ምዕራፍ 10 · 3 ደቂቃ ንባብ
ጌታ ለሥጋ
1ኛ ቆሮንቶስ 6:13 እግዚአብሔር ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት የሁለት ወገን ነው። እግዚአብሔር ለእኔ የሆነልኝን፣ እኔም በተራዬ ለእርሱ ልሆንለት ይገባኛል። ለእርሱ የምሆንለትንም፣ እርሱ ደግሞ መልሶ ለእኔ ሊሆንልኝ ይወዳል። በፍቅሩ ራሱን ፈጽሞ ለእኔ ቢሰጥ፣ እኔም በፍቅር ራሴን ፈጽሜ ለእርሱ እንድሰጥ ነው። ሁለንተናዬን በበዛም ባነሰም መጠን በእውነት ለእርሱ ባስረከብሁበት ልክ፣ በዚያው ልክ እርሱም ራሱን ይበልጥ በእውነት ለእኔ ይሰጣል። በዚህ መንገድ እግዚአብሔር አማኙ ይህ ራስን መስጠት ሥጋንም እንደሚጨምር እንዲረዳ ይመራዋል፤ ሕይወታችን ሥጋ ለጌታ እንደ ሆነ ይበልጥ በመሰከረ መጠን፣ ጌታም ለሥጋ እንደ ሆነ ይበልጥ በተሞክሮ እናውቃለን። «ሥጋ ግን ለጌታ ነው» ስንል፣ ሥጋችንን ፈጽሞ ለእርሱ የተለየ፣ ለጌታ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበና በእርሱ የተቀደሰ አድርገን ልንቈጥረው ያለንን ምኞት እንገልጣለን። «ጌታም ለሥጋ ነው» ስንል ደግሞ መባችን ተቀባይነት እንዳገኘ፣ ጌታም በመንፈሱ የገዛ ብርታቱንና ቅድስናውን ለሥጋችን እንደሚያካፍል፣ ከእንግዲህም እንደሚያበረታንና እንደሚጠብቀን ያለንን የከበረ እርግጠኝነት እንገልጣለን።
ይህ የእምነት ጉዳይ ነው። ሥጋችን ግዙፍ፣ ደካማ፣ ልፍስፍስ፣ ኃጢአተኛና ሟች ነው። ስለዚህ «ጌታም ለሥጋ ነው» የሚለውን ቃል ሙሉ ስፋት በአንድ ጊዜ መጨበጥ አስቸጋሪ ነው። ይህን የራሳችን የምናደርግበትን መንገድ የሚያስረዳን የእግዚአብሔር ቃል ነው። ሥጋ በጌታ ለጌታም ተፈጠረ። ኢየሱስ ምድራዊ ሥጋን ለበሰ። በሥጋው ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ፤ በዚህም ሥጋችንን ከኃጢአት ኃይል ነጻ አወጣው። በክርስቶስ ሥጋ ከሙታን ተነሥቶ በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ተቀምጧል። ሥጋ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው፤ በሰማይ ክብር ለዘላለም እንዲካፈል ተጠርቷል። ስለዚህ በእርግጠኝነት፣ በሰፊና ሁሉን አቀፍ ትርጕምም፦ «አዎን፣ ጌታ ኢየሱስ፣ አዳኛችን፣ ለሥጋ ነው» ማለት እንችላለን። ይህ እውነት በብዙ መንገድ ሥራ ላይ ይውላል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ለተግባራዊ ቅድስና ታላቅ ረዳት ነው። ብዙ ኃጢአት ብርታቱን የሚያገኘው ከአንዳች ሥጋዊ ዝንባሌ ነው። ንስሐ የገባ ሰካራም የሚያሰክሩ መጠጦችን ይጸየፋል፤ ቢሆንም ምኞቱ አንዳንድ ጊዜ ወጥመድ ይሆንበታል፤ አዲሱንም እምነቱን ያሸንፋል። ነገር ግን በትግሉ ሥጋውን በመተማመን ለጌታ ቢሰጥ፣ ሥጋዊ ምኞት ሁሉ፣ የመጠጣት ፍላጎትም ሁሉ ድል ይሆናል። ቍጣችንም ብዙ ጊዜ ከሥጋዊ ተፈጥሮአችን ይመነጫል። የተወጠረና በቀላሉ የሚበሳጭ ነርቭ የሚያቈስሉ፣ ሻካራና ፍቅር የጐደላቸው ቃላትን ያወጣል። ነገር ግን ይህ ሥጋዊ ዝንባሌ ያለበት ሥጋ ወደ ጌታ ይቅረብ፤ መንፈስ ቅዱስም የትዕግሥት ማጣትን መነሣሣት ሊገድል፣ ሥጋንም ቀድሶ ያለ ነቀፋ ሊያደርገው እንደሚችል ቶሎ ይታወቃል።
«ጌታም ለሥጋ ነው» የሚለው ቃል የጌታ አገልግሎት ከእኛ ለሚጠይቀው የሥጋ ብርታትም ይሠራል። ዳዊት፦ «በኃይል የሚያስታጥቀኝ እግዚአብሔር ነው» ብሎ ሲጮኽ የሥጋን ብርታት ማለቱ ነው፤ እንዲህ ብሎ ይጨምራልና፦ «እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል... ክንዶቼም የናስ ቀስት ይለጥጣሉ» (መዝሙር 18:33, 34፣ የተሻሻለው ትርጉም)። ደግሞም፦ «እግዚአብሔር የሕይወቴ ኃይል ነው» (መዝሙር 27:1) በሚለው ቃል መንፈሳዊውን ሰው ብቻ ሳይሆን ሰውን ሁለንተናውን ማለቱ ነው። ብዙ አማኞች፦ «እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ኃይላቸውን ያድሳሉ» (ኢሳይያስ 40:31) የሚለው የተስፋ ቃል ሥጋንም እንደሚመለከት፣ መንፈስ ቅዱስም የሥጋን ብርታት እንደሚያበዛ በተሞክሮ አውቀዋል።
ነገር ግን «ጌታም ለሥጋ ነው» የሚለውን የዚህን ቃል እውነት በተለይ የምናየው በመለኮታዊ ፈውስ ነው። አዎን፣ ሉዓላዊውና መሓሪው ፈዋሽ ኢየሱስ ለማዳንና ለመፈወስ ሁልጊዜ ዝግጁ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በስዊዘርላንድ በሳንባ ነቀርሳ የታመመችና ለሞት የቀረበች አንዲት ወጣት ልጃገረድ ነበረች። ሐኪሙ ለዘብ ያለ የአየር ጠባይ ወዳለበት ስፍራ እንድትሄድ መክሯት ነበር፤ እርሷ ግን ጕዞውን ለማድረግ እጅግ ደካማ ነበረች። ኢየሱስ የድውያን ፈዋሽ እንደ ሆነ ተማረች። ይህን የምሥራች አመነች፤ አንድ ሌሊትም ስለዚሁ ጉዳይ ስታስብ የጌታ ሥጋ ወደ እርሷ የቀረበ መሰላት፤ «ሥጋው ለሥጋችን» የሚለውንም ቃል ቃል በቃል ልትቀበለው እንደሚገባ ተሰማት። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ መሻሻል ጀመረች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ጀመረች፤ ቆይቶም በሴቶች መካከል ለጌታ የምትሠራ ቀናተኛና እጅግ የተባረከች ሠራተኛ ሆነች። ጌታ ለሥጋ እንደ ሆነ ማስተዋልን ተምራ ነበር።
የታመምህ ውድ ወዳጄ ሆይ፣ ጌታ ኃጢአት በሥጋ ላይ ምን ያህል ኃይል እንዳለው በሕመም አሳይቶሃል። በፈውስህ ደግሞ የሥጋን ቤዛነት ኃይል ሊያሳይህ ይወዳል። እስከ አሁን ያላስተዋልኸውን፣ «ሥጋ ግን ለጌታ ነው» የሚለውን እንድታሳይ ይጠራሃል። ስለዚህ ሥጋህን ስጠው። ከሕመምህና የሕመም የመጀመሪያ ምንጭ ከሆነው ከኃጢአት ጋር ስጠው። ጌታ ይህን ሥጋ በኃላፊነት እንደ ያዘው ዘወትር እመን፤ እርሱም በእውነት ለሥጋ የሆነው ጌታ መሆኑን በኃይል ይገልጣል። በዚህ ምድር ላይ ራሱ ሥጋን የለበሰውና ያደሰው ጌታ፣ አሁን ካለበት ከሰማያት ሰማይ፣ የከበረውን ሥጋውን ለብሶ መለኮታዊ ብርታቱን ይልክልናል፤ በዚህም ኃይሉን በሥጋችን ሊገልጥ ይወዳል።
ምዕራፍ 10 ተጠናቋል
ጌታ ለሥጋ