ምዕራፍ 26 · 3 ደቂቃ ንባብ
የእግዚአብሔር ፈቃድ
«ፈቃድህ ትሁን» (ማቴዎስ 6:10)። «ጌታ ቢፈቅድ» (ያዕቆብ 4:15)።
በሕመም ዘመን ሐኪሞችና መድኃኒቶች ሲሳኑ፣ ብዙውን ጊዜ ሰዎች እዚህ ወደ ጠቀስናቸው ቃላት ይጠጋሉ፤ እነዚህም ቃላት በቀላሉ በመለኮታዊ ፈውስ መንገድ ላይ ዕንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። «እንዴት ማወቅ እችላለሁ፣» ተብሎ ይጠየቃል፣ «ታምሜ እንድቆይ የእግዚአብሔር ፈቃድ አለመሆኑን? ይህ ጥያቄ መልስ ሳያገኝ እስካለ ድረስ ስለ ፈውስ እንዴት ማመን እችላለሁ? ስለ እርሱስ በእምነት እንዴት መጸለይ እችላለሁ?» እዚህ እውነትና ስሕተት የሚነካኩ ይመስላሉ። በእርግጥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እየለመንን እንደ ሆነ እርግጠኞች ካልሆንን በእምነት መጸለይ አይቻልም። አንዱ፦ «እችላለሁ፣» ይል ይሆናል፣ «ቢቻል እንደሚፈውሰኝ በማመን ለእኔ የሚበጀውን እንዲያደርግልኝ እግዚአብሔርን በብርቱ እየለመንሁ መጸለይ።» ሰው እንዲህ እስከ ጸለየ ድረስ በእርግጥ በመገዛት ይጸልያል፤ ይህ ግን የእምነት ጸሎት አይደለም። የእምነት ጸሎት ሊሆን የሚችለው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እየለመንን እንደ ሆነ እርግጠኞች ስንሆን ብቻ ነው። እንግዲህ ጥያቄው የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ወደ ማረጋገጥ ይመለሳል። የእግዚአብሔር ልጅ ስለ ፈውስ ፈቃዱ ምን እንደ ሆነ ሊያውቅ አይችልም ብሎ ማሰብ ታላቅ ስሕተት ነው።
መለኮታዊ ፈቃዱን ለማወቅ በእግዚአብሔር ቃል መመራት አለብን። ፈውስን ተስፋ የሚሰጠን ቃሉ ነው። የያዕቆብ 5 ተስፋ እጅግ ፍጹም ስለ ሆነ ልንክደው አይቻለንም። ይህ ተስፋ ሕመማችንን ስለ ተሸከመ ኢየሱስ ክርስቶስ የደዌያችንን ፈውስ እንዳገኘልን የሚነግሩንን፣ እንደ እርሱ ብርቱ የሆኑትን ሌሎች ክፍሎች ያጸናል እንጂ ሌላ አያደርግም። በዚህ ተስፋ መሠረት፣ ፈውስ በክርስቶስ ያለን የድኅነት ክፍል ስለ ሆነ ለእርሱ መብት አለን፤ ስለዚህም በእርግጠኝነት ልንጠብቀው እንችላለን። መጽሐፍ ሕመም በእግዚአብሔር እጅ ልጆቹን ስለ ኃጢአታቸው የሚቀጣበት መሣሪያ እንደ ሆነ፣ ነገር ግን የሚሠቃየው ልጁ ኃጢአቱን አምኖ ከእርሱ እንደ ተመለሰ ወዲያውኑ ይህ ተግሣጽ እንደሚቆም ይነግረናል። ይህም እግዚአብሔር ሕመምን የሚጠቀምበት ልጆቹ ሲባዝኑ ወደ እርሱ ሊመልሳቸው ብቻ እንደ ሆነ በግልጽ መናገር አይደለምን?
የታመምህ ክርስቲያን ሆይ፣ መጽሐፍ ቅዱስህን ክፈት፤ አጥናው፤ ሕመም ኃጢአትን እንድትተው የሚያስጠነቅቅ እንደ ሆነ፣ ነገር ግን ኃጢአቱን የሚያምንና የሚተው ሁሉ በኢየሱስ ይቅርታንና ፈውስን እንደሚያገኝ በገጾቹ ውስጥ እይ። በቃሉ ያለው የእግዚአብሔር ተስፋ እንዲህ ነው። ጌታ ወደ እርሱ ሊጠራቸው ላሰባቸው ልጆቹ ሌላ አሠራር አስቦ ቢሆን፣ በመንፈስ ቅዱስ የመሄድን ምኞት በመስጠት ፈቃዱን ያስታውቃቸዋል፤ በሌሎች ልዩ ሁኔታዎችም ልዩ የሆነ ውስጣዊ እርግጠኝነትን ያስነሣባቸዋል፤ በአጠቃላይ ግን የእግዚአብሔር ቃል ለእምነት ጸሎት መልስ ፈውስን ተስፋ ይሰጠናል።
አንዳንዶች፦ «ቢሆንም፣» ይሉ ይሆናል፣ «በሁሉ ነገር ለእግዚአብሔር ፈቃድ መተው አይሻልምን?» «ፈቃድህ ትሁን» ሳይጨምሩ በመጸለይ፣ ለማለት ያህል የእግዚአብሔርን እጅ ያስገደዱና በጸሎታቸው መልስ በረከትን ያላገኙ የዚህንና የዚያን ክርስቲያኖች ምሳሌ ይጠቅሳሉ። እነዚሁም፦ «ሕመም ከጤና ይልቅ ይሻለን እንደ ሆነ እንዴት እናውቃለን?» ይላሉ። እዚህ ልብ በል፤ ሊፈውሰን ፈቃዱ እንደ ሆነ የሚነግረን ቃሉ ስለ ሆነ ይህ የእግዚአብሔርን እጅ የማስገደድ ጉዳይ አይደለም። «የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል።» እግዚአብሔር የነፍስ ጤና በሥጋ ጤና ላይ የተባረከ ነጸብራቅ ተጽዕኖ እንዲያሳድር፣ በነፍስ ውስጥ ያለው የኢየሱስ መገኘት በአካል መልካም ሁኔታ እንዲረጋገጥ ይፈቅዳል። ፈቃዱ እንዲህ እንደ ሆነ ካወቅህ እንዲህ ስትናገር በሁሉ ነገር ለእርሱ እንደምትተወው በእውነት ልትል አትችልም። ተስፋውን አጥብቀህ በመያዝ ፈንታ ፈውስን ለማግኘት የሚቻሉትን መድኃኒቶች ሁሉ ስትጠቀም ለእርሱ መተው አይደለም። መገዛትህ እግዚአብሔር እንድታደርግ ከሚያዝህ ነገር አንጻር መንፈሳዊ ስንፍና እንጂ ሌላ አይደለም።
ሕመም ከጤና ይሻል እንደ ሆነ ስለ ማወቅ ደግሞ፣ ኃጢአትን የመተው፣ ራስን ለእግዚአብሔር የመቀደስና ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ፍጹም ኅብረት ፍሬ የሆነው ወደ ጤና መመለስ ከሕመም እጅግ ወሰን በሌለው ሁኔታ እንደሚበልጥ ለመመለስ አናመነታም። «ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነው» (1ኛ ተሰሎንቄ 4:3)፤ እግዚአብሔርም የዚህን እውነተኛነት የሚያጸናው በፈውስ ነው። ኢየሱስ ሥጋችንን የራሱ ሊያደርግ መጥቶ በተአምር ሲፈውሰው፣ የተቀበልነውም ጤና ከእርሱ ጋር በማያቋርጥ ኅብረት ከቀን ወደ ቀን መጠበቅ እንዳለበት ሲከተል፣ በዚህ መንገድ ስለ አዳኙ ኃይልና ስለ ፍቅሩ የምናገኘው ልምምድ ሕመም ሊሰጠው ከሚችለው ከማንኛውም ውጤት እጅግ የላቀ ነው። ሕመም መገዛትን ሊያስተምረን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፤ ነገር ግን በቀጥታ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ፈውስ ጌታችንን አብልጠን እንድናውቀው ያደርገናል፤ በእርሱም አብልጠን እንድንታመን ያስተምረናል። ከዚህም በላይ አማኙ የእግዚአብሔርን አገልግሎት አብልጦ እንዲፈጽም ያዘጋጀዋል።
የታመምህ ክርስቲያን ሆይ፣ በዚህ ነገር የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ በእውነት ልታውቅ ብትሻ፣ በሌሎች አሳብ ወይም በቀድሞው በራስህ ጭፍን አመለካከት አትወሰድ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን አድምጥ፤ አጥናውም። መለኮታዊ ፈውስ የኢየሱስ ቤዛነት ክፍል እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔርም እያንዳንዱ አማኝ ሊጠይቀው መብት እንዲኖረው እንደሚፈቅድ አይነግርህ እንደ ሆነ መርምር፤ ስለዚህ ነገር የእያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ጸሎት እንደሚሰማ ተስፋ አይሰጥ እንደ ሆነ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተመለሰ ጤናም በቤተ ክርስቲያንና በዓለም ፊት የእግዚአብሔርን ክብር አይገልጥ እንደ ሆነ እይ። ጠይቀው፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሕመም በኃጢአት (ወይም በጕድለት) የሚመጣ ተግሣጽ እንደ ሆነ፣ ለእምነት ጸሎት የሚሰጥ ፈውስም ይቅር ለሚለው፣ ለሚቀድሰውና ኃጢአትን ለሚያስወግደው ጸጋው እንደሚመሰክር ይመልስልሃል።
ምዕራፍ 26 ተጠናቋል
የእግዚአብሔር ፈቃድ