ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ
ያልተገባኝ ግርፋት

ምዕራፍ 5 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ያልተገባኝ ግርፋት

እስከዚህ ጊዜ ድረስ የፕራይም ቤተሰብ እንደ ገዛ ልጃቸው አድርገው ይዘውኝ ነበር። አሁን ግን ለእነርሱ የነበረኝ ስሜት ታላቅ ለውጥ አደረገ፤ ቀድሞ ከነበረኝ ፍቅር ይልቅ አሁን ያደረብኝ ጥላቻ በለጠ፤ ምክንያቱም ይህ ነበር። አንድ ቀን ወይዘሮ ፕራይም እንግዶች ስለ ነበሩአት፣ ከጥቂት ቀናት በፊት የጋገረቻቸውን ትናንሽ ኬኮች እንዳመጣ ወደ ምድር ቤቱ ላከችኝ። የቀሩት ሁለት ወይም ሦስት ብቻ ነበሩ፤ እነርሱንም አመጣሁላት። ሌሎቹ የት እንዳሉ ጠየቀችኝ። እኔም «አላውቅም» አልኋት። በዚህ ጊዜ እጅግ ተቈጥታ፦ «እንግዶቹ ከሄዱ በኋላ እንድታውቂ አደርግሻለሁ» አለች። ሁልጊዜ እንደዚያ ደግና እንደ እናት የነበረችው እርሷ በአስተያየቷና በድርጊቷ እጅግ ስላስፈራችኝ፣ መናገር እስኪያቅተኝ ድረስ በኃይል ተንቀጠቀጥሁ። ይህም የጥፋተኛነቴ ማስረጃ ተደርጎ ተወሰደ። በተከሰስሁበት ወንጀል ፈጽሞ ንጹሕ ስለ ነበርሁ፣ ትንሹ ልቤ ምን ያህል እንደ ታመመ የሚያውቀው ውዱ ጌታ ብቻ ነው። ምንም ነገር የምሰርቅበት ምክንያት አልነበረኝም፤ በዚያ ከነበረው ነገር ሁሉ የተትረፈረፈ ነበረኝና።

ለአቶ ፕራይም የሚሠራ አንድ ልጅ ነበረ፤ ኬኮቹን የወሰደው እርሱ እንደ ሆነ ሁልጊዜ አስብ ነበር፤ ከምድር ቤቱ ሲመለስ ማንንም ቢያገኝ እጁን በችኮላ ወደ ኪሱ ሲከትትና አፉን በጥንቃቄ ሲጠርግ አይቼው ነበርና። ነገር ግን ምን ማድረግ እችል ነበር? ላረጋግጠው አልቻልሁም፤ ደጋፊ ከሌለው ከእኔ ቃል ይልቅ የእርሱ ጽኑ ክህደት ታመነ።

በዚያች ሌሊት እንደ ጆን ቫን ፔተን ተሰቅዬ ብሞት ብዬ ደጋግሜ ተመኘሁ። በጨለማውና በጸጥታው ውስጥ ሰይጣን ወደ እኔ መጥቶ ወደ ጎተራው ሄጄ ራሴን እንድሰቅል ነገረኝ። በማለዳም ይህን ለማድረግ ፈጽሜ ቈርጬ ነበር። ለዚሁ ዓላማ ወደ ጎተራው ሄድሁ፤ ነገር ግን እጅግ የምጠላው ያ ልጅ በዚያ ነበረ፤ በተቻለውም መጠን በኃይል ሣቀብኝ። ወዲያውኑ ደካማ ስሜቴ ጠፍቶ ከዚያ በፊት አጋጥሞኝ በማያውቅ ታላቅ ቍጣ ወደ እርሱ ዘለልሁ፤ እርሱ ግን ከእጄ አምልጦ እየሣቀ ሮጠ። በዚህ ሁኔታ ከአስከፊ ኃጢአት ለሁለተኛ ጊዜ ዳንሁ።

በዚያ ቀን አቶና ወይዘሮ ፕራይም ከከተማ ሲመለሱ ከጥሬ ቆዳ የተሠራ አለንጋ ይዘው መጡ። ወይዘሮ ፕራይምም እስኪደክማት ድረስ ጀርባዬን በእርሱ ገረፈችኝ፤ ኬኮቹን መውሰዴን እንዳምን ሁልጊዜ አጥብቃ ትጠይቀኝ ነበር። ይህን በእርግጥ ላደርግ አልቻልሁም። ከዚያም አለንጋውን አስቀምጣ፦ «ነገ እንደ ገና እጠቀምበታለሁ፤ እውነቱን እንድትናገሪ ለማድረግ ቈርጫለሁ» አለች።

በዚያ ከሰዓት በኋላ ወይዘሮ ፕራይም ወጥታ በቤት ውስጥ ብቻዬን ተወችኝ። አለንጋውን ወደ ማገዶ ክምሩ ወሰድሁት፤ መጥረቢያውንም አንሥቼ ትናንሽ ቍርጥራጭ አድርጌ ቈራረጥሁትና ጣልሁት፤ ዳግመኛ በዚያ ነገር ላለመገረፍ ቈርጬ ነበርና። በማግስቱ ጠዋት በቤቱ ውስጥ ማንም ከመነሣቱ በፊት በጣም ማልጄ ተነሣሁና ወደ ቤታችን ጉዞ ጀመርሁ። በጫካ ውስጥ የሚያልፍ ረዥምና ብቸኛ መንገድ ነበር፤ እያንዳንዱ ድምፅ ያስፈራኝ ነበር፤ አንድ ሰው የሚከተለኝ እየመሰለኝም እሮጥ ነበር። ቤት ስደርስ የሆነውን ሁሉ ለእናቴ ነገርኋት፤ እርሷ ግን ስለ ጉዳዩ ብዙም አልተናገረችም። ከሰዓት በኋላ አቶና ወይዘሮ ፕራይም ወደ ቤታችን መጥተው ስለ ጉዳዩ ከእኛ ጋር ረዥም ጊዜ ተነጋገሩ። እናቴ በፊቴ ብዙ ባትናገርም ውሸት እንደ ተናገርሁ አላመነችም ነበር። ከዓመታት በኋላ፣ እኔ በሌለሁበት የፕራይም ቤተሰብን በጠንካራ ቃል እንደ ተናገረቻቸው ነገረችኝ። ዳግመኛ እንደማይገርፉኝ ቃል ገቡ፤ እናቴም ፈጽሞ ሳልፈልግ ከእነርሱ ጋር መልሳ ላከችኝ።

ከተመለስሁ በኋላ እንደ ቀድሞው ደግነት አደረጉልኝ፤ ምንም እንኳ በዚያን ጊዜ እንደዚያ ባይመስለኝም። በዚያ መኖር አልረካሁም ነበር፤ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ገደማ ሳለሁም ለቅቄ ሄድሁ። የዚያ የመጨረሻ ዓመት ልምምድ ልበ ደንዳና ኃጢአተኛ አደረገኝ። ብዙ ጊዜ አልጸልይም ነበር፤ ስጸልይም አንድ ነገር፦ «ያ ነጭ ጠጕር ያለው ደግ ሰው ከእንግዲህ አይወድድሽም» የሚለኝ ይመስለኝ ነበር።

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ