መለኮታዊ ፈውስ
ኢየሱስ ድውያንን ይፈውሳል

ምዕራፍ 23 · 2 ደቂቃ ንባብ

ኢየሱስ ድውያንን ይፈውሳል

«ድውዮችን ሁሉ ፈወሰ፤ ይህም በነቢዩ በኢሳይያስ፦ እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ ተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው» (ማቴዎስ 8:16, 17)።

በቀደመው ምዕራፍ የነቢዩን የኢሳይያስን ቃል አጥንተናል። አንባቢው ስለ ተሰጠው ትርጓሜ አሁንም ጥርጣሬ ቢኖርበት፣ መንፈስ ቅዱስ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ስለዚሁ እንዲጽፍ ያደረገውን እናሳስበዋለን። ኢየሱስ ስለ ፈወሳቸው ድውያን ሁሉ፦ «በነቢዩ በኢሳይያስ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ» ተብሎ በግልጽ ተጽፏል። ኢየሱስ ደዌያችንን በራሱ ላይ ስለ ተቀበለ ነው ሊፈውሳቸው የቻለው፣ ሊፈውሳቸውም የተገባው። ይህን ባያደርግ ኖሮ የቤዛነት ሥራው አንዱ ክፍል ኃይል የሌለውና ፍሬ ቢስ ሆኖ በቀረ ነበር።

ይህ የእግዚአብሔር ቃል ክፍል በአብዛኛው በዚህ መንገድ አይረዳም። ጌታ ኢየሱስ ያደረጋቸው ተአምራዊ ፈውሶች የምሕረቱ ማስረጃ ብቻ፣ ወይም የመንፈሳዊ ጸጋዎች ምሳሌ ብቻ ሆነው ሊታዩ ይገባል የሚለው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አመለካከት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንኑ ቢናገርም፣ ፈውሶቹ የቤዛነት የግድ ውጤት እንደ ሆኑ አይታይም። አካልና ነፍስ በአንድነት የእግዚአብሔር ማደሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ ተፈጥረዋል፤ የነፍስ ድካም እንደ ሆነ ሁሉ የአካል ደዌም የኃጢአት ውጤት ነው፤ ኢየሱስም ሊሸከመው፣ ሊያስተሰርየውና ድል ሊነሣው የመጣው ይህንኑ ነው።

ጌታ ኢየሱስ በምድር ሳለ ድውያንን የፈወሰው በእግዚአብሔር ልጅነቱ ሳይሆን ደዌን በራሱ ላይ የተቀበለና የተሸከመ መካከለኛ ሆኖ ነው፤ ይህም ኢየሱስ ለፈውስ ሥራው ይህን ያህል ጊዜ ለምን እንደ ሰጠ፣ ወንጌላውያንም ስለዚህ ሥራ ለምን እንዲህ በዝርዝር እንደ ተናገሩ እንድንረዳ ያስችለናል። ለምሳሌ ማቴዎስ ስለዚህ የሚለውን አንብብ፦ «ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም» (ማቴዎስ 4:23, 24)። «ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር» (ማቴዎስ 9:35)። «አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው» (10:1)። የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ መሲሕ እንደ ሆነ እንዲያረጋግጥላቸው ሊጠይቁት በመጡ ጊዜ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ «ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል» (11: 5)። የሰለለችውን እጅ ከፈወሰ በኋላ፣ ሊያጠፉትም የፈለጉት ፈሪሳውያን ከተቃወሙት በኋላ፣ እንዲህ እናነባለን፦ «ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው» (12:15)። ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ወደ ምድረ በዳ በተከተሉት ጊዜ እንዲህ ተብሏል፦ «ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ» (14:14)። ቀጥሎም፦ «በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፥ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ» (14: 35, 36)። ከሕዝቡ መካከል ስለ ነበሩት ድውያንም «በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም» ተብሏል፤ ማቴዎስም እንዲህ ይጨምራል፦ «ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ» (15:30, 31)። በመጨረሻም ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ አገር በመጣ ጊዜ፦ «ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ በዚያም ፈወሳቸው» (19:2)።

በእነዚህ ብዙ ጥቅሶች ላይ ኢየሱስ ያደረጋቸውን ፈውሶች በዝርዝር የሚተርኩልንን ክፍሎች እንጨምር፤ እነዚህ ፈውሶች እዚህ በምድር በኖረበት ዘመን የኃይሉ ማስረጃ ብቻ ናቸውን? ወይስ ይልቁንም የምሕረቱና የፍቅሩ ሥራ የማያጠራጥርና የማያቋርጥ ውጤት፣ ነፍስንና ሥጋን ከኃጢአት ግዛት ነጻ የሚያወጣው የቤዛነት ኃይሉ መገለጫ አይደሉምን? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። አዎን፤ የእግዚአብሔር ዓላማ በእውነት ይህ ነበር። እንግዲህ ኢየሱስ ደዌያችንን የቤዛነት የማይነጠል ክፍል አድርጎ ከተሸከመ፣ ድውያንንም «በኢሳይያስ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ» ከፈወሰ፣ የአዳኝነት ልቡም ሁልጊዜ በምሕረትና በፍቅር የተሞላ ከሆነ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ለእምነት ጸሎት መልስ ድውያንን መፈወስ የኢየሱስ ፈቃድ እንደ ሆነ በእርግጠኝነት ማመን እንችላለን።

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል