ምዕራፍ 21 · 3 ደቂቃ ንባብ
የእግዚአብሔር ማዘዣ ለድውያን
«ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል» (ያዕቆብ 5:14, 15)።
ይህ ጥቅስ ከሌሎቹ ሁሉ በላይ ድውያን ይፈወሱ ዘንድ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እጅግ በግልጽ የሚነግራቸው ነው። ሕመምና የሚያስከትለው መዘዝ በዓለም ላይ በዝተዋል። እንግዲያስ አማኝ ለድውያን የሚሆነውን የፈውስ መንገድ ከእግዚአብሔር ቃል መማሩ እንዴት ያለ ደስታ ነው! ልጆቹን በጤና ሆነው ማየት የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ሐዋርያው ያዕቆብ፦ «የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል» ለማለት አያመነታም። ጌታ ቃሉ የሚነግረንን እንድናደምጥና በቅንነት እንድንቀበል ያስተምረን!
በመጀመሪያ ያዕቆብ በዚህ ስፍራ በመከራ (ወይም በሥቃይ) እና በሕመም መካከል ልዩነት እንደሚያደርግ ልብ በል። እንዲህ ይላል (ቍ. 13)፦ «ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ» (የተሻሻለው ትርጉም)። በእንዲህ ያለው ሁኔታ ምን መለመን እንዳለበት አይገልጽም፤ ከመከራው መዳን እንዲለመን ደግሞ ከቶ አይናገርም። አይደለም፤ ከልዩ ልዩ ውጫዊ ምክንያቶች ሊመጣ የሚችለው መከራ የክርስቲያን ሁሉ ዕድል ፈንታ ነው። ስለዚህ የያዕቆብ ዓላማ የተፈተነውን አማኝ ከመከራው መዳንን እንዲለምን የሚመራው ለእግዚአብሔር ፈቃድ በመገዛት መንፈስ ብቻ እንደ ሆነ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአማኝ መብት አድርጎ የሚቆጥረውን ትዕግሥት እንዲለምን እንደ ሆነ እንረዳ (ያዕቆብ 1:2—4, 12፤ 5:7, 8)።
ነገር ግን «ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር» የሚለውን ቃል ሲመለከት ያዕቆብ ፈጽሞ በሌላ መንገድ ይመልሳል። አሁን የታመመው ሰው እንደሚያገኘው በመተማመን ፈውስን ሊለምን እንደሚችል፣ ጌታም እንደሚሰማው በእርግጠኝነት ይናገራል። ስለዚህ በመከራና በሕመም መካከል ታላቅ ልዩነት አለ። ጌታ ኢየሱስ ስለ መከራ አስፈላጊ እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔር የፈቀደውና የባረከው እንደ ሆነ ተናገረ፤ ስለ ሕመም ግን ሊፈወስ እንደሚገባው ይናገራል። ሌላው መከራ ሁሉ ከውጭ ወደ እኛ ይመጣል፤ የሚያበቃውም ኢየሱስ በዓለም ባሉት ኃጢአትና ክፋት ላይ ድል በሚነሣበት ጊዜ ብቻ ነው፤ ሕመም ግን በአካል ራሱ ውስጥ ያለ ክፋት ነው፤ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ክርስቶስ ባዳነው በዚህ አካል ውስጥ ያለ ክፋት ነው፤ ስለዚህም የታመመው አማኝ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ፣ ማለትም በእርሱ ውስጥ ያለውን የኢየሱስን ሕይወት በእምነት እንደ ተቀበለ ወዲያውኑ ሊፈወስ ይገባዋል።
እዚህ ለድውያን የተሰጠው መመሪያ ምንድን ነው? የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ይጥራ፤ ሽማግሌዎቹም ይጸልዩለት። በያዕቆብ ዘመን ሐኪሞች ነበሩ፤ የታመመው አማኝ ግን ወደ እነርሱ መዞር የለበትም። በዚያን ጊዜ ሽማግሌዎቹ የአብያተ ክርስቲያናት እረኞችና መሪዎች ነበሩ፤ ወደ አገልግሎት የተጠሩትም የሥነ መለኮት ትምህርት ቤቶችን ስላለፉ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ስለ ተሞሉና በመንፈሳዊ ኑሮአቸውና በእምነታቸው የታወቁ ስለ ነበሩ ነው። የታመመው ሰው የእነርሱ መገኘት ለምን ያስፈልገዋል? ወዳጆቹ ሊጸልዩለት አይችሉም ነበርን? ይችሉ ነበር፤ ነገር ግን ፈውስን የሚያገኘውን እምነት መለማመድ ለሰው ሁሉ ቀላል አይደለም፤ ያዕቆብ እምነታቸው የጸናና እርግጠኛ የሆነ ሰዎች እንዲጠሩ የፈለገበት አንዱ ምክንያት ይህ እንደ ሆነ አያጠራጥርም። ከዚህም በላይ ለታመመው ሰው የቤተ ክርስቲያን፣ ማለትም የክርስቶስ የጋራ አካል፣ ወኪሎች ነበሩ፤ መንፈስ በኃይል እንዲሠራ የሚጋብዘው የአማኞች ኅብረት ነውና። በአጭሩ ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን አብነት አድርገው እንደ እርሱ መንጋውን ሊጠብቁ፣ ራሳቸውን ከታመመው ሰው ጋር አንድ ሊያደርጉ፣ ችግሩን ሊረዱ፣ ሊያስተምሩትና በእምነት እንዲጸና ሊያበረታቱት የሚያስፈልጋቸውን ማስተዋል ከእግዚአብሔር ሊቀበሉ ይገባቸዋል። እንግዲህ የድውያን ፈውስ በአደራ የተሰጠው ለቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ነው፤ የጌታንም ጸጋ ለነፍስና ለሥጋ ለሌሎች እንዲያስተላልፉ የተጠሩት እነርሱ፣ በደልን ይቅር የሚለውና ደዌን የሚፈውሰው የእግዚአብሔር አገልጋዮች (መዝሙር 103) ናቸው።
በመጨረሻም ከዚህ ይበልጥ ቀጥተኛ የሆነ ተስፋ አለ—የፈውስ ተስፋ፤ ሐዋርያው ስለዚህ ፈውስ የእምነት ጸሎት የሚያስከትለው የማይቀር ውጤት አድርጎ ይናገራል። «የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል።» ይህ ተስፋ በአማኝ ሁሉ ልብ ውስጥ የፈውስን ምኞትና ናፍቆት ሊያነሣሣ ይገባዋል። እነዚህን ቃሎች በቅንነትና እንደ ተጻፉ ከተቀበልናቸው፣ በእምነት ለሚጸልይ ሁሉ ፈውስን የሚሰጥ ወሰን የሌለው ተስፋ በውስጣቸው ልናይ አይገባንምን? ጌታ ቃሉን በእውነት በሚያምን ልብ እምነት እንድናጠና ያስተምረን!
ምዕራፍ 21 ተጠናቋል
የእግዚአብሔር ማዘዣ ለድውያን