ምዕራፍ 5 · 11 ደቂቃ ንባብ · 15 ደቂቃ ማዳመጥ
ራእይ
በክርስቶስ ወዳለን የሕይወት ዕጣ ፈንታችን ልንደርስ ከፈለግን ከሁኔታዎቻችን ባሻገር የሚያይ ራእይ ሊኖረን የግድ ነው። አመለካከታችን - ስለ ራሳችን ያለን አመለካከት (ወደ ውስጥ መመልከት)፣ ስለ ዓለም ያለን አመለካከት (ወደ ውጭ መመልከት) ወይም ስለ ጌታ ያለን አመለካከት (ወደ ላይ መመልከት) - አኗኗራችንን ይወስነዋል።
ወደ ውስጥ መመልከት
«ራስህን እንደምታስበው ነህ» ተብሏል። እርግጥ ነው፣ ይህ በሕመም ምክንያት በቅዠት ውስጥ ላሉ ሰዎች እውነት አይደለም።
በአንድ የአእምሮ ሕሙማን ማቆያ ውስጥ ስለ ነበሩ ሁለት ታካሚዎች የሚነገረውን ታሪክ ምናልባት ሰምተህ ይሆናል።
«ሰላም» አለ አንደኛው፤ «አንተ ማን ነህ?»
«እኔ ናፖሊዮን ነኝ» ብሎ ጓደኛው መለሰ።
«አይደለህም።»
«አዎ፣ ነኝ።»
«አይደለህም!»
«አዎ፣ ነኝ!»
«ማን ነገረህ?»
«እግዚአብሔር ነዋ!»
«አይ፣ እኔ አልነገርሁህም!!!»
የሚያሳዝነው፣ በክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ ማንነታቸው ልክ እንደ እነዚያ ምስኪን ታካሚዎች ዕውሮች የሆኑ ብዙዎች አሉ። ሆኖም ልንጋፈጠው የሚገባን የታላቅነት ቅዠትን ወይም ትዕቢትን ብቻ ሳይሆን ተቃራኒውን፣ ራስን አሳንሶ የማየትን ስሜት ጭምር ነው። ከላይ የተጠቀሰው አባባል በዚህ አሉታዊ መስክ በእርግጥ እውነት ነው። ራሳችንን የሚያዋርዱ አሳቦችን ስናስብ በእነዚያው ዝቅተኛ አሳቦች ሸለቆ ውስጥ እንኖራለን። ስለ ራሱ ከፍ ያለ ግምት ያለውን ሰው እየጠቆምን «ትዕቢተኛ» ብለን እንጠራዋለን፤ እግዚአብሔር በእርግጥ የሚያዋርደው ሰው ነው እንላለን።
ሆኖም ራሳችሁን እጅግ ታዋርዳላችሁ ተብለን ስንከሰስ ራሳችንን ለመከላከል እንቸኩላለን፤ (በጥቂት ትዕቢት ይሆን?) «ትሑታን» እንድንሆን ተጠርተናል ብለን እንጨምራለን። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ትሕትና ምን እንደ ሆነ አለማወቃችንን ብቻ ነው። ትሕትና የትዕቢት ተቃራኒ አይደለም - ያ የሐሰት ትሕትና ነው - ይህም ልክ እንደ ተቃራኒው የከፋ ሕመም ነው።
በመንግሥተ ሰማያት ታላላቆች ልንሆን ብንወድ «እንደ ትናንሽ ሕፃናት ትሑታን» እንድንሆን ተጠርተናል። ልጆች ጨዋታ ሊጫወቱ፣ ልዩ ልዩ አልባሳትንና ጭምብልን ሊለብሱ ይችላሉ፤ የመኝታ ሰዓት ሲደርስ ግን የጨዋታ ዕቃዎቹን አውልቀው ከብርድ ልብሱ ሥር ይገባሉ፤ እንደ ገናም ደካሞች፣ የደከሙ፣ የአባታቸውን እቅፍና ብርድ ልብስ የምታለብሳቸውን እናታቸውን የሚሹ ይሆናሉ። እንደ ገና «ራሳቸውን ብቻ» ይሆናሉ።
አልባሳቱንና ጭምብሉን ለብሰው የሚቀሩት ትልልቆቹ ብቻ ናቸው፤ ራሳችንን እንደምናውቀው አድርገው ሌሎች እንዲያዩን አንፈልግምና። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ግብዝነት ብሎ ይጠራዋል (በግሪክኛ = የሌላን ገጸ ባሕርይ ሚና መጫወት)።
እስቲ ይህን አስብ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ትሑት የሆነው ንግግር የመጣው ከእግዚአብሔር ራሱ ነው! ሙሴ «ከእስራኤል ልጆች ጋር ስነጋገር ማን ላከኝ ልበላቸው?» ብሎ በጠየቀው ጊዜ ዘላለማዊው አምላክ፦ «ያለና የሚኖር እኔ ነኝ! ያለና የሚኖር እንደ ላከህ ንገራቸው!» ብሎ መለሰለት።
ትሕትና ማንነትህን በእውነት ማወቅና - ያንኑም መሆን - ነው። ከዚያ አይበልጥም፤ ከዚያም አያንስም።
እንግዲያስ አንተ ማን ነህ?
ክርስቲያን አማኝ፣ ከእግዚአብሔር መንፈስ ዳግመኛ የተወለድህ ከሆንህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንተ የሚናገራቸው ብዙ ድንቅ ነገሮች አሉ። የአማኞች ሁሉ የጋራ ባለ ጠግነት ናቸው የተባሉትን እጅግ ብዙ ክቡራን ነገሮች እየፈለግህ አዲስ ኪዳንን አንብብ። ከእነዚህ ባለ ጠግነቶች አንዳንዶቹ በእኛ በኩል በሚደረግ አንዳች ድርጊት ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ አብዛኞቹ ግን ከችሎታችን ወይም ከብስለታችን ጋር ብዙም ግንኙነት የላቸውም፤ ይልቁንም ሙሉ በሙሉ የተያያዙት ኢየሱስ በመስቀል ላይ ካስገኘልን ነገር ጋር ነው፤ አብም ልጁን ስለሚወድ ብቻ እነዚህን ሊሰጠን ደስ ይለዋል።
እያንዳንዱ አዲስ አማኝ «በክርስቶስ» ያለውን ስፍራ ያውቅ ዘንድ በአዲሱ ሕይወቱ መጀመሪያ ላይ የኤፌሶንን መልእክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ሊማር ይገባዋል ብዬ አምናለሁ።
በእርሱ ተመርጠናል፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ በልጅነት ተወስደናል፤ አብ እርሱን ስለሚወድ ተቀባይነትን አግኝተናል። በእርሱ «በሰማያዊ ስፍራ» ተቀምጠናል፤ ከአለቅነትና ከሥልጣን (ከክፉ ኃይላት) ሁሉ እጅግ በላይ ነን። ሰይጣን ስለ አንተ የሚናገረውን ውሸት ማመንህን ተው፤ እግዚአብሔር ስለ አንተ የሚናገረውን ማመን ጀምር!
ኃጢአተኛ ነበርሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አሁን ቅዱስ እንደ ሆንሁ ይነግረኛል!
የኃጢአት ባሪያ ነበርሁ፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ!
ኃጢአቴ ተሰርዮልኛል፤ እርሱንም «አባት!» ብዬ ልጠራው እችላለሁ! በአንድ ወቅት በጨለማ እመላለስ ነበር፤ አሁን ግን በብርሃን እመላለሳለሁ!
ሙት ነበርሁ፤ አሁን ግን ሕያው ነኝ!
ጠፍቼ ነበር፤ አሁን ግን ተገኝቻለሁ - የእርሱ ነኝ!
አዲስ ፍጥረት (መንፈስ) ነኝ፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።
— በእኔ ውስጥ ባለ አንዳች ነገር ሳይሆን እኔ በእርሱ ስለ ሆንሁ ነው።
ከሰገነት ላይ ሆነህ አውጀው! ራሳችሁን አንሡ፤ ዘምሩም! የንጉሡ ልጆች ነን፤ ሃሌ ሉያ! ይህ ሕይወት ከንጉሣችን ጋር እንድንነግሥ የሚያዘጋጀን የአጭር ጊዜ የምልምል ወታደሮች ማሠልጠኛ ብቻ ነው፤ እርሱ በእኛ ስለሚኖርም ድል ልንነሣ እንችላለን፤ ክርስቶስ በእኛ ነው፤ እርሱም የክብራችን ዋስትና ነው።
ሰይጣን የበደለኛነትንና የኩነኔን ስሜት እያመጣ ይከስሃል፤ እውነቱ ግን «ምንም ነገር በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለይህ እንደማይችል» ያውጃል። ማንን ልታምን ነው - የሐሰት አባት የሆነውን ሰይጣንን ወይስ የእግዚአብሔር ቃል ደራሲ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን?
ሁኔታዎች ሊያጎብጡህ ይችላሉ፤ አንተ ግን «ኃይልን በሚሰጥህ በክርስቶስ ከአሸናፊዎች ልትበልጥ» ትችላለህ። ይህን ታምናለህን? ወይስ ጠላትህን ሰይጣንን ማመን ትመርጣለህ?
በክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካሉ ታላላቅ አሳዛኝ ነገሮች አንዱ (በክርስቶስ) ማንነታቸውን የማያውቁና ራሳቸውን በእግዚአብሔርና በሌሎች ፊት ለማጽደቅ ብዙ ጊዜ የሚያጠፉ አማኞች ብዛት ነው። ይህ እጅግ የሚያሳዝነው በስፍራቸው ዋስትና በሌላቸው (ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ እንዲሆኑ ስላልጠራቸው)፣ ማዕረጋቸውን ይዘው ለመቆየትም የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ መጫወት በሚያስፈልጋቸው መሪዎች መካከል ሲታይ ነው። ለእንዲህ ያሉ ሰዎች ጌታ ሁላችንንም እንድንሆን የጠራንን አገልጋይ መሆን እጅግ ከባድ ነው። ይልቁንም «ሥልጣናቸውን» አጥብቀው ይይዛሉ፤ በዚህም ሂደት ብዙ ጊዜ ሌሎች አማኞችን ይጎዳሉ። ሁልጊዜ እጅግ አስፈላጊ መስሎ የሚታየኝ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቁጥር አለ፤ ሆኖም በጠቀስሁትና አድማጮቼን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የት እንደሚገኝ በጠየቅኋቸው ጊዜ አንድም ሰው ሊመልስልኝ አልቻለም። እንዲህ ይላል፦
«ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ....»
(በሌላ አነጋገር፦ «ኢየሱስ ማን እንደ ሆነ፣ ከወዴት እንደ መጣ፣ ምን እያደረገ እንዳለና ወዴት እንደሚሄድ አውቆ ....»)
ቀጥሎ የሚመጣውን ታውቃለህን? (አንድ ሰው እንዲህ ድንገት ጥያቄ ውስጥ ሲከትህ አትጠላውም??) በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 13 ራስህ ፈልገህ አንብበው! በማንነቱና በጥሪው ላይ ጽኑ ዋስትና ነበረው።
ጌታ እንድንሆን የሚፈልገውን ሁሉ ለመሆን - እንደ ንስር ለመብረር - ብንወድ እኛም እንዲሁ ዋስትና ሊኖረን ያስፈልገናል። አንተ ራስህ ማን እንደ ሆንህና የት እንዳለህ ስታውቅ ሌሎችን ማገልገል ቀላል ነው።
ወደ ውጭ መመልከት
የሰውን ማኅበረሰብ ስትመለከት ምን ታያለህ - የዓለም አመለካከትህ ምንድን ነው? በዙሪያህ ያለው ሁሉ የተመሰቃቀለ ሲመስል ለምን ትደነቃለህ? የዓለም መንገድ ይህ መሆኑን ልታውቅ ይገባሃል። በዕውሮች እየተመራች፣ እየቃተተችና እያማጠች፣ ፈጣሪዋ የእግዚአብሔርን ልጆች ይዞ የሚመለስበትን ቀን የምትጠባበቅ የደከመች አሮጌ ፍጥረት ናት።
እስከዚያው ድረስ ሰው የራሱ ዓለም ማዕከል የሆነበትንና እግዚአብሔር ወደ ዳርቻው የተገፋበትን የዓለማዊ ሰብአዊነት ሃይማኖት ትከተላለች። በእርግጥም አሁን በምንኖርበት ከክርስትና በኋላ ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ ብዙዎች ከሃያኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ሊበራል የሥነ መለኮት ሊቃውንት ጋር ተባብረው እግዚአብሔር ሞቷል ይላሉ! ከራሱ ውጭ ላለ አንድ አካል ተጠያቂ የመሆን ፍጹም መመዘኛዎች ከሌሉት፣ ሰው ራሱ የሥነ ምግባር - ትክክል የሆነውንና ስሕተት የሆነውን - ወሳኝ ይሆናል፤ ማኅበረሰቡም ከአንዱ ቀውስ ወደ ሌላው ቀውስ እየተንገዳገደ ይሄዳል።
በስኮትላንድ ከሁለት የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ፓስተሮች፣ ከኢያንና ከፒተር ጋር የጸሎት ጉባኤ በጋራ እያስተናገድሁ ነበር። በምሽቱ የኢያን መንፈስ እጅግ ተክዞ ስለ ነበር ምክንያቱን ጠየቅሁት። በዚያ ቀን የብሔራዊቱ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ግብረ ሰዶማውያን ወንዶችን ለመሾም ድምፅ ሰጥቶ ነበር፤ ይህንንም ኢያንም ፒተርም ከመጻሕፍት ጋር የሚቃረን ነገር እንደ ሆነ ያምኑ ነበር። እነርሱና ሌሎች ብዙዎች ተቃውሟቸውን በይፋዊው መዝገብ ላይ እንዲያሰፍሩ ተፈቅዶላቸው ነበር፤ ውሳኔው ግን ጸድቋል።
ከዚያም ፒተርን እርሱ ለምን እንደዚያው መንፈሱ እንዳልተደፋ ጠየቅሁት። መልሱ ዓይን የሚከፍት ነበር። ግማሹ ሞልቶ - ወይም ግማሹ ጎድሎ - ስላለው የውኃ ብርጭቆ የሚነገረው ምሳሌ ነበር። «ከሃያ ዓመት በፊት ወደዚህ ከተማ ስመጣ» አለ፤ «ወንጌል በታማኝነት የሚሰበክባቸው ምናልባት ሁለት ወይም ሦስት የእኛ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ነበሩ። ዛሬ ሃያ ሁለት ናቸው!» «መለያየት እየተፈጠረ ነው። ጨለማው በበዛበት ስፍራ ብርሃኑም ይበዛል።» ስለ ዓለም ያለው ራእይ ስለ ጌታ ያለውን ራእይ እንዲነጥቀው አልፈቀደም።
በአሁኑ ሰዓት አንተና እኔ በዚህ ዓለም ውስጥ ነን፤ ከዓለም ግን አይደለንም። ዓለም እንዲያስተናግድህ አትጠብቅ። ጌታ ኢየሱስን እንዳልተቀበለው ሁሉ አንተንም ሊቀበልህ አይችልም። ሆኖም ጌታ በዓለም ውስጥ ምስክሮቹ እንድንሆን ስለሚፈልግ ከዚህ ዓለም ሊወስደን አልመረጠም። ንቁ ጠላት ስላለን ይህ ከባድ እንደሚሆን ያውቃል፤ ነገር ግን ስለ እኛ ጸልዮአል፤ አሁንም ይጸልያል። «አባት ሆይ፥ ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም»። እርግጥ ነው፣ አማኞች በብዙ የዓለም ዘርፎች ውስጥ ሊሳተፉ ይገባቸዋል - የሚያስጠላውን ነገሩን ለማጣፈጥና ክፋቱን ለመቃወም እንደ ጨው፤ ሕመሙን ለመግለጥና ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ ለማመልከት እንደ ብርሃን። በዓለም ተቋማትና ድርጅቶች ውስጥ በእግዚአብሔር በተሰጠ አገልግሎት እንደ ንስር የሚበሩ አንዳንዶች ይኖራሉ።
ሆኖም ዋነኛ ትኩረታችን ይህ ዓለም ሳይሆን በዚህ ዓለም ሕዝቦች መካከል ያለው መንግሥቱ ነው።
የተጠራነው በዓለም ውስጥ ቆመን ስለ ክርስቶስ ለመመስከር አይደለም፤ የተጠራነው በክርስቶስ ውስጥ ቆመን ለዓለም ለመመስከር ነው!
ኢየሱስ በመንግሥቱ ታላላቆች አድርጎ ስለሚቆጥራቸው አምስት ዓይነት ሰዎች ተናገረ። እነርሱም አገልጋዮች፣ እንደ ሕፃናት የሆኑ፣ ከሁሉ በኋላ ለመሆን ወይም ከሁሉ ለማነስ ፈቃደኞች የሆኑ፣ እንደ ታናሽም የሆኑ ናቸው። «እንደ ታናሽ» መሆን ምን ማለት እንደ ሆነ አስበህ ታውቃለህን? በኢየሱስ ዘመን የአባት ንብረት ሁሉ ለበኩር ልጁ ይተላለፍ ነበር። እርሻውም ከብቱም ሁሉ የእርሱ ነበሩ። ታናሹ ልጅ ግን ጠፊው ልጅ ቤቱን ትቶ ሲወጣ እንዳደረገው ርስቱን ሁሉ በትከሻው ተሸክሞ ሊሄድ ይችል ነበር። ንስሐ ገብቶ ወደ አባቱ ቤት በተመለሰ ጊዜ የአባቱ ልጅ ሊባል እንደማይገባው ቆጠረ፤ ሽማግሌው አባት ግን በፍቅር እቅፍ፣ በአዲስ ጫማ፣ በልብስና በግብዣ ተቀበለው።
በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ ተቆጣ። «ለዚህ አባካኝ የሰባውን ፊሪዳ ለምን አረድህለት?» ብሎ ጠየቀ። አባቱም በመልሱ የሰቡት ጥጆች ሁሉ የታላቁ ልጅ መሆናቸውን አመለከተው። በእርግጥም እርሻው ሁሉ የእርሱ ነበር። ሁሉም የእርሱ ነበር! እውነቱ ግን እርሻው እርሱን ገዝቶት ነበር! ንስሐና ይቅርታ ግድ አልሰጡትም፤ ብቸኛ ትኩረቱ በያዘው ንብረት ላይ ነበር። ይህ የእኔ እርሻ ነው! አትንኩት!
(ማስተጋባቱን ትሰማለህን? ይህ የእኔ አገልግሎት/ የእኔ ቤተ ክርስቲያን/ የእኔ ፕሮግራም/ የእኔ መዘምራን ነው! እነዚህ የእኔ በጎች ናቸው! ጀልባውን አታናውጡ!) ለመሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱ የማን ናት?
«እንደ ታናሽ» መሆን ማለት ይህ ዓለም - ሥልጣኑም፣ ንብረቱም፣ ተወዳጅነቱም፣ ዝናውም ሆነ ግቦቹ - እንዲገዙን አለመፍቀድ ማለት ነው። «ከዚህ ዓለም አይደለንም»፤ «አልተቆራኘንም»፤ የሌላ፣ የላቀ ዓለም አምባሳደሮች ነንና። ይህ ማለት ግን ንብረት ልንይዝ ወይም ሲሰጠን ክብርን ልንቀበል አይገባንም ማለት አይደለም። በእርግጥም ክርስቲያን ሥራውን በሚገባ የሚሠራና በዓለም መመዘኛ እንኳ ክብር የሚገባው ሆኖ ከሕዝቡ መካከል ጎልቶ ሊታይ ይገባዋል።
ሆኖም ዓለምን የራሳችን ብናደርግም እርሱ ግን የራሱ ሊያደርገን አይገባም፤ ጌታችን ጠርቶ ሲወስደን መቆራኘታችን ወደ ኋላ እንዳይይዘን ቀለል አድርገን እንይዘዋለን። እንደ ንስር እንድንበር ሲጠራን ለብዙ ዓመታት ከዓለምና ከመንገዶቹ ጋር በነበረን ግንኙነት በተገመዱ መቆራኘቶች፣ ግዴታዎችና «ገመዶች» «ከምድር ጋር ታስረን» አንቀርም።
ይህ ሕይወት - በዚህ ዓለም ያለው - ለእውነተኛው የዘላለም ዓለም ፍጹማን ሊያደርገን እግዚአብሔር ያዘጋጀው የወታደር ማሠልጠኛ ብቻ መሆኑን ልናስተውል ያስፈልገናል። በሚመጣው ሕይወት ከእርሱ ጋር ይነግሡ ዘንድ በዚህ ሕይወት ድል የሚነሡ ሕዝብን ይፈልጋል። ሰዎች የባሕር ኃይል ኮማንዶ (ማሪን) ለመሆን በሥልጠና ላይ ሳሉ ታላቅ ጫናና የግል ውርደት ቢደርስባቸው እንግዳ ነገር አይመስለንም፤ ጌታችን ግን በሥልጠናችን ውስጥ ችግሮችና የሚያገሣ አንበሳ እንዲያጠቁን ሲፈቅድ ብዙ ጊዜ ማጉረምረም እንጀምራለን። ከዓለም ጋር ወዳጅነትን በመሻት ዝግጅታችንን ለማበላሸት እጅግ ፈጣኖች ነን።
ሆኖም ጌታ እንድንሆን የጠራንን ስንሆን በዚህ ዓለም እንኳ ድል ነሺዎች እንሆናለን፤ መንግሥቱም በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትመሠረታለች። ቤተ ክርስቲያኑን ይሠራል፤ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።
በነገራችን ላይ፣ «ሚያው» የምትል ድመት የምታድነውን ከቶ አትይዝም፤ የሚያገሣ አንበሳም እንዲሁ አቅመ ቢስ ነው - ጩኸቱ ስሜታችንን እንዲነካና ድርጊታችንን እንዲያሽመደምድ በመፍቀድ እኛ ራሳችን ኃይል ስንሰጠው ካልሆነ በቀር።
ድላችንን ሊነጥቀን ፍርሃትን፣ ኀፍረትን፣ ቅናትን፣ ምቀኝነትን፣ ቁጣንና እነዚህን የመሳሰሉ አሉታዊ ስሜቶችን ይጠቀማል። ስልቶቹን ለይተን ማወቅና እነዚህ ስሜቶች እንዳያደናቅፉን መቁረጥ መማር ያስፈልገናል። ለሚስዮናውያን በርካታ ሴሚናሮችን እየመራሁና የአገሪቱን ብዙ ክፍል እየተዘዋወርሁ በኔፓል እጅግ አስደሳች የሆነ አንድ ወር አሳለፍሁ።
በዳራን ከተማ፣ በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ታላቅ ስደት በነበረበት ዘመን በዚያ ለብዙ ዓመታት ፓስተር ሆኖ ካገለገለ አንድ አረጋዊ ሰው ጋር ተዋወቅሁ። ከሃያ አምስት ጊዜ በላይ ተይዞ ሰባት ጊዜ ታስሮ ነበር፤ ረጅሙ እስራቱም ስምንት ዓመት ነበር። ከእስር ቤት እንደ ተፈታ ወዲያውኑ ወደ መንደሩ ተመልሶ ወንጌልን እንደ ገና መስበክ ይጀምር ነበር። «እንደ ገና መታሰርን አትፈራም ነበርን?» ብዬ ጠየቅሁት። መልሱም፦ «ለምን እፈራለሁ? አንበሳው የቻለውን ያህል አግስቷል!» የሚል ነበር። ትክክለኛው ራእይ ነበረው - በመንፈሳዊ ነገሮች ፍጹም (20/20) እይታ!
በ1959 በኢኳዶር ጫካዎች በሰማዕትነት ከተገደሉት አምስት ወጣቶች አንዱ የሆነው ጂም ኤሊየት ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ፦ «ሊያጣው የማይችለውን ለማግኘት ሊያቆየው የማይችለውን የሚሰጥ ሰው ሞኝ አይደለም!» ብሎ ጽፏል።
ከዚህ ዓለም እጅግ የላቀ ራእይ ነበረውና ይህ ዓለም እንዳልገዛው ግልጽ ነው።
ኢየሱስ በምድር ያለው የሰው የወደፊት ዕጣ ምን እንደሚሆን ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ «ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ» ይለናል። ራእያችን ወደ ላይ መሆን ያስፈልገዋል።
ወደ ላይ መመልከት
ዓለም በዕውርነቷ «እግዚአብሔር ሞቷል» ልትል ትችላለች፤ የሰማያዊው መንግሥት ዜጎች ግን ሌላ እውነታ ያውቃሉ። እግዚአብሔር አሁንም በዙፋኑ ላይ ነው፤ ሁሉንም ነገር ወደ ፍጻሜው እያደረሰ ነው፤ አሳቡም በዘመን ፍጻሜ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው። ዓላማዎቹን ይፈጽማል።
በ2ኛ ነገሥት 6 ነቢዩ ኤልሳዕ ሶርያውያን እስራኤልን ለመውረር ያወጡትን ዕቅድ ለንጉሡ ካሳወቀ በኋላ ስለ ደረሰበት ችግር እናነባለን። የሶርያ ንጉሥ ነቢዩን በዶታይን ከተማ ይይዙት ዘንድ ታላቅ ሠራዊት ላከ። ፀሐይ ስትወጣ የነቢዩ አገልጋይ ከአልጋው ተነሥቶ አዲሱን ቀን ለመቀበል መስኮቶቹን ከፈተ። ከተማይቱ በሶርያ ሠራዊት ተከብባ ባየ ጊዜ የተሰማውን መደነቅና ድንጋጤ አስብ! ሁኔታዎቹ ብዙም ተስፋ ሰጪ አልነበሩም! የወደፊቱ ጨለማ ነበር። ዓለም ሁሉ በእግዚአብሔር ሰው ላይ የተሰለፈ ይመስል ነበር።
«ወዮ ጌታዬ ሆይ! ምን እናደርጋለን?» ብሎ አገልጋዩ ጮኸ።
ኤልሳዕ ከአልጋው ተነሣ፤ ቀስ ብሎ ወደ መስኮቱ ሄደ፤ ጠላትን ተመለከተ፤ ጸለየም። የጭንቀት ቃል የለም፣ የመዳን ልመና የለም፣ ለእግዚአብሔር የቀረበ ጥያቄ የለም። ቀላል ጸሎት ብቻ፦ «አቤቱ፥ ዓይኖቹን ክፈት!»
እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ከፈተ፤ እርሱም በከተማይቱ ዙሪያ ያሉት ተራሮች የእግዚአብሔር ሠራዊት በሆኑ የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተሞልተው አየ። የሶርያ ንጉሥ ታላቅ ሠራዊቱን ሊልክ ይችል ይሆናል፤ ለእግዚአብሔር ሰው ግን አቻ አይሆኑትም ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ስንሆን ጠላት ወይም ዓለም በእኛ ላይ ሊወረውረው በሚችለው ነገር ሁሉ ላይ ሁልጊዜ «ከአሸናፊዎች እንበልጣለን»። ሁኔታዎቻችንን የከበቡት ኮረብቶች ወደ ሁኔታው እንዲለቀቁ ትእዛዙን ብቻ በሚጠባበቁ የጌታ ሠራዊቶች የተሞሉ መሆናቸውን ለማየት ወደ ላይ መመልከት ያስፈልገናል።
ንጉሥ ዳዊት ሁሉ ነገር በእርሱ ላይ የተነሣ የሚመስልባቸውን ብዙ ቀናት አሳልፏል። ንጉሥ ሳኦል ብዙ ጊዜ ሊገድለው ሞክሮ ነበር፤ በኢየሩሳሌም ካለው ቤተ መንግሥት ከወጣ በኋላም ያሳድደው ስለ ነበር ዳዊት ለዓመታት የተገለለ ሰው ሕይወት ኖረ። ሆኖም በሕይወቱ ካሳለፋቸው እጅግ አሳዛኝ ቀናት አንዱ ልጁ አቤሴሎም አባቱን ከእስራኤል ዙፋን ለማውረድ ሠራዊት እያሰባሰበ መሆኑን የተገነዘበበት ቀን ነበር። ዳዊት የስሜቱን ለውጥ በመዝሙር 3 መዝግቧል። - ከቁጥር 1 ጨለማ አመለካከት («አቤቱ፥ ጠላቶቼ ምንኛ በዙ») ወደ ቁጥር 8 መተማመን («እግዚአብሔር አዳኜ ነው!»)። ይህ የአመለካከት ለውጥ እንዴት እንደ መጣ ለማየት ቁጥር 3ን ልብ ማለት አለብን፦ «አንተ ግን፥ አቤቱ፥ በዙሪያዬ መከታዬ ነህ፤ ክብሬና ራሴን ከፍ ከፍ የምታደርገው አንተ ነህ።» ከጊዜ በኋላም፦ «ረዳቴ ወደሚመጣበት ወደ ተራሮች ዓይኖቼን አነሣለሁ። ረዳቴ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው!» ብሎ ይጽፋል።
ሁኔታህ ምንም ይሁን፣ ጠላት ምንም ያህል ቢከስህ፣ ዓለም ምንም ያህል ቢያስቀይምህ፣ ዓይኖችህን አንሣ፤ በሰማያዊው ዓለም እውነታዎች ላይም አተኩር። ሙሽራህ እየጠበቀ ነው፤ የግብዣው ማዕድ ተዘጋጅቷል፤ ወደ በጉ ሰርግ እራት የሚጋብዘንን የመለከት ድምፅ በቅርቡ እንሰማለን።
ጌታህ ሁሉን በቁጥጥሩ ሥር አድርጓል፤ «በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው» እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።
ይህ አዎንታዊ አስተሳሰብ ብቻ አይደለም፤ የተስፋችን ግልጽ መግለጫ እንጂ (ይኸውም፦ እርግጠኛ የሆነውን ነገር በጉጉት መጠበቅ)። እስከዚያው ድረስ እንደ ንስር እንድንበር ይፈልጋል!
ስለ ራስህ ጤናማ አመለካከት፣ ስለ ዓለም እውነታውን የተረዳ አመለካከትና በጌታ ላይ የጓጓ ተስፋ ሊኖርህ ይችላል፤ ስለ ቤተ ክርስቲያንስ ያለህ አመለካከት ምንድን ነው? በዓለምህ ላይ እምብዛም ተጽዕኖ የሌላት ደካማና ፍሬ አልባ ናትን? ሕያው አካል - ሕያው የክርስቶስ አካል - ከመሆን ይልቅ ድርጅት ሆናለችን? ለሰዎች ከማሰብ ይልቅ በፕሮግራም ላይ ያተኮረች ናትን?
ካሉኝ ታላላቅ መብቶች አንዱ ወጣቶችንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ለማገልገል ወደ ብዙ አገሮች መጓዝ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ስፍራዎች ሕያውና ጤናማ መሆኗን ጮክ ብዬ በግልጽ ማወጅ እፈልጋለሁ። በሄድሁበት ሁሉ ለእግዚአብሔር ታላላቅ ነገሮችን የሚሠሩ ወንዶችንና ሴቶችን አገኛለሁ፤ እርግጥ ነው፣ ዓለማዊው መገናኛ ብዙኃን ዓለማቸውን ስለሚለውጡት ስለ እነዚህ አማኞች ብዙም አይነግሩንም። የሚያመሳስላቸው ነገር ሸክምና እግዚአብሔር በእነርሱ በኩል ሊሠራ ስለሚችለው ነገር ያላቸው ታላቅ ራእይ ነው።
ሎረን ካኒንግሃም በወጣትነቱ ራእይ ነበረው። ራእዩ እንደ ባሕር ማዕበል ተለቅቀው ወደ ዓለም ዳርቻዎች የሚደርሱ የወጣቶች ማዕበሎች ነበሩ። እግዚአብሔር በወንጌል ሁለት እጆች እንዲወጡ እጅግ ብዙ ሕዝብን ሊያነሣሣ እንደሚችል አመነ። መልካሙን የምሥራች በቃላቸው መናገርም ሆነ የኢየሱስን ባሕርይ በድርጊታቸው ማሳየት ነበረባቸው።
ዛሬ ዩዝ ዊዝ ኤ ሚሽን በዓለም ሁሉ የታወቀ ነው፤ ከሃምሳ በላይ በሆኑ አገሮች የሚያገለግሉ ወደ ስምንት ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞች ያሉት የሚስዮን ኃይል አለው፤ የተባበሩት መንግሥታት በሚያውቃቸው አገሮች ሁሉም አገልግሏል።
ታዲያ የአንተ ራእይ ምንድን ነው?
ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች
ኢቫንስ ራእያችንን ይቀርጻሉ የሚላቸው ሦስቱ «መመልከቶች» ምንድን ናቸው?
ወደ ውስጥ መመልከት — ስለ ራሳችን ያለን አመለካከት፤ ወደ ውጭ መመልከት — ስለ ዓለም ያለን አመለካከት፤ እና ወደ ላይ መመልከት — ስለ ጌታ ያለን አመለካከት። በመደምደሚያው ስለ አራተኛ አመለካከትም — ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለን አመለካከት — ይጠይቃል።
ኢቫንስ እውነተኛ ትሕትናን እንዴት ይተረጕመዋል?
ትሕትና ማንነትህን በእውነት ማወቅና ያንኑም መሆን ነው — ከዚያ አይበልጥም፤ ከዚያም አያንስም። የትዕቢት ተቃራኒ አይደለም ይላል፤ ያ የሐሰት ትሕትና ሲሆን ልክ እንደ ትዕቢት ሕመም ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ትሑት የሆነው ንግግርም የእግዚአብሔር «ያለና የሚኖር እኔ ነኝ» የሚለው ቃል እንደ ሆነ ይናገራል።
ኢቫንስ «እንደ ታናሽ» መሆን ሲል ምን ማለቱ ነው?
በኢየሱስ ዘመን እርሻውን የሚወርሰው በኩሩ ልጅ ነበር፤ በጠፊው ልጅ ታሪክም ታላቁ ወንድም በእውነቱ እርሻው የገዛው ሰው ነበር። «እንደ ታናሽ» መሆን ማለት ይህ ዓለም — ሥልጣኑ፣ ንብረቱ፣ ተወዳጅነቱና ግቦቹ — እንዲገዙን አለመፍቀድ ነው፤ ጌታ እንድንበር ሲጠራን መቆራኘታችን ከምድር ጋር አስሮ እንዳያስቀረን ቀለል አድርገን መያዝ ነው።
በዳራን የነበረው ኔፓላዊ ፓስተር እንደ ገና መታሰርን ይፈራ እንደ ሆነ ሲጠየቅ ምን አለ?
ከሃያ አምስት ጊዜ በላይ ተይዞ ሰባት ጊዜ ታስሮ ነበር፤ ረጅሙ እስራቱም ስምንት ዓመት ነበር፤ ሆኖም «ለምን እፈራለሁ? አንበሳው የቻለውን ያህል አግስቷል!» ብሎ መለሰ። ኢቫንስ ትክክለኛው ራእይ እንደ ነበረው ይናገራል — በመንፈሳዊ ነገሮች ፍጹም (20/20) እይታ።
ሁኔታዎች የሚያሸንፉ በሚመስሉበት ጊዜ ኢቫንስ አንባቢው ምን እንዲያደርግ ይመክራል?
ኤልሳዕ በዶታይን ስለ አገልጋዩ «አቤቱ፥ ዓይኖቹን ክፈት!» ብሎ እንደ ጸለየ፣ ወደ ላይ እንድንመለከትና ሁኔታዎቻችንን የከበቡት ኮረብቶች በጌታ ሠራዊቶች የተሞሉ መሆናቸውን እንድናይ ያሳስበናል። ሁኔታህ ምንም ይሁን፣ ጠላት ምንም ያህል ቢከስህ፣ ዓይኖችህን አንሣና በሰማያዊው ዓለም እውነታዎች ላይ አተኩር፤ ጌታ ሁሉን በቁጥጥሩ ሥር አድርጓልና።
ምዕራፍ 5 ተጠናቋል
ራእይ