ምዕራፍ 22 · 3 ደቂቃ ንባብ
ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ
«በግብፃውያን ላይ ካመጣሁት ደዌ ሁሉ አንዱን በአንተ ላይ አላመጣም፤ ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ» (ዘጸአት 15:26)።
እነዚህን ቃሎች ለራሳችን ለመውሰድ ሳንደፍር፣ ጌታም ለእኛ ይፈጽማቸዋል ብለን ሳንጠብቅ ስንት ጊዜ አንብበናቸዋል! የእግዚአብሔር ሕዝብ በግብፃውያን ላይ ከወረዱት ደዌዎች ነጻ ሊሆን እንደሚገባው በውስጣቸው አይተናል፤ ደግሞም ይህ ተስፋ ለብሉይ ኪዳን ብቻ የተሰጠ እንደ ሆነ፣ በአዲስ ኪዳን ሥርዓት ሥር የምንኖር እኛም በጌታ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ከሕመም እንድንጠበቅ ወይም እንድንፈወስ ልንጠብቅ እንደማንችል አምነናል! ሆኖም የአዲሱን ኪዳን ብልጫ ለመቀበል ስለ ተገደድን፣ ባለማወቃችን ሕመም ብዙ ጊዜ ታላላቅ በረከቶችን እንደሚያመጣ፣ ስለዚህም እግዚአብሔር ቀድሞ ተስፋ የሰጠውን መመለሱና ለእስራኤል የነበረውን፣ ማለትም «ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ» የሚለውን፣ ከእንግዲህ ለእኛ አለመሆኑ መልካም እንዳደረገ ወደ መናገር ደርሰናል።
ነገር ግን በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ስትነቃና ስሕተቷን ስታምን እናያለን። ጌታ ኢየሱስ የመፈወስ ኃይሉን ለደቀ መዛሙርቱ ያስተላለፈው በአዲሱ ኪዳን ሥር እንደ ሆነ ታያለች። ቤተ ክርስቲያኑን ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን እንድትሰብክ ባዘዛት ጊዜ «እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ» ከእርስዋ ጋር እንደሚሆን (ማቴዎስ 28:20) ተስፋ እንደ ሰጠ፣ ለመገኘቱም ማስረጃ ይሆን ዘንድ ደቀ መዛሙርቱ እጃቸውን በድውያን ላይ የመጫን ኃይል እንደሚኖራቸውና ድውያኑም እንደሚፈወሱ (ማርቆስ 16:15—18) ማየት ጀምራለች። ደግሞም ከበዓለ ኀምሳ በኋላ ባሉት ቀናት የመንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ መፍሰስ በተአምራዊ ፈውሶች ታጅቦ እንደ ነበር ታያለች፤ እነዚህም ከላይ የመጣው ኃይል ያስገኛቸው በረከቶች ግልጽ ማስረጃዎች ነበሩ (የሐዋርያት ሥራ 3:16፤ 5:12፤ 9:40)። ለእስራኤል የተሰጠው ተስፋ ከዚያ ወዲህ እንደ ተሻረ እንድታምን የሚያደርጋት ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፤ ከሐዋርያው ያዕቆብም አፍ ይህን አዲስ ተስፋ ትሰማለች፦ «የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል» [ወይም ይፈውሳል] (ያዕቆብ 5:15)። የእስራኤልን ቅዱስ ሁልጊዜ የወሰነው (ወይም ድንበር ያበጀለት) አለማመን እንደ ሆነ ታውቃለች (መዝሙር 78:41)፤ በዚህ ዘመንም ይህን የእግዚአብሔርን ኃይል መገለጥ የሚከለክለው አለማመን አይደለምን? ብላ ራስዋን ትጠይቃለች። ይህን ማን ሊጠራጠር ይችላል? በዚህ ነገር ተወቃሽ እግዚአብሔር ወይም ቃሉ አይደለም፤ የጌታን ተአምራዊ ኃይል የሚከለክለውና እንደ ቀድሞው ዘመን ከመፈወስ የሚያግደው የእኛ አለማመን ነው። እምነታችን ይንቃ፤ «ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ» የሚለውን የእርሱን ሁሉን የሚችል ኃይል በክርስቶስ ይወቅ፣ ይስገድለትም። ቃሉ የሚነግረንን በተሻለ ልንረዳ የምንችለው በእግዚአብሔር ሥራዎች ነው፤ ዳግመኛ ለእምነት ጸሎት መልስ ሆነው የሚገኙት ፈውሶች የተስፋውን እውነት በክብር እየገለጡ ያጸኑታል።
ከሙታን በተነሣው ኢየሱስ መለኮታዊውን ፈዋሽ ማየትን እንማር፤ እንደዚሁም እንቀበለው። ኢየሱስን ጽድቄ፣ ብርታቴና ጥበቤ አድርጌ እንዳውቀው፣ እርሱ በእውነት ይህ ሁሉ ለእኔ እንደ ሆነ በእምነት መጨበጥ አለብኝ፤ እንደዚሁም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ሉዓላዊ ፈዋሽ እንደ ሆነ ሲነግረኝ ይህን እውነት እኔ ራሴ የግሌ ማድረግና፦ «አዎን ጌታ ሆይ፣ ፈዋሼ አንተ ነህ» ማለት አለብኝ። እንደዚህ አድርጌ ልይዘው የምችለውስ ለምንድን ነው? ራሱን ለእኔ ስለሚሰጥ፣ እኔም «ከእርሱ ጋር አንድ ተክል» ስለ ሆንሁ (ሮሜ 6:5፣ የፈረንሳይኛ ትርጉም)፣ ከእርሱም ጋር በማይለያይ ሁኔታ ተባብሬ የመፈወስ ኃይሉን ገንዘቤ ስለማደርግ ነው፤ ፍቅሩ የሚወዳቸውን በሞገሱ መሙላት፣ ሊቀበሉትም ለሚፈልጉ ሁሉ በፍጹም ልቡ ራሱን ማካፈል ደስ ስለሚያሰኘው ነው። «ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ» በሚለው ስም ውስጥ ያለውን የበረከት መዝገብ ይህን መለኮታዊ ስም ለሚያውቁና በእርሱ ሊታመኑ ለሚችሉ ሁሉ ሊያዳርስ ዝግጁ እንደ ሆነ እናምን። የመንግሥቱ ሕግ ለድውያን ያመለከተው ሕክምና ይህ ነው። ሕመሜን ወደ ጌታ ሳመጣ የምደገፈው በማየው፣ በሚሰማኝ ወይም በማስበው ላይ ሳይሆን እርሱ በሚለው ላይ ነው። የምጠብቀውን ፈውስ ሁሉ ነገር የሚቃረን ቢመስል እንኳ፣ እቀበለዋለሁ ብዬ ባሰብሁበት ጊዜ ወይም መንገድ ባይሆን እንኳ፣ የሕመሙ ምልክቶች ይበልጥ የሚባባሱ ቢመስሉ እንኳ፣ በመጠበቁ ራሱ የበረታው እምነቴ ከእግዚአብሔር አፍ በወጣው በዚህ ቃል ላይ ሳይነቃነቅ ሊጣበቅ ይገባዋል፦ «ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።» እግዚአብሔር እውነተኛ አማኞች ሊያደርገን ዘወትር ይፈልጋል። ፈውስና ጤና እግዚአብሔርን ካላከበሩና ከእርሱ ጋር ይበልጥ አጥብቀው ካላስተባበሩን ዋጋቸው ጥቂት ነው፤ ስለዚህ በፈውስ ጉዳይ እምነታችን ሁልጊዜ መፈተን አለበት። በአምላኩ ስም የሚታመን፣ ኢየሱስ፦ «ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?» (ዮሐንስ 11:40) ሲለው መስማት የሚችል ሰው የአካልን ፈውስ ከእግዚአብሔር ራሱ የመቀበልንና ፈውሱም ለእግዚአብሔር በሚገባ መንገድ፣ እንደ ተስፋዎቹም ሲፈጸም የማየትን ደስታ ያገኛል። «ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ» የሚሉትን እነዚህን ቃሎች ስናነብ፦ «አዎን ጌታ ሆይ፣ ፈዋሼ እግዚአብሔር አንተ ነህ» ብለን በጕጕት ለመመለስ አንፍራ።
ምዕራፍ 22 ተጠናቋል
ፈዋሽህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ