በጸሎት የሚገኝ ኃይል
ከአእምሮ ይልቅ ከልብ የሚመነጭ ጸጋ

ምዕራፍ 13 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ከአእምሮ ይልቅ ከልብ የሚመነጭ ጸጋ

ጥሩ ሰባኪ ለመሆን አትጣር። ኢያሪኮዎች የሚፈርሱት በአውራ በግ ቀንደ መለከት ነው። ለስብከት የሚሆንህን ምግብ ለማግኘት በቅንነት ወደ ኢየሱስ ብቻ ተመልከት፤ የሚያስፈልገውም ይሰጥሃል፤ የተሰጠውም ይባረካል፤ የገብስ ቅንጣትም ሆነ የስንዴ እንጀራ፣ ቅርፊትም ሆነ ፍርፋሪ ቢሆን። አፍህ እንደ ልብህ ሁኔታ የሚፈስ ወንዝ ወይም የታተመ ምንጭ ይሆናል። በስብከትም ሆነ በንግግር ወይም በጽሑፍ ክርክርን ሁሉ አስወግድ፤ ከዲያብሎስ በቀር ምንም አታዋርድ፤ ከኢየሱስ ክርስቶስም በቀር ምንም ከፍ አታድርግ።—ቤሪጅ

ልብ የዓለም አዳኝ ነው። አእምሮዎች አያድኑም። ተሰጥኦ፣ ጭንቅላት፣ ብልጭታ፣ ብርታት፣ የተፈጥሮ ስጦታዎች አያድኑም። ወንጌል የሚፈስሰው በልቦች በኩል ነው። እጅግ ብርቱዎቹ ኃይሎች ሁሉ የልብ ኃይሎች ናቸው። እጅግ ጣፋጮቹና ውቦቹ ጸጋዎች ሁሉ የልብ ጸጋዎች ናቸው። ታላላቅ ልቦች ታላላቅ ሰዎችን ይሠራሉ፤ ታላላቅ ልቦች መለኮታዊ ጠባይ ያላቸውን ሰዎች ይሠራሉ። እግዚአብሔር ፍቅር ነው። ከፍቅር የሚበልጥ፣ ከእግዚአብሔርም የሚበልጥ ምንም የለም። ልቦች ሰማይን ይሠራሉ፤ ሰማይ ፍቅር ነው። ከሰማይ ከፍ ያለ፣ ከሰማይም የሚጣፍጥ ምንም የለም። የእግዚአብሔርን ታላላቅ ሰባኪዎች የሚሠራው አእምሮ ሳይሆን ልብ ነው። በሃይማኖት ውስጥ ልብ በሁሉ ረገድ እጅግ ዋጋ አለው። ልብ ከመድረክ ሊናገር ይገባዋል። ልብ በምእመናን መቀመጫ ሊሰማ ይገባዋል። በእርግጥም እግዚአብሔርን የምናገለግለው በልባችን ነው። የአእምሮ ብቻ አምልኮ በሰማይ ተቀባይነት የለውም።

የዘመናዊው መድረክ ከባድና እጅግ የተስፋፉ ስሕተቶች አንዱ በስብከቶቹ ውስጥ ከጸሎት ይልቅ አሳብን፣ ከልብ ይልቅ አእምሮን ማብዛቱ ነው ብለን እናምናለን። ትልልቅ ልቦች ትልልቅ ሰባኪዎችን ይሠራሉ፤ መልካም ልቦች መልካም ሰባኪዎችን ይሠራሉ። ልብን የሚያሰፋና የሚያለማ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት የወንጌል ወርቃማ ምኞት ነው። እረኛው ሕዝቡን ከራሱ ጋር የሚያስተሳስራቸውና የሚመራቸው በልቡ ነው። ስጦታዎቹን ሊያደንቁ፣ በችሎታው ሊኮሩ፣ ለጊዜውም በስብከቶቹ ሊነኩ ይችላሉ፤ የኃይሉ ምሽግ ግን ልቡ ነው። በትረ መንግሥቱ ፍቅር ነው። የኃይሉ ዙፋን ልቡ ነው።

መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። አእምሮዎች ሰማዕታትን ፈጽሞ አያፈሩም። ሕይወትን ለፍቅርና ለታማኝነት አሳልፎ የሚሰጠው ልብ ነው። ታማኝ እረኛ ለመሆን ታላቅ ድፍረት ያስፈልጋል፤ ይህን ድፍረት ግን ሊሰጥ የሚችለው ልብ ብቻ ነው። ስጦታና ተሰጥኦ ደፋር ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይህ ግን የልብ ስጦታና ተሰጥኦ እንጂ የአእምሮ አይደለም።

ልብን ከማዘጋጀት ይልቅ አእምሮን መሙላት ይቀላል። የልብ ስብከትን ከማዘጋጀት ይልቅ የጭንቅላት ስብከትን ማዘጋጀት ይቀላል። የእግዚአብሔርን ልጅ ከሰማይ የሳበው ልብ ነበር። ሰዎችንም ወደ ሰማይ የሚስባቸው ልብ ነው። ዓለም የሚያስፈልጋት ከሥቃይዋ ጋር የሚራራላት፣ ኀዘኗን በመሳም የሚያብስላት፣ ለጕስቍልናዋ የሚያዝንላትና ሕመሟን የሚያቀልላት የልብ ሰዎች ናቸው። ክርስቶስ ከሁሉ በላይ የልብ ሰው ስለ ነበረ በተለየ ሁኔታ የሕማም ሰው ነበረ።

«ልብህን ስጠኝ» እግዚአብሔር ከሰዎች የሚጠይቀው ነው። «ልብህን ስጠኝ!» ሰው ከሰው የሚጠይቀው ነው።

ሙያዊ አገልግሎት ልብ የሌለው አገልግሎት ነው። በአገልግሎት ውስጥ ደመወዝ ትልቅ ስፍራ ሲይዝ ልብ የሚይዘው ስፍራ ትንሽ ነው። ስብከትን ሥራችን አድርገን ልባችንን ግን በሥራው ውስጥ ላናኖር እንችላለን። በስብከቱ ራሱን ወደ ፊት የሚያስቀድም ልቡን ወደ ኋላ ያደርጋል። በጥናት ክፍሉ በልቡ የማይዘራ ለእግዚአብሔር መከርን ፈጽሞ አያጭድም። የጸሎት እልፍኝ የልብ ጥናት ክፍል ነው። እንዴት መስበክ እንዳለብንና ምን መስበክ እንዳለብን በቤተ መጻሕፍቶቻችን ከምንማረው ይልቅ በዚያ አብልጠን እንማራለን። «ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ» በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ አጭሩና እጅግ ታላቁ ቁጥር ነው። የከበረውን ዘር ተሸክሞ እያለቀሰ (ታላላቅ ስብከቶችን እየሰበከ ሳይሆን) የሚሄድ ሰው ነው ነዶውን ተሸክሞ በደስታ የሚመለሰው።

መጸለይ ማስተዋልን ይሰጣል፤ ጥበብን ያመጣል፤ አእምሮን ያሰፋል፤ ያበረታልም። የጸሎት እልፍኝ ለሰባኪው ፍጹም አስተማሪና ትምህርት ቤት ነው። አሳብ በጸሎት የሚበራና የሚጠራ ብቻ ሳይሆን በጸሎትም ይወለዳል። በእውነት በምንጸልይበት ጊዜ በአንድ ሰዓት ጸሎት በጥናት ክፍል ውስጥ ከብዙ ሰዓታት ይልቅ አብልጠን መማር እንችላለን። በሌላ በየትም ሊገኙና ሊነበቡ የማይችሉ መጻሕፍት በጸሎት ጓዳ ውስጥ አሉ። በሌላ በየትም የማይገለጡ መገለጦች በጸሎት ጓዳ ውስጥ ይገለጣሉ።

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ