ምዕራፍ 8 · 5 ደቂቃ ንባብ · 7 ደቂቃ ማዳመጥ
እምነት ምንድር ነው?
ስለ እርሱ፦ «ጸጋው በእምነት አድኖአችኋል» ተብሎ የተነገረለት ይህ እምነት ምንድር ነው? ስለ እምነት ብዙ መግለጫዎች አሉ፤ ነገር ግን ያጋጠሙኝ ትርጓሜዎች ሁሉ ማለት ይቻላል፣ ከማየቴ በፊት ከነበረኝ ማስተዋል ይልቅ ያነሰ እንድረዳው አድርገውኛል። አንድ ሰው ምዕራፉን ካነበበ በኋላ «አብራራዋለሁ» ለማለት ፈልጎ «አምታታዋለሁ» አለ ይባላል፤ ሊያብራራው አስቦ የነበረ ቢሆንም፣ በእርግጥም ያምታታው ሳይሆን አይቀርም። እኛም ማንም እስከማይረዳው ድረስ እምነትን ልናብራራ እንችላለን። እኔ በዚህ ስሕተት እንዳልገኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እምነት ከነገሮች ሁሉ እጅግ ቀላሉ ነው፤ ምናልባትም ቀላል በመሆኑ ምክንያት ለማብራራት ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል።
እምነት ምንድር ነው? ከሦስት ነገሮች የተሠራ ነው፤ እነርሱም እውቀት፣ ማመንና መታመን ናቸው። እውቀት በመጀመሪያ ይመጣል። «ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ?» አንድን እውነታ ማመን ከመቻሌ በፊት ስለ እርሱ መረዳት ያስፈልገኛል። «እምነት ከመስማት ነው»፤ የሚታመነው ምን እንደ ሆነ እናውቅ ዘንድ አስቀድመን መስማት ይገባናል። «ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ።» ለእምነት የተወሰነ እውቀት የግድ ያስፈልጋል፤ ስለዚህም እውቀትን ማግኘት አስፈላጊ ነው። «ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ኑ፤ ስሙ፥ ነፍሳችሁም በሕይወት ትኖራለች።» የጥንቱ ነቢይ ቃል እንዲህ ነበረ፤ አሁንም የወንጌል ቃል ይኸው ነው። መጻሕፍትን መርምር፤ መንፈስ ቅዱስ ስለ ክርስቶስና ስለ መዳኑ የሚያስተምረውንም ተማር። እግዚአብሔርን ለማወቅ ፈልግ፤ «ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።» መንፈስ ቅዱስ የእውቀትንና እግዚአብሔርን የመፍራትን መንፈስ ይስጥህ! ወንጌልን እወቅ፤ የምሥራቹ ምን እንደ ሆነ፣ ስለ ነጻ ይቅርታ፣ ስለ ልብ መለወጥ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤተ ሰብ በልጅነት ስለ መግባትና ስለ ሌሎች ቍጥር የሌላቸው በረከቶች እንዴት እንደሚናገር እወቅ። ይልቁንም የእግዚአብሔርን ልጅ፣ የሰዎችን አዳኝ ክርስቶስ ኢየሱስን እወቅ፤ እርሱ በሰውነቱ ከእኛ ጋር የተዋሐደ፣ ሆኖም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሆነ ነው፤ ስለዚህም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል መካከለኛ ሆኖ ሊሠራ፣ በሁለቱም ላይ እጁን ሊጭን፣ በኃጢአተኛውና በምድር ሁሉ ፈራጅ መካከልም ማገናኛ ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ ኢየሱስን ይበልጥ እያወቅህ እንድትሄድ ትጋ። ይልቁንም የክርስቶስን መሥዋዕት ትምህርት ለማወቅ ትጋ፤ የሚያድን እምነት በዋናነት የሚያርፍበት ነጥብ ይህ ነውና፦ «እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር።» ኢየሱስ «ስለ እኛ እርግማን ሆኖ» እንደ ዋጀን እወቅ፤ «በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና»። የክርስቶስን የምትክነት ሥራ ትምህርት በጥልቅ ጠጣ፤ በዚያ ውስጥ ለበደለኞቹ የሰው ልጆች ሊኖር የሚችል እጅግ ጣፋጭ መጽናናት አለና፤ ጌታ «እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው» ተብሎ ተጽፎአልና። እምነት በእውቀት ይጀምራል።
አእምሮ ቀጥሎ እነዚህ ነገሮች እውነት እንደ ሆኑ ወደ ማመን ይሄዳል። ነፍስ እግዚአብሔር እንዳለ፣ የቅኖችንም ልብ ጩኸት እንደሚሰማ ታምናለች፤ ወንጌል ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ በእምነት መጽደቅም እግዚአብሔር በእነዚህ በመጨረሻዎቹ ዘመናት በመንፈሱ ከቀድሞው ይልቅ ይበልጥ ግልጥ አድርጎ የገለጠው ታላቅ እውነት እንደ ሆነ ታምናለች። ከዚያም ልብ ኢየሱስ በእውነትና በእርግጥ አምላካችንና አዳኛችን፣ የሰዎች ቤዛ፣ የሕዝቡ ነቢይ፣ ካህንና ንጉሥ እንደ ሆነ ያምናል። ይህ ሁሉ ሊጠራጠሩበት የማይገባ እርግጠኛ እውነት ሆኖ ይቀበላል። አንተም ወዲያውኑ ወደዚህ እንድትደርስ እጸልያለሁ። «የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል» የሚለውን አጽንተህ እመን፤ መሥዋዕቱ ፍጹም እንደ ሆነ፣ ስለ ሰውም በእግዚአብሔር ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንዳገኘ፣ ስለዚህም በኢየሱስ የሚያምን እንዳይፈረድበት እመን። እነዚህን እውነቶች ሌላውን ማንኛውንም ቃል እንደምታምን እመን፤ በተራ እምነትና በሚያድን እምነት መካከል ያለው ልዩነት በዋናነት እምነቱ በሚያርፍባቸው ነገሮች ላይ ነውና። የገዛ አባትህን ወይም የወዳጅህን ምስክርነት እንደምታምን እንዲሁ የእግዚአብሔርን ምስክር እመን። «የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል።»
እስከዚህ ድረስ ወደ እምነት ገፍተህ ሄደሃል፤ እምነትን ለማሟላት የሚያስፈልገው አንድ ተጨማሪ ክፍል ብቻ ነው፤ እርሱም መታመን ነው። ራስህን ለመሐሪው አምላክ አደራ ስጥ፤ ተስፋህን በጸጋው ወንጌል ላይ አሳርፍ፤ ነፍስህን በሞተውና ሕያው በሆነው አዳኝ ላይ ጣል፤ ኃጢአትህን በሚያስተሰርየው ደም እጠብ፤ ፍጹሙን ጽድቁንም ተቀበል፤ ያን ጊዜ ሁሉ መልካም ይሆናል። መታመን የእምነት የሕይወት ደም ነው፤ ያለ እርሱ የሚያድን እምነት የለም። ፒዩሪታኖች እምነትን «መደገፍ» በሚል ቃል ያብራሩት ነበር። ትርጉሙም በአንድ ነገር ላይ ተደግፎ ማረፍ ማለት ነው። ክብደትህን ሁሉ ጥለህ በክርስቶስ ላይ ተደገፍ። «በሙሉ ቁመትህ ውደቅ፤ በዘመናት ዓለት ላይም ተጋደም» ብልህ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ምሳሌ ይሆን ነበር። ራስህን በኢየሱስ ላይ ጣል፤ በእርሱ እረፍ፤ ራስህን ለእርሱ አደራ ስጥ። ይህን ካደረግህ የሚያድን እምነትን በተግባር አሳይተሃል። እምነት ዕውር ነገር አይደለም፤ እምነት በእውቀት ይጀምራልና። የግምት ነገርም አይደለም፤ እምነት እርግጠኛ የሆነባቸውን እውነታዎች ያምናልና። ከተግባር የራቀ የሕልም ነገርም አይደለም፤ እምነት ይታመናል፤ ዕጣ ፈንታውንም በመገለጡ እውነት ላይ ያስይዛልና። እምነት ምን እንደ ሆነ የሚገለጥበት አንዱ መንገድ ይህ ነው።
እንደ ገና ልሞክር። እምነት ክርስቶስ እንደሚባለው ዓይነት እንደ ሆነ፣ አደርጋለሁ ብሎ ተስፋ የሰጠውንም እንደሚያደርግ ማመን፣ ከዚያም ይህን ከእርሱ መጠበቅ ነው። መጻሕፍት ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ሥጋ የተገለጠ አምላክ እንደ ሆነ፣ በባሕርዩ ፍጹም እንደ ሆነ፣ ስለ እኛ የኃጢአት መሥዋዕት እንደ ተደረገ፣ ኃጢአታችንንም በገዛ ሥጋው በእንጨት ላይ እንደ ተሸከመ ይናገራሉ። መጽሐፍ መተላለፍን እንደ ፈጸመ፣ ኃጢአትን እንደ ጨረሰ፣ የዘላለምንም ጽድቅ እንዳመጣ ይናገራል። ቅዱሳት መዛግብትም ደግሞ «ከሙታን እንደ ተነሣ»፣ ስለ እኛ «ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል»፣ ወደ ክብር እንዳረገና ስለ ሕዝቡ ሆኖ መንግሥተ ሰማያትን እንደ ያዘ፣ «በዓለሙ ላይ በጽድቅ፣ በሕዝቡም ላይ በቅንነት ሊፈርድ» በቅርቡ እንደ ገና እንደሚመጣ ይነግሩናል። ይህ በእርግጥ እንዲሁ እንደ ሆነ አጽንተን ልናምን ይገባናል፤ ይህ እግዚአብሔር አብ፦ «የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት» ባለ ጊዜ የሰጠው ምስክርነት ነውና። ይህም ደግሞ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተመስክሮአል፤ መንፈስ በመንፈሱ መሪነት በተጻፈው ቃልም፣ በልዩ ልዩ ተአምራትም፣ በሰዎችም ልብ ውስጥ በሚሠራው ሥራ ስለ ክርስቶስ መስክሮአልና። ይህ ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ ልናምን ይገባናል።
እምነት ደግሞ ክርስቶስ ተስፋ የሰጠውን እንደሚያደርግ ያምናል፤ ወደ እርሱ የሚመጡትን ማንንም ወደ ውጭ እንደማያወጣ ተስፋ ስለ ሰጠ፣ ወደ እርሱ ብንመጣ እኛን ወደ ውጭ እንደማያወጣን እርግጥ ነው። ኢየሱስ፦ «እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል» ስላለ፣ እምነት ይህ እውነት መሆን እንዳለበት ያምናል፤ ይህን የሕይወት ውኃ ከክርስቶስ ብናገኝ በእኛ ውስጥ ይኖራል፤ በቅዱስ ሕይወት ጅረቶችም በውስጣችን ይፈልቃል። ክርስቶስ አደርጋለሁ ብሎ ተስፋ የሰጠውን ሁሉ ያደርገዋል፤ እኛም ይህን ልናምን ይገባናል፤ ስለዚህም በእርሱ ለሚያምኑ ተስፋ እንደ ሰጠው ይቅርታን፣ መጽደቅን፣ መጠበቅንና የዘላለም ክብርን ከእጁ እንጠብቃለን።
ከዚያም ቀጣዩ አስፈላጊ እርምጃ ይመጣል። ኢየሱስ እንደሚባለው ዓይነት ነው፤ ኢየሱስ አደርጋለሁ ያለውን ያደርጋል፤ ስለዚህ እያንዳንዳችን እንዲህ እያልን በእርሱ ልንታመን ይገባናል፦ «እርሱ ነኝ እንዳለው ለእኔ ይሆንልኛል፤ አደርጋለሁ ብሎ ተስፋ የሰጠውንም ያደርግልኛል፤ እንዲያድነኝ ራሴን ለማዳን በተሾመው በእርሱ እጅ እተዋለሁ። እንዳለው እንደሚያደርግ በገባው ተስፋ ላይ አርፋለሁ።» ይህ የሚያድን እምነት ነው፤ ያለውም የዘላለም ሕይወት አለው። አደጋውና ችግሩ ምንም ቢሆን፣ ጨለማውና ጭንቀቱ ምንም ቢሆን፣ ድካሙና ኃጢአቱ ምንም ቢሆን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ እንዲህ የሚያምን አይፈረድበትም፤ ወደ ፍርድም ከቶ አይመጣም።
ይህ ማብራሪያ በጥቂቱ እንኳ ቢጠቅም ምኞቴ ነው! አንባቢዬን ወዲያውኑ ወደ ሰላም ለመምራት የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲጠቀምበት ተስፋ አደርጋለሁ። «እመን ብቻ እንጂ አትፍራ።» ታመን፤ እረፍም።
የምፈራው አንባቢው መደረግ ያለበትን በማስተዋሉ ብቻ ረክቶ ከቶ ሳያደርገው እንዳይቀር ነው። በግምት ዓለም ውስጥ ከተተወ ከሁሉ የላቀ የእምነት አሳብ ይልቅ በእውነት በሥራ ላይ ያለ እጅግ ደካማው እውነተኛ እምነት ይሻላል። ዋናው ነገር በጌታ ኢየሱስ ወዲያውኑ ማመን ነው። ስለ ልዩነቶችና ስለ ትርጓሜዎች አትጨነቅ። የተራበ ሰው የምግቡን ይዘት፣ የአፉን አሠራር ወይም የምግብ መፈጨትን ሂደት ባያውቅም ይበላል፤ የሚኖረውም ስለሚበላ ነው። ከእርሱ እጅግ የበለጠ ብልህ የሆነ ሌላ ሰው የአመጋገብን ሳይንስ በሚገባ ያውቀዋል፤ ነገር ግን ካልበላ ከነእውቀቱ ሁሉ ይሞታል። የእምነትን ትምህርት አስተውለው ነገር ግን ያላመኑ ብዙዎች በዚህች ሰዓት በሲኦል እንዳሉ አያጠራጥርም። በሌላ በኩል ደግሞ እምነቱን በማስተዋል ሊተረጒም ከቶ ባይችልም፣ በጌታ ኢየሱስ የታመነ አንድ ሰው እንኳ ወደ ውጭ ተጥሎ አያውቅም። ኦ ውድ አንባቢ ሆይ፣ ጌታ ኢየሱስን ወደ ነፍስህ ተቀበለው፤ ለዘላለምም በሕይወት ትኖራለህ! «በእርሱ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።»
ምዕራፍ 8 ተጠናቋል
እምነት ምንድር ነው?