ምዕራፍ 2 · 19 ደቂቃ ንባብ · 25 ደቂቃ ማዳመጥ
መቅድም
ይህን መጽሐፍ ለሚያነብቡ ላልተቀደሱ ሰዎች ሁሉ፤ በተለይም በኪደርሚንስተር ከተማና ደብር ለሚገኙ አድማጮቼ።
ወንድሞች ሆይ፣
ለዘላለም ሕይወት የፈጠራችሁ፣ ያን ሕይወትና ራሳችሁንም ባጣችሁ ጊዜ በአንድያ ልጁ የዋጃችሁ ዘላለማዊው አምላክ በኃጢአታችሁና በጕስቍልናችሁ ውስጥ ሳላችሁ አስቦአችሁ ወንጌልን አጻፈ፤ በመንፈሱም አተመው፤ ለዓለምም እንዲሰብኩት አገልጋዮቹን አዘዘ። ይህንም ያደረገው ይቅርታ በነጻ ቀርቦላችሁ፣ መንግሥተ ሰማያትም በፊታችሁ ተዘርግቶላችሁ ከሥጋዊ ተድላችሁና ይህን አታላይ ዓለም ከመከተል ይጠራችሁ ዘንድ፣ ሞታችሁ ከመድኃኒት ከማለፋችሁም በፊት ከተፈጠራችሁለትና ከተዋጃችሁለት ሕይወት ጋር ያስተዋውቃችሁ ዘንድ ነው። መልእክታቸውን በቀጥታ መገለጥ የሚቀበሉ ነቢያትን ወይም ሐዋርያትን አይልክላችሁም፤ ይሁን እንጂ ክርስቶስና ሐዋርያቱ መጀመሪያ ያስተላለፉትን ያንኑ ወንጌል እንዲሰብኩ ከእርሱ ሥልጣን በተቀበሉ በተራ አገልጋዮቹ በኩል ይጠራችኋል። ልታደርጉት ወይም ልትቀበሉት ያለባችሁን እንደማያስተውሉ ሰዎች ሆናችሁ እርሱንና ፍጻሜአችሁን እንዴት እንደምትረሱ፣ ዘላለማዊ ነገሮችንም ምን ያህል እንደምታቃልሉ ጌታ ያያል። በኃጢአት ምን ያህል ደፋሮች እንደ ሆናችሁ፣ ማስጠንቀቂያዎቹን ምን ያህል እንደማትፈሩ፣ ስለ ነፍሳችሁም ምን ያህል ግድ የለሾች እንደ ሆናችሁ፣ የክርስቲያኖች እምነት በአፋችሁ ሳለ የማያምኑ ሰዎች ሥራ በሕይወታችሁ እንዳለ ያያል። ኀዘናችሁ የሚጀምርበት፣ ይህንንም ሁሉ በሥቃይና በተስፋ መቍረጥ ውስጥ ፍሬ በሌለው ጩኸት የምታለቅሱበት አስፈሪው ቀን እንደ ቀረበ ያያል፤ እውነተኛ መለወጥ አሁን ካልቀደመው በዚያን ጊዜ የሞኝነታችሁ ትዝታ ልባችሁን ይሰነጣጥቃል። ሁኔታችሁን እናንተ ልታውቁት ከምትችሉት በላይ የሚያውቀው ጌታ ለኃጢአተኛና ለጐስቋላ ነፍሳችሁ በመራራት በስሙ እንድንናገራችሁ ግዴታ አደረገብን (2ኛ ቆሮንቶስ 5:19)፤ ኃጢአታችሁንና ጕስቍልናችሁን፣ ፍጻሜአችሁ ምን እንደሚሆን፣ ጥቂት ጊዜ እንኳ በዚሁ ብትቀጥሉ በቅርቡ ምን ያህል የሚያሳዝን ለውጥ እንደምታዩ በግልጥ እንድንነግራችሁ አዘዘን። በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በዚያ ውድ ዋጋ ገዝቶአችሁ፣ የይቅርታን፣ የጸጋንና የዘላለም ክብርን ነጻና ለሁሉ የሆነ የተስፋ ቃል ከሰጣችሁ በኋላ፣ ይህን ሁሉ የእግዚአብሔር ስጦታ አድርገን እንድናቀርብላችሁ፣ የሚያቀርብላችሁንም ነገር አስፈላጊነትና ዋጋ እንድታስቡበት እንድንለምናችሁ ያዝዘናል። — በዓለማዊ ጭንቀትና ተድላ ሰጥማችሁ፣ የልጅ መጫወቻዎችን በጕጕት እየተከተላችሁ፣ ለዘላለም ሕይወት ልትዘጋጁበት የሚገባውን ያንን አጭርና ውድ ጊዜ ለከንቱ ነገር ስታባክኑ ያያችኋል፤ ይራራላችሁማል፤ ስለዚህም ከኋላችሁ እንድንጣራ፣ ድካማችሁን እንዴት በከንቱ እንደምታጠፉ፣ ነፍሳችሁንም ልታጡ እንደ ተቃረባችሁ እንድንነግራችሁ፣ ጥሪውንም ብትሰሙ በእርግጥ ልታገኙት የምትችሉትን የሚበልጥና የሚሻል ነገር እንድናሳያችሁ አዘዘን (ኢሳይያስ 55:1-3)። እኛም የእግዚአብሔርን ድምፅ እናምናለን፤ እንታዘዘዋለንም፤ እንድንሰብክ፣ በጊዜውም አለጊዜውም ከእናንተ ጋር እንድንጸና፣ ድምፃችንንም እንደ መለከት አንሥተን መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን እንድንነግራችሁ ባዘዘን በእርሱ መልእክት ወደ እናንተ እንመጣለን (ኢሳይያስ 58:1፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 4:1-2)። ነገር ግን ወዮ! ለነፍሳችን ኀዘንና ለእናንተው ጥፋት ጆሮአችሁን ትደፍናላችሁ፤ አንገታችሁን ታደነድናላችሁ፤ ልባችሁን ታጸናላችሁ፤ መልእክቱን እንዳደረስን፣ ነገር ግን በእናንተ ላይ አንዳች መልካም ነገር ልናደርግ፣ ረጋ ያለ ጆሮ እንኳ ልናገኝ እንዳልቻልን እንድንነግረው በመቃተት ወደ እግዚአብሔር ትመልሱናላችሁ። — ወይኔ! ክርስቶስ፣ ይቅርታ፣ ሕይወትና መንግሥተ ሰማያት በፊታቸው ቀርበው ሳሉ እነርሱን ለማወቅም ሆነ ለማክበር ልብ የሌላቸውን ያልተማሩና ግድ የለሽ ሕዝቦቻችንን እናለቅስላቸው ዘንድ ዓይኖቻችን የእንባ ምንጭ ቢሆኑ! ሆን ብለው በሚያደርጉት ቸልተኝነትና ንቀት ባይሆን ኖሮ እንደ ሌሎች ሁሉ ክርስቶስን፣ ጸጋንና ክብርን ሊያገኙ በቻሉ ነበር! ኦ፣ ጌታ ለእነዚህ ጐስቋላ ነፍሳት የበለጠ ርኅራኄ ልባችንን ቢሞላው! ያን ጊዜ በእግራቸው ሥር እንኳ ራሳችንን እንጥል፣ እስከ ቤታቸውም እንከተላቸው፣ በመራራ እንባችንም እንናገራቸው ነበር፤ ለብዙዎቹ ለረጅም ጊዜ በከንቱ ሰብከናልና። እንዲያስተውሉ ግልጽ ለመሆን እንጥራለን፤ ብዙዎቹ ግን ሊያስተውሉን አይወዱም፤ እንዲሰማቸው ብርቱና ልብ የሚወጉ ቃላትን እንመርጣለን፤ እነርሱ ግን ሊሰማቸው አይወዱም። ታላላቅ ጉዳዮች ቢሠሩባቸው ኖሮ በቀሰቀስናቸው ነበር፤ ጣፋጭ ነገሮች ቢሠሩባቸው ኖሮ በሳብናቸውና ልባቸውን በማረክነው ነበር፤ እጅግ አስፈሪ ነገሮች ቢሠሩባቸው ኖሮ ቢያንስ ከክፋታቸው አስደንግጠን በመለስናቸው ነበር፤ እውነትና እርግጠኝነት ቢይዟቸው ኖሮ ፈጥነን ባሳመንናቸው ነበር፤ የፈጠራቸው አምላክና የገዛቸው ክርስቶስ ቢሰሙ ኖሮ ነገራቸው ፈጥኖ በተለወጠ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ቢሰማ ኖሮ ፈጥነን ባሸነፍን ነበር፤ አእምሮ፣ ያውም ከሁሉ የተሻለውና የጸናው አእምሮ ቢሰማ ኖሮ ፈጥነን እንደምናሳምናቸው ባልተጠራጠርን ነበር፤ ተሞክሮ፣ ያውም የራሳቸው ተሞክሮና የዓለም ሁሉ ተሞክሮ ቢሰማ ኖሮ ነገሩ በተስተካከለ ነበር፤ አዎን፣ በውስጣቸው ያለው ሕሊና ቢሰማ ኖሮ ሁኔታቸው አሁን ካለው በተሻለ ነበር። ነገር ግን ምንም ነገር የማይሰማ ከሆነ፣ ታዲያ ምን እናድርግላቸው? አስፈሪው የሰማይ አምላክ የሚናቅ ከሆነ፣ ታዲያ ማን ይከበራል? ሊገመት የማይችለው የቤዛ ፍቅርና ደም የሚቃለል ከሆነ፣ ታዲያ ምን ዋጋ ይሰጠዋል? መንግሥተ ሰማያት በእነርሱ ዘንድ የሚያስመኝ ክብር ከሌለው፣ የዘላለም ደስታም ምንም ዋጋ ከሌለው፣ በሲኦል ላይ ቢቀልዱ፣ በጥልቁ ዙሪያ ቢጨፍሩ፣ በሚበላውም እሳት ቢጫወቱ፣ ያውም እግዚአብሔርና ሰው ስለ እርሱ እያስጠነቀቋቸው ይህን ቢያደርጉ፣ እንደነዚህ ላሉ ነፍሳት ምን እናድርግላቸው?
እንደ ገና በሰማይ አምላክ ስም ያዘዘንን መልእክት አደርስላችኋለሁ፤ ሊለውጣችሁ ወይም ሊኰንናችሁ፣ ሊያድሳችሁ ወይም በፍርድ በእናንተ ላይ ሊነሣ፣ አንድ ጊዜ ትመለሱ ዘንድ ከልብ የሆነ ጥሪ እንደ ደረሳችሁ በፊታችሁ ምስክር ሊሆን በእነዚህ በጸኑ መስመሮች ውስጥ እተወዋለሁ። እናንተ የዓለም ባሪያዎች፣ የሥጋና የሰይጣን አገልጋዮች ሁሉ ስሙ! ዘመናችሁን በምድር ላይ ብልጽግናን በመፈለግ የምታሳልፉ፣ ሕሊናችሁን በመጠጥ፣ በሆዳምነት፣ በሥራ ፈትነትና በከንቱ ጨዋታ የምታሰጥሙ፣ ኃጢአታችሁን እያወቃችሁ እግዚአብሔርን እንደምትገዳደሩና የቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ፣ እንዳይራራም እንደምትጋብዙት ሆናችሁ አሁንም ኃጢአት ለመሥራት የቈረጣችሁ ሁሉ ስሙ! እግዚአብሔርን የማታስቡ፣ ለቅዱሳት ነገሮች ልብ የሌላችሁ፣ በጌታ ቃል ወይም አምልኮ፣ የዘላለምን ሕይወት በማሰብም ሆነ በመጥቀስ አንዳች ጣዕም የማይሰማችሁ፣ ስለማትሞተው ነፍሳችሁ ግድ የሌላችሁ፣ ነፍሳችሁ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች — የተቀደሰች ወይም ያልተቀደሰች መሆንዋን፣ በጌታ ፊትስ ለመቅረብ የተዘጋጃችሁ መሆናችሁን — ለመመርመር አንዲት ሰዓት እንኳ የማትሰጡ ሁሉ አድምጡ! በብርሃን ውስጥ ኃጢአት በመሥራት ራሳችሁን ወደ አለማመን ያደነዘዛችሁ፣ የእግዚአብሔርንም ቃል የማታምኑ ሁሉ አድምጡ። የሚሰማ ጆሮ ያለው የእግዚአብሔርን ቸርና ደግሞም የሚያስፈራ ጥሪ ይስማ! ዓይኑ በዚህ ሁሉ ጊዜ በእናንተ ላይ ነው። ኃጢአታችሁ ተመዝግቧል፤ ደግሞም በእርግጥ ትሰሙታላችሁ። መዝገቡን አሁን እግዚአብሔር ይዞታል፤ በኋላ ግን ሁሉንም በሽብሩ በሕሊናችሁ ላይ ይጽፈዋል፤ ያን ጊዜም እናንተ ራሳችሁ ደግሞ ትይዙታላችሁ። ኃጢአተኞች ሆይ፣ ምን እያደረጋችሁ እንዳለ ብታውቁ! በዚህ ሁሉ ጊዜ የምታስቀይሙት ማንን እንደ ሆነ ብታውቁ! በየዕለቱ በምትደፍሩትና በግድ የለሽነት በምታስቈጡት በዚያ ግርማ ፊት ፀሐይ እንኳ ጨለማ ነው። ኃጢአት የሠሩ መላእክት በፊቱ መቆም አልቻሉም፤ ነገር ግን ከአጋንንት ጋር እንዲሠቃዩ ወደ ታች ተጣሉ። ታዲያ እንደ እናንተ ያሉ ምስኪን ትሎች እንዲህ በግድ የለሽነት ሊያስቀይሙትና በፈጣሪያቸው ላይ ሊነሡ ይደፍራሉን? ኦ፣ ሕያው እግዚአብሔርን በራሷ ላይ ያስነሣች ያቺ ምስኪን ነፍስ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች ጥቂት እንኳ ብታውቁ! የፈጠረህ የአፉ ቃል ሊያጠፋህ ይችላል፤ የፊቱ መኰሳተር ይቈርጥሃል፤ በውጭ ወዳለው ጨለማም ይጥልሃል። የፈተኑህ አጋንንት በአንተ ላይ ሥራቸውን ለመጀመር እንዴት ይጓጓሉ! ወስደው እንደ ገዛ ንብረታቸው ሊጠቀሙብህ ከእግዚአብሔር ቃል ብቻ ይጠብቃሉ፤ ያን ጊዜም በቅጽበት በሲኦል ትሆናለህ። እግዚአብሔር ከተቃወመህ ሁሉም ነገር ይቃወምሃል፤ ይህ ዓለም ምንም ያህል ብትወደው እስር ቤትህ ብቻ ነው፤ በእርሱም ውስጥ የተጠበቅኸው ለቍጣ ቀን ብቻ ነው (ኢዮብ 21:30)። ፈራጁ እየመጣ ነው፤ ነፍስህም እየሄደች ነው። ገና ጥቂት ጊዜ ነው፤ ወዳጅህም ስለ አንተ፦ «ሞተ» ይላል፤ አንተም አሁን የምትንቃቸውን ነገሮች ታያለህ፤ አሁን የማታምነውንም ይሰማሃል። ሞት ልትመልስለት የማትችለውን ማስረጃ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር ቃልና መንገድ ላይ የምታነሣውን ክርክር፣ በራስህም የተመካህባቸውን ቅዠቶችህን ሁሉ በብቃት የሚያፈርስ ማስረጃ ነው። ያን ጊዜስ አሳብህ እንዴት ፈጥኖ ይለወጣል? ከቻልህ ያን ጊዜ የማታምን ሁን፤ በቅዱስና በሰማያዊ ሕይወት ላይ ትናገረው በነበረው የቀድሞ ቃልህ ሁሉ ያን ጊዜ ጸንተህ ቁም። በአስተማሪዎችህና እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰዎች ላይ ትሟገትለት የነበረውን ያንን ክርክር ያን ጊዜ በጌታ ፊት አጽናው። ስለ ቅዱሳን ትጋት የነበረህን የቀድሞ አስተያየትህንና የንቀት አሳብህን ያን ጊዜ አጽና፤ አሁን ጠንካራ ምክንያቶችህን አዘጋጅ፤ ያን ጊዜም በፈራጁ ፊት ቆመህ ስለ ሥጋዊ፣ ስለ ዓለማዊና እግዚአብሔርን ስለማይፈራ ሕይወትህ እንደ ወንድ ተሟገት። ነገር ግን በአንተ የማይደፈር፣ እንደ እኛ እንደ ባልንጀሮችህ ፍጥረታትም በቀላሉ የማይመለስ ከአንዱ ጋር እንደምትሟገት እወቅ። ምስኪን ነፍስ ሆይ! ፈጥኖ ዝም በሚያሰኝህ፣ ድምፅህን በሚለውጠውና ሌላ አሳብ በሚያሳድርብህ በዚያ አስደናቂ ትዕይንትና በአንተ መካከል ያለው ቀጭን የሥጋ መጋረጃ ብቻ ነው! ሞት ይህን መጋረጃ እንደ ገለጠ ወዲያው ፈጥኖ አፍህን የሚያስይዝህን ነገር ታያለህ። ያቺ ቀንና ያቺ ሰዓትስ እንዴት ፈጥና ትመጣለች! ጥቂት ተጨማሪ የደስታ ሰዓታት፣ ጥቂት ተጨማሪ ጣፋጭ መጠጦችና ጕርሻዎች፣ ጥቂት ተጨማሪ የዓለም ክብርና ሀብት ካገኘህ በኋላ ድርሻህ ያልቃል፤ ተድላህም ይፈጸማል፤ ልብህን ያኖርህበት ሁሉ ያን ጊዜ ያልፋል፤ አዳኝህንና መዳንህን ከሸጥህለት ሁሉ ከከባድ ሒሳብ በቀር ምንም አይቀርም። ሰዎች ሊይዙት በፈረስ እየገሠገሡ ሲመጡ የሰረቀውን ገንዘብ በመጠጥ ቤት ተቀምጦ በደስታ እንደሚያባክን ሌባ፣ እናንተም እንዲሁ ናችሁ። በጭንቀት ወይም በሥጋዊ ተድላ ሰጥማችሁ፣ በገዛ ኀፍረታችሁ እየተደሰታችሁ ሳላችሁ፣ ሞት ሊይዛችሁ፣ ነፍሳችሁንም አሁን እምብዛም ወደማታውቁትና ወደማታስቡት ስፍራና ሁኔታ ሊወስዳት እየገሠገሠ ይመጣል። በኃጢአታችሁ ደፋሮችና ተጠምዳችሁ ሳላችሁ ሊይዛችሁና ሕይወታችሁን ሊያጠፋ አንድ መልእክተኛ ከለንደን በፍጥነት እየመጣ ነው እንበል፤ ባታዩትም እንኳ እየመጣ መሆኑን ብታውቁ ደስታችሁን ያበላሽባችሁ ነበር፤ የሚገሠግሠውንም እያሰባችሁ በራችሁን መቼ እንደሚያንኳኳ ታዳምጡ ነበር። ኦ፣ ሞት ገና ባይደርስባችሁም ምን ያህል እየገሠገሠ እንደ ሆነ ብታዩ! እንደ እርሱ የሚፈጥን መልእክተኛ የለም! ከእርሱ የበለጠ የማይቀር መልእክተኛም የለም! ፀሐይ በሌሊት የሚሄደው ብዙ ሺህና መቶ ሺህ ማይል ቢኖረውም በማለዳ በእርግጥ ከእናንተ ጋር እንደሚሆን፣ እንዲሁ ሞትም በእርግጥ ፈጥኖ ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ያን ጊዜ ጨዋታችሁና ተድላችሁ የት አለ? ያን ጊዜ ትቀልዳላችሁን? በድፍረትስ ትቋቋሙታላችሁን? ያን ጊዜ ያስጠነቀቋችሁን ታፌዙባቸዋላችሁን? ያን ጊዜ የሚያምን ቅዱስ መሆን ይሻላል ወይስ ሥጋዊ የዓለም ሰው? የሰበሰባችሁትን ነገር በተመለከተም ያን ጊዜ፦ «ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል?» (ሉቃስ 12:19-21)። ቀናትና ሳምንታት ፈጥነው እንደሚያልፉ፣ ሌሊቶችና ማለዳዎች በፍጥነት እንደሚመጡና እርስ በርሳቸው በችኰላ እንደሚተካኩ አታስተውሉምን? እናንተ ትተኛላችሁ፤ «ጥፋታችሁ ግን አያንቀላፋም»፤ እናንተ ትዘገያላችሁ፤ «ፍርዳችሁ ግን ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም» (2ኛ ጴጥሮስ 2:3-5)፤ ለዚህም «ለቅጣት ተጠብቃችኋል» (2ኛ ጴጥሮስ 2:8-9)። — ኦ፣ ጠቢባን ሆናችሁ ይህን ብታስተውሉ፥ ፍጻሜአችሁንም ብታስቡ! (ዘዳግም 32:29) — «የሚሰማ ጆሮ ያለው በዚህ በመዳኑ ቀን የእግዚአብሔርን ጥሪ ይስማ።»
ግድ የለሽ ኃጢአተኞች ሆይ! ውለታ ቢስ ሆናችሁ ቸል የምትሉትን ፍቅር፣ የምትንቁትንም የክርስቶስን ደም ክቡርነት ብታውቁ! ኦ፣ የወንጌልን ባለጠግነት ብታውቁ! ኦ፣ አሁን ልባችሁን ልታኖሩበት የማትወዱትን፣ አስቀድማችሁና በትጋት እንድትፈልጉትም የማትታመኑለትን የዚያን የዘላለም ሕይወት እርግጠኝነት፣ ክብርና ብፅዕና ብታውቁ፣ ጥቂት እንኳ ብታውቁ! (ዕብራውያን 11:6፤ 12:28፤ ማቴዎስ 6:12)። አሁን ቸል የምትሉትን ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ማብቂያ የሌለውን ሕይወት ብታውቁ፣ ኃጢአታችሁን እንዴት ፈጥናችሁ በጣላችሁ! አሳባችሁንና ሕይወታችሁን፣ አካሄዳችሁንና ባልንጀሮቻችሁን እንዴት ፈጥናችሁ በለወጣችሁ! የፍቅራችሁንም ፈሳሽ አቅጣጫ በመለሳችሁ፣ ጥንቃቄአችሁንም ወደ ሌላ መንገድ ባዞራችሁ! አሁን የሚያታልሏችሁንና የሚወስዷችሁን ፈተናዎች ለመቀበል እንዴት በቈራጥነት በናቃችሁ! ለዚያ እጅግ ለተባረከ ሕይወት እንዴት በቅንዓት በተጋችሁ! በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት አጥብቃችሁ በታገላችሁ! በመስማት፣ በመማርና በመጠየቅ እንዴት በተጋችሁ! — የእግዚአብሔርን ሕግ በማሰላሰል እንዴት በጸናችሁ! (መዝሙር 1:2)። በአሳብ፣ በቃል ወይም በሥራ ኃጢአት ከመሥራት እንዴት በፈራችሁ፤ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘትና በቅድስና ለማደግ እንዴት በተጠነቀቃችሁ! — ኦ፣ እንዴት ያለ የተለወጠ ሕዝብ በሆናችሁ ነበር! ታዲያ እነዚህን ክቡራንና ዘላለማውያን ነገሮች የሚገልጥላችሁ እርግጠኛው የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ዘንድ ለምን አይታመንም? ለምንስ አያሸንፋችሁም?
አዎን፣ እዚህ በምድር እንኳ የምትጠሉትን ሕይወትና የምትመርጡትን ሕይወት ልዩነት እምብዛም እንደማታውቁ ልንገራችሁ። እናንተ እርሱን ለማሰብ እንኳ በማትደፍሩበትና ከምድርና ከሥጋ ጋር ብቻ በምትኖሩበት ጊዜ የተቀደሱት ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገራሉ። — እናንተ ለሰማይ ፈጽሞ እንግዶች ሆናችሁ፣ ሆዳችሁ አምላካችሁ ሆኖ፣ አሳባችሁም ምድራዊ ሆኖ ሳለ የእነርሱ አገር በሰማይ ነው (ፊልጵስዩስ 3:18-20)። እናንተ ከዚህ ዓለም የሚበልጥ ነገር በማትፈልጉበት ጊዜ እነርሱ የእግዚአብሔርን ፊት ይፈልጋሉ። — እናንተ በጥላና በሚያልፍ ከንቱ ነገር ተይዛችሁ ሳላችሁ፣ እነርሱ እንደ መላእክት ለሚሆኑበት ማብቂያ ለሌለው ሕይወት በትጋት ይዘጋጃሉ (ሉቃስ 20:36)። ምድራዊ፣ ሥጋዊና ኃጢአተኛ ሕይወታችሁ ከእውነተኛ አማኞች ክቡርና መንፈሳዊ ሕይወት ጋር ሲነጻጸር እንዴት የተናቀና ዝቅተኛ ነው! እንደነዚህ ያሉት ሰዎች የሚያስቡት ከፍ ያለ ነገር እንደሌላቸው ሆነው ጥቂት ምግብና ልብስ፣ ወይም ጥቂት ጠፊ ገንዘብ፣ ወይም ሥጋዊ ተድላ፣ ወይም ባዶ ክብር ብቻ ለማግኘት በዓለም ላይ ሲንከራተቱ፣ ሕይወታቸውንና ጥንቃቄአቸውን ድካማቸውንም ሲያባክኑ ሳይ ብዙ ጊዜ በኀዘንና በርኅራኄ ተመልክቻቸዋለሁ። — በእነዚህ ሰዎች ሕይወትና እየሠሩ፣ እየበሉና እየኖሩ ጊዜአቸውን በሚያሳልፉት፣ ይህንንም የሚያደርጉት በሕይወት ለመቆየት ብቻ በሆነ በሚጠፉ እንስሶች ሕይወት መካከል ምን ልዩነት አለ? አማኞች የሚቀምሱትንና በእርሱ የሚኖሩበትን ውስጣዊ ሰማያዊ ደስታ አይቀምሱም። — የእነርሱን ንቀትና መከራ ሁሉ አብሬ ብቀበልም፣ የሰማያዊ ርስታቸው ቅድመ አሳብ የሚሰጣቸውን መጽናናት ጥቂቱን ማግኘት የእናንተን ተድላና አታላይ ብልጽግና ሁሉ ከማግኘት ይሻለኛል። ዓለም እስከ ዛሬ ያደረገላችሁን ሁሉ፣ ወይም ያደርግላችኋል ብላችሁ በምክንያት ልትጠብቁት የምትችሉትን ሁሉ ብሰጥ እንኳ ከስውሩ የሕሊና ጭንቀታችሁና ምጣችሁ፣ ስለ ሞትና ስለሚመጣው ሕይወት ካለባችሁ የጨለማና የሚያስፈራ አሳብ አንዱን እንኳ እንዲኖረኝ አልፈልግም። እኔ ባልተለወጠው ሥጋዊ ሁኔታችሁ ብሆን፣ ነገር ግን የማውቀውን ባውቅና አሁን የማምነውን ባምን፣ ሕይወቴ የሲኦል ቅድመ ቅምሻ የሚሆን ይመስለኛል፤ ስለ ጌታ ሽብር፣ እየፈጠነ ስለሚመጣውም ስለዚያ አስጨናቂ ቀን ምን ያህል ደጋግሜ ባሰብሁ ነበር! በእርግጥ ሞትና ሲኦል ዘወትር በፊቴ ይሆኑ ነበር። በቀን አስባቸው፣ በሌሊትም አልማቸው ነበር፤ ሳልለወጥ ሞት እንዳይመጣ በፍርሃት እተኛ፣ በፍርሃት እነሣ፣ በፍርሃትም እኖር ነበር። በእግዚአብሔር እርግማንና ቍጣ ሥር መሆኔን እስካወቅሁ ድረስ ባለኝ ነገር ሁሉ ደስታዬ ጥቂት፣ በማንኛውም ባልንጀርነት ተድላዬ ጥቂት፣ በዓለም ባለ ነገር ሁሉ ሐሴቴ ጥቂት ይሆን ነበር። ያንን፦ «አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል» የሚለውን ድምፅ ከመስማት ዘወትር እፈራ ነበር (ሉቃስ 12:20)። ያም የሚያስፈራ ፍርድ፦ «ለክፉዎች ሰላም የላቸውም፥ ይላል አምላኬ» የሚለው በሕሊናዬ ላይ ተጽፎ ይኖር ነበር (ኢሳይያስ 48:22፤ 57:21)። — ምስኪን ኃጢአተኞች ሆይ! ክርስቶስን ለመስማትና ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤት ለመመለስ በእውነት ፈቃደኞች ብትሆኑ፣ ከዚህ የበለጠ ደስታ ያለበትን ሕይወት ልትኖሩ ትችሉ ነበር። ያን ጊዜ በድፍረት ወደ እግዚአብሔር ልትቀርቡ፣ አባታችሁ ብላችሁ ልትጠሩት፣ ነፍሳችሁንና ሥጋችሁንም በመጽናናት በአደራ ልትሰጡት ትችሉ ነበር። የተስፋ ቃሎችን ብትመለከቱ ሁሉም የእኔ ናቸው ልትሉ ትችላላችሁ፤ እርግማኑን ብትመለከቱ ከዚህ ዳንሁ! ልትሉ ትችላላችሁ። ሕጉን ስታነብቡ ከምን እንደ ዳናችሁ ታያላችሁ! — ወንጌልን ስታነብቡ የዋጃችሁን ታዩታላችሁ፤ የፍቅሩን፣ የቅዱስ ሕይወቱንና የመከራውን ሂደት ታያላችሁ፤ ለመዳናችሁ በሠራው ሥራ በፈተናዎቹ፣ በእንባውና በደሙ ትከተሉታላችሁ። ሞት ድል ተነሥቶ፣ መንግሥተ ሰማያት ተከፍቶ፣ የእናንተም ትንሣኤና ክብር በጌታችሁ ትንሣኤና ክብር ተዘጋጅቶላችሁ ታያላችሁ። ቅዱሳንን ብትመለከቱ፦ «ወንድሞቼና ባልንጀሮቼ ናቸው» ልትሉ ትችላላችሁ። ያልተቀደሱትን ብትመለከቱ ከዚያ ሁኔታ እንደ ዳናችሁ በማሰብ ደስ ሊላችሁ ይችላል። ሰማያትን፣ ፀሐይንና ጨረቃን፣ ቍጥር የሌላቸውንም ከዋክብት ብትመለከቱ እንዲህ ብላችሁ ልታስቡና ልትናገሩ ትችላላችሁ፦ «የአባቴ ፊት ከዚህ እጅግ በማይወሰን መጠን የከበረ ነው፤ ለቅዱሳኑ ያዘጋጀው ከዚህ የሚበልጥ ነው፤ ያ የምናየው የሰማይ የውጭ አደባባይ ብቻ ነው፤ ተስፋ የሰጠን ብፅዕና ሥጋና ደም ሊያዩት እስከማይችሉ ድረስ እጅግ ከፍ ያለ ነው።» መቃብርን ብታስቡ፣ የከበረው መንፈስ፣ ሕያው ራስና አፍቃሪ አባት ከትቢያችሁ ጋር እጅግ የቀረበ ግንኙነት ስላላቸው ትቢያችሁ ሊረሳ ወይም ቸል ሊባል እንደማይችል፣ ይልቁንም በፀደይ ወራት ከሚያቈጠቍጡ ተክሎችና አበቦች ይልቅ በእርግጠኝነት ሕያው እንደሚሆን ልታስታውሱ ትችላላችሁ፤ የሥጋ ሥር የሆነችው ነፍስ አሁንም ሕያው ናትና፤ የሁለቱም ሥር የሆነው ክርስቶስም ሕያው ነውና። — የፍርሃቶች ሁሉ ንጉሥ የሆነው ሞት እንኳ፣ ከኃጢአትና ከኀዘን ቅሬታ የምትድኑበት ቀን በመሆኑ፣ ያመናችሁበትና ተስፋ ያደረጋችሁት የጠበቃችሁትም ቀን በመሆኑ በደስታ ሊታሰብና ሊቀበሉት ይችላል፤ በዚያን ቀን ስትሰሙት የነበራችሁትን የተባረኩ ነገሮች ታያላችሁ፤ መልካሙን ዕድል መምረጥና ቅን አማኝ ቅዱስ መሆን ምን ማለት እንደ ሆነ አሁን በሚገኝ አስደሳች ተሞክሮ ታውቃላችሁ። ጌታዬ ሆይ፣ ምን ትላለህ? መዳንህን አረጋግጠህ ለሞት ተዘጋጅተህ መኖር፣ ልባቸው በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ ከብዶ ያ ቀን በድንገት እንደሚመጣባቸው እንደ እግዚአብሔርን የማይፈሩት ከመኖር የበለጠ የሚያስደስት ሕይወት አይደለምን? (ሉቃስ 21:34, 36)። አንድ ጊዜ የሰማይ ወራሽ ብትሆንና ዓለምን ስትለቅ እንደምትድን እርግጠኛ ብትሆን የተጽናና ሕይወት ልትኖር አትችልም ነበርን? — እንግዲያውስ ኦ፣ ዙሪያህን ተመልከት፤ የምታደርገውን አስብ፤ እንዲህ ያለውን ተስፋ ለምንም ነገር አትጣል። ሥጋና ዓለም እንዲህ ያለ ተስፋ ወይም መጽናናት ሊሰጡህ አይችሉም።
በራሳችሁ ላይ ከምታመጡት ጕስቍልና ሁሉ በተጨማሪ፣ ያልተለወጣችሁ እስከ ሆናችሁ ድረስ ሌሎችን የምታውኩ ናችሁ። በሕጋቸው እንዲገዟችሁ ገዦችን ታስቸግራላችሁ፤ የሚያቀርቡላችሁን ብርሃንና መመሪያ በመቃወም አገልጋዮችን ታስቸግራላችሁ። ኃጢአታችሁና ጕስቍልናችሁ በዓለም ላይ ካለው ሁሉ የሚበልጥ ኀዘንና ጭንቀት ይሆንባቸዋል። — አገሩን ታውካላችሁ፤ የእግዚአብሔርንም ፍርድ በላያችሁ ታመጣላችሁ። የአብያተ ክርስቲያናትን ቅዱስ ሰላምና ሥርዓት ከሁሉ በላይ የምታውኩ፣ አንድነታችንንና ተሐድሶአችንን የምታደናቅፉ፣ ሰተት ብላችሁ በምትገቡባቸው አብያተ ክርስቲያናትና ባላችሁባቸው ስፍራዎች ኀፍረትና ችግር የምትሆኑ እናንተ ናችሁ። — ወዮ፣ ጌታ ሆይ! ወንጌል ከዓለም ሕዝቦች ሁሉ በላይ በበዛባት፣ ትምህርት እጅግ ግልጽና የተለመደ በሆነባት፣ የምንመኘውም ርዳታ ሁሉ በእጃችን ባለባት በእንግሊዝ እንኳ፣ ሰይፍ ሲቈርጠን፣ ፍርድም እንደ እሳት በምድሪቱ ውስጥ ሲሮጥ፣ ማዳኖችም ሲያሳርፉን፣ እጅግ ብዙ አስደናቂ ምሕረቶችም ለእግዚአብሔርና ለወንጌል፣ ለቅዱስም ሕይወት ሲያስገዙን ከቆየ በኋላ፣ ከዚህ ሁሉ በኋላ ከተሞቻችን፣ መንደሮቻችንና አውራጃዎቻችን ባልተቀደሱ ሰዎች ብዛት መሞላታቸው፣ በየስፍራውም በኀዘን እንደምናየው ሥጋዊነት መትረፍረፉ እንዴት ያለ ከባድና የሚያሳዝን ነገር ነው! ከዚህ ሁሉ ብርሃን፣ ከዚህ ሁሉ ተሞክሮ፣ ከእነዚህም ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርዶችና ምሕረቶች በኋላ፣ የዚህ አገር ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ተባብሮ ወደ ጌታ ይመለሳል፣ ወደ ቅዱሱ መምህራቸውም መጥተው የቀድሞ ኃጢአታቸውን ሁሉ ያለቅሳሉ፣ ኃጢአታቸውን በግልጥ ለመናዘዝና ከጌታ ይቅርታ ለመለመን በሕዝብ ፊት በሚደረግ መዋረድ ከእነርሱ ጋር እንዲተባበር ይለምኑታል፣ ለሚመጣውም ጊዜ ትምህርቱን ይሻሉ፣ በእግዚአብሔርም ቃል መሠረት በውስጥ ባለው መንፈስና በውጭ ባሉት የክርስቶስ አገልጋዮች ለመመራት ደስ ይላቸዋል ብሎ ማንም ባሰበ ነበር። የሚሰሙትን ያህል ምክንያትና የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ከሰሙ በኋላ፣ ከእነዚህም ሁሉ መንገዶችና ምሕረቶች በኋላ፣ በመካከላችን እግዚአብሔርን የማይፈራ አንድ ሰው እንኳ፣ ዓለማዊ ሰው ወይም ሰካራም፣ ተሐድሶን የሚጠላ ወይም ቅድስናን የሚቃወም በከተሞቻችንና በአውራጃዎቻችን ሁሉ አይገኝም ብሎ ማንም ባሰበ ነበር። ስለ አንዳንድ ሥርዓቶች ወይም ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዓይነቶች ሁላችንም ባንስማማ እንኳ፣ ለእግዚአብሔር፣ ለቃሉና ለአገልጋዮቹ በመታዘዝ፣ እርስ በርሳችንም በፍቅርና በሰላም ቅዱስና ሰማያዊ ሕይወት ለመኖር እስከ አሁን ሁላችን በተስማማን ነበር ብሎ ማንም ያስባል። — ነገር ግን ወዮ! ሕዝባችን ከዚህ መንገድ ምን ያህል የራቀ ነው! አብዛኞቹ በአብዛኛው ስፍራ ልባቸውን በምድራዊ ነገር ላይ ያኖራሉ፤ «አስቀድመው የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም» አይፈልጉም፤ ቅድስናን እንደማያስፈልግ ነገር ይመለከቱታል፤ ቤተሰቦቻቸው ጸሎት የለባቸውም፤ ወይም ከልብ ከሆነ፣ ከጋለና ከዕለት ዕለት ጸሎት ይልቅ ልብ የሌላቸውና ሕይወት የሌላቸው ጥቂት ቃላት ይበቃሉ [ወይም ምናልባት በጌታ ቀን ምሽት ብቻ]፤ ልጆቻቸው ክርስቶስን ማወቅና የጸጋን ኪዳን አይማሩም፤ በጥምቀታቸው ይህን ሁሉ አጥብቀው ቃል ቢገቡም በጌታ ምክርና በተግሣጽ አያሳድጓቸውም።
አገልጋዮቻቸውን በመዳን ጉዳይ አያስተምሩም፤ ሥራቸው ብቻ ይሠራ እንጂ ግድ የላቸውም። በቤተሰቦቻቸው ውስጥ ለማነጽ ከሚጠቅሙ የጸጋ ቃላት ይልቅ የስድብ ንግግር ይበዛል። ጌታን የሚፈሩ፣ እንዴት መኖርና ምን ማድረግ እንዳለባቸው ቃሉንና አገልጋዮቹን የሚጠይቁ፣ ለመማርና ለመመራት ፈቃደኞች የሆኑ፣ የዘላለምንም ሕይወት ከልብ የሚሹ ቤተሰቦች እንዴት ጥቂቶች ናቸው! እግዚአብሔር እንዲህ ያስደሰታቸው እነዚያ ጥቂቶችም ብዙ ጊዜ የጎረቤቶቻቸው መተረቻ ናቸው። አንዳንዶቹ በስካር፣ አንዳንዶቹም በትዕቢትና በዓለማዊነት ሲኖሩ፣ አብዛኞቹም ስለ መዳናቸው እምብዛም ግድ ሳይላቸው ስናይ፣ ነገሩ ግልጽና ከክርክር ሁሉ በላይ ቢሆንም፣ ስለ ጕስቍልናቸው ለማሳመን ያስቸግራሉ፤ ለመመለስና ለመታደስ ደግሞ ይበልጥ ያስቸግራሉ፤ ከኃጢአታቸው ልናድናቸው የምንችለውን ሁሉ ካደረግን በኋላም አብዛኞቹን እንዳገኘናቸው እንተዋቸዋለን። በእግዚአብሔርም ሕግ መሠረት ምክራችንን ሁሉ በእልከኝነት ከናቁ በኋላ ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት ብናወጣቸው፣ ጠላቶቻቸው እንደ ሆንን ይቈጡብናል፤ ልባቸውም በእኛ ላይ በክፋት ይሞላል፤ ከሚገድላቸው ኃጢአታቸው ይልቅ በጌታና በሕጉ፣ በቤተ ክርስቲያኑና በአገልጋዮቹ ላይ ቶሎ ይነሣሉ። የእንግሊዝ አሳዛኝ ሁኔታ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን የመምሰልን መንገድ የሚደግፉ ገዦች አሉን፤ ለአንድነትና ለተሐድሶ የሚሆን መልካም አጋጣሚ በፊታችን አለ፤ ታማኝ አገልጋዮችም የቤተ ክርስቲያንንና የእግዚአብሔርን ሥርዓቶች ትክክለኛ አደረጃጀት ለማየት ይናፍቃሉ፤ ነገር ግን በሕዝባችን ውስጥ ያለው የኃጢአት ኃይል ሁሉንም ማለት ይቻላል ያከሽፋል። ታማኝ አገልጋይ የማያጠራጥረውን የክርስቶስን ሥርዓተ ተግሣጽ ሊያቆም፣ ወይም እጅግ አሳፋሪና ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን ከቤተ ክርስቲያን ኅብረትና ከምሥጢራት ተካፋይነት ሊያግድ የሚችልበት ስፍራ ከሞላ ጎደል የለም፤ አብዛኞቹ ሰዎች ይሰድቧቸዋል፤ ያንቋሽሿቸዋልም፤ እነዚህ ያልተማሩና ግድ የለሽ ነፍሳት ከአስተማሪዎቻቸው፣ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ራሱ ይበልጥ ጠቢባን የሆኑ ይመስል። እንዲሁም በምንጐበኝበት ቀን፣ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን እንድናድስ በሚጠራን ጊዜ፣ ገዦች ፈቃደኞች ቢመስሉም፣ ታማኝ አገልጋዮችም ፈቃደኞች ቢመስሉም፣ የሕዝቡ ብዛት ግን አሁንም ፈቃደኛ አይደለም፤ ራሳቸውንም እንዲህ አሳውረው ልባቸውንም አጽንተዋል፤ በእነዚህ የብርሃንና የጸጋ ዘመናት እንኳ የብርሃንና የጸጋ እልከኛ ጠላቶች ናቸው፤ ሞኝነታቸውን እንዲያዩና የሚጠቅማቸውን እንዲያውቁ በእግዚአብሔር ጥሪዎች አይመለሱም። ኦ፣ የእንግሊዝ ሕዝብ ከዓይናቸው ሳይሰወር ለሰላማቸው የሚሆነውን በዚህ ቀናቸው እንኳ ቢያውቁ! (ሉቃስ 19:42)።
የማታስተውሉ ጐስቋሎች ነፍሳት ሆይ! (ገላትያ 3:1)። አእምሮአችሁን ለእንዲህ ያለ እብደት፣ ልባችሁንም ለእንዲህ ያለ ሙትነት አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? ለራሳችሁ እንዲህ ያላችሁ የሞት ጠላቶች ሆናችሁ፣ የእግዚአብሔር ቃልም ሆነ የሰዎች ምክር አሳባችሁን ሊለውጥ፣ እጃችሁን ሊይዝ ወይም ሊያቆማችሁ እስከማይችል ድረስ መድኃኒት ወደሌለበት እስክትደርሱ በእልከኝነት ወደ ኵነኔ ትገሠግሣላችሁ! እንግዲህ ኃጢአተኞች ሆይ! ይህ ሕይወት ለዘላለም አይቈይም፤ ይህ ትዕግሥትም ዘወትር አይጠብቃችሁም። ፈጣሪያችሁንና ቤዛችሁን ስትደፍሩ፣ ጠላቶቹን ስታገለግሉ፣ ነፍሳችሁን ስታዋርዱ፣ ዓለምን ስታውኩ፣ ቤተ ክርስቲያንን ስትበድሉ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ስትሰድቡ፣ አስተማሪዎቻችሁን ስታሳዝኑ፣ ተሐድሶን ስታደናቅፉ ይህን ሁሉ ያለ ዋጋ የምታደርጉ አይምሰላችሁ። ይህ ምን እንደሚያስከፍላችሁ ገና አታውቁም፤ ነገር ግን በጤናማ መለወጥና የእግዚአብሔርን ጥሪ ፈጥኖ በመታዘዝ የዘላለምን ሥቃይ ካልቀደማችሁት፣ ከጨካኞቹ ገዦችና ከግልጽ ተናጋሪዎቹ መጋቢዎች በተለየ መንገድ የሚይዛችሁ ጻድቁ እግዚአብሔር በእጁ በያዛችሁ ጊዜ በቅርቡ ታውቃላችሁ። ምሕረት የሚጠራበት ድምፅ ገና እያለው፣ «የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ»።
እግዚአብሔርን በማይፈሩ ሰዎች አፍ፣ በተለይም በቅርብ ዓመታት፣ በብዛት የማገኘው አንድ ተቃውሞ አለ፤ እንዲህ ይላሉ፦ «ያለ እግዚአብሔር ምንም ማድረግ አንችልም፤ እግዚአብሔር ካልሰጠን ጸጋን ልናገኝ አንችልም፤ ቢሰጠን ግን ፈጥነን እንመለሳለን፤ አስቀድሞ ካልወሰነንና ካልመለሰን ራሳችንን እንዴት ልንመልስ ወይም ልንድን እንችላለን? ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም።» እንዲህም ከበደል ነጻ እንደ ሆኑ ያስባሉ።
ይህን ቀደም ሲልም በዚህም መጽሐፍ መልሼዋለሁ፤ አሁን ግን ይህን ያህል ልናገር። — 1. ራሳችሁን መፈወስ ባትችሉም ራሳችሁን መጕዳትና መመረዝ ትችላላችሁ። ልባችሁን መቀደስ ያለበት እግዚአብሔር ነው፤ ያረከሰው ግን ማን ነው? ራሳችሁን መፈወስ ስለማትችሉ ሆን ብላችሁ መርዝ ትወስዳላችሁን? እንዲያውም ይበልጥ ልትርቁት ይገባችኋል ብዬ አስባለሁ። ኃጢአት ያበላሸውን ማደስ ካልቻላችሁ ከኃጢአት ይበልጥ ልትጠነቀቁ ይገባችኋል። — 2. ያለ እግዚአብሔር ልዩ ጸጋ ልትለወጡ ባትችሉም፣ እግዚአብሔር ጸጋውን የሚሰጠው ለዚሁ ዓላማ በወሰናቸው በቅዱሳት መንገዶቹ አጠቃቀም መሆኑን ማወቅ አለባችሁ፤ የጋራው ጸጋም ከግልጽ ኃጢአታችሁ (ከውጫዊው ድርጊት አንጻር) እንድትታቀቡና እነዚያንም መንገዶች እንድትጠቀሙ ሊያስችላችሁ ይችላል። የምትችሉትን ያህል እያደረጋችሁ እንደ ሆነ በእውነት መናገር ትችላላችሁን? በመጠጥ ቤት በር አልፎ መሄድ፣ ወይም በኃጢአት የሚያደነድናችሁን ባልንጀርነት መተው አትችሉምን? ቃሉን መስማት፣ ወደ ቤት ስትመለሱም የሰማችሁትን ማሰብ፣ ስለ ራሳችሁ ሁኔታና ስለ ዘላለማዊ ነገሮች በልባችሁ ማሰላሰል አትችሉምን? በየዕለቱ፣ ቢያንስ በጌታ ቀን፣ መልካም መጻሕፍትን ማንበብ፣ ጌታን ከሚፈሩትም ጋር መወያየት አትችሉምን? የምትችሉትን አድርገናል ማለት አትችሉም። — 3. ስለዚህ ያለ ጸጋ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ባትችሉም፣ ሆን ብላችሁ በምትሠሩት ኃጢአት ወይም በቸልተኝነታችሁ የእግዚአብሔርን ጸጋና ርዳታ ልታጡ እንደምትችሉ ማወቅ አለባችሁ። የምትችሉትን ካላደረጋችሁ፣ ከዚያ የበለጠ ልታደርጉበት የምትችሉትን ጸጋ እግዚአብሔር ቢከለክላችሁ ፍትሕ ነው። 4. ስለ እግዚአብሔር ውሳኔዎችም፣ ፍጻሜውንና መንገዱን እንደማይለያዩ፣ ይልቁንም አጣምረው እንደሚያስሩአቸው ማወቅ አለባችሁ። እግዚአብሔር ከተቀደሱት በቀር ማንንም ሊያድን፣ ካልተቀደሱትም በቀር ማንንም ሊኰንን ከቶ አልወሰነም። እግዚአብሔር እንድትድኑ ወይም እንዳትድኑ በእርግጥ እንደ ወሰነ፣ እንዲሁ በዚህ ዓመት መሬታችሁ ፍሬ ቢስ ወይም ፍሬያማ እንደምትሆን፣ በዓለም ላይም ልክ ምን ያህል ጊዜ እንደምትኖሩ በእርግጥ ይወስናል፤ ቢሆንም ማረሱንና መዝራቱን ትቶ፦ «እግዚአብሔር መሬቴ እህል እንድታፈራ ወስኖ ከሆነ ባርስም ባልዘራም ታፈራለች። እግዚአብሔር በሕይወት እንድኖር ወስኖ ከሆነ ብበላም ባልበላም እኖራለሁ፤ ካልወሰነ ግን በሕይወት የሚያቆየኝ መብላት አይደለም» የሚለውን ሰው ሞኝ እንደ ሆነ ታስባላችሁ። እንዲህ ላለው ሰው እንዴት መልስ እንደምትሰጡ ታውቃላችሁ ወይስ አታውቁም? ካወቃችሁ ለራሳችሁ እንዴት መልስ እንደምትሰጡ ታውቃላችሁ፤ ነገሩ አንድ ነውና፤ የእግዚአብሔር ውሳኔ ስለ ነፍሳችሁ እንደ ሆነ ሁሉ ስለ ሥጋችሁም የማይታጠፍ ነው። ካላወቃችሁ ግን እነዚህን ድምዳሜዎች በነፍሳችሁ ላይ ለመሞከር ከመድፈራችሁ በፊት በመጀመሪያ በሥጋችሁ ላይ ሞክሩአቸው፤ እግዚአብሔር ያለ ምግብና ልብስ በሕይወት ያቆያችሁ እንደ ሆነ፣ ያለ እርሻና ድካም እህል ይሰጣችሁ እንደ ሆነ፣ ያለ ጕዞና ያለ መጓጓዣም ወደ መንገዳችሁ መድረሻ ያደርሳችሁ እንደ ሆነ አስቀድማችሁ እዩ፤ በዚህ ከተሳካላችሁ፣ ያን ጊዜ መንገዶቹን በትጋት ሳትጠቀሙ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያደርሳችሁ እንደ ሆነ ሞክሩ፤ ተቀምጣችሁም፦ ራሳችንን መቀደስ አንችልም በሉ።
እንግዲህ ወገኖቼ ሆይ፣ ሦስት ልመናዎች ብቻ አሉኝ፤ ከዚያም ጨርሻለሁ።
አንደኛ፣ ይህን ትንሽ ጽሑፍ በጥንቃቄ እንድታነብቡት ነው፤ (በቤተሰቦቻችሁም ውስጥ የሚያስፈልጋቸው ካሉ ደጋግማችሁ እንድታነብቡላቸው፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩም አልፎ አልፎ ወደ ያልተማረው ጎረቤታቸው ሄደው ይህን ወይም በዚህ ጉዳይ ላይ የተጻፈ ሌላ መጽሐፍ ቢያነብቡላቸው ነፍሳትን ለመማረክ መሣሪያ ሊሆኑ ይችሉ ነበር)። ሰዎችን ለገዛ መዳናቸው እንዲህ ያሉ አጭር ትምህርቶችን የማንበብ ያህል ትንሽ ድካም እንኳ ልንለምናቸው ካልቻልን፣ ለራሳቸው የሚሰጡት ዋጋ ጥቂት ነው፤ በፍትሕም ይጠፋሉ።
ሁለተኛ፣ ይህን መጽሐፍ አንብባችሁ ከጨረሳችሁ በኋላ ለብቻችሁ ሄዳችሁ ያነበባችሁትን ጥቂት እንድታሰላስሉ፣ በእግዚአብሔርም ፊት እንዳላችሁ ሆናችሁ ይህ እውነት እንደ ሆነና ነፍሳችሁን በቅርብ እንደሚነካ፣ ዙሪያችሁን የምትመለከቱበትም ጊዜ እንደ ደረሰ እንድታስቡበት እለምናችኋለሁ። ደግሞም ዓይኖቻችሁን እውነትን እንዲያስተውሉ እንዲከፍት፣ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር እንዲመልስ በጕልበታችሁ ተንበርክካችሁ ጌታን እንድትለምኑት፣ ለረጅም ጊዜ ቸል ያላችሁትንም የሚያድን ጸጋ ሁሉ እንድትለምኑት፣ ልባችሁ እስኪለወጥም ድረስ ከቀን ወደ ቀን እንድትከታተሉት እለምናችኋለሁ። — ከዚህም ጋር ወደ መጋቢዎቻችሁ እንድትሄዱ (ሐኪሞች ለሥጋችሁ ጤንነት እንደሚጠነቀቁ ለነፍሳችሁ ጤንነትና ደኅንነት እንዲጠነቀቁ በላያችሁ ወደ ተሾሙት)፣ ምን መንገድ መያዝ እንዳለባችሁ እንዲመሩአችሁ እንድትጠይቋቸው፣ መንፈሳዊ ሁኔታችሁንም እንድታስታውቋቸው፣ ከምክራቸውና ከአገልግሎታቸው ርዳታ ጥቅም እንድታገኙ እለምናችኋለሁ።
ወይም በአገራችሁ ታማኝ መጋቢ ከሌላችሁ፣ በእንዲህ ያለ ታላቅ ችግር ሌላውን ተጠቀሙ።
ሦስተኛ፣ በንባብ፣ በማሰላሰል፣ በጸሎትና በአገልጋዮች ምክር አንድ ጊዜ ኃጢአታችሁንና ጕስቍልናችሁን፣ ግዴታችሁንና መድኃኒታችሁን ካወቃችሁ በኋላ አትዘግዩ፤ ይልቁንም ኃጢአተኛ ባልንጀርነታችሁንና መንገዳችሁን ወዲያውኑ ትታችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ ጥሪውንም ታዘዙ። ነፍሳችሁን የምትወዱ ከሆነ፣ በፍርድ ቀን ከሰዶምና ከገሞራ ይልቅ እንዳይከፋባችሁ፣ እንዲህ ያለውን ታላቅ የእግዚአብሔር ጥሪ፣ የገዛ እውቀታችሁንና ሕሊናችሁንም ተቃውማችሁ እንዳትቀጥሉ ተጠንቀቁ። እውነትን ለማወቅ እንደሚፈልግ ሰው እግዚአብሔርን ጠይቁ እንጂ ሆን ብላችሁ ነፍሳችሁን የምታታልሉ አትሁኑ። ነገሩ እንደዚሁ ይሆን እንደ ሆነ ዕለት ዕለት ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምሩ፤ ሰማይን ወይስ ምድርን መታመን ይበልጥ አስተማማኝ እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔርን ወይስ ሰውን፣ መንፈስን ወይስ ሥጋን መከተል ይሻል እንደ ሆነ፣ በቅድስና ወይስ በኃጢአት መኖር ይሻል እንደ ሆነ፣ ያልተቀደሰ ሁኔታስ ለአንድ ቀን እንኳ ለመኖር አስተማማኝ እንደ ሆነ ሳታደሉ ፈትኑ፤ የሚሻለውንም ካገኛችሁ በኋላ በዚያው ቍረጡ፤ ያለ ምንም ተጨማሪ ማመንታትም ምርጫችሁን አድርጉ። ለገዛ ነፍሳችሁ ታማኞች ብትሆኑና የዘላለምን ሥቃይ ባትወዱ፣ ይህን ምክንያታዊ ምክር ብቻ እንድትቀበሉ ከጌታ እንደ ተላክሁ ሆኜ እለምናችኋለሁ። ኦ፣ ጎረቤቶቻችንን እንዲህ ባለው አስፈላጊ ሐሳብ እንዲስማሙ ብናሳምናቸው እንዴት ያሉ ደስተኞች ከተሞችና አውራጃዎች፣ እንዴትስ ያለ ደስተኛ ሕዝብ ሊኖረን በቻለ ነበር! ታማኝ አገልጋዮች ሁሉ ሕዝባቸውን በእውነት ሰማያውያንና ቅዱሳን ሆነው ቢያዩ እንዴት ያሉ ደስተኞች ሰዎች በሆኑ ነበር! ይህ የአብያተ ክርስቲያኖቻችን አንድነት፣ ሰላም፣ ደኅንነትና ክብር፣ የጎረቤቶቻችን ደስታና የነፍሳችንም መጽናናት ይሆን ነበር። ያን ጊዜ ይቅርታንና ሰላምን እንዴት በመጽናናት በሰበክንላችሁ፣ የሰላም ማኅተሞች የሆኑትንም ምሥጢራት እንዴት ባቀረብንላችሁ ነበር! በመካከላችሁስ በምን ያህል ፍቅርና ደስታ በኖርን ነበር! በሞት አልጋችሁ አጠገብ የምትሄደውን ነፍሳችሁን እንዴት በድፍረት ባጽናናናትና ባበረታታናት ነበር! በቀብራችሁም ነፍሳችሁን በመንግሥተ ሰማያት ለማግኘት፣ ሥጋችሁንም ወደዚያ ክብር ተነሥቶ ለማየት በተስፋ እየጠበቅን እንዴት በመጽናናት በመቃብር በተውናችሁ ነበር!
ነገር ግን አብዛኞቻችሁ አሁንም በግድ የለሽ፣ ባልተማረ፣ በሥጋዊ፣ በዓለማዊ ወይም ቅድስና በሌለው ሕይወት ብትቀጥሉ፣ ምኞታችንና ድካማችን ሁሉ ሆን ብላችሁ ራሳችሁን ከመኰነን ሊከለክላችሁ ያህል ማሸነፍ ካልቻለ፣ ያን ጊዜ ዕንቍዎች በሆኑት በእነዚያ ጥቂቶች፣ መንግሥትንም በሚቀበለው በታናሹ መንጋ ደስ የሚሰኘውን ጌታችንን ልንመስል ይገባናል፤ አብዛኞቹ ግን የዘሩትን ጕስቍልና ያጭዳሉ። በተፈጥሮ ውስጥ ግሩም ነገሮች ጥቂቶች ናቸው። ዓለም ብዙ ፀሐዮች ወይም ጨረቃዎች የሉትም፤ ወርቅ ወይም ብር የሆነው የምድር ክፍል ጥቂት ብቻ ነው። መሳፍንትና መኳንንት ከሰው ልጆች ትንሽ ክፍል ብቻ ናቸው፤ በዚህ ዓለም የተማሩ፣ አስተዋዮች ወይም ጠቢባን የሆኑትም ብዙ አይደሉም። ስለዚህ ደጁ የጠበበና እጅግ የቀጠነ በመሆኑ መዳንን የሚያገኙት ጥቂቶች ቢሆኑም እግዚአብሔር በእነዚያ ጥቂቶች ክብሩንና ደስታውን ያገኛል። ክርስቶስም ከኃይሉ መላእክት ጋር በሚነድ እሳት ሲመጣ እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ መምጣቱም በቅዱሳኑ ይከበራል፤ በእውነተኛ አማኞች ሁሉም ይደነቃል (2ኛ ተሰሎንቄ 1:7-10)።
ስለ ቀሩት ደግሞ፣ እግዚአብሔር አብ ሊፈጥራቸው እንደ ወደደ፣ እግዚአብሔር ወልድም የኃጢአታቸውን ቅጣት በመስቀል ላይ ለመሸከም እንዳልናቀ፣ የመንፈስ ቅዱስን መቀደስ በመቃወም በመጨረሻ ራሳቸውን እንደሚያጠፉ ቢያውቅም እንዲህ ያለውን መከራ ከንቱ እንዳልቈጠረው፣ እንዲሁ እኛ አገልጋዮቹም እነዚህ ባይሰበሰቡም ድካማችን ፈጽሞ እንደ ጠፋ አንቈጥረውም። ኢሳይያስ 49:5ን ተመልከቱ።
አንባቢሆይ፣ (ይህን መጽሐፍ ካነበብህ በኋላ) እኔ ከአንተ ጋር ጨርሻለሁ፤ ኃጢአት ግን (ከብዙ ጊዜ በፊት የተረሱ የመሰሉህ ኃጢአቶች እንኳ) ገና ከአንተ ጋር አልጨረሰም፤ ሰይጣንም (አሁን ከዓይን የተሰወረ ቢሆንም) ገና ከአንተ ጋር አልጨረሰም፤ እግዚአብሔርም ገና ከአንተ ጋር አልጨረሰም፤ አንተ ከሚገድለውና ከሚነግሠው ኃጢአት ጋር ለመጨረስ አትታመንምና። ይህን የማግባቢያ ጽሑፍ የጻፍሁልህ እዚህ የምናገራቸው ነገሮች ወደሚታዩበት ወደ ሌላ ዓለም እንደሚሄድ ሰው፣ አንተም በቅርቡ በዚያ መገኘት እንዳለብህ እንደሚያውቅ ሰው ሆኜ ነው። በፈጠረን በጌታ ፊት በመጽናናት ልታገኘኝ ብትፈልግ፣ የመዳንን ነገር እስከ መጨረሻ ቸል ለሚሉ፣ በመንፈስ ቅዱስም ላልተቀደሱ፣ የቅድስትና የኵላዊት ቤተ ክርስቲያን አባላት እንደ መሆናቸው የቅዱሳንን ኅብረት ለማይወዱ ሁሉ ከተዘጋጀው ከዘላለም መቅሠፍት ልታመልጥ ብትፈልግ፣ የፈራጁን የክርስቶስን ፊትና የአብን ግርማ በሰላምና በመጽናናት ለማየት፣ ከዚህ ዓለም ራቁትህን በወጣህ ጊዜም ወደ ክብር ለመግባት ተስፋ ብታደርግ፣ የእግዚአብሔርን ጥሪ እንድትሰማና እንድትታዘዝ፣ በሕይወትም ትኖር ዘንድ ቈርጠህ እንድትመለስ እለምንሃለሁ፤ አደራም እልሃለሁ። ነገር ግን ባትፈቅድ — ስለማትፈቅድ እንጂ ሌላ እውነተኛ ምክንያት ሳይኖርህ እንኳ — በጌታ ፊት መልስ እንድትሰጥበት እጠራሃለሁ፤ በዚያም አስጠንቅቄህ እንደ ነበር፣ የተፈረደብህም ተመልሰህ ትኖር ዘንድ ጥሪ ስላጣህ ሳይሆን ልታምነውና ልትታዘዘው ስላልፈቀድህ እንደ ሆነ እንድትመሰክርልኝ እጠይቅሃለሁ፤ ይህም ደግሞ የሚከተለው ሰው ምስክርነት ሊሆን ይገባዋል፦
ከልብ የሚመክርህ፣
ዲሴምበር 11 ቀን 1657።
ሪቻርድ ባክስተር።
ምዕራፍ 2 ተጠናቋል
መቅድም