ምዕራፍ 4 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ
መምህሬ በወንጀል ተሰቀለ
አዲስ ኪዳንን ለማንበብ የነበረኝ ታላቅ ጕጕት ፊደል መቍጠርን በፍጥነት እንድማር አደረገኝ፤ ማንበብ ገና ልጀምር ስል ግን ታላቅ መዓት በላያችን ወረደ። የመምህራችን ስም ጆን ቫን ፔተን ነበር። እርሱ ከአንዲት ወጣት ሴት ጋር ይተጫጭ ነበር፤ እርሷም አንዲት ወዳጇ የተናገረችውን ነገር ነገረችው፤ ይኸውም ጆን ቫን ፔተን ብዙም ብልህ እንዳልሆነና ይህች ወጣት ለምን ልታገባው እንደምትፈልግ እንዳልገባት የሚገልጽ ነበር። እርሱም እጅግ ተቈጣ፤ ጠመንጃ ይዞ ወደዚያች ሴት ቤት ሄደና ተኩሶ ገደላት። እርሷም አምስቱ ልጆቿ እያለቀሱ በዙሪያዋ ሳሉ ወደቀች። ከዚያም ራሱን ለባለ ሥልጣናት አሳልፎ ሊሰጥ ወደ ከተማ ጉዞ ጀመረ። በመንገድም የሴቲቱን ባል አግኝቶ ያደረገውን ነገረው። ምስኪኑ ባልም ቤት ሲደርስ የጆን ቃል እውነት ሆኖ አገኘው፤ ሚስቱ ወዲያውኑ ማለት ይቻላል ሞታ ነበር።
ከቀብሩ በኋላ ሚስቱን ያጣው ሰው ወደ ወህኒ ቤት ሄዶ ከጆን ጋር ተነጋገረ፤ ጸሎቱ እስኪመለስለትም ድረስ ስለ መዳኑ ጸለየ፤ ነፍሰ ገዳዩ ጆን ቫን ፔተንም በክርስቶስ ማመኑን መሰከረ።
በመጨረሻም የተፈረደበት ሰው በሕዝብ ፊት የሚሰቀልበት ቀን ደረሰ (በዚያ ዘመን በስሜት ግፊት ለጊዜው አእምሮዬን ስቼ ነበር ብሎ መከላከል አልተለመደም ነበር)። ሰው ሁሉ ስቅላቱን ለማየት ሄደ፤ እኔም ከሌሎቹ ጋር ሄድሁ። እንዴት ያለ ትዕይንት ነበር! የመጀመሪያ መምህሬን ስቅላት ፈጽሞ አልረሳውም። በመስቀያው መድረክ ላይ ንግግር አደረገ፤ ደስተኛ እንደ ሆነና ለመሞት ዝግጁ እንደ ሆነ ከመናገሩ በቀር ሌላውን አላስታውስም። አንድ መዝሙር ዘመረ፤ አዝማቹም፦ «ወደ መንግሥቱ እሄዳለሁ፤ ከእኔ ጋር ወደ ክብር ትሄዳለህን?» የሚል ነበር።
— እጆቹን እያጣመረና ሁልጊዜም ሐሤት እያደረገ።
የዚህ ትዕይንት ትዝታ በአእምሮዬ ላይ እጅግ ጥልቅ ምልክት ስለ ተወ ለብዙ ሌሊቶች መተኛት አልቻልሁም። ልክ እንቅልፍ ሲወስደኝ የመምህሬ ራስ በክፍሉ ውስጥ በተቻለው ፍጥነት ሲንከባለል አየው ነበር፤ እየጮኽሁ እነቃ ነበር፤ አንድ ሰው መጥቶ አብሮኝ እስኪቆይ ድረስም ልረጋጋ አልችልም ነበር።
ከዚያን ቀን ጀምሮ አንድ ሰው እንደ ተሰቀለ በሰማሁ ቍጥር መላ ሰውነቴን ይዘገንነኛል፤ መንቀጥቀጥም ይይዘኛል። ኦ፣ ብዙዎች እግዚአብሔር ያዘዘው ነው ብለው እንደሚያምኑት «ነፍስ በነፍስ» ቢሆንም እንኳ፣ የሰውን ሕይወት ማጥፋት ምንኛ አረመኔያዊ ነገር ነው! ያ የአሮጌው ዘመን ሥርዓት ነበር። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ «እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ… አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።» ደግሞም፦ «ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት።» በወንጌል ዘመን የምንኖር እንደ መሆናችን፣ ሲሰድቡት መልሶ ያልተሳደበውንና በሞት ጣር ውስጥ ሆኖ፦ «አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» ብሎ የጸለየውን የእርሱን ትእዛዛትና ምሳሌ እንድንከተል እግዚአብሔር ይርዳን። ክርስቲያን ወንዶች ሆይ፣ በሕግ የተፈቀደው የአልኮል መጠጥ ንግድ እንዲወገድ እንደምትጸልዩት ሁሉ በምርጫም ድምፃችሁን ስጡ፤ እግዚአብሔርም የሞት ቅጣት ከምድራችን እንዲወገድ ያድርግ።
ምዕራፍ 4 ተጠናቋል
መምህሬ በወንጀል ተሰቀለ