መለኮታዊ ፈውስ
ይቅርታና ፈውስ

ምዕራፍ 1 · 3 ደቂቃ ንባብ

ይቅርታና ፈውስ

«ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፥ በዚያን ጊዜ ሽባውን። ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው» (ማቴዎስ 9:6)።

በሰው ውስጥ ሁለት ባሕርያት ተጣምረዋል። እርሱ በአንድ ጊዜ መንፈስም ግዙፍ ነገርም፣ ሰማይም ምድርም፣ ነፍስም ሥጋም ነው። ስለዚህም በአንድ በኩል የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውድቀት ምክንያት ለጥፋት የተፈረደበት ነው፤ በነፍሱ ያለው ኃጢአትና በሥጋው ያለው ሕመም ሞት በእርሱ ላይ ላለው መብት ይመሰክራሉ። በመለኮታዊ ጸጋ የተዋጀው ይህ ሁለት ገጽታ ያለው ባሕርይ ነው። መዝሙረኛው በውስጡ ያለው ሁሉ ስለ ቸርነቱ እግዚአብሔርን እንዲባርክ ሲጠራ እንዲህ ብሎ ይጮኻል፦ «ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ . . . ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ» (መዝሙር 103:3)። ኢሳይያስ የሕዝቡን መዳን አስቀድሞ ሲናገር እንዲህ ይጨምራል፦ «በዚያም የሚኖር። ታምሜአለሁ አይልም፤ በእርስዋ የሚቀመጥ ሕዝብ ኃጢአቱ ይሰረይለታል» (ኢሳይያስ 33:24)።

ቤዛው ኢየሱስ ወደዚህች ምድር በወረደ ጊዜ ይህ ትንቢት ከተጠበቀው ሁሉ በላይ ተፈጸመ። መንግሥተ ሰማያትን በምድር ላይ ሊመሠርት በመጣው በእርሱ የተደረጉት ፈውሶች ምንኛ ብዙ ነበሩ! በራሱ ሥራም ይሁን ኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በተወላቸው ትእዛዛት፣ የወንጌል ስብከትና የድውያን ፈውስ ሊያመጣው በመጣው ድኅነት ውስጥ አብረው እንደሚሄዱ በግልጽ አያሳየንምን? ሁለቱም መሲሕ ሆኖ ለመላኩ ግልጽ ማስረጃ ሆነው ተሰጥተዋል፦ «ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ . . . ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል» (ማቴዎስ 11:5)። የሰውን ነፍስና ሥጋ የለበሰው ኢየሱስ ሁለቱንም ከኃጢአት መዘዝ በእኩል መጠን ያድናል።

ይህ እውነት ከሽባው ታሪክ ይበልጥ በየትም ስፍራ አይገለጥም፤ በተሻለ ሁኔታም አይረጋገጥም። ጌታ ኢየሱስ በመጀመሪያ፦ «ኃጢአትህ ተሰረየችልህ» ይለዋል፤ ከዚያም በኋላ፦ «ተነሣና ሂድ» ብሎ ይጨምራል። የኃጢአት ይቅርታና የሕመም ፈውስ እርስ በርሳቸው ይሟሟላሉ፤ ባሕርያችንን በሙሉ በሚያየው በእግዚአብሔር ዓይን ኃጢአትና ሕመም እንደ ሥጋና እንደ ነፍስ የተቈራኙ ናቸውና። ጌታችን ኢየሱስ ከመጻሕፍት ጋር በመስማማት ኃጢአትንና ሕመምን እኛ ከምናይበት በተለየ ብርሃን ተመልክቶአቸዋል። ለእኛ ኃጢአት የመንፈሳዊው ዓለም ጉዳይ ነው፤ በእግዚአብሔር ትክክለኛ ቍጣ ሥር እንደ ሆነ፣ በእርሱም በትክክል እንደ ተፈረደበት እንቀበላለን፤ ሕመም ግን በተቃራኒው የአሁኑ ባሕርያችን ሁኔታ ክፍል ብቻ መስሎ ይታየናል፤ ከእግዚአብሔር ፍርድና ከጽድቁ ጋርም ምንም ግንኙነት የሌለው ይመስለናል። አንዳንዶች እንዲያውም ሕመም የእግዚአብሔር ፍቅርና ጸጋ ማስረጃ ነው እስከ ማለት ይደርሳሉ።

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ስለ ሕመም በዚህ ብርሃን ፈጽሞ አልተናገሩም፤ ሕመምንም እንደ በረከት፣ በትዕግሥት ሊሸከሙት እንደሚገባ የእግዚአብሔር ፍቅር ማስረጃ አድርገው ፈጽሞ አያቀርቡትም። ጌታ ደቀ መዛሙርቱ ሊሸከሟቸው ስለሚገቡ ልዩ ልዩ መከራዎች ነገራቸው፤ ስለ ሕመም ሲናገር ግን ሁልጊዜ በኃጢአትና በሰይጣን ስለ መጣ፣ ልንድንበትም ስለሚገባን ክፉ ነገር አድርጎ ነው። እያንዳንዱ ደቀ መዝሙሩ መስቀሉን መሸከም እንዳለበት እጅግ አጥብቆ ተናገረ (ማቴዎስ 16:24)፤ ነገር ግን አንድም የታመመ ሰው ታሞ ለመኖር እሺ እንዲል አላስተማረም። ኢየሱስ በየስፍራው ድውያንን ፈወሰ፤ በየስፍራውም ፈውስን የመንግሥተ ሰማያት ከሆኑት ጸጋዎች እንደ አንዱ አድርጎ ያዘው። በነፍስ ያለው ኃጢአትና በሥጋ ያለው ሕመም ሁለቱም ለሰይጣን ኃይል ይመሰክራሉ፤ «የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ» (1ኛ ዮሐንስ 3:8)።

ኢየሱስ የአብን ፍቅር ያሳውቅ ዘንድ ሰዎችን ከኃጢአትና ከሕመም ሊያድን መጣ። በሥራው፣ ደቀ መዛሙርቱን በማስተማሩ፣ በሐዋርያትም አገልግሎት ይቅርታና ፈውስ ሁልጊዜ አብረው ይገኛሉ። የሚናገሯቸው ሰዎች እንደ ደረሱበት ዕድገት ወይም እንደ እምነታቸው መጠን አንዱ ወይም ሌላው ያለ ጥርጥር ይበልጥ ጎልቶ ይታይ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ፈውስ ይቅርታን ለመቀበል መንገድ ያዘጋጅ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይቅርታ ፈውስን ይቀድም ነበር፤ ፈውሱም ከኋላ መጥቶ ለይቅርታው ማኅተም ይሆን ነበር። በአገልግሎቱ መጀመሪያ ኢየሱስ ብዙ ድውያን በመፈወሳቸው ለማመን ዝግጁ ሆነው ስላገኛቸው ፈወሳቸው። በዚህም ኃጢአትን ይቅር ማለት የሚችለው እርሱ እንደ ሆነ አውቀው እንዲቀበሉት ልቦችን ለማነሣሣት ፈለገ። ሽባው ይቅርታን ወዲያውኑ ሊቀበል እንደሚችል ባየ ጊዜ እጅግ አስፈላጊ በሆነው ነገር ጀመረ፤ ከዚያም በኋላ ለተሰጠው ይቅርታ ማኅተም የሆነው ፈውስ መጣ።

በወንጌሎች ከተጻፉት ታሪኮች እንደምናየው፣ በዚያን ጊዜ ለነበሩት አይሁድ በመለኮታዊ ፈውስ ከማመን ይልቅ በኃጢአታቸው ይቅርታ ማመን ይከብዳቸው ነበር። አሁን ግን ተቃራኒው ነው። የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን የኃጢአትን ይቅርታ ስብከት እጅግ ብዙ ስለ ሰማች፣ የተጠማች ነፍስ ይህን የጸጋ መልእክት በቀላሉ ትቀበላለች፤ መለኮታዊ ፈውስ ግን እንደዚህ አይደለም፤ ስለ እርሱ እምብዛም አይነገርም፤ የተለማመዱትም አማኞች ብዙ አይደሉም። እውነት ነው፤ በዚህ ዘመን ፈውስ ክርስቶስ ቀድሞ ምንም ሳይመለሱ ለፈወሳቸው ብዙ ሕዝብ እንደ ተሰጠ እንደዚያን ጊዜ አይሰጥም። ፈውስን ለመቀበል በኃጢአት ኑዛዜና በቅድስና ለመኖር በመቍረጥ መጀመር ያስፈልጋል። ሰዎች ከይቅርታ ይልቅ በፈውስ ለማመን የሚቸገሩበት ምክንያት ያለ ጥርጥር ይህ ነው፤ ፈውስን የሚቀበሉ ሰዎች በዚያው ጊዜ አዲስ መንፈሳዊ በረከት የሚቀበሉት፣ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ይበልጥ እንደ ተቈራኙ የሚሰማቸው፣ እርሱንም ይበልጥ መውደድንና ማገልገልን የሚማሩትም ስለዚሁ ነው። አለማመን እነዚህን ሁለት ስጦታዎች ለመለያየት ይሞክር ይሆናል፤ በክርስቶስ ግን ሁልጊዜ አንድ ናቸው። እርሱ ሁልጊዜ የነፍስም የሥጋም ያው አዳኝ ነው፤ ይቅርታንም ፈውስንም ለመስጠት በእኩል ዝግጁ ነው። የተዋጁት ሁልጊዜ እንዲህ ብለው ሊጮኹ ይችላሉ፦ «ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ . . . ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ» (መዝሙር 103:3)።

ምዕራፍ 1 ተጠናቋል

ይቅርታና ፈውስ

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል