ምዕራፍ 14 · 2 ደቂቃ ንባብ
መንፈስ ቅዱስ የፈውስ መንፈስ
1ኛ ቆሮንቶስ 12:4, 9, 11 የእግዚአብሔርን ልጆች የሚለያቸው ምንድር ነው? ክብራቸውስ ምንድር ነው? እግዚአብሔር በመካከላቸው ማደሩና በኃይል ራሱን ለእነርሱ መግለጡ ነው (ዘጸአት 33:16፤ 34:9, 10)። በአዲስ ኪዳን ሥር ይህ እግዚአብሔር በአማኝ ውስጥ ማደሩ ከቀድሞው ዘመን ይልቅ ይበልጥ ይገለጣል። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን የክርስቶስ አካል ወደ ሆነችው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በእርስዋ ውስጥ በኃይል እንዲሠራ ይልካል፤ ሕይወትዋና ብልጽግናዋም በእርሱ ላይ የተመሠረተ ነው። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን፣ የጌታ አካል መሆንዋ እንዲታወቅ መንፈስ በእርስዋ ውስጥ ያለ ገደብ ሙሉ ነጻነት ማግኘት አለበት። በየዘመኑ ቤተ ክርስቲያን የመንፈስን መገለጦች ልትጠባበቅ ትችላለች፤ እነርሱ የማይፈርስ አንድነታችንን ይመሠርታሉና፤ «አንድ አካልና አንድ መንፈስ» (ኤፌሶን 4:4)።
መንፈስ በዚህ ወይም በዚያ የቤተ ክርስቲያን ብልት ውስጥ በልዩ ልዩ መንገድ ይሠራል። ለአንድ ልዩ ሥራ በመንፈስ ተሞልቶ ለሌላው ግን አለመሞላት ይቻላል። ደግሞም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አንዳንድ የመንፈስ ስጦታዎች በኃይል የሚሰጡበት፣ በዚያው ጊዜ ግን አለማወቅ ወይም አለማመን ሌሎችን ስጦታዎች የሚያደናቅፍበት ዘመናት አሉ። ይበልጥ የበዛው የመንፈስ ሕይወት በሚገኝበት ሁሉ ስጦታዎቹን ሁሉ እንዲገልጥ ልንጠብቀው እንችላለን።
የፈውስ ስጦታ እጅግ ውብ ከሆኑት የመንፈስ መገለጦች አንዱ ነው። ስለ ኢየሱስ፦ «እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ» ተብሎ ተጽፎአል (የሐዋርያት ሥራ 10:38)። በእርሱ ውስጥ የነበረው መንፈስ ቅዱስ የፈውስ መንፈስ ነበረ፤ ከበዓለ ኀምሳም በኋላ በደቀ መዛሙርቱ ውስጥ ያው ነበረ። ስለዚህ የጥቅሳችን ቃላት የጥንቲቱ ቤተ ክርስቲያን የማያቋርጥ ተሞክሮ ምን እንደ ነበረ ይገልጣሉ (በጥንቃቄ አስተያይ፦ የሐዋርያት ሥራ 3:7፤ 4:30፤ 5:12, 15, 16፤ 6:8፤ 8:7፤ 9:41፤ 14:9, 10፤ 16:18, 19፤ 19:12፤ 28:8, 9)። የመንፈስ በብዛት መፍሰስ ብዙ ፈውስን አስገኘ። ይህ በዘመናችን ላለችው ቤተ ክርስቲያን እንዴት ያለ ትምህርት ነው!
መለኮታዊ ፈውስ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። የክርስቶስ ቤዛነት ብርቱ አሠራሩን እስከ አካል ድረስ ያደርሳል፤ ይህንንም ወደ እኛ የማስተላለፍና በእኛ ውስጥ የመጠበቅ ኃላፊነት የመንፈስ ቅዱስ ነው። አካላችን የቤዛነት ጥቅም ተካፋይ ነው፤ አሁንም እንኳ በመለኮታዊ ፈውስ በኩል መያዣውን ሊቀበል ይችላል። የሚፈውሰው ኢየሱስ ነው፤ የሚቀባውና በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀውም ኢየሱስ ነው። ደቀ መዛሙርቱን በዚያው መንፈስ ያጠመቀው ኢየሱስ፣ እዚህ በምድር ላይ መንፈስ ቅዱስን የሚልክልን እርሱ ነው— ሕመምን ከእኛ ለማራቅ፣ ወይም ሕመም በያዘን ጊዜ ወደ ጤና ሊመልሰን።
መለኮታዊ ፈውስ በመንፈስ ከሚሆነው ቅድስና ጋር አብሮ ይሄዳል። መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስ ቤዛነት ተካፋዮች የሚያደርገን ቅዱሳን ሊያደርገን ነው። ስሙ «ቅዱስ» የተባለው ስለዚህ ነው። ስለዚህ የሚሠራው ፈውስ የመለኮታዊ ተልእኮው ውስጣዊ ክፍል ነው፤ ይህንንም የሚሰጠው የታመመውን ሰው ወደ መመለስና ወደ ማመን ለመምራት (የሐዋርያት ሥራ 4:29, 30፤ 5:12, 14፤ 6:7, 8፤ 8:6-8)፣ ወይም አስቀድሞ ተመልሶ ከሆነ እምነቱን ለማጽናት ነው፤ እንዲህም ኃጢአትን እንዲተውና ራሱን ፈጽሞ ለእግዚአብሔርና ለአገልግሎቱ እንዲቀድስ ያስገድደዋል (1ኛ ቆሮንቶስ 10:31፤ ያዕቆብ 5:15, 16፤ ዕብራውያን 12:10)።
መለኮታዊ ፈውስ ኢየሱስን ወደ ማክበር ያዘነብላል። ልጁ እንዲከበር የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም የክርስቶስ ቤዛነት ለእኛ የሚያደርግልንን ሊያሳየን ሲመጣ ይህን ያደርጋል። የሚሞተው አካል ቤዛነት ከማትሞተው ነፍስ ቤዛነት ይልቅ እጅግ የሚደነቅ ይመስላል ማለት ይቻላል። በእነዚህ በሁለቱ መንገዶች እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል በእኛ ውስጥ ሊያድርና በዚህም ሥጋን ድል ሊነሣ ይወዳል። አካላችን በመንፈስ በኩል የእግዚአብሔር መቅደስ እንደ ሆነ ወዲያውኑ ኢየሱስ ይከበራል።
የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል በሚሠራበት ስፍራ ሁሉ መለኮታዊ ፈውስ ይሆናል። ለዚህም ማስረጃዎች በተሐድሶ አራማጆች ሕይወት፣ እንዲሁም በመልካሙ ዘመናቸው በነበሩ በአንዳንድ ሞራቪያውያን ሕይወት ውስጥ ይገኛሉ። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ያልተፈጸሙ ስለ መንፈስ ቅዱስ መፍሰስ የሚናገሩ ሌሎች የተስፋ ቃሎች ገና አሉ። ጌታ በእኛ ውስጥ እንዲፈጽማቸው እየለመንን በቅዱስ ተስፋ እንኑር።
ምዕራፍ 14 ተጠናቋል
መንፈስ ቅዱስ የፈውስ መንፈስ