የእንጦንስ ሕይወት
ፈውሶቹ በጸሎት በክርስቶስ ብቻ እንደ ተደረጉ

ምዕራፍ 36 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ

ፈውሶቹ በጸሎት በክርስቶስ ብቻ እንደ ተደረጉ

83. የአባ እንጦንስ ቃላት እንዲህ ናቸው፤ እንዲህ ያሉ ድንቆች በሰው እጅ ተደርገዋልን ብለን ልንጠራጠር አይገባንም። ይህ የመድኃኒታችን ተስፋ ነውና፤ እርሱ፦ «የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።» ብሏል። ደግሞም፦ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። ለምኑ ትቀበሉማላችሁ።» ብሏል። ለደቀ መዛሙርቱና በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ፦ «ድውዮችን ፈውሱ፤ … አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ።» የሚለውም እርሱ ራሱ ነው።

84. አባ እንጦንስ ግን የሚፈውሰው በማዘዝ ሳይሆን በጸሎትና የክርስቶስን ስም በመጥራት ነበር። ስለዚህ የሚሠራው እርሱ ራሱ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን በእርሱ በኩል ምሕረት ያደረገውና ሕመምተኞችን የፈወሰው ጌታ እንደ ሆነ ለሁሉ ግልጥ ነበር። የአባ እንጦንስ ድርሻ ግን ጸሎትና ተጋድሎ ብቻ ነበር፤ ስለዚህም በተራራው ይኖር ነበር፤ መለኮታዊ ነገሮችን በማሰላሰልም ደስ ይለው ነበር፤ ብዙ ሕዝብ ሲያስቸግሩትና ወደ ውጪው ተራራ ሲጐትቱት ግን ያዝን ነበር። ዳኞች ሁሉ ይከተሏቸው በነበሩት ባለ ጕዳዮች ብዛት ምክንያት ወደ እርሱ መግባት ስለማይቻላቸው ወደ ታች እንዲወርድ ይለምኑት ነበርና። ቢሆንም ብቻ ያዩት ዘንድ እንዲመጣ ለመኑት። እርሱም በሸሸና ወደ እነርሱ ለመሄድ እምቢ ባለ ጊዜ፣ ጸንተው በዚህ ምክንያት ይወርድ ዘንድ እስረኞችን በወታደሮች አስጠብቀው አብዝተው ወደ እርሱ ይልኩ ነበር። በግድም ተገፋፍቶ፣ ሲያለቅሱም አይቶ ወደ ውጪው ተራራ መጣ፤ ድካሙም ደግሞ ከንቱ አልሆነም። መምጣቱ ለብዙዎች ጠቃሚና ረዳት ነበርና፤ ዳኞችንም ከሁሉ በላይ ፍትሕን እንዲያስቀድሙ፣ እግዚአብሔርን እንዲፈሩ፣ «በሚፈርዱበትም ፍርድ እንዲፈረድባቸው» እንዲያውቁ እየመከረ ጠቀማቸው። ከሁሉ ይልቅ ግን በተራራው መቀመጥን ይወድ ነበር።

ገጽ 1 / 1 · 1 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ