የጸሎት መሠረታዊ ነገሮች
ጸሎትና መሰጠት

ምዕራፍ 3 · 8 ደቂቃ ንባብ · 10 ደቂቃ ማዳመጥ

ጸሎትና መሰጠት

«በ1737 ለጤንነቴ ስል በፈረስ ወደ ጫካ በወጣሁ ጊዜ፣ ለመለኮታዊ ማሰላሰልና ለጸሎት በእግር መመላለስ ልማዴ እንደ ነበረው በአንድ ገለልተኛ ስፍራ ከፈረሴ ወርጄ ሳለሁ፣ ለእኔ ያልተለመደ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ክብር ታየኝ። እኔ እንደምገምተው ይህ አንድ ሰዓት ያህል ቆየ፤ አብዛኛውንም ጊዜ በእንባ ጎርፍና ጮኼ በማልቀስ ውስጥ አቆየኝ። ከዚህ በቀር እንዴት እንደምገልጸው በማላውቀው ሁኔታ ባዶ ለመሆንና ለመደምሰስ፣ እርሱን በቅዱስና በንጹሕ ፍቅር ለመውደድ፣ እርሱን ለማገልገልና ለመከተል፣ ፍጹም ለመቀደስና በመለኮታዊና በሰማያዊ ንጽሕና ንጹሕ ለመሆን የነፍስ ጽኑ ናፍቆት ተሰማኝ።»—ጆናታን ኤድዋርድስ።

መሰጠት ሃይማኖታዊ ትርጉም አለው። የመሰጠት ሥሩ አንድን ነገር ለተቀደሰ አገልግሎት መለየትና መስጠት ነው። ስለዚህ መሰጠት በእውነተኛ ትርጉሙ ከሃይማኖታዊ አምልኮ ጋር የተያያዘ ነው። ከእውነተኛ ጸሎት ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው። መሰጠት ፈጽሞ ለእግዚአብሔር በተሰጠ ሰው ውስጥ የሚገኝ ልዩ የአእምሮ ሁኔታ ነው። የአክብሮት፣ የመደነቅና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ነው። በጸሎትና በአምልኮ በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ የልብ ሁኔታ ነው። ከመንፈስ ቅለት ጋር ከሚመሳሰል ነገር ሁሉ የራቀ ነው፤ ቧልትን፣ ጫጫታንና ፉከራን ይቃወማል። መሰጠት በጸጥታ ግዛት ውስጥ ይኖራል፤ በእግዚአብሔርም ፊት ጸጥ ይላል። ጭምት፣ አሳቢና አሰላሳይ ነው።

መሰጠት የውስጣዊ ሕይወት ክፍል ነው፤ በጸሎት እልፍኝ ይኖራል፤ ነገር ግን በመቅደሱ የሕዝብ አምልኮም ይገለጣል። የእውነተኛ አምልኮ መንፈስ ክፍል ነው፤ የጸሎት መንፈስ ባሕርይም አለው።

መሰጠት ሐሳቡና ስሜቱ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ሰው ገንዘብ ነው። እንዲህ ያለ ሰው ፈጽሞ ለሃይማኖት የተሰጠ አእምሮ አለው፤ ለእግዚአብሔር ጽኑ ፍቅር፣ ለቤቱም የሚነድ ፍቅር አለው። ቆርኔሌዎስ «ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ» ሰው ነበረ። «በጸሎትም የተጉ ሰዎች እስጢፋኖስን ቀበሩት።» «እንደ ሕጉም በጸሎት የተጋ ሐናንያ የሚሉት አንድ ሰው» ሳውል ዕውር በነበረ ጊዜ ጌታ ምን እንዲያደርግ እንደሚፈልግ ሊነግረው ወደ እርሱ ተላከ። እግዚአብሔር እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች በድንቅ ሁኔታ ሊጠቀምባቸው ይችላል፤ ለእግዚአብሔር የተሰጡ ሰዎች ዕቅዱን ወደ ፊት ለማራመድ የመረጣቸው ወኪሎቹ ናቸውና።

ጸሎት የመሰጠትን መንፈስ ያሳድጋል፤ መሰጠትም ለመልካሙ ጸሎት ምቹ ነው። መሰጠት ጸሎትን ያግዛል፤ ጸሎትም የሚፈልገውን ግብ እንዲመታ ይረዳል። ጸሎት በእውነተኛ መሰጠት ከባቢ አየር ውስጥ ይለመልማል። በመሰጠት መንፈስ ውስጥ ሲሆኑ መጸለይ ቀላል ነው። በመሰጠት ውስጥ ያለው የአእምሮ አቋምና የልብ ሁኔታ ጸሎት ወደ ጸጋው ዙፋን በመድረስ የሚሠራ እንዲሆን ያደርጉታል። እግዚአብሔር የመሰጠት መንፈስ በሚኖርበት ስፍራ ይኖራል። የመንፈስ ጸጋዎች ሁሉ መሰጠት በሚፈጥረው ከባቢ ውስጥ ይመገባሉ፤ በሚገባም ያድጋሉ። እንዲያውም እነዚህ ጸጋዎች ከዚህ በቀር በሌላ ስፍራ አያድጉም። የመሰጠት መንፈስ አለመኖር በታደሰ ልብ ውስጥ ለተወለዱት ጸጋዎች ሞት ማለት ነው። እውነተኛ አምልኮ በመሰጠት መንፈስ በተፈጠረ ከባቢ ውስጥ የሚስማማውን ስፍራ ያገኛል። ጸሎት ለመሰጠት ረዳት እንደ ሆነ ሁሉ፣ በዚያው ጊዜ መሰጠትም በጸሎት ላይ መልሶ ይሠራል፤ እንድንጸልይም ይረዳናል።

መሰጠት ልብን በጸሎት ያሰማራል። ልብ ከጸሎቱ ርቆ ሳለ ከንፈር ለመጸለይ መሞከሩ ቀላል ሥራ አይደለም። እግዚአብሔር በአንድ ወቅት በጥንቱ ሕዝቡ በእስራኤል ላይ ያቀረበው ክስ ልባቸው ከእርሱ የራቀ ሆኖ በከንፈራቸው ያከብሩታል የሚል ነበር።

የጸሎት ዋና ምንነት የመሰጠት መንፈስ ነው። ያለ መሰጠት ጸሎት ባዶ ሥርዓት፣ ከንቱ የቃላት ዙረት ነው። የሚያሳዝነው፣ እንዲህ ያለው ጸሎት ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በብዛት ይገኛል። ይህ ዘመን የተጣደፈ፣ የሚራወጥና ሥራ የበዛበት ዘመን ነው፤ ይህ የመራወጥ መንፈስም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ወርሯል። ሃይማኖታዊ ተግባሮቿ ብዙ ናቸው። ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖትን ሥራ በእውነተኛ ማሽን ሥርዓት፣ ትክክለኛነትና ኃይል ትሠራለች። ነገር ግን ብዙ ጊዜ በማሽን ልብ የለሽነት ትሠራለች። ማቋረጫ በሌለው የሃይማኖታዊ ተግባሮቻችን ዙረትና ልማድ ውስጥ እንደ ወፍጮ መንኮራኩር ያለ ብዙ ሽክርክሪት አለ። ሳንጸልይ እንጸልያለን። በመንፈስና በአእምሮ ሳንዘምር እንዘምራለን። የእግዚአብሔር ምስጋና በውስጡም ሆነ በአጠገቡ የሌለበት ሙዚቃ አለን። በልማድ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄዳለን፤ ቡራኬው ሲሰጥም እጅግ ደስ ብሎን ወደ ቤት እንመለሳለን። የለመድነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ እናነባለን፤ ሥራው ሲያልቅም እፎይ እንላለን። ተማሪ ትምህርቱን በቃሉ እንደሚያነበንብ ጸሎታችንን በቃል እንደግማለን፤ «አሜን» ሲባልም አናዝንም።

ሃይማኖት ከልባችን በቀር ከሁሉ ነገር ጋር ጉዳይ አለው። እጃችንንና እግራችንን ያሰማራል፤ ድምፃችንን ይይዛል፤ በገንዘባችን ላይ እጁን ይጭናል፤ የሰውነታችንን አቋም እንኳ ይነካል፤ ነገር ግን ፍቅራችንን፣ ምኞታችንንና ቅንዓታችንን አይዝም፤ ጭምቶችና በእጅጉ ትጉዎች አያደርገንም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ጸጥ ብለን እንድናመልክ አያደርገንም። ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚስበን የአምልኮው መንፈስ ሳይሆን ማኅበራዊ ቅርርብ ነው። የቤተ ክርስቲያን አባልነት በውጫዊ አካሄዳችን በተወሰነ ደረጃ ጨዋዎች አድርጎ ያቆየናል፤ ለጥምቀት ስእለታችንም የታማኝነት ጥላ ያህል ያስጠብቀናል፤ ልብ ግን በነገሩ ውስጥ የለም። በዚህ ሁሉ ውጫዊ ተግባር መካከል ቀዝቃዛ፣ ሥርዓታዊና ያልተነካ ሆኖ ይቀራል፤ እኛ ግን በሃይማኖት ረገድ እጅግ ጥሩ እየሠራን እንደ ሆነ ራሳችንን እያመሰገንን እንኖራለን።

በእግዚአብሔር የመምሰል ሕይወታችን ውስጥ ይህ ሁሉ የሚያሳዝን ጉድለት ለምን ሆነ? የኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት እውነተኛ ባሕርይ ይህ ዘመናዊ መጣመም ለምን ሆነ? የዘመኑ ሃይማኖት ውድ ዕንቍዎቹ የጠፉበትን የዕንቍ ሣጥን የሚመስለው ስለ ምንድር ነው? ሃይማኖትን በእጅ—ብዙ ጊዜም ንጽሕናው አጠራጣሪ በሆነ እጅ—መያዝ ለምን በዛ? በልብ የሚሰማውና በሕይወት የሚመሰከረውስ ለምን አነሰ?

የዘመኑ ሃይማኖት ታላቅ ጉድለት የመሰጠት መንፈስ ማጣት ነው። ስብከቶችን ንግግር ወይም ዲስኩር በምንሰማበት መንፈስ እንሰማለን። የእግዚአብሔርን ቤት ከቲያትር ቤት፣ ከንግግር አዳራሽ ወይም ከሕዝብ መሰብሰቢያ አደባባይ ጋር እኩል እንደ ሆነ ተራ ስፍራ እንጎበኛለን። የእግዚአብሔርን አገልጋይ በመለኮት የተጠራ የእግዚአብሔር ሰው አድርገን ሳይሆን ከፖለቲከኛው፣ ከጠበቃው፣ ከተራው ተናጋሪ ወይም ከመምህሩ ጋር እኩል የሆነ አንድ ዓይነት የሕዝብ ተናጋሪ ብቻ አድርገን እንመለከተዋለን። አቤት፣ የእውነተኛና ልባዊ መሰጠት መንፈስ ይህን ሁሉ ከሥሩ ለበጎ እንዴት በለወጠው ነበር! የተቀደሱ ነገሮችን የዓለም ነገሮች እንደ ሆኑ አድርገን እንይዛቸዋለን። የጌታ እራት ሥርዓት እንኳ ተራ ሃይማኖታዊ ተግባር ይሆናል፤ አስቀድሞ ዝግጅት፣ በኋላም ማሰላሰልና ጸሎት የለም። የጥምቀት ሥርዓት እንኳ ብዙ ግርማውን አጥቷል፤ በውስጡ ምንም የተለየ ነገር የሌለበት ባዶ ልማድ ሆኖ ወርዷል።

ዓለማዊ ጉዳዮቻችንን በጨው ለማጣፈጥ ብቻ ሳይሆን ጸሎታችንን እውነተኛ ጸሎት ለማድረግም የመሰጠት መንፈስ ያስፈልገናል። በእሑድ አምልኮ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሰኞ ሥራችንም ውስጥ የመሰጠትን መንፈስ ልናኖር ያስፈልገናል። የእግዚአብሔርን ህልውና ሁልጊዜ ለማስታወስ፣ ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ፣ ሁሉንም ነገር ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር ክብር ለማቅናት የመሰጠት መንፈስ ያስፈልገናል።

የመሰጠት መንፈስ እግዚአብሔርን በሁሉ ነገር ውስጥ ያኖራል። እግዚአብሔርን በጸሎታችንና ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄዳችን ብቻ ሳይሆን በሕይወት ጉዳዮች ሁሉ ውስጥ ያኖራል። «እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።» የመሰጠት መንፈስ የምድርን ተራ ነገሮች የተቀደሱ፣ ትንንሾቹንም ነገሮች ታላላቅ ያደርጋቸዋል። በዚህ የመሰጠት መንፈስ እሑድ ወደ ቤተ ክርስቲያን በሄድንበት በዚያው ተጽዕኖ ተመርተንና በዚያው መንፈስ ተነሣሥተን ሰኞ ወደ ሥራ እንሄዳለን። የመሰጠት መንፈስ ቅዳሜን ሰንበት ያደርጋል፤ ሱቁንና ቢሮውን ወደ እግዚአብሔር መቅደስ ይለውጣል።

የመሰጠት መንፈስ ሃይማኖትን ስስ የውጭ ቅብ ከመሆን አውጥቶ ወደ ነፍሳችን ሕይወትና ማንነት ውስጥ ያስገባዋል። በእርሱም ሃይማኖት ተራ ሥራ መሥራት መሆኑ ቀርቶ ልብ ይሆናል—የበለጸገ ደሙን በየደም ሥሩ የሚልክና በብርቱና በሚያበራ ሕይወት ትርታ የሚመታ ልብ።

የመሰጠት መንፈስ የሃይማኖት መዓዛ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖት የሚያድግበት ግንድና አገዳ ነው። ሃይማኖታዊ ተግባራትን ሁሉ ሰርጎ የሚገባና የሚያጣፍጥ ጨው ነው። ተግባርን፣ ራስን መካድንና መሥዋዕትን የሚያጣፍጥ ስኳር ነው። የሃይማኖታዊ ተግባራትን ድንዛዜ የሚያስወግድ ደማቅ ቀለም ነው። ቅለትን ይበትናል፤ ላይ ላዩን ብቻ የሆኑ የአምልኮ ዓይነቶችን ሁሉ ያባርራል፤ አምልኮንም ሥጋን፣ ነፍስንና መንፈስን በሰማያዊ ቅመሙ የሚያጠግብ ጭምትና ሥር የሰደደ አገልግሎት ያደርገዋል። እስቲ በፍጹም ቁም ነገር እንጠይቅ፦ ይህ ከሰማይ መላእክት እጅግ የላቀው፣ ይህ ሰማያዊ የመሰጠት መንፈስ፣ ይህ የምድር እጅግ ደማቅና ምርጥ መልአክ ትቶን ሄዷልን? የመሰጠት መልአክ በሄደ ጊዜ የጸሎት መልአክ ክንፉን ያጣል፤ የተበላሸና ፍቅር የለሽ ነገርም ይሆናል።

የመሰጠት ትጋት በጸሎት ውስጥ ነው። በራእይ መጽሐፍ በአራተኛው ምዕራፍ በስምንተኛው ቁጥር እንዲህ እናነባለን፦ «ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም።» የተመሰጠ አምልኮአቸው መነሻና ማዕከል የእግዚአብሔር ቅድስና ነው። ያ የእግዚአብሔር ቅድስና ትኩረታቸውን ይስባል፤ መሰጠታቸውንም ያቀጣጥላል። በእነርሱም ሆነ በሰማያዊ አምልኮአቸው ቀዝቃዛ፣ ደብዛዛ ወይም አሰልቺ የሆነ ምንም ነገር የለም። «ቀንና ሌሊት አያርፉም።» እንዴት ያለ ቅንዓት ነው! እንዴት ያለ የማይዝል ትጋትና የማያቋርጥ ተመስጦ ነው! የጸሎት አገልግሎት በዚህ ስም የሚገባው ከሆነ የትጋት አገልግሎት ነው፤ እግዚአብሔርንና ቅድስናውን የሚናፍቅ የማይታክትና ብርቱ ናፍቆት አገልግሎት ነው።

የመሰጠት መንፈስ በሰማይ ያሉትን ቅዱሳን ይሞላል፤ የሰማይ መላእክታዊ ፍጥረታትን አምልኮም ይለያል። በዚያ ሰማያዊ ዓለም መሰጠት የሌላቸው ፍጥረታት የሉም። እግዚአብሔር በዚያ አለ፤ ህልውናውም ራሱ የአክብሮትን፣ የመደነቅንና የልጅነት ፍርሃትን መንፈስ ይወልዳል። ከሞት በኋላ ከእነርሱ ጋር ተካፋዮች ልንሆን ብንወድ፣ ወደዚያ ከመድረሳችን በፊት በምድር ላይ የመሰጠትን መንፈስ መማር አለብን።

እነዚህ ሕያዋን ፍጥረታት እረፍት በሌለውና በማይታክተው ወደ እግዚአብሔር የመዘርጋት አቋማቸውና ለቅድስናው ባላቸው የተመሰጠ መሰጠት የእውነተኛ ጸሎትና የትጋቱ ፍጹም ምሳሌዎችና ማስረጃዎች ናቸው። ጸሎት መንደድ አለበት። ትጋቱ የሚያቃጥል መሆን አለበት። ግለት የሌለው ጸሎት ብርሃንና ሙቀት እንደሌላት ፀሐይ፣ ወይም ውበትና መዓዛ እንደሌለው አበባ ነው። ለእግዚአብሔር የተሰጠች ነፍስ የምትቃጠል ነፍስ ናት፤ ጸሎትም የዚያ ነበልባል ፍጥረት ነው። በእውነት ሊጸልይ የሚችለው ለቅድስና፣ ለእግዚአብሔርና ለሰማይ ሁለንተናው የሚነድ ሰው ብቻ ነው።

እንቅስቃሴ ብርታት አይደለም። ሥራ ቅንዓት አይደለም። መሯሯጥ መሰጠት አይደለም። እንቅስቃሴ ብዙ ጊዜ ያልታወቀ የመንፈሳዊ ድካም ምልክት ነው። በአምልኮ ውስጥ ለእውነተኛ መሰጠት ምትክ ሲደረግ ለእግዚአብሔር የመምሰል ሕይወት ጎጂ ሊሆን ይችላል። ውርንጭላ ከእናቱ ይልቅ እጅግ ንቁ ነው፤ እርሷ ግን ያለ ጫጫታ፣ ያለ ፉከራና ያለ ትርኢት ሸክሙን የምትጎትት የጋሪው ዋና ፈረስ ናት። ልጅ ከአባቱ ይልቅ ንቁ ነው፤ አባቱ ግን የአንድን መንግሥት አገዛዝና ሸክም በልቡና በትከሻው ተሸክሞ ሊሆን ይችላል። ስሜታዊ ግለት ከእምነት ይልቅ ንቁ ነው፤ ነገር ግን ተራሮችን ሊያፈልስ ወይም እምነት ሊያዝዛቸው ከሚችላቸው ሁሉን ቻይ ኃይሎች አንዱንም ወደ ሥራ ሊጠራ አይችልም።

ደካማ፣ ሕያው መስሎ የሚታይና ለትርኢት የሆነ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ከብዙ ምክንያቶች ሊመነጭ ይችላል። በዛሬው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ብዙ መሯሯጥ፣ ብዙ መንቀሳቀስ፣ ወዲያና ወዲህ ብዙ መሄድ አለ፤ የሚያሳዝነው ግን የእውነተኛና ልባዊ መሰጠት መንፈስ በሚያስገርም ሁኔታ ጎድሏል። እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ካለ ጥልቅ መሠረት ያለው እንቅስቃሴ ከእርሱ ይመነጫል። ነገር ግን ከድካም ሳይሆን ከብርታት የሚመነጭ እንቅስቃሴ ነው። ብዙና ጠንካራ ጥልቅ ሥሮች ያሉት እንቅስቃሴ ነው።

በነገሮች ተፈጥሮ ሃይማኖት ብዙውን እድገቱን ከመሬት በላይ ማሳየት አለበት። ብዙ ነገር ይታያል፤ ለዓይንም ግልጽ ይሆናል። በመልካም ሥራዎች የበዛ የቅዱስ ሕይወት አበባና ፍሬ መታየት አለበት። ከዚህ ሌላ ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ከመሬት በላይ ያለው እድገት በማይታይ ሕይወትና በተሰወሩ ሥሮች ብርቱ እድገት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። በውጭ የሚታየው ሃይማኖት ሥሮቹ በታደሰው ባሕርይ ውስጥ በጥልቅ መውረድ አለባቸው። ውጫዊው ጥልቅ ውስጣዊ መሠረት ሊኖረው ይገባል። የማይታየውና ከመሬት በታች ያለው እድገት ብዙ መሆን አለበት፤ ያለዚያ ሕይወቱ ደካማና አጭር ዕድሜ ያለው፣ ውጫዊ እድገቱም የታመመና ፍሬ የለሽ ይሆናል።

በነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ እነዚህ ቃላት ተጽፈዋል፦

«እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ አይደክሙም።» (ኢሳይያስ 40:31)።

እጅግ ብርቱ፣ የማያልቅና የማይታክት ዓይነት የሆነው የእንቅስቃሴና የብርታት ጉዳይ ሁሉ መነሻው ይህ ነው። ይህ ሁሉ እግዚአብሔርን የመጠባበቅ ውጤት ነው።

በልምምድ የተፈጠረ፣ በስሜታዊ ግለት የተወለደ፣ የሥጋ ድካም ውጤት የሆነ፣ ከተለዋዋጭና አጭር ዕድሜ ካላቸው ኃይሎች የመነጨ ብዙ እንቅስቃሴ ሊኖር ይችላል። እንቅስቃሴ ብዙ ጊዜ ይበልጥ ጽኑና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን በማጣት የሚገኝ ነው፤ ባብዛኛውም ጸሎትን ፈጽሞ ቸል በማለት ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ እስኪሳነን ድረስ በእግዚአብሔር ሥራ መጠመድ፣ ስለ ሥራው ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ጊዜ ሳይወስዱ የቤተ ክርስቲያንን ሥራ በመሥራት መጠመድ ወደ ኋላ የመመለስ አውራ ጎዳና ነው፤ ብዙ ሰዎችም የማትሞተውን ነፍሳቸውን እየጎዱ በዚያ ተመላልሰዋል።

ታላቅ እንቅስቃሴ፣ ታላቅ ስሜታዊ ግለትና ለሥራው ብዙ ሆታ ቢኖርም፣ የጸሎት ጸጋዎች ካልተኮተኮቱና ካልበሰሉ ሥራውና እንቅስቃሴው ዕውርነት ብቻ ይሆናሉ።

ገጽ 1 / 1 · 8 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ