ምዕራፍ 6 · 3 ደቂቃ ንባብ
እንደ እምነት መጠን
«ኢየሱስም ለመቶ አለቃ። ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ» (ማቴዎስ 8:13)።
ይህ የመጽሐፍ ክፍል ከመንግሥተ ሰማያት ዋና ዋና ሕግጋት አንዱን በፊታችን ያቀርባል። እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያለውን አካሄድና ከጌታ ጋር ያለንን ግንኙነት ለመረዳት ይህን ሕግ በሚገባ ማስተዋልና ከእርሱም አለማፈንገጥ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ስጦታዎቹን የሚሰጠው ወይም የሚከለክለው እንደ እያንዳንዱ እምነት ወይም አለማመን ብቻ አይደለም፤ ስጦታዎቹም በብዙ ወይም በጥቂት መጠን የሚሰጡት በሚቀበላቸው እምነት ልክ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን የመምረጥ መብት ያከብራል። ስለዚህ ሊባርከን የሚችለው እያንዳንዱ ራሱን ለመለኮታዊ ሥራው አሳልፎ በሰጠበትና ልቡን ሁሉ ለእርሱ በከፈተበት መጠን ብቻ ነው። በእግዚአብሔር ማመን ሁሉን ከእግዚአብሔር ለመቀበል ልብን ፈጽሞ ከመክፈት በቀር ሌላ አይደለም፤ ስለዚህ ሰው መለኮታዊውን ጸጋ ሊቀበል የሚችለው እንደ እምነቱ ብቻ ነው፤ ይህም ለሌላው የእግዚአብሔር ጸጋ ሁሉ እንደሚሠራ ለመለኮታዊ ፈውስም እንዲሁ ይሠራል።
ከሕመም ሊገኙ የሚችሉት መንፈሳዊ በረከቶች ይህን እውነት ያጸኑታል። ብዙ ጊዜ ሁለት ጥያቄዎች ይጠየቃሉ፦ (1) ልጆቹ አንዳንድ ጊዜ ለረጅም ጊዜ በሕመም እንዲቆዩ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለምን? (2) መለኮታዊ ፈውስ ከሕመሙ ራሱ የሚበልጥ መንፈሳዊ በረከት እንደሚያመጣ የታወቀ ነገር ከሆነ፣ እግዚአብሔር ከልጆቹ አንዳንዶቹ ለብዙ ዓመታት ታመው እንዲቆዩ ለምን ይፈቅዳል? በዚህስ ሁኔታ ሳሉ በቅድስናና ከእርሱ ጋር ባለ ኅብረት ለምን ይባርካቸዋል? ለእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች መልሱ እግዚአብሔር ለልጆቹ የሚሰጣቸው እንደ እምነታቸው መሆኑ ነው። ቤተ ክርስቲያን ዓለማዊ በሆነችበት መጠን በመለኮታዊ ፈውስ ላይ ያላት እምነት እየቀነሰ ሄዶ በመጨረሻ እስከ መጥፋት እንደ ደረሰ ቀደም ብለን ለማስተዋል አጋጣሚ አግኝተናል። አማኞች ከሕመማቸው እንዲፈወሱ እግዚአብሔርን ሊለምኑ እንደሚችሉ፣ በዚህም ሊቀደሱና ለአገልግሎቱ ሊዘጋጁ እንደሚችሉ የሚያውቁ አይመስሉም። ለፈቃዱ መገዛትን ብቻ ወደ መፈለግና ሕመምን ከዓለም የሚለዩበት መንገድ አድርገው ወደ መቍጠር ደርሰዋል። በእንዲህ ያለው ሁኔታ ጌታ የለመኑትን ይሰጣቸዋል። ከዚህ የበለጠ ሊሰጣቸው፣ የእምነት ጸሎት በቀረበ ጊዜ ፈውስን ሊሰጣቸው ዝግጁ በሆነ ነበር፤ እነርሱ ግን ይህን ለመቀበል እምነት ጐደላቸው። እግዚአብሔር ምንም ያህል ደካሞች ቢሆኑ ልጆቹን ሁልጊዜ ባሉበት ስፍራ ያገኛቸዋል። ስለዚህ በፍጹም ልባቸው እርሱን ለመቀበል የወደዱ ድውያን፣ ፈቃዳቸው ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር እንዲስማማ በነበራቸው ምኞት የሕመሙን ፍሬ ከእርሱ ተቀብለዋል። በተጨማሪም እግዚአብሔር መገዛታቸውን እንደ ተቀበለ ማስረጃ ሆኖ ፈውስን ሊቀበሉ በቻሉ ነበር፤ ይህ ካልሆነ ግን ፈውስን ለመለመን እምነት ስለ ጐደላቸው ነው።
«እንዳመንህ ይሁንልህ።» እነዚህ ቃላት ለሌላም ጥያቄ መልስ ይሰጣሉ፤ ጥያቄውም ይህ ነው፦ በጌታ በኢየሱስ ከተፈወሱት ሰዎች አብዛኞቹ ከነበረባቸው ሥቃይ ከመዳን ያለፈ ምንም እንዳልተቀበሉ፣ በመንፈስም እንደ ተባረኩ አንዳች ማስረጃ እንዳላሳዩ እየታየ፣ መለኮታዊ ፈውስ ይህን ያህል መንፈሳዊ በረከት ያመጣል እንዴት ትላለህ? እዚህም ደግሞ እንዳመኑ እንዲሁ ሆነላቸው።
ብዙ ድውያን የሌሎችን መፈወስ ካዩ በኋላ ለመፈወስ ብቻ የሚበቃ ያህል በኢየሱስ ተማመኑ፤ ኢየሱስም ለነፍሳቸው ሌላ በረከት ሳይጨምር የለመኑትን ሰጣቸው። ጌታ ከማረጉ በፊት አሁን ወደ ሰው ልብ ያለውን ያህል ነጻ መግቢያ አልነበረውም፤ ምክንያቱም «መንፈስ ገና አልወረደም ነበር» (ዮሐንስ 7:39)። የድውያን መፈወስ በዚያን ጊዜ ለሥጋ ከሆነ በረከት ብዙም የሚያልፍ አልነበረም። ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ፣ ያዕቆብም ለተበተኑት ለአሥራ ሁለቱ ነገዶች በጻፈው መልእክቱ እንደሚነግሩን (1ኛ ቆሮንቶስ 11:31, 32፤ ያዕቆብ 5:16)፣ የኃጢአት መወቀስና መናዘዝ ለአማኙ የሚቀበለው የመጀመሪያ ጸጋ፣ ፈውስንም ለማግኘት አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ የሆኑት ከጊዜ በኋላ፣ በመንፈስ ዘመን ብቻ ነው። ስለዚህ ልንቀበለው የምንችለው የመንፈሳዊ ጸጋ ደረጃ፣ ለውጫዊ መገለጡም ቢሆን፣ ይልቁንም በውስጣዊ ሕይወታችን ላይ ላለው ተጽዕኖ፣ በእምነታችን መጠን ላይ የተመሠረተ ነው።
ፈውስን ለሚጠባበቅና ኢየሱስን መለኮታዊ ፈዋሹ አድርጎ ሊያውቀው ለሚሻ ለእያንዳንዱ ሕመምተኛ ይህን እንመክራለን፤ በአለማመኑ እንዳይሰናከል፣ የእግዚአብሔርንም የተስፋ ቃሎች እንዳይጠራጠር፣ በዚህም እንደሚገባው «ለእግዚአብሔር ክብርን እየሰጠ በእምነት የበረታ» እንዲሆን ነው። «እንዳመንህ ይሁንልህ።» በፍጹም ልብህ በሕያው እግዚአብሔር ብትታመን በብዛት ትባረካለህ፤ አትጠራጠር።
የእምነት ድርሻ ሁልጊዜ በሰው ዓይን የማይቻል ወይም እንግዳ የሚመስለውን ነገር አጥብቆ መያዝ ነው። ስለ ክርስቶስ ሞኞች ተብለን ልንቈጠር ፈቃደኞች እንሁን (1ኛ ቆሮንቶስ 4:10)። ሌሎች ገና ሊቀበሉት የማይችሉትን ነገር በእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን ስለምናምን፣ በዓለምና እነዚህን ነገሮች በማያውቁ ክርስቲያኖች ዓይን እንደ አእምሮ ደካሞች መቈጠርን አንፍራ። ስለዚህ እግዚአብሔር መልስ ሊሰጥህ ቢዘገይ ወይም ሕመምህ ቢጸናብህ እንኳ በመጠባበቅህ ተስፋ አትቍረጥ። እግርህን በማይናወጠው በእግዚአብሔር ቃል ዓለት ላይ አንድ ጊዜ በጽኑ ካቆምህ፣ አንተ ከአካሉ ብልቶች አንዱና የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ስለ ሆንህም ሁሉን ቻይነቱን በአካልህ እንዲገልጥ ጌታን ከለመንህ በኋላ፣ ስለ አንተ ኃላፊነትን እንደ ወሰደ፣ ስለ አካልህም ራሱን ተጠያቂ እንዳደረገ፣ የሚፈውስ ኃይሉም በአንተ እንዲከበር እንደሚመጣ በጽኑ በመተማመን በእርሱ ማመንህን ቀጥል።
ምዕራፍ 6 ተጠናቋል
እንደ እምነት መጠን