የሰማይ ቀናት በምድር ላይ
ኖቬምበር

ምዕራፍ 11 · 21 ደቂቃ ንባብ · 27 ደቂቃ ማዳመጥ

ኖቬምበር

ኖቬምበር 1

«ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን» (ዮሐንስ 14:23)።

የራስህን ቅድስና ለማግኘት ደክመህ ከዚያም ክርስቶስ ስለ እርሱ እንዲሸልምህ መጠበቅ — ይህ አሳብ የእርሱ ትምህርት አይደለም። ኧረ በጭራሽ! ቅድስናው ራሱ ክርስቶስ ነው፤ እርሱ ቅድስናውን ይዞ ይመጣል፤ መጥቶም ለዘላለም በልብ ውስጥ ይኖራል።

ከባለ ሚሊዮኖቻችን አንዱ አሮጌ ጎጆ የቆመበትን ቦታ ሲገዛ አሮጌውን ጎጆ አያድሰውም፤ ይልቁንም ያገለገሉ ዕቃዎችን የሚገዛ ሰው፣ ቢፈልገው፣ መጥቶ እንዲያፈርሰው ያደርጋል፤ በስፍራውም ታላቅ መኖሪያ ቤት ይሠራል። የሚያስፈልግህ ቤቱን ማደስ አይደለም፤ ባዶውን ቦታ ለክርስቶስ መስጠት ነው እንጂ፤ እርሱም ከአሮጌው ሕይወታችን በታች ቈፍሮ ለዘላለም የሚኖርበትን ቤት ይሠራል።

ክርስቶስ ራሱ ለበረከቱ ዝግጅት ይሆናል፣ ለራሱም መምጣት መንገድ ያዘጋጃል ስንል ይህን ማለታችን ነው። ይህም አንድ ታላቅ የአሦር ንጉሥ ለዘመቻ በሚነሣበት ጊዜ ያደርግ እንደ ነበረው ነው። ሕዝቡን መንገድ እንዲሠሩ አያዝዛቸውም ነበር፤ ይልቁንም የራሱን ሰዎች አስቀድሞ ይልክ ነበር፤ እነርሱም ዛፎቹን ይቈርጡ፣ የተሰበሩትን ስፍራዎች ይሞሉ፣ ተራሮቹንም ይደለድሉ ነበር። እንዲሁ እርሱም፣ ብንፈቅድለት፣ የሚመጣው ንጉሥ፣ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ ይሆናል።

ኖቬምበር 2

«ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን» (2ኛ ቆሮንቶስ 10:5)።

በክርስቶስ እንኖር ዘንድ ብንወድ በራሳችን ምንም መታመን ሊኖረን አይገባም። ራስን መግታት ለመለኮታዊ ሙላትና ብቃት ሁልጊዜ ቀዳሚው አስፈላጊ ነገር ሊሆን ይገባዋል። አንድ ድንገተኛ ጉዳይ ሲነሣ ምን ያህል ፈጥነህ ወደ ፊት እንደምትዘልል ታውቃለህ። አንተን የሚመለከት ነገር ሲመጣ በድንገተኛ ግፊት የምታስበውን ትናገራለህ፤ ከዚያም ምናልባት አሳብህን መልሰህ በእርሱ ፋንታ የጌታን አሳብ ለመቀበል ሳምንታት ይፈጅብሃል። ጌታ ሊጠቀምብን የሚችለው ከመንገዱ ገለል ስንልለት ብቻ ነው። ስለዚህ ከራስህ ውጣ፤ ስለ ነገር ሁሉ ተመልክተህ፦ «ጌታ ሆይ፣ ፈቃድህ ምንድር ነው? ስለዚህ ነገር ያለህ አሳብ ምንድር ነው?» እስክትል ድረስ ፈቃድህን ሁልጊዜ አቈይ።

እንዲህ በክርስቶስ የሚኖሩ ሰዎች የመቈጠብና የጸጥታ ልማድ አላቸው፤ ለፍላፊዎችና ግድ የለሽ ተናጋሪዎች አይደሉም፤ ስለ ነገር ሁሉ ሁልጊዜ አስተያየት አይኖራቸውም፤ የሚያደርጉትንም ሁልጊዜ አስቀድመው አያውቁም። በአክብሮት ፍርድን የመያዝና ከእግዚአብሔር ጋር በዝግታ የመመላለስ ጠባይ ይኖራቸዋል። ጌታን እንዳንሰማውና እንዳንከተለው ዘወትር የሚያግደን ችኩልና ግልፍተኛ መንፈሳችን ነው።

ኖቬምበር 3

«ውዴ ይህ ነው፥ ወዳጄም ይህ ነው» (መኃልየ መኃልይ 5:16)።

እርሱ ወዳጃችን ነው። «ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው፥ በእኩል ሌሊትስ …?» ይህ ቃል በእያንዳንዳችን ልምምድ ጥልቅ ትርጉም አለው። በአንዳንድ ነገሮች ከአባት እንኳ የሚበልጥ ወዳጅ ያልነበረው ማን አለ?

ከሰው ደም ያልተወለዱ፣ ሆኖም ከምድራዊ ፍቅር ማሰሪያዎች ሁሉ እጅግ የጠነከሩና የሚጸኑ የሆኑ አንዳንድ ቅርበቶች አሉ። አንድ በአንድ እንቍጠራቸው፤ እያንዳንዱን የፍቅር ሥራና ማሰሪያ እናስታውስ፤ በእነርሱ የምንታመንባቸውን ነገሮች ሁሉ፣ ከጎናችንም የቆሙባቸውን ጊዜያት ሁሉ እናስብ፤ ከዚያም የትዝታንና የፍቅርን ሙሉ ክብደት አንድ ላይ ስናከማች፣ እግዚአብሔርን በዚያ የመታመን ስፍራ እናኑረው፤ እርሱም ያ ሁሉ፣ እንዲያውም ከዚያ እጅግ የሚበልጥ እንደ ሆነ እናስብ።

ወዳጃችን! በግል ስለ እኛ የሚያስብ፤ ልቡን በእኛ ላይ ያኖረ፤ በማይነገር ኅብረት ርኅሩኅና ስስ ቅርበት ወደ እኛ የቀረበ፤ በዋጋ የማይተመኑ መያዣዎችንና የተስፋ ቃሎችን የሰጠን፤ ስለ እኛ እጅግ ብዙ ያደረገ፣ እኛንም ለመርዳት ማንኛውንም ድካም ለመቀበል ወይም ማንኛውንም ወጪ ለማውጣት ሁልጊዜ ዝግጁ የሆነ — ወደ እርሱ፣ ወደ ሰማያዊው ወዳጃችን፣ በጸሎት እንመጣለን።

ኖቬምበር 4

«በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት ይልቅ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልን?» (1ኛ ሳሙኤል 15:22)።

ብዙ ነፍስ ስለ መቀደስ ይጸልያል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስና በውስጣችን በሚኖረው መንፈስ የወሰነውን መንገድ በማስተዋል ስለማይረዳና በእምነት ስለማይቀበል ወደ በረከቱ መግባት ይሳነዋል። ስለ ሌሎች መዳን የሚቀርብ ብዙ ጸሎት ይታገዳል፤ ምክንያቱም የሚጸልየው ወዳጅ ራሱ መልሱን ለማምጣት የተሳሳተ መንገድ ይይዛል፤ መልካሙን ዓላማውን ፈጽሞ ሊያከሽፉ ወደሚችሉ ዘዴዎችም ይሄዳል።

ለባልዋ ነፍስ የምትማልድ፣ የሚያስቀይመውንም ነገር ሁሉ በማስወገድና ለዓለማዊ ፍላጎቶቹ ሁሉ በመሸነፍ ወደ ክርስቶስ ልትስበው በከንቱ ተስፋ የምታደርግ ብዙ ሚስት እናውቃለን። ከዚህ እጅግ የሚበልጥ ፍሬ የሚያስገኘው ግን ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆንና ስለ እርሱ ያለ ፍርሃት መመስከር ነው፤ እግዚአብሔር ሊባርከው የሚችለው እንዲህ ያለውን አቋም ነውና።

ብዙ ጉባኤ ለምን እንዲህ ድሀና በችግር የሚታገል እንደ ሆነ ይገረማል። የገንዘብ አሰባሰብ ዘዴዎቹ ፈጽመው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑና ብዙ ጊዜም ለተራ ራስን ማክበር እንኳ የማይገቡ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ።

እግዚአብሔርን ማንኛውንም በረከት ስንለምን መልሱን የሚያመጡትን እርምጃዎች እርሱ እንዲመራ መፍቀድ አለብን።

ኖቬምበር 5

«እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ» (ዮሐንስ 17:23)።

እስከ እግዚአብሔር ዓላማ ሙሉ ልክ ድረስ እንሰፋ ዘንድ ብንወድ፣ እርሱ እንዲሞላን ያለንን የራሳችንን አቅም በጥቂቱ እንኳ ለመገንዘብ እንጣር።

የሰው ነፍስና መንፈስ ምን ያህል ታላቅ እንደ ሆነ እምብዛም አናውቅም። እርሱ ልብን እስኪያድስ፣ እስኪያነጻና እስኪገባበት ድረስ፣ እግዚአብሔር በራሱ መልክ የፈጠረውንና አሁንም በጌታ ኢየሱስ ራሱ አምሳል የሚያድሰውን ፍጡር ዕድሎች በሚገባ ልንገነዘብ ፈጽሞ አንችልም።

ቢሆንም እግዚአብሔር የሰውን ነፍስ ቤተ መቅደሱና መኖሪያው እንድትሆን እንደ ፈጠራት፣ ወሰን የሌለውን ሙላቱን ሊይዝ የሚችል ቤት እንዴት እንደሚሠራም እንደሚያውቅ እናውቃለን። መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ ተፈጥሮአችን ሁሉ እንደ ጸደይ ወራት ሕይወት ሲነቃቃ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜም አዳዲስ ጥምቀቶች እንዳሉን የማናውቃቸውን ያንቀላፉ ኃይሎችንና ስሜቶችን ሲያነቁ፣ ከዚህ ነገር ጥቂቱን እናውቃለን።

እንግዲህ ከእኛ የተሻለውን ያደርግ ዘንድ መብቱን እንስጠው፤ እኛም በመደነቅ ተሞልተን አንድ ቀን እርሱ ያቆመውን የከበረ ቤተ መቅደስ እናያለን፤ «ጌታ ሆይ፣ ልብህን በእርሱ ላይ ታኖር ዘንድ ሰው ምንድር ነው?» እንላለንም።

ኖቬምበር 6

«ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ» (መዝሙር 103:1)።

ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ በውስጤ ያለውም ሁሉ ቅዱስ ስሙን ለማክበር ይነቃቃ። «ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ ቸርነቱንም ሁሉ አትርሺ፤ ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥ ሕይወትሽን ከጥፋት የሚቤዥ፥ በምሕረቱና በርኅራኄው ዘውድ የሚያቀዳጅሽ፥ አፍሽን በበጎ ነገር የሚያጠግብ፤ ጕልማስነትሽም እንደ ንስር ይታደሳል።» ብዙዎቻችን፣ እንደምንታመነው፣ በዚህ ሙሉ መዳን ደስ እያለንና ስለ ተነሣው ጌታ የከበረ ጤናና ስለማያልቀው ወጣትነት እግዚአብሔርን እያመሰገንን ስለ ሆንን፣ ይህን የምስጋና መዝሙር እንደ እኛ በሚገባ ሊዘምር የሚችል ማን ነው?

ይህ መዝሙርና የመጀመሪያዎቹ ቁጥሮቹ፣ ፊደላትና ቁጥሮች በትክክል ሲቈጠሩ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት እምብርት ላይ ይገኛሉ። እንዲሁም በሕይወታችን መካከል ይቁም፤ ወደ ኋላና ወደ ፊት፣ ወደ ላይም በአመስጋኝ ልብ ስንመለከት፣ በመዝጊያ ዜማዎቹም፦ «ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ በውስጤ ያለውም ሁሉ ቅዱስ ስሙን ይባርክ» ብለን ስንዘምር። ጌታ ሆይ፣ ልቤን በአንተ፣ በፍቅርና በምስጋናም መንፈስ ውስጥ አጽናው።

ኖቬምበር 7

«አበረታሃለሁ፥ እረዳሃለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ እጅ ደግፌ እይዝሃለሁ» (ኢሳይያስ 41:10)።

እግዚአብሔር የሚረዳን በሦስት መንገዶች ነው። አንደኛ፦ «አበረታሃለሁ» ይላል፤ ይህም አንተን ራስህን ጥቂት ብርቱ አደርግሃለሁ ማለት ነው። ሁለተኛ፦ «እረዳሃለሁ»፤ ይህም ብርታቴን በብርታትህ ላይ እጨምራለሁ፤ አንተ ትመራለህ፣ እኔም እረዳሃለሁ ማለት ነው። ሦስተኛ ግን፣ ዝግጁ በሆንህ ጊዜ፦ «በጽድቄም ቀኝ እጅ ደግፌ እይዝሃለሁ»፤ ይህም በሙሉ አካልህ አንሥቼ ፈጽሞ እሸከምሃለሁ፤ ያም የአንተ ብርታት ወይም የእኔ እርዳታ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የእኔ ደግፎ መያዝ ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ የብርታታችን መጨረሻ ላይ ስንደርስ የእርሱ ብርታት መጀመሪያ ላይ እንደምንደርስ፣ በእርሱም ዘንድ ከሁሉ ደካማ የሆኑት ከሁሉ ብርቱዎች፣ ከሁሉ ይበልጥ ረዳት የሌላቸውም ከሁሉ ይበልጥ የሚረዱ እንደ ሆኑ በእርግጥ እውነት ነው። «ለደካማ ኃይልን ይሰጣል»፤ ነገር ግን ጨርሶ «ጕልበት ለሌለውም» «ብርታትን ያበዛል»፤ ቃሉም ለዘላለም «ጸጋዬ ይበቃሃል» የሚል ነው። መልሱ እርስ በርስ የሚቃረኑ ነገሮች እንቆቅልሽ ነው፤ ሆኖም ከሁሉ እጅግ ተግባራዊ የሆኑ እውነቶች ነው፦ «እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ፤ … ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።»

ኖቬምበር 8

«በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና» (ሮሜ 8:2)።

የኃጢአትና የሕመም ተፈጥሯዊ ሕግ አለ፤ ራሳችንን ዝም ብለን ብንለቅና ከሁኔታዎች ፍሰት ጋር ብንሰምጥ ወደ ታች እንወርዳለን፤ በፈታኙም ኃይል ሥር እንሰምጣለን። ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለ ሌላ የመንፈሳዊ ሕይወትና የሥጋዊ ሕይወት ሕግ አለ፤ ወደ እርሱ ልንወጣ፣ በእርሱም ወደ ታች የሚጎትተንን ሌላውን ሕግ ልንመዝንና ልናሸንፍ እንችላለን። ይህን ለማድረግ ግን እውነተኛ መንፈሳዊ ብርታት፣ የጸና ዓላማ፣ የተደላደለ የእምነት አቋምና ልማድ ያስፈልጋል። በፋብሪካችን ውስጥ ኃይሉን ስናገናኝም እንዲሁ ነው። ቀበቶውን ማገናኘትና ተገናኝቶ እንዲቆይ ማድረግ አለብን። ኃይሉ አለ፤ እኛ ግን ግንኙነቱን መጠበቅ አለብን፤ ይህን እስካደረግን ድረስም የዚህ የላቀ ኃይል ሕግ ይሠራል፤ ማሽኖቹም ሁሉ ይንቀሳቀሳሉ። በመቀደሳችንም ሆነ በፈውሳችን መንፈስ ቅዱስ እንዲሠራ የግድ የሚያስፈልገው፣ ከእግዚአብሔር ጋር በምናደርገው አካሄድ የመምረጥ፣ የማመን፣ በእርሱ የመኖርና ሳንናወጥ የመጽናት መንፈሳዊ ሕግ አለ።

ነፍስን የሚያድን አንድ ቃል አለ፦ «እታመናለሁ»፤ የታመመውንና የሚሠቃየውን ፈውሶ ሙሉ ያደርጋል፦ «እታመናለሁ»።

ኖቬምበር 9

«እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ» (ዮሐንስ 14:19)።

ከሕያው ራሳችንና ከሕይወታችን ምንጭ ጋር ከተስተካከልን በኋላ፣ አሁን ሥራችን በእርሱ መኖር፣ መምጠጥና ማደግ ነው፤ በብርታቱ እየተደገፍን፣ ሕይወቱን እየጠጣን፣ ሕያው እንጀራ እንደ መሆኑ እርሱን እየተመገብን፣ በማያቋርጥ መደገፍና ኅብረትም ሀብታችንን ሁሉ ከእርሱ እየቀዳን። በዚህ በተባረከ ሂደት መንፈስ ቅዱስ ታላቁ አስተማሪና አገልጋይ ይሆናል። ከክርስቶስ ያለውን ወስዶ ያሳየናል፤ በመንፈሳዊ ሰውነታችን ቦዮችና ተግባራት ሁሉም ያካፍለናል። ራሳችንን ለእርሱ ስንሰጥ የራሱን የኅብረት ጸሎት በውስጣችን ይተነፍሳል፤ ልባችንን በናፍቆትና በረሀብ ይስባል፤ እነዚህም ራሳቸው የፍጻሜያቸው መያዣ ናቸው፤ በጸጥታና ቃል በሌለው ጸሎት ለብቻችን ይጠራናል፤ ሕይወቱንም እንድንቀበል የመንፈሳዊ ማንነታችንን ቀዳዳ፣ ብልት፣ ስሜትና ትብነት ሁሉ ይከፍታል። ሳንባ የአየሩን ኦክስጅን እንደሚመጥ፣ የስሜት ሕዋሳትም የአትክልቱን ጣፋጭ መዓዛ እንደሚተነፍሱ፣ እንዲሁ ልብ ከጎናችን ያለውን የተወደደውን ፍቅርና ኅብረት በተፈጥሮው ይቀበላል፤ በእርሱም ደስ ይለዋል። እንዲሁም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች ዛፍ እንሆናለን።

ኖቬምበር 10

«ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር» (የሐዋርያት ሥራ 12:5)።

ነገር ግን ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኘን ሰንሰለት ነው። ገደሉን ሁሉ የሚሻገርና በአደጋ ወይም በችግር ጥልቁ ሁሉ ላይ የሚያሻግረን ድልድይ ይህ ነው። የሐዋርያዊቱ ቤተ ክርስቲያን ሥዕል ምንኛ ትርጉም ያለው ነው፦ ጴጥሮስ በወኅኒ፣ አይሁድ በድል አድራጊነት፣ ሄሮድስ በሥልጣኑ ጫፍ፣ የሐዋርያውን ደም ለመጠጣት የሰማዕትነት አደባባይ የንጋቱን መምጣት ሲጠባበቅ፣ — ሌላው ነገር ሁሉ በተቃራኒው። «ነገር ግን … ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር።» ውጤቱስ ምን ሆነ? ወኅኒው ተከፈተ፣ — ሐዋርያው ነጻ ወጣ፣ — አይሁድ ግራ ተጋቡ፣ — ክፉው ንጉሥ አስከፊ የቅጣት ትዕይንት ሆኖ በትል ተበላ፤ የእግዚአብሔርም ቃል በታላቅ ድል ወደ ፊት ገሠገሠ።

ከተፈጥሮ በላይ የሆነውን የጦር መሣሪያችንን ኃይል እናውቃለንን? እንደሚለምን ብቻ ሳይሆን እንደሚያዝም በሆነ የእምነት ሥልጣን ልንጠቀምበት እንደፍራለንን? እግዚአብሔር በቅዱስ ድፍረትና በመለኮታዊ መተማመን ያጥምቀን። እርሱ የሚፈልገው ታላላቅ ሰዎችን አይደለም፤ የአምላካቸውን ታላቅነት ለማረጋገጥ የሚደፍሩ ሰዎችን እንጂ።

ነገር ግን እግዚአብሔር! ነገር ግን ጸሎት!

ኖቬምበር 11

«እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቈጠሩ» (ሮሜ 6:11)።

ከሙታን የተነሣው ሕይወታችን ከዚህ በኋላ የዚህ ሁሉ ተገቢ ውጤት በሆነ ልማድና አቋም ሊከተል ይገባዋል። «ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቈጠሩ … ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ»፤ ይህም በየቀኑ እንደ ገና ለመሞት አይደለም፤ «ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ …፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።»

ደግሞም የትንሣኤው ሕይወት የተሰጠን «የመከራውን ኅብረት» እንድናውቅና «በሞቱም እንድንመስለው» ያዘጋጀን ዘንድ ነው።

ይህም በደስታና በድል እንድንደክምና መከራ እንድንቀበል ሊያስችለን የታሰበ ነው። «እንደ ንስር በክንፍ» የምንወጣው ተመልሰን «እንድንሮጥና እንዳንታክት፣ እንድንሄድና እንዳንደክም» ነው።

ነገር ግን መከራዎቹን አንሳሳት። እነርሱ የሚያመለክቱት የእኛን መከራዎች ሳይሆን የእርሱን ነው። ለቅድስና የምናደርገው ትግል፣ ሕመሞቻችንና ሥቃዮቻችን አይደሉም፤ ነገር ግን ከእርሱ ጋር ሆነን ስለ ሌሎች፣ መከራ ስለምትቀበል ቤተ ክርስቲያንና እየሞተ ስላለ ዓለም የምንሸከማቸው እነዚያ የላቁ መከራዎች ናቸው። እግዚአብሔር ከዚህ በኋላ ስለ ራሳችን ሌላ ሐዘን ፈጽሞ እንዳይኖረን ይርዳን፤ በትንሣኤውም ኃይል ሸክሞቹን እንድንሸከምና ጽዋውን እንድንጠጣ ነጻ ያድርገን።

ኖቬምበር 12

«የመንፈሱንም መያዣ በልባችን …» (2ኛ ቆሮንቶስ 1:22)።

በእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ «መያዣ» ተብሎ የተተረጐመው ቃል «ትጋት» ማለትም ነው። በትጋት የሚኖር ሕይወት! ምንኛ ብርቅ፣ ምንኛስ የከበረ ትዕይንት ነው! በእግዚአብሔር ልጅ እናየዋለን፤ በሐዋርያው እናየዋለን፤ ራሱን በቀደሰና በእውነት በተሳካለት ክቡር ሕይወት ሁሉ እናየዋለን። ያለ እርሱ ሺህ መልካም ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሁሉን አስተሳስሮ የኃይልና የጽናት ሰንሰለት የሚያደርጋቸው የወርቅ ክር ይጎድላቸዋል። በተበጠሰ ክር ላይ እንዳሉ ውድና ውብ ዶቃዎች ናቸው፤ ይበታተናሉ፤ ወጥና ዘላቂ ኃይል ወዳለው ሕይወት ብቻውን ሊያስራቸው የሚችለው ማሰሪያ ስለሌላቸውም በመጨረሻ ይጠፋሉ። ኦ፣ የእሳት ጥምቀት ምነው በተሰጠን! ኦ፣ «የትጋቱ መንፈስ» ምነው በተሰጠን! ኦ፣ የሚያደርጉትና የሚያስቡት አንድ ነገር ብቻ ያላቸው ሕይወቶች ምነው በበዙ! ኦ፣ እንደ እርሱ እንድንወድ፣ እንድንሠዋ፣ እንድንፈጽም፣ እንድንጸና፣ እንድንኖርና እንድንሞት የክርስቶስ ልብ ጥልቀትና ዘላለማዊ ብርታት በደረታችን ውስጥ ምነው በኖረ!

በእጅግ ቅዱስ አደራ፣ በመለኮታዊና ጥልቅ እውነት፣ በግልጽ መልእክትና በከበረ ሥራ፣ የምንጠብቀውንም ኃላፊነት — እንዴት ያለ ኃላፊነት! — ይዘን እንወጣለን። ወንድሜ ሆይ፣ ጌታ ሊታመንብህ መቻሉ ታላቅ ደስታህ ይሁን፤ ሌላው ሁሉ ቢወድቅና ቢያመነታ እንኳ ለአደራህ ሁልጊዜ ታማኝ ሁን።

ኖቬምበር 13

«በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ» (መዝሙር 37:4)።

የዳንኤል ልብ ለሥራውና ለመንግሥቱ ባለው የእግዚአብሔር ፍቅር ተሞልቶ ነበር፤ ጸሎቶቹም በዘመኑ ከነበሩት ኃይሎች ሁሉ እጅግ ብርቱዎች ነበሩ፤ በእነርሱም እግዚአብሔር እስራኤል ወደ ገዛ ምድራቸው እንዲመለሱ፣ የዓለም ገዢዎችም ዳንኤል የመሰከረለትንና የኖረለትን አምላክ እንዲያውቁ ሰጠው።

በሠላሳ ሰባተኛው መዝሙር ውስጥ «በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል» የሚል ውብ የተስፋ ቃል አለ፤ ምናልባትም እንዲህ ብሎ መተርጎም ተገቢ ይሆናል፦ ትርጉሙ የምኞታችን መፈጸም ብቻ ሳይሆን የምኞታችን መነሣሣት ራሱ፣ ማለትም የእርሱ አሳቦች በውስጣችን መተንፈሳቸው ነው፤ ስለዚህም ጸሎቶቻችን ከፈቃዱ ጋር የሚስማሙ ይሆናሉ፤ እንዲሁም የኃያሉን መግቦቱን የማይወድቅ መልስ መልሰው ያመጡልናል።

አምላክ ሆይ፣ አሳብህን አስተምረኝ! አንተ ራስህ በእኔ ውስጥ አስብ፤ ያን ጊዜ ዘወትር የአንተን አሳብ ብቻ ተከትዬ አስባለሁ። አምላክ ሆይ፣ አሳብህን አስተምረኝ! መለኮታዊ ዕቅድህን አሳየኝ፤ ከዕቅዶቼና ከሥራዎቼ ሁሉ አድነኝ፤ ወደ አንተም ዕቅድ ምራኝ።

ኖቬምበር 14

«የሚታየው የጊዜው ነውና» (2ኛ ቆሮንቶስ 4:18)።

የሚታዩት ነገሮች ወጥመድ ምንኛ ብርቱ ነው! እግዚአብሔርም በማይታዩት ነገሮች ውስጥ ሊጠብቀን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ጴጥሮስ በውኃ ላይ ሊሄድ ከሆነ መሄድ አለበት፤ ሊዋኝ ከሆነ መዋኘት አለበት፤ ሁለቱን ግን በአንድነት ማድረግ አይችልም። ወፍ ልትበር ከሆነ ከአጥሮቹና ከዛፎቹ መራቅ፣ በሚያንሳፍፉትም ክንፎችዋ መታመን አለባት። ከመሬት በቅርብ ርቀት ለመቈየት ብትሞክር ግን በረራዋ ደካማ ይሆናል።

እግዚአብሔር አብርሃምን ወደ ራሱ ብርታት መጨረሻ ሊያደርሰው፣ በገዛ ሥጋውም ምንም ማድረግ እንደማይችል ሊያሳየው ግድ ሆነበት። እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋ መመልከት፣ ከዚያም ሥራውን ሁሉ ለእግዚአብሔር መስጠት ነበረበት፤ ከራሱም ዞር ብሎ በእግዚአብሔር ብቻ በታመነ ጊዜ፣ የሰጠውን ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ ታመነ።

እግዚአብሔር እያስተማረን ያለው ይህንኑ ነው፤ ያለ እነርሱ መታመንን እስክንማር ድረስ የሚያበረታቱ ውጤቶችን ከእኛ ማራቅ ግድ ይሆንበታል፤ ከዚያም ቃሉን በእምነት ብቻ ሳይሆን በተግባርም እውን ማድረግ ይወዳል።

ዛሬ ሁሉን ነገር እርሱ እንደሚመርጠው፣ እርሱም በሚመርጠው መንገድ እንዲያደርግ ወደ እርሱ ብቻ እንመልከት።

ኖቬምበር 15

«አንተ የምኞት ሰው ሆይ» (የግርጌ ንባብ) (ዳንኤል 10:11)።

ይህ ቀድሞ ለዳንኤል የተሰጠው መለኮታዊ መጠሪያ ነበር። በእኛ ትርጉም «እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ» ተብሎ ተተርጉሟል። ቃል በቃል ግን «አንተ የምኞት ሰው ሆይ!» ማለት ነው። ይህ በመንፈሳዊ ኃይሎች ሁሉ ውስጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። ለሚሠራ ጸሎት ከሚሆኑ ምሥጢሮች አንዱ ነው፦ «የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል።» የብርቱ ምኞት ኃይል ለዓላማዎቻችንና ለጸሎቶቻችን ግፊት ይሰጣል። ግድ የለሽነት ጤናማ ያልሆነ ሁኔታ ነው፤ ስንፍናና ደንታ ቢስነትም ለእግዚአብሔርም ለተፈጥሮም አስጸያፊዎች ናቸው።

እንዲሁም በመንፈሳዊ ሕይወታችን እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ በሚፈትኑ ሁኔታዎች ሊያነቃን፣ ልናሸንፋቸው በሚገቡ፣ አለዚያም በኃይላቸው ሥር በምንሰምጥባቸው ኃይሎች ወደ አዲስ የመታመን ስፍራዎች ሊገፋን ግድ ይሆንበታል። በጸሎት ውስጥ ከፍቅር የበለጠ የሚሠራ ነገር የለም። ለአንድ ዓላማ ወይም ለአንድ ሰው እጅግ የምናስብ ከሆንን፣ ልመናዎቻችን እንደ ሕያዋን ኃይሎች ይሆናሉ፤ የእነርሱን ችግሮች ወደ እግዚአብሔር ማድረስ ብቻ ሳይሆን፣ በአንድ መንገድ የእግዚአብሔርን እርዳታ መልሰው ወደ እነርሱ ያደርሳሉ።

እግዚአብሔር በቅዱስ ምኞት መለኮታዊ እሳት እንድንግል ዛሬ በክርስቶስ ልብ ይሙላን።

ኖቬምበር 16

«ቀኒቱንና … አታውቁምና እንግዲህ ንቁ» (ማቴዎስ 25:13)።

ኢየሱስ የመምጣቱን ድንገተኛነት ባለቤቱ በሌለበት ወደ ቤት በሚገባ ሌባ ምሳሌ ያስረዳል። ሕይወት እንደ ጥንቱ የአይሁድ ሌሊት በሦስት የጥበቃ ክፍሎች ልትከፈል ትችላለች፦ ወጣትነት፣ ጕልምስና፣ ሽምግልና። እግዚአብሔርን እንድንገናኝ የሚደረገው ጥሪ በማናቸውም በእነዚህ ክፍሎች ሊመጣብን ይችላል። አንድ ጸሐፊ አባል ስለ ነበረበት የሰፈር ቡድን የገጠመውን ይነግረናል፤ ቡድኑም፣ እንደሚለው፣ በሌሊት ሁልጊዜ ተራ ጥበቃ ያዘጋጅ ነበር። «የምተርከው ነገር ከደረሰ በኋላ በተለይ ጠንቃቆች ሆንን። በመጀመሪያው ሌሊት ከፀሐይ መጥለቅ እስከ ፀሐይ መውጣት በተራ ሰፈራችንን በጥንቃቄ ጠብቀን ነበር። ሁለተኛው ሌሊት ሲመጣ ግን የአካባቢው ሥርዓታማነት እጅግ ስላስደነቀን እስከ መኝታ ሰዓት ድረስ ጠባቂ አያስፈልግም ብለን ደመደምን። በዋናው ድንኳናችን ውስጥ ምሽቱ በተረት፣ በዝማሬና በልዩ ልዩ መዝናኛ አለፈ። የመኝታ ሰዓት በደረሰ ጊዜ ሌሎቹ ድንኳኖቻችን እንደ ተዘረፉና ዋጋ ያለው ነገር ሁሉ እንደ ተሰረቀ ታወቀ። ሥራው የተፈጸመው ጠባቂ ያስፈልጋል ብለን ከማሰባችን በፊት ነበር።» ኃጢአትን ለመጠበቅ መንቃት ለመጀመር ጊዜው ፈጽሞ አይቀድምም።

ኖቬምበር 17

«የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑ ታቦት … በፊታቸው ይሄድ ነበር» (ዘኍልቍ 10:33)።

እግዚአብሔር በልባችን ውስጣዊ ስሜቶችን ይሰጠናል፤ ነገር ግን ስሜት በመሆናቸው ብቻ በእነርሱ ላይ ተመሥርተን እንድንሠራ አይደለም። ስሜቱ ከእግዚአብሔር ከሆነ፣ ከጥርጥር ሁሉ በላይ ሊያጸናው የሚችል በቂ ማስረጃ እርሱ ራሱ ይሰጣል።

በኤርምያስ ታሪክ ውስጥ በዓናቶት ያለውን እርሻ ስለ መግዛት ወደ እርሱ ስለ መጣው ውስጣዊ ስሜት ምንኛ በሚያምር ሁኔታ እናነባለን! ኤርምያስ ግን የአጎቱ ልጅ በማግሥቱ ወደ እርሱ መጥቶ እርሻውን እንዲገዛ በመጠየቅ ውጫዊ ማስረጃ እስካመጣለት ድረስ በዚህ ስሜት ላይ ተመሥርቶ አልሠራም። ከዚያም ኤርምያስ፦ «ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ አወቅሁ» አለ።

እግዚአብሔር ውስጣዊ ስሜቱን በመግቦት እስኪያጸናለት ድረስ ጠበቀ፤ ከዚያም ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም እርግጠኝነትን ሊያመጡ በሚችሉ በግልጽ በሚታዩ እውነታዎች ፊት ሠራ።

እግዚአብሔር እንደ አሳቡ እንድንሠራ ይፈልጋል።

የእረኛውን የግል ድምፅ ቸል ልንል አይገባንም፤ ነገር ግን እንደ ጳውሎስና በጢሮአዳ እንደ ነበሩት ባልንጀሮቹ የሚናገሩትን ድምፆች ሁሉ ልናደምጥ፣ እነርሱም እንዳደረጉት ከሁኔታዎች ሁሉ የጌታን ሙሉ አሳብ «ልናስተውል» ይገባናል።

ኖቬምበር 18

«በዙፋንም የተቀመጠው … ተፈጽሞአል አለ» (ራእይ 21:5-6)።

በድርጊትና በውል መካከል ያለው ልዩነት ታላቅ ነው። ምንም ሳንፈጽም ዘወትር ስንሠራ ልንኖር እንችላለን፤ ውል ግን ከመመለሻው ነጥብ አልፎ የሚሄድና ዘላቂ ቃል መግባት የሚሆን ድርጊት ነው። መዳን በነፍስና በክርስቶስ መካከል የሚደረግ፣ ጉዳዩ ወደማይመለስበት የሚያልፍ ውል ነው። መቀደስ ፈጽመን ራሳችንን የምንሰጥበት፣ በማይሻር ሁኔታ የምንቀደስበትና ሙሉ በሙሉ ለመንፈስ ቅዱስ የምንሰጥበት ታላቅ ውል ነው፤ ከዚያም እርሱ መጥቶ ውሉን ያትማል፤ ሥራውንም ይረከባል። ለጌታ ፈውስ የምንገባው ቃል ኪዳንም እንዲሁ ግልጽ፣ የተወሰነና የማይሻር ሊሆን ይገባዋል። እግዚአብሔር ልጆቹን ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለ ሌሎች የመታዘዝና የአገልግሎት ጉዳዮች ወደሚመራቸው ቃል ኪዳኖች ሁሉም ይህ ይሠራል። በዚህ በተቀደሰ ቀን ራሳቸውን የቀደሱ ብዙ ሕይወቶች በአዲስ ትርጉምና ጽናት፦ «ተፈጸመ፣ ታላቁ ውል ተፈጸመ» ማለት እንዲችሉ እግዚአብሔር ይስጥ።

ሕያው የወይን ግንድ ኢየሱስ ነውና፤ በሙላቱ ልንሰወር እንችላለን፤ በእርሱም ስንኖር ሕይወታችንንና ፍሬያማነታችንን እናገኛለን።

ኖቬምበር 19

«ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን» (ዮሐንስ 12:21)።

ታላቅ በረከት በሚጠብቀን ጊዜ፣ እንዳያመልጠን ዲያብሎስ በረከቱን እጅግ የሚያስጠላ ሊያደርግብን መሞከሩ አይቀርም። ውሸታም መሆኑን ማወቅ መልካም ነው፤ በአንድ ጉዳይ ላይ አጥብቆ ሊያስጠላን ሲሞክርም የሕይወታችን ታላቅ በረከት ምናልባት በዚያ እንዳለ ማስታወስ መልካም ነው። ቻርልስ ስፐርጀን በአንድ ወቅት እግዚአብሔር ከጎናችን ለመሆኑ ከሁሉ የተሻለው ማስረጃ የዲያብሎስ ጕርምርምታ ነው ብሎ ነበር፤ አንድን ነገር ሰይጣን በሚጠላው መጠን ብንከተለው በአብዛኛው ደኅና ነን። ወዳጆች ሆይ፣ ጭፍን ጥላቻዎችህ ከእግዚአብሔር ሕዝብና ከእግዚአብሔር እውነት በሚለዩህ በዚያው መስመር የሕይወትህን ሀብት እንዳታጣ ተጠንቀቅ። የሰማይን ሀብት በማንኛውም መንገድ ወደ አንተ ቢመጣ ተቀበለው፤ ምድራዊ ሀብት በአብዛኛው እንደሚመጣ፣ በሻካራ ቅርፊት ውስጥ እንዳለ ፍሬ ወይም በጠንካራ ዓለት እቅፍ ውስጥ እንዳለ ዕንቍ ሆኖ ቢመጣ እንኳ።

ኢየሱስን አይቻለሁ፤ ልቤም ለሌላው ሁሉ ሞቷል፤ ኢየሱስን አይቻለሁ፤ ፍላጎቶቼም ሁሉ በእርሱ ተሟልተዋል። ኢየሱስን አይቻለሁ፤ ልቤም በመጨረሻ ረክቷል፤ ኢየሱስን ካየሁ ወዲህ።

ኖቬምበር 20

«ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር … በደረቱ ተጠግቶ …» (ዮሐንስ 21:20)።

አንድ አሜሪካዊ ጨዋ ሰው በአንድ ወቅት ቅዱሱን አልበርት ቤንግልን ሊጎበኘው ሄደ። ሲጸልይ ለመስማት እጅግ ይናፍቅ ነበር። ስለዚህ አንድ ምሽት የመጨረሻ ጸሎቱን በድብቅ ለመስማት ተስፋ አድርጎ በበሩ አጠገብ ቈየ። ክፍሎቹ ተያያዥ ነበሩ፤ በሮቹም ገርበብ ብለው ነበር። ደጉ ሰው ጥናቱን ጨረሰ፤ መጻሕፍቱን ዘጋ፤ ለአንድ አፍታ ተንበርክኮ በቀላሉ፦ «ውድ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ በመካከላችን ያለው ነገር አሁንም እንደ ቀድሞው ነው» አለ፤ ከዚያም በጣፋጭ ሰላም አንቀላፋ። ከጌታው ጋር የነበረው ኅብረት እጅግ የቀረበ ስለ ነበር ሥራ አያቋርጠውም፤ ለማደስም ጸሎት አያስፈልገውም ነበር። እንደ በጋ አትክልት መዓዛ፣ ወይም የሥራ ሰዓታት እያለፉ አንድ ቃል እንኳ ሳንለዋወጥ በሆነ መንገድ መገኘቱ እንደሚሰማን ከጎናችን እንዳለ ውድ ሰው፣ የማያቋርጥ፣ ከሞላ ጎደል ሳይታወቅ የሚኖር መገኘት ነበር።

«ኦ የተባረከ ኅብረት፣ መለኮታዊ፤ ኦ እጅግ ጣፋጭ ደስታ፤ እዚህ ከኢየሱስ ጋር ያለ ባልንጀርነት ሕይወትን በደስታ ይሞላታል፤ ኦ ድንቅ ጸጋ፣ ኦ ከፍ ያለ ደስታ፤ ኢየሱስ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነው።»

ኖቬምበር 21

«የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ» (ማቴዎስ 6:28)።

አንድ ትንሽ ልጅ አንድ ቀን እግሮቹን መሬት ውስጥ ቀብሮ ከአንድ ረጅም የሱፍ አበባ አጠገብ ቆሞ እናቱ እንዳገኘችው ይነገራል። እርሷም፦ «ለመሆኑ እዚያ ምን እየሠራህ ነው?» ብላ በጠየቀችው ጊዜ በየዋህነት፦ «አድጌ ሰው ለመሆን እየሞከርሁ ነው» ብሎ መለሰ።

እናቱም እንደ ሱፍ አበባው ለማደግ ብሎ መሬት ውስጥ መተከሉን አስባ ከልብ ሳቀች፤ ከዚያም ራሱን በቀስታ እየዳበሰች፦ «ሃሪ፣ የሚታደገው እንዲህ አይደለም። በመሞከር ፈጽሞ ልትጨምር አትችልም። ዝም ብለህ ወደ ቤት ግባ፤ ብዙ ጥሩ ምግብ ብላ፤ በደንብም ተጫወት፤ እንዲህ ሳትደክም ቶሎ አድገህ ሰው ትሆናለህ» አለችው።

እንግዲህ የሃሪ እናት ትክክል ነበረች። ወይዘሮ ሃና ዊታል ስሚዝ፦ «አበቦች እንዴት ያድጋሉ?» ለሚለው ጥያቄ በቀላሉ፦ «ሳይሞክሩ ያድጋሉ» ብላ ከመለሰችው የበለጠ ጣፋጭ ነገር ተናግራ አታውቅም።

ከሁሉ የሚጣፍጠው መንፈሳዊ ሕይወታችን ራስን የማያስብ ሕይወት ነው፤ በእርሱም ከክርስቶስ ጋር እጅግ ተዋሕደን ዘወትር በሕይወቱ እንኖራለን፤ በመንፈሱና በመገኘቱ፣ በሚያካፍለንም ሕይወት ሙላት ሁሉ እንመገባለን፣ እንጠግባለን፣ ዘወትርም እንሞላለን።

ኖቬምበር 22

«አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ» (ማቴዎስ 7:5)።

ከምትኰንነውና ከምትነቅፈው ስሕተት ይልቅ የነቀፋና የኵነኔ ኃጢአት ይበልጣል። ከተሳሳተ ሰው ጋር ስንገናኝ የሚያስፈልገንን ያህል ጸጋ በሌላ በየትም ስፍራ አያስፈልገንም። አንዲት ሴት በአንድ ወቅት የተሳሳተችን አንዲት እኅት ሄዳ ልትወቅሳት ስትሄድ በመንገዷ ወደ እኛ ጎራ አለች። ትንሽ አብልጣ ልትወድዳት እስክትችል ድረስ እንድትቆይ መከርናት። የተሳሳቱትን በሚገባ ሊይዝ የሚችለው ኃጢአተኞችን ስለ እነርሱ እስኪሞት ድረስ የወደዳቸው እርሱ ብቻ ነው። እኛ ልብን ሁሉ ፈጽሞ አናይም። እርሱ ግን ያያል፤ ሳይኰንንም ይወቅሳል፤ ተስፋ ሳያስቈርጥም ይገሥጻል። ኦ፣ የክርስቶስ ልብ ምነው ይበልጥ በኖረን! ወንድሜ ሆይ፣ ስለ ሌላው ስሕተት እንዴት እንደምትናገር ተጠንቀቅ። ሳታውቀው በዚያው ወይም በከፋ ኵነኔ ውስጥ ልትገኝ ትችላለህ። ጌታችን በወንድሙ ዓይን ጉድፍ የሚያይ ሰው በአብዛኛው በገዛ ዓይኑ ምሰሶ እንዳለበት መናገሩ እጅግ ትርጉም ያለው ነው! ከመጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ይቅር የማይባሉ ኃጢአቶች አንዱ ይቅር የማይል ፍቅር የለሽነት ነው።

«እንደ ልብህ ያለ ልብ ስጠኝ፤ እንደ ልብህ ያለ ልብ ስጠኝ፤ በድንቅ ኃይልህ፣ በየሰዓቱም በጸጋህ፣ እንደ ልብህ ያለ ልብ ስጠኝ።»

ኖቬምበር 23

«ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ …» (ሮሜ 13:11)።

ከእምነት ታላላቅ ጠላቶች አንዱ ስንፍና ነው። ተነሥቶ ከማሸነፍ ይልቅ ተኝቶ መሠቃየት እጅግ ይቀላል፤ ራስን አነቃቅቶ ድካሙን ከማራገፍና ድንዛዜውን ከማሸነፍ ይልቅ በበረዶ ክምር ላይ አንቀላፍቶ ዳግመኛ አለመንቃት እጅግ ይቀላል። እምነት ትጋት የሚጠይቅ ጥበብ ነው፤ ጸሎት ብርቱ ድካም ነው፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።

ሰይጣን በአትክልቱ ውስጥ ደቀ መዛሙርትን እንዳደረገው ሊያስተኛን ይሞክራል፤ ነገር ግን እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ፤ በጸሎት እየተጋን በእርሱም በመጽናት ሁሉ እየነቃን፣ ብርታቱንም ለመያዝ ራሳችንን እያነቃቃን፣ «ዳተኞች ሳንሆን፥ በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን የምንመስል» እንሁን። መርከቢቱን በማዕበሉ ላይ የሚያሻግራት ነፋስ ነው፤ ነገር ግን የጀልባ ነጂው እጅ መሪውን አጥብቆ ካልያዘ፣ መሪውም ነፋሱን ተቃውሞ በጽናት ካልተቀመጠ ነፋሱ ኃይል የለውም። እንዲሁም እኛ መሪውን እንይዛለን፤ እግዚአብሔር ሸራዎቹን ይሞላል። መርከቢቱን የሚያሻግራት መሪው አይደለም፤ ነገር ግን መርከቢቱን የሚያሻግረውን ነፋስ የሚቀበለው መሪው ነው፤ እንዲሁም በእርሱ ላይ ተደግፈን ሳለን እግዚአብሔር በፍጹም ሰላም ይጠብቀናል።

ኖቬምበር 24

«ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ» (ፊልጵስዩስ 4:13)።

አንዲት ውድ እኅት አንድ ቀን፦ «የምሠራው ሥራ እጅግ ብዙ ስለ ሆነ እርሱን ለመሥራት የሚያስፈልገኝን ብርታት ጌታን በመጠባበቅ ለማግኘት ጊዜ የለኝም» አለች። ይህ በእርግጥ ያለ ገለባ ጡብ መሥራት ነበር፤ በጌታና በቤተ ክርስቲያን ስም ቢሆን እንኳ የዲያብሎስ ባርነት ነበር። እግዚአብሔር አገልጋዮቹን በገዛ ገንዘባቸው አይልክም፤ ነገር ግን «በነገር ሁሉ ሁልጊዜ ብቃትን ሁሉ እያለን ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድንበዛ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛልን ይችላል።» ከጠላቶቹ ሲሸሽና ሊደርሱበት ጥቂት ሲቀራቸው፣ ይበልጥ በስኬት እንዲሸሽ በሽሽቱ መካከል ቆሞ ለፈረሱ የብረት ጫማ ያስመታው የጐሣ አለቃ የጥንት ታሪክ ለክርስቲያን ሠራተኞች እውነተኛ ምሳሌና ትምህርት ነው።

ፌስቲና ሌንቴ፣ ማለትም «ቀስ ብለህ ፍጠን» የሚለው የጥንቱ የላቲን መፈክር ለእኛ ታላቅ ትምህርት አለው። የምንሠራው ሥራ በበዛ ቁጥር፣ ራሳችንን በጠረጴዛችን ላይ ደፍተን ሰማያዊ እርዳታንና ፍቅርን ለጥቂት ጊዜ መጠበቅ፣ ከዚያም በአዲስ ብርታት ወደ ፊት መግፋት ይበልጥ ደጋግሞ ያስፈልገናል። በመንፈስ ቅዱስ ፍቅር የተጠመቀች አንዲት ሰዓት ያለ ሰማያዊው ሕይወት ነፋስንና ማዕበልን ከሚታገሉ አሥር ሰዓታት ትበልጣለች።

ኖቬምበር 25

«ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ» (1ኛ ቆሮንቶስ 4:5)።

በልብ ውስጥ የመንፈስን ሥራ ከነቀፋ መንፈስ ይበልጥ የሚያቆመው ነገር የለም። በአንድ ስብሰባ መጨረሻ አንድ ወጣት አገልጋይ ወደ ፊት መጥቶ በዚያ ከሰዓት በኋላ ስለ ተቀበለው ታላቅ በረከት፣ ወደ ልቡና ወደ ማንነቱ ስለ መጣውና ከዓመታት ባርነት ነጻ ስላወጣው የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትም ነገረን። ከዚያም፦ «ይህ ሁሉ የመጣው ‹የነቀፋ መንፈስ መንፈስ ቅዱስ ልብን እንዳይሞላ ያግዳልን?› ለሚለው ጥያቄ በሰጣችሁት መልስ ነው» ብሎ ጨመረ።

እንዲህም አለ፦ «ጥያቄው ሲጠየቅና ሲመለስ፣ በዚያ በሚደረገው ብዙ ነገር ላይ እየነቀፍሁ፣ ይህንና ያንን እየተቃወምሁ፣ በአገላለጾቹ፣ በምስጋናዎቹና በምስክርነቶቹ ላይ ስሕተት እየፈለግሁ፣ ፈጽሞም ደስታ አጥቼ በቤተ ክርስቲያን ተቀምጬ ነበር። ጌታ መልሱን ወደ ልቤ አደረሰው፤ ስለ ኃጢአቴም ወቀሰኝ፤ በዚያው ቅጽበትም ተውሁት፤ ከክፉው ይልቅ መልካሙን ማየት ጀመርሁ። በረከት በላዬ ወረደ፤ ነፍሴም በደስታና በምስጋና ተሞላች፤ ስሕተቴም የት እንደ ነበረ አየሁ፤ ለዓመታት እውነትን በልቤ ሳይሆን በራሴ ለማየት ስሞክር ነበር።»

ኖቬምበር 26

«ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል» (ዮሐንስ 15:2)።

አንድ ቀን በአንድ አትክልት ቦታ አጠገብ አለፍን። አትክልተኛው መግረዙን ጨርሶ ነበር፤ የቢላዋውና የመጋዙ ቍስሎች መዳን ጀምረው ነበር፤ ሞቃቱ የሚያዝያ ፀሐይም የተመታውን ተክል ወደ አዲስ ሕይወትና ብርታት በቀስታ ይመግበው ነበር። ያንን ተክል ስንመለከት በሚቀጥለው ሳምንት እንደ ገና መቍረጥ መጀመር ምንኛ ጭካኔ እንደሚሆን አሰብን። ደም ፈስሶት እስከ ሞት ይደርስ ነበር። አሁን የአትክልተኛው ሥራ ማነቃቃትና ወደ ሕይወት መመገብ ነው። የተክሉ ሥራ መሞት ሳይሆን መኖር ነው። እኛም አሰብን፦ የነፍስ ተግሣጽም እንዲሁ ነው። እርሷም የምትሞትበት ሰዓት አላት፤ ነገር ግን ሁልጊዜ እየሞተች መኖር የለባትም። ይልቁንም በዘላለማዊው ጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአት በእውነት እንደ ሞትን፣ ለእግዚአብሔርም ሕያዋን እንደ ሆንን ራሳችንን እንቍጠር።

የራስህን እስትንፋስ በሟች ሰውነቴ ሁሉ ተንፍስ፤ የትንሣኤ ሕይወትህን እንድወርስ እርዳኝ፤ ይህም በለውጦች ሁሉ መካከል ሳይለወጥ ይኖራል፤ በዘላለማዊውም መንገድ ምራኝ። እለምንሃለሁ፣ የሰማዩን ቅምሻ እዚህ ስጠኝ፤ እምነት የዘላለሙን ቀን አስቀድሞ ይቀበል፤ በክብሩም ውስጥ መንገዱን ሁሉ እየሄድሁ፣ ኦ፣ በዘላለማዊው መንገድ ምራኝ!

ኖቬምበር 27

«የቀረውንም ዘይት … በራሱ ላይ ያፈስሰዋል» (ዘሌዋውያን 14:18)።

በዕብራዊው ለምጻም ፈውስ ታሪክ ውስጥ ጆሮዎቹ፣ እጆቹና እግሮቹ በሚቤዠው ደምና በሚቀድሰው ዘይት እንደ ተነኩ የሚያሳይ ውብ ሥዕል አለ፤ ይህም የማስተዋል፣ የአገልግሎትና የአካሄድ ችሎታዎቹ ለእግዚአብሔር እንደ ተለዩና ለጌታ ሥራና ፈቃድ በመለኮት ኃይል እንደ ተሞሉ ምልክት ነው።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን «የቀረው ዘይት» በራሱ ላይ እንዲፈስ እንደ ተደረገ ትርጉም ባለው ሁኔታ ተነግሮናል።

የቀድሞው ቅብዓት በካህኑ እጅ ከነበረው ዘይት ነበር፤ የኋለኛው ግን ከሎጉ፣ ማለትም ከዘይቱ ዕቃ ራሱ ነበር። በይዘቱ ሁሉ እስኪታጠብ ድረስ በላዩ ላይ ቃል በቃል ይገለበጥ ነበር።

ይህ የታላቁና ወሰን የለሹ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ምሳሌ ነው። ራሱን ከቀደሰ ክርስቲያን ተራ ልምምዶች እንኳ የሚበልጥን ነገር ይናገራል። እግዚአብሔር ከማይለካው ሙላቱ ለእኛ ስላዘጋጀው የተትረፈረፈና ሞልቶ የሚፈስስ ስጦታ ይነግረናል።

«የቀረውን ዘይት» ተቀብለናልን? በመንፈስ ተሞልተናልን? ትርፉስ ሌሎችን እንዲባርክ እየፈቀድን ነውን?

ኖቬምበር 28

«ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና» (ዮሐንስ 15:5)።

ለክርስቶስ ምን ያህል ማድረግ እችላለሁ? ብለን ስንጠየቅ፣ የምችለውን ያህል ብለን መመለስ ልማዳችን ነው። ከምንችለው በላይ ማድረግ እንደምንችል አስበን እናውቃለንን?

ይህ አሳብ በቅርቡ ወደ አእምሮአችን የመጣው ከአንዲት ክርስቲያን ወዳጅ ንግግር ነው፤ እርሷም እግዚአብሔር ከአቅሟ በላይ የሆነ ነገር ለሥራው እንድታደርግ በልቧ እንዳኖረባት፣ ልትታዘዘውም በደፈረች ጊዜ የኃይሉንና የሀብቱን ማረጋገጫ እንደ ሰጣት፣ እምነቷንም በሚያስደንቅ ሁኔታ ስለ መለሰላት በሌላ መንገድ ከምትችለው በላይ ማድረግ፣ የልቧን ምኞት መፈጸምና ሀብቷ የማይበቃውን ሥራ ተፈጽሞ ማየት እንደ ቻለች ነገረችን።

ሐዋርያው፦ «ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ» ይላል፤ ሆኖም በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም ይላል።

ኦ፣ የተባረከ አለመብቃት! ኦ፣ የተባረከ ሁሉን የሚበቃ ብቃት! ኦ፣ ሁሉን ነገር የሚያመጣልን የተባረከ ምንም አለመሆን! ኦ፣ የበለጸገ ጥሎሹ «ለሚያምን ሁሉ ይቻላል» የሆነ የተባረከ እምነት!

ኦ፣ በሰላም፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ በእርሱ ምነው በተገኘሁ!

ኖቬምበር 29

«ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን?» (ማቴዎስ 26:40)።

ወላጆቿ በሕፃንነቷ የሞቱባት አንዲት ወጣት ሴት በአንድ የቤተ ሰቡ ውድ ወዳጅ በደግነት ትጠበቅ ነበር። እርሱን ለማወቅ ዕድሜዋ ሳይደርስ ወደ አውሮፓ ሄደ። በሌለባቸው ዓመታት ሁሉ በየጊዜው ይጽፍላት ነበር፤ ለፍላጎቶቿም ሁሉ ገንዘብ መላክ ፈጽሞ አላቋረጠም። በመጨረሻም በአንድ በተወሰነ ሳምንት ውስጥ ተመልሶ እንደሚጎበኛት ወሬ መጣ። ቀኑንም ሰዓቱንም አልወሰነም። በዚያ ሳምንት ከወዳጆቿ ጋር አስደሳች ጉዞዎችን እንድታደርግ ብዙ ግብዣዎች ደረሷት። ከእነዚህም አንዱ እጅግ አስደሳች ስለ ነበር ከመቀበል ራሷን ልትገታ አልቻለችም። በጉዞዋ ላይ ሳለች እርሱ መጣ፤ ስለ መቅረቷ ጠየቀ፤ ሄደም። ስትመለስ ይህን ማስታወሻ አገኘች፦ «ሕይወቴ ስለ አንቺ ስትደክም ኖራለች፤ አንድ ሳምንት ልትጠብቂኝ አይገባሽም ነበርን?» ከዚያ በኋላ ስለ እርሱ ምንም አልሰማችም፤ የተትረፈረፈ ሕይወቷም የችግር ሕይወት ሆነ። ኢየሱስ የሚመለስበትን ቀን ወይም ሰዓት አልወሰነም፤ ነገር ግን «ትጉ» ብሏል፤ ዛሬ ቢመጣ ግድ የለሽ በሆነ ፈንጠዝያ ተውጠን ያገኘን ይሆን? የተወደደውን ሰው እንደሚጠባበቁ ሰዎች በየቀኑ በተስፋ በመጠባበቅ አቋም እንገኝ።

ኖቬምበር 30

«እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር» (ፊልጵስዩስ 2:3)።

ሐዋርያው «የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር» ሲል ከጥልቅ መንፈሳዊ እውነት የበለጠን ነገር ማለቱ ነው። ከዚህ በፊት አንድ ነገር መኖር አለበት። ጥልቅ አፈርና ጽኑ መሠረት መኖር አለበት።

ብዙው መንፈሳዊ ትምህርታችን የሚከሽፈው የምንሰጣቸው ሰዎች እጅግ ጥልቀት የሌላቸው ስለ ሆኑ ነው። ጥልቁ ማንነታቸው ከቶ አልተነቃቃም።

ብፅዓን የሚጀምሩት ከነገሮች ሥር ነው፦ በመንፈስ ድሆች ከሆኑት፣ ከሚያዝኑትና ከተራቡ ልቦች። መከራ ለጥልቅ መንፈሳዊ ሕይወት አስፈላጊ ነው። እርሱን ለማግኘት ወደ ገዳም ወይም ወደ ሥጋ ደዌ ሆስፒታል መሄድ አያስፈልገንም። ከአዳም ዘር የተለየ ዘር ካልሆንህ በቀር፣ ራስ ወዳድ ላለመሆን የሚገጥምህ የመጀመሪያው እውነተኛ አጋጣሚ የስቅለትን ጣር ወደ ሕይወትህ ያመጣል።

ወንዶችና ሴቶች ስለ መከራና ስለ ሞት እጅግ ጥቂት የሚያውቁት ይህን ስላልተጋፈጡ ነው። ጥልቅ ጽኑ እምነቶች ሊኖሩን ይገባል። እውነት ለእኛ የግድ አስፈላጊ፣ መርሕም የማንነታችን ክፍል ሊሆን ይገባዋል። ጌታ ሆይ፣ በመንፈስ ድሀ አድርገኝ። ጌታ ሆይ፣ በምድር ሳለህ እንደ ነበርህ፣ ሁልጊዜ ከሁሉ ዝቅ ያልህና ስለዚህም «ያለ ልክ ከፍ ከፍ» የተደረግህ እንደ ሆንህ፣ እኔም እንዲሁ እንድሆን እርዳኝ።

ገጽ 1 / 1 · 21 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ