ምዕራፍ 7 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
መለወጤ
በአሥራ አምስት ዓመቴ ወደ ጌታ ተመለስሁ። ይህም የሆነው በአንድ የሩብ ዓመት ጉባኤ ላይ በእሑድ ምሽት ነበር። አገልጋዩ የሰበከው ከዚህ ጥቅስ ነበር፦ «በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም» (ራእይ 14:3)።
አገልጋዩ የጥቅሱን የመጀመሪያ ሐረግ በታላቅ ብርታትና ኃይል ሲያብራራ፣ የጠፋሁበትን ሁኔታ ከዚያ በፊት አይቼው በማላውቀው መንገድ አየሁት። በውስጤ አንድ ነገር፦ «እንደ አንቺ ያለች ኃጢአተኛ ያን አዲስ ቅኔ ከቶ ልትዘምር አትችልም» እያለ ይደጋግም ነበር። የተቀበልሁትን ሥቃይ ምንም አንደበት ሊናገረው አይችልም። ራሴን ስቼ ወለሉ ላይ ወደቅሁ፤ ተሸክመውም ወደ ቤት ወሰዱኝ። ብዙዎች እየዘመሩና እየጸለዩ ሌሊቱን ሁሉ ከእኔ ጋር አደሩ። ማንንም አላወቅሁም፤ ነገር ግን በጨለማ ውስጥ የምሄድ መሰለኝ፤ አንድ ሰውም እየተከተለኝ፦ «እንደ አንቺ ያለች ኃጢአተኛ ያን አዲስ ቅኔ ከቶ ልትዘምር አትችልም» ይል ነበር። ወደ ጌታ የተመለሰ ወንድና ሴት ሁሉ ስሜቴ ምን ይመስል እንደ ነበር መገመት ይችላል። እግዚአብሔር ወደ ሲኦል እየነዳኝ ያለ መሰለኝ። በታላቅ ፍርሃት ሆኜ፦ «ጌታ ሆይ፣ እኔን ምስኪኗን ኃጢአተኛ ማረኝ!» ብዬ ጮኽሁ። በጆሮዬ ይጮኽ የነበረው ድምፅ ወዲያው ቆመ፤ የብርሃን ጮራም በዓይኖቼ ፊት ብልጭ አለ፤ ከሩቅ የሚሰማ የዝማሬ ድምፅም አብሮት ነበር፤ ብርሃኑ እየደመቀ፣ ዝማሬውም እየጠራ ሄደ፤ ብዙም ሳይቆይ፦ «ይህ አዲሱ ቅኔ ነው — የተዋጁ፣ የተዋጁ!» የሚሉትን ቃላት ለየሁ። ያለ ምግብና ያለ መጠጥ ለሀያ ሰዓት ተኝቼበት ከነበረው አልጋ ወዲያው ዘልዬ ተነሣሁና፦ «ተዋጀሁ! ተዋጀሁ! ክብር! ክብር!» እያልሁ መዘመር ጀመርሁ። እንደ ተዋጀሁና አዲሱን ቅኔ መዘመር እንደ ቻልሁ በተሰማኝ ጊዜ ልቤን የሞላው ደስታና ሰላም እንዴት ያለ ነበር! እንዲህም ከዘላለም እሳት በሚያስደንቅ ሁኔታ ዳንሁ።
ስለ አዲሱ ቅኔ ለማንበብ መጽሐፍ ቅዱስን ፈጥኜ አወረድሁ፤ ዓይኔ መጀመሪያ ያረፈባቸውም ቃላት እነዚህ ነበሩ፦ «አሁን ግን፥ ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤል ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ። በውኆች ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም» (ኢሳይያስ 43:1-2)።
ነፍሴ፦ «ክብር! ክብር!» ብላ ጮኸች፤ በቃላት ሊገለጥ በማይችል ጥልቅ ሐሴትም ተሞላሁ። በእውነትስ ከእሳት የተነጠቅሁ ትንታግ አልነበርሁምን? ምን ያህል ውድ አዳኝ እንዳገኘሁና እርሱም አዲሱን ቅኔ እንዳስተማረኝ ለወጣት ጓደኞቼ እየነገርሁ ከቤት ወደ ቤት ዞርሁ። ኦ! ትዝታዬ ወደ እነዚያ የየዋህነትና የደስታ የልጅነት ዘመናት እንዴት ይመለሳል!
አንዳንድ ጓደኞቼ ሳቁብኝና፦ «ከዚህ በፊትም ልብሽ ለሃይማኖት ሲነካ አይተናል፤ ግን ብዙም አልዘለቀም» አሉኝ። እኔም፦ «አዎን፣ ከዚህ በፊትም ልቤ ተነክቶ ነበር፤ ያን አዲስ ቅኔ ግን እስከ አሁን ድረስ ከቶ መዘመር አልቻልሁም ነበር» አልኋቸው።
ወደ ጌታ ከተመለስሁ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሰይጣን እጅግ ክፉኛ ፈተነኝ፤ እንደ ተታለልሁ ነገረኝ፤ ሰዎች ሃይማኖትን የሚያገኙት እንዲህ ሳይሆን ወደ መሠዊያው ሄደው አገልጋዩ ሲጸልይላቸው ነው አለኝ። ይህ እጅግ ምክንያታዊ መስሎ ስለ ታየኝ በእርግጥ ሃይማኖት እንዳገኘሁ መጠራጠር ጀመርሁ። ነገር ግን በዚህ ጥርጣሬ የመጀመሪያ ሰዓት ውስጥ እግዚአብሔር አገልጋያችንን ከእኔ ጋር እንዲነጋገር ላከው። የሚሰማኝን፣ ወደ ጌታ ያልተመለስሁ መሆኔም እንደሚያስፈራኝ ነገርሁት። እርሱም፦ «ልጄ ሆይ፣ ነፍሳትን የሚያድነው መሠዊያው ወይም አገልጋዩ አይደለም፤ ስለ ሰዎች ሁሉ በሞተው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው እንጂ» ብሎ መለሰልኝ። መጽሐፍ ቅዱስን አውርዶም፦ «ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም» ብሎ አነበበልኝ። ከዚያም ኃጢአቶቼ ሁሉ ይቅር እንደ ተባሉልኝና አዳኙ እንደሚወደኝ አምን እንደ ሆነ ጠየቀኝ። በፍጹም ልቤ እንደማምን መለስሁለት። በዚያች ቅጽበት የመጣልኝን ደስታ ምንም አንደበት ሊገልጠው አይችልም። በማመን ታላቅ ሰላም አለ። ለበጉ ክብር ይሁን!
ምዕራፍ 7 ተጠናቋል
መለወጤ