ጸሎትና የሚጸልዩ ሰዎች
ኃጢአተኞች በጸሎት ያላቸው እምነት

ምዕራፍ 12 · 7 ደቂቃ ንባብ · 10 ደቂቃ ማዳመጥ

ኃጢአተኞች በጸሎት ያላቸው እምነት

ስብከቶቹ ብዙ ነፍሳትን ወደ ጌታ ይመልሱ የነበረ አንድ ሰባኪ፣ ይህ የሆነው በስብከቶቹ ወይም በሥራዎቹ ፈጽሞ ሳይሆን፣ በመድረኩ ደረጃዎች ላይ ተቀምጦ ስለ ስብከቱ መከናወን ይማልድ በነበረ በአንድ ያልተማረ ምእመን ወንድም ጸሎት እንደ ሆነ ከእግዚአብሔር መገለጥ ተቀበለ። ሁሉ በሚገለጥበት በዚያ ቀን ከእኛም ጋር እንዲሁ ሊሆን ይችላል። ለረጅም ጊዜ በድካም ከሠራን በኋላ፣ ክብሩ ሁሉ ጸሎቱ ወርቅ፣ ብርና የከበረ ድንጋይ ለሆነ ለሌላ ገንቢ እንደሚገባ፣ ከጸሎት ተለይተው የተዘጋጁት ስብከቶቻችን ግን ሣርና አገዳ ብቻ እንደ ሆኑ እናምን ይሆናል።—ቄስ ቻርልስ ስፐርጀን።

ይህን ርዕስ በብሉይ ኪዳን ስናጠና ከምናገኛቸው የጸሎት ልዩ ገጽታዎች አንዱ፣ ዓመፀኞችና ወደ ኋላ የተመለሱ ሰዎች በጸሎት ላይ የነበራቸው እምነትና በዘመኑ በነበሩ በሚጸልዩ ሰዎች ጸሎት ላይ የነበራቸው ታላቅ መታመን ነው። አንዳንድ ሰዎችን በእግዚአብሔር የሚያምኑ፣ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኙና ወደ እግዚአብሔር የሚጸልዩ የጸሎት ሰዎች መሆናቸውን ያውቁ ነበር። እነዚህ ሰዎች ቍጣን በመመለስና ከክፉ በማዳን ረገድ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰሚነት እንዳላቸው ይገነዘቡ ነበር።

ብዙ ጊዜ በችግር ውስጥ ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ ሲያሰጋቸው፣ ስለ በደላቸውም ክፉ ነገር በላያቸው በወረደ ጊዜ እንኳ፣ እግዚአብሔር ቅሬታውን እንዲመልስና ቍጣውን ከእነርሱ እንዲያርቅ ይለምኑላቸው ዘንድ ወደሚጸልዩት ሰዎች በመሄድ በጸሎት ላይ ያላቸውን እምነት አሳዩ። ጸሎት ሰዎችን ለማዳን የተሰጠ መለኮታዊ መሣሪያ መሆኑን ተገንዝበው፣ ስለ እነርሱ በእግዚአብሔር ፊት እንዲማልዱ ወደሚጸልዩት ሰዎች ተማጸኑ።

በዚያ በጥንቱ ዘመን ከታዩት እንግዳ ተቃርኖዎች አንዱ ይህ ነው፦ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ቢርቁና ወደ ከባድ ኃጢአት ቢገቡም፣ ጸሎትን የሚመልስ አምላክ ስለ መኖሩ ጉዳይ ሲነሣ ከሓዲዎች ወይም ኢአማኞች አልሆኑም። ክፉ ሰዎች እግዚአብሔር እንዳለ በማመንና ጸሎት የኃጢአትን ይቅርታ ለማስገኘትና ከእግዚአብሔር ቍጣ ለማዳን ባለው ኃይል በማመን ጸንተው ቆሙ። ኃጢአተኞች በጸሎት ሲያምኑና ክርስቲያኖችን እንዲጸልዩላቸው ሲለምኑ፣ ይህ ቤተ ክርስቲያን በኃጢአተኞች ላይ ያላትን ተጽዕኖ የሚያሳይ በመሆኑ ዋጋ አለው። አንድ ኃጢአተኛ በሞት አልጋው ላይ ሆኖ ይጸልይለት ዘንድ የሚጸልይ ሰው ወደ አልጋው አጠገብ እንዲመጣ ሲጠራ፣ ይህ ትኵረት የሚስብና ትልቅ ቍም ነገር ያለው ነገር ነው። ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች የበደላቸው ስሜት ተሰምቷቸው፣ የእግዚአብሔርንም ቅሬታ ተገንዝበው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሠዊያ ቀርበው፦ «እናንተ የምትጸልዩ ወንዶችና ሴቶች ሆይ፣ ጸልዩልኝ» ሲሉ፣ ይህ ትርጉም አለው። ቤተ ክርስቲያን የዚህን ሙሉ ትርጉም እምብዛም አትረዳም፤ በተለይም ስለ ዘላለማዊ ነፍሳቸው እንዲጸልዩላቸው ለሚለምኗት ላልዳኑ ወንዶችና ሴቶች መጸለይ ያለውን ሙሉ ትርጉም ደግሞ ከዚያ ይበልጥ አትገነዘበውም፤ ዋጋም አትሰጠውም። ቤተ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ሕያው ብትሆን፣ በዙሪያዋ ያሉት ያልተለወጡ ሰዎች ያሉበትን እውነተኛ አደጋ ብትነቃ፣ በመልካም ሁኔታም ላይ ብትገኝ፣ ብዙ ኃጢአተኞች የቤተ ክርስቲያንን መሠዊያዎች እየፈለጉ ወደሚጸልዩ ሰዎች፦ «ስለ ነፍሴ ጸልዩ» እያሉ ሲጮኹ በተገኙ ነበር።

ለኃጢአተኞች ጸሎት ተብሎ የሚጠራ ብዙ ጸሎት ይኖር ይሆናል፤ ነገር ግን ወደ የትም የማይሄድ፣ ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ የማይደርስ፣ ምንም የማያከናውን ቀዝቃዛ፣ የሥርዓትና የሥራ ድርሻ ጸሎት ነው። መነቃቃቶች የሚጀምሩት ኃጢአተኞች የሚጸልዩ ሰዎችን ጸሎት ሲፈልጉ ነው።

ወደ እነዚያ የብሉይ ኪዳን ዘመናት ስንመለከት ብዙ ነገሮች ጎልተው ይታያሉ፦

አንደኛ፣ በእግዚአብሔር ላይ የበደሉ ኃጢአተኞች ችግር ሲቀርብ ሳያስቡት ማለት ይቻላል ለእርዳታና ለመጠጊያ ወደሚጸልዩ ሰዎች የመዞርና ከችግራቸው እንዲገላገሉና እንዲድኑ ጸሎታቸውን የመለመን ዝንባሌያቸው። ጩኸታቸው «ጸልዩልን» የሚል ነበር።

ሁለተኛ፣ እነዚያ የሚጸልዩ ሰዎች ለእነዚህ ልመናዎች የሰጡት ፈጣን ምላሽና ይህን ለፈለጉት ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መጸለያቸው። ከዚህም በላይ፣ እነዚህ የሚጸልዩ ሰዎች ሁልጊዜ በጸሎት መንፈስ ውስጥ እንደ ነበሩና በማንኛውም ጊዜ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ዝግጁ እንደ ነበሩ ልብ እንላለን። ሁልጊዜ ለጸሎት የተዘጋጁ ነበሩ።

ሦስተኛ፣ እነዚህ የጸሎት ሰዎች ወደ እግዚአብሔር በተማጸኑ ቍጥር በእርሱ ዘንድ የነበራቸውን አስደናቂ ተሰሚነት እናስተውላለን። እግዚአብሔር ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ፈጥኖ መለሰ፤ ስለ ሌሎች ያቀረቡትንም ጸሎት ሰማ። ስለዚህ በእነዚያ በእግዚአብሔር ጉባኤ የመጀመሪያ ዘመናት የምልጃ ጸሎት የበላይነት ነበረው።

በዚህ ዘመን ያሉ ኃጢአተኞች ጸሎት የእግዚአብሔርን ቍጣ ለመመለስ፣ ፍሬ ቢስ ሕይወቶችን ለማትረፍና ለማዳን እንደ መሣሪያ ያለውን ዋጋ ላለማመናቸው የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ተጠያቂ ናት የሚለው በጥሞና ሊታሰብበት የሚገባ ጥያቄ ነው። በዚህ ዘመን በጽዮን የሚያለቅሱት እጅግ ጥቂት መሆናቸውን፣ ሰዎችም የመሠዊያ ጥሪያችሁን ችላ ብለው ቀርበው እንዲጸለይላቸው የምታቀርቡትን ልመና በግዴለሽነት መመልከታቸውን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ተጠያቂ ናት?

ክፉ ሰዎች በጸሎት ያላቸውን እምነትና የእግዚአብሔር ሰው ስለ እነርሱ እንዲማልድ ያቀረቡትን ልመና የሚያሳየው የመጀመሪያው ምሳሌ በእስራኤላውያን ላይ የተላኩት የእሳት እባቦች ታሪክ ነው። ከሖር ተራራ ተነሥተው የኤዶምያስን ምድር ለመዞር በኤርትራ ባሕር መንገድ ሲጓዙ፣ በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ እንዲህ ብለው ተናገሩ፦

«በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃም የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈች።»

ነገሩ እግዚአብሔርን እጅግ ስላስቈጣው በሕዝቡ መካከል የእሳት እባቦችን ሰደደ፤ ከእስራኤልም ሕዝብ ብዙዎች ሞቱ።

«ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው፦ በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን ኃጢአት ሠርተናል፤ እባቦቹን ከእኛ እንዲያርቅልን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉ።» ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ።

እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር ምንም ያህል ቢርቁ፣ እግዚአብሔር ባደረገባቸው ነገር ላይ በማጕረምረማቸው ኃጢአታቸው ምንም ያህል ታላቅ ቢሆን፣ በጸሎት ላይ ያላቸውን እምነት አላጡም፤ በእስራኤልም ውስጥ በጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰሚነት ያለው፣ በዚያም መንገድ ጥፋትን መመለስና ማዳንን ማምጣት የሚችል መሪ እንዳለ አልረሱም።

ሌላው ምሳሌ፣ መንግሥቱ በተከፈለ ጊዜ የአሥሩ ነገድ የመጀመሪያው ንጉሥ የነበረው ኢዮርብዓም ነው። ከእግዚአብሔር መራቁ እጅግ የታወቀ ስለ ነበረና በኋለኛው የእስራኤል ታሪክ ውስጥ «የናባጥ ልጅ የኢዮርብዓም ኃጢአት» ተብሎ ብዙ ጊዜ ስለሚጠቀስ ይህ እጅግ የታወቀ ምሳሌ ነው፤ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ክፋት ቢሠራም በጸሎት ውጤታማነት ላይ ያለውን እምነት እንዳላጣም ያሳያል። ይህ ንጉሥ በአንድ ወቅት የሊቀ ካህናቱን ስፍራ ለመያዝ ደፈረ፤ ዕጣንም ለማጤስ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ። አንድ የእግዚአብሔር ሰው ከይሁዳ ወጥቶ በመሠዊያው ላይ ጮኸ፤ እንዲህም ብሎ ተናገረ፦ «እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፥ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል።» ይህም ኢዮርብዓምን አስቈጣው፤ በሌዋውያን ሕግ ላይ የእግዚአብሔርን ካህን ሹመት ለመውሰድ በመሞከሩ ለእርሱ የተሰጠ የአደባባይ ተግሣጽ እንደ ሆነ አይቶ ነበርና፤ ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው ለማስያዝ ወይም ለመጉዳት ያሰበ በሚመስል ሁኔታ እጁን ዘረጋ፤ በዚያው ጊዜም በዙሪያው ላሉት፦ «ያዙት» አለ።

ወዲያውኑ እግዚአብሔር ንጉሡን በለምጽ መታው፤ ስለዚህ እጁን ወደ ራሱ መመለስ አልቻለም፤ በዚያው ጊዜም መሠዊያው ተሰነጠቀ። ልክ ከሰማይ እንደ መብረቅ በመጣው በዚህ ድንገተኛ የኃጢአቱ ቅጣት ከመጠን በላይ ተደንቆና እጅግ ፈርቶ የእግዚአብሔርን ሰው፦ «እጄ እንድትመለስልኝ እባክህ ስለ እኔ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን» ብሎ ጮኸ። «የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እንደ ቀድሞዋም ሆነች» ተብሎ ተጽፎአል።

አሁን የምንመለከተው የእግዚአብሔርን ሰው የጸሎት ልማድ ወይም የጸሎትን ዕድሎች እንዳልሆነ፣ ሁለቱም እዚህ ፊታችን ቢቀርቡም፣ እናስታውስ። ይልቁንም እዚህ የምናገኘው፣ በከባድ ኃጢአት የበደለና ከእግዚአብሔር የራቀ አንድ የእስራኤል ገዥ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላዩ በወደቀ ጊዜ፣ ስለ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት እንዲማልድ ወዲያውኑ የሚጸልይን ሰው መጥራቱን ነው። ይህ በእግዚአብሔር ላይ የበደለ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር ሰው ጸሎት ኃይል ላይ ያለውን እምነት ያሳየበት ሌላ ምሳሌ ብቻ ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጸሎት የሚያሽቆለቍልበት ብቻ ሳይሆን፣ ኃጢአተኞች በቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ፈጽሞ ስለማይነኩ በጸሎት ላይ እምነት የሌላቸውና ለሚጸልዩ ሰዎች ጸሎት ደንታ የሌላቸው በሆኑበት በክርስቲያን አገር ያ ቀን የሚያሳዝን ነው።

ሌላ ምሳሌ ይህን ታሪክ ፈጥኖ ይከተላል። የንጉሡ የኢዮርብዓም ልጅ ታመመ፤ ሊሞትም ተቃረበ። ይህም ክፉና ግዴለሽ ንጉሥ የልጁ ሕመም ፍጻሜ ምን እንደሚሆን እንዲነግራት ሚስቱን ወደ እግዚአብሔር ነቢይ ወደ አኪያ በፍጥነት ላካት። እርሷም ማንነቷን ሳታሳውቅ ዓይኑ ሊጠፋ የተቃረበውን አረጋዊ ነቢይ ለማታለል ሞከረች። እርሱ ግን ዓይኑ ቢደክምም የነቢይ ራእይ ነበረው፤ ወዲያውኑም እንዳወቃት ገለጠላት። ስለ መንግሥቱ እጅግ ታላቅ ቍም ነገር ያላቸውን ብዙ ነገሮች ከነገራት በኋላ፣ ባሏም የእግዚአብሔርን ትእዛዛት እንዳልጠበቀ ነገር ግን ወደ ጣዖት አምልኮ እንደ ሄደ ከወቀሰው በኋላ እንዲህ አላት፦ «አንቺም ተነሥተሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እግርሽ ወደ ከተማይቱ በገባ ጊዜ ብላቴናው ይሞታል።»

በችግር ላይ ያለ አባት ከችግሩ እንዲገላገል ወደሚጸልይ ነቢይ መማጸኑ እንዴት ተፈጥሯዊ ነው? እንደ መጀመሪያውም ምሳሌ፣ ኃጢአቱ የእግዚአብሔር ሰው ስለ እርሱ እንዲማልድ የማድረግን ዋጋ ከማየት ዓይኖቹን አላሳወረውም። እንደ ተረጋገጠው ምንም አልጠቀመውም፤ ነገር ግን በብሉይ ኪዳን ዘመን ኃጢአተኞች ራሳቸው የሚጸልዩ ሰዎች ባይሆኑም በሚጸልዩ ሰዎች ጸሎት አጥብቀው ያምኑ እንደ ነበረ የምንለውን አቋማችንን በእርግጥ አረጋገጠ።

የእስራኤል ልጆች በባቢሎን የምርኮ ኑሮአቸውን ልክ በጀመሩበት ጊዜ የነበረውን የዮሐናንን ምሳሌ ውሰድ። ዮሐናንና ኤርምያስ ከጥቂት ሰዎች ጋር በአገራቸው ቀርተው ነበር፤ እስማኤልም የአገሪቱ ተሾሚ ገዥ በነበረው በጎዶልያስ ላይ አሢሮ ገድሎት ነበር። ዮሐናን ለማዳን ደረሰ፤ ሕዝቡንም ከአገራቸው እየወሰዳቸው ከነበረው ከእስማኤል እጅ አዳናቸው። ዮሐናን ግን ከመለኮታዊው ዕቅድ በተቃራኒ ወደ ግብፅ መሸሽ ፈለገ። በዚህ ልዩ ወቅት ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፤ እነርሱም በዚህ ልባዊ ልመና ወደ ኤርምያስ ሄዱ፦

«እባክህ፥ ልመናችን በፊትህ ተቀባይነት ይኑረው፤ አምላክህ እግዚአብሔር የምንሄድበትን መንገድና የምናደርገውን ነገር ያሳየን ዘንድ ስለ እኛ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ።»

ደጋግ ሰዎች እንዲጸልዩ እንደ ቀረቡት ሌሎች ልመናዎች ሁሉ፣ ኤርምያስ ትክክለኛውን መንገድ ለሚጠይቁት ለእነዚህ ሰዎች ማለደ፤ ከአሥር ቀንም በኋላ መልሱ መጣ፤ እግዚአብሔር እንዲያደርጉ የሚፈልገውንም ኤርምያስ ነገራቸው። ይህም ወደ ግብፅ እንዳይወርዱ፣ ነገር ግን በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እንዲቀሩ የሚል ነበር፤ ሕዝቡና ዮሐናን ግን ኤርምያስን ከዱት፤ ለጸሎት መልስ ሆኖ እግዚአብሔር የነገራቸውንም ለማድረግ እንቢ አሉ። ይህ ግን በጸሎትና በሚጸልዩ ሰዎች እምነት እንደ ነበራቸው የሚያሳየውን እውነት አላስተባበለም።

ኃጢአተኞች በብሉይ ኪዳን ዘመን በጸሎት እምነት እንደ ነበራቸው የሚለውን የአሳባችንን እውነት የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ልብ ልንለው እንችላለን፤ ይህም በእነዚያ ዘመናት የጸሎትን የበላይነት በተዘዋዋሪ ያረጋግጣል፤ ኃጢአተኞች እንኳ በድርጊታቸው ለጸሎት ኃይልና አስፈላጊነት ምስክርነት ከሰጡ፣ በእርግጥ ጸሎት ታዋቂ ስፍራ ነበረው፤ አስፈላጊነቱም በሰዎች ሁሉ ዘንድ የታወቀ ነበረ ማለት ነውና። ኃጢአተኞች ስለ ጸሎት ዋጋ ከመሰከሩ፣ በዚያ ጊዜም በሌላ ሰው ጸሎት እንኳ ቢሆን ጸሎት እንደሚያስፈልጋቸው ካሳዩ፣ በዚህ ዘመን ያሉ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች የጸሎት አስፈላጊነት በጥልቅ ሊሰማቸው፣ በጸሎትና በኃይሉም ጽኑ እምነት ሊኖራቸው በእርግጥ ይገባል። የብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች እንዲህ ያሉ የጸሎት ሰዎች ከነበሩና የሚጸልዩ ሰዎች ተብለው እንዲህ ያለ ስም ካተረፉ፣ በዚህ በተባረከ ዘመን ክርስቲያን ወንዶች እነርሱም የሚጸልዩ ሰዎች ተብለው ሰፊ ስም እስኪያተርፉ ድረስ ራሳቸውን ለጸሎት ሊሰጡ በእርግጥ ይገባቸዋል።

ሴዴቅያስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ምርኮ ልክ በጀመረበት ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ነበር። ኢየሩሳሌም በባቢሎን ንጉሥ በተከበበች ጊዜ መንግሥቱን የሚመራው እርሱ ነበር። ልክ በዚያን ጊዜ ሴዴቅያስ ሁለት የተመረጡ ሰዎችን ወደ ኤርምያስ እንዲህ ብሎ ላከ፦ «የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋናልና እባክህ ስለ እኛ እግዚአብሔርን ጠይቅ፤ ምናልባት እግዚአብሔር እንደ ተአምራቱ ሁሉ ያደርግልን እንደ ሆነ፥ እርሱም ከእኛ ይመለሳል።»

እግዚአብሔርም ለዚህ ጥያቄ መልስ ኤርምያስ ምን እንደሚያደርግና ምን እንደሚሆን ነገረው፤ ነገር ግን እንደ ሌላው ምሳሌ፣ እንደ ዮሐናን ሁሉ፣ ሴዴቅያስም ከዳ፤ እግዚአብሔር ኤርምያስን እንዲነግረው ያዘዘውንም አላደረገም። ይሁን እንጂ ይህ ሴዴቅያስ የእግዚአብሔርን አሳብ ለማወቅ መንገድ በሆነው በጸሎት ላይ እምነቱን እንዳላጣ፣ በሚጸልይ ሰው ጸሎት ኃይል ላይ ያለውም እምነት እንዳልተነካ በማያጠራጥር ሁኔታ አረጋገጠ።

በእውነት፣ የእግዚአብሔር ሰዎች በጸሎት ልማዳቸው የታወቁ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከእግዚአብሔር የራቁና የከዱ ሰዎች እንኳ ስለ እነርሱ ምልጃ እንዲያቀርቡ ወደ ጸሎት ሰዎች በመማጸን ለጸሎት ኃይል ከመሰከሩ፣ ጸሎት በብሉይ ኪዳን ታሪክ ሁሉ ውስጥ የላቀ ስፍራ ነበረው ማለት ነው። ይህ በብሉይ ኪዳን ታሪክ ውስጥ እጅግ የታወቀ በመሆኑ እነዚህን የጥንት መጻሕፍት በጥንቃቄ የሚያነብ ማንም ሰው ሊያገኘውና ሊያስተውለው አይሳነውም።

ገጽ 1 / 1 · 7 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ