ሁሉም በጸጋ
ቅዱሳን ስለ ምን ይጸናሉ?

ምዕራፍ 19 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ

ቅዱሳን ስለ ምን ይጸናሉ?

ጳውሎስ ስለ ቆሮንቶስ ወንድሞች በልቡ የያዘው ተስፋ፣ ስለ ወደ ፊት ሕይወታቸው ለሚንቀጠቀጡ ሰዎች መጽናናት የሞላበት እንደ ሆነ አስቀድመን አይተናል። ነገር ግን ወንድሞች እስከ ፍጻሜ ድረስ እንደሚጸኑ ያመነው ስለ ምን ነበር?

ምክንያቶቹን እንደሚሰጥ እንድታስተውል እወዳለሁ። እነሆ፦

ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 1:9)።

ሐዋርያው «እናንተ የታመናችሁ ናችሁ» አይልም። ወዮ! የሰው ታማኝነት እጅግ የማይታመን ነገር ነው፤ ከንቱ ብቻ ነው። «የሚመሩአችሁና የሚያስተምሩአችሁ የታመኑ አገልጋዮች ስላሏችሁ በደኅና እንደምትኖሩ እተማመናለሁ» አይልም። ኦ፣ አይደለም! በሰዎች የምንጠበቅ ብንሆን አጠባበቃችን እጅግ ደካማ በሆነ ነበር። እርሱ ግን «እግዚአብሔር የታመነ ነው» ይላል። እኛ የታመንን ሆነን ብንገኝ፣ ይህ የሚሆነው እግዚአብሔር የታመነ ስለ ሆነ ነው። የመዳናችን ሸክም ሁሉ ማረፍ ያለበት በቃል ኪዳን አምላካችን ታማኝነት ላይ ነው። ነገሩ ሁሉ የተንጠለጠለው በዚህ ክቡር የእግዚአብሔር ባሕርይ ላይ ነው። እኛ እንደ ነፋስ ተለዋዋጮች፣ እንደ ሸረሪት ድር ተሰባሪዎች፣ እንደ ውኃም ደካሞች ነን። በተፈጥሮ ባሕርያችንም ሆነ በደረስንበት መንፈሳዊ ደረጃ ላይ መተማመን አይቻልም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የታመነ ሆኖ ይኖራል። በፍቅሩ የታመነ ነው፤ መለወጥ በእርሱ ዘንድ የለም፣ በመዞርም የተደረገ ጥላ የለበትም። ለዓላማው የታመነ ነው፤ ሥራን ጀምሮ ሳይፈጽም አይተወውም። ለግንኙነቶቹ የታመነ ነው፤ እንደ አባት ልጆቹን አይጥልም፣ እንደ ወዳጅ ሕዝቡን አይክድም፣ እንደ ፈጣሪም የገዛ እጁን ሥራ አይተውም። ለተስፋ ቃሎቹ የታመነ ነው፤ ከእነርሱም አንዲቱ እንኳ ለአንድ አማኝ ስንኳ እንድትቀር ከቶ አይፈቅድም። በክርስቶስ ኢየሱስ ከእኛ ጋር ላደረገውና በመሥዋዕቱ ደም ላጸናው ቃል ኪዳኑ የታመነ ነው። ለልጁ የታመነ ነው፤ ክቡር ደሙም በከንቱ እንዲፈስ አይፈቅድም። የዘላለም ሕይወትን ተስፋ ለሰጣቸውና ፊቱን ከእነርሱ ለማይመልስ ለሕዝቡ የታመነ ነው።

ይህ የእግዚአብሔር ታማኝነት እስከ መጨረሻ ድረስ የመጽናታችን ተስፋ መሠረትና የማዕዘን ድንጋይ ነው። ቅዱሳን በቅድስና ይጸናሉ፤ እግዚአብሔር በጸጋ ይጸናልና። እርሱ መባረኩን ይቀጥላል፤ ስለዚህ አማኞች ተባርከው ይጸናሉ። ሕዝቡን መጠበቁን ይቀጥላል፤ ስለዚህ እነርሱም ትእዛዛቱን መጠበቃቸውን ይቀጥላሉ። ይህ የምናርፍበት መልካምና ጽኑ መሬት ነው፤ ደግሞም ከዚህች ትንሽ መጽሐፍ ርእስ፣ «ሁሉም በጸጋ» ከሚለው ጋር በሚያስደስት ሁኔታ ይስማማል። እንዲሁም የመዳንን ንጋት በደወል የሚያበሥሩት ነጻ ሞገስና ወሰን የሌለው ምሕረት ናቸው፤ እነዚያው ጣፋጭ ደወሎችም በጸጋው ቀን ሁሉ በዜማ ይደወላሉ።

እስከ ፍጻሜ ድረስ እንደምንጸናና በመጨረሻም ያለ ነቀፋ ሆነን እንደምንገኝ ተስፋ የምናደርግባቸው ምክንያቶች ሁሉ የሚገኙት በአምላካችን ብቻ እንደ ሆነ ታያለህ፤ በእርሱ ግን እነዚህ ምክንያቶች እጅግ የበዙ ናቸው።

በመጀመሪያ፣ እግዚአብሔር ባደረገው ነገር ውስጥ ይገኛሉ። እኛን በመባረክ እጅግ ርቆ ሄዶአልና ወደ ኋላ መመለስ አይቻለውም። ጳውሎስ «ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት ጠርቶናል» ብሎ ያሳስበናል። ጠርቶናልን? እንግዲያስ ጥሪው ሊሻር አይችልም፤ «እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትምና»። ጌታ ከጸጋው ውጤታማ ጥሪ ከቶ አይመለስም። «የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው»፤ ይህ የመለኮታዊው አሠራር የማይለወጥ ሕግ ነው። ስለ እርሱ «የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው» የተባለለት ለሁሉ የሚቀርብ የወል ጥሪ አለ፤ አሁን የምናስበው ግን ሌላ ዓይነት ጥሪ ነው፤ ልዩ ፍቅርን የሚያመለክትና የተጠራንለትን ነገር መውረሳችንን ግድ የሚያደርግ ጥሪ ነው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ የተጠራው ሰው ልክ እንደ አብርሃም ዘር ነው፤ ስለ እርሱም ጌታ እንዲህ አለ፦ «ከምድር ዳርቻ ጠራሁህ፥ አንተ ባሪያዬ ነህ፥ መርጬሃለሁ፥ አልጣልሁህምም አልሁህ።»

ጌታ ባደረገው ነገር ውስጥ ለመጠበቃችንና ለሚመጣው ክብራችን ጠንካራ ምክንያቶችን እናያለን፤ ጌታ ወደ ልጁ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት ጠርቶናልና። ይህ ማለት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ሽርክና ማለት ነው፤ ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ በጥንቃቄ እንድታስብበት እወዳለሁ። በእርግጥ በመለኮታዊ ጸጋ ተጠርተህ ከሆነ፣ በነገር ሁሉ ከእርሱ ጋር የጋራ ባለቤት እስክትሆን ድረስ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ኅብረት ገብተሃል። ከእንግዲህ ወዲህ በልዑል ፊት ከእርሱ ጋር አንድ ነህ። ጌታ ኢየሱስ ስለ አንተ እርግማን ሆኖ በሥጋው ኃጢአትህን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በዚያው ጊዜም በእርሱ እንድትጸድቅ ጽድቅህ ሆኖልሃል። አንተ የክርስቶስ ነህ፤ ክርስቶስም የአንተ ነው። አዳም ስለ ዘሩ እንደ ቆመ፣ እንዲሁ ኢየሱስ በእርሱ ስላሉት ሁሉ ይቆማል። ባልና ሚስት አንድ እንደ ሆኑ፣ እንዲሁ ኢየሱስ በእምነት ከእርሱ ጋር ከተባበሩት ሁሉ ጋር አንድ ነው፤ ከቶ ሊፈርስ በማይችል የጋብቻ አንድነት አንድ ናቸው። ከዚህም በላይ አማኞች የክርስቶስ አካል ብልቶች ናቸው፤ ስለዚህም በፍቅር፣ በሕያውና በዘላቂ አንድነት ከእርሱ ጋር አንድ ናቸው። እግዚአብሔር ወደዚህ አንድነት፣ ወደዚህ ኅብረት፣ ወደዚህ ሽርክና ጠርቶናል፤ በዚሁ ነገርም እስከ ፍጻሜ ድረስ እንደምንጸና ምልክትንና መያዣን ሰጥቶናል። ከክርስቶስ ተለይተን ብንታይ ኖሮ፣ ፈጥነው የሚፈርሱና ወደ ጥፋት የሚወሰዱ ምስኪንና ጠፊ ግለሰቦች በሆንን ነበር፤ ከኢየሱስ ጋር አንድ እንደ መሆናችን ግን የባሕርዩ ተካፋዮች ሆነናል፤ የማይሞተውንም ሕይወቱን ተሰጥተናል። ዕጣ ፈንታችን ከጌታችን ዕጣ ፈንታ ጋር የተሳሰረ ነው፤ እርሱ ሊጠፋ እስካልቻለ ድረስ እኛ እንጠፋ ዘንድ አይቻልም።

ወደ ተጠራህበት ወደዚህ ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር ወደ ሆነው ሽርክና አብዝተህ አስብ፤ ተስፋህ ሁሉ ያለው በዚያ ነውና። ኢየሱስ ባለ ጠጋ እስከ ሆነ ድረስ ከቶ ድሀ ልትሆን አትችልም፤ ከእርሱ ጋር በአንድ የንግድ ድርጅት ውስጥ ነህና። የሰማይና የምድር ባለቤት ከሆነው ከእርሱ ጋር የጋራ ባለ ንብረት ስለ ሆንህ ችግር ከቶ ሊያጠቃህ አይችልም። ከቶ ልትከስር አትችልም፤ በድርጅቱ ውስጥ ካሉት ባልንጀሮች አንዱ ምንም የሌለው ምስኪን፣ በራሱም ፈጽሞ የከሰረ፣ ከከባድ ዕዳው ትንሿን እንኳ ሊከፍል የማይችል ቢሆንም፣ ሌላኛው ባልንጀራ ግን ሊታሰብ በማይቻልና በማያልቅ ሁኔታ ባለ ጠጋ ነው። በዚህ ዓይነት ሽርክና ውስጥ ከዘመኑ ድቀት፣ ከወደ ፊቱ ለውጦችና ከነገር ሁሉ ፍጻሜ መናወጥ በላይ ከፍ ብለሃል። ጌታ ወደ ልጁ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት ጠርቶሃል፤ በዚያም በፈጸመውና ባጸናው ድርጊት ፈጽሞ በማይወድቅ ጥበቃ ስፍራ አኑሮሃል።

በእርግጥ አማኝ ከሆንህ ከኢየሱስ ጋር አንድ ነህ፤ ስለዚህም በደኅና ነህ። እንዲህ መሆን ግድ እንደ ሆነ አታይምን? በእርግጥ በማይሻረው በእግዚአብሔር ድርጊት ከኢየሱስ ጋር አንድ ከሆንህ፣ እርሱ እስከሚገለጥበት ቀን ድረስ እስከ ፍጻሜ መጽናትህ ግድ ነው። ክርስቶስና የሚያምነው ኃጢአተኛ በአንዲት ጀልባ ውስጥ ናቸው፤ ኢየሱስ ካልሰመጠ አማኙ ከቶ አይሰጥምም። ኢየሱስ የዋጃቸውን ከራሱ ጋር እንዲህ ባለ ትስስር አስተሳስሮአቸዋል፤ ስለዚህ በደሙ ከገዛቸው ከትንሹ አንዱ እንኳ ጕዳት ከመድረሱ በፊት እርሱ ራሱ አስቀድሞ መመታት፣ መሸነፍና መዋረድ ይኖርበታል። በድርጅቱ ራስ ላይ የተጻፈው የእርሱ ስም ነው፤ ይህ ስም ሊዋረድ እስካልተቻለ ድረስ ከመክሰር ፍርሃት ሁሉ በደኅና ነን።

እንግዲያስ፣ ከኢየሱስ ጋር ለዘላለም ተሳስረን፣ በፍጹም መተማመን ወደማይታወቀው የወደ ፊት ዘመን እንግፋ። የዓለም ሰዎች «ይህች በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ ማን ናት?» ብለው ቢጮኹ፣ በእርግጥ በኢየሱስ ላይ እንደምንደገፍ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜም ይበልጥ በእርሱ ላይ ለመደገፍ እንዳሰብን በደስታ እንመሰክራለን። የታመነው አምላካችን ዘወትር የሚፈልቅ የደስታ ምንጭ ነው፤ ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር ያለን ኅብረትም የሐሤት ሙሉ ወንዝ ነው። እነዚህን ክቡር ነገሮች እያወቅን ተስፋ ልንቆርጥ አንችልም፤ ይልቁንም ከሐዋርያው ጋር «በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ማን ይለየናል?» ብለን እንጮኻለን።

ምዕራፍ 19 ተጠናቋል

ቅዱሳን ስለ ምን ይጸናሉ?

ገጽ 1 / 1 · 5 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ