ምዕራፍ 12 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
የልብ ዝግጅት አስፈላጊ ነው
ከልብ የወጣ ካልሆነ በቀር ወደ ልብ የሚደርስ ነገር የለም፤ ከሕያው ኅሊና የመጣ ካልሆነ በቀርም ኅሊናን የሚወጋ ነገር የለም።—ዊልያም ፔን
ጠዋት ላይ ከልቤ ይልቅ አእምሮዬን በማዘጋጀት ተጠምጄ ነበር። ይህ ብዙ ጊዜ ስሕተቴ ሆኖአል፤ ክፋቱንም ሁልጊዜ፣ በተለይም በጸሎት፣ ተረድቼዋለሁ። ጌታ ሆይ፣ እንግዲህ አስተካክለው! ልቤን አስፋው፤ እኔም እሰብካለሁ።—ሮበርት መሪ ማክሼን
ከልብ ይልቅ አእምሮ የበዛበት ስብከት በኃይል ወደ ሰሚዎቹ አይደርስም።—ሪቻርድ ሴሲል
ጸሎት በብዙ ዓይነትና በብዙ ገጽታ ባሉት ኃይሎቹ አፍ እውነትን በሙላቱና በነጻነቱ እንዲናገር ይረዳል። ስለ ሰባኪው መጸለይ ይገባል፤ ሰባኪው የሚሠራው በጸሎት ነው። ስለ ሰባኪው አፍ መጸለይ ይገባል፤ አፉ በጸሎት ሊከፈትና ሊሞላ ይገባዋል። ቅዱስ አፍ የሚሠራው በመጸለይ፣ በብዙ መጸለይ ነው፤ ደፋር አፍ የሚሠራው በመጸለይ፣ በብዙ መጸለይ ነው። ቤተ ክርስቲያንና ዓለም፣ እግዚአብሔርና ሰማይ ለጳውሎስ አፍ ብዙ ባለ ዕዳ ናቸው፤ የጳውሎስ አፍ ደግሞ ኃይሉን ያገኘው ከጸሎት ነበር።
ጸሎት ለሰባኪው በብዙ መንገድ፣ በብዙ ነጥብ፣ በሁሉም ረገድ ምንኛ ብዙ ገጽታ ያለው፣ ወሰን የሌለው፣ ውድና ረዳት ነው! ከታላላቅ ጥቅሞቹ አንዱ ልቡን መርዳቱ ነው።
መጸለይ ሰባኪውን የልብ ሰባኪ ያደርገዋል። ጸሎት የሰባኪውን ልብ በሰባኪው ስብከት ውስጥ ያኖራል፤ ጸሎት የሰባኪውን ስብከት በሰባኪው ልብ ውስጥ ያኖራል።
ሰባኪውን የሚሠራው ልብ ነው። ታላቅ ልብ ያላቸው ሰዎች ታላላቅ ሰባኪዎች ናቸው። ክፉ ልብ ያላቸው ሰዎች በተወሰነ መጠን መልካም ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ይህ ግን እምብዛም አይሆንም። ሞያተኛውና እንግዳው በአንዳንድ ነገር በጎቹን ሊረዱ ይችላሉ፤ ነገር ግን በጎቹን የሚባርካቸውና የእረኛነትን ስፍራ በሙላት የሚፈጽመው የመልካም እረኛ ልብ ያለው መልካሙ እረኛ ነው።
የስብከትን ዝግጅት እጅግ ከማጉላታችን የተነሣ ሊዘጋጅ የሚገባውን ዋናውን ነገር—ልብን—ዘንግተናል። የተዘጋጀ ልብ ከተዘጋጀ ስብከት እጅግ ይሻላል። የተዘጋጀ ልብ የተዘጋጀ ስብከትን ያስገኛል።
የስብከት አዘገጃጀትን ስልትና ውበት የሚዘረዝሩ ብዙ መጻሕፍት ተጽፈዋል፤ በዚህም የግንባታው መወጣጫ ራሱ ሕንጻው ነው በሚል አስተሳሰብ እስክንያዝ ደርሰናል። ወጣቱ ሰባኪ ኃይሉን ሁሉ በስብከቱ ቅርጽ፣ ጣዕምና ውበት ላይ—እንደ አንድ የእጅ ሥራና የአእምሮ ውጤት—እንዲያፈስስ ተምሮአል። በዚህም በሕዝቡ ዘንድ የተበላሸ ጣዕም አሳድገናል፤ ከጸጋ ይልቅ ተሰጥኦን፣ ከመንፈሳዊነት ይልቅ አንደበተ ርቱዕነትን፣ ከመገለጥ ይልቅ የንግግር ጥበብን፣ ከቅድስና ይልቅ ዝናንና ብልጭልጭነትን የሚሻ ጩኸት አስነሥተናል። በዚህም እውነተኛውን የስብከት ትርጉም አጥተናል፤ የስብከትን ኃይል አጥተናል፤ ስለ ኃጢአት የሚወጋውን ወቀሳ አጥተናል፤ የበለጸገውን ልምምድና ከፍ ያለውን ክርስቲያናዊ ጠባይ አጥተናል፤ ከእውነተኛ ስብከት ሁልጊዜ የሚመነጨውን በኅሊናና በሕይወት ላይ ያለውን ሥልጣን አጥተናል።
ሰባኪዎች ከመጠን በላይ ያጠናሉ ማለት አይቻልም። አንዳንዶቹ ፈጽሞ አያጠኑም፤ ሌሎቹ በበቂ አያጠኑም። ብዙዎቹ የማያሳፍሩ ሠራተኞች ሆነው የተፈተነውን ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ በሚገባው መንገድ አያጠኑም። ነገር ግን ታላቁ ጉድለታችን የአእምሮ እርሻ ሳይሆን የልብ እርሻ ነው፤ አሳዛኙና ጎልቶ የሚታየው ጉድለታችን የእውቀት ማጣት ሳይሆን የቅድስና ማጣት ነው—እጅግ ብዙ ስለምናውቅ አይደለም፤ ይልቁንም በእግዚአብሔርና በቃሉ ላይ በበቂ ስለማናሰላስል፣ በበቂ ስለማንተጋ፣ ስለማንጾምና ስለማንጸልይ ነው። ለስብከታችን ታላቁ እንቅፋት ልብ ነው። መለኮታዊ እውነትን ያረገዙ ቃላት በልባችን ውስጥ የማያስተላልፍ ግድግዳ ያገኛሉ፤ በዚያም ተገትተው፣ ተሸልተውና ኃይል አጥተው ይወድቃሉ።
ምስጋናንና ሥልጣንን የምትመኝ ምኞት ራሱን ባዶ ያደረገውንና የባሪያን መልክ የያዘውን የእርሱን ወንጌል ልትሰብክ ትችላለችን? ትዕቢተኛው፣ ከንቱው፣ ራሱን የሚያመልከውስ የዋህና በልቡ ትሑት የሆነውን የእርሱን ወንጌል ሊሰብክ ይችላልን? ቁጡው፣ በስሜት የሚነዳው፣ ራስ ወዳዱ፣ ጨካኙና ዓለማዊው ሰውስ ትዕግሥትን፣ ራስን መካድንና ርኅራኄን የተሞላውን፣ ከጠላትነት መለየትንና ለዓለም መሰቀልንም አጥብቆ የሚጠይቀውን ትምህርት ሊሰብክ ይችላልን? ልብ የሌለው፣ ለይስሙላ የሚያገለግል ሞያተኛ ባለ ሥልጣንስ እረኛው ነፍሱን ስለ በጎቹ እንዲሰጥ የሚጠይቀውን ወንጌል ሊሰብክ ይችላልን? ደመወዝንና ገንዘብን የሚቈጥር ስስታም ሰውስ ልቡን እስኪያጠራና በክርስቶስና በጳውሎስ መንፈስ በዌስሊ ቃላት፦ «እንደ ጕድፍና እንደ ዝቃጭ እቈጥረዋለሁ፤ ከእግሬ በታች እረግጠዋለሁ፤ እኔ (ነገር ግን እኔ አይደለሁም፣ በእኔ ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ) እንደ መንገድ ጭቃ እቈጥረዋለሁ፤ አልመኘውም፤ አልፈልገውም» ማለት እስኪችል ድረስ ወንጌልን ሊሰብክ ይችላልን? የእግዚአብሔር መገለጥ ሊያስጌጠውም ሆነ ሊያጸናው የሰው ብልሃት ብርሃን፣ የሰው ትምህርት ማለስለሻና ብርታት፣ የሰው አሳብ ብልጭታ፣ የሰው አእምሮ ጕልበት አያስፈልገውም፤ ነገር ግን የሕፃን ልብ የሆነውን ቅንነት፣ ለመማር ዝግጁነትን፣ ትሕትናንና እምነትን ይጠይቃል።
ጳውሎስን ከሐዋርያት መካከል አቻ የሌለው ያደረገው ይህ አእምሮንና ተሰጥኦን ለመለኮታዊና ለመንፈሳዊ ኃይሎች መስጠትና ማስገዛት ነው። ዌስሊን ኃይል የሰጠውና ድካሙን በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ያደረገው ይህ ነው። ሎዮላም ወደ ኋላ የሚያፈገፍጉትን የካቶሊክ ኃይሎች ለማስቆም ብርታት ያገኘው በዚህ ነው።
ታላቁ ፍላጎታችን የልብ ዝግጅት ነው። ሉተር፦ «በሚገባ የጸለየ በሚገባ አጥንቶአል» የሚለውን እንደ መሠረታዊ እውነት ይዞት ነበር። ሰዎች ማሰብና አእምሮአቸውን መጠቀም የለባቸውም አንልም፤ ነገር ግን አእምሮውን አብልጦ በሚገባ የሚጠቀመው ልቡን አብልጦ የሚያለማ ነው። ሰባኪዎች ተማሪዎች መሆን የለባቸውም አንልም፤ ነገር ግን ታላቁ ጥናታቸው መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለበት እንላለን፤ መጽሐፍ ቅዱስንም አብልጦ የሚያጠናው ልቡን በትጋት ሁሉ የጠበቀ ነው። ሰባኪው ሰዎችን ማወቅ የለበትም አንልም፤ ነገር ግን የሰውን ተፈጥሮ አብልጦ የሚያውቀው የገዛ ልቡን ጥልቀትና ውስብስብነት የመረመረ ነው። የምንለው ይህ ነው፦ የስብከት ቦይ አእምሮ ቢሆንም ምንጩ ልብ ነው፤ ቦዩን ልታሰፋውና ልታጠልቀው ትችላለህ፤ ነገር ግን የምንጩን ንጽሕናና ጥልቀት በሚገባ ካልተጠነቀቅህ የደረቀ ወይም የተበከለ ቦይ ይኖርሃል። የምንለው ይህ ነው፦ ማንኛውም መካከለኛ ማስተዋል ያለው ሰው ወንጌልን ለመስበክ የሚበቃ ማስተዋል አለው፤ ይህን ለማድረግ የሚበቃ ጸጋ ያላቸው ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው። የምንለው ይህ ነው፦ ከገዛ ልቡ ጋር ታግሎ ያሸነፈው፣ ትሕትናን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ እውነትን፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄንና ድፍረትን ያስተማረው፣ በዚህ ሁኔታ የሠለጠነውን የልብ ባለጠግነት በወንጌል ኃይል በተሞላ ጽኑ አእምሮ በኩል በሰሚዎቹ ኅሊና ላይ ሊያፈስስ የሚችል—እንዲህ ያለው ሰው በጌታው ዘንድ እጅግ እውነተኛና እጅግ የተሳካለት ሰባኪ ይሆናል።
ምዕራፍ 12 ተጠናቋል
የልብ ዝግጅት አስፈላጊ ነው