ሁሉም በጸጋ
ዳግመኛ መወለድና መንፈስ ቅዱስ

ምዕራፍ 13 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

ዳግመኛ መወለድና መንፈስ ቅዱስ

«ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል።» ይህ የጌታችን የኢየሱስ ቃል በገነት ደጅ ላይ እንደ ቆመው እንደ ኪሩቡ የተመዘዘ ሰይፍ በብዙዎች መንገድ ላይ የሚንበለበል መስሎ ታይቶአቸዋል። ይህ ለውጥ ከሙሉ ጥረታቸው በላይ ስለ ሆነ ተስፋ ቈርጠዋል። አዲሱ ልደት ከላይ ነው፤ ስለዚህም በፍጥረት ኃይል ውስጥ አይደለም። እንግዲህ የሐሰት መጽናናትን ለመፍጠር ብዬ አንድን እውነት መካድ፣ ወይም ከቶ መደበቅ፣ ከአሳቤ እጅግ የራቀ ነው። አዲሱ ልደት ከተፈጥሮ በላይ እንደ ሆነ፣ በኃጢአተኛው በራሱም ሊፈጸም እንደማይችል በነጻነት እቀበላለሁ። ያለ ጥርጥር እውነት የሆነውን እንዲጥል ወይም እንዲረሳ በማግባባት ለማበረታታት ብሞክር፣ ይህን ያህል ክፉ ብሆን፣ ለአንባቢዬ የምሰጠው ርዳታ ደካማ በሆነ ነበር።

ነገር ግን ጌታችን ይህን ሁሉን የሚያጠቃልል ቃል የተናገረበት ያው ምዕራፍ፣ ስለ እምነት መዳንም እጅግ ግልጥ የሆነውን ቃል የያዘ መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለምን? የዮሐንስን ወንጌል ሦስተኛ ምዕራፍ አንብብ፤ በመጀመሪያዎቹ ዓረፍተ ነገሮቹ ላይ ብቻ አትቈይ። ሦስተኛው ቁጥር እንዲህ ማለቱ እውነት ነው፦

ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።

ነገር ግን ደግሞ አሥራ አራተኛውና አሥራ አምስተኛው ቁጥሮች እንዲህ ይናገራሉ፦

ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል።

አሥራ ስምንተኛው ቁጥር ያንኑ ትምህርት ሰፋ ባለ ቃል ይደግመዋል፦

በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።

እነዚህ ሁለት ቃሎች ከአንድ አፍ የወጡ፣ በመንፈስ በተጻፈ በአንድ ገጽ ላይም የተመዘገቡ ስለ ሆኑ፣ መስማማት እንዳለባቸው ለማንኛውም አንባቢ ግልጥ ነው። ችግር ሊኖር በማይችልበት ስፍራ ስለ ምን ችግር እንፈጥራለን? አንዱ ቃል እግዚአብሔር ብቻ ሊሰጠው የሚችል አንድ ነገር ለመዳን አስፈላጊ እንደ ሆነ ቢያረጋግጥልን፣ ሌላው ደግሞ በኢየሱስ ብናምን ጌታ እንደሚያድነን ቢያረጋግጥልን፣ ጌታ ለሚያምኑት ለመዳን አስፈላጊ ነው የተባለውን ሁሉ እንደሚሰጣቸው ያለ ሥጋት መደምደም እንችላለን። ጌታ በእርግጥም በኢየሱስ በሚያምኑ ሁሉ ውስጥ አዲሱን ልደት ይፈጥራል፤ ማመናቸውም ዳግመኛ እንደ ተወለዱ ከሁሉ የላቀው ማስረጃ ነው።

ራሳችን ማድረግ ለማንችለው ነገር በኢየሱስ እንታመናለን፤ በራሳችን ኃይል ቢሆን ኖሮ ወደ እርሱ መመልከት ምን ያስፈልግ ነበር? ማመን የእኛ ድርሻ ነው፤ አዲስ አድርጎ መፍጠር የጌታ ድርሻ ነው። እርሱ በእኛ ፋንታ አያምንም፤ እኛም በእርሱ ፋንታ ዳግመኛ የመውለድን ሥራ አንሠራም። የጸጋውን ትእዛዝ መታዘዝ ለእኛ ይበቃናል፤ አዲሱን ልደት በእኛ ውስጥ መሥራት የጌታ ነው። ስለ እኛ በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ የሄደው እርሱ ለዘላለም ደኅንነታችን የሚያስፈልገንን ሁሉ ሊሰጠን ይችላል፤ ይሰጠንማል።

«ነገር ግን የሚያድን የልብ ለውጥ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው።» ይህም እጅግ እውነት ነው፤ ልንጠራጠረው ወይም ልንረሳው ከእኛ ይራቅ። ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ስውርና ምሥጢራዊ ነው፤ ሊታይ የሚችለውም በፍሬው ብቻ ነው። በተፈጥሮ ልደታችን ዙሪያ ለመመርመር መሞከር ያልተቀደሰ የማወቅ ጕጕት የሚሆንባቸው ምሥጢሮች አሉ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱሳት ሥራዎች ደግሞ ይልቁን እንዲሁ ናቸው። «ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።» ይህን ያህል ግን እናውቃለን፤ የመንፈስ ቅዱስ ምሥጢራዊ ሥራ ያው መንፈስ በሚመሰክርለት በኢየሱስ ላለማመን ምክንያት ሊሆን አይችልም።

አንድ ሰው እርሻ እንዲዘራ ቢታዘዝ፣ እግዚአብሔር ዘሩን ካላበቀለው መዝራት ከንቱ ነው በማለት ቸልተኝነቱን ሊያመካኝ አይችልም። መከርን ሊፈጥር የሚችለው የእግዚአብሔር ስውር ኃይል ብቻ ስለ ሆነ ማረስን ቸል ቢል ትክክል ሊሆን አይችልም። እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ እንደሚደክሙ በማወቁ በተራው የሕይወት ሥራው የሚከለከል ማንም የለም። በኢየሱስ የሚያምን ሰው መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ውስጥ ለመሥራት እምቢ እንዳለ ከቶ እንደማያገኝ እርግጠኛ ነው፤ በእርግጥም ማመኑ መንፈስ ቅዱስ በልቡ ውስጥ አስቀድሞ እየሠራ እንዳለ ማስረጃ ነው።

እግዚአብሔር በመግቦቱ ይሠራል፤ ሰዎች ግን ስለዚህ ዝም ብለው አይቀመጡም። መለኮታዊው ኃይል ሕይወትንና ብርታትን ካልሰጣቸው መንቀሳቀስ አይችሉም፤ ሆኖም ያለ ጥያቄ መንገዳቸውን ይቀጥላሉ፤ ኃይሉም እስትንፋሳቸው በእጁ ባለው፣ መንገዳቸውም ሁሉ የእርሱ በሆነው ከቀን ወደ ቀን ይሰጣቸዋል። በጸጋም እንዲሁ ነው። ጌታ ባያስችለን ሁለቱንም ማድረግ ባንችልም ንስሐ እንገባለን፤ እናምናለንም። ኃጢአትን እንተዋለን፤ በኢየሱስም እንታመናለን፤ ከዚያም ጌታ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእኛ እንደ ሠራ እናስተውላለን። በዚህ ጉዳይ ውስጥ እውነተኛ ችግር እንዳለ ማስመሰል ከንቱ ነው።

በቃላት ለማብራራት አስቸጋሪ የሆኑ አንዳንድ እውነቶች በተግባር ተሞክሮ እጅግ ቀላል ናቸው። ኃጢአተኛው ያምናል በሚለውና እምነቱ በመንፈስ ቅዱስ በእርሱ ውስጥ ይሠራል በሚለው እውነት መካከል ምንም ተቃርኖ የለም። ነፍሳቸው በአደጋ ላይ ሳለች ሰዎች በግልጥ ነገሮች ራሳቸውን እንዲያደናግሩ የሚመራቸው ሞኝነት ብቻ ነው። ነገሮች በውኃ ላይ የሚንሳፈፉበትን የክብደት ሕግ ስለማያውቅ ብቻ ወደ ነፍስ አድን ጀልባ ለመግባት እምቢ የሚል ሰው የለም፤ በረሀብ የሚሞት ሰውም የምግብን አፈጫጨት ሂደት ሁሉ እስኪያስተውል ድረስ ለመብላት እምቢ አይልም። ውድ አንባቢ ሆይ፣ ምሥጢርን ሁሉ እስክታስተውል ድረስ የማታምን ከሆነ ከቶ አትድንም፤ በራስህ የፈጠርካቸው ችግሮች በጌታህና በአዳኝህ በኩል ይቅርታን ከመቀበል እንዲከለክሉህ ብትፈቅድ፣ ፈጽሞ በሚገባህ ፍርድ ትጠፋለህ። ስለ ረቂቅ የፍልስፍና ጥያቄዎች ለመከራከር ባለህ ፍቅር ምክንያት መንፈሳዊ ራስን ማጥፋት አትፈጽም።

ምዕራፍ 13 ተጠናቋል

ዳግመኛ መወለድና መንፈስ ቅዱስ

ገጽ 1 / 1 · 3 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ