ምዕራፍ 30 · 2 ደቂቃ ንባብ
በጌታ ስም መቀባት
«ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት» (ያዕቆብ 5:14)።
በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው።» እነዚህ ቃላት ክርክር አስነሥተዋል። አንዳንዶች ቅዱስ ያዕቆብ ያለ መድኃኒት በእምነት ጸሎት ብቻ እንዲጠጉ ማዘዝ ይቅርና፣ በተቃራኒው በዘይት መቀባትን ሊሠራበት የሚገባ መድኃኒት አድርጎ እንደ ጠቀሰ፣ በጌታ ስም መቀባትም ሕመምተኛውን በዘይት ከማሸት ሌላ ትርጕም እንዳልነበረው ከእነዚህ ቃላት ለመደምደም ሞክረዋል። ነገር ግን ይህ ትእዛዝ ለሕመም ዓይነቶች ሁሉ የሚሠራ ስለ ሆነ፣ ይህ በሕመም ሁሉ ላይ ተአምራዊ ኃይል ለዘይት መስጠት ይሆናል። እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ በዘይት ስለ መቀባት የሚነግረንን፣ ለእነዚህም ሁለት ቃላት የሚሰጠውን ትርጕም እንመልከት።
በምሥራቅ የሚኖሩ ሰዎች ከመታጠቢያ ሲወጡ ሰውነታቸውን በዘይት መቀባት ልማዳቸው ነበር፤ ይህም በሞቃት አገር እጅግ የሚያረካ ነበር። ደግሞም ለእግዚአብሔር ልዩ አገልግሎት የተጠሩ ሁሉ ለእግዚአብሔር የመቀደሳቸው፣ ጥሪያቸውንም ለመፈጸም ከእርሱ የሚቀበሉት ጸጋ ምልክት ሆኖ በዘይት ሊቀቡ እንደሚገባቸው እናያለን። ስለዚህ ካህናቱንና ማደሪያውን ለመቀባት ይውል የነበረው ዘይት «እጅግ ቅዱስ» ሆኖ ይቈጠር ነበር (ዘጸአት 30:22—32)፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘይት መቀባት በሚናገርበት ስፍራ ሁሉ የቅድስናና የመቀደስ ምሳሌ ነው። ዘይት እንደ መድኃኒት ይሠራበት እንደ ነበር የሚያሳይ ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትም አናገኝም።
በእርግጥ አንድ ጊዜ በዘይት መቀባት ከሕመም ጋር ተያይዞ ተጠቅሶአል፤ ነገር ግን በዚያ ስፍራ የተጠቀሰው እንደ መድኃኒት ሳይሆን እንደ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንደ ሆነ ግልጥ ነው። በማርቆስ 6:13 አሥራ ሁለቱ «ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው» ብለን እናነባለን። በዚህ ስፍራ ድውያንን መፈወስ ከአጋንንት ማውጣት ጋር ጎን ለጎን ይሄዳል፤ ሁለቱም የተአምራዊ ኃይል ውጤቶች ናቸው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ በላካቸው ጊዜ ያዘዛቸው ተልእኮ እንዲህ ያለ ነበር፦ «እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው» (ማቴዎስ 10:1)። ስለዚህ አጋንንትን እንዲያወጡም ሆነ ድውያንን እንዲፈውሱ ያስቻላቸው ያው አንድ ኃይል ነበር።
ነገር ግን አሥራ ሁለቱ ያደረጉት መቀባት ምንን ያመለክት እንደ ነበር ለማወቅ እንሞክር። በብሉይ ኪዳን ዘይት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ምሳሌ ነበረ፦ «የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና» ወዘተ. (ኢሳይያስ 61:1)። በአዲስ ኪዳን ስለ ጌታ ኢየሱስ፦ «እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው» (የሐዋርያት ሥራ 10:38) ተብሎ ተነግሮአል፤ ስለ አማኞችም፦ «እናንተም ከቅዱሱ ቅባት [መቀባት፣ የተሻሻለው ትርጉም] ተቀብላችኋል» (1ኛ ዮሐንስ 2:20) ተብሎ ተነግሮአል። አንዳንድ ጊዜ ሰው እምነቱን እንዲደግፍና መንፈሳዊውን ትርጕም እንዲጨብጥ ሊረዳው የሚችል፣ ለስሜቶቹ የሚናገር የሚታይ ምልክት ያስፈልገዋል።
ስለዚህ መቀባቱ ፈውስን የሚሰጠውን የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ለታመመው ሊያመለክትለት ይገባል።
እንግዲህ ከእምነት ጸሎት በተጨማሪ መቀባትም ያስፈልገናልን? የሚያዝዘው የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ ስለ ፈውስ ከሚጸልዩት አብዛኞቹ መቀባትን የሚቀበሉት ትምህርቱን ለመከተል ነው፤ የግድ አስፈላጊ ነው ብለው ስለሚቈጥሩት ሳይሆን በሁሉ ነገር ለእግዚአብሔር ቃል ለመገዛት ዝግጁ መሆናቸውን ለማሳየት ነው። ጌታ ኢየሱስ በሰጠው በመጨረሻው ተስፋ የፈውስ ኃይል ሲተላለፍ አብሮ እንዲሄድ ያዘዘው መቀባትን ሳይሆን እጅ መጫንን ነው (ማርቆስ 16:18)። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በገረዘው ጊዜና ራሱ ልዩ ስእለት በተሳለ ጊዜ፣ የወንጌል ነጻነት በዚህ እስካልተጐዳ ድረስ የብሉይ ኪዳንን ሥርዓቶች ለመጠበቅ ተቃውሞ እንደሌለው ለማሳየት ነበር። በተመሳሳይ መንገድ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ራስ የነበረው ያዕቆብ የአባቶቹን ሥርዓቶች በተቻለ መጠን በመጠበቅ ታማኝ ሆኖ የመንፈስ ቅዱስን ሥርዓት ቀጠለ። እኛም መቀባትን እንደ መድኃኒት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ብርቱ ኃይል መያዣ፣ እምነትን የማጠንከሪያ መንገድ፣ በታመመውና እርሱን በዘይት እንዲቀቡ በተጠሩት የቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል የመገናኛና የኅብረት ነጥብ አድርገን ልንመለከተው ይገባናል።
«ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ» (ዘጸአት 15:26)።
ምዕራፍ 30 ተጠናቋል
በጌታ ስም መቀባት