ምዕራፍ 20 · 3 ደቂቃ ንባብ
ሕመም ቅጣት ነውን?
«ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል። ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤ ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን» (1ኛ ቆሮንቶስ 11:30—32፣ የተሻሻለው ትርጉም)።
ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ የጌታን እራት ያከበሩበትን መንገድ መገሠጽ ግድ ሆነበት፤ በዚህም የእግዚአብሔርን ቅጣት በራሳቸው ላይ አምጥተው ነበር። ስለዚህ እዚህ ሕመምን እንደ እግዚአብሔር ፍርድ፣ ስለ ኃጢአት እንደሚመጣ ቅጣት እናያለን። ጳውሎስ ከዚያ በኋላ «በጌታ እንገሠጻለን» ስለሚል እውነተኛ ቅጣት እንደ ሆነ ያያል፤ እንዲህ የሚታመሙትም ይበልጥ ጠልቀው በኃጢአት እንዳይወድቁ ለመከልከል፣ «ከዓለም ጋር እንዳንኮነን» እንደሚለው እንዳይኮነኑ ለማድረግ እንደ ሆነ ይጨምራል። በጌታ መፈረድም መገሠጽም ባይፈልጉ፣ እንዲህ ባለው ምርመራ የሕመሙን ምክንያት አግኝተው ኃጢአታቸውን ቢኰንኑ ጌታ ከእንግዲህ ጽኑ ቅጣት ማድረግ እንደማያስፈልገው ያስጠነቅቃቸዋል። እዚህ ሕመም የእግዚአብሔር ፍርድ፣ የኃጢአት ቅጣት እንደ ሆነ፣ ራሳችንንም በመመርመርና በመኰነን ልናስቀረው እንደምንችል ግልጽ አይደለምን?
አዎን፣ ሕመም ከምናምነው በላይ ብዙ ጊዜ ፍርድ፣ ስለ ኃጢአት የሚመጣ ቅጣት ነው። እግዚአብሔር «ከልቡ አያስጨንቅምና፥ የሰውንም ልጆች አያሳዝንምና» (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:33)። ጤናችንን የሚወስድብን ያለ ምክንያት አይደለም። ምናልባት ልናውቀው ለምንችለው ለአንድ ኃጢአት ትኵረት እንድንሰጥ ሊሆን ይችላል፦ «ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ» (ዮሐንስ 5:14)፤ ምናልባት የእግዚአብሔር ልጅ በትዕቢትና በዓለማዊነት ስለ ተጠላለፈ ይሆናል፤ ወይም ለእግዚአብሔር በሚሰጠው አገልግሎት ውስጥ በራስ መተማመን ወይም ወላዋይነት ተቀላቅሎ ሊሆን ይችላል። ደግሞም ቅጣቱ በአንድ በተለየ ኃጢአት ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን በሰው ዘር ሁሉ ላይ የሚከብደው የኃጢአት ብዛት ውጤት ሊሆን መቻሉ ፈጽሞ የሚቻል ነው። ዕውር ሆኖ በተወለደው ሰው ጉዳይ (ዮሐንስ 9:3) ደቀ መዛሙርቱ ጌታን፦ «ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ?» ብለው በጠየቁት ጊዜ፣ እርሱም፦ «እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም» ብሎ በመለሰ ጊዜ፣ በኃጢአትና በሕመም መካከል ምንም ግንኙነት የለም ማለቱ በፍጹም አይደለም፤ ነገር ግን የታመመውን ሁሉ በኃጢአት እንዳንከስ ያስተምረናል።
በማንኛውም ሁኔታ ሕመም ሁልጊዜ ትኵረታችንን ወደ ኃጢአት የሚያነቃና ከእርሱ የሚመልሰን ተግሣጽ ነው። ስለዚህ የታመመ ሰው ራሱን በመኰነን ወይም በመመርመር (1ኛ ቆሮንቶስ 11:31) ሊጀምር ይገባዋል፤ ሰማያዊውን አባቱን ያሳዘነውን ወይም ቅጣቱን አስፈላጊ ያደረገውን ማንኛውንም ነገር ለማየት ከልብ በመሻት ራሱን በፊቱ ያቅርብ። እንዲህ ሲያደርግ ጕድለቱን በግልጽ በሚያሳየው በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በእርግጥ ሊተማመን ይችላል። ያስተዋለውን ነገር ወዲያውኑ ለመተው ዝግጁ ይሁን፤ በፍጹም መታዘዝ ጌታን ሊያገለግል ራሱን ለእርሱ ያስገዛ፤ ነገር ግን ኃጢአትን በራሱ ጥረት ሊያሸንፍ እንደሚችል አያስብ። አይደለም፤ ይህ ለእርሱ የማይቻል ነው። ነገር ግን በፊቱ ኃጢአት የሆነውን በመተው በፈቃዱ ኃይል ሁሉ ከእግዚአብሔር ጎን ይቁም፤ እርሱም እንደ ተቀበለው ይመን። እንዲህ ሲያደርግ በሁሉ ነገር ቅዱስ ፈቃዱን ብቻ ለማድረግ ወድዶ ራሱን ያስረክባል፤ ራሱንም እንደ ገና ለእግዚአብሔር ይቀድሳል።
እንዲህ ራሳችንን ብንመረምር ጌታ እንደማይፈርድብን መጽሐፍ ያረጋግጥልናል። አባታችን ልጁን የሚቀጣው የሚያስፈልገውን ያህል ብቻ ነው። እግዚአብሔር ከኃጢአትና ከራስ ሊያድነን ይፈልጋል፤ እርሱን ተረድተን ከእነዚህ ጋር በተለያየን ጊዜ ሕመሙ ሊቆም ይችላል፤ ሥራውን ፈጽሞአልና። ሕመሙ ምን ማለት እንደ ሆነ ልናይ፣ በእርሱም የእግዚአብሔርን ተግሣጽ ልናውቅ ይገባናል። አንድ ሰው ኃጢአት እንደሚሠራ በደፈናው ያውቅ ይሆናል፤ እነዚያ ምን እንደ ሆኑ ለመለየት ግን አይሞክርም ማለት ይቻላል፤ ቢለያቸውም እንኳ ሊተዋቸው እንደሚቻል አያምን ይሆናል፤ ሊተዋቸውም ቢወስን እግዚአብሔር ቅጣቱን እንደሚያቆም በእግዚአብሔር መታመን ይሳነው ይሆናል። ሆኖም የጳውሎስ ቃል እዚህ የሚሰጠን ማረጋገጫ ምንኛ የከበረ ነው!
ውድ ታማሚ ሆይ፣ ሰማያዊ አባትህ በአንተ ውስጥ የሚገሥጸው ነገር እንዳለ ታስተውላለህን? ሕመምህ ያን እንድታገኘው እንዲረዳህ ይፈልጋል፤ መንፈስ ቅዱስም በፍለጋህ ይመራሃል። እንግዲያስ እርሱ የሚያመለክትህን ወዲያውኑ ተው። በአባትህና በአንተ መካከል ትንሽ ጥላ እንኳ እንዲቀር አትፈልግም። ኃጢአትህን ይቅር ሊልና ሕመምህን ሊፈውስ ፈቃዱ ነው። በኢየሱስ ይቅርታም ፈውስም አለን፤ እነርሱ የቤዛነት ሥራው ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ከቀድሞው ይልቅ በላቀ ደረጃ በእርሱ ላይ ተደግፈህ እንድትኖር ይጠራሃል። እንግዲያስ በፍጹም መታዘዝ ራስህን ለእርሱ አሳልፈህ ስጥ፤ ከአሁን ጀምሮም እንደ ትንሽ ልጅ ፈለጉን ተከትለህ ተመላለስ። ሰማያዊ አባትህ ከቅጣት የሚያድንህ፣ ፈዋሽህ ሆኖ ራሱን የሚገልጥልህ፣ በዚህ አዲስ የፍቅሩ ማሰሪያ ወደ እርሱ የሚያቀርብህ፣ በማገልገልም ታዛዥና ታማኝ የሚያደርግህ በደስታ ነው። ጥበበኛና ታማኝ አባት እንደ መሆኑ ሊቀጣህ ግድ ሆኖበት ከሆነ፣ ፈውስህን የሚፈልገው፣ ከአሁን ጀምሮም ሊባርክህና ሊጠብቅህ የሚወደው እንደ አባት ነው።
ምዕራፍ 20 ተጠናቋል
ሕመም ቅጣት ነውን?