቁጥር ከአርባ ሰው እምብዛም አያልፍም ነበር።

አንድ ዓመት እርሱና ፓስተሩ ከአውስትራሊያ ሰሜን ምሥራቅ ጠረፍ ባሻገር ወደምትገኘው በአቅራቢያቸው ወዳለችው ያልበለጸገች አገር ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚስዮን ጉዞ አደረጉ። ጂም ወደ ቤቱ ሲመለስ ጌታ አገልግሎታቸውን፣ በተለይም የፓስተራቸውን አገልግሎት እንዴት እንደ ቀባው የሚያሳዩ ታሪኮችን በታላቅ ደስታ ይተርክ ነበር።

«ካቲ» አላት፤ «ፓስተራችን ለፓፑዋ ኒው ጊኒ ሕዝብ ሲያገለግል ታላቅ ቅባት በእርሱ ላይ ነበረ። የጌታ መንፈስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተጠቀመበት፤ ብዙ ሰዎችም በክርስቶስ ወደ ማመን መጡ። ብዙ ጊዜ ወደዚያ ልንልከው ይገባናል፤ ነገር ግን እርሱም ሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአሁኑ ጊዜ ይህን ለመሸፈን አቅም እንደሌላቸው አውቃለሁ። ፓስተሩን ብዙ ጊዜ ለሚስዮን ጉዞ የምንልክበትን ገንዘብ ለማጠራቀም ገቢያችንን አብቃቅተን በየወሩ ጥቂት ገንዘብ ማስቀመጥ እንችል ይሆን?»

ይህን ለማድረግም ተስማሙ። ፓስተራቸውን ወደ ተሾመበት አገልግሎት ሊለቅቁት ወሰኑ። ጂም ይህን ታሪክ ከአንድ ዓመት በኋላ ሲነግረኝ አንድ አስደናቂ ተጨማሪ ነገር አከለበት። በዚያ አንድ ዓመት ውስጥ ሥራው ከዚያ በፊት በነበረ በየትኛውም ዓመት ካገኙት ገቢ አሥር እጥፍ አስገኝቶ ነበር፤ ፓስተራቸውንም ጥቂት ጊዜ ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ መላክ ብቻ ሳይሆን፣ በአገልግሎቱ አብረውት እንዲሄዱ ሌሎች በርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላትም ወጪ መሸፈን ችለው ነበር!

የጂም የሥራ መጠን ያው ነበር፤ አሁን የሚቀጥሩት ድርጅቶች ግን ከዚህ ቀደም አግኝቶት ከማያውቀው እጅግ የሚበልጥ ኮሚሽን ይከፍሉት ነበር። እግዚአብሔር የፓስተራቸውን አገልግሎት መቀባቱ ብቻ ሳይሆን የጂምንና የካቲንም «በልግስና የመስጠት» አገልግሎት እየቀባ ነበር። ጂም ምናልባት ፈጽሞ ሰባኪ ወይም ወንጌላዊ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን አገልግሎቱን አግኝቷል፤ እጅግም ረክቷል፤ እንደ ንስርም እየበረረ ነው።

ጂምንና ካቲን በሚቀጥለው ጊዜ ስጎበኛቸው ታሪኩ ይበልጥ አስደናቂ ሆኖ ነበር። እኔ እዚያ ከነበርሁበት ጊዜ ጀምሮ ገቢው በየዓመቱ እጥፍ እንደ ሆነ ነገረኝ፤ ስለዚህ አሁን ቀድሞ ያገኘው ከነበረው ስምንት እጥፍ ያገኝ ነበር። «ይሁን እንጂ» አለ፤ «አሁንም በዚያው ቤት እንደምኖርና በመኪና ማቆሚያዬ ላይ ያችው (ትንሽ) መኪና እንዳለች ታያለህ። ምክንያቱም ባለፉት አራት ዓመታት እያንዳንዱን የቤተ ክርስቲያናችንን አባል ወደ ሚስዮን መስክ ልከናል፤ አንዳንዶቹንም ብዙ ጊዜ። ጌታን በማገልገል ይህን ያህል እየተደሰትን ሳለ ትልቅ ቤት ወይም የተሻለ መኪና ለምን እንፈልጋለን?»

ኢየሱስ «ከመንፈስ ቅዱስ የተወለደ» ነበረ፤ እኛ ግን እንደ እርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ በዚያው መንፈስ «ዳግመኛ መወለድ» ያስፈልገናል — ከእኛ ማናችንም እንደ እርሱ አይደለንም። የእግዚአብሔር መንፈስ በሰውዬው በኢየሱስ ውስጥ አደረ።

በእውነት እርሱ ሥጋ የለበሰ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ። ቃል (እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበት) ሥጋ ሆኖ በእኛ አደረ። አንድ ቀን ኢየሱስ በዮርዳኖስ ሰዎችን እያጠመቀ ወደ ነበረው ወደ ዘመዱ ወደ ዮሐንስ መጣ። የዮሐንስ ጥምቀት የዳግም ልደት ጥምቀት ወይም በሕዝብ ፊት እምነትን የመመስከር ጥምቀት አልነበረም፤ የንስሐና ወደ ሕጉ ትክክለኛ አስተምህሮ የመመለስ ጥምቀት ነበር እንጂ።

«ዮሐንስ ሆይ፣ አጥምቀኝ» አለ ኢየሱስ።

«ኢየሱስ ሆይ፣ እኔ ላጠምቅህ አልችልም። እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል!» አለ ዮሐንስ።

«ዮሐንስ ሆይ፣ አጥምቀኝ» አለ ኢየሱስ ደግሞ፤ «እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና።»

ዮሐንስም አጠመቀው።

«መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።»

ወዲያውኑ በመንፈስ ተመርቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ በዚያም አርባ ጸጥ ያሉ ቀናትን ያሳልፍ ነበር። ጸጥ ያሉ የሚባሉት በዚያ ጊዜ ፍጻሜ ሰይጣን እስኪፈትነው ድረስ የሆነውን የሚነግረን መዝገብ ስለሌለን ብቻ ነው። መገመት ትምህርተ መለኮት እስካላደረግነው ድረስ ጉዳት የለውም፤ እኔ ግን መንፈስ ቅዱስ ለምን እንዲህ እንደ መራው ብዙ ጊዜ አስቤአለሁ።

እነዚያ አርባ ቀናት ከአባቱ ጋር በኅብረት ያሳለፋቸው እንደ ሆኑ ለማመን ደርሻለሁ፤ በዚያም በፊቱ የተዘረጋውን መንገድ — ቤዛነታችንን ብቻውን ሊገዛ በሚችለው በጌቴሴማኒና በቀራንዮ በኩል ያለውን ጉዞ — ተማረ። አገልግሎቱ ተሰጠው።

ኢየሱስ ወደ ትውልድ ከተማው ወደ ናዝሬት ሲመለስ ወደ ምኩራብ ገባ፤ መጻሕፍትንም አንሥቶ እንዲህ ብሎ አነበበ፦ «የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ፥ የተወደደችውንም የጌታ ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል።»

…ይህንም ማድረግ ጀመረ። በሌሎች ፍላጎትና ምኞት ከመንገዱ ፈቀቅ እንዲል ራሱን አልፈቀደም።

ዮሐንስ ከሄሮድስ ቤተ መንግሥት በታች ወዳሉት የወህኒ ጉድጓዶች በተጣለ ጊዜ ዘመዱ ኢየሱስ ስለዚህ አንድ ነገር እንደሚያደርግ ይጠብቅ ነበር። ለመሆኑ መንግሥቱን በምድር ላይ ሊያቋቁም አልነበረምን?

የሮማን መንግሥት ከሄሮድሶቹ ጋር ሊገለብጥ አልነበረምን? ምርኮኞችን ነጻ ሊያወጣ አልነበረምን? ጥቂት ጊዜ ካለፈ በኋላ ኢየሱስ እንደማይመጣ ለመጥምቁ ግልጽ ሆነ — እንዲያውም ለታሰረው ዘመዱ «በቶሎ ውጣ» የሚል የመልካም ምኞት ካርድ እንኳ አልላከም! ዮሐንስ ከራሱ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹን ጠርቶ ኢየሱስን እንዲፈልጉት፣ ሲያገኙትም ይህን ጥያቄ እንዲጠይቁት አዘዛቸው፦ «በእርግጥ መሲሑ አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?»

ዮሐንስ በኢየሱስ ግድ የለሽነት መስሎ በታየው ነገር በእውነት ተበሳጭቶ መሆን አለበት፤ ኢየሱስ መሲሕ እንደ ሆነ ከዮሐንስ ራሱ ይበልጥ እርግጠኛ ሊሆን የሚችል ማንም አልነበረምና። ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ ርግቢቱን አይቶ ነበር፤ እርሱንም እንዲህ ብሎ የሚያውጀውን ድምፅ ሰምቶ ነበር። ኢየሱስ ለዮሐንስ የላከውን መልስ አስተውል።

«ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ፥ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤

…በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው!»

በሌላ አነጋገር፦ «ልሠራው የተጠራሁትን፣ የታጠቅሁትንና የተቀባሁትን በትክክል እየሠራሁ ነው!»

ኢየሱስ አገልግሎቱን ለመፈጸም መቀባት ካስፈለገው፣ እኛማ እንዴት አብልጦ አያስፈልገንም?

ከልደቱ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ነበረ፤ ሆኖም አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት የመንፈስ ቅባት አስፈለገው!

በእነዚህ ሁለት የመንፈስ ቅዱስ ተሞክሮዎች መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፤ ይህን ሳንረዳ መቅረታችንም የክርስቶስን አካል አገልግሎት አዳክሞታል።

ዳግመኛ በተወለድን ጊዜ «በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል»። ይህ በመጀመሪያ የሆነው ከቀራንዮ ከሦስት ቀን በኋላ ነበር፤ ያን ጊዜ ኢየሱስ በተቆለፈ ክፍል ውስጥ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ እፍ አለባቸውና «መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ!» አላቸው (በግሪኩ ቋንቋ ይህ ወዲያውኑ እንዲፈጸም የሚጠይቅ የአኦሪስት ትእዛዝ አንቀጽ ነው)። እኔ ከሁለት ሺህ ዓመት ገደማ በኋላ በአሥራ ሰባት ዓመቴ ያው መንፈስ ቅዱስ ወደ ሕይወቴ በገባ ጊዜ እንደ ተወለድሁ እነርሱም «ዳግመኛ ተወለዱ»። መጽደቅ የምንለው ይህ ነው።

ዮሐንስ ከእርሱ በኋላ ስለሚመጣውና «በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል» ስለሚለው ለሕዝቡ ነገራቸው። ይህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን «ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ» ብሎ ሲያዝዛቸው ያመለከተው «አባቴ የሰጠውን ተስፋ» ነበረ። ይህ በመጀመሪያ የሆነው ከቀራንዮ ከሰባት ሳምንት በኋላ በበዓለ ሃምሳ ቀን ነበር፤ ያን ጊዜ የከበረው ኢየሱስ በሰገነቱ ላይ የተሰበሰቡትን መቶ ሃያዎቹን በመንፈስ ቅዱስ ባጠመቃቸው ጊዜ በታላቅ ኃይል ተሞሉ። ይህ ጥምቀት ኢየሱስ ወደ መንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀን ጥምቀት ነው። መጻሕፍት ስለ ሁለት የተለያዩ ተሞክሮዎች እየተናገሩ እንደ ሆነ ግልጽ ነው።

እያንዳንዱ አማኝ በመንፈስ እንዲሞላ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ይህ ከመለወጥ በኋላ የሚመጣ፣ በአንድ ወሳኝ ቅጽበት የሚሆንም የሚቀጥልም ተሞክሮ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን 5:18 ላይ «ዘወትር መንፈስ ይሙላባችሁ» ብሎ ይመክረናል። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት (የመጀመሪያው መሞላት) የጌታ ሉዓላዊ ሥራ ቢሆንም፣ የቀጣዩ መሞላት ኃላፊነት ግን የእኛ እንደ ሆነ ግልጽ ነው። ልናደርገው የምንችለው አንድ ነገር አለ።

ጳውሎስ በመቀጠል በመንፈስ የተሞላ ሕይወት ሦስት ማስረጃዎችን ይዘረዝራል፦ ቁጥር 19፦ የአምልኮ ዝንባሌ፤ ቁጥር 20፦ የምስጋና ዝንባሌ፤ ቁጥር 21፦ የአገልጋይነት ዝንባሌ።

የቀረው የምዕራፍ 5 ክፍልና አብዛኛው ምዕራፍ 6 ይህን በመንፈስ የተሞላ ሕይወት ከትዳር አጋሮቻችን፣ ከልጆቻችንና ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር ባለን ግንኙነት እንዴት እንደምንኖረው የሚያሳዩ ምሳሌዎች ናቸው።

የሚያሳዝነው፣ ይህን በመንፈስ ቅዱስ መሞላት (ወይም ጥምቀት) ከመንፈስ ቅባት ጋር አምታተነዋል። የመጀመሪያው መሞላት ነው — በውስጥህ፤ ሁለተኛው ኃይል መልበስ ነው — በላይህ። የመጀመሪያው ለአገልግሎት ዝግጅት የሚሆን ማስታጠቅ ነው፤ ሁለተኛው ወደ አገልግሎት ከተለቀቁ በኋላ ይመጣል። የመጀመሪያው አሁን በዝንባሌዎቻችንና በግልጽነታችን ላይ የተመሠረተ ነው፤ ሁለተኛው አሁንም የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ሥራ ነው።

በዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ሐዋርያና ነቢይ ያሉትን የአዲስ ኪዳን ዘመን የአገልግሎት ስጦታዎች እንደ ገና የማወቅ እንቅስቃሴ አለ። ሰዎችን ወንጌላውያን፣ እረኞች ወይም አስተማሪዎች ብለን ለመጥራት አልተቸገርንም፤ በኤፌሶን 4 የተጠቀሱት እነዚህ ሌሎቹ ሁለቱ ግን የበለጠ አሳስበውናል። እነዚህ አገልግሎቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መገኘትና በቅባታቸው መታየት እንዳለባቸው አምናለሁ።

የሚያሳዝነው ግን፣ አንድ ተናጋሪ የመድረክ ጊዜውን በጉባኤው ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን ለይቶ ስለ ወደፊታቸው በአደባባይ ትንቢት በመናገር ሲደመድም ብዙ ጊዜ ተገኝቻለሁ። ከእነዚህ ብዙዎቹ ፈጽሞ አልተፈጸሙም፤ ስለ ተሳሳተ ንግግሩም ነቢዩን ተጠያቂ ያደረገው ማንም የለም። ፓስተር እንደ መሆኔ የሌላ ሰውን የትንቢት ምክር ተከትለው በመሥራታቸው በግለሰቦች ሕይወት ላይ የደረሱ በርካታ አሳዛኝ ሁኔታዎችን ማስተናገድ ነበረብኝ። በብሉይ ኪዳን ዘመን የነቢዩ ቃል እውነት ካልሆነ ይገደል ነበር! የሚናገረው የእግዚአብሔር ቅባት እንዳለበት ሲያውቅ ብቻ ነበር!

በዚህ አጋጣሚ ለአገልግሎት አንዲትን ከተማ ጎብኝቶ፣ በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ሊወርድ ስለ ተቃረበ ታላቅ የእግዚአብሔር መንፈስ መፍሰስ ጠንካራ ቃል ትቶ የሄደውን ወንድም ማመስገን አለብኝ። «እዚህ ፓስተር ብሆን ኖሮ» አለ፤ «በሚመጡት ወራት ወደ ቤተ ክርስቲያኔ ለሚመጡት ብዙ ሰዎች ዝግጁ እሆን ዘንድ የእረፍት ጊዜዬን እሰርዝ ነበር።»

አንዳንድ ፓስተሮች ልክ እንዲሁ አደረጉ፤ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ብቻቸውን ለእረፍት እንዲሄዱ ተዉአቸው።

ሆኖም ዓመቱ ወደ መገባደጃው ሲቃረብ ምንም ልዩ ነገር እንዳልሆነ ግልጽ ነበር፤ ስለዚህ የአካባቢው ፓስተሮች ተወካዮች የእግዚአብሔርን በረከት ከከተማቸው ያራቀ አንዳች ነገር አድርገው እንደ ሆነ ለነቢዩ በትሕትና የሚጠይቅ ደብዳቤ ላኩለት። መልሱ ትሕትናን የሚያስተምር ነበር፤ «ነገሩን እንዳበላሸው» አምኖ፣ በዚህም ምክንያት ሌሎች የትንቢት ስብሰባዎቹን ለበርካታ ወራት እንደ ሰረዘና ራሱን ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ መሪዎች ተግሣጽ በታች እንዳደረገ ገለጸ። ይቅርታቸውንም ለመነ።

ስለ ትንቢት ከሰማሁት ምክር ሁሉ የሚበልጠው ከዩዝ ዊዝ ኤ ሚሽን ከፍሎይድ ማክለንግ የሰማሁት ነው።

እንዲህ አለ፦ «ማንም የትንቢት ቃል ቢሰጥህ፣ በቁም ሳጥንህ ታችኛው መሳቢያ ውስጥ አኑረውና መሳቢያውን ቆልፈው። የተሰጠህ ለወደፊት ማበረታቻ እንዲሆንህ እንጂ ለአሁኑ ጊዜ አቅጣጫ እንዲሆንህ አይደለም።» ቀጥሎም ትንቢቱ ከእግዚአብሔር ከሆነ ማረጋገጫ በሚያስፈልግህ ሁኔታ ውስጥ የምትገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ አብራራ። ያን ጊዜ ይህ እንደሚሆን የነገረህን ትንቢት ታስታውሳለህ፤ በዚህም እግዚአብሔር ወደዚህ እንደ መራህ ይበልጥ ትተማመናለህ።

የትንቢቱ መፈጸም ብቻ ነው የቅባቱ ማስረጃ።

ሰዎች ቅባት አለን ለማለት ይቸኩላሉ፤ የቅባት ማጣት የሚያስከትለውን ዋጋ ግን አያስቡም። የብሉይ ኪዳን ሐሰተኛ ነቢያት ይገደሉ ከነበረ ጌታ የአዲስ ኪዳንን ሐሰተኛ ነቢያት እንዴት እንደሚመለከታቸው ሰው ያስባል። ከምርጡ በረከቱ ምን ያህሉን ያጣሉ?

ስለ አስተማሪዎችም ተመሳሳይ ስጋት ሊገለጽ ይችላል። ጳውሎስ የጥንቲቱን ቤተ ክርስቲያን ስለ «ሐሰተኛ» አስተማሪዎች፣ እንዲሁም ሰዎች እንዴት እንደሚሆኑ ዘወትር ያስጠነቅቅ ነበር፦ «ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።»

በላቲን አሜሪካ ለተወሰነ ጊዜ ቆይቻለሁ፤ በዚያ አንዳንድ የሰሜን አሜሪካ አስተማሪዎች እጅግ ተወዳጅ ናቸው፤ ብዙ መጻሕፍቶቻቸውና ቪዲዮዎቻቸው ወደ ስፓንኛና ወደ ፖርቱጋልኛ ተተርጉመዋል። ከላቲን አሜሪካውያን ወዳጆቼ ጋር ቪዲዮዎችን ተመልክቻለሁ፤ በዚያም አስተማሪው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የሌላቸውን ሥልጣናዊ ንግግሮች ተናግሯል። አምስት ነገሮችን ይናገራል፤ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትክክለኛነት አላቸው፤ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ግን የራሱ ምናብ ውጤቶች ናቸው።

አድማጮቹ ግን አምስቱንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደ ሆኑ አድርገው ይቀበላሉ፤ በግል ጥናትና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሁርነት ልምድ የሌላቸው ብዙ ፓስተሮችም ይህን ትምህርት የአስተምህሮአቸው መሠረት አድርገው እየተቀበሉት ነው። ፓስተርን ተጽዕኖ ብታደርግበት ቤተ ክርስቲያንን ተጽዕኖ ታደርጋለህ — ለበጎም ሆነ ለክፉ።

ሽማግሌን ከዲያቆን የሚለየው ባሕርይ እርሱ «ለማስተማር የሚበቃ» (ቃሉን ለመተግበር ብቁና ፈጣን) መሆኑ እንደ ሆነ ቀደም ብዬ ጽፌአለሁ። በሚገባ የሚያስተምር ሽማግሌ «እጥፍ ክብር» እንደሚገባው ሊቆጠር ይገባዋል። አገልግሎቱ እጅግ ጠቃሚ ተደርጎ ስለሚቆጠር ቤተ ክርስቲያን «በእጥፍ ክብር» ከሌሎቹ ሁሉ በላይ ታስቀምጠዋለች። ለምን?

ጥያቄውን ከመመለሳችን በፊት ደግሞ ይህን እንጨምር፦ በአገልግሎታቸው የሚወድቁ ሽማግሌዎች (እረኞችና አስተማሪዎች) በቤተ ክርስቲያን ሁሉ ፊት ሊገሠጹ ይገባል! እጥፍ ክብር፣ እጥፍ ተጠያቂነት። ይህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሌላ በየትኛውም ቦታ ላይ አይሠራም!

ወደ ጥያቄው እንመለስ። ነቢዩ ወይም ወንጌላዊው ወይም ሌላ ማንም ሳይሆን አስተማሪ እጥፍ ክብር የሚቀበለው ለምንድን ነው?

ምክንያቱ በሚከተሉት ምሳሌዎች ሊብራራ እንደሚችል ልጠቁም።

ወንጌላዊ ሥራውን በሚገባ ቢሠራ ብዙ አዳዲስ አማኞችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመጣል። ሥራውን በደካማ ሁኔታ ቢሠራ ምንም አዲስ አማኝ በቤተ ክርስቲያን ላይ አይጨምርም። ውጤቱ ዜሮ ወይም ብዙ ነው፤ የሚደመርም ነው።

አስተማሪ ሥራውን በሚገባ ቢሠራ ራሳቸውን የሚያበዙ ብዙ ደቀ መዛሙርትን ያፈራል። ሥራውን በደካማ ሁኔታ ቢሠራም እንዲሁ ብዙ ደቀ መዛሙርትን ያፈራል — ራሳቸውን የሚያበዙ መጥፎ ደቀ መዛሙርትን። ውጤቱ ብዙ አዎንታዊ ወይም ብዙ አሉታዊ ነው፤ ሁለቱም የመብዛት አቅም አላቸው።

«እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን … ሦስተኛም አስተማሪዎችን … አድርጎአል» ብሎ ጳውሎስ ጻፈ። ቀጥሎም «ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን?» ብሎ ጠየቀ። የተሰወረውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት ለማስተማር በመንፈስ የተቀቡ አስተማሪዎች ያስፈልጉናል። ከጌታ የተቀበልኸውን ግልጽ ሸክምና ስጦታ አውቀው ሌሎች ወደዚያ አገልግሎት ካልለቀቁህ በቀር፣ እንደ ፓስተር፣ አስተማሪ ወይም ነቢይ ካሉት የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ጥሪዎች አንዱንም ለራስህ አትውሰድ። ቅባት በሌለበት ቅባት አለኝ ማለት አደገኛ ነገር ነው። ያ እምነት አይደለም — ትምክህት ነው፤ ኃጢአትም ነው።

ዛሬ ተስፋ በቆረጡ አማኞች ዘንድ የቤት አብያተ ክርስቲያናትን የመጀመር እንቅስቃሴ አለ። የቤተ እምነት ቤተ ክርስቲያናቸው የሥልጣን ተዋረድ መዋቅር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነና ተቆጣጣሪ እንደ ሆነ አምነው ሰልችቷቸዋል። የሚያሳዝነው፣ ሥልጣን ወዳድና ተቆጣጣሪ «መሪዎች» ወደ ላይ ሲወጡ ከእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት እጅግ ብዙዎቹ ልክ እንደ ቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን በዚያው ቅርጽ ይጠናቀቃሉ። ከእኛ ይልቅ ደካማ ወይም ብቃት የሌላቸው አድርገን የምንቆጥራቸውን መቆጣጠር የሰው ተፈጥሮ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ በታናሽ እስያ የቤት አብያተ ክርስቲያናትን በተከለ ጊዜ እነዚህን ገና ጀማሪ ጉባኤዎች እንዲጠብቁ ሽማግሌዎችን ሾመ። ያ ከእግዚአብሔር የተሰጠ አገልግሎት ነው። የመሪው ሥልጣን ያለው በማዕረጉ ሳይሆን እንደ ሽማግሌ በተቀባው ቅባት ውስጥ ነው።

በቲቶና በ1ኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ የተቀመጡትን የሽማግሌን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መስፈርቶች በእውነት ሲያሟላ፣ ያቺ የቤት ቤተ ክርስቲያን በጌታ ቅባት ሥር ለማደግ ታላቅ አቅም ይኖራታል።

ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

ኢቫንስ «የዕርቅ ጉዞን» የተቀባ አገልግሎት ምሳሌ አድርጎ የሚጠቅሰው ለምንድን ነው?

አማኞች የመስቀል ጦረኞች የሄዱበትን መንገድ ዳግመኛ በመከተል በመስቀል ዓርማ ሥር ለተፈጸሙት በደሎች ለሙስሊም መሪዎች የጽሑፍ ይቅርታ አቀረቡ። ኢማሞቹ በመደነቅና በመቀበል ምላሽ ሰጡ፤ አንዳንዶቹ ከአስተርእዮ ጋር አመሳሰሉት፤ የተሳተፉት ሰዎችም እግዚአብሔር ሲሠራ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆነው ቆዩ።

እግዚአብሔር ጂምንና ካቲን ፓስተራቸውን ስለ ለቀቁት እንዴት ባረካቸው?

የተቀባውን ፓስተራቸውን ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ መልሰው ለመላክ ገንዘብ ማጠራቀም ከጀመሩ በኋላ የጂም የሥራ ገቢ በአንድ ዓመት ውስጥ አሥር እጥፍ ሆነ፤ ከዚያም በኋላ በየዓመቱ እጥፍ መሆኑን ቀጠለ። ሆኖም በዚያው ቤትና በዚያችው ትንሽ መኪና ቀጠሉ፤ በአራት ዓመታት ውስጥም እያንዳንዱን የቤተ ክርስቲያናቸውን አባል ወደ ሚስዮን መስክ ላኩ።

ኢቫንስ በመንፈስ መሞላትን ከመንፈስ ቅባት እንዴት ይለየዋል?

መሞላት በውስጥህ ነው፤ ቅባት ግን በላይህ የሚያርፍ ኃይል መልበስ ነው። መሞላት ለአገልግሎት ዝግጅት የሚሆን ማስታጠቅ ነው፤ ቅባት ግን ወደ አገልግሎት ከተለቀቁ በኋላ ይመጣል፤ መሞላት አሁን በዝንባሌዎቻችንና በግልጽነታችን ላይ የተመሠረተ ሲሆን ቅባት ግን አሁንም የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ሥራ ነው።

ኢቫንስ ከፍሎይድ ማክለንግ ያገኘውን ስለ ትንቢት የሚያስተላልፈው ምክር ምንድን ነው?

ማንኛውንም የትንቢት ቃል በታችኛው መሳቢያ ውስጥ አኑረህ መሳቢያውን ቆልፈው፤ የተሰጠህ ለአሁኑ ጊዜ አቅጣጫ ሳይሆን ለወደፊት ማበረታቻ ነውና። ከእግዚአብሔር ከሆነ የምታስታውሰውና እግዚአብሔር ወደዚያ እንደ መራህ የምትተማመንበት ጊዜ ይመጣል፤ የትንቢቱ መፈጸም ብቻ ነው የቅባቱ ማስረጃ።

ኢቫንስ አስተማሪዎች «እጥፍ ክብር» እንደሚሰጣቸውና እጥፍ ተጠያቂነትም እንዳለባቸው የሚያምነው ለምንድን ነው?

የወንጌላዊ ሥራ የሚደመር ነው፦ በደካማ ሁኔታ ቢሠራው ምንም ሰው አይጨምርም። የአስተማሪ ሥራ ግን በሁለቱም መንገድ ይበዛል፤ ደካማ አስተማሪም ደቀ መዛሙርትን ያፈራል — ራሳቸውን የሚያበዙ መጥፎ ደቀ መዛሙርትን። ስለዚህ በሚገባ የሚያስተምሩ ሽማግሌዎች እጥፍ ክብር ይቀበላሉ፤ የሚወድቁት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ሁሉ ፊት ይገሠጻሉ።

ምዕራፍ 9 ተጠናቋል

ቅባት

ገጽ 1 / 1 · 12 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ