መለኮታዊ ፈውስ
የእምነት መንገድ

ምዕራፍ 7 · 3 ደቂቃ ንባብ

የእምነት መንገድ

«ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ። አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ» (ማርቆስ 9:24)።

እነዚህ ቃላት መዳንንና የእግዚአብሔርን ስጦታዎች ለሚፈልጉ በሺህ ለሚቆጠሩ ነፍሳት እርዳታና ብርታት ሆነዋል። የተነገሩት በሥቃይ ስላለ ልጅ፣ ከጌታ ኢየሱስ ፈውስን በመፈለግ በሚደረግ የእምነት ትግል ውስጥ መሆኑን አስተውል። በእነርሱም በአንዲት ነፍስ ውስጥ በእምነትና ባለማመን መካከል ትግል ሊነሣ እንደሚችል፣ በኢየሱስና ድውያንን ለመፈወስ ባለው ሁሉን በሚችል ኃይሉ ወደ ማመን የምንደርሰውም ያለ ትግል እንዳልሆነ እናያለን። በዚህም የአዳኙን ኃይል በተሞክሮ ለማወቅ የሚያስፈልገንን ማበረታቻ እናገኛለን።

እዚህ በተለይ የምናገረው ጌታ ኢየሱስ በዚህ ዘመን ያለ ምድራዊ መድኃኒቶች ለመፈወስ ያለውን ኃይልም ሆነ ፈቃድ ለማይጠራጠሩ፣ ነገር ግን ፈውስን ለራሳቸው ለመቀበል ድፍረት ለሚጎድላቸው ሕሙማን ነው። በክርስቶስ መለኮታዊ ኃይል ያምናሉ፤ ለመፈወስ ያለውን በጎ ፈቃድም በጠቅላላው ያምናሉ፤ በመጻሕፍት ወይም በዘመናችን በጌታ ብቻ በተደረጉ ፈውሶች አማካይነት ጌታ እነርሱንም እንኳ ሊረዳቸው እንደሚችል በአእምሮ ተረድተዋል፤ ነገር ግን ፈውስን ከመቀበልና በእምነት፦ «ጌታ ሰምቶኛል፤ እየፈወሰኝ እንደ ሆነ አውቃለሁ» ከማለት ወደ ኋላ ይላሉ።

በመጀመሪያ ያለ እምነት ማንም ሊፈወስ እንደማይችል አስተውል። በሥቃይ ያለው ልጅ አባት ኢየሱስን፦ «ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም» ባለው ጊዜ፣ ኢየሱስ፦ «ማመን ብትችል» ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ ለመፈወስ ኃይል ነበረው፤ ሊያደርገውም ዝግጁ ነበረ፤ ነገር ግን ኃላፊነቱን በሰውየው ላይ ይጥላል። «ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል» (የተሻሻለው ትርጉም)። ፈውስህን ከኢየሱስ ለማግኘት መጸለይ ብቻ በቂ አይደለም። ያለ እምነት የሚደረግ ጸሎት ኃይል የለውም። ድውዩን የሚያድነው «የእምነት ጸሎት» ነው (ያዕቆብ 5:15)። ፈውስን አስቀድመህ ከጌታ ለምነህ ከሆነ፣ ወይም ሌሎች ለአንተ ለምነውልህ ከሆነ፣ ምንም ለውጥ ሳይሰማህ በፊት በእምነት፦ «በእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን እንደሚሰማኝና እንደምፈወስ እርግጠኛ ነኝ» ለማለት መቻል አለብህ። ለአንተ ማመን ማለት አካልህን ፈጽመህ በጌታ እጅ መስጠትና ራስህን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ መተው ማለት ነው። እምነት በአካል ላይ የሚታወቅ ለውጥ ገና ሳይኖር እንኳ ፈውስን ከጌታ እንደሚወጣ መንፈሳዊ ጸጋ አድርጎ ይቀበላል። እምነት እግዚአብሔርን ሊያከብርና፦ «ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ. . . ደዌዬንም ሁሉ የሚፈውስ» (መዝሙር 103:1—3) ሊል ይችላል። ጌታ ይፈውስ ዘንድ ይህን እምነት ይሻል።

ነገር ግን እንዲህ ያለው እምነት እንዴት ይገኛል? በልብህ ውስጥ የምታገኘውን አለማመን ለአምላክህ ንገረው፤ ከእርሱም እንዲያድንህ በእርሱ ተማመን። እምነት ፈውስህን ከጌታ የምትገዛበት ገንዘብ አይደለም። አስፈላጊውን እምነት በአንተ ውስጥ ሊያነቃቃውና ሊያሳድገው የሚወድ እርሱ ነው። የብላቴናው አባት፦ «አለማመኔን እርዳው» ብሎ ጮኸ።

እምነቱ እንዳይጎድል የልቡ ጽኑ ምኞት ነበረ። በቃሉ ላይ ተመሥርተህ እርሱን ለማመን ያለብህን ችግር ሁሉ ለጌታ ተናዘዝ፤ ከዚህ አለማመን ነጻ ልትሆን እንደምትወድ፣ ቃሉን ብቻ ለመስማት ቈርጠህ አለማመንህን ወደ እርሱ እንደምታመጣውም ንገረው። ስለ አለማመንህ በማዘን ጊዜ አታጥፋ፤ ነገር ግን ወደ ኢየሱስ ተመልከት። የፊቱ ብርሃን በእርሱ ለማመን ኃይልን እንድታገኝ ያስችልሃል (መዝሙር 44:3)። በእርሱ እንድትታመን ይጠራሃል፤ አድምጠው፤ በጸጋውም እምነት በአንተ ውስጥ ድል ያደርጋል። እንዲህ በለው፦ «ጌታ ሆይ፣ በእኔ ውስጥ ያለው አለማመን አሁንም ይታወቀኛል። ፈውሴን የሚሠራውን እርሱን ገንዘቤ ስላደረግሁ ፈውሴ የተረጋገጠ እንደ ሆነ ማመን ይከብደኛል። ቢሆንም ይህን አለማመን ማሸነፍ እወዳለሁ። አንተ ጌታ ሆይ፣ ድልን ትሰጠኛለህ። ማመን እወዳለሁ፤ ለማመን ቈርጫለሁ፤ በጸጋህም ማመን እችላለሁ ለማለት እደፍራለሁ። አዎን ጌታ ሆይ፣ አምናለሁ፤ አለማመኔን ልትረዳ ትመጣለህና።» አለማመን ተሸንፎ የሚወገደው ከጌታ ጋር በቅርብ ኅብረት ስንሆንና ልባችን ለልቡ ምላሽ ሲሰጥ ነው።

ያለህን እምነት መመስከርም ያስፈልጋል። ጌታ የሚነግርህን፣ ከሁሉም በላይ እርሱ ማን እንደ ሆነ ለማመን ቍረጥ። በተስፋ ቃሎቹ ላይ ፈጽመህ ተደገፍ። «የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል።» «ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ» (ዘጸአት 15:26)። ወደ ኢየሱስ ተመልከት፤ እርሱ «ደዌያችንን ተሸከመ» (ማቴዎስ 8:17)፤ ወደ እርሱ የመጡትንም ሁሉ ፈወሰ። አሁን በሰማይ ያለውን የኢየሱስን መገኘት በልብህ እንዲገልጥ፣ የጸጋውንም ኃይል በአካልህ ደግሞ እንዲሠራ በመንፈስ ቅዱስ ተማመን። መሻሻል እስኪሰማህ ወይም ተጨማሪ እምነት እስኪኖርህ ሳትጠብቅ ጌታን አመስግን። አመስግነው፤ ከዳዊትም ጋር፦ «አቤቱ አምላኬ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አንተም ፈወስኸኝ» (መዝሙር 30:2) በል። መለኮታዊ ፈውስ በአካል ላይ ያለው ውጤት ከመሰማቱ በፊት በመንፈሳዊ መንገድና በእምነት ብቻ የሚቀበሉት መንፈሳዊ ጸጋ ነው። እንግዲያስ ተቀበለው፤ ለእግዚአብሔርም ክብርን ስጥ። ጌታ ኢየሱስ ርኵሱ መንፈስ ከልጁ እንዲወጣ ባዘዘው ጊዜ፣ መንፈሱ እጅግ አንፈራገጠው፤ ብዙዎችም፦ «ሞተ» እስኪሉ ድረስ እንደ ሙት ሆነ። ስለዚህ ሕመምህ ወዲያው ባይለቅህ፣ ሰይጣንና የራስህ አለማመን ሊያሸንፉህ ቢሞክሩ፣ አትስማቸው፤ ፈዋሽህ ከሆነው ከኢየሱስ ጋር አጥብቀህ ተጣበቅ፤ እርሱም በእርግጥ ይፈውስሃል።

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል