መለኮታዊ ፈውስ
መታዘዝና ጤና

ምዕራፍ 27 · 3 ደቂቃ ንባብ

መታዘዝና ጤና

«በዚያም ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤ እንዲህም አለ፦ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም የቀናውን ብታደርግ፥ ትእዛዛቱንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ካመጣሁት ደዌ ሁሉ አንዱን ስንኳ አላመጣብህም፤ ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ» (ዘጸአት 15:25, 26)።

ጌታ ይህን ሥርዓት ለሕዝቡ የሰጠው በማራ ነበር። እስራኤል እምነታቸው በምድረ በዳ በማራ ውኃ የተፈተነው ገና ከግብፅ ቀንበር እንደ ተላቀቁ ነበር። ጌታ እርሱን እስከ ታዘዙ ድረስ በግብፃውያን ላይ ካመጣው ደዌ አንዱንም በእስራኤል ልጆች ላይ እንደማያመጣ ተስፋ የሰጠው መራራውን ውኃ ካጣፈጠ በኋላ ነበር። ሌሎች ፈተናዎች ይደርሱባቸው ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ እንጀራና ውኃ ሊያጡ፣ ታላላቅ አደጋዎችም ሊገጥሟቸው ይችሉ ነበር፤ ይህ ሁሉ ቢታዘዙም እንኳ ሊደርስባቸው ይችል ነበር፤ ሕመም ግን ሊነካቸው አይገባም ነበር። ገና በሰይጣን ኃይል ሥር ባለ ዓለም ውስጥ ከውጭ ለሚመጡ ጥቃቶች ዒላማ ሊሆኑ ይችሉ ነበር፤ አካላቸው ግን በሕመም አይጨቆንም ነበር፤ እግዚአብሔር ከእርሱ አድኖአቸዋልና። «የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ... በግብፃውያን ላይ ካመጣሁት ደዌ ሁሉ አንዱን ስንኳ አላመጣብህም፤ ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ» ብሎ አልተናገረምን? ደግሞም በሌላ ስፍራ፦ «አምላካችሁን እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ፥ ... ደዌንም ከመካከልህ አርቃለሁ» ይላል (ዘጸአት 23:25፤ ደግሞም ዘሌዋውያን 26:14,16፤ ዘዳግም 7:15, 23፤ 28:15—61 አንብብ)።

ይህ እጅግ ታላቅ ትርጕም ወዳለው እውነት ትኵረታችንን ይስባል፤ እርሱም በመታዘዝና በጤና መካከል፣ የነፍስ ጤና በሆነው በቅድስናና የአካልን ጤና በሚያረጋግጠው በመለኮታዊ ፈውስ መካከል ያለው የጠበቀ ግንኙነት ነው— ሁለቱም ከእግዚአብሔር በሚመጣው ድኅነት ውስጥ ይጠቃለላሉ። በብዙ ቋንቋዎች እነዚህ ሦስት ቃላት፣ ድኅነት፣ ፈውስና ቅድስና፣ ከአንድ ሥር የወጡና አንድ መሠረታዊ ሐሳብ የሚያቀርቡ መሆናቸው ልብ ሊባል የሚገባው ነው። (ለምሳሌ በጀርመንኛ Heil ድኅነት፣ Heilung ፈውስ፣ Heilichung ቅድስና ነው።) ድኅነት አዳኙ ያስገኘልን ቤዛነት ነው፤ ጤና ደግሞ ከመለኮታዊው ፈዋሽ ወደ እኛ የሚመጣው የአካል ድኅነት ነው፤ በመጨረሻም ቅድስና እውነተኛ ድኅነትና እውነተኛ ጤና እግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆነ ቅዱስ በመሆን እንደሚገኙ ያሳስበናል። እንግዲህ ኢየሱስ በእውነት የሕዝቡ አዳኝ የሆነው ለአካል ጤናን ለነፍስም ቅድስናን በመስጠት ነው። ጥቅሳችን በሕይወት ቅድስናና በአካል ፈውስ መካከል ያለውን ግንኙነት በግልጽ ይናገራል። ይህን የሚያስረዱት አነጋገሮች ሆን ተብለው የተደጋገሙ ይመስላሉ፦ «አጥብቀህ ብትሰማ..፣ የቀናውን ብታደርግ..፣ ብታደምጥ... ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፣ ምንም ደዌ አልሰድብህም።»

የእውነተኛ መታዘዝና ቅድስና ሁሉ መክፈቻ እዚህ አለን። በቃሉ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሚገባ የምናውቅ ብዙ ጊዜ ይመስለናል፤ ነገር ግን ይህ እውቀት መታዘዝን የማያፈራው ስለ ምንድን ነው? ለመታዘዝ በማድመጥ መጀመር ስላለብን ነው። «የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ..፣ ብታደምጥም... ።» የእግዚአብሔር ፈቃድ በሰው ድምፅ ወይም መጽሐፍ በማንበብ ብቻ እስከ ደረሰኝ ድረስ በእኔ ላይ ያለው ኃይል ጥቂት ሊሆን ይችላል፤ ከእግዚአብሔር ጋር ቀጥተኛ ኅብረት ውስጥ ብገባና ድምፁን ባደምጥ ግን ትእዛዙ እንዲፈጸም የሚያስችል ሕያው ኃይል ይለብሳል። ክርስቶስ ሕያው ቃል ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ድምፁ ነው። ድምፁን ማድመጥ ማለት የራሳችንን ፈቃድና ጥበብ ሁሉ መካድ፣ ከመንፈስ ቅዱስ አመራር በቀር ሌላ አመራር እንዳንጠብቅ ለሌላ ድምፅ ሁሉ ጆሮን መዝጋት ነው። የተዋጀ ሰው መመራት እንደሚያስፈልገው አገልጋይ ወይም ልጅ ነው፤ ፈጽሞ የእግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ ሁለንተናውም፣ መንፈሱ፣ ነፍሱና ሥጋው እግዚአብሔርን ሊያከብር እንደሚገባው ያውቃል።

ነገር ግን ይህ ከአቅሙ በላይ እንደ ሆነ፣ የሚያስፈልገውንም አመራር ሰዓት በሰዓት መቀበል እንዳለበት እንዲሁ ያውቃል። ደግሞም መለኮታዊው ትእዛዝ ለእርሱ የሞተ ፊደል ሆኖ እስካለ ድረስ ብርታትንና ጥበብን ሊሰጠው እንደማይችል፣ የሚፈልገውንም ብርታት የሚያገኘው በትኵረት ሲያደምጥ ብቻ እንደ ሆነ ያውቃል፤ ስለዚህ ያደምጣል፤ በዚህም የእግዚአብሔርን ሕግጋት መጠበቅን ይማራል። ቅዱስ ሕይወት ማለት ይህ የማድመጥና የተግባር፣ ራስን የመካድና የመሰቀል ሕይወት ነው። ጌታ ወደዚህ ሕይወት የሚያመጣን በመጀመሪያ በሕመም ነው፤ የጐደለንንም እንድናስተውል ያደርገናል፤ ከዚያም ደግሞ ነፍስን የእግዚአብሔርን ድምፅ ዘወትር ወደ ማድመጥ ወደዚህ ሕይወት በሚጠራው ፈውስ ነው።

አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በመለኮታዊ ፈውስ ውስጥ ለአካል ከሚሆን ጊዜያዊ በረከት በቀር ሌላ አያዩም፤ ቅዱሱ አምላካችን በሰጠው ተስፋ ግን ዓላማው እኛን ቅዱሳን ማድረግ ነው። የቅድስና ጥሪ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀን በቀን ይበልጥ እየበረታና እየጠራ ይሰማል። እግዚአብሔር ክርስቶስን እንዲመስሉ እንደሚፈልግ የሚገነዘቡ አማኞች እየበዙ ነው፤ ጌታም የፈውስ ኃይሉን እንደ ገና መጠቀም ጀምሯል፤ በዚህም በዘመናችን እንኳ የእስራኤል ቅዱስ «ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ» የሚለው እርሱ እንደ ሆነ፣ ሕዝቡንም በአካል ጤናና በመታዘዝ ሊጠብቃቸው ፈቃዱ እንደ ሆነ ሊያሳየን ይሻል።

ከጌታ ፈውስን የሚጠብቅ በደስታ ይቀበለው። ከእርሱ የሚፈለገው በራሱ ብርታት ላይ የተመሠረተ የሕግ መታዘዝ አይደለም። አይደለም፤ በተቃራኒው እግዚአብሔር የሚጠይቀው የሕፃን ልጅን ራስን መተው፣ የሚያደምጥና ለመመራት የሚፈቅድ ትኵረትን ነው። እግዚአብሔር ከእርሱ የሚጠብቀው ይህን ነው፤ የአካልም ፈውስ የዚህ የልጅነት እምነት ፍሬ ይሆናል፤ ጌታ አካልን የሚፈውስና ነፍስን የሚቀድስ ኃያል አዳኝ ሆኖ ራሱን ይገልጥለታልና።

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል