ሁሉም በጸጋ
እምነት በምን ሊመሰል ይችላል?

ምዕራፍ 9 · 7 ደቂቃ ንባብ · 9 ደቂቃ ማዳመጥ

እምነት በምን ሊመሰል ይችላል?

የእምነትን ጉዳይ ይበልጥ ግልጥ ለማድረግ ጥቂት ምሳሌዎችን እሰጥሃለሁ። አንባቢዬን እንዲያይ ሊያደርገው የሚችል መንፈስ ቅዱስ ብቻ ቢሆንም፣ የምችለውን ብርሃን ሁሉ መስጠትና መለኮታዊው ጌታ የዕውሮችን ዓይኖች እንዲከፍት መጸለይ ግዴታዬም ደስታዬም ነው። ኦ፣ አንባቢዬ ለራሱ ይህንኑ ጸሎት ምነው ቢጸልይ!

የሚያድን እምነት በሰው አካል ውስጥ ምሳሌዎች አሉት።
እምነት የሚመለከት ዓይን ነው። በዓይን አማካይነት እጅግ ሩቅ ያለውን ነገር ወደ አእምሮአችን እናመጣለን፤ በአንድ የዓይን ቅጽበት ፀሐይንና ሩቅ ያሉትን ከዋክብት ወደ አእምሮአችን ልናመጣ እንችላለን። እንዲሁም በመታመን ጌታ ኢየሱስን ወደ እኛ እናቀርበዋለን፤ እርሱ በሰማይ እጅግ ሩቅ ቢሆንም ወደ ልባችን ይገባል። ወደ ኢየሱስ ብቻ ተመልከት፤ መዝሙሩ ፍጹም እውነት ነውና—
ወደ ተሰቀለው በመመልከት ሕይወት አለ፤
ለአንተም በዚህች ቅጽበት ሕይወት አለ።

እምነት የሚጨብጥ እጅ ነው። እጃችን አንድን ነገር ለራሱ በሚይዝበት ጊዜ፣ እምነት ክርስቶስንና የቤዛነቱን በረከቶች የራሱ በሚያደርግበት ጊዜ የሚያደርገውን በትክክል ያደርጋል። እምነት፦ «ኢየሱስ የእኔ ነው» ይላል። እምነት ይቅርታ ስለሚያስገኘው ደም ይሰማና፦ «ይቅር እንዲለኝ እቀበለዋለሁ» ብሎ ይጮኻል። እምነት ኢየሱስ በሞቱ ያወረሳቸውን ውርሶች የራሱ ብሎ ይጠራል፤ እነርሱም በእርግጥ የራሱ ናቸው፤ እምነት የክርስቶስ ወራሽ ነውና፤ እርሱ ራሱንና ያለውን ሁሉ ለእምነት ሰጥቶአል። ወዳጄ ሆይ፣ ጸጋ ያዘጋጀልህን ውሰድ። ሌባ አትሆንም፤ መለኮታዊ ፈቃድ አለህና፦ «የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።» ሀብትን በመጨበጥ ብቻ ሊያገኝ የሚችል ሰው ድሃ ሆኖ ቢቀር በእርግጥ ሞኝ ነው።

እምነት ክርስቶስን የሚመገብ አፍ ነው። ምግብ ሊመግበን ከመቻሉ በፊት ወደ ውስጣችን መግባት አለበት። ይህ መብላትና መጠጣት ቀላል ነገር ነው። ምግባችን የሆነውን በፈቃደኝነት ወደ አፋችን እንቀበላለን፤ ከዚያም ወደ ውስጣዊ ክፍሎቻችን እንዲወርድ እንፈቅዳለን፤ በዚያም ተወስዶ ከአካላችን ጋር ይዋሐዳል። ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ በአሥረኛው ምዕራፍ፦ «በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል» ይላል። እንግዲህ መደረግ ያለበት ሁሉ እርሱን መዋጥ፣ ወደ ነፍስ እንዲወርድ መፍቀድ ብቻ ነው። ኦ፣ ሰዎች የምግብ ፍላጎት ምነው በኖራቸው! የተራበና ምግብ በፊቱ ያየ ሰው እንዴት እንደሚበላ መማር አያስፈልገውምና። አንዱ፦ «ቢላዋና ሹካ፣ ዕድልም ስጡኝ» አለ። ቀሪውን ለማድረግ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነበረ። በእውነት ክርስቶስን የሚራብና የሚጠማ ልብ እርሱ በነጻ እንደ ተሰጠ ማወቅ ብቻ ያስፈልገዋል፤ ወዲያውኑም ይቀበለዋል። አንባቢዬ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ከሆነ ኢየሱስን ለመቀበል አያመንታ፤ ይህን በማድረጉ ከቶ እንደማይወቀስ እርግጠኛ ሊሆን ይችላልና፤ «ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ … የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው»። እርሱ አንድንም ሰው አይገፋም፤ ነገር ግን የሚመጡትን ሁሉ ለዘላለም ልጆች ሆነው እንዲኖሩ ሥልጣን ይሰጣቸዋል።

የሕይወት ሥራዎች እምነትን በብዙ መንገድ ይገልጣሉ። ገበሬ መልካም ዘርን በምድር ውስጥ ይቀብራል፤ በሕይወት እንዲኖር ብቻ ሳይሆን እንዲበዛም ይጠብቃል። «ዘርና መከር … አያቋርጡም» በሚለው የቃል ኪዳን ሥርዓት እምነት አለው፤ ስለ እምነቱም ዋጋውን ያገኛል።

ነጋዴ ገንዘቡን በባንክ ሰው እጅ ያስቀምጣል፤ በባንኩ ታማኝነትና ጽናት ላይም ፈጽሞ ይታመናል። ገንዘቡን በሌላ ሰው እጅ አደራ ይሰጣል፤ ጠንካራውን ወርቅ በብረት ሣጥን ውስጥ ቈልፎ ከሚያስቀምጠው ይልቅ እጅግ ተረጋግቶ ይኖራል።

መርከበኛ ራሱን ለባሕሩ አደራ ይሰጣል። ሲዋኝ እግሩን ከታችኛው መሬት አንሥቶ በሚያንሳፍፈው ውቅያኖስ ላይ ያርፋል። ራሱን ሙሉ በሙሉ በውኃው ላይ ካልጣለ መዋኘት አይችልም ነበር።

ወርቅ አንጥረኛ የከበረውን ብረት ሊበላው የጓጓ በሚመስል እሳት ውስጥ ያስገባዋል፤ ነገር ግን በሙቀቱ ነጥሮ ከእቶኑ መልሶ ይቀበለዋል።

በሕይወት ውስጥ በሰውና በሰው መካከል ወይም በሰውና በተፈጥሮ ሕግ መካከል እምነት ሲሠራ ሳታይ ወደ የትም ዘወር ማለት አትችልም። እንግዲህ በዕለት ተዕለት ሕይወት እንደምንታመን እንዲሁ በክርስቶስ ኢየሱስ በተገለጠው በእግዚአብሔር ልንታመን ይገባናል።

እምነት በተለያዩ ሰዎች ዘንድ እንደ እውቀታቸው መጠን ወይም በጸጋ እንዳደጉበት መጠን በልዩ ልዩ ደረጃ ይገኛል። አንዳንድ ጊዜ እምነት በክርስቶስ ላይ በቀላሉ ከመጣበቅ ብዙም የሚበልጥ አይደለም፤ የመደገፍ ስሜትና እንዲህ ለመደገፍ ፈቃደኛነት ብቻ ነው። በባሕር ዳርቻ በምትሆንበት ጊዜ በዓለቱ ላይ ተጣብቀው የሚኖሩ ሊምፔት የሚባሉ ትናንሽ የባሕር ቀንድ አውጣዎችን ታያለህ። ቀስ ብለህ ወደ ዓለቱ ትጠጋለህ፤ አንዱን በምርኵዝህ ፈጥነህ ትመታዋለህ፤ እርሱም ይላቀቃል። ቀጣዩንም እንዲሁ ሞክር። ማስጠንቀቂያ ሰጥተኸዋል፤ ጎረቤቱን የመታህበትን ምት ሰምቶአል፤ በሙሉ ኃይሉም ይጣበቃል። ከቶ ልታላቅቀው አትችልም፤ አንተማ አትችልም! ምታ፤ ደግመህም ምታ፤ ነገር ግን ዓለቱን ብትሰብረው ይቀልሃል። ትንሹ ወዳጃችን ሊምፔት ብዙ አያውቅም፤ ነገር ግን ይጣበቃል። የዓለቱን የመሬት አሠራር አያውቅም፤ ነገር ግን ይጣበቃል። መጣበቅ ይችላል፤ የሚጣበቅበትንም ነገር አግኝቶአል፤ እውቀቱ ሁሉ ይህ ብቻ ነው፤ ለደኅንነቱና ለመዳኑም ይጠቀምበታል። ለሊምፔቱ ሕይወቱ በዓለቱ ላይ መጣበቅ ነው፤ ለኃጢአተኛውም ሕይወቱ በኢየሱስ ላይ መጣበቅ ነው። በሺዎች የሚቈጠሩ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከዚህ የበለጠ እምነት የላቸውም፤ በሙሉ ልባቸውና በሙሉ ነፍሳቸው በኢየሱስ ላይ ለመጣበቅ የሚበቃ ያህል ያውቃሉ፤ ይህም ለአሁኑ ሰላምና ለዘላለም ደኅንነት ይበቃል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነርሱ ብርቱና ኃያል አዳኝ፣ የማይነቃነቅና የማይለወጥ ዓለት ነው፤ ሕይወታቸውን ለማዳን አጥብቀው ይጣበቁበታል፤ ይህም መጣበቅ ያድናቸዋል። አንባቢ ሆይ፣ አንተስ መጣበቅ አትችልምን? ወዲያውኑ እንዲሁ አድርግ።

አንዱ ሰው ሌላው ከእርሱ እንደሚበልጥ በማወቅ በእርሱ ሲደገፍ እምነት ይታያል። ይህ ከፍ ያለ እምነት ነው፤ ለመደገፉ ምክንያቱን የሚያውቅና በዚያም መሠረት የሚሠራ እምነት ነው። ሊምፔቱ ስለ ዓለቱ ብዙ የሚያውቅ አይመስለኝም፤ ነገር ግን እምነት እያደገ ሲሄድ ይበልጥ አስተዋይ እየሆነ ይሄዳል። ዕውር ሰው ወዳጁ ማየት እንደሚችል ስለሚያውቅ ራሱን ለመሪው አደራ ይሰጣል፤ እየታመነም መሪው ወደሚወስደው ስፍራ ይሄዳል። ምስኪኑ ሰው ዕውር ሆኖ ከተወለደ ማየት ምን እንደ ሆነ አያውቅም፤ ነገር ግን ማየት የሚባል ነገር እንዳለ፣ ወዳጁም እንዳለው ያውቃል፤ ስለዚህም እጁን በሚያየው ሰው እጅ ውስጥ በነጻነት ያኖራል፤ አመራሩንም ይከተላል። «በማየት ሳይሆን በእምነት እንመላለሳለንና።» «ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው።» ይህ ሊገኝ ከሚችለው የእምነት ምሳሌ ሁሉ ያህል መልካም ነው፤ ኢየሱስ እኛ የሌለን ብቃት፣ ኃይልና በረከት እንዳለው እናውቃለን፤ ስለዚህም ለራሳችን ልንሆን የማንችለውን ይሆንልን ዘንድ ራሳችንን በደስታ ለእርሱ አደራ እንሰጣለን። ዕውሩ ሰው በመሪው እንደሚታመን በእርሱ እንታመናለን። እርሱ መተማመናችንን ከቶ አይክድም፤ ነገር ግን «ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም ሆነልን»።

ወደ ትምህርት ቤት የሚሄድ ልጅ ሁሉ በሚማርበት ጊዜ እምነትን መጠቀም አለበት። መምህሩ መልክዓ ምድርን ያስተምረዋል፤ ስለ ምድር ቅርጽና ስለ አንዳንድ ታላላቅ ከተሞችና መንግሥታት መኖር ያስረዳዋል። ልጁ መምህሩንና በእጁ የተሰጡትን መጻሕፍት ከማመኑ በቀር እነዚህ ነገሮች እውነት እንደ ሆኑ ራሱ አያውቅም። ልትድን ከሆንህ ከክርስቶስ ጋር ማድረግ ያለብህ ይህንኑ ነው፤ እርሱ ስለ ነገረህ ብቻ ልታውቅ፣ እንዲሁ እንደ ሆነ ስላረጋገጠልህ ልታምን፣ ውጤቱም መዳን እንደሚሆን ተስፋ ስለ ሰጠህ ራስህን ለእርሱ አደራ ልትሰጥ ይገባሃል። እኔና አንተ የምናውቀው ሁሉ ማለት ይቻላል ወደ እኛ የመጣው በእምነት ነው። አንድ የሳይንስ ግኝት ተገኝቶአል፤ እኛም በእርሱ እርግጠኞች ነን። በምን መሠረት እናምነዋለን? ስማቸው በሚገባ በታወቀና ዝናቸው በጸና በአንዳንድ ምሁራን ሥልጣን ላይ ተመሥርተን ነው። ሙከራዎቻቸውን አድርገን ወይም አይተን አናውቅም፤ ነገር ግን ምስክርነታቸውን እናምናለን። ስለ ኢየሱስም እንዲሁ ማድረግ አለብህ፤ አንዳንድ እውነቶችን ስለሚያስተምርህ ደቀ መዝሙሩ ልትሆንና ቃሉን ልታምን ይገባሃል፤ አንዳንድ ሥራዎችን ስለ ፈጸመ ጉዳይህን ለእርሱ የምትሰጥ ልትሆንና ራስህን ለእርሱ አደራ ልትሰጥ ይገባሃል። እርሱ ከአንተ ወሰን በሌለው መጠን ይበልጣል፤ መምህርህና ጌታህ ሆኖ መተማመንህን ለማግኘት ራሱን ያቀርባል። እርሱንና ቃሉን ብትቀበል ትድናለህ።

ሌላውና ከፍ ያለው የእምነት ዓይነት ከፍቅር የሚመነጨው እምነት ነው። ልጅ በአባቱ የሚታመነው ለምንድር ነው? ልጁ በአባቱ የሚታመንበት ምክንያት ስለሚወደው ነው። ለእርሱ ካላቸው ጥልቅ ፍቅር ጋር የተቈራኘ ጣፋጭ እምነት በኢየሱስ ያላቸው የተባረኩና ደስተኞች ናቸው፤ ይህ የሚያሳርፍ መተማመን ነውና። እነዚህ ኢየሱስን የሚወዱ በባሕርዩ ይማረካሉ፤ በተልእኮውም ደስ ይላቸዋል፤ ባሳየው ቸርነትም ልባቸው ተማርኮአል፤ ስለዚህም እጅግ ስለሚያደንቁት፣ ስለሚያከብሩትና ስለሚወዱት በእርሱ ከመታመን በቀር ሌላ ማድረግ አይችሉም።

በአዳኙ ላይ ያለው የፍቅር መታመን መንገድ እንዲህ ሊገለጥ ይችላል። አንዲት ሴት በዘመኑ እጅግ የታወቀው ሐኪም ሚስት ናት። በአደገኛ ሕመም ተይዛ በኃይሉ ተመትታ ወድቃለች፤ ሆኖም በሚያስደንቅ ሁኔታ የተረጋጋችና ጸጥ ያለች ናት፤ ባሏ ይህን በሽታ በልዩ ሁኔታ አጥንቶታልና፤ በዚሁ የተጠቁ በሺዎች የሚቈጠሩትንም ፈውሶአል። ፈጽሞ አትታወክም፤ ለእርሷ እጅግ ውድ በሆነው፣ ችሎታና ፍቅር በከፍተኛ ደረጃቸው በተዋሐዱበት በእርሱ እጅ ፍጹም ደኅና እንደ ሆነች ይሰማታልና። እምነቷ ምክንያታዊና ተፈጥሮአዊ ነው፤ ባሏ በየትኛውም አቅጣጫ ቢታይ ይህ ከእርሷ ይገባዋል። ከአማኞች እጅግ ደስተኞቹ በክርስቶስ ላይ የሚያሳዩት እምነት እንዲህ ያለ ነው። እንደ እርሱ ያለ ሐኪም የለም፤ እርሱ እንደሚያድን ማንም ሊያድን አይችልም፤ እኛ እንወደዋለን፤ እርሱም ይወደናል፤ ስለዚህ ራሳችንን በእጁ እንሰጣለን፤ የሚያዝልንን ሁሉ እንቀበላለን፤ የሚለንንም ሁሉ እናደርጋለን። እርሱ ጉዳዮቻችንን የሚመራ ሆኖ ሳለ አንዳች ነገር በስሕተት ሊደረግ እንደማይችል ይሰማናል፤ እንድንጠፋ ወይም አንዲት አላስፈላጊ ሥቃይ እንኳ እንድንቀበል እንዳይፈቅድ እጅግ ይወደናልና።

እምነት የመታዘዝ ሥር ነው፤ ይህም በሕይወት ጉዳዮች በግልጥ ሊታይ ይችላል። የመርከብ አዛዥ መርከቡን ወደ ወደብ እንዲያስገባ በወደብ መሪው ሲታመን መርከቡን እንደ እርሱ መመሪያ ያንቀሳቅሳል። መንገደኛ አስቸጋሪ የተራራ መተላለፊያን እንዲያሻግረው በመሪ ሲታመን መሪው የሚያሳየውን መንገድ ይከተላል። ሕመምተኛ በሐኪም ሲያምን ያዘዘለትን መድኃኒትና መመሪያ በጥንቃቄ ይከተላል። የአዳኙን ትእዛዛት ለመታዘዝ እምቢ የሚል እምነት ማስመሰል ብቻ ነው፤ ነፍስንም ከቶ አያድንም። እንዲያድነን በኢየሱስ እንታመናለን፤ እርሱ ስለ መዳን መንገድ መመሪያ ይሰጠናል፤ እኛም ያንን መመሪያ እንከተላለን፤ እንድናለንም። አንባቢዬ ይህን አይርሳ። በኢየሱስ ታመን፤ የሚያዝህንም ሁሉ በማድረግ መታመንህን አረጋግጥ።

የታወቀ አንድ የእምነት ዓይነት ከተረጋገጠ እውቀት ይመነጫል፤ ይህ በጸጋ ከማደግ የሚመጣ ነው፤ ክርስቶስን ስለሚያውቀው የሚያምነው፣ ፈጽሞ የማይሳሳት ታማኝ መሆኑን ስላረጋገጠም የሚታመንበት እምነት ነው። አንዲት አሮጊት ክርስቲያን አንድን የተስፋ ቃል ሞክራ ባረጋገጠች ቍጥር በመጽሐፍ ቅዱሷ ዳር ላይ «ፈ.» እና «ረ.» ብላ የመጻፍ ልማድ ነበራት፤ ይህም «ተፈትኖአል፣ ተረጋግጦአል» ማለት ነበር። የተፈተነና የተረጋገጠ አዳኝን መታመን ምንኛ ቀላል ነው! አንተ ገና ይህን ማድረግ አትችልም፤ ነገር ግን ታደርገዋለህ። ሁሉም ነገር መጀመሪያ ሊኖረው ይገባል። በጊዜው ወደ ብርቱ እምነት ትደርሳለህ። ይህ የበሰለ እምነት ምልክትንና ማስረጃን አይለምንም፤ ነገር ግን በድፍረት ያምናል። የመርከብ አዛዡን እምነት ተመልከት—ብዙ ጊዜ ተደንቄበታለሁ። ገመዱን ይፈታል፤ ከምድሩም ርቆ ይጓዛል። ለቀናት፣ ለሳምንታት፣ ወይም ለወራት እንኳ ሸራ ወይም የባሕር ዳርቻ አያይም፤ ሆኖም አንድ ማለዳ ሲመራበት ከነበረው ከተመኘው ወደብ ፊት ለፊት በትክክል ራሱን እስኪያገኝ ድረስ ሌሊትና ቀን ያለ ፍርሃት ይጓዛል። መንገድ በሌለበት ጥልቅ ባሕር ላይ መንገዱን እንዴት አገኘ? በኮምፓሱ፣ በባሕር ጉዞ መምሪያ መጽሐፉ፣ በመነጽሩና በሰማይ አካላት ታምኖአል፤ መሪነታቸውንም በመታዘዝ ምድርን ሳያይ ወደ ወደቡ ለመግባት አቅጣጫውን በጥቂቱ እንኳ መለወጥ እስከማያስፈልገው ድረስ በትክክል መርቶአል። ይህ—ሳያዩ በሸራ ወይም በእንፋሎት መጓዝ—አስደናቂ ነገር ነው። በመንፈሳዊ ሁኔታም የማየትንና የስሜትን የባሕር ዳርቻዎች ፈጽሞ ትቶ ለውስጣዊ ስሜቶች፣ ለሚያበረታቱ መግቦቶች፣ ለምልክቶችና ለማስረጃዎች ለመሳሰሉትም «ደኅና ሁኑ» ማለት የተባረከ ነገር ነው። በመለኮታዊ ፍቅር ውቅያኖስ ላይ ሩቅ ሆኖ በእግዚአብሔር እያመኑ በእግዚአብሔር ቃል መሪነት ቀጥ ብሎ ወደ ሰማይ መጓዝ እንዴት ያለ ክብር ነው። «ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው»፤ ለእነርሱ በመጨረሻ በሙላት መግባት፣ በመንገዳቸውም ደኅና ጉዞ ይሰጣቸዋል። አንባቢዬ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው በእግዚአብሔር አይታመንምን? እኔ በዚያ በደስታ መተማመን አርፋለሁ። ወንድሜ ሆይ፣ ከእኔ ጋር ና፤ አባታችንንና አዳኛችንንም እመን። ወዲያውኑ ና።

ገጽ 1 / 1 · 7 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ