ምዕራፍ 2 · 4 ደቂቃ ንባብ
ስለ እምነታችሁ ማነስ
«ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና። እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምን ነው? አሉት።
«ኢየሱስም። ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም» (ማቴዎስ 17:19, 20)።
ጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ልዩ ልዩ የፍልስጤም ክፍሎች በላካቸው ጊዜ ሁለት ዓይነት ኃይል አለበሳቸው፤ ርኩሳን መናፍስትን የማውጣትና ደዌንና ሕማምን ሁሉ የመፈወስ ኃይል ነው (ማቴዎስ 10:1)። ለሰባዎቹም እንዲሁ አደረገ፤ እነርሱም በደስታ ተመልሰው፦ «ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል» አሉት (ሉቃስ 10:17)። በተራራው ላይ በተለወጠበት ቀን፣ ጌታ ገና በተራራው ላይ ሳለ፣ አንድ አባት ጋኔን ያደረበትን ልጁን ወደ ደቀ መዛሙርቱ አምጥቶ ክፉውን መንፈስ እንዲያወጡለት ለመናቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም። ኢየሱስ ልጁን ከፈወሰ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንደ ሌሎቹ ጊዜያት ራሳቸው ሊያደርጉት ያልቻሉት ስለ ምን እንደ ሆነ በጠየቁት ጊዜ፦ «ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው» ብሎ መለሰላቸው። እንግዲህ ለውድቀታቸው ምክንያት የሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ ሳይሆን አለማመናቸው ነበር።
በእኛ ዘመን በመለኮታዊ ፈውስ የሚያምኑ እጅግ ጥቂቶች ናቸው፤ ከክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ ማለት ይቻላል ጠፍቶአልና። ምክንያቱ ምንድር ነው ብሎ መጠየቅ ይቻላል፤ የተሰጡትም ሁለት መልሶች እነሆ። አብዛኞቹ ተአምራት፣ የፈውስ ስጦታም ጭምር፣ በመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን ዘመን ብቻ የተወሰኑ እንደ ሆኑ፣ ዓላማቸውም የክርስትናን የመጀመሪያ መሠረት መጣል እንደ ነበረ፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ግን ሁኔታዎች እንደ ተለወጡ ያስባሉ። ሌሎች አማኞች ደግሞ ሳያመነቱ እንዲህ ይላሉ፦ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ስጦታዎች አጥታ ከሆነ በራስዋ ጥፋት ነው፤ መንፈስ በእርስዋ ውስጥ በደካማ ሁኔታ ብቻ የሚሠራው ዓለማዊ ስለ ሆነች ነው፤ ከማይታየው ዓለም ሙሉ ኃይል ጋር ቀጥተኛና የዘወትር ግንኙነት ይዛ ስላልኖረች ነው፤ ነገር ግን የእምነትንና የመንፈስ ቅዱስን ሕይወት የሚኖሩ፣ ፈጽመው ለአምላካቸው የተቀደሱ ወንዶችና ሴቶች በውስጥዋ እንደ ገና ሲነሡ ብታይ፣ እንደ ቀድሞው ዘመን ያንኑ የስጦታዎች መገለጥ ዳግመኛ ታያለች። ከእነዚህ ሁለት አሳቦች ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ይበልጥ የሚስማማው የትኛው ነው? «የመፈወስ ስጦታ» የተወገደው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነውን ወይስ ተጠያቂው ሰው ነው? ተአምራት እንዳይደረጉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውን? በዚህም ምክንያት ተአምራትን የሚያስገኘውን እምነት ከእንግዲህ አይሰጥምን? ወይስ ደግሞ በእምነት ማጣት በደለኛ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ናት?
መጽሐፍ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ በጌታም ሆነ በሐዋርያቱ ቃል የፈውስ ስጦታዎች የተሰጡት ለቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ዘመን ብቻ እንደ ሆነ እንድናምን አይፈቅድልንም፤ በተቃራኒው፣ ኢየሱስ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ ስለ ተልእኮአቸው መመሪያ ሲሰጣቸው ለሐዋርያት የሰጣቸው የተስፋ ቃሎች ለዘመናት ሁሉ የሚሠሩ ሆነው ይታዩናል (ማርቆስ 16:15—18)። ጳውሎስ የፈውስን ስጦታ ከመንፈስ ቅዱስ አሠራሮች መካከል ይቈጥረዋል። ያዕቆብ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለ ምንም የጊዜ ገደብ ግልጽ ትእዛዝ ይሰጣል። መጻሕፍት ሁሉ እነዚህ ጸጋዎች እንደ መንፈስና እንደ እምነት መጠን እንደሚሰጡ ይናገራሉ።
ደግሞም እግዚአብሔር በእያንዳንዱ አዲስ ዘመን መጀመሪያ ተአምራትን እንደሚያደርግ፣ ይህም የተለመደ አሠራሩ እንደ ሆነ ይነገራል፤ ነገር ግን እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ የለም። በቀድሞው ዘመን የነበረውን የእግዚአብሔር ሕዝብ አስብ፤ በአብርሃም ዘመን፣ በሙሴ ዕድሜ ሁሉ፣ ከግብፅ በወጡበት ጊዜ፣ በኢያሱ ዘመን፣ በመሳፍንትና በሳሙኤል ዘመን፣ በዳዊትና እግዚአብሔርን በሚፈሩ በሌሎች ነገሥታት ዘመነ መንግሥት እስከ ዳንኤል ዘመን ድረስ፤ ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ ተአምራት ይደረጉ ነበር።
ነገር ግን ተአምራት በክርስትና የመጀመሪያ ዘመን ከኋለኛው ዘመን ይልቅ እጅግ አስፈላጊ ነበሩ ይባላል። ታዲያ ወንጌል አረማዊነትን ለመዋጋት በሚሞክርበት ስፍራ ሁሉ በዚህ ዘመን እንኳ ስላለው የአረማዊነት ኃይልስ ምን ይባላል? ተአምራት ዛሬ በአፍሪካ ካሉት አረማውያን ይልቅ በኤፌሶን ለነበሩት አረማውያን (የሐዋርያት ሥራ 19:11, 12) ይበልጥ አስፈላጊ ነበሩ ብሎ መቀበል አይቻልም። በክርስቲያን ሕዝቦች መካከል እንኳ የነገሠውን አለማወቅና አለማመን ብናስብ፣ የአማኞችን ምስክርነት ለመደገፍና እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደ ሆነ ለማረጋገጥ ግልጽ የእግዚአብሔር ኃይል ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ ለመደምደም አንገደድምን? ከዚህም ሌላ በአማኞች መካከል ራሳቸው ምን ያህል ጥርጥር፣ ምን ያህል ድካም አለ! የጌታን በመካከላቸው መገኘት በሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ እምነታቸው መንቃትና መበረታታት እንዴት ያስፈልገዋል። የሁለንተናችን አንዱ ክፍል ሥጋና ደም ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር መገኘቱን ሊገልጥ የሚወደው በሥጋና በደም ነው።
የፈውስን ስጦታ ያጣችው የቤተ ክርስቲያን አለማመን እንደ ሆነ ለማረጋገጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ነገር ምን እንደሚል እንመልከት። ከአለማመን፣ ከአምላካችንም ሊያርቀንና ሊመልሰን ከሚችል ነገር ሁሉ ብዙ ጊዜ አያስጠነቅቀንምን? የቤተ ክርስቲያን ታሪክስ የእነዚህን ማስጠንቀቂያዎች አስፈላጊነት አያሳየንምን? የዓለም መንፈስ የበላይነትን በያዘበት ልክ እምነት የደከመበትን፣ ወደ ኋላ የመመለስንና ዓለምን የማስደሰትን ብዙ ምሳሌዎች አይሰጠንምን? እንዲህ ያለ እምነት ሊኖረው የሚችለው በማይታየው ዓለም የሚኖር ብቻ ነውና። እስከ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በክርስቶስ በማመን የሚደረጉ ፈውሶች ብዙ ነበሩ፤ በተከታዮቹ ክፍለ ዘመናት ግን እየተመናመኑ ሄዱ። የእግዚአብሔርን ኃያል አሠራር የሚከለክለው ሁልጊዜ አለማመን እንደ ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ አናውቅምን?
ኦ፣ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ማመንን ብንማር! እግዚአብሔር ከተስፋ ቃሎቹ ወደ ኋላ አላለም፤ ኢየሱስ አሁንም ነፍስንም ሥጋንም የሚፈውስ ያው ነው፤ ድኅነት አሁንም እንኳ ፈውስንና ቅድስናን ያቀርብልናል፤ መንፈስ ቅዱስም የኃይሉን መገለጫዎች ሊሰጠን ሁልጊዜ ዝግጁ ነው። ይህ መለኮታዊ ኃይል ለምን አዘውትሮ እንደማይታይ ስንጠይቅ እንኳ፦ «ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው» ብሎ ይመልስልናል። በእምነት የሚገኘውን ቅድስና በግል ለመለማመድ ራሳችንን በሰጠን መጠን፣ በእምነት የሚገኘውን ፈውስም ይበልጥ እንለማመዳለን። እነዚህ ሁለት ትምህርቶች ጎን ለጎን ይሄዳሉ። የእግዚአብሔር መንፈስ በአማኞች ነፍስ ውስጥ ይበልጥ በኖረና በሠራ መጠን በሥጋ ላይ የሚሠራባቸው ተአምራት ይበልጥ ይበዛሉ። በዚህም ዓለም ቤዛነት ምን ማለት እንደ ሆነ ሊያውቅ ይችላል።
ምዕራፍ 2 ተጠናቋል
ስለ እምነታችሁ ማነስ