መለኮታዊ ፈውስ
ብርቱና ኃይል ያለው ጸሎት

ምዕራፍ 24 · 3 ደቂቃ ንባብ

ብርቱና ኃይል ያለው ጸሎት

«ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ (ወይም በባሕርይ እንደ እኛ) የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች» (ያዕቆብ 5:16—18)።

ያዕቆብ ፈውስን የምታገኝ እምነት የሰው ባሕርይ ፍሬ እንዳልሆነች ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ ጸሎቱ «ብርቱ» ሊሆን እንደሚገባው ይጨምራል። ኃይል የሚኖረው እንዲህ ያለው ጸሎት ብቻ ነው። በዚህም እንደ እኛ ያለ ባሕርይ የነበረውን («እንደ እኛ የሆነ») የኤልያስን ምሳሌ መሠረት ያደርጋል፤ ስለዚህም ጸሎታችን እንደ እርሱ ጸሎት ዓይነት ሊሆን እንደሚችልና ሊሆንም እንደሚገባው ይደመድማል። እንግዲህ ኤልያስ እንዴት ጸለየ? ይህ የእምነት ጸሎት ምን መሆን እንዳለበት በመጠኑ ያበራልናል።

ኤልያስ በምድር ላይ ዝናብ ሊዘንብ እንደ ሆነ ከእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ተቀብሎ ነበር (1ኛ ነገሥት 18:1)፤ ይህንንም ለአክዓብ ተናግሮ ነበር። በአምላኩ የተስፋ ቃል ጸንቶ ለመጸለይ ወደ ቀርሜሎስ ይወጣል (1ኛ ነገሥት 18:42፤ ያዕቆብ 5:18)። ዝናብ መላክ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ሆነ ያውቃል፣ ያምናልም፤ ቢሆንም መጸለይ አለበት፤ ያለዚያ ዝናቡ አይመጣም። ጸሎቱ ባዶ ሥርዓት አይደለም፤ ብርታቱ በሰማይ ሊሰማ ያለ እውነተኛ ኃይል ነው። እግዚአብሔር ዝናብ እንዲዘንብ ይፈቅዳል፤ ዝናቡ ግን የሚመጣው በኤልያስ ልመና ብቻ ነው፤ ይህም በሰማይ የመጀመሪያው ደመና እስኪታይ ድረስ በእምነትና በጽናት የተደጋገመ ልመና ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ ይፈጸም ዘንድ ይህ ፈቃድ በአንድ በኩል በተስፋ ቃል ሊገለጥ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሚጸልየው አማኝ ሊቀበለውና አጥብቆ ሊይዘው ይገባል። ስለዚህ አማኙ እምነቱ መልስን እንደምትጠብቅ፣ መልሱንም እስክታገኝ ድረስ እንደማትታክት ለአምላኩ ያሳይ ዘንድ በጸሎት ሊጸና ይገባዋል።

ለድውያን ልንጸልይ የሚገባን እንዲህ ነው። «ጌታም ያስነሣዋል» በሚለው የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ መደገፍ፣ ለመፈወስ ያለውንም ፈቃድ ማወቅ ያስፈልጋል። ኢየሱስ ራሱ በእግዚአብሔር መልስ ላይ በሚተማመን እምነት እንድንጸልይ ያስተምረናል፤ እንዲህ ይለናል፦ «የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል» (ማርቆስ 11:24፣ የተሻሻለው ትርጉም)። እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠውን አስቀድሞ ከሚቀበለው ከእምነት ጸሎት በኋላ፣ እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን እስኪፈጽም ድረስ የለመነውን ከዓይኑ የማያርቀው የጽናት ጸሎት ይመጣል (1ኛ ነገሥት 18:43)። የተስፋውን ቃል መፈጸም የሚያግድ አንዳች እንቅፋት ይኖር ይሆናል፤ ይህም በእግዚአብሔርና በጽድቁ በኩል (ዘዳግም 9:18)፣ ወይም በሰይጣንና የእግዚአብሔርን ዕቅድ ዘወትር በመቃወሙ በኩል፣ አሁንም የጸሎቱን መልስ ሊያዘገይ የሚችል ነገር ሊሆን ይችላል (ዳንኤል 10:12, 13)። ደግሞም እምነታችን መንጻት ያስፈልገው ይሆናል (ማቴዎስ 15:22—28)። ምንም ይሁን ምን፣ እምነታችን መልሱ እስኪመጣ ድረስ እንዲጸና ተጠርቷል። ሰባት ጊዜ መጸለይ ሲገባው ስድስት ጊዜ አጥብቆ ጸልዮ የሚያቆም ሰው (2ኛ ነገሥት 13:18, 19) የጸሎቱን መልስ ራሱን ያሳጣል።

በጸሎት መጽናት፣ ማለትም መልሱን የሚቃወም ከሚመስለው ነገር ሁሉ ፊት የአማኙን እምነት የሚያበረታ ጽናት፣ እውነተኛ ተአምር ነው፤ ከእምነት ሕይወት የማይመረመሩ ምሥጢራት አንዱ ነው። ይህ በአዳኙ የተዋጀው ሰው በእውነት ወዳጁ፣ የአካሉም ብልት እንደ ሆነ፣ የዓለም አስተዳደርና የመለኮታዊ ጸጋ ስጦታዎችም በአንድ መልኩ በጸሎቱ ላይ እንደሚመሠረቱ አይነግረንምን? ስለዚህ ጸሎት ከንቱ ሥርዓት አይደለም። እዚህ በምድር በእኛ ውስጥና በእኛ በኩል የሚማልደው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው፤ እንደዚህም በመሆኑ ወልድ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ስለ እኛ የሚማልድበትን ሥራ ያህል ኃይል ያለውና አስፈላጊ ነው። እንደሚሰማልን በእርግጠኝነት ከጸለይንና በዚህም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ካየን በኋላ አሁንም በጸሎት መቀጠል ያስፈልገናል ማለት እንግዳ ነገር ሊመስል ይችላል። ቢሆንም እንዲሁ ነው። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ ሦስት ጊዜ በተከታታይ ጸለየ። ኤልያስ በቀርሜሎስ ሰባት ጊዜ ጸለየ፤ እኛም የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ሳንጠራጠር ካመንን መልሱን እስክንቀበል ድረስ እንጸልያለን። በእኩለ ሌሊት የሚወተውተው ወዳጅም፣ ዓመፀኛውን ዳኛ እረፍት የነሣችው መበለቲቱም የተመኙትን ፍጻሜ በመሻት የመጽናት ምሳሌዎች ናቸው።

ራሳችንን ዝቅ ማድረግን ከኤልያስ ጸሎት እንማር፤ በድውያን ፈውስም ቢሆን፣ በኃጢአተኞች መመለስም ቢሆን፣ በቅድስናም ቢሆን የእግዚአብሔር ኃይል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከዚህ በላይ ሊገለጥ ያልቻለው ለምን እንደ ሆነ እንገንዘብ። «አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም» (ያዕቆብ 4:2)። ትዕግሥትንም ያስተምረን። ፈውስ በዘገየባቸው ሁኔታዎች በጸሎት መጽናት ብቻ ድል ሊነሣቸው የሚችል እንቅፋቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ እናስታውስ። መጸለይን የምታቆም፣ ወይም ግለቷ እንዲበርድ የምትፈቅድ እምነት እግዚአብሔር የሰጠውን እንኳ የራሷ ልታደርገው አትችልም። ገና ከአቅማችን በላይ በሆኑ ነገሮች ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ የተስፋ ቃሎች ላይ ያለን እምነት አይናወጥ። የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ያው ነው፦ «የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል።» የኤልያስ ጸሎት እምነታችንን ያበርታው። በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን ልንመስል እንደሚገባን እናስታውስ (ዕብራውያን 6:12)። በጸሎት መጽናትን ብንማር ፍሬው ሁልጊዜ ይበልጥ የበዛ፣ ሁልጊዜም ይበልጥ የሚታይ ይሆናል፤ ኢየሱስም በምድር ሳለ እንዳገኘው፣ እግዚአብሔርን የሚያከብር የድውያንን ፈውስ፣ ብዙ ጊዜም ፈጣን ፈውስ እናገኛለን።

ምዕራፍ 24 ተጠናቋል

ብርቱና ኃይል ያለው ጸሎት

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል