ምዕራፍ 10 · 13 ደቂቃ ንባብ · 16 ደቂቃ ማዳመጥ
መብረር
እግዚአብሔር በአንድ ሰው አገልግሎት ላይ ቅባቱን ሲያኖር ያ ሰው — ወንድም ይሁን ሴት — «እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ» የሚለው ምን ማለት እንደ ሆነ ይለማመዳል። ሌሎች ብዙ አማኞች ከሚኖሩት ተራ ሕይወት እጅግ ከፍ ብሎ እየተንሳፈፈ የመንፈስ ነፋሳት ወደ ላይ ሲሸከሙት ይሰማዋል። ቀንበሩ ልዝብ፣ ሸክሙም ቀሊል ይሆናል።
በቀደሙት ምዕራፎች ሕይወታቸውን የማወቅ መብት ስለ ተሰጠኝ ስለ አንዳንድ ሰዎች ብዙ ታሪኮችን ተርኬአለሁ። ከደስታቸው ጥቂት ተጋብቶብኛል፤ ከቅባታቸውም ጥቂት ተሰምቶኛል፤ አሁን ለራሴ አገልግሎት ከዚህ ባነሰ ነገር ልረካ አልችልም። ከጌታ ጋር ጥልቅ ጉዞን ከሚሹ የተራቡ ወጣት አማኞች ጋር ጊዜ ከማሳለፍ የበለጠ የሚያረካኝና የሚሞላኝ ምንም ነገር የለም። ብዙዎች ተሸክመውት ከሚዞሩት ጉዳትና ቁስል ነጻ ወደ ሆነ ጤናማ የክርስቲያን አኗኗር፣ በስጦታቸውም ወደ ማገልገል ልመራቸው ብችል «የማይነገርና ክብር የሞላበት» ደስታን አውቃለሁ! በዚያም ከጌታ ጋር በአንድ ቀንበር የመጠመድን ቅርበት እለማመዳለሁ፤ የምሸከመው የእርሱን ሸክም — ከእርሱ ጋር እንድሸከመው የሰጠኝን ሸክም — ነውና።
ስላገኘኋቸው ሌሎች ሰዎች ልንገርህ። ከስሞቹ አንዳንዶቹን ታውቃቸዋለህ፤ ሌሎቹ ለአንተ እንግዶች ናቸው፤ ለጌታ ግን አይደሉም።
ጃኪ ፑሊንገር
ጃኪን ከ1967 እስከ 1969 ባወቅኋት ጊዜ ሁለታችንም በሆንግ ኮንግ ወጣት መምህራን ነበርን።
የልጆች ስብሰባዎችን ስትመራ ሁለት ጊዜ ከእርሷ ጋር ወደ «የዘንዶው ዋሻ» (በክፋቱ ወደ ታወቀው ወደ ኮውሉን ቅጥር ከተማ) ገብቻለሁ። ቀላል ሁኔታ አልነበረም፤ ከእርሷ ጋር ወደዚያ ለመግባት የሚደፍሩ ሌሎች ሰዎችም ጥቂቶች ነበሩ።
በመንገዱ መሃል በሚፈሰው ፍሳሽ ውስጥ እንዳንረግጥ እጅግ እየተጠነቀቅን በጠባቦቹ መንገዶች እንሄድ ነበር። አንድ ጊዜ በሄሮይን «ሰክሮ» በፍሳሹ ውስጥ የተኛ ሰው አገኘን። ጃኪ ሰውየውን ከግድግዳው ጋር እንድታስደግፈው ረዳኋት፤ ከዚያም በንጹሕ የእጅ መሐረቧ ፊቱን ስታጥበው ተመለከትሁ።
በዚያን ጊዜ ጌታን ለማገልገል ከሚፈልጉ ከሌሎች ብዙ ወጣት ሴቶች የተለየች አድርጌ አልቆጠርኋትም ነበር። ከአብዛኞቹ ትንሽ የሚበልጥ ድፍረት — ወይም ሌሎች ብዙ ሚስዮናውያን እንዳሰቡት ሞኝነት — ሊኖራት ይችላል፤ ነገር ግን ጌታ የሚጠቀምበት ሌላ አንድ «ደካማ ነገር» እና «ሞኝ ነገር» ብቻ ነበረች። ብስጭቷን አየሁ፤ ወደ አዳኟ ልታስተዋውቃቸው የናፈቀቻቸው የብዙዎቹ ሰዎች «ተስፋ ቢስ» ሁኔታም ከእርሷ ጋር ጸለይሁ። ይህን መጽሐፍ የሚያነብ ወጣት ሴትም ሆነ ወንድ ጃኪ ፑሊንገር እንዳላት ያለ ዓለምን የመለወጥ ያው አቅም «በክርስቶስ» የሌለው የለም። ድሉን ያመጣው እርሷ ሳትሆን «በእርሷ ያለው ክርስቶስ» እንደ ሆነ ለመመስከር እርሷ ፈጣን ናት።
ከብዙ ዓመታት በኋላ «ዘንዶውን ማሳደድ» የተባለውን የጃኪን መጽሐፍ ሳነብ፣ በዚያ በሚኖሩት ሱሰኞችና የወሮበላ ቡድን መሪዎች አስገድዶ የመድፈርና የሞት ዛቻ በተሰነዘረባት ጊዜ እንኳ በዚያ ክፉ ስፍራ ፈጽሞ ፍርሃት እንዳልተሰማት መናገሯን አስተዋልሁ።
ይህ ለእርሷ እንግዳ፣ ለሌሎች ደግሞ ሊገባቸው የማይችል ነገር ነበር፤ ነገር ግን በአገልግሎቷ ላይ ለነበረው የእግዚአብሔር ቅባት እርግጠኛ ማስረጃ ነበር — ይህም አሁን የክርስቲያኑ ዓለም ሁሉ የሚያውቀው እውነታ ነው።
ሻለቃ ኤ. ኤስ.
ሻለቃ ኤስ. ከታላላቅ ሰባኪዎቹ ይልቅ በሰብአዊ ሥራው በሚታወቀው በድኅነት ሠራዊት ውስጥ ያገለግል ነበር። ይሁን እንጂ ከዩኒቨርሲቲ በምመረቅበት ዓመት ለአንድ ሳምንት ስብሰባዎች በአካባቢው ወዳለው የሠራዊቱ ማዕከል (ሲታዴል) ወደ ከተማችን መጣ። ከመጀመሪያው ምሽት በኋላ ማዕከሉ ለተሰብሳቢዎቹ ብዛት በጣም ስላነሰ ስብሰባዎቹ ወደ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ተዛወሩ። ከድኅነት ሠራዊት ውጭ ያሉት አብዛኞቹ ባያውቁትም፣ የታላቅ ቅባት ወሬ ከአፍ ወደ አፍ ተዛመተ፤ ብዙም ሳይቆይ እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ ስብሰባዎቹ ይመጡ ጀመር። በሳምንቱ አጋማሽ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንም በጣም ጠበበች፤ ስፍራውም እንደ ገና መቀየር ነበረበት!
ለመጨረሻ ፈተናዎቼ እያጠናሁ ስለ ነበር በብዙዎቹ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አልቻልሁም። ይሁን እንጂ ሐሙስ ምሽት ተገኝቼ ነበር፤ በዚያም ሻለቃ ኤስ. ንግግሩን አቁሞ ሰዓቱን ተመለከተ፤ ለሁለተኛ ጊዜም ረጅም ጊዜ ካየው በኋላ እንዲህ አለ፦ «በጣም አዝናለሁ! ጊዜዬ ቀድሞ ማለቁን ፈጽሞ አላወቅሁም ነበር። እስከዚህ ሰዓት ድረስ እዚህ ስላቆየኋችሁ እባካችሁ ይቅር በሉኝ። ብዙዎቻችሁ የምትደርሱበት አውቶቡስ እንዳላችሁ አውቃለሁ፤ ስለዚህ አሁን እዘጋለሁ፤ ይህንም ርእስ ነገ ምሽት እቀጥላለሁ።» ማንም አልተንቀሳቀሰም፤ ከጉባኤው መካከል አንድ ሰው ተነሥቶ «ጌታዬ፣ እዚህ ትተኸን ልትሄድ አትችልም! በጌታ ፊት ነን። እባክህ ቀጥል» እስኪል ድረስ ጸጥታ ሆነ።
ሻለቃ ኤስ. መሄድ የሚገባቸው ሁሉ እንዲሄዱ ጋበዘ፤ ነገር ግን ማንም ስላልተንቀሳቀሰ ለተጨማሪ ግማሽ ሰዓት ያህል መናገሩን ቀጠለ። የመጨረሻዎቹ አውቶቡሶች ቀድመው ስለ ሄዱ በዚያ ምሽት ታክሲ የሚጠሩ ወይም ከወዳጆቻቸው ጋር በመኪና ወደ ቤታቸው የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩ።
ሰዎች «አዝናኝ» ስብከቶችን በሚፈልጉበትና ከአርባ ደቂቃ በላይ ቢሰብኩ ጉባኤያቸውን ይዘው መቆየት የሚችሉ ሰባኪዎች ጥቂቶች በሆኑበት በዚህ ዘመን፣ ሻለቃ ኤስ. ከዘጠና ደቂቃ በላይ ተመስጠን እንድንቆይ ያደረገን ምን ቢኖረው ነው ብለን እንጠይቅ ይሆናል። መልሱ ቅባት ነው።
ዶክተር ማርቲን ሎይድ-ጆንስ
በዚህ ታላቅ ሰባኪ አገልግሎት ሥር የመቀመጥ መብት ያገኘ ማንም ሰው በቅባቱ ሊጠራጠር አይችልም። በሳምንቱ አጋማሽ ምሽቶች፣ በአብዛኛው ከለንደን ዩኒቨርሲቲ ልዩ ልዩ ኮሌጆች ለመጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሮሜ መጽሐፍ ሲያስተምር ተመልክቼዋለሁ። በዌስትሚንስተር ቻፕል ከፍ ባለው መድረኩ ላይ ቆሞ ቃሉን ሲናገር አድማጮቹ ወደ አምስት ሺህ ገደማ ይገመቱ ነበር። ዛሬ በትንንሾቹ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎች እንኳ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የድምፅ ማጉያ ይጠቀም እንደ ነበር እርግጠኛ አይደለሁም፤ ነገር ግን እንዲህ ያለ የሚያስተጋባ ድምፅ ስለ ነበረው አስፈላጊ እንደ ነበረ እጠራጠራለሁ። የሰውነት እንቅስቃሴው ጥቂት ነበር፤ በአለባበሱም ሆነ በአቀራረቡ የሚያብረቀርቅ ነገር አልነበረውም፤ የግል ማራኪነቱ (ካሪዝማው) ጥቂት ነበር፤ የጸጋ ስጦታዎቹ (ካሪስማታ) ግን ያለ ጥርጥር ነበሩ — ቅባቱም እንዲሁ።
ዋይ. አር.
ዋይ. ክፉኛ ይንተባተብ ስለ ነበር ከእርሱ ጋር መነጋገር የማይቻል ነበር። በወጣትነቱ በስርቆት ተከሶ ከሌሎች የወሮበላ ቡድኑ አባላት ጋር የፍርድ ቀኑን ይጠባበቅ በነበረ ጊዜ ሕይወቱን ለጌታ ሰጠ።
ባልደረቦቹ ሁሉ ወደ ታዳጊ ወንጀለኞች ማቆያ ተላኩ፤ ዋይ. ግን የቡድኑ መሪ ቢሆንም በአካባቢው ባለ አንድ ፓስተር ጥበቃ ሥር እንዲሆን ተለቀቀ። ያ ጥበበኛ ዳኛ የባከነን ሕይወት ለማቅናት በእስር ቤት ከሚያልፉ ዓመታት ይልቅ እግዚአብሔር እጅግ የሚበልጥ ችሎታ እንዳለው ያውቅ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ — በዚያ ጊዜ ውስጥ እርሱና እኔ የቅርብ ወዳጆች ሆነን ነበር — አንድ ቀን ዋይ. ጌታ ያደረገለትን ለሁሉም ይነግር ዘንድ በትውልድ ከተማው ስብሰባ እንዳዘጋጅለት ፈለገ።
በሚንተባተበው አንደበቱ ምክንያት ሐሳቡን ላስቀይረው ብሞክርም አጥብቆ ጠየቀ፤ ጌታ ያንን ደካማ ዕቃ ወስዶ በእርሱ አማካይነት በግልጽነት ሲናገርና አገልግሎቱን ሲቀባ በአድናቆት ወደ ኋላ ቆሜ መመልከት ነበረብኝ። ምሥጢሩን ብዙም ሳይቆይ ተረዳሁ፤ ሁልጊዜ ማታ ማለት ይቻላል ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ መብራትና መጽሐፍ ቅዱስ ወዳለበት በአትክልት ቦታው ወዳለች ትንሽ ጎጆ ገለል ይል ነበርና። ዋይ. ከፍተኛ ትምህርት ባይማርም በኢየሱስ እግር ሥር ተማሪ ሆነ። በምእመናን ሰባኪዎች ዙር ላይ መደበኛ ተናጋሪ ሆነ፤ የተቀባ ስብከቱንም ለመስማት ብዙ ሕዝብ ይወጣ ነበር። ለማገልገል ሁለት ጊዜ ወደ ካናዳ ተጉዟል፤ በዚያና በታላቋ ብሪታንያም ፓስተር እንዲሆን የቀረቡለትን ግብዣዎች ላለመቀበል ተገድዷል።
ኤ. ጄ.
ኤ. በመምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሳለች የሥራው ሁሉ ጫናና የቅርብ ወዳጆች ማጣቷ ራሷን ለማጥፋት እንድታስብ ገፋፋት። አንድ ቀን በባሕሩ ዳርቻ ስትሄድ አንድ ወረቀት በአሸዋው ላይ በነፋስ ሲበር አየች። የወንጌል በራሪ ጽሑፍ ነበር፤ ስታነበውም የጌታ መንፈስ በነፍሷ ላይ ሠራ፤ በዚያው በባሕሩ ዳርቻ ተንበርክካ እያለቀሰች ጌታ እንዲያድናት ለመነች። ወደ ቤተ ክርስቲያናችን መምጣት ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ በእሑድ አገልግሎት ላይ አንድ ግጥም ማቅረብ ትችል እንደ ሆነ ጠየቀች።
ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ የተለመደ ነገር ስላልነበረ ፓስተሩ ትንሽ እያመነታ ተስማማ፤ እኛ ግን እሺ በማለቱ እጅግ አመስጋኞች ነን። ኤ. በተቀቡ ቃሎቿ አማካይነት ከጌታ ጋር ወደ አዲስ ተሞክሮ ስታስገባን ልብ ሁሉ ተነካ፤ በየፊቱም ላይ ሞቅ ያለ የደስታ እንባ ነበረ። እኔም ግጥም ማቅረብ እወዳለሁ፤ ነገር ግን ሰዎችን እንደዚያ ልነካ ፈጽሞ አልችልም! ኤ. በዚያ ቅባት የምታገለግልበትን እያንዳንዱን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቅ ነበር።
ኤች. ደብሊው.
ኤች. ወደ ጌታ የመጣው በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለ ነበር፤ ይህም አንድን ሰው የገደለ መስሎት በነበረበት የጎዳና ድብድብ ውስጥ ከተሳተፈ በኋላ ነበር። ደግነቱ ስጋቱ መሠረት አልነበረውም፤ ነገር ግን በፍርሃቱ ውስጥ በማግሥቱ ጠዋት ወደ ቤተ ክርስቲያናችን መጣ፤ ወንጌልን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰማ፤ ራሱንም ለጌታ አሳልፎ ሰጠ። ስለ አስተምህሮዎች ወይም ስለ ቤተ እምነቶች ምንም እውቀት ስላልነበረው የተከፈተ በር ባየበት ሁሉ ከአንዱ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላው እየሄደ እየተካሄደ ባለው በማንኛውም ስብሰባ ላይ ይቀላቀል ነበር። የጸሎት ስብሰባ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ቆሞ ይጸልይ ነበር። እንደ ትቢያ በደረቁ ብዙ ስብሰባዎች ውስጥ ኤች. ለመጸለይ እስኪቆም ድረስ ተቀምጬአለሁ። ያን ጊዜ ሰማያት ተከፈቱ፤ እግዚአብሔርም መገኘቱን በመካከላችን አሳወቀ። በዚህ ቀላል ሰው ጸሎቶች ላይ በራሴ ጸሎቶች ላይ ፈጽሞ የማላውቀው ቅባት ነበረ፤ በጥቂት ቃላት ብቻ ሰማይን ማንቀሳቀስ ይችል ነበርና።
ሲ. ማክ.
በምስጋናና በአምልኮ ቡድኑ የሚመራውን ዝማሬ እያዳመጥሁ በብዙ ስብሰባዎች ውስጥ ተቀምጬአለሁ። መቼ ማጨብጨብ፣ መቼ መቀመጥ ወይም መቆም እንዳለብኝ ታዘዝሁ፤ ድምፄን ከፍ አድርጌ እንድዘምር ወይም መቼ መሣሪያዎቹን ብቻ እንዳዳምጥ ተነገረኝ። ቃሎቹን በማውቅበት ጊዜ አንዳንድ ጊዜ መቀላቀል ችያለሁ፤ ነገር ግን ይህ እየቀነሰና እየቀነሰ መምጣቱን እመሰክራለሁ።
የምስጋናና የአምልኮ ጊዜ ማለት አብሮ ከመዘመር ብዙም የማይበልጥ ሆነ፤ በዚህም ውስጥ አምላኪዎች የሆኑት በግላቸው ሊያመልኩ ይችላሉ (ብዙ ጊዜ የሚከባቸውን ጩኸት ማግለል ከቻሉ!)
ሲ. ግን በፒያኖው ፊት ተቀምጦ ወደ አምልኮ ሲመራን ወደ ጌታ መገኘት ያስገባን ስለ ነበር ቃሎቹን ሁሉ ማወቅ አስፈላጊ አልነበረም፤ እኛም «በአድናቆት፣ በፍቅርና በምስጋና ተዋጥን»። እርሱ አመለከ፤ እኛም አመለክን። መዝሙሮችን የመረጠው በሙዚቃ ስልታቸው፣ በቅኝታቸው ወይም በምታቸው ሳይሆን ወደ ኢየሱስ ስለሚያመለክቱን ነበር። የምስክርነትን ወይም የመንፈሳዊ ውጊያን መዝሙሮች ከስግደት መዝሙሮች ጋር እያፈራረቀ፣ በአግድሞሹ (እርስ በርስ በመዘማመር) እና በቁመቱ (ጌታን በማነጋገር) መካከል እየተመላለሰ እንደ ዮ-ዮ አላጫወተንም። አምልኮን የመምራት አገልግሎቱ የተቀባ ነበር፤ በዚያ የነበሩትም ሁሉ ያውቁት ነበር።
እኔ የምናገር ከሆንሁ ብዙውን ጊዜ የምናገረው በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ነበር፤ ይህም በመጨረሻ ወደ አምልኮ እንድንመጣና ጊዜው እንደ ደረሰ እስኪሰማው ድረስ ማንም መሄድ እንዳያስፈልገው ነበር። በብዙ ስብሰባዎች ሌሎች ከሄዱ ከብዙ ጊዜ በኋላ በመለኮታዊው መገኘት ውስጥ መቆየት የሚያስፈልጋቸው በርካታ ሰዎች ይቀሩ ነበር። በእርሱ የተቀባ አምልኮና በሌላ ስፍራ ብዙ ጊዜ ባየሁት መካከል ያለው ልዩነት ጌታ አሁንም «በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት» የሚችሉትን እየፈለገ እንደ ሆነ እንዳምን ያደርገኛል።
ሲ. ኤን.
የቤተ ክርስቲያን ፓስተር ሆኜ በመጀመሪያው ዓመቴ ነበርሁ፤ በየሳምንቱ ለሕዝቤ ጥሩ መንፈሳዊ ምግብ ለማዘጋጀት እጓጓ ነበር። ከብዙ ሳምንታት አስቀድሞ ሊገመት በሚችል የማስተማር ልማድ ውስጥ መታሰር አልፈለግሁም፤ ይልቁንም ለእያንዳንዱ ስብከት አዲስ ነገር ከጌታ እፈልግ ነበር።
ስለዚህ በየረቡዑ የቢሮዬን በር ቆልፌ፣ የስልኩን ገመድ ነቅዬ፣ ጌታ ለሕዝቤ ያለውን እየፈለግሁ ቃሉን በማጥናት ጊዜ አሳልፍ ነበር።
ሽማግሌዎቹ ከአገልግሎቱ አንድ ሰዓቱን ለቃሉ ትምህርት መድበው ስለ ነበር በየእሑዱ ስብከት ውስጥ ጥቂት «ጠንካራ ምግብ» ይጠብቁ ነበር። ብዙ ጊዜ ቃሉ እንዳለኝ በመተማመን ወደ መድረኩ ወጥቻለሁ፤ ነገር ግን የምሰጋባቸውም ብዙ ጊዜያት ነበሩ።
ከሽማግሌዎቹ አንዱ የሆነው ሲ. እንደ ልማዱ በአገልግሎቱ የመጀመሪያ ክፍል ቆሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያነብ ነበር። በዚያ ሳምንት ከጌታ መስማቴን እርግጠኛ ባልሆንሁበት ጊዜ ብዙውን ጊዜ፣ ሲ. የሚያነበውን ክፍል ያስታውቅና በዚያ ጠዋት የምሰብክበትን ጥቅስ አውድ ሲያነብ በመገረም ወደ ኋላ ተደግፌ እቀመጥ ነበር! በእርግጥ ከጌታ እንደ ሰማሁና ለዚያ ጠዋት መልእክቱ በእጄ እንዳለ ማወቄ ምን ያህል መተማመን እንደ ሰጠኝ መገመት ትችላለህ። ሲ. ርእሴን ወይም ጥቅሴን በየሳምንቱ የሚያውቅበት ምንም መንገድ አልነበረም፤ ነገር ግን ለዚያ ቀን ወደ መጻሕፍት የሚመራውን የጌታን ድምፅ ሰምቶ ነበር።
ቅባት ይህ ነው።
ኤ. ኤ.
ከ1991 እስከ 1994 በምሕረት መርከብ «አናስታሲስ» ላይ ፓስተር ሆኜ ሳገለግል ከአፍሪካዊው ወንድም ከኤ. ጋር አብሬ የመሥራት መብት አግኝቼ ነበር። የእርሱ ኃላፊነት በመርከቡ ላይ ያለው ውኃ ሁልጊዜ ለመጠጥ የሚሆንና በአፍሪካ ውኃዎች ውስጥ በብዛት በሚገኙ ባክቴሪያዎች ያልተበከለ መሆኑን ማረጋገጥ ነበር።
ማክሰኞ ምሽቶች ለወደፊቱ ሊኖር ለሚችል የእረኝነት አገልግሎት ራሳቸውን በማዘጋጀት ጊዜ ማሳለፍ ለሚፈልጉ ሰዎች አነስተኛ ክፍል አስተምር ነበር፤ ኤ. ደግሞ የቡድኑ ትጉ አባል ነበር። ሆኖም በተናገረ ቁጥር እርሱ መምህሩ እኔ ደግሞ ተማሪው የሆንሁ ያህል አዳምጠው ነበር፤ አስተያየቶቹ ራሱን በቃሉ ውስጥ ያጠለቀ ሰው ማስተዋል የበዛባቸው ነበሩና።
ወደ ምዕራብ አፍሪካ ካደረግናቸው የሚስዮን ጉዞዎች በአንዱ፣ ኤ. የምሕረት መርከቦች ባቋቋሙት የመስክ የጥርስ ሕክምና ክሊኒክ ሕዝቡን በሥርዓት እንዲያስተናግድ እንዲረዳ ተጠየቀ። ሥራውን በትጋት ሠራ፤ በጥርስ ሐኪሞቻችን ለመታየት ተራቸውን በትዕግሥት ለሚጠባበቁት ሙስሊሞችም ብዙ ጊዜ ወንጌልን ያቀርብ ነበር። የምዕራብ አፍሪካ ሙስሊሞች አክራሪዎች አይደሉም፤ አብዛኞቹም ስለ እስልምና መሠረተ እምነቶች እጅግ ጥቂት ግንዛቤ ብቻ አላቸው፤ ስለዚህ ሙስሊምም ይሁን ክርስቲያን ወይም ባዕድ አምላኪ ጠንቋይ ማንኛውንም ቅዱስ ሰው ያከብራሉ። አንድ ቀን ኤ. ሁለቱም ሽባ በሚያደርግ በሽታ ለተያዙ ሁለት ሽማግሌዎች እንዲጸልይ ተጠየቀ፤ እርሱም የሚጸልየው «በኢየሱስ ክርስቶስ ስም» ብቻ እንደ ሆነ አጥብቆ እየነገራቸው እንደ ጠየቁት አደረገ። ሁለቱም ወዲያውኑ ተፈወሱ፤ ፈውሳቸውም ከጌታ እንደ ሆነ ለመመስከር ፈጣኖች ነበሩ፤ በዚህም ምክንያት የዚያ መንደር አለቃ መንደሩ ከዚያ ቀን ጀምሮ «የኢየሱስ መንደር» እንደ ሆነ አወጀ። ይህ ለኤ. ያልተለመደ ክስተት አልነበረም፤ በአገልግሎቱ ላይ ያለውን የእግዚአብሔር ቅባት የሚያሳዩ ሌሎች በርካታ ተመሳሳይ ምሳሌዎችም ነበሩ።
አይ. እና ኤ.
ጌታ በማንኛውም «እውነተኛ» አገልግሎት ይጠቀምባቸዋል ብዬ ብዙም ሳልጠብቅ የአይ.ንና የኤ.ን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ፈጸምሁ።
በዓለማዊ ማዕረግ፣ በንብረት ወይም በጫና ያልተጨናነቀ ሕይወት መኖር የሚፈልጉ ቀላል ባልና ሚስት ነበሩ፤ ስለዚህ በባሕሩ ዳርቻ አቅራቢያ ወዳለው ቤታቸው ገለል ብለው ኖሩ። ለበርካታ ዓመታት እንደ ገና አላየኋቸውም፤ ስለ አኗኗራቸውም ብዙም አላውቅም ነበር፤ አንድ ወዳጄ ሊጠይቀኝ መጥቶ በቅርቡ ስላገኘው ድንቅ የምክርና የውስጥ ፈውስ አገልግሎት ይነግረኝ እስኪጀምር ድረስ።
በመለየት ስጦታቸውና በጥበብ ቃሎቻቸው እጅግ ስለ ረዱት፣ በሕይወቱ ውስጥ መለወጥ ያለባቸውን ነገሮችም በማመልከት ስለ ተገዳደሩት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ነገረኝ። እያዳመጣቸው ተደነቀ፤ ጌታ እየመራቸው እንደ ነበረም ተገነዘበ። የየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ወይም ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተባብሮ የሚሠራ አገልግሎት አካል ባይሆኑም ምክራቸውንና ጸሎታቸውን ከሚፈልጉ ሰዎች ከአገሪቱ ሁሉ የስልክ ጥሪዎች እንደሚደርሷቸው ነገረኝ።
እነዚህን አስደናቂ ባልና ሚስት የማግኘት ፍላጎቴን ገለጽሁ፤ ስማቸውን ሲነግረኝ ግን በጣም ደነገጥሁ። «በጭራሽ!» አልሁ፤ «ሰርጋቸውን የፈጸምሁት እኔ ነኝ፤ ጌታን በማገልገል ረገድ ይህን ያህል ታላቅ አቅም እንደ ነበራቸው ፈጽሞ አላሰብሁም ነበር!» ጌታ ግን አስቦት ነበር — ቅባቱም በእነርሱ ላይ ነው!
ኤም. ኤም.
ስለዚህ መጽሐፍ ርእስ ከአንድ ፓስተር ወዳጄ ጋር ስነጋገር የሚከተለውን ታሪክ ነገረኝ።
በካናዳ የሜዳማ ክፍለ ግዛቶች ውስጥ ባለች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግል ከምእመናኑ አንዱ እንደ ታመመ የሚገልጽ የስልክ ጥሪ ደረሰው። ወዲያውኑ የታመመውን ሰው ለመጠየቅ ሄደ፤ ጥቂት መጽናናትም ሊሰጠው ቻለ።
ከክፍሉ ሲወጣ ከአልጋው አጠገብ በአበባ ማስቀመጫ ውስጥ ስለ ቆመው ውብ ትንሽ የዱር አበባ እቅፍ አስተያየት ሰጠ። «ኤም. ዛሬ ከሰዓት በኋላ ቀደም ብላ ላከቻቸው» ተባለ።
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወዳጄ ሌላ ቤት ሄዶ የቀረበለትን ኬክ እየበላ ነበር። አስተናጋጇን ሲያመሰግናት «ኤም. ዛሬ ከሰዓት በኋላ አመጣችልኝ» ተባለ።
ከበርካታ ተመሳሳይ አጋጣሚዎች በኋላ ፓስተሩ የኤም. ስም ደጋግሞ መነሣቱ አስደነቀው። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በየትኛውም ስብሰባ በቀላሉ ሳትታይ ልትቀር የምትችል ያላገባች አረጋዊት ሴት ነበረች። ምንም አትናገርም ነበር፤ በጠባይዋም እጅግ ዓይናፋር ነበረች። ቤተሰቡ እርሱን ከማሳወቁ በፊት እንኳ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሰዎች መታመማቸውን እንዴት እንደምታውቅ ለማወቅ ኤም.ን ለመጠየቅ ወሰነ። መጀመሪያ ላይ ለታመሙት ስልክ በመደወል፣ በመጠየቅ ወይም አበባና ኬክ በመላክ ከልክ በላይ ስለ ደፈረች ፓስተሩ ሊገሥጻት እንደ መጣ አስባ ትንሽ ሰግታ ነበር፤ እርሱ ግን እንዲህ እንዳልሆነ ፈጥኖ አረጋገጠላት።
ኤም. በየምሽቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ላለው ለእያንዳንዱ ሰው በጸሎቷ ስማቸውን እየጠራች እንዴት እንደምትጸልይ ነገረችው። አንድ ጊዜ የአንድ አረጋዊ ሚስት የሞተባቸው ሰው ስም እንድትደውልላቸው ከሚገፋፋ ሐሳብ ጋር ደጋግሞ ወደ አእምሮዋ ይመጣ ነበር። እርግጥ ነው፣ ድርጊቷ ሊሳሳት ይችላል ብላ በማሰብ ለማድረግ አመነታች፤ ሐሳቡ ግን አልለቀቃትም። በመጨረሻም ብዙ ካዘገየችና ለበርካታ ሰዓታት ከተረበሸች በኋላ ስልኩን አንሥታ ደወለችላቸው። ስልኩ ሲገናኝ ሰውዬው በጭንቅ ውስጥ እንደ ነበሩና እጅግ ግራ የተጋቡ እንደሚመስሉ ግልጽ ነበር።
ወድቀው ተጎድተው ነበር፤ ነገር ግን በጭንቀታቸውና ግራ በመጋባታቸው ምን እንደሚያደርጉ ወይም ወደ የትኛው ስልክ ቁጥር እንደሚደውሉ አላወቁም ነበር። ኤም. የሚያበረታታቸውን ነገር ተናገረች፤ ከዚያም ሐኪሙን ጠራች፤ እርሱም ፈጥኖ ወደ ቤቱ ሄዶ አረጋዊውን መርዳት ቻለ። ያዘገየቻቸውን ረጅም ሰዓታት ተቆጨች፤ ከዚያ ወዲያ ጌታ በገፋፋት ቁጥር ጌታ ስለ ነገራት ሰው ሁሉ ወዲያውኑ በመደወል ወይም በመጠየቅ ምላሽ ለመስጠት ቆረጠች።
ፓስተር ወዳጄ ኤም. አገልግሎቷን በማግኘቷ እጅግ ተደሰተ፤ በብርቱም ደገፋት፤ ይህንም መልካም ሥራ እንድትቀጥል አበረታታት፤ አበባ ለመግዛት፣ ኬክ ለመጋገርና ለመሳሰሉት ለሚወጣ ማንኛውም ወጪ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሂሳብ ለመጠየቅ ፈጽሞ መፍራት እንደሌለባትም ነገራት።
አገልግሎቷን አግኝታ ነበር፤ ጌታም እየቀባው ነበር።
ኤስ. ቢ.
ኤስ. ከዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች በእስር ቤት ቆይቷል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ክርስቲያን የሆነ ቢሆንም ለጌታ አልኖረም ነበር፤ ለአልኮልና ለሲጋራ ብቻ ሳይሆን ለከባድ ዕፆችም ሱሰኛ ነበር። ሕይወቱ ከሆነበት ምስቅልቅል መውጫው ብቸኛ መንገድ ራስን ማጥፋት እንደ ሆነ አስቦ ነበር። ከእስር ቤት ሲፈታ የአልኮል ሱሰኞች የመረዳጃ ማኅበር ስብሰባዎችን ይካፈል ጀመር፤ በዚያም ሕይወቱን እንደ ገና ለክርስቶስ ሰጠ። ከተለወጠ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ እግዚአብሔር ይህን ሰው ለወጠው፤ በሱሶቹም ሁሉ ላይ ድልን ሰጠው።
ከሱስ ነጻ ሆኖ ለመቆየት የሚረዳው ምርኩዝ እንደማያስፈልገው፣ ይልቁንም ጌታ ሙሉ በሙሉ እንደ ፈወሰው — ሥራው የተፈጸመ እንደ ሆነ — ለማመን ደረሰ። «በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን» በሚለው የቃሉ ተስፋ ላይ ተመሥርቶ ለሱሰኞች የመረዳጃ ቡድን የሆነ አዲስ ሥራ ጀመረ።
ይህን በምጽፍበት ጊዜ «ወደ ነጻነት የሚያገናኝ» (ኮኔክሽን ቱ ፍሪደም) የተባለው አገልግሎቱ በትውልድ ከተማዬ ባሉ ሱሰኞች፣ እስረኞችና ቀድሞ እስረኞች በነበሩ ሰዎች መካከል ትልቅ ተጽዕኖ ማድረግ እየጀመረ ነው፤ ሰፊዋ ቤተ ክርስቲያን ልትደርስባቸው ወደማትችላቸው ሕይወቶችና ስፍራዎች ጌታ በሮችን እየከፈተ ስለ ሆነ በሥራው ላይ ግልጽ ቅባት አለ። ኤስ. ጌታ በመካከላችን አስደናቂ ነገሮችን እያደረገ እንደ ሆነ ለመመስከር ፈጣን ነው፤ ጌታ በሚደሰትበትና በሚቀባው ስፍራ መቆየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደ ሆነም ያውቃል።
የአብዛኞቹን የእነዚህን ሰዎች ስሞች ሆን ብዬ በምልክት ጽፌአለሁ፤ ሁሉም ግን በሚገባ የማውቃቸው ናቸው። ቀሳውስት፣ ዝነኞች ወይም በዓለም የተከበሩ ባይሆኑም ሕይወታቸው ስለ ጌታ ቅባት ተመሳሳይ ምስክርነት የሚሰጥ ሌሎች ብዙዎች አሉ። አንተ አንባቢዬም በዚህ ዝርዝር ላይ ሌሎች በርካታ ምስክርነቶችን ልትጨምር እንደምትችል እርግጠኛ ነኝ። ኃይላቸው፣ ሥልጣናቸውና አገልግሎታቸው የመጣው ከግል ማራኪነት (ያ ለታዋቂ ዘፋኞች አለ) ወይም በአደባባይ ጥሩ ገለጻ የማድረግ ችሎታ (ያ ለፖለቲከኞች አለ) ወይም ከጥበብ የተሞሉ የአመራር ዘዴዎች (ያ ለስኬታማ ነጋዴዎች አለ) አይደለም፤ ከእግዚአብሔር ጥሪ፣ ማስታጠቅና ቅባት ነው እንጂ።
በአንድ የቤተ ክርስቲያን የበጎ አድራጎት ዝግጅት ላይ ስለ ተገኘው ዝነኛ ተዋናይ ታሪክ ሰምተህ ይሆናል። ለሁሉም መዝናኛ እንዲሆን አንዳንድ የብቻ ንግግሮችን እንዲያቀርብ ተጋበዘ፤ እርሱም እንዲሁ አደረገ። ከእያንዳንዱ አቀራረብ በኋላ የጋለ ጭብጨባ ነበረ፤ በተለይም ታላቁን የእረኛ መዝሙር፣ መዝሙር 23ን በማንበብ በደመደመ ጊዜ።
ጭብጨባው ጋብ ሲል አንድ አረጋዊ ሰው ከወንበሩ ተነሥቶ ወደ ድምፅ ማጉያው ሄደ፤ ያንኑ መዝሙርም ቃል በቃል ደገመው።
በዚህ ጊዜ ሲጨርስ ጭብጨባ አልነበረም፤ ብዙዎች ግን እንባቸውን ከዓይናቸው እየጠረጉ ነበር፤ ሌሎችም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ነበር። ተዋናዩ ወደ አረጋዊው ቀረበ።
«በትምህርት ብዙ ሺህ ፓውንድ አውጥቻለሁ፤ በሙያዬም ከፍተኛው ደረጃ ላይ ደርሻለሁ» አለ፤ «ነገር ግን አንተ አሁን እንዳደረግኸው አድማጮቼን ፈጽሞ ልነካ አልቻልሁም። ምሥጢርህ ምንድን ነው?»
አረጋዊውም «አንተ መዝሙሩን ታውቃለህ — እኔ ግን እረኛውን አውቃለሁ!» ብሎ መለሰ።
የቅባት ምሥጢር ይህ ነው — ከእረኛው ጋር መተሳሰር። የእርሱን ሸክም (ለአንተ የሰጠህን) አብራችሁ ስትሸከሙ ከእርሱ ጋር በአንድ ቀንበር መጠመድ።
ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች
ኢቫንስ እንደሚለው እግዚአብሔር በአንድ ሰው አገልግሎት ላይ ቅባቱን ሲያኖር ምን ይመስላል?
ያ ሰው «እንደ ንስር በክንፍ ይወጣል»፤ ሌሎች ብዙ አማኞች ከሚኖሩት ተራ ሕይወት እጅግ ከፍ ብሎ የመንፈስ ነፋሳት ወደ ላይ ሲሸከሙት ይሰማዋል። ቀንበሩ ልዝብ፣ ሸክሙም ቀሊል ይሆናል።
ኢቫንስ በጃኪ ፑሊንገር አገልግሎት ውስጥ ምን የእግዚአብሔር ቅባት ምልክት አየ?
«ዘንዶውን ማሳደድ» በተባለው መጽሐፏ፣ በሱሰኞችና በወሮበላ ቡድን መሪዎች አስገድዶ የመድፈርና የሞት ዛቻ በተሰነዘረባት ጊዜ እንኳ በቅጥር ከተማው ፈጽሞ ፍርሃት እንዳልተሰማት ተናግራለች። ኢቫንስ ይህን በአገልግሎቷ ላይ ያለ የእግዚአብሔር ቅባት እርግጠኛ ማስረጃ ይለዋል፤ እርሱ በሚያውቃት ጊዜ ግን ጌታን ለማገልገል ከሚፈልጉ ከሌሎች ብዙ ወጣት ሴቶች የተለየች አትመስልም ነበር።
ዋይ. አር. ቢንተባተብም የተቀባ ስብከቱ ምሥጢር ምን ነበር?
ሁልጊዜ ማታ ማለት ይቻላል ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ መብራትና መጽሐፍ ቅዱስ ወዳለበት በአትክልት ቦታው ወዳለች ትንሽ ጎጆ ገለል ይል ነበር፤ በዚያም በኢየሱስ እግር ሥር ተማሪ ሆነ። ጌታ በእርሱ አማካይነት በግልጽነት ተናገረ፤ እርሱም ብዙ ሕዝብ የሚወጣለት መደበኛ የምእመናን ሰባኪ ሆነ።
ኤም. ኤም. በካናዳ የሜዳማ ክፍለ ግዛቶች በምትገኘው ቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎቷን ያገኘችው እንዴት ነው?
በየምሽቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ላለው ለእያንዳንዱ ሰው ትጸልይ ነበር፤ አንድ ጊዜ ያዘገየችው ውድ ዋጋ ካስከፈለ በኋላ ጌታ በገፋፋት ቁጥር ወዲያውኑ ምላሽ ለመስጠት ቆረጠች — ለታመሙት ስልክ በመደወል፣ በመጠየቅ ወይም አበባና ኬክ በመላክ። ፓስተሯ አበረታታት፤ ለሚወጣውም ወጪ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሂሳብ እንድትጠይቅ ነገራት።
የተዋናዩና መዝሙር 23ን ያነበበው አረጋዊ ታሪክ ስለ ቅባት ምን ያስተምራል?
ተዋናዩ ጭብጨባ ተቸረው፤ የአረጋዊው ንባብ ግን ሰዎችን አስለቀሰ፤ እርሱም «አንተ መዝሙሩን ታውቃለህ — እኔ ግን እረኛውን አውቃለሁ!» ብሎ አስረዳ። ኢቫንስ የቅባት ምሥጢር ይህ ነው ይላል፦ ከእረኛው ጋር መተሳሰርና የእርሱን ሸክም አብራችሁ ስትሸከሙ ከእርሱ ጋር በአንድ ቀንበር መጠመድ።
ምዕራፍ 10 ተጠናቋል
መብረር