መለኮታዊ ፈውስ
የእግዚአብሔር ኃይል መገለጥ አስፈላጊነት

ምዕራፍ 17 · 3 ደቂቃ ንባብ

የእግዚአብሔር ኃይል መገለጥ አስፈላጊነት

የሐዋርያት ሥራ 4:29—31 ዛሬም እንዲህ ብሎ መጸለይ፣ ጌታን፦ «ለመፈወስ እጅህን ስትዘረጋ ለባሮችህ ቃልህን በፍጹም ግልጥነት እንዲናገሩ ስጣቸው» (የተሻሻለው ትርጉም) ብሎ መለመን ይፈቀዳልን? ይህን ጥያቄ እንመርምር።

የእግዚአብሔር ቃል በዚያን ጊዜ እንደ ገጠመው በዘመናችንም ብዙ መሰናክል አይገጥመውምን? ዛሬስ ያለው ችግር እንዲሁ አስቸኳይ አይደለምን? ሐዋርያትን በኢየሩሳሌምና በአለማመንዋ መካከል ሆነው በዓይነ ሕሊናችን እንያቸው፤ በአንድ ወገን የሕዝቡ አለቆችና ዛቻቸው፣ በሌላ ወገን ደግሞ በተሰቀለው ለማመን እንቢ ያሉ የታወሩ ብዙ ሕዝብ ነበሩ። አሁን ዓለም ቤተ ክርስቲያንን መፍራቱን ስለ ተወ እንደ ቀድሞው በግልጥ አይጠላትም፤ ነገር ግን የሽንገላ ቃሉ ከጥላቻው ይልቅ የሚያስፈራ ነው። ማስመሰል አንዳንድ ጊዜ ከግፍ ይከፋል። በግዴለሽነት እንቅልፍ ውስጥ ያለ የመልክ ብቻ ክርስትናስ በግልጥ እንደሚቃወመው የአይሁድ እምነት ያህል የማይደረስበት አይደለምን? ቃሉ በፍጹም ግልጥነት ይሰበክ ዘንድ፣ የእግዚአብሔር ባሮች በዚህ ዘመንም እንኳ የእግዚአብሔር ኃይል በመካከላቸው በግልጥ እንዲገለጥ ያስፈልጋቸዋል።

የእግዚአብሔር ርዳታ በዚያን ጊዜ እንደ ነበረው አሁንም አስፈላጊ አይደለምን? እውነትን ድል ያስነሣው የስብከታቸው አንደበተ ርቱዕነት እንዳልሆነ ሐዋርያት በሚገባ ያውቁ ነበር፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ መገኘቱን በተአምራት እንዲገልጥ የግድ እንደሚያስፈልግ ያውቁ ነበር። በቅዱስ ልጁ በኢየሱስ ስም ፈውስ፣ ተአምራትና ምልክቶች ይሆኑ ዘንድ ሕያው እግዚአብሔር እጁን ሊዘረጋ ያስፈልግ ነበር። ባሮቹ ደስ የተሰኙት፣ በመገኘቱም በርትተው ቃሉን በግልጥነት መናገርና ዓለምን ስሙን እንዲፈራ ማስተማር የቻሉት በዚህ ብቻ ነበር።

መለኮታዊው የተስፋ ቃል እኛንም አይመለከተንምን? ሐዋርያት ጌታ ከማረጉ በፊት በተናገረው በዚህ ቃል ተማምነው ነበር፦ «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ… ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል… እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ» (ማርቆስ 16:15, 17, 18)። ይህ ትእዛዝ የቤተ ክርስቲያንን መለኮታዊ ጥሪ ያመለክታል፤ ከእርሱም በኋላ የሚመጣው የተስፋ ቃል የጦር ዕቃዋ ምን እንደ ሆነ ያሳየናል፤ ጌታም ከእርስዋ ጋር አብሮ እንደሚሠራ ያረጋግጥልናል። ሐዋርያት ይህን የመገኘቱን ማስረጃ እንዲሰጣቸው ጌታን የለመኑት በዚህ የተስፋ ቃል ስለ ተማመኑ ነበር። በበዓለ ኀምሳ ቀን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ነበር፤ ነገር ግን ኃይሉ የሚሠራቸው ከተፈጥሮ በላይ የሆኑ ምልክቶች ገና ያስፈልጓቸው ነበር። ያው የተስፋ ቃል ለእኛም እንዲሁ ነው፤ ወንጌልን ስለ መስበክ የተሰጠው ትእዛዝ አብሮት ከሚሄደው ከመለኮታዊ ፈውስ የተስፋ ቃል ሊለይ አይችልምና። ይህ የተስፋ ቃል ለሚመጡት ዘመናት አይደለም የሚል ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትም አይገኝም። በዘመናት ሁሉ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጌታ ከእነርሱ ጋር እንዳለ ማወቅና የማይካድ ማስረጃውንም መያዝ እጅግ ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ ይህ የተስፋ ቃል ለእኛ ነው፤ እንዲፈጸምም እንጸልይ።

ያንኑ ጸጋ ልንጠብቅ ይገባናልን? ሐዋርያት በጸለዩ ጊዜ እንዲህ እንደ ሆነ በሐዋርያት ሥራ እናነባለን፦ «ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥነት ተናገሩ።» «በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር… የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ» (የሐዋርያት ሥራ 4:31፤ 5:12—15)። ኦ፣ ጌታ ዳግመኛ እንዲህ እጁን ቢዘረጋ የእግዚአብሔር ሕዝብ ዛሬ ምንኛ ደስታና ምንኛ አዲስ ብርታት በተቀበሉ ነበር! ስንቶች የደከሙና ተስፋ የቈረጡ ሠራተኞች በድካማቸው ላይ ብዙ ፍሬ፣ ብዙ በረከት ባለማየታቸው ያዝናሉ! እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንዳለ የሚያረጋግጡላቸው እንዲህ ያሉ ምልክቶች ቢነሡ በእምነታቸው ውስጥ ምንኛ ሕይወት በገባ ነበር! ግድ የለሽ የሆኑ ብዙዎች ወደ ማሰላሰል በተመሩ ነበር፤ ከአንድ በላይ የሆኑ ተጠራጣሪዎች መተማመናቸውን መልሰው ባገኙ ነበር፤ የማያምኑትም ሁሉ ዝም በተሰኙ ነበር። ምስኪኑ አረማዊስ! ቃላት እንዲጨብጠው ያላስቻሉትን በተግባር ቢያየው፣ የክርስቲያኑ አምላክ ድንቅ የሚያደርግ ሕያው አምላክ፣ የሚባርክም የፍቅር አምላክ መሆኑን ለመቀበል ቢገደድ እንዴት በነቃ ነበር!

የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሆይ፣ ንቂ፣ ንቂ፣ ኃይልሽን ልበሺ! የቃሉ ስብከት ለመፈወስ ከተዘረጋው ከጌታ እጅ ጋር ተባብሮ የማየትን ደስታ በታማኝነት ጕድለትሽ ብታጪም፣ ጌታ ይህን ጸጋ ዳግመኛ ሊሰጥሽ የተዘጋጀ ነው። ይህን ለረጅም ጊዜ ያሳጣሽ የራስሽ አለማመን መሆኑን አምነሽ ተናዘዢ፤ ይቅርታንም ለምኚ። የጸሎትን ብርታት ልበሺ።

«የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ፥ ንቃ፥ ንቃ፥ ኃይልን ልበስ፤ እንደ ቀድሞው ዘመን ንቃ» (ኢሳይያስ 51:9)።

ምዕራፍ 17 ተጠናቋል

የእግዚአብሔር ኃይል መገለጥ አስፈላጊነት

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል